ማክሰኞ, ጃንዋሪ 28, 2014

የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ


    አርበኝነት ፈርጀ ብዙ ነው፡፡ አርበኝነት በአውደ- ግንባር ይፈጠራል፡፡ ጠላትን በማንኛውም አጋጣሚ እና መሳሪያ / የብዙሃን መገናኛን በመጠቀም/ ጨምሮ በሚደረግ ፍልሚያ አርበኝነትን ማግኘት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ በፋሽስት ጣሊያን በተወረረችበት ጊዜ ህዝቧ በዱር በገደል መሽጎ ጠላትን ድል እንደነሳ ሁሉ በውጪ የሚኖሩ ዜጎቿም ባሉበት ሆነው በዲፕሎማሲው መስክ በመሰማራት አርበኝነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
    
      በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የውጭ ሃገር ዜጎች ኢትዮጵያንና ዜቿንበመውደድ እና ለእነሱም በመሆን ዘመን ተሻጋሪ የአርበኝነት ታሪክ አስመዝግበዋል፡፡ ለዚህ በማስረጃነት ከሚጠቀሱት አንዷ የኢትዮጵያ ህዝብ የቁርጥ ቀን ወዳጅ እና የፀረ-ፋሺዝም ንቅናቄ ፈር ቀዳጅ / ሲልቪያ ፓንክረስት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በጣሊያን በተወረረችበት ጊዜ የፋሺስትን -ሰበአዊ የሆነ ጭፍጨፋ እና ግፍ አጋልጠዋል፡፡ የሰበአዊ መብት ታጋይ የሆኑት ሲልቪያ ፓንክረስትም በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ ስፍራ የተሰጣቸው ጣላቅ ሴት ናቸው፡፡ ሲልቪያ ፓንክረስት ታጋይ ብቻ ሳይሆኑ የታሪክ ተመራማሪ እና ፀሀፊም ነበሩ፡፡
     ሲልቪያ ፓንክረስት የተወለዱት ሚያዝያ 27 ቀን 1874 .. በእንግሊዝ አገር ማንችስተር በተባለው ከተማ ነው፡፡ ለሲልቪያ ፓንክረስት የወደፊት ሕይወት ላይ ደማቅ አሻራን ያኖሩት አባታቸው / ሪቻርድ የእንግሊዝ ሌበር ፓርቲ ንቁ ተሳታፊ፣ ለድሆች ተሟጋችና መብታቸውን ለተነፈጉ ሁሉ ድምፅ ነበሩ፡፡ እናታቸው ኤምሊ ፓንክረስትም ሴቶች በእንግሊዝና በአውሮፓ ፖለቲካና ምርጫ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ትልቅ ሚና የተጫወቱና ብርቱ ትግል ያደረጉ ሴት ነበሩ፡፡

    
ሲልቪያ የአባታቸውንና እናታቸውን አርአያ በመከተል ዕድሜ ዘመናቸውን ሁሉ ለሰው ልጆች መብትና ነፃነት በመታገል አሳልፈዋል፡፡ 1928 .. ወራሪው ፋሽስት ኢጣሊያ የኢትዮጵያን ሕዝብ በመርዝ ቦምብ ሲፈጅና የፍትሕ ያለህ እያለ በሚጮኽበት፣ ኢትዮጵያውን አርበኞች በዱር በገደል ለአገራቸው ነፃነት ደማቸውን በማፍሰስ ላይ በነበሩበት ጊዜ ሲልቪያ ፓንክረስት ማንንም ሳይፈሩ የፋሽስት ወራሪውን ኃይል ግፍ እና በድል በግልፅ በአደባባይ በመቃወም ድምፃቸውን ለዓለም ሁሉ ሕዝብ ያሰሙ የነፃነት አርበኛና የጭቁን ሕዝቦች አለኝታ ነበሩ፡፡
    

      የኢጣሊያ ወታደሮች አዲስ አበባን ከያዙበት 1928 .. ጀምሮ በእንግሊዝ ‹‹The New Times and Ethiopian News›› የተባለውን ጋዜጣ አቋቁመው ያለ ማቋረጥ በየሳምንቱ በማሳተም ለኢትዮጵያውያን ነፃነት፣ ክብርና ልዑላዊነት ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡ በዚህ ጋዜጣም ፋሽስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እያደረስ ያለውን ግፍ በመግለፅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነትን ሊያገኙ ችለው ነበር፡፡ በኢትዮጵያም ውስጥም ‹‹Ethiopian Observer›› የተባለውን መጽሔት በማዘጋጀት በየወሩ ያሳትሙ ነበር፡፡
      የአዲስ ዘመን ጋዜጣ መስከረም 18 ቀን 1953 .. እትሙ በሲልቪያ ፓንክረስት የቀብር ሥነ ሥርዓት የአገር ግዛት ሚኒስትር የነበሩት ራስ አንዳርጋቸው መሳይ ለእኚህ የኢትዮጵያ ወዳጅ ያደረጉትን ንግግር እንዲህ ዘግቦት ነበር፡-

‹‹…
ሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስት በኢትዮጵያ ገና ብዙ ለማገልገል ከፍ ያለ ምኞት ስለነበራቸው በዛሬው ቀን የቀጠሩን እዚህ ሳይሆን ሌላ ስፍራ ነበር፡፡ በእውነት እላችኋለሁ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ መከራ፣ ግፍና ስደት አልቆ ውጤቱ እስኪደርስ ድረስ ሚስስ ሲልቪያ የሠሩት ሥራ በሽማግሌ ጉልበታቸውና ላባቸው ብቻ ሳይሆን ጤናቸውን እስኪያጡ፣ ርስታቸውን ሽጠው እስኪደኸዩ፣ በግል ገንዘባቸው ጭምር ለኢትዮጵያ የሠሩ ሰው ናቸው፡፡ ስለዚህ ታላቋ እንግሊዛዊት ሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስት የኢትዮጵያ ወዳጅ፣ እውነተኛዋ ኢትዮጵያዊ አርበኛ መባል የሚገባቸው ናቸው፡፡




ክቡር ራስ አንዳርጋቸው ንግግራቸውን በመቀጠልም፡-
       ‹‹…
ወዳጃችን ሲልቪያ ፓንክረስት ሆይ 25 ዓመት ሙሉ ያለ ዕረፍት የዕድሜዎን ሸክም ሳያስቡ በእውነትና በታማኝነት የረዱዋቸው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትና ሕዝብ አሁን በዙሪያዎ ቆመው ያለቅሱልዎታል፡፡ ወዳጆችዎ አርበኞችና ስደተኞች እዚሁ ባጠገብዎ ቆመዋል፡፡ ያንንም የመከራ ዘመን ያስባሉ፡፡ ታሪክዎ ከታሪካቸው በደም ቀለም ተጽፎ ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡ እርስዎም በዚህች በኢትዮጵያ ምድር ላይ በሰላም አርፈው እንዲኖሩ የግርማዊነታቸው መልካም ፈቃድ ስለሆነ እንደ ኢትዮጵያዊት ዜጋ ቆጥረን በክብር እናሳርፍዎታለን፡፡ እግዚአብሔር በምድር ላይ ሳሉ የሠሩትን በጎ ሥራ ሁሉ ቆጥሮ በሰማይ ቤት የክብር ቦታ እንዲያድልዎ እንመኛለን፡፡›› በማለት ነበር እኚህ ታላቅ የኢትዮጵያ ባለውለታ በጥልቅ ሐዘን ስሜት ውስጥ ሆነው የተሰናበቷቸው፡፡
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም በሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስት የቀብር ዕለት ባደረጉት ንግግራቸው፡-

     ‹‹…
ሚስስ ሲሊቪያ ፓንክረስት ኢትዮጵያን ለማገልገል ቆርጠው ከተነሱበት ጊዜ ጀምሮ የመጨረሻው ድል እስኪገኝ ድረስ ያደረጉትን የአሳብና የሥራ ተጋድሎ ሰፊ የታሪክ መስመር የያዘ ነው፡፡ ምኞታቸውና እምነታቸው የማይበገር የምሪት ምሽግ ነበር፡፡ የመንፈሳቸው ጽናት በፊታቸው የተጋረደውን እንቅፋት አስወግዶ ለማለፍ የተለየ ሥልጣን ነበረው፡፡ የኢጣሊያ ፋሽስት ጦር በዓለም መንግሥታት የተከለከለ የመርዝ ጢስ እየጣለ ሰላማውያኑን ሕዝብ ሴቱንና ሽማግሌውን ሕጻኑን ለመጨረስ ስለተነሳ ይህን ግፍ ለዓለም ሸንጎ ለማሰማት ወደ ጄኔቭ መሄዳችንን ሲከታተሉ የቆዩት ሚስስ ሲልቪያ በዓለም ላይ ከዚህ የባሰ ምን በደል ይድረሳል በማለት ለእውነተኛው ፍርድ በመቆርቆር ተነሱ፡፡
 

     ‹‹ፋሽስቶች የኢትዮጵያን ሕዝብ ያለ ፍርድ ፈጁት፡፡ ሚስስ ፓንክረስትም የጽሑፍና የፎቶግራፍ ማስረጃዎች እያሰባሰቡ ዓለም ይህን ሰምቶና አይቶ ካልፈረደ ለራሱ ወዮለት እያሉ ጮኹ፡፡ የኢትዮጵያን አርበኞች ተስፋ ለማስቆረጥ ፋሽስቶች በመርዝ ጢስና ቦምብ ያደረጉባቸውን የጭካኔ ውጊያ ሴቱንና ሕጻኑን ያለ ምክንያት እየሰበሰቡ በመትረየስ መፍጀታቸውን ማስረጃ አቀረቡ፡፡ ሚስስ ፓንክረስት በባሕርያቸው እውነተኛ ፍርድ ለማግኘት ሲታገሉ፣ የዚህችን ጥንታዊ አገር ታሪክ፣ ሥልጣኔና ቅርስ የሕዝቦቿን ጀግንነትና ፍቅር እየማረካቸው ሄደ፡፡ ከኢትዮጵያና ከሕዝቦቿ ጋር በፍቅር የወደቁት ሲልቪያ ፓንክረስት ለሀገራቸው ነፃነትና አንድነት ክቡር ሕይወታቸውን ከከፈሉት ኢትዮጵያን አርበኞች የሚደመሩ ናቸውና በዚህ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ያርፉ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ሆኗል፤›› በማለት ነበር እኚህን ታላቅ የኢትዮጵያ ወዳጅ መቼም ቢሆን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሁሌም ሥራቸው ሲታወስ እንደሚኖር በትልቅ አድናቆትና አክብሮት የተሰናበቷቸው፡፡

      

Sylvia Pankhurst with her son Richard

  
  
  ሚስስ ፓንክረስት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሰፊ የሆነ ጥናትና ምርምር ያደረጉም ሴት ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ከጻፏቸው መጻሕፍት መካከልም፡- የኢጣሊያ ጦርነት ወንጀል በኢትዮጵያ፣ የእንግሊዝ አመራር በኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች መብታቸውና ዕርምጃቸው፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ፣ ‹‹The Cultural History of Ethiopia›› የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

  
 

    

   ሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስትን ምንም እንኳን በሞት ቢለዩንም ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የከፈሉት መስዋእትነት፣ ያሳዩት ፍቅርና ክብር መቼም ቢሆን በሁላችን ልብ ውስጥ ሕያው ሆኖ የሚዘልቅ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ያደረጉት መልካም ሥራና በጎ ውለታ ዳግም እንደገና በልጃቸው በፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትና በቤተሰቦቻቸው አሁንም ድረስ ቀጥሏል፡፡



    ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ በዓለም አቀፍ መድረክ ከማስተዋወቅ በተጨማሪ በፋሽስት ኢጣሊያ ተዘርፎ የሄደውን የአክሱም ሐውልት እንዲመለስ በዓለም አቀፍ መድረክ ከሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ታላቅ ሥራን ሠርተዋል፡፡ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመንም በእንግሊዛውያን የተዘረፉ የኢትዮጵያ ቅርሶችን በማስመለስ ረገድም ጉልህ ሚና ነበራቸው፡፡ የሚስስ ሲልቪያና የቤተሰቦቻቸው ለኢትዮጵያ ያላቸው ፍቅር፣ ክብርና ያደረጉት ውለታ ሁሌም ሕያው ሆኖ የሚዘከር ነው፡፡
            
**********************************************************************************
            ምንጭ -http://mekilit.blogspot.com/2013_11_01_archive.html
                         www.bolepark.com

ማሞ ካቻ (አቶ ማሞ ይንበርብሩ)

  አቶ ማሞ ይንበርብሩ (ማሞ ካቻ) እስቲ እናስታውሳቸው፣ ተቀብሮ እንዳይቀር አኩሪ ታሪካቸው  (ደረጀ መላኩ)   አቶቢሲ ማሞ ካቻ የት ትሄዳለህ? ገብረ ጉራቻ… ታዳጊው ማሞ ይንበርበሩ ገና በጨቅላ እድሜው አባቱ አቶ...