ረቡዕ, ሴፕቴምበር 11, 2019

መስከረም የወራቱ ጌታ



<< መስከረም አበባ መስከረም አበባ ፣ 
     እንቁጣጣሽ መጣ አዲስ ዓመት ገባ ፤ 
     መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ፣ 
     እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ ። >>
የኢትዮጵያ የወራት ሁሉ መጀመሪያ መስከረም ነው፡፡


‹‹ኢዮሃ አበባዬ . . . መስከረም ጠባዬ›› ዘመን በተሞሸረ ዓመት በተቀመረ ቁጥር ሰው መልካም ምኞት የሚለዋወጥበት ሐረግ ነው፡፡ ድምፃውያንም ያቀነቅኑታል፡፡ እንግዲህ ኃያሉ ክረምት ሊያበቃ፣ መሰስ እያለ ወጥቶ ለከርሞ ሊመለስ ከመስቀል በዓል በኋላ ሁለት ሳምንት (መስከረም 25 ቀን 2012 ..) ቢቀረው ነው፡፡ በመጻሕፍት እንደተጠቀሰው፣ ኢዮሃ አበባዬ የደስታ ቃል ነው፡፡ ወንዶች የደመራ ለት እየዘፈኑ ድምሩን የሚዞሩበት ያበባ ዘፈን ነው፡፡ ሰኔ ግም ብሎ፣ ያምሌን ጨለማ አልፎ፣ የነሐሴን ጎርፍ ሙላትን በእኝኝ ተሻግሮና ተንተርሶ በጠንካራው ዝናብ (ውሃ) ምክንያት ብቅ የምትለዋ ያደይ አበባ ናትና፤ ውሃ ያደረገውን ታምር፣ ያስበቀለውን አበባ አደያዊን ተመልከት ለማለት ‹‹ኢዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ›› ይባላል፡፡
ታዋቂው ደራሲ በዓሉ ግርማ ‹‹ደራሲው›› በተሰኘው ልቦለዱ የመስከረምን ድባብ የገለፀበት አገላለጹ አዲሱ ዓመት በመጣ ቁጥር ሁሌ የሚታወስ ነው፡፡ ‹‹መስከረም ጠባ፡፡ የመስከረም ጮራ ዕንቁጣጣሽ ብላ ተግ አለች፡፡ ልጃገረዶች ሳዱላቸውን አሳመሩ፡፡ አደስ ተቀቡ፡፡ እንሶስላ ሞቁ፡፡ ወንዝ ወረዱ፡፡ ቄጤማ ለቀሙ፡፡ ፀአዳ ልብሳቸውን ለብሰው፣ አሽንክታባቸውን አጥልቀው፣አበባዬ ሆይ - ለምለምበማለት ተሰብስበው ብቅ አሉ - እንደ ጮራይቱ፡፡ የወርሀ መስከረም ብሩህ ተስፋና ስሜት በምድሪቱ አስተጋባ፡፡ ጠፍ እያለ መጣ ምድሩ፡፡ ወንዙም እየጠራ፡፡ ኩል መሰለ ሰማዩ፡፡ ሜዳው፣ ጋራው፣ ሸንተረሩ ወርቃማ የአደይ አበባ ካባ ለበሰ፡፡ ደመራ ተደመረ፡፡ ተቀጣጠለ ችቦ፡፡ኢዮሃ አበባዬ - መስከረም ጠባዬተባለ፡፡››
‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ጥያቄዎችና ባሕሎች›› በተሰኘው የሀብተማርያም አሰፋ (/) መጽሐፍ መስከረምን እንዲህ ገልጸዋታል፡፡
መስከረም ‹‹ምስ-ከረም›› ከከረመ በኋላ ወይም ክረምት ካለፈ በኋላ ማለት ነው፡፡ የመስከረም ወር ዝናብ የሚቆምበት ፀሐይ የምትወጣበት ወንዞች ንጹሕ ውሃ ጽሩይ ማይ የሚጎርፍበት፣ አፍላጋት የሚመነጩበት፣ አዝርዕት ማለት የተዘሩት አድገው ማሸት የሚጀምሩበት፣ ሜዳዎችና ተራራዎች ሸለቆዎችም በአበባ የሚያሸበርቁበትና የሚቆጠቆጡበት ነው ይሉታል፡፡
እንዲህም በመሆኑ የጨለማ የችግርና የአፀባ ጊዜ የሚያበቃበት የብርሃን፣ የደስታ የሸት፣ የፍሬና የጥጋብ ጊዜ የሚጀምርበትና የሚተካበት ነው ብሎ ሕዝቡ ስለሚያምንበትም የዕንቁጣጣሽ በዓልን ከሁሉ አብልጦ ግምት ስለሚሰጠው በእሳት ብርሃንና በእሳት ቡራኬ በየቤቱ እንደ ሁኔታው እንስሳ አርዶ ደም አፍስሶ ይቀበለዋል፡፡ ያከብረዋል ሲሉም አክለውበታል፡፡
በመምህር ዓለሙ ኃይሌ አገላለጽ በወርኃ መስከረም መሬቷ በአደይ አበባ አሸብርቃ ስለምትታይና በተለይም ዕንቁ የመሰለ አበባ ስለምታወጣ መሬቷን ዕንቁጣጣሽ፣ ዕንቁ የመሰለ አበባ አስገኘሽ ለማለት ዕንቁጣጣሽ ተብላለች፡፡ አያይዘው አቧራ፣ ቡላ የነበረው መሬት በዝናቡ ኃይል ለምልሞ ተመልከቱኝ፣ ተመልከቱኝ የምትል ያሸበረቀች፣ አበባ የተንቆጠቆጠች ሆነች የሚል ለዕንቁጣጣሽ ስያሜ መነሻ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡

አብሣሪው እንግጫ
እንግጫ የሣር ዓይነት ነው፡፡ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ልጃገረዶች መስክ ወርደው የሚነቅሉት ነው፡፡ የዕንቁጣጣሽ ብሥራት ነጋሪ ነው፡፡ ‹‹በሰሜን ሸዋ በምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች የተመዘገቡ የኢንታጀብል ባህላዊ ቅርሶች›› መድበል ላይ ስለ እንግጫ እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡
በዘመን መለወጫ ዋዜማ እንግጫ ሳር በልጆች እየተነቀለ እንደቋጨራ እየተጎነጎነ ጣራ ላይ ተወርውሮ ያድርና ጠዋት ላይ ለዘመን መለወጫ እየተጎነጎነ ራስ ላይ፣ ቡሃቃ አንገት ላይና ሌማት ክዳን ላይ ይታሰራል፡፡ ቡሃቃ እና ሌማት ላይ የመታሰሩ ምልክትነት ለረድኤትና ለበረከት ሲባል የሚደረግ ነው፡፡ ራስ ላይ የታሰረው ደግሞ ለመስቀል በዓል ተቀምጦ ይቆይና ደመራው ላይ ይታሰርና እንዲቃጠል ይደረጋል፡፡ ለራስ ምታትና ለጤንነት ሲባል በማኅበረሰቡ የሚከወን ነው፡፡
እንግጫ ነቀላ ዘመን ሲለወጥ የሚከወን ባህላዊ ሥርዓት ነው፡፡ በዋዜማው ያላገቡ ሴቶች ወደ መስክ ወርደው እንግጫ ይቆርጣሉ፡፡ ምሽቱን ደግሞ እንግጫውን ሲጎነጉኑ ይቆያሉ፡፡ ሲነጋ ደግሞ በጠዋት ተጠራርተው በመሰባሰብ በየሰው ቤት እየዞሩ የተጎነጎነው እንግጫ ከቤቱ ምሰሶ ላይ ያስራሉ፡፡ እንግጫ የአዲስ ዓመት የምሥራች ምልክት ነው፡፡ እንግጫ ከአዲስ ዓመት ማብሰሪያ በተጨማሪ የመተጫጫ በዓልም ጭምር ነው፡፡
እንግጫው ነቀላ በዜማ የታጀበ ነው፡፡
‹‹እቴ አበባዬ ነሽ
አደይ ተክለሻል
አደይ ተቀምጠሻል
ባሶና ሊበን
አዋጋው ብለሻል
ቦሶና ሊበን
ምነው ማዋጋትሽ
አንዱ አይበቃም ወይ››
በዚህ ጊዜ ወንዶች ደግሞ ያዘጋጁትን ዳቦት (የችቦ ስም) በእሳት ለኩሰው እያበሩ በመምጣት እንግጫ ለሚጎነጉኑት ሴቶች ያበሩላቸዋል፡፡ ዳቦታቸውን እያበሩ ወደ ሴቶቹ በሚያመሩበት ጊዜ የሚያዜሙት ዜማ አላቸው፡፡
‹‹ኢዮሃ ኢዮሃ
የቅዱስ ዮሐንስ
የመስቀል የመስቀል
አሰፉልኝ ሱሪ
ኢዮሃ›› በማለት ያዜማሉ፡፡
በከተሞች አካባቢ እንግጫ ነቀላው እየቀረ አበባዮሽ የሚለው ጨዋታ በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡ ልጃገረዶቹ ወደየሰው ቤት ሲሄዱ ሎሚ ይሰጣቸው የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ግን የእንግጫው ሴቶች ራሳቸው ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› እያሉ ሎሚ ሲሰጡ ገንዘብ ይሰጣቸዋል፡፡
እንግጫ ከአዲስ ዓመት ማብሰሪያ በተጨማሪ የመተጫጫ በዓልም ጭምር ነው፡፡ ልጃገረዶች እንግጫውን እየነቀሉ የሚያዜሙት ዜማ ይህንኑ ይጠቁማል፡፡
‹‹በቅዱስ ዮሐንስ ያልዘፈነች ቆንጆ
ቆማ ትቀራለች እንደ ሰፈር ጎጆ
እቴ አደይ አበባ ነሽ
ውብ ነሽ ውብ ነሽ››
ዜማውን የሰሙ ጎረምሶች ልጃገረዶቹን እያዩ አፀፋውን ይመልሳሉ፡፡
‹‹እንግጫችን ደነፋ
ጋሻውን ደፋ
እንግጫዬ ነሽ ወይ
እሰይ እሰይ
የቅዱስ ዮሐንስ የመስቀል የመስቀል
የላክልኝ ድሪ ሰላላ መላላ
መልሰህ ውሰደው ጉዳይም አይሞላ

የዘመን አዋጅ
መስከረም አንድ ቀን ያለው ልዩ ነገር የዘመኑን መለወጥ አስመልክቶ የባሕረ ሐሳብ አዋጁ ይነገራል፡፡ በዓመቱ ውስጥ በዓል የሚውልበት፣ ጾም የሚገባባትን ቀን መምህራኑ እያሰሉ ይናገሩታል፡፡ ዓመቱን በፀሐይና በጨረቃ፣ በዓመተ ዓለም ለምዕመናኑ ይገልጹታል፡፡ መምህር ዓለሙ ኃይሌ በምሳሌነት በላሊበላ ያለውን ሥርዓት ሲገልጹ የአሥሩም ቤተ መቅደስ ካህናት ቤተ ማርያም ይሰበሰቡና ማህሌቱ ካበቃ በኋላ ካህኑ ሻሹን ጠምጥሞ፣ ካባ ደርቦ መስቀል ይዞ ዘመኑን ያውጃል፣ የባሕረ ሐሳቡን ጥንተ ታሪክ ይናገራል፡፡
 አዲሱ ዓመት 2011 .. ተጨማሪ አዲስነቱ በዓመቱ ማብቂያ ጳጉሜን 6 ማድረጉ ነው፡፡ በአራት ዓመቱ የሚመላለሰውና ‹‹ዐውደ ጳጉሜን/ዐውደ ወንጌላውያን የሚባለው ሦስተኛ ዓመቱን ይይዛል፡፡ 2011 4 ተካፍሎ 502 ደርሶ ቀሪው 3 መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዘመኑ የሉቃስ መሆኑ ያመለክታል፡፡ (1 ከቀረ ማቴዎስ፣ 2 ከቀረ ማርቆስ፣ እኩል ከሆነ ዮሐንስ ይሆናል፡፡  አዲሱ ዓመት የዓለም ፍጥረት መነሻ በሆነው በኢትዮጵያ ዓመተ ዓለም ሲቆጠር 7511 ዓመተ ዓለም መሆኑና ስምንተኛው ሺሕ ከገባ 510 ዓመታት አልፈው 511 ዓመት ላይ መገኘቱን ስሌቱ ያሳያል፡፡

የመስከረም ወቅት
መስከረም 1 በክረምት ውስጥ የምትገኝ ያመት መነሻ ናት፡፡ ሰኔ 26 ቀን የገባው ክረምት የሚወጣው መስከረም 25 ቀን ላይ ነው፡፡ የስድስተኛው መዕት ዓመት የነገረ መለኮት ሊቁ (ቲኦሎጊያን) መዝሙረኛውና ዜማ ቀማሪው ቅዱስ ያሬድ በመጽሐፈ ድጓው ‹‹ኀለፈ ክረምቱ ጸገዩ ጽጌያት ቆመ በረከት!›› - ክረምቱ አለፈ አበቦችም ፈኩ፣ በረከትም ቆመ ይለናል፡፡
የማክሰኞው መስከረም 1 ቀን 2011 .. በክረምት ውስጥ ይገኛል፡፡  እንደ ቅዱስ ያሬድ አመዳደብ፣ በውስጡም ልዩ ልዩ ንኡሳን ክፍሎች አሉት፡፡ ከነሱም መካከል የነሐሴ መጨረሻና የጳጉሜን ሳምንት ‹‹ጎሕ፣ ጽባሕ››- ወጋገን፣ ንጋት ይለዋል፡፡ ይህም ያዲስ ዘመን መስከረም የሚጠባበት ጊዜ መድረሱን አመላካች ነው፡፡
ሌላው ንኡስ ክፍል ከዓመት አውራ መነሻ (ርእሰ ዐውደ ዓመት) መስከረም 1 ቀን እስከ መስከረም 7 (8) ቀን ያለው ‹‹ዮሐንስ›› ሲባል፣ ከመስከረም 9 እስከ 15 ዘመነ ፍሬ ይባላል፡፡ ‹‹ዮሐንስ›› የሚለው ቃል የተወሰደው በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ከሚገኘውና ኢየሱስ ክርስቶስን ካጠመቀው የዘካርያስ ልጅ ዮሐንስ ነው፡፡
 መስከረም 1 ቀን ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዕለተ ዮሐንስ መባሉ በተምሳሌታዊ ፍች የመጣ ነው፡፡ ከአሮጌው ብሉይ ኪዳን ወደ ሐዲስ ኪዳን፣ ወደ ዓመተ ምሕረት መሸጋገሪያ ላይ የመጣው መንገድ ጠራጊው ዮሐንስ ስለሆነ፤ ባህሉ/ ትውፊቱ ከአሮጌው ዓመት ወደአዲሱ መሸጋገሪያዋን ዕለት፣ መስከረም 1 ቀንን በዘይቤ ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› (ዕለተ ዮሐንስ) እያለ ይጠራዋል፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ ባገልግሎት ላይ ይገኛል፡፡  ምስጢሩን ባለመረዳት ሚዲያዎች በተለይም መንግሥታዊዎቹ በመናገሻ ከተማይቱንም ሆነ በየክልሉ የሚገኙት ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› የሚለውን የመስከረም 1 ቀን ልዩ መጠርያ ሲያነሱት አይሰማም፡፡ ሃይማኖታዊ ብሎ በመደምደም፡፡
በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር አዲሱ ዓመት ዘመን የሚለወጥበት ንጋት 12 ሰዓት ላይ እንጂ እንደ ምዕራባውያን እኩለ ሌሊት (6 ሰዓት) አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ ጋር የማይተዋወቁት፣ እኩለ ሌሊት ላይ ‹‹አዲስ ዓመት ገባ›› እያሉ ማደናገራቸውን ዓመት ዓመት መቀጠላቸውን ሃይ የሚልም ጠፍቷል፡፡ ለነገሩ የዘመን መለወጫ እንቁጣጣሽ ዜማዎች ውስጥ፣ ድምፃውያኑ ቅዱስ ዮሐንስን ፈጽሞ አልረሱትም፡፡ ሁለት የዘመን መለወጫ በዓል የሚከበርባት ኤርትራ መስከረም 1 ቀንን ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› እያለች እያከበረችው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

መስከረም አንድ- በልዩ ልዩ አቆጣጠር
የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት በልዩ ልዩ አቆጣጠሮች እንዲህ ይገለጻል፡፡
  • መስከረም 1 ቀን 7512 ዓመተ ዓለም (ከአዳም ተነሥቶ የሚቆጥር)
  • መስከረም 1 ቀን 2012 ዓመተ ምሕረት (በፀሐይ)
  • መስከረም 1 ቀን 2019 ዓመተ ምሕረት (በፀሐይና በጨረቃ ጥምር አቆጣጠር)
  • የጨረቃ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓመተ ምሕረት (የክርስትና)
  • ዙአልጃህ (መስከረም)  30 ቀን 1440 ዓመተ ሒጅራ (የእስልምና)
  • ቲሽሪ 2 ቀን 5780 ዓመተ ፍጥረት (የአይሁድ ቤተ እሥራኤል) አቆጣጠር)
  • ቲቶ 1 ቀን 1735 ዓመተ ሰማዕታት (ኮፕቲክ/ግብፅ)
  • ኦገስት 30 ቀን 2019 (በዩሊየሳዊ አቆጣጠር)
  • ሴፕቴምበር 12ቀን 2019 (በጎርጎርዮሳዊ አቆጣጠር)

  • ምንጭ:-- https://www.ethiopianreporter.com/article/12944 

ማሞ ካቻ (አቶ ማሞ ይንበርብሩ)

  አቶ ማሞ ይንበርብሩ (ማሞ ካቻ) እስቲ እናስታውሳቸው፣ ተቀብሮ እንዳይቀር አኩሪ ታሪካቸው  (ደረጀ መላኩ)   አቶቢሲ ማሞ ካቻ የት ትሄዳለህ? ገብረ ጉራቻ… ታዳጊው ማሞ ይንበርበሩ ገና በጨቅላ እድሜው አባቱ አቶ...