እሑድ, ኦክቶበር 28, 2012

ተክሎ የሚጽፍ፤ ብርቱ ባለቅኔ

“የማይነጋ ህልም ሳልም
የማይድን በሽታ ሳክም
የማያድግ ችግኝ ሳርም
የሰው ህይወት ስከረክም
እኔ ለእኔ ኖሬ አላውቅም ::”

ብላቴን ጌታ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን

                        (1928-1998 ዓ.ም.)
የዓለም ሎሪየት ታላቅ ባለቅኔ አንትሮፖሎጂስት እና ኢጂፕቶሎጂስት፣ የኮሜርስ ምሩቅ የህግ እውቀት ባለሙያ ጥዑመ ልሣን (ልዩ የትረካ ችሎታ ያለው) ተመራማሪ፣ ፀሐፌ ተውኔት ደራሲና ተርጓሚ ፀጋዬ ገብረ መድህን ቀዌሣ፤ ዛሬ በአፀደ ሥጋ ከእኛ ጋር ቢኖር ኖሮ በሥነ ጽሑፍከፍተኛውን ዓለም አቀፍ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት (Nobel Prize) ለመሸለም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ባለቅኔ፣ የቋንቋ ጠቢብና የጽሑፍ ጥበብ ሊቅ ለመሆን በቻለ፡፡ በአማርኛና በኦሮምኛ፣ በእንግሊዝኛና በግዕዝ ቋንቋዎች ቅኔን የተቀኘ ብርቱ ባለቅኔ፤ በአማርኛ በኦሮምኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ታላላቅ ሃሳቦችን የፃፈ ታላቅ ጠቢብ ነው - ፀጋዬ ገብረ መድህን፡፡ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ በዓለማችን በተለያየ ሥፍራና ዘመን ከተፈጠሩ ታላላቅ ሊቃውንት አንዱ የሆነው ጋሼ ፀጋዬ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ከአንድ በላይ በሆነ ቋንቋ ከፃፉ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ደራሲያን ጐራ ነው፡፡
ሣህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም በጉራጊኛ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ጽፈዋል፤ በሶስት ቋንቋዎች፡፡ ጋሼ ስብሃት ለአብ ገብረ እግዚአብሔር በተለይ በአማርኛና በእንግሊዝኛ፤ በተወሰነ መጠን ደግሞ በትግርኛና በፈረንሳይኛ ጽፏል፤ በአራት ቋንቋዎች፡፡ አቤ ጉበኛና ዳኛቸው ወርቁ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ጽፈዋል፤ በሁለት ቋንቋዎች፡፡ እንዲሁም ሌሎች ኢትዮጵያውያን የጽሑፍ ጥበብ ባለሙያዎች በሁለትና በሶስት ቋንቋዎች የፃፉ አሉ፡፡ ጋሼ ፀጋዬ በሶስት ቋንቋዎች የፃፈ፤ በአራት ቋንቋዎች ቅኔን የተቀኘ ብርቱ ባለቅኔና ሊቀ ጽሑፍ (የፅሁፍ ጥበብ ሊቅ) ነው፡፡ የዋርካው ሥር ንግርት”፤ ኢትዮጵያን የላይኛው እውነት ከፍተኛው እውነት፤ የላይኛው ዙፋን …ያለበት ኤዞፕ የተሰኘውና ስለመጀመሪያው ጥቁር ፈላስፋ የሚቀኘው ያማረ ቅኔው፤ ቴዎድሮስ የተሰኘውና በእንግሊዝ አገር በሚገኙ ዩኒቨርሢቲዎች ውስጥ የታየ ቲያትሩ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ከፃፋቸው ሥራዎቹ ሶስቱ ናቸው፡፡

እንዲሁም በአማርኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች የፃፋቸው በርካታ በከበረ ሃሳብ፣ በተዋበ ጥበብ የተመሉ ሥራዎች አሉት፡፡ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ የተረጐማቸውም እንደዚሁ በርካታ ናቸው፡፡
የሥመ ጥሩውን እንግሊዛዊ ባለቅኔና ፀሐፌ ተውኔት ዊሊያም ሼክስፒርን ሥራዎች ወደ ኢትዮጵያዊ ቋንቋዎች የተረጐሙ ኢትዮጵያውያን ጠበብት አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ የክብር ዶክተር ደራሲ ከበደ ሚካኤልና መሥፍን ዓለማየሁ ይወሳሉ፡፡ ይሁንና በጋሼ ፀጋዬ መጠን የዊሊያም ሼክስፒርን ሥራዎች ለኢትዮጵያውያን ታዳሚዎች ያስተዋወቀ ማንም የለም፡፡ ጋሼ ፀጋዬ በኢትዮጵያ ቲያትር መድረክ በትርጉም ሥራዎቹም ሆነ በፈጠራ ተውኔቶቹ የራሱ የሆነ አዲስ የብርሃን ፈር የቀደደ (ከዘመን ዘመን ወደፊት ቀድሞ የራሱን ተደራሲ የፈጠረ) ታላቅ የተካነ የኪነጥበብ ባለሙያ ነው፡፡ ፀጋዬ ገብረ መድህን የጽሑፍ ጥበብ ባለሟል ብቻ ሳይሆን በኅብረተሰብ የምርምር ዘርፍ ከፍተኛ እውቀት ያለው፣ ከፍ ያለ ደረጃ የሚሰጠው ተመራማሪ ነው፡፡ ሁልጊዜ ወደ እውነት፤ ሁልጊዜ ከፍ ወዳለ እውቀት፤ ሁልጊዜ ወደተሳለ ጥበብ፤ ሁልጊዜ ወደ ሠፊ ምናብና ጥልቅ እውቀት የሚያድግ፣ ትጉህና የተባ ሊቀ ጽሑፍና ተመራማሪ ነው፡፡
ፀጋዬ ገብረ መድህን ቀዌሣ ከፍ ባለ ጥበብና በተኳለ ውበት፣ በእውነትና በፍቅር የተነካ የተሟሸ አንደበት ነው፡፡ የአፍሪቃና የህዝቦቿ አንደበት፤ የኢትዮጵያና የህዝቦቿ አንደበት፤ የኦሮሞ ህዝብ አንደበት፤ የተፈጥሮና የአምላክ አንደበት፤ የጥበብና የጥልቅ ምርምር አንደበት፤ የብርሃን ቃና ህያው አንደበት ነው፡፡
ዓመተምሕረቱን በትክክል ባላስታውስም፤ ከሠባ አምስት ዓመታት በፊት ግድም በአሥራ ዘጠኝ ሃያዎቹ መጨረሻና በአሥራ ዘጠኝ ሠላሳዎቹ መካተቻ ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ አንድ መቶ ሠላሳ ስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አምቦ አካባቢ ነው ጋሼ ፀጋዬ የተወለደው፡፡ ታላላቅ ሰብዕና ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሠሎሞን ደሬሣ በወለጋ ጩታ፤ ሣህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም በጉራጌ፤ ስብሀት ለአብ ገብረእግዚብሔር በአድዋ ርባገረድ፣ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ…የተወለዱት በዚሁ ዘመን በተለያየ ሥፍራ ነው፡፡ አፈወርቅ ወልደ ነጐድጓድ ከዚህ ዘመን ጥቂት ቀደም ይላል፡፡ የክብር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ደግሞ ከሁሉም ቀደም ማለት ብቻ ሳይሆን፤ ከጐጃም ወደ አዲስ አበባ መጥተው ተፈሪ መኮንን እየተማሩ ፀረ ፋሺስት ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበረው በዚህ ዘመን ነው፡፡ ጋሼ ፀጋዬ የተወለደው ሀዲስ ዓለማየሁ በትግራይ ሠለክለካ የኢትዮጵያን አርበኞች ፀረ ፋሺስት ተጋድሎ ለመምራት እየተሰናዱ ነው፡፡
የታዋቂው አፍሪቃዊ ባለቅኔ፣ የትውልድ አገሩ የሴኔጋል ፕሬዚዳንት፣ በፈረንሣይና በፈረንሣይኛ ተናጋሪ አገሮች (Franco Phone) ተሠሚነት ያለው ትልቅ ምሁር፣ ሴዳር ሴንጐር የልብ ወዳጅ የሆነው ፀጋዬ ገብረመድህን ቀዌሣ፤ ከአምቦ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በወጣትነቱ መጀመሪያ የተማረው የንግድ ሥራ ኮሌጅ (ኮሜርስ) ገብቶ ነው፡፡ ከኮሜርስ በንግድ ሥራ ከተመረቀ በኋላ ነፃ የትምህርት ዕድል በማግኘት በአሜሪካን አገር በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት አጥንቶ ከፍ ባለ ማዕረግ ተመርቋል፡፡
በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በአገሪቱ ከፍተኛውን የሥነ ጽሑፍ ሽልማት ከግርማዊ ጃንሆይ ከተቀበሉ ኢትዮጵያውያን የኪነጥበብ ባለሙያዎችና ሊቃውንት መሀከል አንዱ ጋሼ ፀጋዬ ገብረመድህን ነው፡፡
በጥቁር ግብጽ ጥናት ኢጂፕሎጂስትና በኅብረተሰብ የምርምር ዘርፍ አንትሮፖሎጂስት በመሆን ደማቅና ክቡር እውቅና ያለው ጋሽ ፀጋዬ፤ የታሪክ ምሁርና ከፍ ያለ ተመራማሪ ጭምር ነው፡፡
አንድ ኢትዮጵያዊ ምሁር ስለ ጋሽ ፀጋዬ በፃፈው መጽሐፍ፤ ይሄንን ታላቅና ብርቱ ኢትየጵያዊ ባለቅኔ “ምሥጢረኛው ባለቅኔ” እንዳለው አስታውሳለሁ፡፡
ከሃምሣ ዓመታት በላይ በትጋትና በትባት በጽንአት የተባ ብዕሩን ተክሎ ለመፃፍ የቻለ ሊቀ ጽሑፍ ነው ጋሽ ፀጋዬ፡፡
አብዛኞቹ ሥራዎቹ ግጥምና ቅኔዎች ተውኔቶችና የምርምር ሠነዶች ናቸው፡፡ ከተውኔቶቹ ከፊሎቹ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ የተተረጐሙ ሲሆኑ፤ ከነዚህ ውስጥ አብላጮቹ ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት በአውሮጳ የኖረው ታዋቂው እንግሊዛዊ ፀሐፌ ተውኔት የዊሊያም ሼክስፒር ሥራዎች ናቸው፡፡ እርሱ በእንግሊዝኛ ከፃፋቸው ደግሞ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት መድረኮች የታዩም አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ “ቴዎድሮስ” ነው፡፡
የጋሽ ፀጋዬ ሥራዎች በአገርና በህዝብ ፍቅር፤ በጥናትና በምርምር በአገሪቱና በህዝቦቿ ክቡር ቅርሶችና ዓይነታ (typical) ማንነት ላይ ያተኮሩ ብርሃንማ ቃና ያላቸው የተፈጥሮና የእግዚሃር ምሥክርና ህያው አንደበት ናቸው፡፡
በጥቁር አፍሪቃና በአረብ አፍሪቃ ከሃምሳ ሦስት በሚበልጡ አገራት ውስጥ ከሺህ በላይ ቋንቋዎች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ እንኳን ከሰማንያ የሚበልጡ ቋንቋዎችና ከሦስት መቶ በላይ ዲያሌክት አሉ፡፡ ከነዚህ ሺህ ቋንቋዎች የራሳቸው ፊደል ያላቸው ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ አማርኛና አረብኛ፡፡ ይሁንና በሥነ ፅሁፍ የመጀመሪያውን ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ሽልማት ለማግኘት የቻሉት አፍሪቃውያን ደራሲያን:- ወሌ ሱየንካ ከናይጄሪያ፤ እና ነጂብ ማህፉዝ ከግብፅ ናቸው፡፡ እንዲሁም ከደቡብ አፍሪቃ የሰላም ሰው (A man of peace) በመሰኘት ደግሞ ዴዚሞን ቱቱ እና ኔልሰን ማንዴላ፡፡ ወሌ ሱየንካ ከአፍሪቃ ከፍተኛውን ዓለም አቀፍ የሥነ ፅሁፍ ሽልማት (Nobel prize) በማግኘት ቀደምት አፍሪቃዊ ሊቀ ፅሁፍ ሲሆን፤ ከሶስት እና ከአራት ዓመታት በፊት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክተሬት ዲግሪውን ተቀብሏል፡፡ ከነጂብ ማህፉዝ መፃህፍት ሁለቱ “ሌባውና ውሾቹ” የሚለውና “አሳረኛው” በአማርኛ ተተርጉመዋል፡፡ፊደል ያለው ብቸኛ አፍሪቃዊ ህዝብ ሆነን ለሺህ ዘመናት ፀንተን የኖርን ህዝቦች፤ ከፍተኛውን ዓለም አቀፍ የሥነ ፅሁፍ ሽልማት ለማግኘት ዘገየን፡፡ ከዚህ ሽልማት ጋር አንድ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር፤ ወይም ከአሥራ ሰባት ማሊዮን ብር በላይ አብሮት አለ፡፡
ጋሼ ፀጋዬ ገብረመድህን ቀዌሳ እስካሁን በአካለ ሥጋ ቢኖርና ብዕሩ በህያውነት ቢዘልቅ ያንን ታላቅ የሥነ ፅሁፍ ሽልማት ለማግኘት፤ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የሥነ ፅሁፍ ባለሙያ ሊሆን በቻለ ነበር፡፡ ይሄ ፅሁፍ ለብርቱው ኢትዮጵያዊ ባለቅኔ የዓለም ሎሪየት ፀጋዬ ገብረመድህን ቀዌሳ ታላቅ ነፍስ ክብር ይገባዋል፡፡
************************************************************************************
ምንጭ:--http://www.addisadmassnews.com

ማክሰኞ, ኦክቶበር 09, 2012

«...ኢትዮጵያ ልዩና ታሪካዊ አገሬ ናት...»

ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረትስ
*********************
የለንደኑ ትንታግ ወጣት ለኢትዮጵያ በመወገን እንደ አርበኛዋ እናታቸው ፀረ- ፋሽስት ጽሑፎችን በጋዜጣ በማውጣት ትግል የጀመሩት ገና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያሉ ነበር። ይህም በመሆኑ የሥነ ጽሑፍ ክህሎታቸውን በንድፈ ሐሳብ እውቀትና በምርምር አዳብረው ለህትመት ካበቋቸው ከሃያ በላይ መጻሕፍት የተወሰኑት ለአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች የመማሪያና የምርምር ሰነዶች ለመሆን በቅተዋል።
በልጅነት ዕድሜያቸው የኢትዮጵያን ጉዳይ በደማቸው ያሰረፁትና በሃያ ዘጠኝ ዓመታቸው የዶክትሬት (PHD) ዲግሪያቸውን በከፍተኛ ማዕረግ አግኝተዋል። የለንደኑ ዩኒቨርቲቲ የዕውቀት ቀንዲል ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሃምሳ ዓመት በላይ የሰጡት ምሁራዊ ተልዕኮ ተቋሙ ዛሬ ለደረሰበት የዕድገት ምዕራፍ የታሪክ ባለድርሻ አድርጓቸዋል።
በወጣትነት ዕድሜያቸው ከጀመሩት ክቡር የመምህርነት ሙያ ባለፈ በኢትዮጵያ ላይ የላቀ ምርምርና ጥናት ለማካሄድ ያስቻለ፣ ታሪካዊ ቅርሶችን አሰባስቦ ለመያዝ ያገዘ እና አገራችንን ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ያስተዋወቀ፣ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩትን በመመስረት እንደእናታቸው የዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ባለቤት ለመሆን ችለዋል።
በቅኝ ገዥዎችና በፋሽስት ኢጣሊያ የተዘረፉ ታሪካዊ ቅርሶችን ለማስመለስ ከኢትዮጵያውያን ባልንጀሮቻቸው ጋር በመሆን በአደረጉት ዓለም አቀፋዊ ትግል የአክሱም ሐውልትን፣ የአፄ ቴዎድሮስ ክታብንና ሌሎችንም ቅርሶችን በአገራቸው ከወገናቸው ጋር ደምቀው እንዲታዩ በማድረግ ሕዝባችን ለዘመናት ከነበረበት ፀፀትና ቁጭት እንዲላቀቅ አድርገዋል።
የእናታቸውን የአርበኝነት የተጋድሎ ገድል የሕይወት ዘመን ስንቅና መመሪያ አድርገው በተለይም ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ኮሌጅ ጀምረው ተቋሙ ዩኒቨርሲቲ ከሆነም በኋላ ለአበረከቱት ምሁራዊ አስተዋፅኦ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመርጌታነትና የተመራማሪነት ብቃታቸውን በማረጋገጥ የፕሮፌሰርነትና የክብር ዶክትሬት (PHD) ዲግሪ ማዕረግ አጐናፅፏቸዋል።
በብሔራዊም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱታን ያተረፉት እኒሁ ምሁር በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ባደረጉት ጥልቅ ጥናትና ምርምር ከአፄ ኃይለሥላሴ ሽልማት ድርጅትና ከእንግሊዝ መንግሥት የወርቅ ሚዳሊያና ኒሻን ለመሸለምም በቅተዋል።
የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩትን ከመመስረት ባለፈ በሰጡት ያልተቆጠበ አመራርና ድጋፍ ለእኒሁ የአገር ባለውለታ ምሁር የሃምሳ ዓመት ወርቃማ አገልግሎት ለመዘከር በተዘጋጀ ልዩ ሥነ ሥርዓት ላይ በብር የተሰራ የአክሱም ሐውልት ምስል ተሸላሚ ሆነዋል።
የእነዚህና የሌሎችም እውነታዎች ባለቤት የምጣኔ ሀብት ታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ኬር ፔቲክ ፓንክረስት ይባላሉ። እኒህ የዛሬው እውቅ ዓለም አቀፍ ምሁርና የዚያን ጊዜው እምቦቀቅላ ሕፃን የተወለዱት እ.አ.አ በወርሐ ታህሣሥ 1927 በአገረ እንግሊዝ ለንደን ከተማ በሚገኘው ሐምስቴድ ሆስፒታል ነው። የዚያን ጊዜው ብላቴና የዛሬው አዛውንት እናት የኢትዮጵያ ሕዝብ የቁርጥ ቀን የልብ ወዳጅ፣ የሴቶች መብት ተሟጋች ፣ አርቲስት፣የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኝ፣ የፀረ - ፋሽዝም ንቅናቄ ፈር ቀዳጅ፣ ጋዜጠኛና ደራሲ የሆኑት ሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስት ይባላሉ። አባታቸው ሚስተር ሲልቪዮ ኮርዮም ሰዓሊና ጋዜጠኛ፣ እንዲሁም ፀረ ፋሽስት አቋም የነበራቸው እንግሊዝ አገር የሚኖሩ ኢጣሊያዊ ስደተኛ ነበሩ።
የዚያን ጊዜው የለንደኑ ቡቃያና የዛሬው ፕሮፌሰር የተወለዱት አንደኛው እና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በተጠናቀቀበት ማግሥትና ዋዜማ በመሆኑ ጦርነቶቹ የፈጠሩአቸው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መመሰቃቀሎች በዕድገታቸው ላይ አንፃራዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ ባይቀርም ወላጆቻቸው ዕቅፍ ድግፍ አርገው በማሳደጋቸው እነሆ ከዚያ ዘመን የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ተርፈው ዛሬ የሰማንያ አምስት ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ ለመሆን በቅተዋል።
በጦርነቶች መካከል የለመለመች ሕይወት
ምንም እንኳን የያኔው ሕፃን ሪቻርድ ከልደት እስከ ልጅነት የነበራቸው የሕይወት ጉዞ ጦርነት ባስከተለውና በፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ የታጀበ ቢሆንም አንድ ለእናቱ የሆኑት የሚስስ ሲልቪያ የስስት ልጅ በሰባት ዓመታቸው ከእናታቸው ጉያ ወጥተው ችክዌል በሚባለው ትምህርት ቤት ይገባሉ። ሆኖም ግን የገቡበት ትምህርት ቤቱ የሚመላለሰው የባቡር ሀዲድ በመጐዳቱ ሕፃኑ ተማሪ በእግራቸው ተመላልሰው መማር እንደማይችሉ ታመነበት። እናም አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ መኖሪያቸው አካባቢ በነበረው ወደ ባንክራፍት ትምህርት ቤት ይዛወራሉ።
የዚያን ጊዜው ሕፃንና ተማሪ ሪቻርድ ፓንክረስት ትምህርት ቤታቸውን የዕውቀት ማዕከል በማድረግ ከክፍል ወደ ክፍል ከፍተኛ ውጤት እያገኙ መዘዋወረ ሲጀምሩ የብሩህ አዕምሮ ባለፀጋ መሆናቸውን ያመላክታሉ። ይሁን እንጂ 'በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ውሃ ይጠጣል' እንዲሉ ገና የሰባተኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ይጀመራል። ወቅቱ እንኳንስ ለመማር ቀርቶ በህልውና ለመትረፍም አስፈሪ ቢሆንም ትምህርት ቤቶች ባለመዘጋታቸው ተማሪ ሪቻርድ ፓንክረስት እንደሌሎቹ አቻዎቻቸው የመማር ማስተማሩን ሂደት በሚገባ መከታተላቸውን ይቀጥላሉ። ምንም እንኳን ጦርነቱ የፈጠረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በሁሉም እንግሊዛዊ ላይ የሚታይ ነበር። የአርበኛዋ የወይዘሮ ሲልቪያ ልጅ በትምህርት አቀባበላቸውና ዘወትር ከማይለያቸው ትጋታቸው ላይ ተፅዕኖ እንዳልፈጠረባቸው ዛሬ ላይ ሆነው ያስታውሳሉ።
ይህም በመሆኑ ወጣቱ ፓንክረስት ለመማር የነበራቸው ሩጫ ባይጠናቀቅም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመጠናቀቁ በፊት ማለትም እ.አ.አ 1944 በአስራ ስምንት ዓመታቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቅ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት መንፈሳዊ ዝግጅት ያደርጋሉ። ግን ደግሞ የእንግሊዝ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች አገራዊ ግዳጃቸውን ተወጥተው ከግንባር ለሚመለሱ ወጣቶች ቅድሚያ የትምህርት ዕድል እንዲሰጣቸው የሚል አዲስ መመሪያ በማውጣቱ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ቀን ይቆጥሩ የነበሩት ወጣቱ ሪቻርድ በሚፈልጉት ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለመግባት እንቅፋት ይገጥማቸዋል።
ይሁን እንጂ የልጃቸውን ጭንቀት በሚገባ የተረዱት እናታቸው ወይዘሮ ሲልቪያ ጓደኛቸው የሆኑትንና የፖለቲካል ሳይንቲስት የነበሩትን ፕሮፌሰር ላስኬን ያማክሯቸዋል። ምሁሩም የተለያዩ በጐ ምክንያቶችን በመደርደር ወጣቱ ሪቻርድ ለንደን ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ ይደረጋሉ። የሚስስ ሲልቪያ ብቸኛ ልጅ ሩቅ አስበው ቅርብ አዳሪ አልሆኑም። እናም ለንደን ዩንቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት በመግባት ትምህርታቸውን በትጋት መከታተሉን ይቀጥላሉ። ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ አስተውሎ መራመድንና ጊዜን በዋዛ ፈዛዛ ማሳለፍን የማይወዱት የዚያን ጊዜው የለንደን ዩኒቨርስቲ ተማሪና የዛሬው እውቅ የታሪክ ምሁር የሦስት ዓመት የዩኒቨ ርሲቲ ቆይታቸውን አጠናቀው በሃያ አንድ ዓመታቸው በምጣኔ ሀብት (Economics) የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማዕረግ ያገኛሉ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ወጣቱ ፓንክረስት በተቀዳጁት ውጤት ቢደሰቱም ወደ ሥራ ዓለም ከመግባት ይልቅ ጊዜ ሳያጠፉ ትምህርታቸውን መቀጠል እንዳለባቸው ይወስናሉ ። የትና ምን መማር እንዳለ ባቸው ማሰላሰል በያዙበት ወቅት ታላቅ የምስራች ይደርሳቸዋል። በመጀመሪያ ዲግሪያቸው ያስመዘገቡት ውጤት በቀጥታ ለዶክትሬት (PHD) ዲግሪ የሚያበቃቸውን ትምህርት እንዲማሩ ለንደን ዩኒቨርሲቲ የነፃ ትምሀርት ዕድል ይሰጣቸዋል።
አንብበው የማይሰለቹት፣ ፅፈው የማይደክሙት የዚያን ጊዜው ሪቻርድ ፓንክረስት ጀንበር ወጥታ እስከምትጠልቅ ብቻ ሳይሆን የእንቅልፍ ጊዜያቸውን ሳይቀር ለጥናታቸውና ለትምህርታቸው በመስጠታቸው በአስተማሪዎቻቸው ሳይቀር አንቱታን ያተርፋሉ። እናም በሃያ ዘጠኝ ዓመታቸው በምጣኔ ሀብት ታሪክ (Economic History) የዶክተሬት (PHD) ዲግሪያቸውን እ.አ.አ በ1954 በከፍተኛ ውጤት በመመ ረቅ እነሆ ዛሬ ድረስ ያች በሁለት ዓለም አቀፍ ጦርነቶች መካከል የተፈጠረች ነፍስ በዕውቀትና በክህሎት ገዝፋ ዓለም ዕውቅና የቸራት ለመሆን ችላለች።
በዘር የተላለፈ አርበኝነት
አርበኝነት ፈርጀ ብዙ ነው። አርበኝነት በአውደ ግንባር ይፈጠራል። አርበኝነትን ጠላትን በማንኛውም መገናኛ ብዙኃን በመፋለምም ድል ማግኘት ይቻላል። አገራችን በፋሽስት ኢጣሊያ በተወረረችበት ጊዜ ህዝባችን በዱር በገደሉ መሽጐ ጠላትን ድል እንደነሳ ሁሉ አንዳንድ ዜጐቻችንም በውጭ አገር ሆነው በዲፕሎማሲው መስክ በመሰማራት አርበኝነታቸውን አረጋግጠዋል። በሌላም በኩል አንዳንድ የውጭ አገር ዜጐች ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን በመወገን ዘመን ተሻጋሪ የአርበኝነት ታሪክ አስመዝግበዋል። ለዚህ እውነታ ሁነኛ ማሳያ የሚሆኑት ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ የቁርጥ ቀን ወዳጅና የፀረ- ፋሽዝም ንቅናቄ ፈር ቀዳጅ ሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስት ናቸው፡፡ ይህም ብቻም አይደለም « ዘር ከልጓም» ይስባል እንዲሉ ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ ያላቸውን ፍቅርና ከበሬታ በብቸኛው ልጃቸው አዕምሮ ውስጥ እንዲሰርፅ በማድረጋቸው የዛሬው ፕሮፌሰሩ ልጃቸው ከልጅነት እስከ ዕውቀት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው ያስገኙት ውጤትና የሰጡት አገልግሎት ከዘር የተላለፈ አርበኝነት ሆኖ የሚፈረጅ ነው፡፡
በዚህ ረገድ የዚያን ጊዜው ወጣትና የዛሬው አዛውንት ፕሮፌሰር ከኢትዮጵያና ከህዝቧ ጋር መቼ እና እንዴት እንደተዋወቁ ሲናገሩ « ... በእርግጥ የኢትዮጵያ ተምሳሌቴ እናቴ ናት። በተለይም በዕድሜና በትምህርት እየደረጀሁ ስመጣ እናቴ ስለኢትዮጵያ ታሪክ ትነግረኝ ነበር። ኢትዮጵያ የታሪክ ባለፀጋ መሆኗን ሁሌም ታጫውተኝ ነበር። ኢትዮጵያ በነፃነት የኖረችና ሕዝቧም ለነፃነቱ ተጋዳይ እንደሆነ ትተርክልኝ ነበር። በተለይም ፋሽስት ኢጣሊያ በነፃይቱ አገር ገብቶ እያደረሰ ያለውን ጭፍጨፋም ሀዘን በተሞላበት ሁኔታ ትገልፅልኝ ነበር። ከዚህም ሌላ እናቴ ታዘጋጀው በነበረው 'ኒው ታይም' (አዲስ ዘመን) ጋዜጣ ላይ ኢትዮጵያን የተመለከቱ ጽሑፎችን በማንበብ ኢትዮጵያን ለማወቅ አስተዋፅኦ አድርጐልኛል። ይህ ብቻም አይደለም ዩኒቨርሲቲ ስገባ ኢትዮጵያን የበለጠ የማውቅበት ተጨማሪ መድረክ አገኘሁ። ለንደን ከሚኖሩት ከሐኪም ወርቅነህ ልጆች በተጨማሪ ከነፃነት በኋላ ለንደን ከመጡት ፣ ከመንግሥቱ ለማ፣ ከአፈወርቅ ተክሌ፣ ከሐብተዓብ በአይሩ፣ ከሚካኤል እምሩ ... ወዘተ ጋር ጓደኝነት ፈጠፍኩ። እነዚህ ጓደኞቼ ስለኢትዮጵያ የሰጡኝ ዝርዝር መግለጫ ደግሞ ኢትዮጵያን አቅርበው አሳዩኝ።
« ... እናም የእናቴን ጋዜጣ ከማንበብ ባሻገር የኢጣሊያን ፋሽስታዊ ድርጊት በመቃወም ጋዜጣው ላይ መፃፍ ጀመርኩ። ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በፋሽስት ኢጣሊያን ላይ የሚያወጡትን መግለጫ፣ ስብሰባዎችንና ሰላማዊ ሰልፎችን እየተከታተልኩ ለእናቴ ጋዜጣ መዘገብ ጀመርኩ። ከሁሉም በላይ ደግሞ በአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን ጀርመናዊው የታሪክ ሊቅ ሉደልፍ ስለኢትዮጵያ የፃፈውን በማንበብና ለጋዜጣ በሚሆን መልኩ አዘጋጅ ስለነበር ስለ ኢትዮጵያ ያለኝን ዕውቀት የበለጠ አሰፋልኝ። ይህም በመሆኑ ከእናቴ ጋዜጣ በተጨማሪ በምድር ባቡር ሠራተኞች ጋዜጣ ላይም መፃፍ ጀመርኩ። እናም ገና በልጅነት ዕድሜ የቀሰምኩት እውነታ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን እንድወድ አድርጐኛል። ከሁሉም በላይ ግን እ አ አ 1951 ከእናቴ ጋር አብሬ በመምጣት ኢትዮጵያን ማየት መቻሌ በሁለንተናዊ መልኩ 'ማየት ማመን ነው' የሚለውን አባባል አረጋገጠልኝ...» በማለት የትናንቱን የሕይወት ጉዞአቸውን ያስታውሳሉ።
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ትናንት የጀመሩትን የአርበኝነት ፍልሚያ በቀጣይም የህይወታቸው አካል በማድረግ እናታቸው ሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስት ኢትዮጵያን ለመኖሪያቸውም ሆነ ለመቀበሪያቸው መርጠው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ኢትዮጵያን እንደ እናታቸው በማፍቀር ' አንለያይም' በማለት እ.አ.አ በ1956 አዲስ አበባ ይገባሉ።
ሙሽራው ምሁር
ወጣቱ ዶክተር ሪቻርድ ፓንክረስት እናታቸውን ተከትለው አዲስ አበባ ሲመጡ በቅፅበታዊ ትውውቅ ቢቢሲ ዋና መስሪያ ቤት ፊት ለፊት በሚገኝ አደባባይ ቀጥረው ያናገሯቸው እና በስፔን ሬስቶራንት ራት ጋብዘው ከማፍቀር ባለፈ ለትዳር ከጠየቋት ፍቅረኛቸው ጋር በመለያየታቸው ከአካላቸው ክፍል አንዱን ትተው የመጡ ያህል ሆኖ ይሰማቸዋል። ደግሞም ፍቅር ሩቅ ለሩቅ ሲሆን እንከን እንደማያጣው ያምናሉ። እናም ፍቅረኛቸውን አዲስ አበባ እንዲመጡ ያግባቧቸዋል።
ወጣቷም ጥሪው «ሲሻኝ ጢስ ወጋኝ» ሆነባቸውና ለንደንንተሰናብተው አዲስ አበባ ይገባሉ። ቀንም ሆነ ሌሊት ወደ ለንደን ይጓዝ የነበረው የምሁሩ ዕዝነ ልቦናም መንጐዱን አቆመ። «ሳይደግስ አይጣላም» እንዲሉ ወጣቷ ሪታ አልደን ደግሞ ውለው ሳያድሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የቤተ መጽሐፍት ኃላፊ ይሆናሉ።
ወጣቶቹ የለንደን ልጆች ' የአራዳ ልጆች' ከመሆን ባለፈ ፍቅራቸውን በትዳር ለማጥበቅ ይወሰናሉ። የሠርግ ሥነ ሥርዓታቸውን በእንግሊዝ ኦምባሲ ውስጥ ለመፈፀም ይስማማሉ። ይሁን እንጂ የዚያን ጊዜው ወጣት የምጣኔ ሀብት ታሪክ ምሁር ስለኬንያ ነፃነት፣ ጆሞ ኪንያታ ከእስር እንዲፈቱ፣ አፍሪካውያን የትግል መሳሪያ የሚሆናቸውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት እንዳለባቸው የሚያስገነዝቡ ጽሑፎችን ለንደን ይታተም በነበረው ' ዌስት አፍሪካ በሚባል መጽሔትና በአቶ አሀዱ ሳቡሬ ዋና አዘጋጅነት በሚታተመው ፈረንሳይኛና አማርኛ ጋዜጣ ላይ አውጥተው ስለነበር የጥንዶቹ የሠርግ ግብዥ በኤምባሲው ግቢ ውስጥ እንዳይካሄድ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ይከለከላሉ። እናም የሠርጋቸው ሥነ ሥርዓት በኤምባሲው ቅጥር ግቢ ከተፈፀመ በኋላ የራት ግብዣቸውን በገነት ሆቴል ለማካሄድ ይገደዳሉ።
ሙሽሮቹ ለጊዜውም ቢሆን ገነት ሆቴልን የጫጉላ ቤት ያደርጉታል። ይሁንና በዕድሜ የገፉ እናታቸውን በቅርብ ሆነው ለመደገፍ በማሰብ ኑሮአቸውን በእናታቸው መኖሪያ ቤት ያደርጋሉ። ከእናታቸው ጋር በሰላምና በፍቅር በመኖር ላይ እያሉ ሚስስ ሲልቪያ በፀና ታምመው እ.አ.አ በ1960 ከዚህ ዓለም በሞት ይለያሉ። ዶክተር ሪቻርድ በእናታቸው ሞት ምክንያት መራራ ሀዘን ውስጥ ይገባሉ። በሌላም በኩል የእናታቸው ቀብር ኢትዮጵያውያን ከልብ በመነጨ ሀዘንና በተለይም አፄ ኃይለስላሴ በተገኙበት በታላቅ ሥነ ሥርዓት መፈፀሙን ሲመለከቱ ወገን መሀል መሆናቸውን ያረጋግጣሉ። እናም በጊዜ ሂደት ለእናታቸው ተዘጋጅቶ የነበረውንና ጦር ኃይሎች አካባቢ የሚገኘውን ቤት በመግዛት ወልደው ለመሳም ይበቃሉ።
ተመራማሪው - መሪጌታ
ወጣቱ ሪቻርድ ፓንክረስት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እንዳገኙ እዚያው ለንደን ከተማ በአንድ ታዋቂ ኢንስቲትዩት እና ለንደን ዩኒቨርስቲ በተመራማሪነትና በመምህርነት አገልግለዋል። ይሁን እንጂ እ.አ.አ በ1956 ከእናታቸው ጋር ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላም ለንደን ጀምረውት ከነበረው የሥራ መስክ አልተለያዩም። እናም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ መምህር ሆነው ሥራቸውን ሲጀምሩ ጊዜ አልፈጀ ባቸውም።
በወቅቱ ስለአዲስ አበባም ሆነ ስለኮሌጁ ስለነበራቸው ስሜት ሲናገሩ « ... ለአጭር ጊዜም ቢሆን አዲስ አበባን የአየኋት በመሆኑ ብዙም ግርምት አልፈጠረችብኝም። በእርግጥ ከአውሮፓ ለመጣ ሰው እንግዳ መሆን የማይቀር ነው። ግን ደግሞ እናቴም ስላለችና ቀደም ሲልም ለንደን ያፈራኋቸው ኢትዮጵያውያን ጓደኞች ስለነበሩኝ ባይተዋርነት አስተሰማኝም። በእርግጥ ገና ባልተደራጀ ኮሌጅ ውስጥ መስራት ችግሩ ውስብስብ ነው። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲስቲ ኮሌጅ አደረጃጀቱ ያልተጠናከረ በመሆኑ ክፍተቱን ለመሙላት ተደራራቢ ሥራዎችን መሥራት ግድ ነበር። ይህም በመሆኑ የተለያዩ የትምህርት አይነቶችን ማስተማር ነበረብኝ። በዚህም መሠረት ኢኮኖሚክስ ፣ የዓለም፣ የአፍሪካና የኢትዮጵያ እንዲሁም የግብዕ ታሪክ ሳይቀር አስተምር ነበር። ይህ ሲሆን ግን ያልተማርኩትንና የማላውቀውን የትምህርት አይነት አንብቤ አስተምር ነበር። በወቅቱ የነበረው የሥራ ጫና ደግሞ በሰብዕና ላይ ተጨማሪ ዕውቀት እንዳገኝ አድርጐኛል። ከማስተማሩም ባለፈ ወደ ምርምርና ጥናት እንዳተኩርም አድርጐኛል» በማለት ሃምሳ ስድስት ዓመት ወደ ኋላ ተጐዘው ያስታውሳሉ።
ያም ሆነ ይህ በአፍላ ጉልበታቸው በመምህርነት ከሰጡት የላቀ አስተዋፅኦ ባለፈ ኮሌጁን ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለማሸጋገር በተደረገው እንቅስቃሴ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ማበርከታቸውን ይናገራሉ። በተለይም እ.አ.አ ከ1956 እሰከ 1976 የሰጡት ወሰን የለሽ ሙያ ተልዕኮ ዛሬ ላይ ሆነው የሚኮሩበት መሆኑን ይናገራሉ። ዶክተር ሪቻርድ ፓንክረስት በመምህርነት ብቃታቸው፣ በጥናትና ምርምር ውጤታቸው የረካው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ በማጐናፀፍ ማንነታቸውን አዲስ ምዕራፍ ላይ ያስቀምጠዋል።
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በአብዮቱ ማግስት እ.አ.አ በ1976 ወደ ለንደን በማምራት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጀመሩትን ጥናትና ምርምር በኦርየንታልና በአፍሪካን ጥናት ትምህርት ቤት እና በለንደን ዩንሸርስቲ ይቀጥላሉ። እንዲሁም' ሮያል ኤዥያቲክ ሶሳይቲ' ለተባለው ተቋም የቤተመጽሐፍት ኃላፊም በመሆን አገልግለዋል ። ይሁን እንጂ እ.አ.አ በ1986 አዲስ አበባ በመመለስ የመምህርነትና የተመራማሪነቱን ተግባር አጣምረው በማራመድ ለአገራችንም ሆነ ለዓለም አቀፍ ህብረተሰብ የሚጠቅም የጥናትና ምርምር ውጤቶች በመጽሐፍ እያሳተሙ ይፋ አድርገዋል።
ዘመን ተሻጋሪ ስጦታዎች
« ... ምንም እንኳን የእንግሊዝ ፓስፖርት ቢኖረኝም እኔ ግን የዓለም ልጅ ነኝ። ... እናም ዓለም ደግሞ የእኔ አገር ነች» የሚሉት አዛውንቱ ፕሮፊሰር « ...ኢትዮጵያ ደግሞ ለእኔ ልዩና ታሪካዊ አገሬ ናት...» በማለት በልበ ሙሉነት ይናገራሉ። እናም ከልጅነት እስከ ዕውቀት ባለው የሕይወት ዘመናቸው እርሳቸውና ኢትዮጵያ በአካልም በመንፈስም ባለመለያየታቸው ጥናትና ምርምራቸው ሳይቀር ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረገ መሆኑን በአፅንኦት ይናገራሉ።
ገና በወጣትነት ዕድሜያቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት በማገለገል ላይ እያሉ ኢትዮጵያ እልቆ መሳፍርት የሆነውን ታሪኳን የሚፈትሽ አትዮጵያዊ የሆነ የጥናትና ምርምር ተቋም እንደሚያስፈልግ ይወስናሉ። እናም እ.አ.አ በ1963 የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩትን በማቋቋም ለኢትዮጵያ ህዝብ ታላቅ የማንነት ማረጋገጫ ማዕከል ያበረክታሉ።
«... ኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ ያላት መሆኗን የተገነዘብኩት በ17ኛው ክፍለ ዘመን ሉዳልፍ የተባለው ጀርመናዊ የታሪክ ሊቅ ስለ ኢትዮጵያ የፃፈውን ለእናቴ ጋዜጣ በሚሆን መልኩ ሳዘጋጅ ነው። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን የታሪክ ባለፀጋነት የበለጠ ለማወቅ ደግሞ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ብቻ ያነጣጠረ የምርምር ማዕከል አስፈላጊ ነበርና ተግባራዊ አደረኩት። እነሆ ኢንስቲትዩቱም የታለመለትን ዓላማ ዕውን አድርጓል። ኢትዮጵያው ያን ብቻ ሳይሆኑ ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች ሳይቀሩ የኢንስቲትዩቱ ተጠቃሚ ሆነዋል። በሌላም መልኩ በኢንስቲትዩቱ የተቋቋመው ሙዚየም በአገር ገፅታ ግንባታ የማይናቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው። ቤተ መጽሐፍቱም ኢትዮጵያን ለማጥናትና ለመመራመር ሁነኛ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው። ያም ሆነ ይህ ኢንስቲ ትዮቱ በውስጤ የነበረውን ምኞትና ፍላጐቴን በሕይወት ዘመኔ ተግባራዊ ሲያደርግ በማየቴ ኩራት ይሰማኛል።» በማለት የኢንስቲትዩቱ መስራችና ለአስራ ሁለት ዓመት በዳይሬክተርነት ስለመሩት ዘመን ተሻጋሪ ስጦታ ይናገራሉ።
ፕሮፌሰሩ ሪቻርድ ፓንክረስት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበረከቱት ገጸ በረከት ኢንስቲትዩቱ ብቻ ሳይሆን ለአገራችን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማሪያና እና ለዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች ደግሞ ማጣቀሻ የሚሆኑ ከሃያ ሁለት በላይ መጽሐፍትን ለሕትመት አብቅተው ለትውልድ ሁሉ የሚተላለፉ ህያው ቅርስ አበርክተዋል። ይህ ብቻም አይደለም ከ400 በላይ የተለያዩ የምርምር ጽሑፎችን በመፃፍ ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ለንባብ አብቅተዋል። እ.አ.አ ከ1956 ዓ.ም ጀምረው በመምህርነት፣ በጥናት ምርምር ውጤታቸውና ክህሎታቸው በፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያበቃቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መጠነ ሰፊ ለሆነው ምሁራዊ አስተዋፅኦአቸው የክብር ዶክትሬት (PHD) ዲግሪ አበርክቶላቸዋል።
በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጥናትም ምርምር በማድረጋቸውም ከአፄ ኃይለሥላሴ የሽልማት ድርጅትና ከእንግሊዝ መንግሥት የወርቅ ሜዳሊያና ኒሻን ተሸላሚ የሆኑት እኒህ የአገር መከታ በቅኝ ገዥዎችና በፋሽስት ኢጣሊያ የተዘረፈ ታሪካዊ ቅርሶችን በማስመለሱ ረገድም በፊታውራሪነት ተሰልፈው ውጤት አስመዝግበዋል። ለዚህም የተዘረፉ ቅርሶችን ለማስመለሰ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆንና በፊታውራሪነት በመሰለፍ የአክሱም ሐውልትን ፣ የአፄ ቴዎድሮስ ክታብን ፣ ታቦትና ታሪካዊ የብራና ፅሑፎችን፣ ጋሻና ጦርን ... ወዘተ የመሳሰሉት ታሪካዊ ቅርሶች ለአገራቸው እንዲበቁ በማድረግ ሕዝባችንን ከዘመናት ፀፀትና ቁጭት እንዲላቀቅ አድርገዋል፡፡ ይህን በማድረጋቸው እንደ አርበኛዋ እናታቸው ከኢትዮጵያና ከህብረተሰቡ ከበሬታን ከመጐናፀ ፋቸው ባለፈ እርሳቸውም በልጅነት የጀመሩትን አርበኝነት ዛሬም ገናና ሆኖ እንዲታይ አድርገዋል።
አዛውንቱ ፕሮፌሰር
ፋሽስት ኢጣሊያን ገና በልጅነት ዕድሜያቸው በጽሑፋቸው የተፋለሙት ትንታጉ የለንደኑ ቡቃያ ዛሬ የሰማኒያ አምስት ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ሆነዋል። ከዚሁ የህይወት ዘመናቸው ከሃምሳ አምስት ዓመት በላይ የሆነውን የዕድሜያቸውን ክፍል ደከመኝና ሰለቸኝ ሳይሉ ዕውቀታቸውንም ሥነ ጉልበታቸውን ለኢትዮጵያ እና ለሕዝቦቿ ዕድገት አበርክተዋል።
እነሆ የተፈጥሮ ሕግ ሆነና እኒህ የአገር ባለውለታ ዛሬ እርጅና ተጫጭኖአቸዋል። ይሁን እንጂ የእርሳቸው ውጤት የሆኑት የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ እንዲሁም መማሪያና ማጣቀሻ የሆኑት መጽሐፍ ቶቻቸው የዛሬው አዛውንት ዘላለማዊ ወጣት አድርገው ያሳዩአቸዋል።
ፕሮፌሰር ፓክረስት እንደ እናታቸው ሁሉ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ቁርኝት ወሰን የለሽ ነው። ቤተሰ ቦቻቸውም እርሳቸው ከሚጓዙበት ፈር አላፈገፈጉም።
******************************
http://www.ethpress.gov.et
ሪፖርተር ዋካ ይርሳው
ቀን 2012

ሲልቪያ ፓንክረስት - የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ

በፍቅር ለይኩን

እንግሊዛዊቷ ሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስት በ1953 ዓ.ም. በወርሀ መስከረም በመስቀል በዓል ዕለት  አርፈው የቀብራቸው ሥነ ስርዓት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተፈጸመው በማግስቱ መስከረም 18 ቀን ነበር፡፡
ሲልቪያ ፓንክረስት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ፣ የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ ኢትዮጵያ በኢጣሊያን በተወረረችበት ጊዜም ወረራውን በመቃወም የፀረ ፋሽስት ዘመቻን በአውሮፓ ያስፋፉ፣ የፋሽስትን ኢሰብአዊ የሆነ ጭፍጨፋና ግፍ ያጋለጡ፣ የሰው ልጆች መብትና ነፃነት ተቆርቋሪ የሆኑ በታሪክ ትልቅ ስፍራ የተሰጣቸው ታላቅ ሴት ናቸው፡፡ ሲሊቪያ ፓንክረስት ታጋይ ብቻ ሳይሆኑ የታሪክ ተመራማሪና ጸሐፊም ናቸው፡፡ እኚህን የኢትዮጵያን የቁርጥ ቀን ወዳጅ የሞቱበትን 52ኛ ዓመት በማስመልከት ታሪካቸውን በጥቂቱ ልንዘክረው ወደድን፡፡

ሲልቪያ ፓንክረስት የተወለዱት ሚያዝያ 27 ቀን 1874 ዓ.ም. በእንግሊዝ አገር ማንችስተር በተባለው ከተማ ነው፡፡ ለሲልቪያ ፓንክረስት የወደፊት ሕይወት ላይ ደማቅ አሻራን ያኖሩት አባታቸው ዶ/ር ሪቻርድ የእንግሊዝ ሌበር ፓርቲ ንቁ ተሳታፊ፣ ለድሆች ተሟጋችና መብታቸውን ለተነፈጉ ሁሉ ድምፅ ነበሩ፡፡ እናታቸው ኤምሊ ፓንክረስትም ሴቶች  በእንግሊዝና በአውሮፓ ፖለቲካና ምርጫ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ትልቅ ሚና የተጫወቱና ብርቱ ትግል ያደረጉ ሴት ነበሩ፡፡

ሲልቪያ የአባታቸውንና እናታቸውን አርአያ በመከተል ዕድሜ ዘመናቸውን ሁሉ ለሰው ልጆች መብትና ነፃነት በመታገል አሳልፈዋል፡፡ በ1928 ዓ.ም. ወራሪው ፋሽስት ኢጣሊያ የኢትዮጵያን ሕዝብ በመርዝ ቦምብ ሲፈጅና የፍትሕ ያለህ እያለ በሚጮኽበት፣ ኢትዮጵያውን አርበኞች በዱር በገደል ለአገራቸው ነፃነት ደማቸውን በማፍሰስ ላይ በነበሩበት ጊዜ ሲልቪያ ፓንክረስት ማንንም ሳይፈሩ የፋሽስት ወራሪውን ኃይል ግፍን በድል በግልፅ በአደባባይ በመቃወም ድምፃቸውን ለዓለም ሁሉ ሕዝብ ያሰሙ የነፃነት አርበኛና የጭቁን ሕዝቦች አለኝታ ነበሩ፡፡

የኢጣሊያ ወታደሮች አዲስ አበባን ከያዙበት ከ1928 ዓ.ም. ጀምሮ በእንግሊዝ ‹‹The New Times and Ethiopian News›› የተባለውን ጋዜጣ አቋቁመው ያለ ማቋረጥ በየሳምንቱ በማሳተም ለኢትዮጵያውያን ነፃነት፣ ክብርና ልዑላዊነት ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡ በዚህ ጋዜጣም ፋሽስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እያደረስ ያለውን ግፍ በመግለፅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነትን ሊያገኙ ችለው ነበር፡፡

በዚህም እንቅስቃሴያቸው ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች ገንዘብ በመሰብሰብና በመላክ ታላቅ የሆነ ሰብአዊ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ ከኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ሥልጣኔ፣ ታሪክ፣ ባህል፣ የሕዝቦቿ የነፃነት ተጋድሎና ኩራት እጅግ የተማረኩት ሲልቪያ ፓንክረስት ከነፃነት በኋላ በቀሪው ዕድሜያቸው በሩቅ የሚያውቋትን ኢትዮጵያን በአካል በመገኘት ስለ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያውያን ለማጥናት ሲሉ በ1948 ዓ.ም. ከወንድ ልጃቸው ከሪቻርድ ፓንክረስት ጋር ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡

በኢትዮጵያም ውስጥም ‹‹Ethiopian Observer›› የተባለውን መጽሔት በማዘጋጀት በየወሩ ያሳትሙ ነበር፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ ጋር የነበራትን ግንኙነት በተመለከተ፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ በኩል ስላለው ታሪካዊ ግንኙትና ፖለቲካዊ ቀውስ ሰፊ የሆነ ጥናትና መልካም ተሳትፎ ያደርጉ እንደነበር በዘመኑ ካስነበቧቸው ጽሑፎች መረዳት ይቻላል፡፡ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ መስከረም 18 ቀን 1953 ዓ.ም. እትሙ በሲልቪያ ፓንክረስት የቀብር ሥነ ሥርዓት የአገር ግዛት ሚኒስትር የነበሩት ራስ አንዳርጋቸው መሳይ ለእኚህ የኢትዮጵያ ወዳጅ ያደረጉትን ንግግር እንዲህ ዘግቦት ነበር፡-

‹‹… ሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስት በኢትዮጵያ ገና ብዙ ለማገልገል ከፍ ያለ ምኞት ስለነበራቸው በዛሬው ቀን የቀጠሩን እዚህ ሳይሆን ሌላ ስፍራ ነበር፡፡ በእውነት እላችኋለሁ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ መከራ፣ ግፍና ስደት አልቆ ውጤቱ እስኪደርስ ድረስ ሚስ ሲልቪያ የሠሩት ሥራ በሽማግሌ ጉልበታቸውና ላባቸው ብቻ ሳይሆን ጤናቸውን እስኪያጡ፣ ርስታቸውን ሽጠው እስኪደኸዩ፣ በግል ገንዘባቸው ጭምር ለኢትዮጵያ የሠሩ ሰው ናቸው፡፡ ስለዚህ ታላቋ እንግሊዛዊት ሚስ ሲልቪያ ፓንክረስት የኢትዮጵያ ወዳጅ፣ እውነተኛዋ ኢትዮጵያዊ አርበኛ መባል የሚገባቸው ናቸው፡፡

ክቡር ራስ አንዳርጋቸው ንግግራቸውን በመቀጠልም፡-
‹‹… ወዳጃችን ሲልቪያ ፓንክረስት ሆይ 25 ዓመት ሙሉ ያለ ዕረፍት የዕድሜዎን ሸክም ሳያስቡ በእውነትና በታማኝነት የረዱዋቸው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትና ሕዝብ አሁን በዙሪያዎ ቆመው ያለቅሱልዎታል፡፡ ወዳጆችዎ አርበኞችና ስደተኞች እዚሁ ባጠገብዎ ቆመዋል፡፡ ያንንም የመከራ ዘመን ያስባሉ፡፡ ታሪክዎ ከታሪካቸው በደም ቀለም ተጽፎ ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡ እርስዎም በዚህች በኢትዮጵያ ምድር ላይ በሰላም አርፈው እንዲኖሩ የግርማዊነታቸው መልካም ፈቃድ ስለሆነ እንደ ኢትዮጵያዊት ዜጋ ቆጥረን በክብር እናሳርፍዎታለን፡፡ እግዚአብሔር በምድር ላይ ሳሉ የሠሩትን በጎ ሥራ ሁሉ ቆጥሮ በሰማይ ቤት የክብር ቦታ እንዲያድልዎ እንመኛለን፡፡›› በማለት ነበር እኚህ ታላቅ የኢትዮጵያ ባለውለታ በጥልቅ ሐዘን ስሜት ውስጥ ሆነው የተሰናበቷቸው፡፡

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም በሚስ ሲልቪያ ፓንክረስት የቀብር ዕለት ባደረጉት ንግግራቸው፡-

‹‹…ሚስስ ሲሊቪያ ፓንክረስት ኢትዮጵያን ለማገልገል ቆርጠው ከተነሱበት ጊዜ ጀምሮ የመጨረሻው ድል እስኪገኝ ድረስ ያደረጉትን የአሳብና የሥራ ተጋድሎ ሰፊ የታሪክ መስመር የያዘ ነው፡፡ ምኞታቸውና እምነታቸው የማይበገር የምሪት ምሽግ ነበር፡፡ የመንፈሳቸው ጽናት በፊታቸው የተጋረደውን እንቅፋት አስወግዶ ለማለፍ የተለየ ሥልጣን ነበረው፡፡ የኢጣሊያ ፋሽስት ጦር በዓለም መንግሥታት የተከለከለ የመርዝ ጢስ እየጣለ ሰላማውያኑን ሕዝብ ሴቱንና ሽማግሌውን ሕጻኑን ለመጨረስ ስለተነሳ ይህን ግፍ ለዓለም ሸንጎ ለማሰማት ወደ ጄኔቭ መሄዳችንን ሲከታተሉ የቆዩት ሚስስ ሲልቪያ በዓለም ላይ ከዚህ የባሰ ምን በደል ይድረስ በማለት ለእውነተኛው ፍርድ በመቆርቆር ተነሱ፡፡

‹‹ፋሽስቶች የኢትዮጵያን ሕዝብ ያለ ፍርድ ፈጁት፡፡ ሚስስ ፓንክረስትም የጽሑፍና የፎቶግራፍ ማስረጃዎች እያሰባሰቡ ዓለም ይህን ሰምቶና አይቶ ካልፈረደ ለራሱ ወዮለት እያሉ ጮኹ፡፡ የኢትዮጵያን አርበኞች ተስፋ ለማስቆረጥ ፋሽስቶች  በመርዝ ጢስና ቦምብ ያደረጉባቸውን የጭካኔ ውጊያ ሴቱንና ሕጻኑን ያለ ምክንያት እየሰበሰቡ በመትረየስ መፍጀታቸውን ማስረጃ አቀረቡ፡፡

‹‹ሚስስ ፓንክረስት በባሕርያቸው እውነተኛ ፍርድ ለማግኘት ሲታገሉ፣ የዚህችን ጥንታዊ አገር ታሪክ፣ ሥልጣኔና ቅርስ የሕዝቦቿን ጀግንነትና ፍቅር እየማረካቸው ሄደ፡፡ ከኢትዮጵያና ከሕዝቦቿ ጋር በፍቅር የወደቁት ሲልቪያ ፓንክረስት ለሀገራቸው ነፃነትና አንድነት ክቡር ሕይወታቸውን ከከፈሉት ኢትዮጵያን አርበኞች የሚደመሩ ናቸውና በዚህ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ያርፉ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ሆኗል፤›› በማለት ነበር እኚህን ታላቅ የኢትዮጵያ ወዳጅ መቼም ቢሆን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሁሌም ሥራቸው ሲታወስ እንደሚኖር በትልቅ አድናቆትና አክብሮት የተሰናበቷቸው፡፡

ሚስስ ፓንክረስት በሁለተኛ ዓለም ጦርነት ባሎቻቸውን ያጡትን ባልቴቶችና እንዲሁም ድኃ አደግ የሆኑትን ልጆች በመሰብሰብ ከፍ ያለ ዕርዳታ አድርገዋል፡፡ ትምህርት ቤትና ክሊኒኮችንም ከፍተው ገቢው ለሠራተኞች በተለይም ለመርከበኞችና ለወታደሮች ሚስቶች ጉዳይ እንዲውል በማድረግ ራሳቸው ጸሐፊ በመሆን ታላቅ ሥራ ሠርተዋል፡፡ በአምስቱ ዓመት የፋሽስት ወረራ ዘመን ማቲዎቲ የሚባለው የፋሽስት ተቃዋሚ ድርጅት መሥራችና ዋና ጸሐፊ ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሰፊ የሆነ ጥናትና ምርምር ያደረጉም ሴት ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ከጻፏቸው መጻሕፍት መካከልም፡- የኢጣሊያ ጦርነት ወንጀል በኢትዮጵያ፣ የእንግሊዝ አመራር በኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች መብታቸውና ዕርምጃቸው፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ፣ ‹‹The Cultural History of Ethiopia›› የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በቅርቡም በርካታ ኢትዮጵያንን በግፍ ለፈጀውና ላስገደለው ለፋሽስቱ የጦር ጄኔራል ለፊልድ ማርሻል ግራዚያኒ በደቡብ ኢጣሊያ አፊላ በተባለችው መንደር ለቆመው መታሰቢያ ሐውልትና ፓርክ በዓለም ዙሪያ የተቃውሞ ድምፃቸውን ካሰሙት መካከል የሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስት ልጅ የሆኑት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትና ባለቤታቸው ሪታ ፓንክረስት ይገኙበታል፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ ወዳጆች የሆኑ ምሁራን የኢትዮጵያን የቁርጥ ቀን ወዳጅ የሆኑትን የሲልቪያ ፓንክረስትን መንገድ በመከተል ከሌሎች ኢትዮጵያን ጋር በመተባበር ለጦር ወንጀለኛው ለግራዚያኒ መታሰቢያ በኢጣሊያ የተሠራውን መታሰቢያ በመቃወም በለንደን ከተማ ተቃውሞአችውን ማስማታቸው በልዩ ልዩ የመገናኛ ብዙኃን ተገልጾ ነበር፡፡

እነዚህ የኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ የረጅም ዘመንና የቁርጥ ወዳጅና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ነጻነት ቀናኢ የሆኑትን ሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስትን ምንም እንኳን በሞት ቢለዩንም ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የከፈሉት መስዋእትነት፣ ያሳዩት ፍቅርና ክብር መቼም ቢሆን በሁላችን ልብ ውስጥ ሕያው ሆኖ የሚዘልቅ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ያደረጉትን መልካም ሥራና በጎ ውለታ ዳግም እንደገና በልጃቸው በፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትና በቤተሰቦቻቸው አሁንም ድረስ ቀጥሏል፡፡

እነኚህ የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑ እንግሊዛውያን  ቤተሰቦች በየዓለም አቀፉ መድረክ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ያላቸውን ወዳጅነት በተለያየ አጋጣሚ አሳይተዋል፣ እያሳዩም ነው፡፡ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ በዓለም አቀፍ መድረክ ከማስተዋወቅ በተጨማሪ በፋሽስት ኢጣሊያ ተዘርፎ የሄደውን የአክሱም ሐውልት እንዲመለስ በዓለም አቀፍ መድረክ ከሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ታላቅ ሥራን ሠርተዋል፡፡ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመንም በእንግሊዛውያን የተዘረፉ የኢትዮጵያ ቅርሶችን በማስመለስ ረገድም ጉልህ ሚና ነበራቸው፡፡ የሚስስ ሲልቪያና የቤተሰቦቻቸው ለኢትዮጵያ ያላቸው ፍቅር፣ ክብርና ያደረጉት ውለታ ሁሌም ሕያው ሆኖ የሚዘከር ነው፡፡

የሲልቪያ ፓንክረስትን ታላቅ ታሪክና መልካም ሥራቸውን ለመዘከር ሲባል ከሁለት ዓመት በፊት በስማቸው መታሰቢያ ለማቋቋም እንቅስቃሴ ተጀምሮ እንደነበር ይታወሳል፤ ይህ እንቅስቃሴ የት እንደደረሰና ምን ያህል እንደተጓዘ ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቋም ያሉ በተለይም ደግሞ በዚህ ተቋም ውስጥ ያሉ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ወዳጆች ማኅበር የእኚህን ታላቅ የኢትዮጵያ ወዳጅ ሥራና ታሪክ የሚዘክር ዐውደ ጥናት /Public Lecture  ለማካሄድ ቢታሰብበት መልካም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

የኢትዮጵያን ጥናትና ምርምር ተቋም ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ተቋሙን በመምራትና በማደራጀት ሰፊ የሆነ ተሳትፎ የነበራቸው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትና ባለቤታቸው ሚስስ ሪታ ፓንክረስት ከተቋሙ የሥራ ባልደረቦችና ከተቋሙ ወዳጆች ጋር በመሆን በእኚህ ታላቅ ሴት ስም ለማቋቋም የታሰበው መታሰቢያ ጅምር እቅድ ወደፊት መጓዝ ይችል ዘንድ እንዲህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በኩል ቢጀመር መልካም እንደሆነ ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡ ፍቅርና ክብር ለኢትዮጵያ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝቦችና ወዳጆች ሁሉ!
ሰላም! ሻሎም!
***********
ምንጭ:---http://www.ethiopianreporter.com

 

የአማርኛ ፊደል ክርክር በታይፕራይተር ዘመን

የአማርኛ ፊደል ክርክር በታይፕራይተር ዘመን 

ዮናስ ብርሃኔ  

በንጉሡ ዘመን ነው፡፡ ታይፕራይተር ወደ አገራችን እንደገባ ሰሞን በአጠቃቀም ዙሪያ ውዝግብ ተነስቶ የነበረ ሲሆን እነ መንግሥቱ ለማም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አደባባይ መድረክ ብቅ ያሉበት አጋጣሚም ነበር፡፡ መንግሥቱ ለማን ጨምሮ ሌሎች ወጣት ተማሪዎች የትምህርት እድል አግኝተው ወደ እንግሊዝ ለመሄድ እየተዘጋጁ በነበረበት ወቅት፣ በአራት ኪሎ ቅድስት ሥላሴ ግቢ ደግሞ በአማርኛ ፊደል ዙሪያ ቅልጥ ያለ ክርክር እየተካሄደ ነበርና ወጣቶቹ ተማሪዎቹም እዚያ ላይ እንዲገኙ በትምህርት ሚኒስቴር ተጋብዘው ይሄዳሉ፡፡
ነገሩን ራሳቸው መንግሥቱ ለማ እንደገለፁት በማለት ንቡረ እጽ ኤርምያስ ከበደ ስለ ሁኔታው ሲያትቱ፤ ..መንግሥቱ ከሌሎች ወዳጆቹ ጋር ወደ ጉባኤው ሲገቡ ሁለቱ ቀንደኛ ተከራካሪዎች የወቅቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር አቶ አበበ ረታ እና በቤተመንግሥት የታሪክና የመጻሕፍት ሹም የነበሩት ብላታ መርሰዔ ሀዘን ወልደ ቂርቆስ የጉባኤው ሊቀመንበር እና በጊዜው የሥራ ሚኒስትር ከነበሩት ብላታ ዘውዴ በላይነህ ግራ እና ቀኝ ተቀምጠው ነበር፡፡ እነሱ በገቡበት ሰዓት የነበረው ድባብ ..በላቲኑ ሥርዓት፣ በላቲኑ ፊደል እንጻፍ.. የሚለው የብላታ መርስዔ ኅዘን ሃሳብ ወደመሸነፉ አጋድሎ፣ ቅጥሉን አንድ አይነት አድርገን አሻሽለን በራሳችን ፊደል እንጠቀም የሚለው የአቶ አበበ ረታ ሃሳብ ሳያሸንፍ፣ ታዳሚው የአቶ አበበን ሃሳብ እንቀበለው አንቀበለው እያለ በማመንታት ላይ እንደነበር የሚገልፁት መንግሥቱ ለማ፤ እሳቸው የሚደግፏቸው የነበሩትና ቀደም ሲል በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በዚሁ ዙሪያ ሲደረግ በነበረው የጦፈ ክርክር፤ የአገራችን ፊደል መነካት የለበትም በማለት ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ የነበሩት አቶ ብርሃኑ ድንቄም ስብሰባው ላይ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ ..ፊደላችን ይለውጥና በፈረንጆቹ መንገድ እንሥራ.. የሚለውን የራስ እምሩን ሃሳብ የሚያቀነቅኑት ኮሎኔል ታምራት ይገዙም እዚሁ ስብሰባ ላይ ነበሩ፡፡ የአማርኛ መጻፊያ ፊደል ይሻሻል የሚለው ሃሳብ በወቅቱ የተነሳበት ዋነኛ ምክንያት የአማርኛው ፊደላት ለታይፕራይተር መጻፊያ አያመችም በሚል ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያየ አቋም የነበራቸው ተከራካሪዎች በሃሳብ እየተፋጩ በነበረበት በዚህ ጉባዔ ላይ በርካታ የመንግስት ባለስልጣናት እና ታላላቅ ሰዎች የነበሩ ሲሆን በወቅቱ ታዲያ ..ቱርክ ፈረንጅ ሆናለችና እኛም ፈረንጅ እንሁን.. የሚለው የመርስዔ ኅዘን ሃሳብ መረታቱ ቢሰማኝም አልሸሹም ገለል አሉ (አይነት ነገር) የሆነው የራስ እምሩ ሃሳብ ወድቆ አይቀርም ብዬ ደስ ብሎኝ ነበር፡፡ ከሁለቱም ይብሱን አደገኛ የሆነው የአቶ አበበ ረቂቅ የማባበያ ሃሳብ አልወድቅም ብሎ ሲንገዳገድ፣ አንዳንዴም የመርስዔ ኅዘንንም የራስ እምሩንም ማየቴ፣ የኔም የጥንታዊ ፊደል ጠበቃነት ወኔን ነሸጥ አድርጐት ነበር፡፡  ግን ያ ሁሉ ሰው በተሰበሰበበት መሀል ተነስተው ለመናገር ድፍረቱን ስላጡ ዝም ብሎ ተቀምጠው እንደነበር ይነግሩናል፡፡ - መንግሥቱ ለማ፡፡ይሁንና በኋላ ላይ በጓደኞቻቸው ግፊት ሳይወዱ በግድ ወደ መድረኩ መውጣታቸው አልቀረላቸውም፡፡ በነገራችን ላይ መንግሥቱ ለማ ቀደም ሲል ፊደላችን መነካት የለበትም የሚለውን የአቶ ብርሃኑ ድንቄን ሃሳብ በመደገፍ ሰፋ ያለ መጣጥፍ አዘጋጅተው ለአዲስ ዘመን ጦማር (ጋዜጣ) አዘጋጅ ልኮ የነበረ ሲሆን በአንዳንድ የውስጥ ችግሮች ሳቢያ ግን ጽሑፉ አልወጣም ነበር፡፡ ይህንን ታሪክ ራሳቸው መንግሥቱ ለማ ናቸው በኋላ ላይ የተናገሩት፡፡ በመጨረሻ ወደ መድረኩ ተገፍተው የወጡት መንግስቱ ለማ፤ ቱርክ የራሷን ፊደል ትታ የፈረንጆቹን ስለተቀበለች በስልጣኔ ምንም ያህል እንዳልተራመደች፣ በተቃራኒው ግን ጃፓን ለመጻፍ ከእኛ በበለጠ በጣም የሚያስቸግረውን የራሷን ፊደላት ጠብቃ እንደያዘች በስልጣኔ የትና የት መራመድ እንደቻለች በመግለጽ፣ የቱርክን መንገድ እንከተል የሚሉትን ሃሳብ ድባቅ መተውታል፡፡ ከዚያም ቀጠል አደረጉና የፈረንጁ የፊደል ገበታ ሃያ ስድስት ፊደላት ብቻ ነው ያሉት ቢባልም በፈረንጁ እትም መጻፊያ መኪና ላይ የሰፈረው ሁለት የተለያየ የፊደል ገበታ ትልቅና ትንሽ Small & capital Letters  መሆኑን በመጥቀስ የእንግሊዝኛው ፊደላት ቁጥር በድምሩ 26 ሳይሆን 52 እንደሆነና የእኛንም ቅጥሎቹን ከፊደላቱ ለይተን በመኪናው ላይ ብናሰፍራቸው፣ ቅጠላቸው ተለይቶ ለብቻው ቢሠፍር፣ የማይቻሉትን ፊደላት /ደግሞ/ እንዳለ ብናስቀምጣቸው፤ እንዲሁም እነ ..ቸ..፣ ..ጀ..፣ ..ዠ..፣ ..ጰ.. ፣ ..ቷ..፣ ..ጓ.....ወዘተን በዋና ፊደላቸው ብቻ ብንተካቸውና ተጨማሪውን ምልክት ለብቻው ብናሳፍረው ለጽሕፈት መኪና የማያስቸግሩ መሆናቸውን በጥቁር ሰሌዳ ላይ እየጻፉ በማስረዳት ..ፊደላችን ለእጅ መኪና ጽሕፈት አይመችም.. የሚለውን የእነ አቶ አበበ ረታን ሃሳብ ፉርሽ አድርገው ቁጭ አሉ፡፡ መንግሥቱ ለማ ባቀረቡት ሃሳብ የተደመመው በጉባዔው ላይ ተገኝቶ የነበረው ህዝብም አድናቆቱን በሚገልጽ ሞቅ ያለ ጭብጨባ ተቀበለው፡፡ ነገሩም በመንግሥቱ ለማ ድል አድራጊነት የአማርኛ ፊደል የያዘውን ቅርጽ እንደያዘ ለዘመናት በታይፕራይተር ስንገለገልበት ቆይተን አሁን ደግሞ ኮምፒዩተር መጣ፡፡ በኮምፒዩተርም ላይ በአማርኛ መጻፍ የምንችልበት ሶፍትዌር ተሰራ፡፡ ይሁንና ለጽሑፍ ስራው ጥራት መሻሻል ወሳኝ የሆነው የቃላት (አጻጻፍ) ማረሚያ ገና ይቀረናል፡፡ በቅርቡ ጥቅም ላይ እንደሚውል ተስፋ እናድርግ፡፡
*******
ምንጭ:---http://www.addisadmassnews.com

 

ማሞ ካቻ (አቶ ማሞ ይንበርብሩ)

  አቶ ማሞ ይንበርብሩ (ማሞ ካቻ) እስቲ እናስታውሳቸው፣ ተቀብሮ እንዳይቀር አኩሪ ታሪካቸው  (ደረጀ መላኩ)   አቶቢሲ ማሞ ካቻ የት ትሄዳለህ? ገብረ ጉራቻ… ታዳጊው ማሞ ይንበርበሩ ገና በጨቅላ እድሜው አባቱ አቶ...