ሰኞ, ማርች 27, 2017

ዓድዋ ሲታሰብ



. . . አሁንም አገር የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል . . . . በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ . . . ያገሬ ሰው . . . ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፡፡ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በኀዘን እርዳኝ፡፡ . . .

ይህ ኃይለ ቃል ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ሕዝቡንና የየአካባቢውን መኳንንትና ገዢዎች በኢጣሊያ ላይ ያነሳሱበት የክተት አዋጅ ነበር፡፡ በዚህም አዋጅ መሠረትም የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ዓድዋ ላይ የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት ድል ተመቶበታል፡፡ ኢትዮጵያውያን አርበኞች በጠቅላይ አዝማቹ በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ አማካይነት ሕያው ታሪክ ያስመዘገቡበት ዓድዋ፡፡ የካቲት 23 ቀን በመላው ኢትዮጵያ  ዓድዋ ድል መታሰቢያ ይከበራል፡፡ 
ታሪኩ
በ1888 ዓ.ም. ኢጣሊያ የቅኝ ግዛት ሕልሟን እውን ለማድረግ በተነሣች ጊዜ ሰበበ ጦርነት የሆነው የውጫሌው ውል ነበር፡፡ በአንቀጽ 17 በኢጣሊያንኛ ትርጉሙ ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ጥብቅ ግዛት ነች፤ የውጭ ግንኙነቷ በርሷ በኩል ይሆናል የሚለው የተጭበረበረ ሐረግ ነበር ፍልሚያ ውስጥ የከተታቸው፡፡ 

ኢትዮጵያውያንም የውስጥ ችግራቸውን ወደጎን ትተው ከየማዕዘኑ ተጠራርተው በአፄ ምኒልክ መሪነት ከፍልሚያው አውድማ ተሰለፉ፡፡ በታሪክ ጸሐፊው በአቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ አገላለጽ፣ የኢጣሊያንንም ወታደር ከበው እየተፏከሩ በጥይትና በጎራዴ ሲደበድቡት የኢጣሊያ ጦር አራት ሰዓት ከተዋጋ በኋላ ሽሽት ዠመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያውያን እየተከታተሉ ሲወጉት፣ አዝማቹ ጄኔራል አልቤርቶኒ ተቀምጦበት የነበረው በቅሎ ተመቶ ወደቀ፡፡ ወዲያው ተነሥቼ አመልጣለሁ ብሎ ለመነሣት ሲጥር ከቅምጡ ሳይነሳ እየተሽቀዳደሙ የሚሮጡት ኢትዮጵያውያን ደርሰው ጄኔራሉን ማረኩት፡፡
የ1ኛው ክፍለ ጦር አዛዡ ተማርኮ፣ ሠራዊቱ በጭራሽ ከጠፋ በኋላ ሁለተኛው ክፍል የጦር ሠራዊት ራአዮ ከሚባለው ስፍራ ላይ ሆኖ፣ ካራት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ የሦስተኛውን ክፍል የጄኔራል ኤሌናን ጦር ጨምሮ ተዋግቶ በመጨረሻ የጦር አዛዡ ጄኔራል አሪሞንዲ እዚያው እጦርነቱ ላይ ሞቶ ተገኘ፡፡ ከዚህም በኋላ በመጨረሻ ያለው የኢጣሊያ ጦር በተለይ ማርያም ሸዊቶ ከሚባለው ስፍራ ላይ ተጋጥሞ ከቀድሞው የበለጠ ጦርነት ተደረገ፡፡ ይልቁንም የመጨረሻው ድል የሚፈጸምበት በመሆኑ የሁለቱም የጦር ሠራዊት ተደባልቆ በጨበጣ በሚዋጉበት ጊዜ፣ በጨበጣ በሚደረገው ዘመቻ ከኢጣሊያኖች ይልቅ ኢትዮጵያውያን በጎራዴ አነዛዘር የቀለጠፉ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ኢጣሊያኖች ተስፋ በቆረጠ ኃይል እስከ አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ በጉብዝና ሲዋጉ በመጨረሻ አዛዣቸው ጄኔራል ዳቦርሚዳ በጥይት ደረቱን ተመቶ ወድቆ ባንዲት ጠብታ ውሃ ማነው አፌን የሚያርሰኝ እያለ እንደ ተኮነነው ነዌ ሲጮኽ ጥቂት ቆይቶ ሞተ፡፡

«ጣልያን ገጠመ ከዳኛው ሙግት
አግቦ አስመስለው በሠራው ጥይት
አሁን ማን አለ በዚህ ዓለም፣
ጣልያን አስደንጋጭ ቀን ሲጨልም
ግብሩ ሰፊ ነው ጠጁ ባሕር
የዳኛው ጌታ ያበሻ ባሕር»
ተብሎም ስለዓድዋ ድል ስንኞች ታሰሩለት፡፡
የታሪክ ጸሐፊው ቤርክሌይ ስለ ዓድዋ ዐውደ ውጊያ የጻፈውን ጳውሎስ ኞኞ «ዐጤ ምኒልክ» ብሎ ባሳተመው መጽሐፉ እንደሚከተለው ገልጾታል፡፡

«ሃያ ሺሕ ያህል ወታደሮች ያሉበት የአውሮጳ ጦር በአፍሪቃ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸነፈ፡፡ በእኔ እምነት መሠረት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደ ዓድዋው ያለ ጦርነት የለም፡፡ በእልቂቱ በኩል 25,000 ሰዎች በአንድ ቀን ጀምበር የሞቱበትና የቆሰሉበት ነው፡፡ ፖለቲካና ታሪክ አበቃ፡፡ . . . አበሾች አደገኛ ሕዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተጽፎላቸዋል፡፡ የእኛ ዓለም ገና ቶር እና ኦዲዮን በሚባሉ አማልክት ሲያመልክ በነበረበት ጊዜ አበሾች የክርስትናን ሃይማኖት የተቀበሉ ናቸው፡፡»

የዓድዋውን ጦርነት ከመሩት የጦር አዛዦች መካከል እቴጌ ጣይቱ፣ ራስ መኰንን፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ራስ አሉላ፣ ራስ አባተ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ ይገኙበታል፡፡ የዓድዋ ጦርነት ሲነሳ ሁሌም የሚነሳው ባሻዬ አውአሎም ሐረጎት ነው፡፡ በስለላ ሙያው ተጠቅሞ የኢጣሊያን የጦር እቅድ በማሳከር አኩሪ ተግባር አከናውኗል፡፡ የባዕዳኑ አገልጋይ የነበረው አውዓሎም በቁጭት በመነሳሳትና በብላታ ገብረእግዚአብሔር ጊላ አማካይነት ከራስ መንገሻ ዮሐንስ ጋር ይገናኛል፡፡

እንደ ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ ጽሑፍ ራስ መንገሻም ከአፄ ምኒልክና ከእቴጌ ጣይቱ ጋር ይገናኙና የጦርነቱ ጊዜ ሲቃረብ የተሳከረውን እቅድ ለዤኔራል ባራቲየሪ እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ አውዓሎምና ብላታ ገብረ እግዚአብሔር ከኢጣሊያውያን ተለይተው ወደ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ገብተው ጦርነቱ ሲፋፋም ከኢጣሊያ መኰንኖች አንዱ ነገሩን ተገንዝቦ «አውዓሎም አውዓሎም» እያለ ሲጣራ አውዓሎም ሰምቶ፣ «ዝወአልካዮ አያውዕለኒ» (ከዋልክበት አያውለኝ) ብሎ አፌዘበት ይባላል፡፡
ኪነ ጥበብ
የዓድዋ ድልን አስመልክቶ በተለያዩ የጥበብ ሰዎች የተሠሩ ኪነጥበብ ተኮር ሥራዎች በፊልም፣ በተውኔት፣ በሥነ ሥዕል፣ በሥነ ግጥም፣ በቅኔ ወዘተ. የቀረቡት በርካታ ናቸው፡፡ ከ15 ዓመታት በፊት ታዋቂው የፊልም ዳይሬክተር ኘሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ «ዓድዋ» በሚል መጠሪያ የደረሰው ፊልም በበርካታ ታሪካዊ ፎቶግራፎች የታጀበ ነበር፡፡ በተውኔት ዘርፍ ጸሐፌ ተውኔትና ባለቅኔው ነፍስ ኄር ጸጋዬ ገብረመድኅን «ዓድዋ» ከተሰኘውና በ1964 ዓ.ም. ከደረሰው ግጥም ሌላ አሜሪካ ውስጥ ለእይታ የበቃው «ምኒልክ» ተውኔት ዓድዋን ያጎላበት ነበር፡፡ አዲስ አበባ ከተማ 100ኛ ዓመት ኢዮቤልዩዋን በ1979 ዓ.ም. ስታከብር ታዋቂው የቴአትር ዳይሬክተር አባተ መኩሪያ በአጋጣሚው የዓድዋውን ዘመቻ ክተት የሚያሳይ ትርኢት ‹‹ክተት ወደ ዓድዋ ዘመቻ›› በሚል ርእስ አሳይቶ ነበር፡፡ ይኸው ታዋቂ አርቲስቶችን ጨምሮ 4000 ሰዎች የተሳተፉበት ትርኢት በምስል ተቀርፆ በየጊዜው በቴሌቪዥን መስኮት ከመታየት አልተቋረጠምም፡፡ የደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት ካለፉ በኋላ የታተመው «ዓድዋ» ተውኔታቸውም ይጠቀሳል፡፡ የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የ‹‹ጥቁር ሰው›› ዓድዋ ተኮር ቅንቀናውም የቅርብ ዘመን ሥራ ነው፡፡

«ዋ! . . . ያቺ ዓድዋ» የጸጋዬ ገብረመድኅን «እሳት ወይ አበባ» ከተሰኘው የሥነ ግጥም መድበሉ ውስጥ የሚገኝ ስለ ዓድዋ የዘከረበት ነው፡፡ ከፊሉ እነሆ፡፡
. . . . ዋ!
ዓድዋ የዘር ዐፅመ ርስትዋ#
የደም ትቢያ መቀነትዋ
በሞት ከባርነት ሥርየት
በደም ለነፃነት ስለት
አበው የተሰውብሽ ለት፤ . . .
ሲያስተጋባ ከበሮዋ
ሲያስገመግም ዳኘው መድፍዋ
ያባ መቻል ያባ ዳኘው
ያባ ነፍሶ ያባ ቃኘው
ያባ በለው በለው ሲለው
በለው – በለው – በለው!
ዋ! . . . ዓድዋ . . .
ሥነ ሥዕልን በተመለከተ ድሉን የሚያሳዩ በተለያዩ ሠዓልያን የተሣሉ ባህላዊና ዘመናዊ ሥዕሎች የመኖራቸውን ያህል ኢጣሊያናውያንም የምኒልክን ታላቅነትና ድል አድራጊነት፣ የክሪስፒን ተሸናፊነትና ውድቀት የሚያሳይ የካርቱን ሥዕል አሰራጭተዋል፡፡ ሥዕሉ በ«ለ ፐቲት ጆርናል» የታተመ ሲሆን፣ ምኒልክ ክርስፒን በታላቅ ዱላ ሲጎሽሙትና ሲጥሉት ያሳያል፡፡ የዓድዋ ጦርነት ድልን በሥዕል በመግለጽ በኩል የቤተ ክርስቲያን ሠዓሊዎች ዓይነተኛ ሚና እንደነበራቸው ይገለጻል፡፡ ‹‹Ethiopian Paintings on Adwa›› በሚል ርእስ ጥናት የሠሩት በሙኒክ አትኖሎጂካል ሙዚየም የኢትዮጵያ ክፍል ኃላፊ የነበሩትና በቅርቡ ላበረከቱት ሁለገብ አስተዋጽኦ ከጀርመንም ሆነ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሽልማትና ዕውቅና ያገኙት አቶ ግርማ ፍሥሐ፣ ትውፊታዊ ሠዓልያኑ የዓድዋውን ድል በሥዕላቸው የዘከሩበት መንገድ ለኢትዮጵያ ባህላዊ አሣሣል ዕድገትን አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ፡፡

አንዳንዶቹ ሥዕሎች የዐፄ ምኒልክ አማካሪ በነበሩት አልፍሬድ ኢልግ ስብስብ ውስጥ በስዊዘርላንድ ሲገኙ፣ የሆልትዝ ስብስብ በበርሊንና የሆፍማን ስብስብ በዋሽንግተን ይገኛሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1905 አካባቢ የተሣሉት ከነዚህ ሥዕሎች መካከል የአለቃ ኤሊያስ፣ የአለቃ ኅሩይና የፍሬ ሕይወት ይገኙበታል፡፡ በሥዕሉ ጐልተው ከሚታዩት ከጠቅላይ አዝማቹ ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ በተጨማሪ አዝማቾች፣ መካከል ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ራስ መንገሻ፣ ራስ አሉላ፣  ራስ አባተ፣ ደጃዝማች ባልቻ ይጠቀሳሉ፡፡ ከአዝማሪዎች መካከልም አዝማሪ ፃዲቄ እየሸለለችና እየፎከረች ስታዋጋ የሚያሳይ ሥዕልም የዘመኑ ትሩፋት ነው፡፡

አዝማሪዎች ለኢትዮጵያ ሠራዊት ይሰጡት የነበረው ወኔ ቀስቃሽ አዝመራ ጉልህ ነበር፡፡ ስለነዚያ አዝማሪዎች ቤርክሌይ ከጉዞው ጋር አያይዞ የጻፈው የሚጠቀስ ነው፡፡ «. . . በሠራዊቱ መሀል አዝማሪዎችም አብረው ይዘምታሉ፡፡ በዚያ ሁሉ ሁካታ አዝማሪዎቹ ዘማቹን እያጫወቱ ይሄዳሉ፡፡ አብሮአቸው የሚጓዘው ሠራዊትም ለአዝማሪዎቹ ግጥም ይነግሩዋቸዋል፡፡ አዝማሪዎቹ የደከመውን በግጥም እያበረታቱ ይጓዛሉ»
‘ወንድሜ ራበህ ወይ? ወንድሜ ጠማህ ወይ
አዎን የናቴ ልጅ እርቦህ ጠምቶሃል
ታዲያ የናቴ ልጅ አዳኝ ወፍ አይደለህም ወይ?
ግፋ ብረር ወደፊትህ ሂደህ ጠላትህን አትበላም ወይ?
ግፋ ወደፊት ከበዓሉ ቦታ ፈጥነህ ድረስ
የምታርደውን ሥጋ የማቆራርጥልህ እኔ ነኝ
ግፋ የናቴ ልጅ ውሃ ጠምቶሃል
ጠጅ ብታጣ ደሜን እንድትጠጣ እሰጥሃለሁ’


ቅዳሜ የካቲት 22 ቀን 1888 ዓ.ም. ሌሊት ለእሑድ 23 አጥቢያ ወታደሩ እየሸለለ አዝማሪዎችም ማዘመር ጀመሩ፡፡

«ኧረ ጉዱ በዛ ኧረ ጉዱ በዛ
በጀልባ ተሻግሮ አበሻን ሊገዛ» ይሉ ነበር፡፡
ለጦር አዝማቾችም ማንቂያም ተገጥሟል፡፡
‹‹ክፉ አረም በቀለ በምጥዋ ቆላ
አሁን ሳይበረክት አርመው አሉላ፡፡
እነዚያ ጣሊያኖች ሙግት አይገባቸው
አሉላ አነጣጥረህ ቶሎ አወራርዳቸው፡፡
ዳኛው ወዴት ሄዷል እስኪ ወጥተህ እይ
አክሱም መንገሻዬ እስኪያዝ ነወይ፡፡
ዓድዋ ላይ ጣሊያኖች የዘፈኑለት
ምኒልክ ጎራዴህ ወረደ ባንገት፡፡››

የዓድዋ ጦርነት የተካሄደበት ዕለት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የበዓላት ትውፊት መሠረት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቀን ነው፡፡ ከቀደመው ጊዜ አንስቶ እስካሁን «ጠባቂ ቅዱስ» (ዘ ፓትረን ሴንት) ተብሎ ይታወቃል፡፡ እስከነ ዝማሬውም
«የዓድዋ አርበኛ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ከምኒልክ ጋር አብሮ ሲቀድስ፤
ምኒልክ በጦሩ ጊዮርጊስ በፈረሱ
ጣልያንን ድል አደረጉ ደም እያፈሰሱ» እየተባለ እስካሁን ይዘመራል፡፡

የዓይን ምስክር
በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የነበሩት ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም በዓድዋው የጦር ግንባር በመሰለፍ ያዩትን በሕይወት ታሪካቸው ጽፈው አቆይተውልናል፡፡
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ባሉት ሳምንታት የአካባቢው እረኞች ሲጫወቱ ደበሎ እየሰቀሉ አዋጅ ይናገሩ እንደነበር አዋጁንም ጠቅሰው ለዘመናችን አድርሰውልናል፡፡  «እሽ ስማ ብለውሃል መስማሚያ አይንሣህ
«ያድባርን ያውጋርን ጠላት…
«ሐማሴንን ለራስ አሉላ፣ አጋሜን ተምቤንን ለራስ ስብሐት፣ እንደርታን ዋጀራትን ለደጃዝማች ሐጎስ፣ እንዳመኾኒ ሰለሞንን ለፊታውራሪ ተክሌ፣
«ዋድላን ደላንታን ለፊውታራሪ ገበየሁ፣ ሰጥቻለሁ ብለውሃል! ይበጅ ያድርግ፤
«በየካቲት ጣጣችን ክትት
«በመጋቢት እቤታችን ግብት
«በሚያዛሳ ያገግም የከሳ
ይበጅ ያድርግ…» እያሉ ይተነባሉ፡፡
የሰው ብዛት እንደ ጎርፍ ሆነ፡፡ እግረኞችም በቅሎኞችም ተደባልቀን እንርመሰመሳለን፡፡ ፈረሰኞች በጎን እያለፉን ይቀድማሉ፡፡ ይሮጣሉ! እንደተቻለን እንሽቀዳደማለን፡፡
ጠመንጃ ሲንጣጣ ሰማን፣ መድፍ ወዲያው ያጓራ ጀመር፡፡ ተኩሱ እያደር እየባሰበት ተቃረበን፣ ዐረሮቹ ማፏጨት ጀመሩ፡፡ የቆሰሉ ሰዎች ተቀምጠው አገኘን፡፡ አያ ታደግ እጁን ተመትቶ ከመንገዱ ዳር ከዛፍ ሥር ተቀምጧል፡፡ ገና በሩቁ አይቶን ተጣራ፣ ቁስሉን በመቀነቱ አሰርንለት፡፡ ጥለነው እንዳንሄድ ለመነን፣ ፈይሣ ጠመንጃ የለውም፤ የቁስለኛውን ጠመንጃ ተሸከመና እዚያው ቀረ፡፡ እኔ ዝም ብዬ ወደ ግምባር አለፍኩ፡፡ የማውቀውን ሰው አንድም አላጋጠመኝም፡፡ ተኩስ ስለበዛ መሮጥ የማይቻል ሆነ፡፡ የሰውም ብዛት እንደልብ አያስኬድም፡፡

ደጃዝማች ማናዬ እና ልጅ አስፋው (ልጃቸው) ሁለቱም ቆስለው ድንጋይ ተንተርሰው ተጋድመው አገኘኋቸው፡፡ ልጅ አስፋው (በኋላ ፊታውራሪ አስፋው) አወቀኝና ጠቀሰኝ፡፡ ዝም ብዬው እንዳላየ ሰው ወደ ግምባር ሮጥኩ፡፡ ጦራችን ተደባልቋል፡፡ ሰውና ሰው አይተዋወቅም፡፡ ሴቶች ገምቦ ውሃ እያዘሉ፣ በበቅሎቻቸው እንደተቀመጡ፣ ለቁስለኞች ውሃ ያቀርባሉ፡፡ ሲነጋገሩ ሰማኋቸው፡፡ «ኧረ በጣይቱ ሞት» ይላሉ፡፡ እቴጌ የላኳቸው ይሆናሉ እያልኩ አሰብኩ፡፡
ነጋሪቱ ከግምባርም፣ ከጀርባም፣ ከቀኝም ከግራም ይጎሸማል፡፡ የተማረኩ ጣልያኖችን አየሁ፡፡ ወዲያው ምርኮኞቹ በዙ፣ አንዳንዶቹ ወታደሮች፣ ይበልጡን ጣልያኖችን እየነዱ መጡ፡፡ በኋላ የምርኮኞች ብዛት ለዐይን የሚያሰለች ሆነ፤ ድል ማድረጋችንን አወቅሁ፡፡ ጣልያኖች መዋጋታቸውን ትተው ማርኩን እያሉ ይለምናሉ፡፡ እንደዚህ የአድዋ ጦርነት ዕለት አንድ ጥይት እንኳ ሳልተኩስ ጦርነቱ አለቀ፡፡
ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ከድል በኋላ የጣልያኖች ሰፈር በኢትዮጵያውያን ቁጥጥር ሥር ሲወድቅ ዘማቹ ንብረቱን መቃራመቱ ያስታውሳሉ፡፡ ከጣሊያን ዕቃዎች ትኩረታቸውን የሳበው ሰነዶቹ ነበሩ፡፡ እንዲህም ይላሉ:-
ከወረቀቶቹ መካከል ሥዕል የተሳለባቸውን አየሁና «ትላልቆቹን እየመረጥኩ ሰበሰብኳቸው፡፡ በቀለም (በቀይ፣ በሰማያዊ፣ በሃምራዊና በቢጫ፣ በቅጠልማ፣ በአረንጓዴ) የተሣሉ ናቸው፡፡ ባንደኛው ወረቀት ላይ የጃንሆይን መልክ አወቅሁት፡፡ በሌላው ላይ የራስ መኮንን መልክ አገኘሁት፤ ደግሞ የሴት መልክ አገኘሁ፤ ሴትቱ ባለሹሩባ ነች፤ ጥልፍ ቀሚስ ለብሳለች፤ ባንገቷ ላይ ማተብ፣ በማተቡ ላይ መስቀል፣ ቀለበቶች፣ ሌላም ጌጥ አድርጋለች፡፡ ኩታ ደርባለች፤ ቆንጆ ትመስላለች፤ ጥርሶቿ ከከንፈሮቹዋ ውጪ ብቅ ብለው ይታያሉ፡፡ ጃንሆይና እቴጌ ጥርሰ ገላጣዎች ናቸው እየተባለ ሲታሙ እሰማ ነበር፡፡ ከቶም በጉርምስነታቸው በገና ጫወታ ላይ የተገጠመባቸውን ሰምቼ ነበር፡፡
«ዘመዳዬ ዘመዳዬ
በሰማይ የጠደቀ በምድር ያስታውቃል
አቤቶ ምኒልክ ዘመዳዬ
ተከንፈሩ ተርፎ ጥርሱ ጣይ ይሞቃል
ዘመዳዬ አይክፋህ አብዬ
ዘመዳዬ ጨዋታ ነው ብዬ፡፡»
እየተባለ ተገጥሞባቸዋል ይላሉ፡፡ በመላ እቴጌ ሳይሆኑ አይቀሩም አልኩና የሴትዬዋን ሥዕል አነሣሁት፡፡ የሌሎችም ሰዎች መልክ ብዙ አገኘሁ፡፡ እኔ አላውቃቸውምና ትላልቆቹን ሥዕሎች ብቻ እየመረጥኩ ሰበሰብኳቸው፡፡ በወረቀት ጠቀለልኩና በገመድ አሰርኩና ሸክሜን አሳምሬ አሰናዳሁ፡፡ እንደዚህ ሳሰናዳ አንድ ወታደር ባጠገቤ ሲያልፍ አየኝና ጠየቀኝ፡፡
«ምን ያደርግልኝ ብለህ ይህን የሰይጣን ምስል ትሰበስባለህ? ይልቅ ስንት ደህና እቃ ሞልቶልህ የለም» አለኝ፡፡
«እጫወትበታለሁ ያምራል» አልኩት፡፡
«የልጅ ነገር» እያለ እያልጎመጎመ ትቶኝ ሄደ፡፡ ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ያገኟቸውን ፎቶግራፎች ለራስ መኰንን ቆይቶም ለአፄ ምኒልክ እንዳሳይዋቸው በትዝታቸው ውስጥ ተካቷል፡፡ የዓድዋውን ድል ውጤትም እንደሚከተለው ገልጸውታል፡፡
እንደዚህ ዓድዋ ላይ ያን ያህል ሰዎች ተላለቁና፣ ጣልያን የወሰደብንን አገር ሳናስለቅቅ ሄድን፡፡ ይህን ነገር በዚያን ጊዜ ልመለከተው አልቻልኩም ነበር፡፡ የድሉን ዋጋ ለመገመቻ የበቃ ዕውቀት አልነበረኝም፡፡ በአውሮፓ መማር ከጀመርኩ በኋላ እያስታወስኩት እንደ እሳት ያቃጥለኝ ጀመር፡፡
ራስ መኰንንና ዐፄ ምኒልክ በዘመናቸው የሠሩ ሥራ ሊደነቅላቸው የተገባ ነው፡፡ ነገር ግን፣ ስሕተታቸውን በኋላ እየገመትኩት መገረሜ አልቀረም፡፡ ይሁን እንጂ፣ የዚያን ጊዜ ዕውቀትና ኃይል በማነሱ ይቅርታ ሊደረግላቸው የተገባ ነው፡፡ እነሱ በደከሙበት ሥራ ተጠቅመናል፡፡ በስሕተታቸውም አደጋ ተቀብለንበታል፡፡ እኛም ደግሞ በተራችን እንደዚሁ ማድረጋችን አይቀርም፡፡
የኢጣልያንም መንግሥት የዚያን ጊዜ ዕወቀቱና ኃይሉ ትንሽ ነበር፡፡ ስለዚህ እሱም ያደረገው ስሕተት ከኛ የበለጠ ነው፡፡ ስለዚህ ድል ተመታ፡፡ ግን በኛ ስሕተት አገር በእጁ እንደሆነ ስለቀረ፣ 50 ዓመት ያህል ቆይቶ ተሰናድቶ አጠቃን፣ መንግሥቶች ምንጊዜም ፖለቲካቸውን ማሰናዳታቸውን አይተውም ያንኑ ይተማመኑታል፡፡ ነገር ግን፣ ፖለቲካ ለጊዜው ተፈፃሚ መስሎ ቢታይም የመጨረሻውን ፍጻሜ ከፈጣሪ በቀር ማንም ሰው ሊያውቀው አይችልም፡፡ በዓድዋው ዘመቻ የሴቶች ተሳትፎ በወሳኝነት ይታወቃል፡፡ ከእቴጌ ጣይቱ አንስቶ እስከ ታች ድረስ የነበሩት አገልግሎታቸው ለድሉ ስኬት ያስጠቅሳቸዋል፡፡ ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርይት በነበሩበት ዐውደ ግንባር የታዘቡትን እንዲህ ጽፈውታል፡፡
ሴት አገልጋይ የተባለችው (የቤት ውልድ ነች ወለተ አማኔል የእንኮዬ ወለተ ማርያም ልጅ ከኛው ጋር ያደገች ነች) ከዘመቻው ላይ በጣም አገለገለች፤ ከቶ እሷ ባትኖር እንዴት እሆን ኖሯል፡፡ እያልኩ ዘወትር ሳስበው ያስደንቀኛል፡፡ እቃ ተሸክማ ስትሄድ ትውላለች፡፡ ከሰፈርን በኋላ ውሃ ቀድታ፣ እንጨት ለቅማ፣ ቂጣ ጋግራ፣ ወጥ ሰርታ ታበላናለች፡፡ ወዲያው እንደዚሁ ለማታ ታሰናዳለች፡፡ እንደዚህ የወለተ አማኔልን አገልግሎት እያሰብኩ ስደነቅ ደግሞ፣ በየሰፈሩ እንደዚህ እንደርሷ ስንት ሴቶች እንደሚያገለግሉ ይታሰበኛል፡፡
የሴቶቹን አገልግሎት ስገምት፣ ደግሞ የበቅሎቹ አገልግሎት ይታወሰኛል፡፡ በመጨረሻው ድምሩን ስገምተው፣ የዓድዋ ድል የተገኘው በሴቶች አገልጋዮችና በበቅሎች ብርታት መሆኑ ይታወቀኛል፡፡
ሁሉንም አያይዤ በደምሳሳነት ስመለከተው፣ የኢትዮጵያን መንግሥት ነፃነቱን ጠብቀው እዚህ አሁን አለንበት ኑሮ ላይ ያደረሱት፣ እነዚህ የዘመቻ ኃይሎች መሆናቸውን አልስተውም፡፡ ታዲያ ራሴ ለራሴ ጥያቄ ያቀርባል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የተባለው ተቋም ላገልጋዮቹ ውለታ መላሽ ሆኗል ወይ? የዚህን አመላለስ ለመስጠት ላስበው፣ እልቅ የሌለው መንገድ ይገጥመኛል፡፡ ሲሄዱ መኖር ይሆንብኛልና የማልዘልቀው እየሆነብኝ፣ እየተከዝኩ እተወዋለሁ፡፡ የዕለቱን፣ ያሁኑን ብቻ ለማሰብ ባጭሩ እታገዳለሁ፡፡ ይህ ሁሉ ድኩምነቴን ይመሰክራል፡፡

ከዓድዋ መልስ
የዓድዋ ጦርነት ካበቃ በኋላ ድል አድራጊው ሠራዊት ወደ የመጣበት አካባቢ ሲመለስ፣ ንጉሠ ነገሥቱ ሠራዊታቸውን ይዘው አዲስ አበባ የገቡት ግንቦት 15 ቀን 1888 ዓ.ም. ነበር፡፡ የመዲናው ሕዝብ ወንዱ በሆታ፣ ሴቱ በእልልታ አቀባበል ሲያደርግ፣ መድፎችም የደስታ ድምፅን አስተጋብተዋል፡፡
ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ ወልደ አረጋይ በእማኝነት እንደጻፉትም፣ የእንጦጦ ማርያምና የራጉኤል፣ የሥላሴና የዑራኤል እንደዚሁ የጊዮርጊስ ካህናት ልብሰ ተክህኗቸውን ለብሰው፣ በጃንሜዳ ተሰብስበው፣ «ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ፣ ተሐጺባበደመኢጣልያ» መሬቷ በኢጣልያ ደም ታጥባ ፋሲካ (ደስታ) አደረገች የሚለውን ጠቅሰው በንጉሠ ነገሥቱ ፊት አሸበሸቡ፡፡

አቶ ተክለጻድቅ መኩሪያ «ዐፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት» በተሰኘው መጽሐፋቸው የጐጃሙ ሊቅ መምህር ወልደ ሥላሴ እንደመልክ አድርገው ለአፄ ምኒልክ በግእዝ ደርሰው ያበረከቱት የደራሲውን ሊቅነት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካውንም የጦርነቱንም ታሪክ በትክክል የተከታተሉት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
‹‹ሰላም ለአፉከ ለፈጣሪ ዘየአኵቶ
ኢይትናገር ስላቀ ወኢይነብብ ከንቶ
ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ለኢትዮጵያ ማኅቶቶ
ኃልቀ ማንጀር  ወስዕነ ፍኖቶ
ዤኔራል ባራቲዬሪ ሶበ ገብዓ ደንገፀ ኡምቤርቶ፡፡››
(ሰላም ፈጣሪን ለሚያመሰግነው አፍህ
ስላቅ ለማይናገረው፣ ከንቱ ነገር ለማያወጋው አፍህ
ሰላም ይሁን፡፡
ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ለኢትዮጵያ ብርሃኗ
ማዦር ማለፊያ መንገድ አጥቶ አለቀ
ዤኔራል ባራቲዬሪ ወደርሱ በተመለሰ ጊዜ ኡምቤርቶ ደነገጠ፡፡)
ለዳግማዊ ምኒልክ ለእቴጌ ጣይቱ ለመሳፍንቱና ለመኳንንቱ የተደረሰው የአማርኛ ግጥም ብዙ ነው፡፡ የአብዛኞቹ ገጣሚዎች ስም አይታወቅም፡፡ ከነዚያ መካከል አቶ ተክለጻድቅ የሚከተለውን ይጠቅሳሉ፡፡

ዳግማዊ ምኒልክን ከትልቁ እስክንድር በክንፋማ ፈረስ ወደ ሰማይ ወጣ ከተባለው ጋር በማመሳሰል የተደረሰው ቅኔ እነሆ
«የዳኛው አሽከሮች እየተባባሉ
ብልት መቆራረጥ አንድነት ያውቃሉ
ዓድዋ ከከተማው ሥጋ ቆርጠው ጣሉ፡፡
የእስክንድር ፈረስ መቼ ተወለደ
የምኒልክ ፈረስ በክንፎቹ ሔደ»
ታላቁ ባለቅኔ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ዘመን ተሸጋሪ በሆነው ግጥማቸው የኢትዮጵያውያንን ኅብረ አንድነት እንዲህ አመሠጠሩት፡፡
‹‹አጥንቱን ልልቀመው መቃብር ቆፍሬ፣
ጎበናን ተሸዋ አሉላን ተትግሬ፣
ስመኝ አድሬያለሁ ትናንትና ዛሬ፣
ጎበናን ለጥይት አሉላን ለጭሬ።
ተሰበሰቡና ተማማሉ ማላ፣
አሉላ ተትግሬ ጎበና ተሸዋ፣
ጎበና ሴት ልጁን ሊያስተምር ፈረስ፣
አሉላ ሴት ልጁን ጥይት ሊያስተኩስ፣
አገሬ ተባብራ ታልረገጠች እርካብ
ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ የእንቧይ ካብ።››


++++++++++++++++====================++++++++++++++++++++++++

ዓድዋ ሲታሰብ – ተጻፈ በ ሔኖክ ያሬድ

http://theaksumpost.blogspot.com/2016/03/blog-post.html

የኢትዮጵያ ቱሪዝም አባት አቶ ሀብተሥላሴ ታፈሰ

የ13 ወር ፀጋ / Thirteen Months of Sunshine

ብዙዎቻችን ከላይ ያለውን ዓርማ ከፖስት ካርዶች ጀርባ ማየታችን እርግጠኛ ነኝ የዚህ መለያ ፈጣሪ ማን እንደሆኑ እናውቃለን?

‹እኔ ያደግሁት ውጭ አገር ነው፡፡ የትም ዓለም ላይ 13 ወር የለም፡፡ ፒራሚድ ሲታይ ግብፅ ነው፡፡ አይፈልታወር ሲታይ ፈረንሣይ ነው፡፡ የነፃነት ሐውልት ሲታይ አሜሪካ አለ፡፡ እኛ የምንታወቅበት የለንም ነበር፡፡ ሁሉ ነገር ከዘር፣ ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ሳላውቀው አንድ ወቅት ላይ የ13 ወር ደመወዝ ይሰጠን ብዬ ጠየቅሁ፡፡ ወዲያው ይህንን ሐሳብ ወደ ቱሪስት መሳቢያነት መቀየር እንደሚቻል አሰብኩ፡፡ ሌላው ሁሉ ከዘር ከሃይማኖት ጋር የሚያያዝ ነበር፡፡ ላሊበላን ባደርግ ኢትዮጵያ በሙሉ ክርስቲያን ባለመሆኑ ችግር ነበረበት፡፡ የአሥራ ሦስት ወር ፀሐይ ግን ከምንም ነገር ጋር አይገናኝም፡፡ ምንም የፖለቲካና የሃይማኖት ንክኪ የለውም፡፡ አሁን ከዚያ የበለጠ ከተገኘ ደግሞ ቶሎ መተካት ነው፡፡ ምንም ችግር የለበትም፡፡›› አቶ ሀብተሥላሴ ታፈሰ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ መሥራች፣ የአሥራ ሦስት ወራት ፀጋ (13 Months of Sunshine) በሚል መጠሪያ የአገሪቱ ቱሪዝም ለዘመናት ሲያስተዋውቅ የኖረውን መለያ የፈጠሩና በዘርፉ በርካታ ሥራዎችን ያስተዋወቁ፣ የተገበሩ የቱሪዝም አባት ናቸው፡፡ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ይህንን ውለታቸውን ቆጥሮ ዕውቅና በመስጠት ለመጀመሪያ ጊዜ ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡ ሰሞኑንም ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እጅ ለሁለተኛ ጊዜ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡  ሔኖክ ያሬድና ብርሃኑ ፈቃደ_ከሪፖርተር ጋዜጣ



 ሪፖርተር፡- በዘርፉ በጠቅላላው ኢትዮጵያን ለምን ያህል ጊዜ አገልግለዋል?
አቶ ሀብተሥላሴ፡- ከመጀመሪያው እ.ኤ.አ. ከ1954 ጀምሮ አገልግያለሁ፡፡ ያኔ ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣሁ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ እሠራ ነበር፡፡ ከዚያ በግድ ይህንን ሥራ [ቱሪዝምን] እንድሠራ አዘዙኝ፡፡ ገባሁበት፡፡ ከባድ ሥራ ነው፡፡ ያን ጊዜ ካሜራ ወደ ኢትዮጵያ አይገባም ነበር፡፡ ሲገባም ጉምሩክ ይይዘዋል፡፡ ፈቃድ ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ማውጣትም ያስፈልግ ነበር፡፡ በዚህ ሰበብ ሁለት ጊዜ ታስሬያለሁ፡፡ ፎቶግራፍ ለምን ታነሳለህ ብለው ነው ያሰሩኝ፡፡ ያን ጊዜ ፎቶግራፍ የሚያነሳ ሰው ሰላይ ተደርጐ ይታሰብ ስለነበር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በቱሪዝም ሙያዎ ኢትዮጵያን ምን ያህል ያውቋታል?
አቶ ሀብተሥላሴ፡- ያልደረስኩበት ቦታ የለም፡፡ በእግር፣ በፈረስ፣ በግመል፣ በሄሊኮፕተር፣ በአውሮፕላን ሁሉ ተዘዋውሬ ከ100 በላይ ሰው ያልረገጣቸው የኤርትራ ደሴቶችን አይቻለሁ፡፡ ትልቅ ሀብት ናቸው፡፡ ቢያውቁበት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መሰብሰብ ይችሉ ነበር፡፡ በጋምቤላ በኩል ጂካው ድረስ ሄጃለሁ፡፡ የደቡብ ሱዳን ጠረፍ ነው፡፡ በኤርትራ በኩል ቤንአመር ድረስ ወዳለው የጠረፍ ቦታ ደርሻለሁ፡፡ ቤንሻንጉልን በሙሉ እስከ ሱዳን ድረስ አዳርሻለሁ፡፡ መሥራት ካስፈለገ ማየት፣ ማወቅ ግድ ይሆናል፡፡ ካየን፣ ካወቅን በኋላ ማውራት ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት እርስዎ ብዙ ሠርተዋል፡፡ ከሠሯቸው መካከል አሁንም ድረስ የሚታወቀው ኢትዮጵያ የአሥራ ሦስት ወር ፀጋ የሚለው አገሪቱ መጠሪያ ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያ መለያ ለብዙ ጊዜ ያገለገለ ነው፡፡ አሁን መቀየር አለበት የሚሉ አሉ፡፡ ይቀየር ቢባል ምን ይሰማዎታል?
አቶ ሀብተሥላሴ፡- ሁልጊዜ አንድ ነገር ሲፈጠርና የሚበልጠው ሲገኝ ያንን ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ምክትል አፈንጉሥ ገብረ ወልድ ፎቅ ቤት ሠርተው ነበር፡፡ ያን ጊዜ በንጉሡ ዘመን የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ነበር፡፡ መንግሥቱ ንዋይ ደግሞ ጠንሳሽና የእኛም ዘመድ ነበር፡፡ ሰውየው ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ሠርተሃል ተብለው ታሰሩ፡፡ ይህ ከሆነማ አፍርሱት ሲሏቸው የለም አንተን ነው የምናፈርሰው ብለው ገደሏዋቸው፡፡ አሁን ደግሞ በተገላቢጦሽ ሰማይ ጠቀስ ፎቅ እንዲሠራ ነው የሚፈለገው፡፡

ሪፖርተር፡- የአሥራ ሦስት ወር የፀሐይ ፀጋን እንዴት መረጡት?
አቶ ሀብተሥላሴ፡- እኔ ያደግሁት ውጭ አገር ነው፡፡ የትም ዓለም ላይ 13 ወር የለም፡፡ ፒራሚድ ሲታይ ግብፅ ነው፡፡ አይፈልታወር ሲታይ ፈረንሣይ ነው፡፡ የነፃነት ሐውልት ሲታይ አሜሪካ አለ፡፡ እኛ የምንታወቅበት የለንም ነበር፡፡ ሁሉ ነገር ከዘር፣ ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ሳላውቀው አንድ ወቅት ላይ የ13 ወር ደመወዝ ይሰጠን ብዬ ጠየቅሁ፡፡ ወዲያው ይህንን ሐሳብ ወደ ቱሪስት መሳቢያነት መቀየር እንደሚቻል አሰብኩ፡፡ ሌላው ሁሉ ከዘር ከሃይማኖት ጋር የሚያያዝ ነበር፡፡ ላሊበላን ባደርግ ኢትዮጵያ በሙሉ ክርስቲያን ባለመሆኑ ችግር ነበረበት፡፡ የአሥራ ሦስት ወር ፀሐይ ግን ከምንም ነገር ጋር አይገናኝም፡፡ ምንም የፖለቲካና የሃይማኖት ንክኪ የለውም፡፡ አሁን ከዚያ የበለጠ ከተገኘ ደግሞ ቶሎ መተካት ነው፡፡ ምንም ችግር የለበትም፡፡
ሪፖርተር፡- ዛሬም ድረስ መሥራት የሚፈልጓቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡
አቶ ሀብተሥላሴ፡- መርዳት ነው የምፈልገው፡፡ መሥራት ያለባቸው የተመደቡት ሰዎች ናቸው፡፡ እነርሱን ለመርዳት ዝግጁ ነኝ፡፡ አምስት ያህል ፕሮጀክቶች አሉኝ፡፡ ፍልውኃን በአግባቡ አልተጠቀምንበትም፡፡ ወንዶገነትና ሶደሬ አካባቢ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ነገር ግን ከ3,000 በላይ ፍልውኃ በየቦታው አለን፡፡ ያ የማያልቅ፣ ከወርቅና ከከበረ ድንጋይ ሁሉ የበለጠ ሀብት ነው፡፡ ነገር ግን አልተሠራበትም፡፡ እኔጋ ጥናቱ አለ፡፡ ዩኔስኮ ውኃውን ጨምሮ ያገኘው ጉዳይ አለ፡፡ ጥናቱ በእጄ ስላለ ለመንግሥት እሰጣለሁ፡፡ ይሠሩበታል ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን ቱሪስቶች ያሉት እዚሁ ከጐናችን ነው፡፡ ዱባይ፣ ኤምሬቶች አሉ፡፡ ድሮ ዓረብ ድሃ ነው፡፡ አሁን ዓለምን የያዙ እነሱ ናቸው፡፡ ፍልውኃ አረንጓዴያማ መስክ ይወዳሉና አቅሙ ላላቸው ባለሀብቶች መስጠት ከተቻለ ሰው ይመጣል፡፡ ከዱባይ አዲስ አበባ የሦስት ሰዓት በረራ ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ሰው ይመጣል ብሎ መጠበቅ ከባድ እየሆነ ነው፡፡ ቀውስ ላይ ናቸው፡፡ የቅርብ አገሮች ግን መምጣት የሚችሉበት አቅም አላቸው፡፡ በግብፅ ለሁለት ዓመት ቆይቻለሁ፡፡ አባቴ አምባሳደር ነበሩና በዚያ ኖረናል፡፡ በጣም ቃጠሎ ነው፣ ሲበዛ ሞቃት ነው፡፡ በክረምት ብቻ ወደ አሌክሳንድርያ እንሄድ ነበር፡፡ አሁንም በጣም ሞቃት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ የአሥራ ሦስት ወር ፀጋ ብለው ነበር ብዙ ፀጋ አለን ማለት ነው?
አቶ ሀብተሥላሴ፡- ደመወዝ የለውማ፡፡ የአሥራ ሦስት ወር ደመወዝ አይከፈልበትም፡፡
ሪፖርተር፡- እንደ ኬንያ ያሉት አገሮች ግን የዱር እንስሳት ሀብት ብቻ እያላቸው ነገር ግን ብዙ የተጠቀሙበት ሁኔታ አለ፤
አቶ ሀብተሥላሴ፡- እነሱ ስላሠሩ ነዋ፡፡ እኛ አንሠራም፡፡ አንዱ ሲሠራ አሥሩ ወደኋላ ይጐትታል፡፡ ምቀኝነት አለ፡፡ የሐበሻ ፀባይ አብሮ መሥራት ስለሌለው መድረስ ያለብን ቦታ አልደረስንም፡፡
ሪፖርተር፡- አየር በዕቃ ሞልተው ለመሸጥ የሞከሩበት ጊዜ እንደነበር ይነገራልና ስለእርሱ ቢነግሩን?
አቶ ሀብተሥላሴ፡- የኢትዮጵያ አየር የትም ዓለም ላይ አይገኝም፡፡ አንድ ጊዜ ንጉሡ ጋር ገባሁና አየር ይሸጣል አልኳቸው፡፡ ገንዘብ ሚኒስትሩ መጡና ምን ይለፈልፋል ብለው አጣጣሉኝ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ እ.ኤ.አ. በ1970 በኦሳካ ኤግዚቢሽን ነበርና ወደ ቶኪዮ ዞር ዞር ብዬ ለማየት ሄድኩ፡፡ አንድ ቦታ ላይ የፊጂ ተራሮች የሚል ጽሑፍ ያለበት ቆርቆሮ አየሁ፡፡ ሳነሳው ባዶ ነው፡፡ ውስጡ ያለው የፊጂ አየር ብቻ ነው፡፡ ሰው ገዝቶ በአፍንጫው መማግ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ገዛሁና ወደ ንጉሡ አመጣሁት፡፡ ስጦታ አምጥቼሎታለሁ አልኩና ሰጠኋቸው፡፡ አንስተው ሲያዩ ምንም የሌለው መስሏቸው ምን ትቀልዳለህ አሉኝ፡፡ አየር ይሸጣል ያልኩዎትኮ ይኼ ነው፤ ገዝቼ መጣሁ አልኳቸው፡፡ ገንዘብ ሚኒስትሩን ጠሩና ታስታውሳለህ ያልከውን ይኸውልህ አየር ይሸጣል አሏቸው፡፡ ይኼንን አሁንም ማድረግ ይቻላል፡፡ አየር በዕቃ ሞልቶ እንዲማግ ማድረግና መሸጥ ይቻላል፡፡ ውኃ በፕላስቲክ እየተሸጠ እኮ ነው፡፡ ሰው ግን አያምንም፣ አይቀበልም፡፡ አገሪቱን ያጠቃት በምቀኝነት፣ በዘር፣ በሃይማኖት መከፋፈላችን ነው፡፡ አንድ ሆነን ካልሠራን ከባድ ነው፡፡ አሁን ብዙ ለውጥ መጥቷል፡፡ ከሞት የተመለስኩ ያህል የሚሰማኝ ጊዜ አለ፡፡ ሴቱ ሁሉ እንደ ልቡ ነው፡፡ ወደ ዱባይ ወደ መሳሰሉት አገሮች ሲሄዱ፣ ሲሠሩ የሚታዩ ቆነጃጅቶች ብዙ አሉ፡፡ በእኛ ጊዜ እንዲህ አይታሰብም፡፡ ብዙ ለውጥ አለ፡፡ የሰው አስተሳሰብ ተቀይሯል፡፡
ሪፖርተር፡- አንድ ኒውዝላንዳዊ ሚሊየነር ኢትዮጵያን በሄሊኮፕተር ጐብኝቶ መደነቁን ሲናገሩ ነበርና ስለእርሱ ቢገልጹልን?
አቶ ሀብተሥላሴ፡- ፓይለቱ የሰውየው ልጅ ባል ነው፡፡ ሰውየው ደግሞ ባለሄሊኮፕተር ነው፡፡ የእርሱ አስጎብኚ ከእኔ ጋር የሚሠራ ነውና ተዟዙሮ አይቶ እኔን ማየት ፈለገና እራት ጋበዘኝ፡፡ ተኝታችኋል አለኝ፡፡ በሄሊኮፕተር እየተዘዋወርን ከ125 በላይ አገሮች አይተናል እንደ ኢትዮጵያ የሚሆን ግን አላየንም አለኝ፡፡ ሰውየው የምንም ፍላጎት የላቸውም፡፡ ለጥቅም ብለው ነው እንዳይባል አገራቸው ኤምባሲ እንኳ እዚህ የላትም፡፡ ሰውየው ደግሞ እጅግ ባለጠጋ ናቸው፡፡ ቢሊየነር በመሆናቸው ለጉብኝት ብቻ ነው የመጡት፡፡ ያዩትን አይተው ተኝታችኋል አሉኝ፡፡
ሪፖርተር፡- የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሽልማት ሲሰጥዎ፣ በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሽልማት ተጠራሁ ብለዋል፡፡ ለምንድን ነው ከዚህ በፊት ይህን ሁሉ ሠርተው ያልተሸለሙት?
አቶ ሀብተሥላሴ፡- ምቀኞች ስለሆንን፡፡ ሁሌም ሲጠሩኝ ለአንድ ወቀሳ ነው፡፡ ቤተክህነት ተጠርቼ በቴሌቪዥን ለምን እንዲህ ተናገርህ እባላለሁ፣ የአገር ውስጥ ገቢ ይጠሩኝና እወቀሳለሁ፡፡ ያን ጊዜ ከቀረጥ ነፃ ሱቅ ከፍተን ነበር፡፡ የእኛ ቢሮ ከመንግሥት ቢሮዎች ሁሉ ሀብታም የሚባለው ነበር፡፡ ያን ጊዜ ቱሪዝም በጀት 220 ሺሕ ብር ስለነበር በዚህ በጀት እንዴት አገርን ማሳደግ ይቻላል እያልሁ ከጃንሆይ ጋር እጨቃጨቅ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ቁልፉን ይዤ ሄድኩና ጃንሆይ ይኼንን መሥሪያ ቤት ለሒሳብ ሹም ይስጡት ደመወዝ ከመክፈል ውጪ ሌላ ሥራ መሥራት አልቻልኩም አልኳቸው፡፡ የዲውቱ ፍሪ ፈቃድ ስጡኝ ብዬ ጃንሆይን ጠየቅሁ፡፡ ኋላ ላይ ገንዘብ ሚኒስትሩ መጡና እኛ ኮንትሮባንድ መቆጣጠር አቅቶናል፣ ሀብተሥላሴ ደግሞ አናታችን ላይ ኮንትሮባንድ ለመፍጠር ይፈልጋል አሉኝ፡፡ ንጉሡም ሥራህ መቆጣጠር ነው እንጂ ሥራ አይሥራ ነው የምትለው ወይስ መቆጣጠር አልችልም ነውብለው ጠየቋቸውና ተፈቀደልኝ፡፡
ሥራው ሊጀመር ሲል ደግሞ ገንዘብ ስለጠፋ የአባቴን ካርታ ወስጄ ለአንድ እብድ ሰጠሁና 5,000 ዶላር ተበደርኩ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ማግኘት ተቻለን፡፡ በአንድ ወቅት ከመላው ኢትዮጵያ የእኛ መሥሪያ ቤት ነበር ሀብታም የነበረው፡፡ አንድ ሚኒስትር ሲሾም በጊዜው እንዲነግድ አይፈቀድለትም ነበር፡፡ ለእኛ ተፈቅዶ ነበርና ብዙ ገንዘብ አስገብተናል፡፡ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሕንፃ ተሠርቶ ሥራ ሲጀምር የእኛ መኪኖች ነበሩ የሚያገለግሉት፡፡ 46 ያህል ነበሩን፡፡ እኔ እንደ ሾፌር፣ እንደ አስጐብኚ፣ እንደ ፎቶግራፍ አንሺ እየሆንኩ ሠርቻለሁ፡፡ በኋላ ምቀኛ በዛና የዲውቲ ፍሪ ገንዘብ ወደ መንግሥት ይግባ አሉ፡፡ ያ አሠራር ዛሬ ቆይቶ ቢሆን ኖሮ አሥር ሚሊዮን ሰዎች በተሰማሩበት ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በጊዜው ሴቶችን ፎቶግራፍ ያነሱ ነበርና ከንጉሡ ዘንድ የገጠመዎት ጉዳይ አለ ይባላል፤
አቶ ሀብተሥላሴ፡- አዎ፡፡ አንዲት የጋምቤላ ሴት ፎቶግራፍ አንስቼ ነበር፡፡ ሴትየዋ ጡቷ ቆንጆ ነበርና አንስቼ ፖስተሩ ከመታተሙ በፊት ናሙናውን ለንጉሡ አስገብቼ ጠረጴዛ ላይ እደረድር ነበር፡፡ ንጉሡ መጥተው ሲያዩ ይኼ ምንድን ነው አሉና ጠየቁኝ፣ አይ ቱሪስቶች እንዲህ ማየት ይወዳሉ ስላቸው፣ አንተም ትወዳለህ ይባላል አሉኝ፡፡ በኋላ ታትሞ ሲወጣ ሳንሱር ይደረግ ነበር ራቁት እያሳየ ነው ብለው ንጉሡ ጋር መልሰው ይዘው መጡ፡፡ ንጉሡም አይተናል አሉና መለሷቸው፡፡ ከዚያ በኋላ የቱንም ነገር ከመሥራቴ በፊት ቀድሜ ለንጉሡ ስለማሳይ አይተናል እያሉ ሚኒስትሮችን ይመልሷቸው ነበር፡፡ ብዙ መሥራት አንወድም፡፡ ስንሠራ ደግሞ ምቀኛው ወደኋላ የሚጐትት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እሰጣለሁ ካሏቸው ፕሮጀክቶች አንዱ አንድ ብር ቢያንስ በአንድ ዶላር መመንዘር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ ይኼ አስማት አይደለም ሲሉም ሰምተናልና እንዴት ነው ይኼ የሚሆነው?
አቶ ሀብተሥላሴ፡- ይኼ አስማት አይደለም፡፡ እንዴት እንደሆን የምንነግረው ግን ለሚኒስትሩ ነው፡፡ እሳቸው ከተስማሙ በኋላ የእሳቸው ፕሮጀክት ይሁን፡፡ አሁን መናገሩ ጊዜው አይደለም፡፡ 
+++===+++===+++====+++====+++===+++===+++===+++===+++===+++
 ምንጭ፡-https://www.ethiopianreporter.com/የቱሪዝም አባት አቶ ሀብተሥላሴ ታፈሰ የሚታወሱበት የ13 ወር ፀጋ መለያ
ለተጨማሪ መረጃ፡--
whos-who-meet-habteselassie-tafese-who-originated-the-land-of-13-months-of-sunshine-idea_PART-1
whos-who-meet-habteselassie-tafese-who-originated-the-land-of-13-months-of-sunshine-idea_PART-2



በአሥራ ሦስት ወር ጸጋ በ”Thirteen Months of Sunshine” የሚታወቁት "የኢትዮጵያ ቱሪዝም አባት" አቶ ሀብተሥላሴ ታፈሰ በ90 ዓመታቸው አረፈዋል፡፡
የተወለዱት በ1924 ዓም አካባቢ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ግንኙነት አገኙ፡፡ ሥራ የጀመሩት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የፕሬስና መረጃ ክፍል ኃላፊ ሆነው ነበር፡፡ አቶ ሀብተ ሥላሴ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትን እኤአ በ1961 ከመመሥረታቸው በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ቱሪስቶች እንደ ውጭ ሀገር እንግዶች ብቻ ይታዩ ነበር፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸው ከግምት አልገባም፡፡
እኚህ ሰው “የኢትዮጵያ ቱሪዝም አባት” ተብለው ይጠራሉ፡፡ የቱሪዝም ሥራ በአገራችን እንዲጀምር ከውጭ አገር ከቀሰሙት ልምድ በመነሳት በ1950ዎቹ መጀመሪያ ለአጼ ኃይለሥላሴ ሃሳብ ያቀረቡና ባገኙት ፈቃድም ለመጀመሪያ ጊዜ መሥሪያ ቤቱን አቋቁመው ሥራ ያስጀመሩ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡
የውጭ ሀገራት ዜጐች ሀገራችንን እንዲጐበኙ በተለያዩ አገራት እየተዘዋወሩ ቀስቅሰዋል፡፡ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የገበያ እድል ፈጥረዋል፡፡ ታሪካዊ ቦታዎችንና ባህላዊ አልባሳትን የለበሱ ኢትዮጵያውያን ፎቶዎች በፖስተርና በፖስት ካርድ በማሰራት አሁን ድረስ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው የቱሪስት መስህብ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡
በተለይም የአገራችን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ መለያ የሆነውን የ13 ወር የፀሐይ ብርሃን (13 months of sunshine) የሚለውን መርህ የፈጠሩና በሥራ ላይ ያዋሉ ናቸው፡፡ ዓለም ስለ ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲያውቅ፣ቱሪስቶችም ስለ ኢትዮጵያ በቂ መረጃ እንዲያገኙ፣ ዘመናዊ የቱሪዝም ሥራ እንዲያድግ ጠንክረው ሠርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅትን በማቋቋም ቱሪስቶች ባህላዊ መገለጫዎቻችንን እንደልብ እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡
እንዲሁም አሁን ያሉትን የሀገራችን የቱሪስት መስህብ የጉብኝት መስመሮች ማለትም፤ ወደ ጣና ሀይቅ፣ ጢስ አባይ፣ ጎንደር፣ ላሊበላ፣ አክሱምና የመሳሰሉት ትኩረት እንዲያገኙ ትልቅ ጥረት ካደረጉት መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡
ይህ ሥራቸው በንጉሡ ባለሟሎች ባለመወደዱ የውጭ አገር ቱሪስቶችን ለማስጐብኘት ወደ መርካቶ ሲወሰዱ “ገመናችንን ለዓለም ሊያሳይ ነው” ብለው ንጉሡ ዘንድ እስከመክሰስ ደርሰዋል፡፡ ከዚህ በባሰ የዘመኑ ሹማምንት የቱሪዝም መሥሪያ ቤቱን በጀት ስለከለከሉዋቸው በራሳቸው ገንዘብ እስከማስተዳደር፣ ቱሪስቶችንም በራሳቸው መኪና እስከመውሰድ የደረሱበት ጊዜ ነበር፡፡
ይህን ሁሉ መሰናከል በጥረታቸው አሳልፈው የቱሪዝም መሥሪያ ቤቱ በሁለት እግሩ እንዲቆም አብቅተዋል፡፡ እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሲነሳ የእሳቸው ስም አብሮ ይወሳል፡፡ አቶ ሀብተሥላሴ የሀገር ባለውለታ፣ ላመኑበት ነገር እስከመጨረሻው በቁርጠኛነት ጥረት የሚያደርጉ፤ በህይወታቸው ኢትዮጵያን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ማየት የሚመኙ ናቸው፡፡
አቶ ሀብተ ሥላሴ የኢትዮጵያ ቱሪስት ድርጅትን በመመሥረት፣ በመላ ሀገሪቱና በመላ ዓለም ዞረው በማስተዋወቅ፣ ሀገራዊ የወግና የባህል ዕቃዎች ገበያ እንዲፈጠር በማድረግ ተግተዋል፡፡ ፎቶግራፎችን ራሳቸው በማንሣትና ጃፓን ድረስ ልከው በማሳጠብ የመጀመሪያዎቹን የቱሪዝም ፖስተሮች አዘጋጅተዋል፡፡
በቅርስና ባህል ዘርፍ አቶ ሀብተስላሴ ታፈሰ የአመቱ የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ነበሩ።
የሦስት ልጆች አባት ነበሩ።
ነፍስ ይማር!




ዓርብ, ማርች 10, 2017

ባለቅኔው ደበበ ሰይፉ ከ1942 - 1992

ጠብቄሽ ነበረ
መንፈሴን አንጽቼ
ገላዬን አጥርቼ
አበባ አሳብቤ
አዱኛ ሰብስቤ
ጠብቄሽ ነበረ፤
ብትቀሪ ጊዜ፣
መንፈሴን አሳደፍኩ
ገላዬን አጎደፍኩ
አበባው ደረቀ
አዱኛው አለቀ፤
ብትቀሪ ጊዜ፣
የጣልኩብሽ ተስፋ
እኔን ይዞ ጠፋ፡፡
(ደበበ ሰይፉ፣ ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ፣ 1992)



በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ዓለም ውስጥ በሥነ-ግጥም ችሎታቸው አንቱ ተብለው ባለቅኔ ወደመባል ደረጃ ከደረሱ ልሒቃን /elites/ መካከል አንዱ ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውሰጥ ለረጅም ዓመታት ከማስተማሩም በላይ የኢትዮጵያን ቋንቋ በተለይም አማርኛን የሥነ-ጽሑፍና የመደበኛ ትምህርት ማካሄጃ ለማድረግ በነበረው እንቅስቃሴ ውስጥ ያበረከተው አስተዋፅኦ በእጅጉ ግዙፍ ነው። የኢትዮጵያን የሥነ-ጽሑፍ፣ የሥነ-ግጥም እና የቴአትር ጥበብን ታሪክ በማጥናትና በመመራመር ረገድ ለትውልድ አቆይቶት ያለፈው መረጃ ለዘላለም ስሙ እንዲነሳ ያደርገዋል። የአያሌ ታላላቅ ሰብዕናዎች ባለቤት የሆነውን ምሁር ዛሬ በጥቂቱ እናነሳሳዋለን። መምህሩን፣ ገጣሚውን፣ ፀሐፌ-ተውኔቱን፣ ተመራማሪውን ሰው ደበበ ሰይፉን!
ደበበ ሰይፉ ሐምሌ 5 ቀን 1942 ዓ.ም የተወለደባት እና ያደገባት ከተማ ይርጋለም ትባላለች። ይርጋለም በደቡብ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ጥንታዊ ከተሞች መካከል አንዷ ነች። ከአዋሳ ከተማ በአጭር ርቀት ውስጥ ያለችው ይርጋለም ሲዳማ ውስጥ ዝነኛ ከሆኑ ከተሞች መካከል ግንባር ቀደሟ ናት። ይርጋለም ጥንታዊት ናት። ከዚያም አልፎ ጥንት የደቡብ ኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና የልዩ ልዩ ህዝቦች መናሃርያ ነበረች። ይህች ከተማ በ1940ዎቹ፣ 50ዎቹ እና 60ዎቹ ውስጥ ከልዩ ልዩ የደቡብ ከተሞች ተማሪዎች እየመጡ የመካከለኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚከታተሉባት ማዕከል ሆና ቆይታለች። ይርጋለም ኅብረ ህዝብ ያለባት የኢትዮጵያ ምሳሌ ነች። እናም በዚህች ከተማ ውስጥ ተወልዶ ያደገው ደበበ ሰይፉ ለኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ሰፊ ብርሃን ሰጥቶ ያለፈ የኪነት ፀሐይ ነበር።

ደበበ ሰይፉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ በኮከበ ጽባሕ ት/ቤት ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ቀድሞ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ከሚታወቀውና በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት ሥነ-ጽሑፍን መማር ጀመረ። ከዚያም በ1965 ዓ.ም ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ማዕረግ ተመረቀ። ቀጥሎም በዚያው በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሥነ-ጽሑፍን ማስተማር ጀመረ።
እንደ ደበበ ሰይፉ ያሉ መምህራን በዚህ ትምህርት ክፍል ውስጥ መቀላቀል ሲጀምሩ ዲፓርትመንቱም እያደገና እየተስፋፋ የመጣበት ዘመን እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ምክንያቱም የጥናትና የምርምር ውጤቶች በስፋት መሠራት ጀመሩ።
ለምሳሌ ደበበ ሰይፉ የኢትዮጵያ የሥነ-ግጥም እና የሥነ-ጽሁፍ ታሪክን እና በዚህ ታሪክ ውስጥ ደግሞ ኪነታዊ አስተዋፅኦዋቸው ሰፊ የሆነውን ጐምቱ አበው ፀሐፊያንን ታሪክና የአፃፃፍ ቴክኒካቸውንም ጭምር እያጠና ማቅረብ ጀመረ። ያለፈው የጥበብ አሻራ ለመጪው ጥበብ የሚያቀብለውን መረጃ እየወሰደ ትውልድን በጥበብ ማስተሳሰር አንዱ ተግባሩ ነበር።
የአንዲት ሀገር ማንነት ተቀርጾ ከሚኖርባቸው ጉዳዮች ዋነኛው ሥነ-ጽሁፍ ነው። በሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ደግሞ ታሪክ አለ፣ ሥነ-ግጥም አለ፣ ቴአትር አለ፣ ፍልስፍና አለ፣ አስተሳሰብ አለ፣ ፖለቲካ አለ፣ ህዝብ አለ፣ ኧረ ብዙ ብዙ ነገሮች አሉት። ደበበ ሰይፉ ደግሞ እነዚህን የኢትዮጵያን የማንነት መገለጫዎች ከጥንታዊ ሰነዶች ውስጥ እየፈተሸ በማውጣት ትውልድ እንዲህ ነበር፣ እንዲህም ኖሯል፣ እንዲህም አስቧል …. እያለ የዘመን ርቀታችን እንዳያለያየን ከትውልዶች ጋር ያገናኘን ነበር። ደበበ በስነ-ጽሁፍ ውስጥ የትውልድ የመሸጋገሪያ ድልድይ ሆኖ አገልግሏል።
ደበበ ሰይፉ በቀላል አነጋገር ሐያሲ ነበር። ሐያሲ ታሪክ አዋቂ ነው። ያለፈውን ከአሁኑ ጋር እያነፃፀረ የሚያስረዳ፣ የሚተነትን ባለሙያ ነው። የሒስ ጥበብን ደግሞ እንደ ሙያ ከታደሉት ሰዎች መካከል ደበበ ሰይፉ አንዱ ነው። በኢትዮጵያ የዘመናዊ ሂስ ጥበብ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ሰው ቢኖር አንዱ ደበበ ሰይፉ ነው።
ደበበ ገጣሚ ነው። በአገጣጠም ችሎታው ውብ እና ማራኪነት የተነሳ ብዙዎች ባለቅኔው ደበበ ሰይፉ እያሉ ይጠሩታል። ይህ በስነ-ግጥም ዓለም ውስጥ የተሰጠው ፀጋ ከሌሎች ጉዳዮች ሁሉ ገዝፎ የሚነገርለትም ነው። ደበበ ሲነሳ ገጣሚነቱ አብሮ ብቅ የሚልለት የጥበብ ሰው ነው። እነዚህን የግጥም ትሩፋቶቹን በ1980 ዓ.ም የብርሐን ፍቅር በሚል ርዕስ ሰብስቦ አሳትሟቸዋል። በዚህች የብርሐን ፍቅር በተሰኘችው የሥነ-ግጥም ስብስቡ መፅሐፍ ውስጥ ቀደም ሲል በተማሪነት እና በአስተማሪነት ዘመኑ ሲፅፋቸው የነበሩትን ግጥሞች የምናገኝበት ድንቅ መፅሐፉ ነች።
ከዚህች መፅሐፉ በተጨማሪ በ1992 ዓ.ም በሜጋ አሳታሚ ድርጅት አማካይነት ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ በሚል ርዕስ ሁለተኛዋ የሥነ-ግጥም መፅሐፉ ለንባብ በቃች። ነገር ግን በዚህ ወቅት ደበበ በሕይወት የለም ነበር። ስራዎቹ ዘላለማዊ ናቸውና እርሱ በህይወት በሌለበት ወቅትም የትውልድ ሀሴት በመሆናቸው ይታተሙለታል። እናም ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ በምትሰኘው መፅሐፉም የደበበን የሥነ-ግጥም ርቀት እና ጥልቀት የምናይበት ሥራ ነው። ለዚህች ለደበበ መፅሐፍ አጠቃላይ ገፅታዋን በተመለከተ አስተያየት የፃፈው ታዋቂው ወገኛ እና የደበበ ጓደኛ የሆነው መስፍን ኃብተማርያም ነው። መስፍንም ስለዚህችው መፅሐፍ የሚከተለውን ብሏል።
“ደበበ ሰይፉ በርዕስ አመራረጡና በሚያስተላልፋቸው ልብ የሚነኩ መልዕክቶች ብቻ ሳይሆን በስንኞቹ አወራረድና የቤት አመታቱ በአጠቃላይ በውብ አቀራረቡ ተደራሲያንን የሚመስጥ ገጣሚ ነው። ስለ ተፈጥሮ ሲገጥም ፀሐይና ጨረቃ፣ ቀስተ ደመናና የገደል ማሚቶ ያጅቡታል። ስለ ፍቅር ስንኞች ሲቋጥር የፍቅረኞችን ልብ እንደ ስዕል ቆንጆ አድርጐ በቃላት ቀለማት ያሳያል። ክህደት ላይ እንደ አንዳንድ ገጣሚያን አያላዝንም። ይልቁንም ውበትና ህይወትን አገናዝቦ ያውላችሁ ስሙት፣ እዩት፣ ማለትን ይመርጣል። ….. እኔ እንደማውቀው ደበበ ሰይፉ በገጣሚነቱ ሁሌም ዝምተኛ ነው። አይጮህም። ጮሆም አያስበረግግም። ይልቁንስ ለዘብ ለስለስ አድርጐ “እስቲ አጢኑት” ይለናል። ደግመን እንድናነብለት የሚያደርገንም ይኸው ችሎታው ነው።” በማለት የወግ ፀሐፊውና ጓደኛው መስፍን ሐብተማርያም ደበበን ይገልፀዋል።
ደበበ ሰይፉ በስነ-ግጥም ተሰጥኦው እና በሚያነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ጐልቶ ከሚነሱ ከያኒያን መካከል አንዱ መሆኑን ቀደም ያሉት ሃያሲያን ጽፈውታል።

የደበበ ችሎታ በዚህ ብቻም አያበቃም። ደበበ የቴአትር ጥበብ መምህር ከመሆኑም በላይ በዘርፉ ውስጥ ግዙፍ የሚባል አስተዋፅኦ አበርክቶ አልፏል። ደበበ በመድረክ ላይ የሚሰሩ ቴአትሮችን እና የቴአትር ፅሁፎችን የያዟቸውን ሃሳቦች በመተንተን እና ሒስ በመስጠት ለዘርፉ እድገት የበኩሉን ሚና ተጫውቷል። ደበበ የቃላት ፈጣሪም ነው። ለምሳሌ በቴአትር ዓለም በአጠቃላይ በሥነ-ጽሑፉ ዓለም ውስጥ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መጠሪያ የሆኑ ሙያዊ ቃላትን ወደ አማርኛ በማምጣት አቻ የሆነ የአማርኛ ትርጉም በመስጠት ይታወቃል። በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ እስከ አሁን ድረስ መጠሪያ የሆኑትን ለምሳሌ ገፀ-ባህሪ፣ ሴራ፣ መቼት፣ ቃለ-ተውኔት ወዘተ እየተባሉ የሚገለፁትን መጠሪያዎች የፈጠረው ደበበ ሰይፉ ነው።
-    Character የሚለውን የእንግሊዝኛ መጠሪያ “ገፀ-ባህሪ” በማለት አቻ ትርጉም ሰጥቶታል፣
-    Sefting የሚለውን የእንግሊዝኛ መጠሪያ በውስጡ ጊዜ እና ቦታን መያዙን በመረዳት ወደ አማርኛ ቋንቋ ‘መቼት’ ብሎ ደበበ ተረጐመው። መቼት ማለት ‘መች’ እና ‘የት’ ማለት ሲሆን፤ ጊዜንና ቦታን ይገልፃል።
-    Dialogue የሚለው የእንገሊዝኛ ቃል ተዋናዮች በትወና ወቅት የሚናገሩት ሲሆን፤ ይህን Dialogue የተሰኘውን ቃል ወደ አማርኛ አምጥቶት ቃለ-ተውኔት በማለት የተረጐመው ደበበ ሰይፉ ነው።
ደበበ እነዚህንና ሌሎችንም ሥነ-ጽሑፋዊ ቃላትን በመፈጠር በትውልዶች አንደበት፣ አእምሮ እና ብዕር ውስጥ ለዘላለም እንዲኖር ያደረገ ጥበበኛ ነው።
ደበበ ሰይፉ ለዚሁ ለቴአትር ትምህርት ዘርፍ ካበረከታቸው አስተዋፅኦዎች መካከል ለትምህርቱ መጐልበት ይረዳ ዘንድ በ1973 ዓ.ም መፅሐፍም አሳትሟል። መፅሐፏ የቴአትር ጥበብ ከፀሐፌ-ተውኔቱ አንፃር የምትሰኝ ርዕስ የያዘች ሲሆን፤ ለሀገራችን የቴአተር ሙያተኞች እንዲበራከቱ እና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ሰፊ ድርሻ አበርክታለች። ደበበ በዚሁ በቴአትር ዘርፍ ውስጥ የተፃፉ የንባብ መፅሐፍት ያለመኖራቸውን ክፍተት ተገንዝቦ ያንን ክፍተት ለመሙላት ሙያዊ ጥሪውን የተወጣ ባለሟል ነው።
ደበበ ሰይፉ ፀሐፌ - ተውኔትም ነው። በርካታ ተውኔቶችን ፅፎ ለመድረክ አብቅቷል። አንዳንዶቹ ደግሞ ለምሳሌ ክፍተት የተሰኘው ተውኔቱ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለበርካታ ጊዜያት ታይቶለታል። በዚህ ክፍተት በተሰኘው የደበበ የቴሌቭዥን ድራማው ላይ በመተወን ተፈሪ ዓለሙ፣ አለማየሁ ታደሰ እና ሙሉአለም ታደሰ ድንቅ የሆነ ብቃታቸውን አሳይተውበታል።
ደበበ ሰይፉ ከፃፋቸውና ከተረጐማቸው ተውኔቶች መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡-
  1. ከባህር የወጣ ዓሣ
  2. እናትና ልጆቹ
  3. እነሱ እነሷ
  4. ሳይቋጠር ሲተረተር
  5. የህፃን ሽማግሌ
  6. ማክቤዝ እና
  7. ጋሊሊዮ ጋሊሊ ይገኙበታል።
ከእነዚህ ሌላም በ1973 ዓ.ም ማርክሲዝምና የቋንቋ ችግሮቹ የሚል መፅሐፍ ከማሳተሙም በላይ በ1960 ዓ.ም ያዘጋጃት የሦስት አጫጭር ልቦለዶች መድብል የሆነችው ድርሳኑ ትጠቀሳለች።
ደበበ ሰይፉ ከእነዚህ ከረቀቁ እና ከመጠቁ ምሁራዊ አስተዋፅኦው በተጨማሪ በበርካታ ኪነ-ጥበባዊ ጉዳዮች ላይም አሻራውን ያሳረፈ ነው። ለምሳሌ በቀድሞው ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ መስፋፋት እገዛው ሰፊ ሆኖ ኖሯል። በኢትዮጵያ ሬዲዮ ውስጥም የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ውስጥ ያሉትን ፕሮግራሞች አማካሪ ሆኖ ሰርቷል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የቋንቋዎች ተቋም ጆርናል አሳታሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆኖ አገልግሏል። ደበበ ሰይፉ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዚደንት ሆኖ ሰፊ ድርሻ አበርክቷል። ደበበ ሰይፉ በኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ዓለም ውስጥ ትልቅ ድርሻውን አበርክቶ ያለፈ የትውልድ ምሳሌ ነው።
ግን ሁሉም ነገር እንዳማረበት እስከ መጨረሻው አይሄድም፤ እናም ደበበ በዙሪያው ባሉ ሰዎች በሚያውቃቸው ሰዎች ተበሳጨ። ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ ከቤት ዋለ። ታመመ። መናገርም አቆመ። ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ በአጠቃላይ ለኪነ-ጥበቧ እድገት የአንበሳውን ድርሻ ያበረከተው ደበበ ሰይፉ ሚያዚያ 16 ቀን 1992 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ቀብሩም ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ-ክርስትያን ተፈፀመ።
ስለ ደበበ ሰይፉ ምን ተፃፈ?
“ደበበ ሰይፉ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዝዳንት ሆኖ ከ1978 እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ሰርቷል። ከዚህም በላይ በወቅቱ አያሌ የሙያው ባለቤቶች እንዲሰባሰቡ አድርጓል። ከውጭ ሀገር በተለይም ከሶቭዬት ኅብረት ጋር ሙያዊ ድጋፍና ትብብር እንዲደረግ አድርጓል። አንጋፋው ደራሲና ሃያሲ አቶ አስፋው ዳምጤ በአንድ ወቅት ስለ ደበበ የህይወት ታሪክ ለሚያጠናው ተማሪ፣ ለተክቶ ታደሰ በሰጡት ቃለ-ምልልስ እንዲህ ብለዋል።
“ደበበ ስራ ይወዳል ስራው ጥንቅቅ ያለ ነው። ግን ሰዎችን ለመጋፈጥ ድፍረት ያንሰዋል። ለቴአትር ዲፓርትመንት ከመከፈቱ ጀምሮ መጽሐፍ ጽፎላቸዋል። ፅንሰ ሃሳቡን እንዲረዱት አድርጓል። ስለ ደበበ ካስደነቁኝ አንዱ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታው ነው። የደራሲያን ማኅበር ሊቀመንበር ሆኖ እኔ ስራ አስፈፃሚ ሆነን ሠርተናል። ቀድሞ ከነበረው የማኅበሩ የሥራ ዘመን ያልታየ እንቅስቃሴ ደረገ” የሚሉት አቶ አስፋው “እነሆ” የምትሰኘው የአጫጭር ልቦለዶች መድብልና “ብሌን” የተሰኘችው መጽሔትም መታተሟን ያስረዳሉ። “የጽጌረዳ ብዕር” የሚል የግጥም መድብል መታተሙንም አስረድተው የደበበን ጥንካሬ ገልፀዋል።
ታዋቂው የወግ ፀሐፊ መስፍን ኃ/ማርያም ደግሞ ለአጥኚው እንዲህ ብሎ ነግሮታል። “ደበበ በጣም ጠንካራ፣ ትጉህ ሠራተኛ፣ ለተሰለፈበት ዓላማ ወደኋላ የማይል፣ በማስተማር ደበበ innovator /ፈጣሪ/ አይነት ነበር። የምናስተምረውን ኮርስ እንዲህ ብናደርገው፣ እንዲህ ብንለው እያለ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንድናሻሽል በማድረግ በኩል ፈር ቀዳጅ ነበር።…. ደበበ ደራሲ ብቻ አይደለም። ጥሩ የማስተማር ችሎታ ነበረው” ብሏል።
ደራሲ ታደለ ገድሌም ሚያዚያ 29 ቀን 1992 ዓ.ም በወጣው “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ላይ “ደበበ ሰይፉና ስራዎቹ ሲታወሱ” በሚለ ርዕስ ስለዚሁ ታላቅ ሰው አስነብቦናል።
ይህች ከተማ ነሐሴ 5 ቀን 1942 ዓ.ም ደበበን ያህል ታላቅ የኪነ-ጥበብ ሰው አፍርታለች። አባቱ በጅሮንድ ሰይፉ አንተን ይስጠኝ እና እናቱ ወ/ሮ የማርያምወርቅ አስፋው የኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ዋልታ ያቆሙት በዚህች ምድር ነው። ደበበ ሰይፉን! ይርጋለም ከተማ ውስጥ።
“ይርጋለም
ዋ… ይርጋለም
የልጅነቴ ህልም ቀለም
ዓይኔን የከፈትሽው ጨረር
ወርቃማይቱ ጀንበር” ብሎ ደበበ ፅፎታል።
ዛሬ በህይወት የሌለው የስነ-ጽሁፍ መምህሩ ብርሃኑ ገበየሁ ትዝ አለኝ። ስለ ደበበ ሰይፉ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ሲፅፍ እንዲህ ብሏል። “የደበበ አቀራረቡ ቀላልና የማያሻማ ነው። ድምፀቱ ደግሞ ሐዘን ከሰበረው ልብ የሚፈልቅ እንጉርጉሮ። የአቀራረብ ቀላልነት ውበቱ ነው። ይርጋለምና ልጅነቱ በተናጋሪው ህሊና አንድም ሁለትም ናቸው፤ የማይፈቱ” ብሏል። እናም ይርጋለም ደበበ ሰይፉ ናት!
ሌላኛው የስነ-ጽሁፍ መምህር የሆነው ወዳጄ ገዛኸኝ ጌታቸው፣ ደበበ ሰይፉ እንዳረፈ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር። “ዛሬ የኢትዮጵያ ስነ-ጽሁፍ አንድ ለጋ ብዕር አጣ፤ ነጥፎ አይደለም ታጥፎ ነው። ዛሬ የኢትዮጵያ ስነ-ጽሁፍ የዋህ ሃሳብ አጣ። ከፍቶ አይደለም በኖ ተኖ እንጂ። ዛሬ ብዙዎቻችን ካወቅነው ብዙ ነገር አጣን። ካላወቅንም እሰየው፤ ከእንጉርጉሮና ከፀፀት ተረፍን” ብሏል።
ጋዜጠኛ መሠረት አታላይ በፈርጥ መጽሔት ላይ “ለኪነ-ጥበብ ተፈጥሮ ለኪነ-ጥበብ የሞተ” በሚል ርዕስ የደበበን ጓደኞች ዶ/ር ፍቃደ አዘዘን፤ መስፍን ኃ/ማርያምን እና አስፋው ዳምጤን ቃለ መጠይቅ አድርጐ ጽፏል። ሁሉም የኪነ-ጥበብ ጋዜጠኞች ማለት ይቻላል ስለ ደበበ ጽፈዋል። በ1995 ዓ.ም ደግሞ በጀርመን የባህል ተቋም ውስጥ በወ/ሮ ተናኘ ታደሰ አስተባባሪነት ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ፣ ዶ/ር ዮናስ አድማሱ እና ገዛኸኝ ጌታቸው “የደበበ ሰይፉ ምሽት” ብለው እጅግ የደመቀ ዝግጅት አድርገዋል። ነብይ መኮንን፣ አበራ ለማ እና አብርሃም ረታ ቅኔዎች ዘርፈውለታል። የወንዙ ልጅ አብርሃም ረታ እንዲህ ገጥሞለታል፡-
ብናቀጣጥለው ኪነትክን እንደጧፍ
ስምህ ርችት ነበር
ላውዳመት እሚተኮስ
ሰማይ ላይ የሚጣፍ
ሰማይ ላይ የሚጦፍ
ሰማይ ላይ የሚጥፍ።
https://www.youtube.com/watch?v=omZPWPyU1uQ
*************************************************************
http://www.sendeknewspaper.com/arts-sendek/item/486_በጥበቡ በለጠ

ማሞ ካቻ (አቶ ማሞ ይንበርብሩ)

  አቶ ማሞ ይንበርብሩ (ማሞ ካቻ) እስቲ እናስታውሳቸው፣ ተቀብሮ እንዳይቀር አኩሪ ታሪካቸው  (ደረጀ መላኩ)   አቶቢሲ ማሞ ካቻ የት ትሄዳለህ? ገብረ ጉራቻ… ታዳጊው ማሞ ይንበርበሩ ገና በጨቅላ እድሜው አባቱ አቶ...