ሰኞ, ማርች 21, 2016

እራስን መሆን/ እኔ ማን ነኝ?



አንድ ጊዜ ኮሌጅ እያለሁ አንዱ ፕሮፌሰር ሁላችንን እንዲህ ሲል ጠየቀ ” ከእናነንተ ውስጥ ቶሎ ወይ በቀላሉ የሚናደድ ማን ነው?” ክፍል ውስጥ ከነበርነው 25 የምንሆን ተማሪዎች ውስጥ ከስምንት እስከ አስር የሚያክሉ ተማሪዎ እጃቸውን አወጡ። ፕሮፌሰሩም መልሶ ጠየቀ ” እስቲ ማን ይነግርኛል ለምን በቀላሉ እንደሚናደድ?” የዛን ጊዜ ተማሪው ሁሉ ጸጥ አለ። ከዛን ፕሮፌሰሩ ያለው አይረሳኝም። “እዚህ ውስጥ እድሜው ከ20 በታች ያለ ተማሪ ያለ አይመስለኝም፥ ታዲያ ቢያንስ ሃያ አመት ያህል ከራሳችሁ ጋር ኖራችሁ ስለራሳችሁ በደነብ እንዴት ነው የማታውቁት? በቀላሉ ስትናደዱ ለምንድን ነው በቀላሉ ምናደደው ብላችሁ እንኳን እንዴት አትጠይቁም” አለ። ይህ ለብዙዋችን እውነት ነው፥ከእራሳችን ጋር ይህን አመት ስንኖር የምናደርገውን ነገር ለምን በለን አንጠይቅም።ስለ እራሳችን ምን ያህል እናውቃለን? እኛ ስለራሳችን ካላወቅን ሌሎች ስለኛ ሚሉትን ብቻ አሜን ብለን እንቀበላለን።
እራሳችን ማን እንደሆንን ሳናውቅ እንዴት እራሳችንን እንሆናለን? እራስን ማወቅ ማለት ምን ማለት ነው። ከልጅነታችን ጀምሮ የተለያዩ ነግሮች ከቤተስብ፥ ትምህርት ቤት፥ ጓደኞች እና ባጠቃላይ ህብረተሰብ ስለራሳችን ስንሰማ ነው ያደግነው። ባካባቢያችን ያሉ ሰዎች በዘራችን፥ በቆዳ ቀለማችን፥ በትምህርት ቤት ባለን የትምህርት ውጤት፥ በቤተሰቦቻችን የንብረት መጠን ብቻ በተለያዩ ነግሮች ተነስተው ማንንታችንን ይነግሩናል። እኛም የሰማነውን ተቅብለን ያ ያሉኝ ነኝ ብለን እንኖራልን። በእርግጥ ልጅ እያለን የሚነገረንን ሁሉ ከመቀበል ውጪ ነገሮችን አመዛዝኖ እና አጣርቶ የመቀበሉ ጥበቡ አልነበረንም፥ ነገር ግን ካደግን በኃላ ግን እራሳችንን ማወቅ የሚገባን ከሰው ከስማነው ብቻ ከሆነ እራሳችንን ሳይሆን ሌላ ስውን እየኖርን ነው።
እኛ ማን እንደሆንን ሳናውቅ ስንቀር ሰው የጠንን ማንነት ተሸክመን እኖራለን። ሴት ስለሆንሽ ይሄን ማድርግ አትቺይም፥ ወይ ወንድ ስለሆንክ ይህን ማድረግ የለብህም፥ የመጀመሪያ ልጅ ስለሆንክ ይህን ወይ ያን ማድረግ አለብህ፥ ዘርህ ይህ ስለሆነ እንዲህ እና ያን ማሰብ አለብህ፥ ብር ስለሌለህ ይህን ወይ ያን አታቅድ አታስብ •••
ሰው ማን እንደሆንን ሊነግሩን አይገባም ሲባል ባጠቃላይ ሰው አንሰማም ማለት አይድለም።እግዚአብሔር ይመስገን በሒይወታችን  እንዲመሩን፥ መልካሙን መንገድ እንዲያሳዩን፥ ከእነርሱ ሒይወት እንድንማር ስላስቀመጣቸው ሰዎች። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ” ሞኝ ከራሱ ውድቀት ጠቢብ ግን ከሌላው ይማራል” ምክርን እና የሒይወት ምሳሌን እየተማርን ሂይወታችንን ምሻሻል ይኖርብናል።ነገር ግን የሰው ሃሳብ እና ቃል የኛን ማንነት መወስን የለበትም። ማን ነኝ ወይ ምን ማድረግ እፍልጋልሁ ብለን ስንጠይቅ የምናስበው ስዎች ምን እንዳሉን ወይ ከኛ ምን እንደሚጠብቁ ከሆነ ያኔ ስተናል።

ታዲያ እራስን ማወቅ እንዴት ይቻላል?

እራስን ማግኘት ወይ እራስን ማወቅ ማለት ለምንስማው፥ ከምናየው እና ከምናነበው እንዴት ሊያልፍ ይችላል። እነዚህ ነጥቦች እራሳችንን እንድናውቅ ይረዱናል።
1. ውስጣችንን መስማት.  እግዚአብሄር ሲፈጥረን ህሊናችን ከሱ ሃሳብ ጋር እንዲስማማ አድርጎ ነው። የተሳሳተ ነገር ስናደርግ ብዙ ጊዜ ህሊናችን ይወቅስናል፥ ውስጣችን ደስ አይለውም። አንድ ነገር ስናደርግ ውስጣችንን መጠየቅ ፥ ውስጤ ምንድን ነው ሚስማኝ? ምንድን ነው እግዚአብሔር ለውስጤ ሚናገረው ብለን መጠየቅ እናም ከዛ ከሚሰማን ነገር ወይ የውስጥ ድምጽ ጋር መስማማት። ያልሆነውን ስናስመስል ውስጣችን ምቾት አይሰማውም፥ ምክንያቱም ውስጣችን ያለው ድምፅ እግዚአብሔር የእርሱን ባህሪ እንድንወርስ ከማንነታችን ጋር ያያዘው ስለሆነ ነው። ስለዚህ ለራስ ታማኝ መሆን፥ አባቴ ወይ ጎረቤቴ ምን ያላል ወይ ከኔ ይጠብቃል ከማለታችን ይልቅ እግዚአብሔር የሰጠኝ ህሊናዬ የውስጥ ድምጼ ምን ይላል ብለን መጠየቅ። አንድ አንዴ ውስጣችን የሚለንን ስምቶ ለዛ መታዘዝ ይከብደናል ምክንያቱም እድሜ ልካችንን የኖርነው የውጭ ድምጽ እየስማን ስለኖርን። ከራሳችን ጋር እንስማማ።
2. የራስን ዋጋ ማወቅ. ስንፈጠር እኛን የመስለ ሌላ አልተፈጠረም። በእግዚአብሔር እያንዳንዳችን ልዩ ሆነን ነው የተፈጠርነው። የአንድ ስው ዋጋ በምንም በማንም አይለካም። ይኛ ዋጋ የፈለግነው ነገር ሲሳካ አይጨምርም ወይ ስንደክም ወይ ስንወድቅ አይቀንስም። ሃብት፥ውበት፥ትምህርት ደረጃ፥የትውልድ ስፍራ እና ዘር ዋጋችንን አይጨምረውም ወይ አይቅንሰውም። የሰው ሁሉ ዋጋ  እኩል ነው ግን ያንዱ ሌላውን አይተካውም። ስለዚህ እኔ ይሄ ስለሌለኝ ወይ ስላለኝ መደሰት፥ መከበር ወይ በሰላም መኖር አይገባኝም አንበል። ሰው ለኛ ሚሰጠን ዋጋ ሳይሆን እኛ ለራሳችን የምንሰጠው ዋጋ ነው ወሳኝ ነገር።  አብዛኛው ጊዜ ሌላው ሰው የሚሰጠን ዋጋ እኛ ለራሳችን ከሰጠነው ዋጋ ጋር አንድ ነው። በእግዚአብሔር ፊት የፕሬዝዳንት ኦባማ ዋጋ እና መንገድ ላይ የሚተኛው ወንድማችን ዋጋ አንድ ነው።
3. አይምሮን ማደስ.  ከልጅነታችን ጀምሮ ስለኛ ብዙ ተነግሮናል። ያንን እንደ እውነታ ወስድን ሳናስብው ማንንታችን እድርገናችዋል። አሁን ግን ቆም ብለን ስለኛ የምናስባችው ነገሮች ከየት እንደመጡ እንመርምር እና ለኛ የማይጥቅሙን ነግሮች ሁሉ እናስወግድ። አንተ እኮ ፈሪ ነህ፥ ትምህርት አይገባህም፥ ጸባይህ ለሰው አይገባም፥አትረባም፥መልክህ አያምርም፥ መናገር አትችልም ዝም በል፥ ካንተ ያ ወይ ይሄ ይሻላል፥ አይሳካላልህም፥ የተለያዩ መጥፎ እና ማንነታችንን በመጥፎ ሊቅይሩ የመጡ ንግግሮችን ሁሉ ከአይምሮአችን አጥቦ ማውጣት። ትዝ ይለኛል የተውስኑ ልጆች ጋር ቁጭ ብለን ስናወራ ስለራሳችሁ መጥፎ የምታስቡት ነገር ከየት እንደመጣ አስቡ እስቲ ስላችው ሁሉም  ልጅ እያሉአንድ ሰው የተናገራቸው ነገሮች ነበሩ። እኛ ግን ሳናስተውል እራሳችንን በእነርሱ ቃሎች ወስነነዋል። ወይም ሰዎች ባይሉን ደግሞ አንድ አንዴ እኛ እራሳችን ካለፍንባቸው የድሮ ድካሞች ዛሬያችንን ወስነነዋል። ስለዚህ ቆም ብለን እንዚህን ሃሳቦች በመልካም ሃሳቦች እንተካቸው።
4. ነገሮችን እና እራስን መለየት. በአካባቢያችን የሚሆኑ ነግሮች የራሳቸ ማንነት አላቸው የነሱን ማንነት ከእኛ ጋር አለማያያዝ። ለምሳሌ ትምህርት ቤት ጥሩ ውጤት ሳናመጣ ስንቀር ያንን ወስደን እኔ ማለት ሰነፍ ነኝ ወይ እንዲህ ነኝ ከማለት በፊት ትምህርቱን ጥሩ ውጤት ላመጣ የሔድኩበት መንገድ ጥሩ አልነበርም ስለዚህ በሚቅጥለው በየትኛው መንገድ ልሂድ ብሎ ማሰብ። ባጠቃላይ እኔ እንዲህ ነኝ ብሎ ከመደምደም በፊት እንዴት ያንን ነገር ልስራው ወይ ላሻሽለው ብሎ ማሰብ። ሌላ ምሳሌ ከሰው ጋር ያለን ግንኙነት መልካም ካልሆነ አይ እኔ ጥሩ ጓደኛ አልሆንም ከማለት በፊት ነገሩን ከራስ ማንነት ወጣ አድርጎ በምን መንገድ መግባባት እንችላለን፥ ምን ብናደርግ ይሄ ይስትካከላል ማለት አለብን።
5.እራስን ከሌላው ጋር አለማወዳደር.  ከላይ እንዳልነው ሁላችን ስንፈጠር ልዩ ልዩ ሆነን ነው። የሌላው ሒይወት ለመማሪያ ምሳሌ ሊሆነን ይገባል እንጂ ማወዳደሪያ ምስፈርት መሆን የለብትም። ሰው ሁሉ በየራሱ የሚሄድበት መንገድ አለው ፥ ያንተ መንገድ ከሌላው ይለያል፥ የሰው መንገድ ላይ መግባት አንተ መድረስ የሚገባህ ቦታ አያደርስህም። አንተ ማድርግ በምትችለው እና እግዚአብሔር በሰጠህ ነገር መዝነው ። መጽሃፍ ቅዱስ ላይ እግዚአብሔር ለሁሉ የተለያየ ችሎታ ወይ ተሰጥኦ እንደሰጠ ግን እያንዳንዱ ሚጠየቀው በተሰጠው በዛ ነገር ምን እንዳደረገ ነው። የሌላውን ሰው ስጦታ ትተን ይኛ የተሰጠን ላይ ማተኮር።
6. መልካምን ማሰብ ጥሩ ጥሩ ንገሮችን ማሰብን አይምሮአችንን ማስለመድ። ብዙ ጊዜ ለሰው ምንለውን እንጠነቀቃለን በቃላችን እንዳንጎዳቸው ቃላት እንመርጣለን ስለራሳችን ግን ያን ያህል አንጠነቀቅም። ስለ ራሳችን የምናስበው እና ምንናገረው ነገር መልካም ንገር እንዲሆን መጠንቀቅ አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ “በምላስ ላይ ሞት እና ሒይወት አለ” ይላል ለምን? ምክንያቱም በምንናገርው የሰውን መንፈስ ልንገድል ወይ ልናቀና ስለምንችል ነው። ስለራሳችን እንዲሁ በውስጣችን እንናገራለን እናስባለን ያ ሃሳብ መልካም መሆን አለበት።  እራሳችንን መሆን ይከብደናል ስለራሳችን ያለን ሃሳብ መጥፎ ከሆነ። እራሳችንን ማበረታታት፥ መልካም ይሆንልሃል ፥በእግዚአብሔር የተወደድክ ነህ እያልን ብዙ ብዙ መልካም ነገሮችን መናገር አለብን።
7. እራሳችንን በስዎች አይምሮ ውስጥ አለማየት. 
ብዙ ጊዜ እራሳችንን እንዳንሆን ሚያረግን እራሳችንን በሰው ውስጥ ሆነን ነው ምናየው። ማለትም ስናወራ ያ የሚስማን ሰው ስለኛ ምን እንደሚያስብ በሱ ውስጥ ሆነን እራሳችንን ማየት እንጀምራልን ከዛን መናገር የምንፈልገውን ሳይሆን መስማት የሚፍልገውን ማውራት እንጀምራለን። ይሄ በአነጋገራችን ብቻ ሳይሆን፥ ባለባበሳችን፥ ባረማመዳችን፥ በሁሉ ነገራችን በሌላ ሰው ውስጥ ያለው እይታ እንዲስተካከል እያልን እራሳችንን እንቀያይራለን።  ይህ እንዳይሆን ስናወራ ወይ ስንኖር ውስጣችን እንደሚለው መሆን አልበት። ብዙ ጊዜ ውስጣችን የሚለውን መስማት ስንል መጀመሪያ ውስጣችን እግዚአብሔር  ከሚለው ጋር መስማማቱን ማረጋገጥ አለብን።
**********************************************************
ምንጭ፡ -  http://habeshalij.com/

ከድርሰት ዓለም


ሊነበብ የሚገባ መጥሃፍ:-
***********************

  ልጅነት

በዘነበ ወላ
***********************

ልጅነት -
እማዬ መዋሸት ነውር እንደሆነ ደጋግማ የምታስጠነቅቀኝን ያክል፤ ለበጐ ሲሆን እንዴት ማበል እንዳለብኝ የምታስጠናኝ ጊዜም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሁሌም ጠንካራ እውነተኝነቷ ስለሚገዝፍ እኔም በአብዛኛው የምከተለው ይህንኑ ባሕርይዋን ነበር፡፡
ቤተሰቦቼ የአንድነት እድር አባል ናቸው፡፡ አንድ ቀን እማዬ ወርሐዊ መዋጮውን ሄዳ መክፈል አልቻለችም፡፡ አባቴም ለሥራ ከወጣበት አልተመለሰም፡፡ እድርተኛው የሚሰበሰብበት ቦታ ቅርብ ስለነበር እኔን ላከችኝ፡፡
“ብሩን ጭብጥ አድርገህ ያዝ፤ ዜራሞ ኢንቻ ሲሉ አቤት በል፡፡ ካርዱን ስጣቸው፡፡ ስለ አባትህ ሲጠይቁህ ሸማ ለደንበኞቹ ሊያደርስ ጠዋት ነው የወጣው በል፡፡ እናትህን ካሉህ ትናንትና አክስቴን አሟት ከሄደችበት አልተመለሰችም በላቸው፡፡”
“እሺ፡፡”
“ስትመለስ እንጎቻ ጋግሬ እጠብቅሃለሁ፡፡ በል ብርርር ብለህ ሂድ!”
የእድሩን መዋጮ ከፍዬ ተመለስኩ፡፡
“ከፈልክ?”
“አዎን”
“ታዲያ ምነው አኮረፍክ?”
“ምንም፡፡”
በዚህ መካከል አደይ ዝማም ወደ ቤታችን እየሳቁ ገቡ፡፡ እንዳዩኝ “አይ ፉንጋይ! እድርተኛውን ሁሉ በሳቅ ሆዳችንን አፈረሰው፡፡”
“በምን ምክንያት?” አለች እማዬ፣ ትንሽ ፈገግ ብላ አደይ ዝማምን እያየች፡፡
“ዜራሞ ኢንቻ ሲባል አቤት አለ፡፡ አባቱን ሲጠይቅ ሸማ ሊያደርስ ከሄደበት አልተመለሰም አለ፡፡ እናትህስ? ሲሉት አትናገር ብላኛለች እንጂ እቤት ውስጥ አረቄ እያወጣች ነው፡፡”
“አንተ! ብላ አፈጠጠችብኝ ዓይኖቿ ግን አይቆጡም፡፡
“አንቺ ነሻ” አልኳት
እኔ ምን አልኩኝ?”
“አትዋሽ እያልሽ ሁልጊዜ ትቆጫለሽ፤ ሰባቂ እያልሽ ትማቻለሽ፡፡ አሁን ደግሞ ብዋሽ…”
ከትከት ብላ ስቃ በብሩህ ዓይኖቿ ቁልቁል አየችኝና “አይ ፉንጋይ! እስኪ ልብ ይስጥህ፡፡ በል ሂድና ትንሿ ጎርጓዳ ሳህን ውስጥ ያስቀመጥኩልህ እንጎቻ አለ፤ ውሰድና ብላ” ብላኝ በቅርቡ የፈፀምኩትን ሌላ የቂልነት ድርጊት ለአደይ ዝማም ልታወራላቸው ስትጀምር፤ አደይ ዝማም አቋርጠዋት የራሳቸውን ልጅ የጐይቶምን ቂልነት ለእማዬ ያጫውቷት ጀመር “እትዬ ባሎቴ የእኔም ጉድ ያው እንደ ፉንጋይ እኮ ነው! በቀደም ዕለት ከትምህርት ቤት ሲመጣ ምሳውን ጓዳ አስገብቼ ደብቄ ያስቀመጥኩለትን እሰጠዋለሁ አልበላም አለ፡፡
“ለምን?”
“አንቺ ከዘመዶትሽ ጋር በጐመን እየበላሽ ለእኔ በአይብ ትሰጪኛለሽ?”
ሁለቱም ከልብ የኮረኮሯቸውን ያህል ሳቁ፡፡

ጋዜጠኛና ደራሲ ዘነበ ወላ
***********************************
(ምንጭ፡ - ዘነበ ወላ “ልጅነት” (2000))
አሁን ‹‹ልጅቴ፣ ልጅነቴ - ማርና ወተቴ …›› በሉ
  -Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን)
ፎቶግራፍ:--   Muluken Asrat
 




የትምህርት ነገር

በምእራባዊ፡ ትምህርት፡ የኢትዮጵያ፡ አወዳደቅና፤ በጠቃሚ ትምህርት የወደፊት አነሳሷ።
************************************************************************


ጣሊያን፡ የኢትዮጵያን፡ የባህር፡ ጠረፍ፡ ከወረረ፡ በኋላ፡ ወደ፡ መሃል፡ አገር፡ ገሠገሠ፤ በየካቲት፡ ወር፡ ፲፰፻፹፰ ዓ.ም. አድዋ፡ ላይ፡ በተደረገው፡ ጦርነት፡ ቢሸነፍም፡ ሙሉ፡ ለሙሉ፡ ከኢትዮጵያ፡ ሳይወጣ፡ በመረብ፡ መላሺ፡ አካባቢ፡ ቆየ። በዚህ፡ ጊዜም፡ ከኢትዮጵያ፡ ጋር፡ የንግድ፡ ግንኙነት፡ ለማድረግ፡ ይሞክር፡ ነበር። ይህን የጣሊያን፡ እንቅስቃሴ፡ አስመልክቶ፡ በጊዜው፡ ምእራባውያን፡ በየአገሮቻቸው፡ በጋዜጣ፡ ያቀርቡ፡ ነበር። የሚጽፉትም፡ ዘገባ፡ ተመሳሳይነት፡ ነበረው። ከነዚህ፡ ዘገባዎች፡ ውስጥ፡ አንዱን፡ ለምሳሌ፡ ያህል፡ እንመልከት።

ጣሊያኖች፡ የሚሠሩት፡ ሥራ፡ በጣም፡ የሚያስደንቅ፡ ጥበብ፡ ያለበት፡ ነገር፡ ነው። የአቢሲኒያን፡ የባህር፡ በር፡ ተቆጣጠሩ፣ ከዛም፡ የመሃሉን፡ አገር፡ ለመያዝ፡ ሞክረው፡ ከከሸፈባቸው፡ በኋላ፡ አሁን፡ በሚያስገርም፡ ጥበብ፡ አቢሲኒያኖችን፡ አግባብተው፡ ከነሱ፡ ጋር፡ የንግድ፡ ልውውጥ፡ ጀምረዋል። [፩]

ይህን፡ ከዚህ፡ በላይ፡ የሰፈረውን፡ ጥቅስ፡ አዙረው፡ ሲያዩት፡ የምእራባውያንን፡ ባህል፡ ይመለከታሉ። ምእራባውያን፡ የሚያስደንቅ፡ ጥበብ፡ የሚሉት፡ ንጥቂያንንና፡ ማምታታትን፡ እንደሆነ፡ ያያሉ። አንድ፡ ኪስ፡ አውላቂ፡ የአንድን፡ ሰው፡ ቦርሳ፡ ከሰረቀ፡ በኋላ፡ ቦርሳውን፡ መልሶ፡ ለባለቤቱ፡ መሸጡን፡ ነው፡ መልካም፡ ጥበብ፡ ብለው፡ ምእራባውያን፡ የሚያደንቁት። ይህ፡ ጥቅስ፡ ያስፈለገው፡ የዚህ፡ ጽሁፍ፡ መልእክት፡ መሠረታዊ፡ ሃሳብ፡ ለሚያነቡት፡ በቀላሉ፡ እንዲገባቸው፡ ለማድረግ፡ ነው።   

በዚህ፡ ውይይት፡ መልስ፡ የሚያገኘው፡ ጥያቄ፡ ኢትዮጵያ፡ በአሁኑ፡ ዘመን፡ በማንኛውም፡ መስክ፡ ከአገሮች፡ ሁሉ፡ በታች፣ ሰዎቿም፡ ከሰው፡ ዘር፡ ሁሉ፡ በታች፡ የመዋላቸው፡ ጉዳይ፡ ነው።  ከምእራባውያን (ቱርክንም፡ ጨምሮ)፡  ጉብኝት፡ በፊት ኢትዮጵያ፡ ምን፡ አይነት፡ አገር፡ ነበረች? በዛ፡ ዘመን፡ ኢትዮጵያ፡ ምን፡ ትመስል፡ እንደነበር፡ ማወቅ፡ በኋላ፡ ከደረሰችበት፡ ሁኔታዋ፡ ጋር፡ ለማነጻጸር፡ ይጠቅማል። ስለራሳችን፡ ጉዳይ፡ ገድሎችንና፡ ጸሓፊ፡ ትእዛዛት፡ በመዝገብ፡ ያሰፈሩትን፡ ሳንጠቅስ፡ የሌሎችን፣ ያውም፡ የምእራባውያንን፡ የራሳቸውን፡ ምስክርነት፡ ለማግኜት፡ ማርኮ፡ ፖሎ፡ የተባለው፡ ምእራባዊ፡ አሳሽ፡ በአንድ፡ ሺህ፡ ሁለት፡ መቶ፡ ሰማንያ፡ ዓመተ፡ ምህረት፡ (ከሰባት፡ መቶ፡ ሀያ፡ አመታት፡ በፊት) ከቬኑስ፡ ተነስቶ፡ በዓለም፡ ተዘዋውሮ፡ ባገኜው፡ መረጃ፡ ስለ፡ ኢትዮጵያ፡ ያሰፈረውን፡ ምስክርነት፡ እንመልከት።

ስለ፡ አበሻ፡ ሰዎች፡ ይህን፡ ልንገራችሁ። (አበሻ፡ ብሎ፡ የጠራቸው፡ ቃሉን፡ ከአረቦች፡ ሰምቶ፡ ነው፡፡) የአበሻ፡ ሰዎች፡ ዋናው፡ ንጉሣቸው፡ ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ ነው። የንጉሦች፡ ንጉሥ፡ በማሃል፡ አገር፤ ይኖራል። ከዚህ፡ ከአቢዩ፡ ንጉሥ፡ ሌላ፡ በአገሪቷ፡ ስድስት፡ ሌሎች፡ ንጉሦች፡ አሉ፡ ከነዚህ፡ ውስጥ፡ ሶስቱ፡ ክርስቲያኖች፡ ሲሆኑ፡ ሶስቱ፡ ደግሞ፡ በኤደን፡ አቅራቢያ፡ ያሉ፡ እስላሞች፡ ናቸው። ሁሉም፡ ንጉሦች፡ በማሃል፡ አገር፡ ላለው፡ አቢይ፡ ንጉሥ፡ ይገብራሉ። አበሾች፡ የተትረፈረፈ፡ ሰብል፡ ያመርታሉ። ሩዝ፣ ሥጋ፣ ወተት፡ ይመገባሉ። የምግብ፡ ዘይት፡ ከሰሊጥ፡ ይሠራሉ። ዝሆኖችን፡ ከህንድ፡ አስመጥተው፡ ይገለገሉባቸዋል። የበረከቱ፡ ቀጭኔዎች፡ አሏቸው። አንበሶች፣ ግሥላዎች፣ አእዋፍና፡ እንስሳት፡  ሞልተዋል። ብዙ፡ ፍየሎችም፡ አሏቸው። ወፎቻቸው፡ ከኛ፡ ወፎች፡ ይለያሉ። ዶሮዎቻቸው፡ በዓለም፡ ላይ፡ ካሉ፡ ዶሮዎች፡ ሁሉ፡ ያማሩ፡ ናቸው። ግዝፈታቸው፡ አህያ፡ የሚያህል፡ ሰጎኖችም፡ አሏቸው። የሰው፡ መልክ፡ ያላቸው፡ ዝንጆሮዎችና፡ ጦጣወችም፡ ይገኛሉ። በመካከለኛው፡ አገራቸው፡ ብዙ፡ ወርቅ፡ ይገኛል። ከጥጥ፡ የሚያምሩ፡ ልብሶችንና፡ የመጽሐፍ፡ መለበጃወችን፡ ይሠራሉ። ነጋዴዎች፡ በነጻ፡ ይንቀሳቀሳሉ፣ ብዙም፡ ትርፍ፡ ያገኛሉ። ስለ፡ አበሾች፡ ብዙ፡ ልነግራችሁ፡ የምሻው፡ ነበረኝ፡ ነገር፡ ግን፡ አሁን፡ ወደ፡ ኤደን፡ ጠቅላይ፡ ግዛት፡ መሄድ፡ አለብኝ። [፪] 

አባቶቻችን፡ ሲወርድ፡ ሲዋረድ፡ ባቆዩልን፡ ታሪክ፡ እንደምናውቀው፡ እነሆ፡ በባእድ፡ አገር፡ ሰው፡ በማርኮ፡ ፖሎ፡ ምስክርነትም፡ እንደምናየው፡ ኢትዮጵያ፡ በረከቷ፡ የበዛ፣ ሰብሏ፡ የተትረፈረፈ፡ ንጉሧም፡ ክርስቶስ፡ የሆነ፡ ማራኪ፡ አገር፡ ነበረች።

ከምግብ፡ መትረፍረፍ፡ ሌላ፡ በማንኛውም፡ በሌሎች፡ ጉዳዮችም፡ በሰው፡ ፊት፡ የሚያምር፡ ሙያ፡ ያላት፡ አገር፡ ነበረች፤  የሚያሳፍር፡ አንድም፡ ጉድፍ፡ አልነበረባትም። እራሱ፡ ማርኮ፡ ፖሎ፡ እንደመሰከረው፡ ኢትዮጵያውያን፡ ብዙ፡ ሙያዎች፡ ነበሯቸው። የሚያምሩ፡ ሰፈሮችና፡  ሐውልቶችን፡ የሚሰሩ፣  ማህበራዊ፡ አኗኗራቸው፡ የሚማርክ፡ የፈረስ፡ አሰላለፋቸውም፡ ውብ፣ በእግዚአብሔር፡ የሚመካው፡ ጀግንነታቸውም፡ ወደር፡ የሌለው፡ ነበረ።

በህክምናም፡ ቢሆን፡ በመጀመሪያ፡ በሺታን፡ የሚያስከትሉ፡ ምርቶችን፡ አያመርቱም። በሺታም፡ ከመጣ፡ የነቀርሳ፡ በሺታን፡ እንኳን፡ ሳይቀር፡ የሚፈውስ፡ ብልሃት፡ ነበራቸው። የሚበልጠው፡ ቁምነገር፡ የበሺታ፡  መዘዝን፡ የሚያስከትሉ፡ ምግባሮች፡  አልነበሩባቸውም። አሁን፡ የምናያቸው፡ ብዙ፡ ደዌዎች፡ ከምእራባውያን፡ እና፡ ከሸቀጦቻቸው፡ ጋር፡ የገቡ፡ ናቸው። ብዙ፡ አጉል፡ አምልኮዎች፡ ደግሞ፡ ከአረቦች፡ የተገኙ፡ መጤ፡ በሺታወች፡ ናቸው። ለማስታወስ፡ ያህል፡ የሬንደር፡ ፔስት፡ የከብት፡ በሺታ፡ በጣሊያን፡ ወረራ፡ ኢትዮጵያውያንን፡ በምግብ፡ እጦት፡ ለቅኝ፡ ግዛትነት፡ ለማንበርከክ፡ ታቅዶ፡ የተዘራ፣  የአባለዘር፡ በሺታዎች፡ በአጼ፡ ምንሊክ፡ ዘመን፡ ምእራባውያን፣ በኢትዮጵያ፡ መሳፍንቶች፡ መካከል፡ የዘሯቸው፣ የቃልቻ፣ የጥንቆላ፣ የጨሌና፡ የቆሌ፡ አምልኮዎች፡ ደግሞ፡ ከአረቦችና፣ አምልኳቸው፡ ጋር፡ የገቡ፡ እንደሆኑና፡ እነዚህ፡ ደዌዎች፡ በኢትዮጵያ፡ እንዳልነበሩ፡
  ብዙ፡ ኢትዮጵያውያን፡ ያስታውሳሉ።

በእርሻ፡ ሥራም፡ መሬትን፡ የሚመርዝ፡ የኬሚካል፡ ማዳበሪያ፡ ሳያሻቸው፡ ዓለም፡ ገና፡ ብልሃቱ፡ ሳይገባው፡ የሚዘራውን፡ ዘር፡ በመቀያየር፡ አፈሩን፡ ያዳብሩ፡ ነበር። ውኃን፡ የሚያቀዘቅዝ፣ እሳትን፡ ከነሙቀቱ፡ የሚያቆይ፣ ልብስን፡ የሚያጸዳ፣ ምግብን፡ የሚያጣፍጥ፣ በጨለማ፡ አካባቢያቸውን፡ የሚያበራ፣ ሥራቸውንም፡ መዝግበው፡ ለመጭው፡ ትውልድ፡ የሚያስተላልፉበት፣ ሌሎችም፡ አሁን፡ የሌሉ፡ ብዙ፡ ብልሃቶች፡ ነበሯቸው።
 
ይህን፡ ሁሉ፡ ማን፡ ወሰደው? ኢትዮጵያ፡ ሙያዋ፡ እንዴት፡ ነጠፈ፣ ውበቷስ፡ እንዴት፡ ረገፈ? ኢትዮጵያውያን፡ እንኳን፡ የተትረፈረፈ፡ ማምረት፡ እራሳቸውን፡ መመገብ፡ እንኳን፡ የማይችሉ፣ እነሱን፡ ከሚጠሉ፡ የውጭ፡ ሰዎች፡ የእለት፡ ምጽዋት፡ ለመመጽወት፡ እጅ፡ እጅ፡ እያዩ፡ የሚኖሩ፡ ለምን፡ ሆኑ? ልመና፡ የሚያሳፍር፡ መሆኑን፡ እስካለማወቅ፡ ድረስስ፡ ኢትዮጵያውያን፡ ምነው፡ ወደቁ?  ፈረንጅ፡ መጥቶ፡ መብራት፡ ካልሰራ፡ የሚጨልምባቸው፣ የጉድጓድ፡ ውኃ፡ ካልቆፈረ፡ የሚጠሙ፣ ስንዴ፡ ካልመጸወተ፡ የሚራቡ፣ ካላከመ፡ በበሺታ፡ የሚጠቁ፣ ሳይንስ፤ ካላስተማረ፡ የሚደነቁሩ፡ ምነው፡ ሆኑ? አዋቂዎቹ፡ አያቶቻችን፡ ነገር፡ በምሳሌ፡ ብለው፡ እንዳስተማሩን፡ የነሱን፡ ፈለግ፡ በመከተል፡ ጉዟችን፡ እስኪ፡ በምሳሌ፡ እንቃኘው።  



በምጽዋት፡ ግድያ።

በአንድ፡ ቤት፡ ውስጥ፡ ያለች፡ እመቤት፡ ለባልዋና፡ ለልጆችዋ፡ የሚሆነውን፡ ምግብ፡ በማለዳ፡ ተነስታ፡ ታዘጋጃለች፣ ቤቷን፡ ታጸዳለች፣ ባልዋ፡ በንቃት፡ ሰርቶ፡ እንዲመለስ፡ ልቡን፡ በደስታ፡ ትሞላለች። እንዲህ፡ የምታደርግ፡ ብልህ፡ ሴት፡ ቤቷን፡ በደስታ፡ የተሞላ፡ አድርጋ፡ ትይዛለች፣ ልጆቿም፡ መልካም፡ ሥነ፡ ምግባር፡ ይዘው፡ ያድጋሉ፣ ለባልዋም፡ ዘውድ፡ ትሆናለች። ይች፡ ሴት፡ እንዲህ፡ አይነት፡ ብልህ፡ ሴት፡ ባትሆን፡ ኖሮ፡ ቤቱ፡ ምን፡ ይመስል፡ ነበር? ለምሳሌ፡ ይች፡ ሴት፡ ሰነፍ፡ ሴት፡ ናት፡ እንበል። ቤቷ፡ ከሚያፈራው፡ ይልቅ፡ የሩቁ፡ ወይም፡ የጎረቤቷ፡ ያስቀናታል፡ እንበል። ከሩቅ፡ ያለች፡ በብልጭልጭ፡ ያጌጠች፡ ሴት፡ ታይና፡ ብልጭልጯ፡ እንዴት፡ ያምራል፡ ብላ፡ ትጎዳኛታለች። እንግዳዋ፡ ሴትም፡ ወደዚች፡ ሰነፍ፡ ሴት፡ ቤት፡ ትመጣና፡ ቤቷን፡ ታያለች። እንግዳዋም፡ ለሴትዮዋ፡ እንዲህ፡ ትላታለች፥ ለባልሽ፡ እና፡ ለልጆችሽ፡ እኮ፡ ምግብ፡ መሥራት፡ የለብሽም፣ እኔ ምግብ፡ እያዘጋጀሁ፡ በየቀኑ፡ አመጣለሁ፣ አንች፡ ትንሽ፡ ገንዘብ፡ ትሰጭኛለሽ። የምትሰጭኝ፡ ገንዘብ፡ እህል፡ ከምትገዥበት፡ እና፡ ጉልበትሽን፡ ከምታፈሽበት፡ ያነሰ፡ ነው። እኔ፡ እየሠራሁ፡ አመጣለሁ፡ አንቺ፡ ምን፡ አደከመሽ፣ ዝም፡ ብለሽ፡ መተኛትና፡ ቡናሽን፡ መጠጣት፡ ብቻ፡ ነው፡ ትላታለች። ይህችም፡ ሴት፡ በእንግዳዋ፡ ሴት፡ ንግግር፡ ትማረካለች፣ ትስማማለች። እንግዳዋ፡ ምግብ፡ እያዘጋጀች፡ ታመጣለች፣ ባል፣ ሚስት፡ እና፡ ልጆች፡ እንግዳዋ፡ አዘጋጅታ፡ ያመጣችውን፡ እየበሉ፡ መኖር፡ ይጀምራሉ። ምግቡ፡ ይጣፍጣል። ልጆችም፡ ሆኑ፡ ባል፡ የተዘጋጀ፡ መጥቶ፡ ሲመገቡ፡ እንጂ፡ ማንም፡ ሲሠራው፡ አያዩም። የምትሰራው፡ ነገር፡ የላትምና፡ እናት፡ ለልጆቿ፡ ሥራ፡ አላስተማረቻቸውም። ሚስት፡ ሥራዋ፡ አሉባልታ፣ ሐሜትና፡ ወሬ፡ ብቻ፡ ሆነ። ልጆችም፡ ያለ፡ ሙያ፡ አደጉ። እንግዳዋ፡ ባልን፡ ቀርባ፡ ሚስትህ፡ አትሰራ፣ ስለማትሰራም፡ አታምርም፣ ስለምታወራም አታፍርም፣ ለመሆኑ፡ የሷ፡ ሚስትነት፡ ላንተ፡ የሚሰጠው፡ ምን፡ ጥቅም፡ አለ? ምንስ፡ ታደርግልሃለች? አለችው። ባልም፡ ልብ፡ አለ።  የእንግዳዋን፡ ሴት፡ ሙያ፡ እያደነቀ፡ ሚስቱ በስንፍናዋ፡ እያስጠላችው፡ መጣች። የውጭ፡ ሴት፡ አድንቋልና፡ ልቡ፡ ያለ፡ ከውጭ፡ ነው። ትዳሩንም፡ ፈታ። ሴቶች፡ ልጆችም፡ ለአቅመ፡ አዳም፡ ሲደርሱ፡ ሙያና፡ ሥርአት፡  ተምረው፡ አላደጉምና፡ የሚያገባቸው፡ ይጠፋል። ወንዶችም፡ ሥራና፡ ሥነ፡ ምግባርን፡ አላወቁምና፡ ሥራን፡ እራሳቸው፡ አዘጋጅተውም፡ ይሁን፡ ተቀጥረው፡ መስራት፡ አልቻሉም። ሴቶችም፡ ወንዶችም፡ ከጓደኞቻቸው፡ በታች፡ ዋሉ። እራሳቸውን፡ አሳዳጊያቸውንም፡ ጠሉ። ሞትንም፡ ሻቱ። ቤት፡ በብልህ፡ ይገነባል፡ በሰነፍም፡ ይፈርሳል። በኢትዮጵያ፡ የተፈጸመው፡ ታሪክ፡ የዚህን፡ ቤት፡ ታሪክ፡ ይመስላል።

በጥንት፡ ዘመን፡ የጥበብ፡ መፍለቅለቂያ፡ የሆነችውን፡ ኢትዮጵያ፡ በቅርቡ፡ ዘመን፡ የመጡ፣ የሚማርኩና፡ የተብለጨለጩ፡ የውጭ፡ ነገሮች፡ ገብተው፡ ሙያዋን፡ አስጥለዋታል። የውጭ፡ አገር፡ ሰዎች፡ ኢትዮጵያውያንን፡ እንዲህ፡ አሏቸው፥ እኛ፡ ብረት፡ ድስት፡ አዘጋጅተን፡ እናቀርብላችኋለን፣ የገል፡ ድስት፡ በመስራት፡ ለምን፡ ትደክማላችሁ?  እኛ፡ ገበርዲን፡ እና፡ ጀርሲ፡ አዘጋጅተን፡ እናቀርብላችኋለን፣ ጥጥ፡ በመፍተል፡ እና፡ ሸማ፡ በመስራት፡ ለምን፡ ትደክማላችሁ? እኛ፡ መኪና፡ አዘጋጅተን፡ እናቀርብላችኋለን፣ ሠረገላ በመስራት፡ ለምን፡ ትደክማላችሁ? እኛ፡ የብረት፡ ምሰሶ፡ አዘጋጅተን፡ እናቀርብላችኋለን፣ የዝግባ፡ ምሰሶ፡ በመስራት፡ ለምን፡ ትደክማላችሁ? እኛ፡ የምትተዳደሩበትን፡ ህግ፡ አዘጋጅተን፡ እናቀርብላችኋለን፣ ክብረ፡ ነገሥት፣ ፍትሃ፡ ነገሥት፡ እያላችሁ፡ ለምን፡ ትደክማላችሁ? እኛ፡ ለልጆቻችሁ፡ የምታስተምሩትን፡ ሳይንስ፡ አዘጋጅተን፡ እናቀርብላችኋለን፣ ግብረ፡ ገብነት፣ ወንጌል፣ ዳዊት፡ እያላችሁ፡ ለምን፡ ትደክማላችሁ? እንዲህ፡ እያሉ፡ ኢትዮጵያውያንን፡ የሚጣፍጥ፡ ነገር፡ አስቀመሷቸው። ኢትዮጵያውያንም፡ አዳመጡ፣ ቀመሱ፣ ተቀበሉም። የራሳቸውን፡ ናቁ፣ የሰውን፡ አደነቁ። ቤታቸውም፡ ራስን፡ በመጣል፣ በእርስ፡ በርስ፡ መናናቅና፣ በተውሶ፡ ነገር፡ ፉክክርና፡ መናቆር፡ ታመሰ። ኢትዮጵያዊነትም፡ ዋጋው፡ ረከሰ፣ ሰዎቿም፡ ሙያ፡ አጥተው፡ ወደቁ። እነሆ፡ ኢትዮጵያ፡ በዚህ፡ የትውሰት፡ ጎዳና፡ ስትጓዝ፡ በአዋሷትም፡ ተንቃ፣ በልጆቿም፡ ተንቃ፡ አውራ፡ መንገድ፡ ላይ፡ ወድቃለች። ጉልበት፡ ያላቸው፡ መንግሥታት፡ የዳር፡ ድንበር፡ ልብሶቿን፡ እጣ፡ ተጣጥለው፡ ከተቀራመቱ፡ ሰነበቱ። የምትሰራውን፡ ስለነገሯት፡ የናቋት፡ ብዙ፡ መንግሥታትም፡ የስውር፡ ወጥመድን፡ አጠመዱባት። ሰነፍ፡ ናት፡ ብለው፡ አሟት። ተሰብስበውም፡ ትከፋፈል፡ ዘንድ፡ ፈረዱባት። ኢትዮጵያ፡ ተራበች፣ ተጠማች፣ ታረዘች፣ ታሠረችም። የምንመጸውታት፡ እኛ፡ ነን፡ ብለው፡ መንግሥታትና፡ አህዛብ፡ ተሳለቁባት። ዓለም፡ በሙሉ፡ ጽዮን፡ ተራበች፡ ብሎ፡ ተረተባት። የዓለም፡ ጠቢባን፡ ስለረሃብተኝነቷ፡ ጻፉ። ጥንት፡ በንቁ፡ እምነቷና፣ በሙያዋ፡  የተከበረችው፡ ምድር፡ አሁን፡ የሰውን፡ ተውሳ፡ ተዋረደች።


የሃሳብ፡ ድርቀት።

አብዛኞቹ፡ ኢትዮጵያውያን፡ የሚሰሩትን፡ የእለት፡ ከእለት፡ ሥራ፡ በማየት፡ በአሁኑ፡ ዘመን፡ በኢትዮጵያ፡ ታስቦ፡ የሚሰራ፡ ብዙ፡ ነገር፡ እንደሌለ፡ ማወቅ፡ ቀላል፡ ነው።  ጫት፡ የሚሸጥበት፡ ሱቅ፡ መስኮት፡ ላይ፡ ብዙ፡ ጎረምሶችና፡ አዋቂዎች፡ ተሰባስበው፡ ቀኑን፡ በሙሉ፡ ወግ፡ ያወጋሉ። ከመኪና፡ መንገዱ፡ ዳር፡ እስከሱቁ፡ መስኮት፡ ድረስ፡ ያለውን፡ ቦታ፡ አረንቋ፡ የወረሰው፡ ውሃ፡ ከብዙ፡ የሰፈር፡ ቆሻሻና፡ ሽንት፡ ጋር፡ አጥለቅልቆታል። ሸቀጥ፡ ለመገብየት፡ ወደ፡ ሱቁ፡ የሚሄዱ፡ ሰዎች፡ ከአርንቋው፡ ውስጥ፡ ብቅ፡ ብቅ፡ ያሉ፡ ድንጋዮች፡ እየፈለጉ፡ በነሱ፡ ላይ፡ እየተረማመዱ፡ ወደሱቁ፡ ይጠጋሉ። የሚፈልጉትን፡ ነገር፡ ይገዙና፡ ተመልሰው፡ ድንጋይ፡ እየመረጡ፡ በመረገጥ፣ አንዳንድ፡ ጊዜም፡ አንድ፡ እግራቸው፡ አረንቋው፡ ውስጥ፡ እየተዘፈቀ፡ ወደቤታቸው፡ ይመለሳሉ። ከመኪና፡ መንገድ፡ ዳር፡ ሆኖ፡ ለሚያይ፡ ሰው፡ አረንቋው፡ አሰቃቂ፡ ነው። በሽታንም፡ ያመጣል። ባለሱቁ፡ እንኳን፡ ስለ፡ አረንቋው፡ የሚያስብ፡ አይቶት፡ የሚያውቅም፡ አይመስልም። አንድ፡ ወንዝ፡ በአንድ፡ ቀን፡ መገደብ፡ የሚችሉ፡ ጎረምሶች፡ እና፡ አዋቂዎች፡ ተሰብስበው፡ ጫት፡ እየቃሙ፡ አይናቸው፡ የሚያየው፣ ጆሯቸውም፡ የሚሰማው፡ ስለአሜሪካ፡ ብልጽግና፡ እና፡ ስለ፡ እንግሊዝ፡ የኳስ፡ ቡድኖች፡ ጨዋታ፡ ብቻ፡ እንጂ፡ በነሱ፡ ቤት፡ አረንቋው፡ የነሱ፡ ችግር፡ አይደለም። ኢትዮጵያ፡ ውስጥ፡ ማሰብ፡ የመኖሪያ፡ ቦታ፡ የለውም። ከደሃው፡ ሠራተኛ፡ እስከ፡ ከበረው፡ ሃብታም፡ ድረስ፡ የሚያስብ፡ ያለ፡ አይመስልም። የከበሩ፡ ሰዎች፡ ቢኖሩ፡ የከበሩት፡ በማሰብና፡ በማስተዋል፡ ሳይሆን፡ ኢትዮጵያ፡ ውስጥ፡ አሁን፡ ባህል፡ በሆነው፡ በንጥቂያና፡ በብልጠት፡ መንገድ፡ ነው። ማሰብ፡ በኢትዮጵያ፡ ሽታውም፣ ደብዛውም፡ የለም። ለማሰብ፡ አለመኖር፡ አንዱ፡ ምክንያት፡ ማስተዋልን፡ በሚነጥቁ፡ የኢንዱስትሪ፡ ውጤት፡ በሆኑ፡ መርዞች፡ ብዙ፡ ሰዎች፡ መበከላቸው፡ ሲሆን፡ ሌላውና፡ ዋነኛው፡ ግን፡ መሠርቷ፡ እምነት፡ የነበረው፡ ኢትዮጵያ፡ የራሷ፡ የሆነውን፡ መሠረታዊ፡ ባህልና፡ ሙያ፡ ትታ፡ እራስን፡ የሚያስንቁና፡ ጥገኝነትን፡ በሚያበረታቱ፡ የባእዳን፡ ትምህርቶች፡ መወሰዷ፡ ነው። ማስተዋል፡ የሚያስፈልገው፡ ኢትዮጵያ፡ የሌሎችን፡ ትምህርቶች፡ አልወሰደችም፤ በትምህርቶቹ፡ ተወሰደች፡ እንጂ። የውጩ፡ ትምህርት፡ የራሷን፡ ሙያ፡ አስጣላት፡ እራሱ፡ ትምህርቱ፡ ግን፡ ሙያ፡ አልሆናትም። መልካሟ፡ ኢትዮጵያ፡ እንዲህ፡ በባእዳን፡ ትምህርቶች፡ ጠፋች። የውጭ፡ አገር፡ ትምህርቶች፡ ኢትዮጵያዊውን፡ የሚያሰለጥኑት፡ ለውጭ፡ የሚስማማውን፡ ያህል፡ እስኪገራ፡ ድረስ፡ ነው።  የውጭ፡ አገር፡ ትምህርቶች፡ ኢትዮጵያዊው፡ ከነሱ፡ መንገድ፡ ውጭ፡ ወይም፡ በተለየ፡ የትምህርት፡ ጎዳና፡ እንዳይሄድ፡ ዙሪያውን፡ አጨልመውበታል። የውጭ፡ አገር፡ ሰዎች፡ አስበው፡ የአመለካከት፡ መንገድ፡ ይቀይሳሉ። ኢትዮጵያውያን፡ በዚህ፡ በሌሎች፡ በተተለመ፡ መንገድ፡ ይነጉዳሉ። በኢትዮጵያ፡ ውስጥ፡ ከውጭ፡ ተቀምረው፡ የመጡ፡ ትምህርቶች፡ በሙሉ፡ ኢትዮጵያውያንን፡ ከውጭ፡ በተተለመ፡ መንገድ፡ ብቻ፡ እንዲያስቡ፡ ያስገድዷቸዋል። ማንኛውንም፡ የውጭ፡ አገር፡ ትምህርት፡ የተማረ፡ ኢትዮጵያዊ፡ የሚያውቀው፡ ነገር፡ ቢኖር፡ በሌሎች፡ የታሰበውንና፡ የተሠራውን፡ ነገር፡ ሳያስብ፡ መቀበልን፡ ብቻ፡ ነው። የትምህርት፡ ፈተናዎቹም፡ የውጭ፡ ሰዎች፡ አስበው፡ ያመጡትን፡ ጉዳይ፡ አንድ፡ ኢትዮጵያዊ፡ ምን፡ ያህል፡ እንደለመደው፡ ማመሳከሪያዎች፡ እንጂ፡ ኢትዮጵያዊውን፡ የሚያሻሽሉ፡ ወይም፡ እውነተኛ፡ ችሎታውን፡ የሚለኩ፡ አይደሉም። ውሻ፡ ሰው፡ ለሚያደርገው፡ አደን፡ አሰልጣኙን፡ እንዲያገለግል፡ እንደሚሰለጥን፡ በሌሎች፡ ተዘጋጅቶ፡ የመጣን፡ ሃሳብ፡ ለማነብነብ፡ የሚደረግ፡ ሥልጠናም፡ እንዲሁ፡ ውጤቱ፡ የማታ፡ የማታ፡ አሰልጣኙን፡ ማገልገል፡ ብቻ፡ ነው።

የሳይንስና፡ የህብረተሰብ፡ ትምህርት፡ እየተባሉ፡ በትምህርት፡ ቤቶች፡ የሚሰጡ፡ ትምህርቶች፡ ቋንቋን፡ በውጭ፡ አገር፡ ስሞችና፡ አጠራሮች፡ ከማጨቅ፡ ያለፈ፡ ጥቅም፡ ለኢትዮጵያ፡ አልሰጡም። ፒሬዲክ፡ ቴብል፡ ተዘጋጅቶ፡ ኢንዲየም፣ ፌርሚየም፣ ካሊፎርኒየም፣ ኤንስታይኒየም፣ ጋልየም፣ ሞሊብዲነም፣ ይትሪየም፣ ሎውረንሲየም፣ ዳርምስታድትየም፡ እየተባለ፡ ኢትዮጵያዊው፡ ሊጠበብባቸውም፡ ሆነ፡ አስተካክሎ፡ ስማቸውን፡ ሊጠራቸው፡ የማይችል፡ የኤለመንቶች፡ ዝርዝር፡ ከሚታቀፍ፡ በሰፈሩ፡ ያሉትን፡ ነገሮች፡ በራሱ፡ ጥረት፡ ፈልጎ፡ አግኝቶ፣ ኢትዮጵያዊ፡ ስም፡ ሰጥቶ፡ ቢያውቃቸው፡ ለኢትዮጵያዊው፡ ይበጀው፡ ነበር። በእንግሊዝኛ፡ ኤለመንቶች፡ የሚባሉት፡ የራሳቸው፡ አካል፡ የሆኑ፡ የተፈጥሮ፡ ነገሮች፡ መኖራቸውን፡ እንኳን፡ የኢትዮጵያ፡ ቋንቋዎች፡ አያውቁትም፤ ምክንያቱም፡ ነገሮቹ፡ ከውጭ፡ ተዘጋጅተው፡ የውጭ፡ ስም፡ ተሰጥቷቸው፡ ስለሚመጡና፡ ኢትዮጵያዊው፡ ድረሻው፡ የተዘጋጀለትን፡ መቀበል፡ ስለሆነ፡ ስለ፡ ጉዳዩ፡ የጠለቀ፡ እውቀት፡ አይኖረውም። እውቀት፡ ማለት፡ ስለ፡ እቃው፡ የውጭ፡ ሰዎች፡ ያገኙትን፡ ነጠላ፡ ክብደት፣ የሚቀልጥበት፡ ሙቀት፣ ከሌሎች፡ እቃዎች፡ ጋር፡ ቢገናኝ፡ ምን፡ እንደሚሆን፡ እና፡ የመሳሰሉትን፡ መልሶ፡ ማወቅ፡ ሳይሆን፡ ጉዳዩ፡ ኢትዮጵያን፡ ወደሚጠቅም፡ ነገር፡ መቀየር፡ ማለት፡ ነው። ሌሎችም፡ የትምህርት፡ አይነቶች፡ እና፡ ከውጭ፡ የሚመጡ፡ ውጤቶች፡ የሚያስከትሉት፡ ይህንኑ፡ በገደል፡ ማሚቶነት፡ የተሸፈነ፡ ድንቁርና፡ እና፡ የኢትዮጵያዊ፡ የጥበብ፡ ቅርስ፡ መጥፋትን፡ ነው። በተለይ፡ የህብረተሰብ፡ ሳይንስ፡ የሚባሉ፡ ትምህርቶች፡ ደግሞ፡ በቀጥታ፡ ኢትዮጵያዊው፡ ኢትዮጵያን፡ እንዳይጠቅም፡ የሚያደርጉ፣ የሚጨበጥ፡ ፍሬ፡ ሳይኖራቸው፡ የሚጨበጠውን፡ የኢትዮጵያ፡ ፍሬ፡ በትረካ፡ ብዛት፡ ደብዛውን፡ የሚያጠፉ፡ ማደናቆሪያዎች፡ ናቸው። ሳይኮሎጅ፣ ሶሲዮሎጅ፣ ፍልስፍና፣ ህግ፣ የፖለቲካ፡ ሳይንስና፡ የመሳሰሉት፡ በትምህርት፡ ተቋማት፡ የሚሰጡ፡ ትምህርቶች፡ ኢትዮጵያዊ፡ ስም፡ ካላመኖራቸው፡ ጀምሮ፡ ኢትዮጵያዊ፡ ጥበብን፡ እስከማስጣላቸው፡ ድረስ፡ ከጉዳት፡ በቀር፡ ለኢትዮጵያ፡ ያስገኙት፡ ትርፍ፡ አለ፡ ብሎ፡ መናገር፡ ያስቸግራል።

ኢትዮጵያዊው፡ የሚማረክባቸው፡ የውጭ፡ ምርቶችም፡ የሚያደርሱት፡ ጉዳት፡ ቀላል፡ አይደለም። ለምሳሌ፡ አንድ፡ የኦፔል፡ መኪና፡ ወደ፡ ኢትዮጵያ፡ ሲገባ፡ የገባው፡ የውጭ፡ ሥራ፡ ውጤት፡ የሆነ፡ ምርት፡ ነው። ኢትዮጵያዊው፡ ይህን፡ የኦፔል፡ መኪና፡ ሲነዳ፡ ደስ፡ ይለዋል። መኪናውን፡ ሲነዳ፡ ዘመዶቹ፡ እና፡ የሚያውቁት፡ ሰዎች፡ እያዩ፡ ከፍ፡ ያለ፡ ክብር፡ ይሰጡታል። ከርቀት፡ የሚያዩ፡ ሰዎችም፡ ቀረብ፡ ብለው፡ ጓደኛና፡ ወዳጅ፡ ለመሆን፡ በአካባቢው፡ ያንዣብባሉ። መኪናው፡ እንዲሽከረከር፡ ነዳጅና፡ ዘይት፡ እንዲሁም፡ የመለዋወጫ፡ እቃዎች፡ ያስፈልጉታል። እነዚህ፡ እቃዎች፡ የሚገዙት፡ ደግሞ፡ የኢትዮጵያ፡ መንግሥት፡ የኢትዮጵያ፡ ገበሬዎች፡ የሚያመርቱትን፡ የእርሻ፡ ውጤት፡ ሰብስቦ፣ እንዲሁም፡ በኢትዮጵያ፡ የሚገኙ፡ ከብቶችን፡ ሰብስቦ፣ ወርቅና፡ ንጥረ፡ ነገሮችም፡ ቢኖሯት፡ ሰብስቦ፣ እነዚህን፡ ሁሉ፡ ለውጭ፡ ሰዎች፡ በጥቂት፡ ዋጋ፡ ሸጦ፡ በውድ፡ ዋጋ፡ ነዳጅ፣ የሞተር፡ ዘይትና፡ የመኪና፡ መለዋወጫ፡ ይገዛል። ባለ፡ ኦፔሉ፡ ኢትዮጵያዊ፡ ገበሬዎቹ፡ ዘመዶቹ፡ ያፈሩትን፡ ምርት፡ እሱ፡ ነዳጅና፡ ዘይት፡ አድርጎ፡ መኪናዋን፡ ይመግባል። በሌላ፡ አገላለጽ፡ የኢትዮጵያ፡ ገበሬዎች፡ በእርሻ፡ የሚያመርቱት፡ አዲስ፡ አበባ፡ ያለው፡ ጮሌው፡ ወንድማቸው፡ ምርታቸውን፡ በነዳጅ፡ ቀይሮ፡ መጠጥ፡ ቤት፡ ለመጠጥ፡ ቤት፡ እንዲንሸራሸርበት፡ ነው፡ እንደማለት፡ ነው። ጮሌውን፡ የሚያዩ፡ ሁሉ፡ እንደጮሌው፡ ለመሆን፡ ስርቆትና፡ ማምታታት፡ ይጀምራሉ። ይህም፡ ከወረርሺኝ፡ በሺታ፡ በበለጠ፡ ክፋት፡ ኢትዮጵያን፡ አዝቅጧት፡ እናያለን። በእርግጥ፡ የጭነት፡ መኪናዎችም፡ ከከፍለሃገር፡ ክፍለሃገር፡ እቃዎችን፡ ለማመላለስም፡ ነዳጁን፡ ይጠቀማሉ፤ ዋናው፡ ነጥብ፡ ነዳጁን፡ መልካም፡ ነገር፡ ለመሥራትም፡ የሚጠቀሙበት፡ መኖራቸው፡ አይደለም። ቁምነገሩ፡ እያንዳንዱ፡ ሊትር፡ ነዳጅ፡ ቢያንስ፡ የአንድ፡ ገበሬ፡ የወራት፡ ምርት፡ የፈሰሰበት፡ መሆኑና፡ ኢትዮጵያዊው፡ የሚበላው፡ የሌለው፡ እስኪሆን፡ ድረስ፡ የቅንጦት፡ ሱስ፡ አስተናጋጅ፡ መሆኑ፡ ነው።

ትንሽ፡ ቀለል፡ ባለ፡ መንገድ፡ ጉዳዩን፡ እንየው። የውጭ፡ አገር፡ ሰዎች፡ የኢትዮጵያን፡ ፍሬዎች፡ ፈለጉ፤ ነገር፡ ግን፡ ፍሬዎችን፡ ለማግኜት፡ ፍሬ፡ ያለውን፡ ንብረታቸውን፡ እንደመገበያያ፡ አድርገው፡ ለማቅረብ፡ አልፈለጉም። ይልቁንስ፡ ኢትዮጵያዊውን፡ ለሱሰኝነት፡ አሰለጠኑትና፡ ሱሰኛ፡ ሆነ። እነሆ፡ ኢትዮጵያ፡ ውስጥ፡ የሚፈልጉትን፡ ነገር፡ ለመውሰድ፡ በኢትዮጵያ፡ ፍላጎት፡ ፈጥረዋል፣ እሱም፡ የማይጠቅም፡ ነገር፡ ሱሰኝነት፡ ነው። ኢትዮጵያዊው፡ የሰባውን፡ በሬውን፡ ይሰጥና፡ የሱስ፡ እጽ፡ ይመጣለታል። ከመቶ፡ ዓመት፡ ወዲህ፡ የምናየው፡ የኢትዮጵያ፡ ኤኮኖሚ፡ የሚባለው፡ ይሄው፡ ነው። በሙያ፡ ማነስ፡ ምክንያት፡ የመሠረታዊ፡ ምርቶች፡ አቅርቦት፡ ባነሰበት፡ ቦታ፡ እሱኑ፡ በብዙ፡ ቀንሶ፡ በሱስ፡ ፍጆታ፡ ከመቀየር፡ የበለጠ፡ ድንቁርና፡ ምን፡ አለ?

የኦፔል፡ ጉዳቱ፡ የአገርን፡ ምርቶች፡ ከማራቆት፡ ላይ፡ አያቆምም። የውጭ፡ አገር፡ ሰዎች፡ ኦፔሉን፡ ሲሰሩ፡ ሰዎቻቸው፡ ተሰባስበው፡ መኪናው፡ እንዴት፡ እንደሚሽከረከር፡ ይመክራሉ፣ ሃሳብ፡ ይለዋወጣሉ፣ በፍጥነት፡ ሲሽከረከር፡ እንዳይገለበጥ፡ ለማድረግ፡ ብልሃቱን፡ ለመግኜት፡ ሰዎቻቸው፡ ያስባሉ። ሙከራዎችን፡ ያደርጋሉ። መኪናው፡ ምቾት፡ እንዲኖረው፡ ለማድረግ፡ ብልሃት፡ እንዲሰሩ፡ የሚመደቡ፡ አሉ። መኪናው፡ እየበረረ፡ ሲሄድ፡ ከፊት፡ ለፊቱ፡ የሚጋረጥ፡ ነገር፡ ቢመጣ፡ ፍጥነቱን፡ የመቀነሻና፡ የማቆሚያ፡ ብልሃትን፡ የሚያፈልቁ፡ ለዚህ፡ የሚመደቡ፡ አሉ። መኪናው፡ ሲያዩት፡ እንዲያምር፡ የሚያደርገውን፡ ብልሃት፡ የሚፈልጉ፡ አሉ። ሁሉም፡ በሚሠሩት፡ ሥራ፡ አዳዲስ፡ ነገሮች፡ ስለሚያጋጥሟቸው፡ እነዚህን፡ አዳዲስ፡ ነገሮች፡ ለሠሪዎቹ፡ የሚስማማ፡ ስም፡ ይሰጧቸዋል። ለመኪናዎቹ፡ የሚሆን፡ ቀለም፡ የሚያቀርቡ፡ ሰዎች፡ ደግሞ፡ በዚሁ፡ በውጭ፡ አገር፡ ይፈጠራሉ። መስታዎቶችንም፡ ሠርተን፡ እናቀርባለን፡ የሚሉ፡ ይቀርባሉ። ጎማዎቹንም፡ ሠርተን፡ እናቀርባለን፡ የሚሉ፡ ይቀርባሉ። የሚሠራው፡ ሥራ፡ ብዙ፡ መተባበርን፡ የሚጠይቅ፡ በመሆኑ፡ የትብብር፡ ስምምነት፡ ያደርጋሉ። በትብብር፡ ስምምነቱ፡ አንዳንዶቹ፡ በቃላቸው፡ ሳይገኙ፡ ከቀሩ፡ እንዲህ፡ የሚያደርጉ፡ ሰዎችን፡ በህግ፡ የሚጠይቁበት፡ ደንብ፡ ይሰራሉ። መኪናዎቹንም፡ ለገበያ፡ ለማቅረብ፡ እኛ፡ እናስተዋውቃለን፡ የሚሉ፡ ነጋዴዎችም፡ ይመጣሉ። እንደምናየው፡ አንድ፡ መኪና፡ ለመሥራት፡ እጅግ፡ ብዙ፡ የሆኑ፡ የውጭ፡ ህብረተሰብ፡ የሰዎች፡ የሰንሰለት፡ ግንኙነት፡ ተፈጥሮ፡ በብዙ፡ መንገድ፡ ብዙ፡ አዳዲስና፡ በየጊዜው፡ የሚሻሻልን፡ ነገር፡ ይዘው፡ ይቀርባሉ። የኦፔሉ፡ አገር፡ ቋንቋም፡ እነዚህን፡ አዳዲስ፡ የሚፈጠሩ፡ የሥራ፡ አይነቶች፡ እና፡ በሥራ፡ ላይ፡ ያሉ፡ ችግሮችን፡ የሚገልጹ፡ አዳዲስ፡ ቃላቶች፡ እና፡ ምሳሌዎችን፡ ያፈራል። እውቀትም፡ ይዳብራል። መኪናው፡ መኪና፡ ሆኖ፡ ከመውጣቱ፡ ይልቅ፡ መኪናውን፡ ለመሥራት፡ የተደረገው፡ ርብርብ፡ እና፡ ጉዞ፡ የውጭ፡ አገር፡ ሰዎችን፡ ገንብቷል።

ኦፔሉ፡ መኪና፡ ኢትዮጵያ፡ ውስጥ፡ ሲገባ፡ መኪናውን፡ ለመሥራት፡ የፈሰሰው፡ የብልሃት፡ መንገድ፣ ችግሮቹ፣ የችግሮቹ፡ መፍትሄዎች፣ ግንኙነቶቹ፣ ቃላቶቹ፣ ምሳሌዎቹ፣ እውቀቶቹ፡ ሁሉ፡ የሉም። ኢትዮጵያዊው፡ ተመሳሳይ፡ ነገር፡ ሰርቶ፡ ሞቅ፡ ያለ፡ የሥራ፡ ሰንሰለት፡ ግንኙነት፡ እንዳይኖር፣ ህብረተሰቡን፡ እንዳያዳብር፣ በሥራ፡ ላይ፡ የሚያጋጥማቸውን፡ ችግሮችን፡ አውቀው፡ መፍትሄያቸውን፡ እንዳያዘጋጁ፣ ቋንቋውና፡ ባህሉ፡ በሥራ፡ እንዳይዳብር፣ ለትውልድ፡ የሚሆኑ፡ ከሥራ፡ ልምድ፡ የተገኙ፡ ምሳሌዎችን፡ እንዳያፈሩ፡ ተዘጋጅቶ፡ የመጣው፡ ኦፔል፡ ያግዳቸዋል። አሁን፡ ሁሉም፡ እንደሚያየው፡ የኢትዮጵያ፡ ድርሻ፡ ብልጽግናን፡ በማሰብና፡ በሥራ፡ ከማምጣት፡ ይልቅ፡ የውጭ፡ አገር፡ ሰዎች፡ የተጠበቡበትን፡ መግዛት፡ ብቻ፡ ነው። በዚህ፡ የተዘጋጀ፡ በመቃረምና፡ ሳያስቡ፡ በመኖር፡ ጎዳና፡ ስትሄድ፡ የራሷ፡ ሙያ፡ ያጣች፡ ሆና፡ ወድቃለች። ሸቀጣቸውን፡ የሚያራግፉባትም፡ በሙያ፡ ቢስነቷ፡ ከናቋትና፡ ካፌዙባት፡ ቆይተዋል።  ኢትዮጵያ፡ አሁን፡ ያሏት፡ የጥበብ፡ ምሳሌዎች፡ እንኳን፡ ሳይቀር፡  ጥንት፡ የራሷን፡ ሥራ፡ ስትሠራ፡ የተገኙት፡ ብቻ፡ ናቸው። ቤቷ፡ በውጭ፡ የተውሶ፡ ትምህርት፡ ከተወረረ፡ ወዲህ፡ በኢትዮጵያ፡ ሌላው፡ ቀርቶ፡ ለትልውድ፡ የሚሆኑ፡ የጥበብ፡ ምሳሌዎች፡ ተፈጥረውባት፡ አያውቁም።                   

እንግዲህ፡ ማሰብ፡ ሥራን፡ የሚፈጥር፣ በቀላል፡ ወጭ፡ ብዙ፡ ትርፍን፡ የሚያስገኝ፡ ጸጋ፡ በመሆኑ፡ ኢትዮጵያውያን፡ ተዘጋጅቶ፡ የመጣን፡ መቃረም፡ ትተው፡ እያሰቡ፡ እንዲሰሩ፣ አካባቢያቸውንም፡ እንዲያስተውሉ፡ የሚያስችል፡ ኢትዮጵያን፡ በሚጠቅም፡ መንገድ፡ የተነደፈ፡ ኢትዮጵያዊ፡ ትምህርት፡ በትምህርት፡ ቤቶች፡ ሊሰጥ፡ ይገባዋል። በግ፡ እንደ፡ ፍየል፣ ላም፡ እንደ፡ አህያ፣ አንበሳ፡ እንደ፡ ጭልፊት፣ ዶሮ፡ እንደ፡ ወፍ፣ ፈረስ፡ እንደ፡ ግመል፡ ልኑር፡ ቢሉ፡ ኑሯቸው፡ ይበላሻልና፡ ኢትዮጵያውያንም፡ እንደራሳቸው፡ እንጅ፡ እንደ፡ ሩቅ፡ አገር፡ ሰዎች፡ እንኖራለን፡ ሲሉ፡ ኑሯቸው፡ አያምርም። ኑሮን፡ ማሻሻልና፡ እድገትን፡ መሻት፡ መልካም፡ ነገር፡ ሲሆን፡ እድገትን፡ መሻት፡ በኢትዮጵያዊ፡ መንገድ፡ እንጂ፡ በትውስት፡ መንገድ፡ መሆን፡ የለበትም። ለምሳሌ፡ የእግር፡ መንገድ፡ አድክሟቸው፡ ኢትዮጵያውያን፡ የሚሽከረከር፡ ወይም፡ ከቦታ፡ ቦታ፡ ሳይደክሙ፡ የሚያጓጉዛቸው፡ ነገር፡ ቢሹ፡ ተሸካሚውን፡ እራሳቸው፡ መሥራት፡ አለባቸው፡ እንጂ፡ ከውጭ፡ ተሰርቶ፡ ቢመጣ፡  መጓጓዣ፡ ከማጣት፡ የከፋ፡ ውድቀትን፡ ያስከትልባቸዋል። ተሸካሚው፡ ማጓጓዣ፡ መኪና፡ ቢሆን፣ መኪናም፡ በነጻ፡ የሚሰጥ፡ እንኳን፡ ቢሆን፡ ኢትዮጵያውያንን፡ ይጎዳል፡ እንጂ፡ አይጠቅምም።  ጎማውን፡ እንደገና፡ መፍጠር፡ አይጠቅምም፡ የሚለው፡ የውጭ፡ ተረት፡ ተስማሚነቱ፡ ጎማውን፡ ለፈጠሩት፡ እንጂ፡ ለኢትዮጵያውያን፡ አይደለም። የውጭ፡ ሰዎች፡ በጎማው፡ ተሻሽለው፡ ከሆነ፡ እድገትን፡ ያገኙት፡ ጎማ፡ እንድ፡ ውጤት፡ ሆኖ፡ ስለቀረበላቸው፡ ሳይሆን፡ ጎማውን፡ ለመፍጠር፡ ባደረጉት፡ ጉዞ፡ ነው። ኢትዮጵያውያን፡ መልካም፡ ኑሮን፡ እንዲጎናጸፉ፡ ከዚህ፡ ቀደም፡ መልካም፡ ኑሮን፡ ካጎናጸፏቸው፡ የራሳቸው፡ ከሆኑ፡ ጉዳዮች፡ ጉዟቸውን፡ መጀመር፡ አለባቸው።  እነዚህንም፡ በዝርዝር፡ እግዚአብሔር፡ በፈቀደ፡ ወደፊት፡ እናያለን።


እግዚአብሔር፡ የተመሰገነ፡ ይሁን።

*********************************
ምንጭ:--
፩ . ግብይት፡ በአቢሲኒያ፣ ኒው፡ ዮርክ፡ ታይምስ፣ መጋቢት፡ ፴ ቀን፡ ፲፱፻፪ ዓ.ም.

. ሚሊዮኑ፣ ገጽ፡ ፪፻፹፭፡ ሮስቲሸሎ፡ ዳ፡ ፒዛ፡ በ፲፪፻፺፩ እንደጻፈው፣ ማርኮ፡ፖሎ፡ እንዳስጻፈው
http://www.oftsion.org/Education.html
 

ዓርብ, ማርች 18, 2016

ከመጻሃፍት ዓምባ

እንዳለጌታ ያቆመው የበዓሉ ግርማ ሀውልት _ደረጀ በላይነህ

*********************************************************************
 በዓለም ታሪክ፣በትውልድ ሰማይ ላይ የፈኩ፣ የማይረሱ ኮከቦች አሉ፣በሰው ልብ የሚነበቡ በጠመኔ ተጽፈው የሚነድዱ፡፡ ዘውድ-አልባ ነገስታትም እንደዚሁ! … ታላላቅ ፖለቲከኞች፣ ደራሲያንና ሳይንቲስቶች ዘመን ዘልቀው፣ አድማስ ርቀው ይታያሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ ብርቅዬዎች  እንደሚቆረጠም እንባ፣እንደሚፈለጥ ደም እንቆቅልሽ ሆነው፣ አሊያም በታሪካቸው ድምቀት እንደ ገነት አበባ በጽድቅ አረፋ ተሞሽረው ከወረቀት ወደ ልባችን ሊመጡ ይችላሉ-እንደየዕጣቸው፡፡
እኛ ሀገር የጥበብ ብርሃን ከፈነጠቁት፣ ዕውቀትና ውበት እንደ ሽቶ ካርከፈከፉት፣ግን ደግሞ በእንባ ሸለቆ ውስጥ በሰቀቀን ዐመድ ለብሰው ከቀሩት መሀል ደራሲ በዓሉ ግርማ አንዱና ደማቁ ነው፡፡ በዓሉ በመጽሐፍቱ በነፍሳችን ጎጆ የቀለሰ፣ በልባችን በፍቅር የታተመ ታላቅና ተወዳጅ ደራሲ ነው፡፡ ምናልባትም አንዳንዶቻችን ውስጥ በጥበብ እርሻ የዘራና የወለደ አባት ነው፡፡
ታዲያ መቃብሩን ያላየነው፣በነፍሳችን እየባዘንን በትካዜ ፉጨት የፈለግነውን ይህን ደራሲ ወጣቱ ፀሐፊ እንዳለጌታ ከበደ አራት ዓመታት ያህል ከሕይወቱ ቆርሶ ሮጦና ላቡን ጠብ አድርጎ፣ ካገር አገር ተንከራትቶ አዲስ ዱካ፣ በ440 ገጾች ጠርዞ “በዓሉ ግርማ ሕይወቱና ሥራዎቹ” በሚል ርዕስ ይዞልን መጥቷል፡፡
ይህ መጽሐፍ በዓሉ ግርማ ለህፃንነቱ የተሰጠውን የተፀውዖ ስም መነሻና ትርጉም በማነፍነፍ ያልገመትነውን መልስ ሁሉ የሚሰጥ ነው፡፡ “በዓሉ” ማለት ምንድነው? … በምን ቋንቋ ወዘተ … ብሎ የሚነግረን ከግምታችን ራቅ የሚል ነው፡፡ የበዓሉ አባት ማናቸው? … ግርማስ ማነው? … የሚለው ጥያቄ መልስ ከዚህ ቀደም በመገናኛ ብዙኃን ከተወሩት ፈቀቅ ይላል! …
ሱጴ ቦሮ የተወለደው በዓሉ ግርማ በበርካታ መጽሐፍቱ በውበት የሚጋልባቸው የአማርኛ ቃላትና ዐረፍተ ነገሮች አንደበቱ ሳይገቡ በፊት የስነ ትምህርት ምሁራን “የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ዕድሜ” በሚሉትና የሥነ ልቡና ምሁራን “gang age” የቡድን ዕድሜ በሚሉት መሟጠጫ ከኦሮሚፋ በስተቀር አንዳች መናገር ሳይችል ነበር አዲስ አበባ የመጣው-በ14 ዓመቱ፡፡ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ሕንዳዊው አባቱ ያቀጨመበት ፊት፣ የሕንዳዊው ሰራተኛ የሆነው ተቀጣሪ በዓሉን በፍቅር ለማሳደግ ሲወስደው፣ ከገጠር /ከሱጴ ቦሮ/ የመጡት ሰዎች ጥለውት ሲሄዱ፣  … ለከተማው ባይተዋር የሆነ ልጅ በማያውቀው ከተማና አውድ፣ በማያውቀው ማህበረሰብ ውስጥ ለብቻው ሲቀር ምሽቱን እንዴት ያድር ይሆን? … ለኔ ከባድ የሕይወት ፈተና ይህ ነው፡፡  በዓሉ ግርማ ይህንን ፅዋ ቀምሷል፡፡ልጅነቱ ምስቅልቅል፣ ስነ-ልቡናው ዝንጉርጉር ነው፡፡  የበዓሉ ግርማ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ በሰለጠነውና በተሻለው የአፃፃፍ መንገድ የተፃፈ ነው፡፡ የህይወት ታሪክ አፃፃፍ፣ በአርስጣጣሊስ ዘመን ተጀምሮ በአፍላጦን እየዳበረ ሺህ ዓመታት  ይግፋ እንጂ በእንግሊዝኛ “Biography” የሚለውን ቃል አብሮ የተጠቀመው እንግሊዛዊ ገጣሚ ጆን ድራይደን ነው፡- በ1683 ዓ.ም፡፡ ታዲያ ይዘቱም የተለየ ስራ የሰሩ ሰዎችን ታሪክ የሚተርክ ነበር፡፡ “The History of practical men’s lives” ይህም ማለት አንደኛ ስራ የሰሩ፣ የጎላ ታሪክ፣ የዳጎሰ ትዝታ ያላቸውን ማለት ነው፡፡
እንዳለጌታ ከበደ ከዚህኛው ወደዘመነው ከሃያኛው ክፍለ ዘመን፣ ወዲህ በተጀመረው የህይወት አፃፃፍ ይትበሃል በመጠቀም የባለታሪኩን አካላዊ ብቻ ሳይሆን ስነ ልቡናዊና ማህበራዊ፣መልክዐ-ምድራዊ ዐውድ ሳይቀር ፈልፍሎ በማውጣት፣ ሰውየውን እንደ ስጋ ለባሽ እንጂ እንደ መለኮት በማይታይበት ሁኔታ ጽፎታል፡፡
ለመርማሪ አንባቢ ገና የሚዘረዘሩና የሚላጡ ትንተናዎችን የሰጠ ይመስለኛል፡፡ በርግጥም ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሕይወት ታሪክና የግለ ታሪክ አፃፃፍ መልክ በዚህ ተቀይሯል፡፡ ግን ደግሞ በሃገራችንስ የጻፉ ሁሉ መች ተጠቀሙበት!...እንዳለጌታ ግን የእንስትዋ ፀሐፊ ዶክተር ካትሪኒ ሀንተርን መርህ ተግባራዊ አድርጓል፡፡ የልጅነት ሕይወትን መዳሰስ ግድ እንደሚል ያሰመሩበትን ደመቅ አድርጎ ተጠቅሞበታል፡፡
 መረጃ ፍለጋ ጓዳ ጎድጓዳውን ባክኗል፣ የበርካታ ቢሮዎችን ደጃፍ ረግጧል፡፡ አያሌ ሰዎችን ደጅ ጠንቷል፡፡ … የህይወት ታሪክን የሚፅፍ ሰው ችግሮች ከሚቸገርባቸው ነገሮች አንዱ ታሪኩ የሚፃፈው ሰው በህይወት ያለመኖር ነው፡፡ ለምሳሌ በዓሉ ግርማ በሕይወት ቢኖር እንዳለጌታ ከበደ ብዙ ቦታ የሮጠባቸውን ሀሳቦች በቀላሉ ያገኝ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ የዕለት ማስታወሻዎች፣ ሰዎች ጋር የቀሩ ጽሑፎች፣ የግል ገጠመኞች፣ ውስጣዊ ሕልሞችና ሌላ ሰው ያልሰማቸው ፈተናዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
ይሁንና እነዚህን ሁሉ ዋጋ ከፍሎ ሰርቷቸዋል፡፡ ለምሳሌ በመጽሐፉ ውስጥ የተካተተው የተወዳጅዋ ድምፃዊት ብዙነሽ በቀለና የበዓሉ ግርማ አስደማሚ የፍቅር ታሪክ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡ በእጅጉ የሚደንቅና የሚያጓጓ የታላላቅ ሰዎችን ተሰጥዖና ክህሎት ያለፈ ማንነት ጉልህ አድርጎ የሚያሳይ፣ ልብን በፈገግታ ሻማ የሚለኩስ ነው፡፡ ምናልባትም መጽሀፉ ውስጥ ያሉትን አሳዛኝ ድባቦች ወደ ፍልቅልቅ የፍቅር አውድ የሚቀይር ነው፡፡ ለኔ ልዩና ድንቅ ነው፡፡
ለምሳሌ ስለዚህ ዕጹብ-ድንቅ ፍቅር እንዳለጌታ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉን አነጋግሯቸው እንዲህ ብለውታል፡-‹‹ሁለቱ እጅ ለእጅ ተያይዘው፣እንደ ጣሊያኖቹ …በየመንገዱ ሲላፉ፣ ሲሳሳቁ…  በሚያስቀና ስሜት ሆነው በርጋታ ወክ ያደርጉ እንደነበር ሁልጊዜ ትዝ ይለኛል-የእሷን ዘፈን በሰማሁ ፣የእሱን መጽሃፎች ባነበብኩ ቁጥር›› (ገጽ 121)
እንደ ባለ ህልም እንዳለጌታ ከጊዜ ጋር ባይሽቀዳደምና ዛሬ እማኝነት የሰጡ ሰዎች ቢያልፉ ኖሮ ይህ ድንቅ እውነታ ከእግራችን ሥር ሾልኮ - ነበር፡፡ ኪሮስ ወልደሚካኤልን አስሶ ማግኘቱ የሚያስመሰግነውና የሚያስደንቀው ነው፡፡ ሊመሰገንና ሊደነቅ ይገባል! ከላይ እንደጠቀስኩት የተሻሻለው የሕይወት ታሪክ አፃፃፍ የግለሰቦችን ታሪክና አካባቢ ብቻ ሳይሆን እግረመንገዱን የዘመኑን ማህበረ-ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መልክ፣ የማህበረሰብና የህብረተሰቡን እምነትና ሥነ ልቡና ስለሚያሳይ ከበዓሉ ህይወት ጋር አጣምረን የኢትዮጵያን ውስጣዊና ውጫዊ ሥዕል ቃኝተናል። ለታሪኩ ምስክር ይሆኑ ዘንድ የተመረጡትን ጎምቱ የሀገር ልጆች አስተሳሰብና ስነ - ልቡናም ገምግመናል፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ በዓሉ ግርማ ሰው ነው፤ በዓሉ ደራሲ፣ ጋዜጠኛ፣ ባለስልጣን ነው፡፡ በዓሉ ዝነኛ ነው፣ በዓሉ ምስኪንም ነው፡፡ ለምሳሌ ከብዙነሽ በቀለ የፍቅር ጉዞ በኋላ የልጆቹን እናት ወ/ሮ አልማዝ አበራን ሲያገባ ገንዘብ አጥሮት ከመስሪያ ቤቱ ብር ተበድሮ ደግሷል፡፡ ይህንን ደግሞ ያደረገው ለባለቤቱ ካለው ታላቅ ፍቅር የተነሳ ነበር፡፡ ባለቤቱ ከቀደመው ባለቤቷ ልጆች ያሏት ቢሆንም ያገባት ግን በልጃገረድ ወግ ነበር፡፡ … በዓሉ ድንቅ ሰው ነው፡፡ ገጽ 129 ላይ እንዲህ ይላል። ‹‹ያኔ የጋብቻ ስነ-ስርዐታቸው የተፈጸመውና አልማዝ የተሞሸረችው ‹በልጃገረድ ደንብ ነው› በልጃገረድ ደንብ መሆኑ በዘመኑ የነበሩትን ያስገረመና በዓሉ ለአልማዝ ያለውን ፍቅር በገቢር የገለጠበት ነበርም ይባላል፡፡…” እንዳለጌታ ከበደ የበዓሉን የህይወት ታሪክ ሲፅፉ በዘመን አንጓ ሸንሽኖ ነው፡፡ ለምሳሌ ከልጅነቱ እስከ ጉብዝናው ያለውን “ማለዳ” ብሎታል፡፡ ከማህበራዊ ህይወቱ እስከሙያዊ አበርክቶቱ ያለውን ቀትር “የሚል ስያሜ ሰጥቶታል፡፡ “ምሽት” (ሩቅ አልሞ ቅርብ ያደረው ቀዩ ኮከብ) ወዘተ እያለ ተርኮታል፡፡
እንደደራሲ በዓሉ የፃፋቸውን ስድስት ያህል መፃህፍት ለመተንተን ሞክሯል፡፡ በተለይ “የሕሊና ደውል” እና “ሀዲስ” የሚመሳሰሉበትንና የሚለያዩበትን መንገድ ጥናታዊ ጽሑፎችን ዋቢ አድርጎ አሳይቷል። በህይወቱ ላይ ጣጣ ያመጣውን “ኦሮማይ”ን፣ የደራሲነትን ህይወት ፍንትው አድርጎ የሚያሳየውን “ደራሲው”ን ከ “አድማስ ባሻገር”ንና በመስሪያ ቤት ባላንጣዎቹ ዳግም እንዳይታተም ዕድል የተነፈገውን “የቀይ ኮከብ ጥሪ”ን በሚገባ ቃኝቷቸዋል፡፡
ሌላው እንዳለጌታ አንባቢዎቹን የሞገተበት ጉዳይ በዓሉ ግርማ በውኑ አለም ያሉትን ሰዎች ቀድቶ ይጠቀምባቸዋል  የሚለውን ሀሳብ ነው። ለዚህም በዓሉ ግርማ ብቻ ሳይሆን በሀገራችን ሀዲስ አለማየሁ፣ ጳውሎስ ኞኞና ብርሃኑ ዘርይሁን መሰል ልምምድ እንደነበራቸው ማስረጃ ጠቅሷል፡፡ ያ ብቻ ሳይሆን በዓሉ አንድን ሰው በቀጥታ መውሰድ ሳይሆን፣ ከአንድ ሰው አንድ ነገር ቢወስድም፣ ታሪኩ ውስጥ በሚኖረው ቦታና ሚና ግን የዚያን ሰው ህይወት ወርሶ እንደማይኖር አስረድቷል፡፡ እኔም በዚህ ቦታ እንዳለጌታን እደግፈዋለሁ፡፡ ትልቁ ሌዎ ቶልስቶይስ ቢሆን ዙሪያውን ያሉ ሰዎችና ቤተሰቦች አይደል ገፀ ባህሪ አድርጎ የሳለ! … ምርጡ አሜሪካዊ ደራሲ ኧርነስት ሄሚንግዌይ! … ኖቤል የተሸለመው‘ኮ ኩባ ባህር ዳርቻ ያለውን ዓሳ አጥማጅ ሕይወት ሥሎ ነው። ኧረ ብዙ አሉ! … እንዳለጌታ ግን በድፍኑ ሳይሆን፣ በተለይ “ኦሮማይ” ላይ ያሉትን ገፀ ባህሪያት ተንትኖ ያሳያል፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ፅሑፍ መምህር የነበሩት አቶ ብርሃኑ ገበየሁ ያቀረቡትን በገፅ 191 እንዲህ ጠቅሷል፡-
…በህይወት ከሚገኙ ሰዎች ባህሪዎቻቸውን የሚቀዱ ደራሲያን ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ያንን ሰው ወደ ስነ ጽሑፍ እንዳለ ሊያመጡት ግን አይቻልም፡፡ ግን ከዚያስ ነው? ደመቅ ያለው ክፍል ጎልቶ ስለሚታየው ለማንፀሪያነት ይወስዳሉ፡፡ አንዳንዴ የሰውየውን የሕይወት ታሪክ መታገጊያና ዳራ አድርገው ይነሳሉ ግን ያን ሰውዬ እነሱ እንዳዩት ነውን’ጂ፣ ያ ሰውዬ እንደሆነ ነው አይደለም፡፡…” እያሉ ይቀጥላሉ ብርሃኑ ገበየሁ፡፡
“በዓሉ ግርማ ህይወቱና ሥራዎቹ” በሚለው መጽሐፉ ውስጥ ቁልፉ ምዕራፍና ክፍል “ውድቅት፤ ተወንጃዮቹና እንደሙሴ መቃብሬ አይታወቅ” የሚሉት ናቸው፡፡ ውድቅት እንደስሙ ነው፡፡ ሌሎቹ ሁለቱም ፅሁፎች በዓሉ ግርማ ብቻ ሳይሆን ራሱ ፀሐፊው መረጃ ለማግኘት የዳከረበት፣ ግራ የተጋቡ የተሳከሩ መረጃዎች አንጎል የሚንጡበት ነው፡፡ በተለይ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ሰዎች የተሰጡን መረጃዎችን እነ ጓድ መንግስቱ ኃይለማርያምም ሸምጥጠው የካዱትን ነገር ፍጥጥ አድርጎ የሚያጋልጠው፣ የበዓሉ ግርማ በማዕከላዊና “ቤርሙዳ” ውስጥ መታሰሩንና መንገላታቱን የሚያሳዩ መረጃዎች መገኘታቸው ጉድ የሚያሰኝ ነው፡፡ ተረፈ ዘመድአገኘሁ የተባለው ሾፌር በገጽ 380 ላይ ምስክርነቱን ሲሰጥ፤ ፡-‹‹በዓሉ ግርማን ከማዕከላዊ ወደ ቤርሙዳ ሶስት ጊዜ አመላልሼዋለሁ፤ከዚያ በኋላ ደግሜ አላገኘሁትም፤››ብሏል፡፡
ይህ ደግሞ ቀደም ሲል የተያዘ ቀን ተገድሏል የሚለውን ግምት ለውጧል፡፡ አዲስ ጥሬ መረጃ ይሏል እንዲህ ነው፡፡
በተለይ “እንደሙሴ መቃብሬ አይታወቅ” የሚለው ክፍል እንዳለጌታ ሰነድ የፈተሸበትና በኢትዮጵያ ምሁራን ላይ በግፍ የተፈፀመውን ግፍና መከራ ቁልጭ አድርጎ ያሳየበት ነው፡፡ በተለይ የተረፈ ዘመድ አገኘሁና የኪሮስ ወልደማርያም ምስክርነት፣ የበዓሉን በማዕከላዊ እሥር ቤት እንዲሁም በቤርሙዳ መጉላላት - እስከነፍፃሜው ቁልጭ ያለ ማስረጃ ይሰጣል፡፡
ፀሐፊው በዚህ ምዕራፍ እነ ደራሲ አበራ ለማ የሰጡትን እማኝነት ፉርሽ የሚያደርግ ሀሳብ ማግኘቱ በይፋ ካሳየ በኋላ መረር ብሎ ይሞግታል፡፡ እዚህ ምዕራፍ ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው መጽሐፉ ውስጥ በርካታ ጥርጣሬዎችንና መረጃዎችን በድፍረትና በምክንያት ያስጎነብሳል፡፡
በዚህ መጽሐፍ ጠንከር ያለ በራስ መተማመን በማየቴ ተደንቄያለሁ፡፡ … በዕውቀት ማደግ መበልፀግ ማለትም ይህ ነው፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ከመጀመሪያዋ ገፅ ጀምሮ እስከ መጨረሻዋ ገፅ ድረስ ላቡን ጠብ አድርጎ፣ አምጦና ደክሞ፣ ወጥቶ ወርዶ ነው የሰራው፡፡ ከታች ካለው የማህበረሰብ ክፍል እስከ ቀድሞ የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ፍስሀ ደስታ ድረስ መሰላሉን እየረገጠ ተጉዟል፡፡ (በታሪኩ መሟጠጫ ጊዜ ፍስሀ ደስታ ከመንግስቱ ኃይለማርያም ቀጥለው የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣን ነበሩ፡፡)
በአጠቃላይ የእንዳለጌታ አዲሱ መጽሐፍ የልቦለድን ያህል ልብ የሚሰቅል፣ ጣዕም ያለው፣ ቀልብን የሚስብ፣ እንብርት የሚቆነጥጥ ስሜት ያለው፣ ጥልቅ ምርምር የተደረገበትና ግሩም ነው፡፡
እንደ ብርቱ የህይወት ታሪክ ፀሐፊም ፎቶግራፎችን፣ የተለያዩ ደብዳቤዎችን፣ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን፣ መጽሐፍትንና ቃለ -ምልልሶችን ወዘተ ለግብዓትነት ተጠቅሟል፡፡ በአካባቢ ገለፃዎችም ሳይቀር ሥነ ልቡናዊ ምስሎችን ፈልፍሏል፡፡ በጥቅሉ በኢትዮጵያ የስነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ታላቅ የባለውለታነት አሻራውን አትሟል፡፡
ጥቂት ቢስተካከሉ የሚባሉ መጠነኛ የሃሳብ ድግግሞሽ፣ የቃላትና የገለፃ ምርጫ፣ ባይካተቱ ጥሩ ነበር የምንላቸው እጅግ ጥቂት ነገሮች አሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ማንነታቸው ሳይጠቀስ የቀረቡት ሰዎች ጉዳይ አንባቢን ግራ ያጋባል፡፡ ለምሳሌ ገጽ 389 ላይ ‹‹ወሰን ሰገድ ገብረ ኪዳን››ይላል፡፡ ወሰን ሰገድ የቱ!...ጋዜጠኛ ቢባል፣ ቢቻል ከሰራቸው ስራዎች ጋር ቢጠቀስ! ይሁንና ይህን ትልቅ ስራ ላየ ሰው፣ እንከኖቹ ከቁብ የሚገቡ አይደሉም፡፡ በጥቅሉ እጅግ የምንወደውንና እንደ እግር እሳት የሚያንገበግበን ውድ ደራሲ አባታችንን ታሪክ ለዚህ ወግ ማዕረግ በማብቃቱ ለእንዳለጌታ ያለኝ ፍቅርና አክብሮት በእጅጉ ጨምሯል! ነፍስህን በሀሴት የሚያጠግብ ሲሳይ ይስጥህ! … እላለሁ፡፡ በድንጋይ ሳይሆን በልባችን ውስጥ በደም ስለቆመው ጀግና ደራሲ ሀውልት እንዳለጌታ ባለውለታ ነህ! … እ - ሰ -ይ! 
*******************************************************************************
http://www.addisadmassnews.com/

የአምባሳደር ዘውዴ ረታ "የኤርትራ ጉዳይ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት"


"የኤርትራ ጉዳይ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት" የተሰኘው መፅሃፋቸው ይዘት ፣ መፅሃፉን ለመፃፍ የተከተሉት አካሄድና ስለመፅሃፉ የምሁራን አስተያየት።
*****************************************************
"ስለ ኤርትራ ጉዳይ አዘጋጅቼ የማቀርበው ይህ መፅሃፍ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን የነበረውን ታሪክ የሚገልፅ ስለሆነ፣ ከጥቂት አመታት በፊት ከኢትዮጵያዊ ቤተሰብነት ወደ ጎረቢትነት የተለወጡትን የዛሬዎቹን ኤርራዊያኖችንና ዛሬ ያሉበትን ሁኔታ አይመለከትም። ኤርትራዊያኖች እናታቸው ከነበረችው ከኢትዮጵያ ለመለየት ስለደረጉት ረዥም ጉዞና በመጨረሻም ነፃነትን ለመቀዳጀት እንዴት እንደበቁ ታሪካቸውን ፅፈው እስኪያቀርቡልን እንጠብቃለን። ከዚያ በፊት ግን የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች እውነተኛውን ጉዳይ በትክክል ሊያውቁት የሚገባ የሀያ አመታት የታሪክ ሂደት አለ። ይህወም፤

  1. [በኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስትበኤርትራ ውስጥ እጅግ አብዣኛው ሕዝብ፣ ከባዕድ አገዛዝ ለመላቀቅና ኢትዮጵያዊነቱን ለማስመለስ፤ "ኢትዮጵያ ወይ ሞትብሎ መከራና ፈተና እየተቀበለ ምን ያህል እንደታገለ፤
  2. የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግስት ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር ለማዋሃድ፤ በኃያላን መንግስታቶች ዳኝነት እና በተለይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለብዙ አመታት ያደረገው ፋታ የሌለው ሙግት እስከ ምን ድረስ እንደነበረ፤
  3.  በአለም ማህበር ሸንጎ ላይ ኤርትራ በፌደሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል ፍርዱ እንዴት እንደተወሰነና፤ ከዚያም ለአስር አመታት የተካሄደው የፌደሬሽን አስተዳደር በምን መልክ ይሰራበት እንደነበር፣ ሁዋላም በምን አኩዋሁዋን እንደፈረሰ፤
እውነተኛውን ታሪክ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ህዝቦች አውቀውት የየራሳቸውን አቁዋም መያዝ ይገባቸዋል ብዬ ስለመንኩ፣ ባለኝ አቅም እውቀት የየራሳቸውን አቁዋም መያዝ ይገባቸዋል ብዬ ስለመንኩ፣ ባለኝ አቅም ለዚህ ጉዳይ ምርምርና ጥናት ብቻ የሰባት አመታት ጥረት አድርጌአለሁ።

የአፄ ዮሐንሥ ዘመነ መንግስት ካበቃ ከስልሣ አመታት በሁዋላ፣ በኢትዮጵያ እጅ የነበረው የኤርትራ ጉዳይ፣ ትክክለኛውና እውነተኛው ስዕል፣ ለዛሬውና ለመጭው ትውልድ በሀቅ ካልቀረበ፣ የመገንጠሉና ለነፃነት የተደረገው ውጊያ ብቻውን ብዙ ሺህ ጊዜ ተራብቶ ቢፃፍ፣ ታሪኩን የተሟላ አያደርገውም።

እኔም የኤርትራን ታሪክ አንድ ቀን መፃፍ አለብኝ የሚል ሀሳብ ያሳደረብኝ በህይወቴ ዘመን ምን ጊዜም ያልረሳው አንድ ትዝታ አለኝ።

እንደ ኤውሮፓ አቆጣጠር በመስከረም 1953 አም በጋዜጣና ማስታወቂያ መስሪያ ቤት የአዲስ አበባ ራዲዮ ወሬ አንባቢና ሪፖርተር ሆኘ ስቀጠር እድሜየ አስራ ስምንት አመት ነበር። ስለ ዜናዎች አስባሰብና አቀራረብ በዚያን ጊዜ ለራዲዮ የአማርኛ ዜና አዛጋጅ ከሆኑት ከአቶ አስፋ ይርጉ ዘንድ በመለማመድ ለስድስት ወራት ከቆየሁ በሁዋላ፣ በክቡር አቶ መኮንን ሀብተወልድ ትእዛዝ የቤተመንግስት ዜና ሪፖርተር እንድሆን ተመደብኩ። በዚሁ በአዲሱ መደቤ ያጋጠመኝ የመጀመሪያው የሪፖርተርነት ስራ፣ ንጉሠ ነገሥቱ የኤርትራን ቺፍ ኤግዚኩቲፍ ደጃዝባች ተድላ ባይሩን አስጠርተው ማነጋገራቸውን የሚገልፅ ዜና ማዘጋጀት ነበር። በተሠጠኝ መምሪያ መሰረት ገነተ ልዑል ቤተ መንግስት በመገኘት ያየሁበትን ፅፌ [መጠነኛ በሻሻል ተደርጎበትአቀረብኩ።

... በፌደረሽኑ ጊዜ የኤርትራ ቺፍ እግዚኩቲፍ አዲስ አበባ በመጡ ቁጥር፣ ከአውሮፕላን ጣቢያ ጀምሮ እስከ ቤተ መንግስቱ የሚደረገውን የፕሮቶኮል ጀብ ጀብ በምን ምክንያት እንደሆነ ለማወቅ [ፍላጎት] ከዚያን ዘመን ጀምሮ በአእምሮዬ ላይ ተቀርፆ ቀረ።

በፓሪስ የጋዜጠኝነት ሞያ አጥንቼ ከተመለስኩ በሁዋላ ለአስር አመታት በማስታወቂያ ሚንስቴር፣ ለአምስት አመታት በውጭ ጉዳይ ዲፕሎማሲ ስራ ባገለገልኩበት ዘመን፣ የኤርራን ጉዳይ በሰፊው ተከታትያለሁ። እንደ አውሮፓ ዘመን አቆጣጠር 1962 አም የኤርራ ፌደሬሽን ሲፈርስ በጋዤጠኝነት አስመራ ተልኬ ሁሉንም አይቻለሁ። ከክዚያም በሁዋላ በኤርትራ ጉዳይ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱትን የኢትዮጵያንና የኤርትራን ታላላቅ ሰዎች እያናገርኩ የታሪኩን አካሄድ በየመልኩ በዝርዝር ለማጥናት ጥሩ እድል አጋጥሞኛል።
  1. ኤርትራን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ በአለም ሸንጎ ላይ ለሰባት አመታት ተሟግተው ድሉን ያገኙት ጸሀፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ
  2. ኤርትራን ከፌደሬሽን አስተዳደር ወደ ፍፁም አንድነት ለማዋሀድ ያበቁዋት ቢትወደድ አስፍሐ ወልደሚካኤል
በሠጡኝ ሰነዶች በሰፊው ተጠቅሜያለሁ። ከነዚህ ሌላ በአዲስ አበባና በሮም በዋሽንግተንና በኒውዮርክ፣ በሎንዶንና በፓሪስ እየተዘዋወርኩ ብዙ ምርምና ትናጦች አድርጌአለሁ።

ማንም ሰው እንደሚያውቀው የኤርትራ ጉዳይ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ምንጊዜም የሚኖር ነው። ሰው የሚያውቀውን ፅፎ ማስጣወሻ ቢተው፣ በተለይ እኛን ለሚተካው ትውልድ የጠለቀ ምርምር ለማድረግ እንደሚረዳይ አይጠረጠርም። ይህ እጅግ የተወሳሰበ የታሪክ አካሄድ ያለው ጉዳይ፣ በጣት በሚቆጠሩ ሰዎች ብዕር ብቻ ተፅፎ አይቆምም። እንኩዋንስ በቅርቡ የተፈፀመው ቀርቶ የጥንቱም ቢሆን በየጊዜው በሚደረገው ምርምር፣ አዳዲስ ሰነዶች ስለሚፈልቁ ፅሁፉ እንደቀጠለ ነው። ለምሳሌ የዛሬ ሁለት መቶ አመት የተፈጠረው የፈረንሳዩ የቀዳማዊ ናፖሊዮን ታሪክ እስካሁን ተፅፎ አላለቀም። በዚህ አይነት ሲታይየኛ የኢትዮጵያችን ጉዳይ ገና አልተጀመረም ማለት ይቻላል።

በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን የተከናወነውን የኤርትራን ጉዳይ በበኩሌ አሟልቸ ለማቅረብ ብዙ ጥረት ስለአደረኩ፣ አንባቢዎች ጠቃሚ ነገሮች እንደሚያገኙበትተስፋ አደርጋለሁ"  ብለዋል።

ሊሎች ምሁራን ስለዚሁ መፅሃፍ የሚከተለውን አስተያየታቸውን ፅፈዋል።
 

  1. ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት:- "...ይህ የአምባሳደር ዘውዴ ረታ ያሳተሙት 'የኤርትራ ጉዳይየተባለው መፅሃፍ፣ በኛ በታሪክ ተማሪዎችና መምህራን በኩል እስካሁን ሙሉ በሙሉ ያላየናቸውና ያልደረስንባቸውን ቀጥተኛ መረጃዎች ለብዙ አመታት ብክብር ጠብቀው በማጥናትና በማመሳከር፤ አዲስ የተጣራ ዘገባ ስለአቀረቡልን ደራሲውን በሕዝብ ፊት እናመሰግናለን ..."
  2. ፕሮፌሰር መርዕድ ወልደአረጋይ "ይህ ዘውዴ ረታ አዘጋጅቶ ያቀረበልን መፅሀፍ አንደኛ ለኢትዮጵያውያን የመስሪያ ቁዋንቁዋ በሆነው በአማርኛ በመፃፉ  ሁለተኛ ኢትዮጵያዊና ሃገራዊ በሆኑ ምንጮች ተመስርቶ በመፃፉ፤ ለዚህ ውስብስብ መስሎ ለሚያየው የኤርትራ ጉዳይ አስተማማኝ የሆነ ግንዛቤ ይሰጣል ብዬ እገምታለሁ"
  3. ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ:-  "የዛሬ ሠላሳ አመት ግድም አምባሳደር ሐዲስ ዓለማየሁ በሎንዶን ቦሮዋቸው የቀመሙትን ፍቅር እስከ መቃብር የተሰኘውን የዘመናችን ምርጥ ልብወለድ ድርሰት ለአንባቢያን አቀረቡ፣
  4.   ዛሬ ደግሞ አምባሳደር ዘውዴ ረታ ሌላ ፍቅር እስከመቃብር ይዞልን ብቅ ብሏል።...ደራሲው ለአፄ ኃይለሥላሴ መንግስት በነበረው ቀረቤታና በተለይም ለኤርትራ ጉዳይ የታሪኩን ሁለት አበይት ተዋንያን፣ ማለትም የአክሊሉ ሀብተወልድ እና የአስፍሐ ወልደሚካኤልን አመኔታ በማግኘቱ፣ አያሌ ብርቅ ይሆኑ ሰነዶች ለጥናቱ ድምቀትና ጥልቀት ሊሰጡት ችለዋል። በዚህም አማካይነት በትውልዶች መካከል ተፈጥሮ የቆየውን የእውቀትና የልምድ ክፍተት ለመድፈን አንድ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል። አምባሳደር ዘውዴረታ ከፍተኛ የታሪክ ስልጠና ሳያገኝ የተካነበትን የጋዜጠኝነት ሞያ በመመርኮዝ ታሪካዊ ሁኔታዎችን ተረድቶ በሚጥም ቁዋንቁዋ ትልቅ ገፀ-በረከት ስለአቀረበልን እናመሰግነዋለን"
  5. ************************************************************************** 

ማሞ ካቻ (አቶ ማሞ ይንበርብሩ)

  አቶ ማሞ ይንበርብሩ (ማሞ ካቻ) እስቲ እናስታውሳቸው፣ ተቀብሮ እንዳይቀር አኩሪ ታሪካቸው  (ደረጀ መላኩ)   አቶቢሲ ማሞ ካቻ የት ትሄዳለህ? ገብረ ጉራቻ… ታዳጊው ማሞ ይንበርበሩ ገና በጨቅላ እድሜው አባቱ አቶ...