ማክሰኞ, ጁላይ 19, 2016

ንባብ ለሕይወት!



http://www.sendeknewspaper.com___በድንበሩ ስዩም___Thursday, 14 July 2016
********************************************************************************************************

መጽሐፍት ዓለም ሁሉ የቀየሩ የስልጣኔ ዋና ቁልፎች ናቸው። ዓለም እዚህ የደረሰችው መፃሕፍት ታትመው ነው። የሰው ልጅ የዕውቀት ብልፅግና፣ ልዕልና፣ ሃያልነት፣ ግርማ ሞገሱ ሁሉ ከመፃሕፍት ጋር የተቆራኘ ነው። መፃሕፍት የሌለውና የማያነብ ሰው ባዶ ቤት ውስጥ፣ ምንም ነገር በሌለበት ብቻውን እንደሚኖር ፍጡር ይቆጠራል። የሚያናግረው ሰው እንደሌለው፣ የሚያየው፣ የሚያልመው ሃሳብ እንደሌለው ፍጡር ይቆጠራል። ማንበብ የሰው ልጅ መሆንን ይጠይቃል። ሰው ፣ ሰው ለመሆን ማንበብ አለበት። ካለበለዚያ ብዙ ነገሮችን ከሌሎች እንሰሳት ጋር ይጋራል። የሰው ባህሪያትን ያጣል።
የዓለም የሥልጣኔ አውራ ከነበሩት አገራት መካከል አንዷ የነበረችው ሐገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ የሥልጣኔ ውራ ሆናለች። የዚህ ምክንያቱ ሌላ አይደለም። የዕውቀት ማነስ፣ ያለማንበብ ችግር የፈጠረብን አበሳ ነው። ሌላው ዓለም የበለጠን በማንበቡ ነው። ንባብ የሕይወት መሠረት ነው። በጋዜጠኞች በቢኒያም ከበደ እና በአንተነህ ከበደ የሚመራው የዘንድሮው “ንባብ የሕይወት” የተሰኘው ታላቅ የመፃሐፍት አውደ-ርዕይም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ያለባትን የማንበብ ችግር ለመቅረፍ የተደረገ ሙከራ ነው። እሰየው ደግ አደረጋችሁ፤ ወደፊትም በርቱ፣ ጠንክሩ ልንላቸው ይገባል። ዕውቀት ላይ የሚሰራን ማንንም ሰው ትውልድ ያመሰግነዋል።
የመፃሕፍት አውደ ርዕይ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ ይታይባቸዋል። ደራሲ ዳንኤል ወርቁ “ኢትዮጵያ ታንብብ”፣ “አዲስ አበባ ታንብብ” እያለ በተደጋጋሚ ያደረገው ሁሉን አቀፍ ዘመቻ ውጤት እየታየበት ይመስላል። ነገር ግን በአንዳንድ የመፃሐፍት አውደ-ርዕይ ላይ ደግሞ የራሴ የሆኑ ቅሬታዎች አሉኝ።
መፃሕፍት ክቡር ነገሮች ናቸው። ውስጣቸው ዕውቀት አለ፣ ሰው አለ፣ ታሪክ አለ፣ ፈላስፋ አለ፣ ሊቅ አለ፣ ፈጣሪ አለ፣ ኧረ ምን የሌላ ነገር አለ? ስለዚህ የክብር ቦታ ያስፈልጋቸዋል። በአንዳንድ አውደ ርዕዮች ላይ እጅግ የቆሸሸ ስፍራ ላይ መፃሕፍት ተደርድረው “አውደ-ርዕይ” ሲባል ቅር ይለኛል። መፃሕፍት እንደ ስደተኛ በድንኳን ውስጥ መቀመጥ የለባቸውም። የክብር ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል።
ለምሳሌ የስዕል አውደ-ርዕይ ሲኖር ታላላቅ ሆቴሎችና ጋለሪዎች ክፍት ይሆናሉ። ለስዕል ጥበብ የተከፈቱ ሆቴሎችን፣ ጋለሪዎችን፣ አዳራሾችን ለመፃሕፍትም ማስከፈት ይገባል። የመፃሕፍት አውደ-ርዕዮች ሕፃናት ከወላጆቻቸው ጋር መጥተው የሚቦርቁባቸው ቦታዎች መሆን አለባቸው። ሚሊኒየም አዳራሽ፣ ሸራተን ሆቴል፣ ሂልተን ሆቴል፣ ጊዮን ሆቴል ወዘተ የመፃሕፍት አውደ-ርዕዮች እንዲካሄዱባቸው ማድረግ ይገባናል። መጠየቅ፣ በር ማንኳኳት፣ ማስከፈት የሁላችንም ተግባር መሆን አለት እላለሁ።
መፃሕፍትን ይዘው ድንኳን እያፈሰሰባቸው፣ ጐርፍ ከስራቸው እየሄደ፣ ብርድ እያንዘረዘራቸው የሚያስጐበኙ ሰዎችን ማየት የለብንም። መፃሕፍት ትልልቅ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል።
የዘንድሮው “ንባብ ለሕይወት” አውደ ርዕይ በኤግዚቢሽን ማዕከል መካሄዱ ከላይ ያነሳኋቸውን ችግሮች በሰፊው ይቀርፋል የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም መፃሐፍትን በሰፋፊ አዳራሾች ውስጥ ሰብሰብ ብለው የምናይበት ስፍራ በመሆኑ፣ ሕፃናትም ወደ ስፍራው ሲመጡ እንደልባቸው የሚቦርቁበት እና የሚያነቡበት ቦታ በመኖሩ ይህ አሰራር መለመድ ያለባት ተግባር ነው። አውደ-ርዕዩንም መሠረት አድርጐ ታሪካዊ መጽሔት ማሣተምና ማሰራጨትም የዚህ አውደ-ርዕይ ተግባር በመሆኑ ለመፃሕፍት ያለንን አመለካከት ከፍታ ይሰጠዋል።
አምና በዚህ ወቅት የንባብ ለሕይወት የመፃሕፍት አውደ-ርዕይ አዘጋጆች የተለያዩ የሐገር ውስጥ እና የውጭ አገር ጠቢባን ስለ ንባብና መፃሕፍት የተናገሯቸውን ሃሳቦች ሰብሰብ አድርገው በመጽሔታቸውና በኤግዚቢሽን ማዕከል ልዩ ልዩ ስፍራዎች ለሕዝብ ዕይታ አቅርበዋቸው ነበር። ውድ አንባቢዎቼም እነዚህን ጥቅሶች እያነበባችሁ ከራሳችሁ ጋር እንድትነጋገሩ ብተዋችሁስ?
ኢትዮጵያችን ውስጥ አለማንበብ ብዙ ነገር እየጎዳን ነው። ባለማንበባችን አለምን የምናይበት ማንጸሪያ የለንም። ራሳችንን ከሌላው ጋር አስተያይተን እኛ የቱጋ እንደምንገኝ ማወቅ አንችልም። በዚህም የተነሳ መንገዳችን ጉዟችን ወደየት እንደሆነ መለየትም አንችልም። ባለማንበባችን ርዕይ (vision) እናጣለን። ባለማንበባችን ሰው የመባላችን ምክንያት ይጠፋል።  
“ማንበብ ትልቅ ሀብትን ያጎናፅፋል። እስከዛሬ በአለማችን ላይ ስለተከሠቱ እና በሌሎች ሰዎች ስለተሰሩ ነገሮች በሙሉ ማወቅ የምንችለው ማንበብ ስንጀምር ነው።” አብርሃም ሊንከን
“በህይወቴ ማወቅ የምፈልጋቸው ነገሮች በሙሉ መፀሀፍቶች ውስጥ አሉ። የኔ ምርጥ ጓደኛ ብዬ የምቀርበው ሰው ያላነበብኩትን መፀሀፍ “እንካ አንብብ” ብሎ የሚሰጠኝ ነው።” አብርሃም ሊንከን
 “እዚህ ምድር ላይ ግዜ የማይሽረው ደስታን የሚሰጠን ብቸኛው ነገር መፀሀፍ የማንበብ ልምድ ነው። ሁሉም ደስታዎቻችን በወረት ከእኛ ሲለዩን መፀሀፍ የማንበብ ልምዳችን ግን ዘወትር ደስተኞች ያደርገናል።” አንቶኒ ትሮሎፔ
“ዘወትር ባነበብኩኝ ቁጥር ውስጤ የነበረውና ያለው ትልቁ የመቻል አቅም ይቀሰቀሳል።” ማልኮም ኤክሥ
“የኔን የግል ህይወት ብቻ ሳይሆን በዙሪያዬ ያሉ ሰዎችን ህይወት መለወጥ የቻሉ ሀሳቦችን መተግበር የቻልኩት መፀሀፍ በማንበቤ ነው።” ቤል ሑክሥ
“መፀሀፍን የሚያነብ ሰው በህይወት ውጣ ውረዱ አያማርርም። ሠዎች ለምን ጎዱኝ፣ ለምንስ አያስቡልኝም ብሎም ሌሎችን አይወቅስም። ከሌሎች ጋርም አይቀያየምም ምክንያቱም መፀሀፍ የሚያነብ ሰው ለራሱ ስኬትና ደስተኛነት ራሱ ብቁ ነውና ከሌሎች ምንም ስለማይጠብቅ።” ባሮው
“ዛሬ ላይ ያለህ ማንነት የዛሬ አምስት አመት ከሚኖርህ ማንነት ጋር ፍፁም ለውጥ ሳይኖረው ተመሳሳይ ነው። ግን በነዚህ አመታቶች ውስጥ መፀሀፎችን ካነበብክ አዎ! ከአሁኑ ይልቅ የዛሬ አምስት አመት የተሻለ ማንነት ይኖርሃል።” ቻርሊ ጃንሥ
“ለአንድ ሠው መፀሀፍ ስትሸጥ የሸጥከው ብዙ ወረቀቶችን፣ የተፃፈበትን ቀለምና ጥራዙን አይደለም። ለርሱ የሸጥክለት ዋናው ነገር ሙሉ የሆነ አዲስ ህይወትን ነው።” ክርስቶፈር ሞርሌይ
“በዚህ ዘመን በየትኛውም ሁኔታ በጣም ግዜ የለኝም፣ እረፍት የለኝም ብለህ የምታስብ ቢሆን እንኳን ለማንበብ የግድ ግዜ መስጠት አለብህ። ይህን አላደረክም ማለት ግን በገዛ ፍላጎትህ ራስህን አላዋቂ እያደረከው ነው ማለት ነው።” ኮንፊሽየሥ
“ድሮ ልጅ ሣለሁ ወደ ትምህርት ቤት ስሔድ ዘወትር አፍንጫዬን በመፀሀፍ ደብቄ ነበር። ይኸው ዛሬ ላይ ታዲያ እዚህ ለመድረሴ ዋና ምክንያት ሆኖኛል።” የሙዚቃ አቀንቃኙ ሱሊዮ
“መፀሀፍትን በሚገባ ማንበብ ማለት በድሮ ዘመን ይኖር ከነበረ በጣም አስተዋይ ሰው ጋር መወያየት ማለት ነው።” ሬኔ ዴካርቴሥ
“አዎ! የሚታኘክ ማስቲካ ለማምረት ከምናወጣው ወጪ በላይ ለመፀሀፍቶች ብዙ ወጪን ባናወጣ ኖሮ ይህች ሀገራችን እንዲህ የሠለጠነችና የዘመነች አትሆንም ነበር።” አልበርት ሀባርድ (አሜሪካዊ)
“ከየትኛውም ነገር በላይ ትልቁንና ከፍተኛውን ደስታ የማገኘው ሳነብ ነው።” የፋሽን ዲዛይነሯ ቢልብላሥ
“ማንበብ ከቻልክና አንዴ ማንበብ ከጀመርክ በቃ አንተ ነፃነት ያለህ ሠው ነህ።” ፍሪድሪክ ዳግላሥ
“ለመኖር ከፈለክ መፀሀፍ አንብብ።” ጉስታሽ ፍላውበርት
“መፀሀፍን ከማቃጠል የባሰ በርካታ ወንጀሎች አሉ። ከነዚህ መሃል መፀሀፍትን አለማንበብ አንዱ ትልቁ ወንጀል ነው።” ጆሴፍ ብሮድስኪ
“አላዋቂነትንና ችኩልነትን የምንዋጋበት ብቸኛው ወሳኝ መሣሪያ ማንበብ ነው።” ሌኖርድ ቤይንሥ ጆንሰን
“ዛሬ ያነበበ ነገ መሪ ይሆናል።” ማርጋሪት ፉለር
“መፀሀፍን የማያነብ ሠው ማንበብን ከነጭርሱ ከማይችል ሠው በምንም አይሻልም።” ማርክትዌይን
“በርካቶቻችን መፀሀፍ አንባቢ መሆን እንፈልጋለን። የምናነበው ግን ጥቂቶች ብቻ ነን።” ማርክ ትዌይን
“እኔ የተወለድኩት ማንበብ ከሚገቡኝ ግና አንብቤ ከማልጨርሣቸው የመፀሀፍት ዝርዝሮች ጋር ነው።” ማውዲ ኬሲ
“ለአንድ ጨቅላ ልጅ መፅሐፍ እንዲያነብ ከማድረግ በላይ ልንሠጠው የምንችለው ትልቅ ሥጦታ የለም።” ሜይ ኤለን ቼሥ
“አንድ መፀሀፍ ባነበብን ቁጥር እዚህ ምድር ላይ በሆነ ቦታ ለኛ አንድ በር እየተከፈተልን ነው።” ቬራናዛሪያን
“ለኔ ህይወት ማለት ጥሩ መፀሀፍ ማለት ነው። የበለጠ ወደ ውስጡ በገባን ቁጥር የበለጠ ትርጉም እየሰጠን ይመጣል።” ሀሮልድ ሱሽነር
“እስከዛሬ በህይወቴ ካገኘኋቸው ምክሮች ትልቁ እውቀት ሀይል ነው። ማንበብ ደግሞ አማራጭ የሌለው ተግባር ነው የሚለው ነው።” ተዋናይ ዳቪድ ቤይሊ
“የህይወታችን ትልቁ ደስታ መፀሀፍ ከማንበብ የሚገኝ ነው ብዬ በድፍረት ላውጅ እችላለሁ። ወደፊት እኔ የራሴ መኖሪያ ቤት ሲኖረኝ አንድ ጥሩ ላይብረሪ በውስጡ ካላካተትኩኝ ምን እንደሚውጠኝ አላውቅም።” ደራሲ ጆን ኦውስተን
“መፀሀፎች ወረት የማያውቁ ምርጥ ወዳጆች ናቸው። እጅግ መልካም አማካሪዎችና የችግር ግዜ ደራሾችም ናቸው። እንዲሁም ከምንም በላይ ታላቅ መምህር ናቸው።” ቻርሊ ኢሊዬት
“ማንበብ ከምንገምተው በላይ ዘላቂ የሆነ ደስታን ነው የሚሰጠን።” ላውራቡሽ
“መልካም ህይወት መኖር ከፈለግን ዛሬ ነገ ሳንል ማንበብ መጀመር አለብን።” ሞርታይመር አልዴር
“አንድ ሠው ምን አይነት ማንነት እንዳለው ያነበባቸውን መፀሀፎች አይቶ መናገር ይቻላል።” ራልፍ ዋልዶ ኤመርሠን
“አንድ ባህል ወደ ቀጣይ ትውልድ እንዳይተላለፍ ከተፈለገ መፀሀፎችን ማቃጠል አያስፈልግም። ይልቅ ሠዎቹ መፀሀፍ ማንበብን እንዲያቆሙ ማድረግ በቂ ነው።” ራይ ብራድበሪ
“የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለአካላችን የሚጠቅመውን ያህል ንባብም ለአእምሯችን ይጠቅማል።” ሪቻርድ ስቲላ
“ሸረሪቶች እንደተወለዱ በተፈጥሮ ድርን የመስራት ክህሎትን እንደሚያገኙ ሁሉ ህፃናትም ሲወለዱ የመናገር ጥበብና ችሎታ አብሯቸው ይወለዳል። ግና ማንበብ መቻልን እኛ ነን ልናለማምዳቸውና ልናስተምራቸው የሚገባን።” ስቴቨን ፒንከር
“መርከበኞች በአንጸባራቂ ደሴት ላይ ከሚያገኙት ሀብት በላይ ብዙ ሀብት የሚገኘው መፅሀፍቶች ውስጥ ነው።” ዋልት ዲስኒ
“አንተ ጋር ሲመጡ መፀሀፍ በእጃቸው ያልያዙ ሠዎችን በፍፁም አትመን።” ሊሞኒ ስኒኬት
“ለማንበብ ግዜ የለኝም ካልን ለማውራትና ለመፃፍ እንዴት ግዜ እናገኛለን?” ስቴቨን ኪንግ
“ህፃናት እንደሚያደርጉት ለመገረም ብለው መፀሀፍን አያንብቡ። ለመማርም ሆነ ህልመኛ ለመሆንም ፈልገው አያንብቡ። ይልቅ አዎ! ለመኖር ሲሉ ነው ማንበብ ያለብዎት።” ጉስታቮ ፍላውበርት
“እኔና ጥቂት ሰዎች ስለራሳችን መልካም ነገር የምናስበውና ጥሩ ስሜት የሚሠማን መፀሀፍ ስናነብ ነው።” ጄን ስሜይሊ
“ከመናገርህ በፊት አስብ። ከማሠብህ በፊት አንብብ።” ፍራን ሌቦውትዝ
“የልጆቻችንን ቀጣይ ህይወት ብሩህ ልናደርግላቸው የምንችልባቸው ጥቂት መንገዶች አሉ። ከነዚህ መንገዶች መሃል ሠፊውና አስተማማኙ በውስጣቸው የንባብ ፍቅርን መዝራት ነው።” ማያ አንጄሎ
“መፀሀፍ ማንበብ ነገሮችን እንድንረዳ ብቻ ሳይሆን ሌሎች እኛን በቀላሉ እንዲረዱን ይጠቅመናል።” ጆን ግሬን
“አንተ ያላነበብከውን መፀሀፍ አንብብ ብለህ ለልጅህ አትስጠው።” ጆርጅ በርናንድ ሾው
“አንተ ወይም እኛ የማናውቃቸው ነገሮች በሙሉ መፀሀፍት ውስጥ እንዳሉ እናውቃለን?” ሲድኒ ስሚዝ
“እኔ አንብቤ ባስቀመጥኳቸውና በማነባቸው መፀሀፎች ካልተከበብኩ እንቅልፍ በፍፁም አይወስደኝም።” ጆርጅ ሉዊሥ በርጌሥ
“አንዳንድ መፀሀፎች የፈለግነውን እንድናስብ ነፃ ያደርጉናል። አንዳንድ መፀሀፍት ደግሞ ከጭንቀታችን ነፃ ያደርጉናል።” ራልፍ ዋልዶ ኤመርሠን
“ምናባችንን ከተኛበት የሚቀሠቅስልን ሞተር መፀሀፍ ማንበብ ነው።” አለን ቤኔት
“በአሁኑ ሰአት እየተቃጠሉ ካሉ መፀሀፍት በላይ የሚያሳስበኝ በአሁኑ ሰዓት እያልተነበቡ ያሉ መፅሀፎች ናቸው።” ጁዲ ብሉሜ
“ልጆቼ ወደፊት ሲያድጉ ማንበብ የሚወዱና ለእናታችን ትልቅ መፀሀፍ መደርደሬ እንስራላት ብለው የሚጨነቁ ቢሆኑ ደስታዬ ወደር አይኖረውም።” አና ክዊድሰን (የኒዮርክ ታይምስ ፀሃፊ)
“መፅሀፍት ማለት መቼም ቢሆን የማይርቁን፣ የማያስቀይሙን፣ የማይከዱንና መቼም ቢሆን ተስፋችንን የማያጨልሙብን ወዳጆቻችን ናቸው።” ቻርልሥ ኤሊዮት
“ከውሻ ውጪ የሠው ልጅ ታማኝ ወዳጅ መፀሀፍት ናቸው። ከውሻ ጋር ወዳጅ ስንሆን ግን የማንበብ እድላችን በጣም ያነሠ ነው።” ጉርቾ ማርክሥ
“በመመገቢያ ጠረጴዛህ ላይ መፀሀፎች ይሙሉ። ከዛም በጣም ደስተኛ ትሆናለህ። ትራስህም መፀሀፍቶችን ይሁኑ ከዛም ፍፁም የሠላም እንቅልፍ ትተኛለህ።” ፊይዶር ዶስቶኸስኪ
“መፅሀፍ ማለት በኪሳችን ይዘነው የምንዞረው በመልካም ፍሬዎች የተሞላ እርሻ ነው።” ቻይናውያን
“መፅሀፍ ስናነብ ወደ ውስጣችን በጣም ጠልቀን በመግባት ስለራሳችን የበለጠ ብዙ ነገሮችን ማወቅ እንጀምራለን።” ዊልያም ሀዝሊት
“ትንሽዋ የመፅሀፍ መደርደሪያ እስከዛሬ በአለማችን ላይ ከቀረቡ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች በላይ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ሃሣቦችን ይዛለች።” አንድሪው ሮስ
“ለአንድ ሰአት ብቻ ካነበብክ ወይም የማንበብ ልምድ ካለህ መጨነቅህ አይቀርም። ከሁለት ሰአታት በላይ የማንበብ ልምድ ካለህ ግን በምድር ላይ እንዳንተ ደስተኛ ሰው አይኖርም።” ቻርለስ ዴ ሴኮንዳት
“ከአጠገብህ ፋኖስ ለኩሰህ ወይም ሻማ አብርተህ ቁጭ ብለህ መፀሀፍ ማንበብን የመሰለ ምን ነገር አለ? አስበው በዚያ በምታነብበት ሰዓት ሌላው ቀርቶ እዚህ ምድር ላይ አብረውህ ያልነበሩትን የቀድሞ ትውልድ ሰዎችና አብረውህ የማይኖሩትን የመጪው ትውልድ ሰዎችን ማውራት ትችላለህ። ይህ ደግሞ ከምንም በላይ ትልቅ ዋጋና ትርጉም ያለው አስደሳች እሴት ነው።” ኬንኮ ዮሺዳ
“ሠዎች ህይወትን አንድ የሆነ ነገር ነው ብለው ይገልፃሉ። ለእኔ ግን ህይወት ማለት ማንበብ ማለት ነው።” ሎጋን ስሚዝ
“ማንበባቸውን ተከትሎ በየዘመናቸው ታላቅ ስራን የሰሩ ጀግኖች ቁጥራቸው ስንት ይሆን?” ሔነሪ ዳቪድ
“መፅሀፍትን ስናነብ አእምሯችን ራሱን የቻለ አንድ አስደሳች ኮንሰርት ተዘጋጀለት ማለት ነው። ታዲያ አእምሯችን ደስተኛ በሆነበት ሰዓት ደግሞ የሚያስባቸው ሃሣቦች ምን ያህል ጠቃሚና የጠለቁ እንደሆኑ ሁላችንም እናውቃለን።” ስቴፋኒ ማላርሜ
“መፅሀፍ የሚያነቡ ሠዎች ብቸኝነት አያጠቃቸውም።” አጋታ ክርስቲ
“መፅሀፍ ማንበብ ነፍስን ያክማል።” በቴክሳስ ላይብረሪ መግቢያ ላይ የተፃፈ
“መፅሀፍ የሌለበት መምሪያ ቤት ማለት መስኮት የሌለበት ቤት ማለት ነው።” ሎነሬች ማን
“ሠው መንፈሱን መመገብ የሚችለው መፀሀፍትን በማንበብ ብቻ ነው።” ኤድዊን ማርክሃም
“የተራበ ከብት ሳር ሲግጥ የሚሰማውን ደስታ ይህል ነው የሠው ልጅም መፅሀፍትን ሲያነብ ከፍተኛ ደስታን የሚያገኘው።” ሎርድ ቸስተርፌልድ
“አንድ ሠው ለልጁም ሆነ ለመላው ማህበረሰብ ከሚሰጠው ስጦታዎች ሁሉ ትልቁ አንብቦ ሰዎችን እንዲያነቡ ማስቻሉ ነው።” ካርል ካጋን
“ልጆቻችንን ዝም ብለን አይደለም አንብቡ ብለን እንዲያነቡ ማድረግ ያለብን። ይልቁንም በማንበባቸው በጣም ደስተኞች እንዲሆኑና ደጋግሞ የማንበብ ፍቅር እንዲያድርባቸው የሚያደርጉ ነገሮችንም አብረን ማድረግ ይጠበቅብናል።” ካትሪና ፒተርሠን
“ከየትኛውም መዝናኛ በላይ እንደማንበብ ዋጋው ርካሽ ሆኖ በቀላሉ የሚያዝናና ነገር የለም። ደግሞም በማንበብ እንደሚገኘው ዘለቄታዊ ደስታ ሌሎች መዝናኛዎች ዘላቂ ደስታን አይሠጡም።” ሌዲ ሞንታኑ
“እኔ ዘወትር የማስበው በቀጣይ ስለማነበው መፀሀፍ ብቻ ነው።” ሮኦልድ ዳህል
“መፅሀፍትን ማንበብ መታደል ነው። ምክንያቱም ባነበብን ቁጥር አለማችንን በሚገባ እናውቃታለንና።” ኒል ጌይንማን
 

የሀገር ውስጥ ሰዎች አባባል ስለንባብ

“ማንበብ የአአምሮ ምግብ ነው፤ ዋናው የአእምሮ ምግብ!”  ደራሲ ስዩም ገ/ህይወት
“ማንበብ ህይወትን የምንቀይርበት ትልቅ መሳሪያ ነው። ያለ ንባብ ህይወትን በአግባቡ መምራት አይቻልም።” አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው
“ማንበብ የእውቀት ብርሃን ነው። ስለዚህ ባነበብን ቁጥር ውስጣችንም ሆነ በዙሪያችን ያለው ውጫዊ ነገር በሙሉ በብርሃን የተሞላ ይሆናል።” ሰአሊ አንዷለም ሞገስ
“ሰው ምግብ ሳይበላ እንደማይውለው እኔም ሳላነብ አልውልም። ምክንያቱም ማንበቤ እኔን ከምንም ነገር በላይ ተጠቃሚ አድርጎኛል።” ሀይለልዑል ካሳ (የባንክ ባለሙያ)
“ንባብ ያልታከለበት ግንዛቤ ግልብ ያደርጋል።” ደራሲ በአሉ ግርማ
“መፅሀፍትን ማንበብ ታሪክህን በሚገባ እንድታውቅ ያደርግሀል። ታሪክህን ስታውቅ ደግሞ ራስህን ታውቃለህ።” አምባሳደር ዘውዴ ረታ
“በዚህች ጥንታዊ ሀገር መፅሀፍትን መፃፍ ብቻ ሳይሆን ማንበብ፣ ማስነበብ፣ ማስፃፍ፣ ሲነበቡ መስማት ጭምር የተከበረ ነገር ነበር።” ደራሲ/ዲያቆን/ ዳንኤል ክብረት
“ማንበብ በሁሉም ነገር ምልዑ ሆነን እንድንንቀሳቀስና ከግዜው ጋር አብረን እንድንራመድ ያስችለናል።” ፍቅር ተገኑ (የፀጉር ውበት ባለሙያ)
“ማንበብ እኮ ሁሉን ነገሮች ያንተ እንዲሆኑ ያደርጋል። ስታነብ ትዝናናለህ። ማንበብህን ተከትሎ ደግሞ ስለሁሉም ነገር ማወቅና መረዳት ትጀምራለህ።” ድምፃዊ ፀሃዬ ዮሀንስ
“ማንበብ ያልኖርነውን ትላንት ዛሬ ላይ መኖር እንድንችል ያደርጋል። ከዛ ካልኖርንበት ዘመን እንኳን ጓደኞች እንዲኖሩን፤ የነርሱንም ያህል ዘመኑን የኖርነው ያህል እንዲሰማን ያስችላል።” ደራሲና ጋዜጠኛ ዳዊት አለሙ
“መፅሀፍ ያጣ አእምሮ፤ ውሃ ያጣ ተክል ማለት ነው። ሰው ራሱን አውቆና ችሎ እንዲኖር መፀሀፍ ማንበብ በእጅጉ ይጠቅማል።” ንጉሴ ታደሰ (መምህር)
“ማንበብ ከባይተዋርነት ያድናል። ባነበብን ቁጥር በአለም ላይ ስላሉ ነገሮች ስንሰማም ሆነ ስናይ አዲስ አይሆንብንም። ወዳጆችን ለማፍራትም አንቸገርም። ማንበብ የሙሉነት መስፈርት ነውና።” ገጣሚና ጋዜጠኛ ፍርድያውቃል ንጉሴ
“ማንበብ አእምሮን አያስርብም። የሚያነብ ሰው ዘወትር ንቁና በአስተሳሰቡ የበለፀገ ነው።” ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ)
“እውቀቴን ሁሉ ያገኘሁት በማንበብ ነው። በአጭሩ ማንበብ አዋቂ ብቻ ሳይሆን ሙሉ ሰው ያደርጋል።” ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ
“ማንበብ ፍፁም ደስተኛ ያደርጋል። እስከዛሬ ባላነብ ኖሮ ምን ይውጠኝ ነበር? እያልኩ ዘወትር አስባለሁ።” ህዝቅያስ ተፈራ (የህግ ባለሙያ)
“ማንበብ በጣም ያዝናናል። በየትኛውም ግዜ የሚወጡ መፅሀፍትን ማንበብ የሃሳብ ሀብታም ያደርጋል።” ተዋናይ ዋስይሁን በላይ
“እኔ ማታ ማታ አነባለሁ። ሁሌ አንብቤ ሳድር በጣም ደስተኛ ከመሆኔም በላይ የደንበኞቼን ባህርይ እንድረዳ ረድቶኛል።” ካሳሁን ፈየራ (የታክሲ ረዳት)
“ማንበብ በየትኛውም ነገር ላይ ተፈላጊውን ተፅዕኖ መፍጠር እንድትችል ያደርግሃል። ከሰዎች ጋርም በቀላሉ እንድትግባባ መንገዱን ይጠርግልሃል።” እድሉ ደረጀ (የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች)



የ2008 የንባብ ለሕይወት አምባሳደሮቻችን እነዚህ ናቸው


የ2008 የንባብ ለሕይወት አምባሳደሮቻችን እነዚህ ናቸው

- ተዋናይ ግሩም ኤርሚያስ

በትወና ብቃታቸው ከወንበር ብድግ ተብሎ ከሚጨበጨብላቸው ከያኒያን አንደኛው ነው፤ በተሳተፈባቸው የትወና ብቃቱን በገለጡ ስራዎቹ ላይ የተሳካለት ሙያተኛ የሆነው ይህ ወጣት እውቅናው ያልጋረደው ትሁት ፀባዩን ከገፁ ላይ እንዲሁም ከንግግሩ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል፤ የትወና አለምን መቀላቀል ለሚፈልጉ ጀማሪ ታናናሾቹም ለማጎበዝ በማሰብ ‹‹መሰረታዊ የትወና መማሪያ›› የተሰኘ መጽሐፍ ተርጉሞ ለንባብ በማብቃት ንባብን እያበረታታ ሙያን እንዲማሩ እያገዘ በአንድ ጠጠር ሁለት ግብ የመታ ጎበዝ ነው፤ ሌላኛው የንባብ ለሕይወት የንባብ አምባሳደር ነው፡፡

=========================================

- ወ/ሮ ማህሌት ኃ/ማርያም

‹‹ኑ እንማከር፣ እንወያይ›› እያለች መመካከርን፣ ለችግርም ሆነ ለመልካም ጉዳይ ተመካክሮ መፍትሄ መሻትን የምትሞግት የእውቀት አፋላጊ ብሩህ ሴት፤ ወጣቶች ማንበብን እንዲያፈቅሩ ንባብን ወዳጅ እንዲሆኑ የበኩሏን ያበረከተች ጠንካራ ሰው ናት፡፡ ይህንንም እንዲያው በደረቁ ልፈፋ ሳይሆን በመላው ኢትዮጲያ በተለያዩ ክልሎች ከ90 በላይ ቤተ-መጻሕፍትን ገንብታ አንባቢ ትውልድን ለመፍጠር ትተጋለች፤ በንባብ ለሕይወት የ2008 ዓ/ም ከሴት የንባብ አምባሳደሮች አንዷ ናት፡፡


=========================================

- አቶ ታደሰ ጥላሁን

40 አመታት ያህል በተለያዩ ድርጅቶች በሃላፊነት እርከን ያገለገሉ፣ ሰፊ የልምድ ሃብት ያካበቱ፣ በሙያ ብቃት አንቱ የተባሉ፣ ሰው ናቸው፤ ይህም ሆኖ ለማንበብ ለማወቅ አዕምሮዋቸው ክፍት የሆኑ ባለሙያ ናቸው ሁሌም ቢሆን ‹‹ትውልድና አገር የሚገነባው በንባብ ነው›› በሚል ፅኑ አቋማቸው ይታወቃሉ፡፡ አሁን በሚገኙበት ናሽናል ኦይል ኢትዮጲያ ስራ አስኪያጅና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው ያገለግላሉ ያለባቸውን የስራ ጫና መገመት ምጡቅ አያሰኝም ሆኖም በዚህ ጫና ስር ሆነው እንኳ ንባብ ለማዳበር በሚደረግ ጥረት ውስጥ እንዲሳተፉ ሲጠየቁ በደስታ የተቀበሉ መሆናቸው ሊያስወድስ ሊያስመሰግናቸው ይገባል፤ የ2008 ዓ/ም የንባብ ለሕይወት አምባሳደር ናቸው፡፡

========================================

- ኬሚካል ኢንጂነር ጌታሁን ሄራሞ

በቀለም ሳይንሱ ዘርፍ ወደፊት ከተራመዱ ሊቃውንት አንዱ ናቸው፤ ያላቸው እውቀት ሳያጠግባቸው ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት የሚታትሩት እኚህ ሰው Amazon ተብሎ በሚጠራ የመጻሕፍት አቅራቢ ማህበራዊ ድህረ-ገፅ ላይ በየእለቱ እየተገኙ መጻሕፍትን በማንበብም እውቀታቸውን ያዳብራሉ፤ በሰዋዊ ፀባያቸውም ያወቁትን ለማካፈል ሳይሰለቹ የሚተጉ አንደበተ ርቱዕ ጠቢብ ናቸው፤ ከተለያዩ አገራት የቀረበላቸውን ገቢያቸውን በአስተማማኝ መልኩ ሊያዳብር የሚችሉ የአብሮ መስራት ጥያቄዎችን ወደ ጎን በማለት ለንፅፅር እንኳን በማይበቃ ክፍያ ለአገራቸው መስራትን ያሰቀደሙ አይነታቸው እንዲያው እንደዋዛ የማይገኝ ልሂቃን መካከል አንዱ ናቸው፤ የንባብ ለሕይወት የ2008 የንባብ አምባሳደር ተደርገው የተመረጡ አንዱ ባለሙያ ናቸው፡፡

=========================================

- ደራሲና ጋዜጠኛ አለማየሁ ገላጋይ

የጉብዝና ወራቱ አብሮት ያለ ወጣት ደራሲና ጋዜጠኛ ነው፤ ለማንበብና ለመጻፍ የማይደክሙ አይኖችና እጆች ያሉት ባለ ብሩህ አዕምሮ ወጣት የሆነው አለማየሁ በአገሪቱ በሚገኙ ጋዜጣና መጽሄቶች ላይ በሚያሰፍራቸው የተለያየ ይዘት ባላቸው ፅሁፎች በስፋት የሚታወስ ቢሆንም ወሪሳ፣ ኩርቢት፣ አጥቢያ፣ የብርሃን ፈለጎች በተሰኙ ጥራዞቹም ለአንባቢያን ቅርብ ነው፡፡ መጻሕፍትና ንባብን በተመለከተ በሚዘጋጁ የተለያዩ አምዶች ላይ እየተገኘ በሳቅ እያዋዛ እንደ ዋዛ የሚጥላቸው ሃሳቦችም ላሰተዋላቸው ሰው እጅጉን ቁምነገር የሞላቸው አሰደማሚ ሃሳቦች ናቸው፤ አለማየሁ ገላጋይ የ2008 የንባብ ለሕይወት አምባሳደር ነው፡፡

=========================================

- አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው

እኚህ ሰው በእግርኳስ ስፖርቱ ዘርፍ የማይረሳ አሻራ ያስቀመጡ ታሪካዊ ሰው ናቸው፤ ኢትዮጲያ ሌሎች የአፍሪቃ አገራት በባርነት እሳት በሚቃጠሉባቸው በእኒያ ዘመናት ነጻ አገር ከመሆንም አልፋ ስፖርትን ‹‹መዝናኛዋ›› ያደረገች ብሎም ‹‹አፍሪቃውያን የጋራ አንድነታችንን ወዳጅነታችንን ለማጠንከር እግርኳስ አንድ መንገድ ይሆነናል፤ ኑ የየሀገራችንን ቡድኖች ይዘን እንወዳደር›› የሚል ሃሳብ ፀንሳ፣ ሃሳቧንም በተግባር ለማሳየት ድግስ አሰናድታ ጎረቤቶቿን ጠርታ የአፍሪቃ ዋንጫን ጀመረች፡፡ ይህ ከሆነ አመታት በኋላ በጊዜ ሂደት የተሳታፊዎች ቁጥር በጨመረ መጠን ኢትዮጲያ ጉብዝናዋ እየከዳት ጭራሽ ከውድድሩ የራቀችበት ዘመን በዛ፡፡ ድግስ አዘጋጅታ ፣ምሳ አቅርባ ሰዎች ማዕዷን ሲቋደሱ በሩቅ ቆማ እንደምታይ ባልቴትም ተመሰለች፡፡ አቶ ሰውነት ቢሻው በህዝቡ ዘንድ ከህልምነት ሊዘል ያልቻለን አንድ ተልዕኮ በጊዜያዊነት በተቀመጡበት የአሰልጣኝነት መንበር ላይ ሆነው የኢትዮጲያ ብሔራዊ ቡድን ከሶስት አስርት አመታት በኋላ ወደ ውድድር፣ ኢትዮጲያንም በሩቅ ከምታየው ወጪት የመለሱ ሰው ናቸው፡፡ ለወጣቱ ትውልድ ማንበብን እንዲሰበኩ በማለም የ2008 የንባብ ለሕይወት የንባብ አምባሳደር ተደርገዋል፡፡

===========================================

- ደራሲና ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ

የሀገሩን ታሪክ የሚያወሳ የማይረሳ ሰው ነው፤ ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል ከሚለው ጥላ ስር የሚገኝ የታሪክ ፅሁፎችን በድምፁ እያጀበ ዘጋቢ በመሆን ምስል ከሳች አድርጎ ታሪክን ለማስተላለፍ ይታትራል፡፡ ታሪክ ይጠይቃል፤ የት ነበርን? ምን ነበረን? ማን ነበርን? ምን ነበርን? እያለ ይመረምራል ያገኘውንም መልስ በማስረጃ ያስደግፋል ከዚያም ለራሴ ብሎ ሳያስቀር ለሚያውቃቸው ሁሉ ያስተላልፋል፤ ይህን በብዙ ሰዎች ላይ የማይገኝ ውለታውን እንዲቀጥልበት ሌላ ሽልማት ሳይሆን አደራን ተረክቧል - የ2008 የንባብ ለሕይወት የንባብ አምባሳደር ነው፡፡


==========================================

- ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሴ


‹‹ፅልመት በወረሰው ለሊት
ድል አድራጊ ኮከብ ንግስት
በጠራራ ጸሃይ ቢያጧት
እስካሁን የትነበርሽ ያሏት››

የትነበርሽ፤ የትነበርሽ፤ የትነበርሽ፤ ብቻውን ስሟ እንደ ጥሩ ሙዚቃ ጆሮ ያነቃል፡፡ ንግግሯ ደግሞ ሌላ ዝንቅ ነው አንደበተ-ርቱዕ ናት፤ እሷ መሬት የማይጣሉ እንደዋዛ የማይተዉ ጉዳዮችን ስትተነትን፣ ስትናገር በርካቶች እጃቸውን በአፋቸው እየጫኑ ‹‹እውነትስ እንዲህ ስንደናበር እስካሁን የትነበርሽ?›› ብለውላታል፤ ፈገግታ ከፊቷ አይነጠፍም

‹‹መወደስ መከበር ያንሳታል
ለአይነት ለምሳሌ ፈጥሯታል
ምንም ያልጎደለው ስብዕና
አብዝቶ ያደላት ህሊና››

የ2008 የንባብ ለሕይወት አምባሳደር ናት፡፡

=========================================

- ፕሮፌሰር ያለምፀሃይ መኮንን

ትጉህ ተመራማሪና በሀገራችን ኢትዮጲያ ሙሉ የፕሮፌሰርነት ማዕረግን ያገኙ ብቸኛዋ ሴት፤ ለሽልማት እንግዳ ያልሆኑት እኚህ ቀና መምህር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2001 ዓ/ም የወርቅ፣ በ2015 ላሳዩት ተደናቂ የመሪነት ብቃት ኬኒያ ከሚገኝው አግሮፎረስተሪ የሚሰኝ ተቋም፣ እንዲሁም በተደጋጋሚ ጊዜ በጀርመን ሃገር ተሸላሚ ናቸው፤ ሰፊ ተነባቢነት ባላቸው በአለም ዙሪያ በሚዳረሱ የምርምር ሕትመት ውጤቶች ላይ ጥልቀት ያላቸው አሻራቸውንም አሳርፈዋል፤ ለንባብ ለሕይወት የ2008 አምባሳደር ናቸው፡፡

===========================================

- ደራሲና ገጣሚ በእውቀቱ ስዩም
በብዕሩ እሳት ይተፋል! በየትኛውም ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ሲያሻው ታሪክ እያዛመደ በትረካ፣ በል ሲለው በግጥም አለሁ ይላል፤ ‹መግባትና መውጣት› ፣ ‹እንቅልፍና እድሜ› አሻራቹ ያረፉባቸው ገጾችን የያዙ መጻሕፍት ናቸው፤ ወግ ያውቃል የተባ ብዕረኛ ነው፡፡ በእርሱ ዙሪያ የሚነሱ ክርክሮች ‹‹ብዙ ይቀረዋል›› በሚል እንጂ ችሎታውን ጥያቄ ምልክት አስከትሎ የሚፅፍበት የለም፡፡ በእውቀቱ ስዩም የ2008 የንባብ ለሕይወት የንባብ አምባሳደር ነው፡፡


===========================================


- ረዳት ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን

አንዳንዶች በአንድ ሙያ ላይ ለስኬት መንገድ ሲጀምሩ በአቦሸማኔ ፍጥነት ይምዘገዘጉና የማይሆኑትን እየሆኑ አልሳካ ብሏቸው በኤሊ ሩጫ ይሄዳሉ፤ በምድር ሲኖሩ አንድም ሶስትም አራትም ቦታ የሚሳካላቸው ጠንካራ ሰዎች ደግሞ አሉ ለያውም ‹‹ዕስስስስሰይ›› በሚያስብል አንጀት በሚያረሰርስ ብቃት፤ የዚህ ማሳያ ከሚሆኑ መካከል አንዱ ይህ ሰው ነው፤ መምህር፣ ሰዓሊ፣ ቀራፂ፣ ገጣሚ ነው፡፡ ሊናገር ወደ መደረክ ሲጠጋ ፈገግታ የሞላው ፊቱ የተኮሳተረ ሰውን ዘና ያደርጋል፤ የስዕል ስራዎቹን እዚሁ ኢትዮጲያ ውስጥ በተጨማሪ በአፍሪቃ ውቅያኖስ አቋርጦ በአውሮጳ፣ ሌላ ውቅያኖስ ተሻግሮም በአሜሪካ ከዝነኛ ሰዓሊያን ጎን ሆኖ ስራቹን አስተዋውቆ በስኬት እየታጀበ ተመልሷል፡፡ ወንዙን ለማሳመር ምንጩን እንጥረግ ብሎ እየሞገተም ሃገራችን የስነ-ጥበብ ት/ቤት እንዲኖራት አድርጓል፡፡ የ2008 የንባብ ለሕይወት የንባብ አምባሳደር ነው

============================================

*** በእለቱ ለመገኘት ባይመቸውም እሱም አምባሳደር ነው ***

- ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ

‹‹ተማር ልጄ
ስማ ልጄ
ወገን ዘመድ የለን ሃብት የለኝም ከእጄ
ተማር ልጄ
ሌት ጸሃይ ነው
ላልተማረ ሰው ግን ቀኑ ጨለማ ነው››
እያለ ገና ከጠዋቱ ትምህርትን ሲሰብክ የኖረ ከጥበብ የሚጠበቀውን ሁሉ ያበረከተ ሰው ነው፤ ለዚህ ሰው የንባብ አምባሳደርነት ሃላፊነት በክብር ተሰጥቶታል፡፡



*******************************************************************************************

ምንጭ:--ሰንደቅ ጋዜጣ_http://www.sendeknewspaper.com/arts-sendek/
- Biniam Kebede Wolde የፌስቡክ ገጽ               

ማሞ ካቻ (አቶ ማሞ ይንበርብሩ)

  አቶ ማሞ ይንበርብሩ (ማሞ ካቻ) እስቲ እናስታውሳቸው፣ ተቀብሮ እንዳይቀር አኩሪ ታሪካቸው  (ደረጀ መላኩ)   አቶቢሲ ማሞ ካቻ የት ትሄዳለህ? ገብረ ጉራቻ… ታዳጊው ማሞ ይንበርበሩ ገና በጨቅላ እድሜው አባቱ አቶ...