ሐሙስ, ኖቬምበር 16, 2023

ማሞ ካቻ (አቶ ማሞ ይንበርብሩ)

 

አቶ ማሞ ይንበርብሩ (ማሞ ካቻ) እስቲ እናስታውሳቸው፣ ተቀብሮ እንዳይቀር አኩሪ ታሪካቸው 

(ደረጀ መላኩ)

 

አቶቢሲ ማሞ ካቻ

የት ትሄዳለህ? ገብረ ጉራቻ…

ታዳጊው ማሞ ይንበርበሩ ገና በጨቅላ እድሜው አባቱ አቶ ይንበርበሩ በሥራ ምክንያት ወደ ኢሊባቦር ጎሬ ሲዛወሩ አብሮ ሄደ። ብዙም ሳይቆይ አባቱ የጣልያንን ወራሪ ኃይል ለመከላከል ዘምተው፤ በማይጨው ጦርነት የተሰው ሲሆን እናቱ በህመም ምክንያት ቀደም ብለው ሞተው ስለነበር ገና በ12 ዓመት እድሜው ያለ ወላጅ ቀረ። ወላጅ አልባውን ታዳጊ፤ ለግዜው የኢትዮጵያን ሠራዊት አሸንፈው ከገቡት የጣልያን የጦር መኮንኖች አንዱ አግኝቶት ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ይዞት መጣ።

ታዳጊው ማሞ አንበርብር አዲስ አበባ በመምጣቱ የዕለት ጉርሱን የማግኘት እድሉ ቀለል አለለት። እዛው አካባቢ የሚገኝን ሻይ ቤት ተጠግቶ ብርጭቆ እያጠበና እየተላላከ በክፍያ መልክ ምግቡን እየሰጡት ኑሮውን ጀመረ።

ብልህና ፈጣን ልጅ የነበረው ማሞ አንበርብር በሻይቤቱ ሥራ ብዙም ሳይቆይ፤ በራሱ ሠርቶ ገንዘብ የሚያገኝበትን መንገድ ማሰብ ጀመረ። አስቦም ያገኘው ዘዴ፤ አራት ኩሽኔታ የተገጠመለት መቀመጫ ያለው ተሽከርካሪ ሠርቶ፤ ህጻናትን አሳፍሮ እየጎተተ ከሠይጣን ቤት (ከቴዎድሮስ አደባባይ) እስከ ቴሌኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ድረስ እያንሸራሸረ ገንዘብ ማስከፈል ነበር። ቀስ በቀስ ሳንቲሙ እየተጠራቀመ ሲመጣ አሁንም ሌላ የሕጻናት ማንሸራሸሪያ ተሽከርካሪ አዘጋጀ። ይህ ተሽከርካሪ ሳይክል ሲሆን ፔዳልም ሆነ ካቴና የሌለው አሮጌ ነበር። በሁለቱ ጎማዎች ምትክም ማሞ ራሱ ቆራርጦ የሠራቸው ተሽከርካሪዎች ተገጥመውለት አሁንም እሱን እየጎተተ ሕጻናትን በማንሸራሸር የተሻለ ገንዘብ ማግኘት ጀመረ፡፡

 

ይህን ማሞን ጥረት ያስተዋለ አንድ የጣልያን ጦር መኮንን ወደ ምፅዋ በሚሄድበት ጊዜ ማሞን ይዞት ሔዶ፤ ከምፅዋ ሃያ የሚሆኑ ትክክለኛ ሳይክሎችን ገዝቶ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ረዳው።

አሁን የሃያ ሳይክሎች ባለቤት የሆነው ማሞ ሳይክሎቹን እያከራየ ከበፊቱ የተሻለ ገንዘብ ማጠራቀም ጀመረ።

በዚህ ሁኔታ ገንዘቡ እያደገለት እያለ የጣልያን ጦር በተራው ተሸነፈና እንግሊዞች ተተኩ። ለውጡን ተከትሎ ጣልያኖች ኢትዮጵያን ለቅቀው ሲወጡ መኪኖቻቸውን በችኮላ እየሸጡ ነበርና ወጣቱ ማሞም አንዲት ፎርድ ፒክ አፕ በ108 ብር ገዝቶ ከአዲስ አበባ ወሊሶ እና ወልቂጤ ሕዝብ ማመላለስ ጀመረ።

ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው እንግዲህ አቶ ማሞ አንበርብር አውቶቡስ በመግዛት የሕዝብ ማመላለስ አገልግሎታቸውን ማጠናከር የቻሉት። ከዛ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ የሶስት ቀኑን መንገድ በሁለት ቀንና በአንድ ቀን ተኩል በመግባት ሕዝቡን ማስደነቅ ጀመሩ። የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የነበረው ህብረተሰብም ለጉዞ ቀዳሚ ምርጫው የአቶ ማሞ አንበርብር አውቶቡስ ሆነ።

የዚህ አስደናቂ ስራቸው ውጤት የአባታቸውን ስም አስትቶ ከስማቸው ቀጥሎ ‘ካቻ’ በሚል ቅፅል ስም እንዲጠሩ ምክንያት ሆነ። ብሎም እጅግ ታዋቂ ሊሆኑ ቻሉ። ‘ካቻ’ ማለት የጣልያን ፈጣን መትረየስ ተኳሽ አውሮፕላን መጠሪያ ነበር። አሁን ተዋጊ ጀት እንደ ሚባለው።

ይህ ድርጅት ከሌሎቹ ሻል ያሉ መንገዶች እየተመረጡ ስለሚሰጡት አቶ ማሞና ሌሎቹም ግለሰቦች ለእነሱም እንዲህ አይነት መስመር እንዲሰጣቸው ከመጎትጎት አልፈው በየስማቸው ማህበር በማቋቋም የአውቶቡሳቸውንም ቁጥር በመጨመር በሁሉም መስመር ለመሳተፍ ጥረት ማድረጉን ቀጠሉ።

በዚህ ጊዜ የድርጅታቸውን ስም በታወቁበት ስም ‘ማሞ ካቻ’ ብለው ሰየሙት። ይህን ሁሉ ተግባር የፈፀሙት አቶ ማሞ ማንበብና መጻፍ እንኳን የማይችሉ ነበሩ።

 

አንድ ቀን ከእሳቸው ጋር ጭቅጭቅ የነበረው ሰው ሞቶ በመገኘቱ ተጠርጥረው ማስረጃ ባይገኝባቸውም አስራ አምስት አመታት ተፈርዶባቸው ወህኒ ወረዱ። በዛን በእስር ጊዜአቸው ነበር አብረው የታሰሩ ምሁራንን እየጎተጎቱ አማርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋ ማንበብ የቻሉት። እንዲሁም መደበኛ ሒሳብም መሥራት ቻሉ።

የሚመሩት የትራንስፖርት ድርጅት ያለው አስተዋፅኦ ታይቶ በእስር ጊዜአቸው ከእስር ቤት በሳምንት ሁለት ቀን እየወጡ ሥራቸውን አከናውነው እንዲመለሱ ተደርጎ ነበር። በ 1960 ዎቹ መግቢያ ላይ ከእስር ቤት ወጡ። እንግዲህ ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ነው አንድ አስደናቂ ተግባር ያከናወኑት። ነገሩ እንዲህ ነው ፦

የንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅት ንብረት ነው የሚባለው የአንበሳ አውቶቡስ ድርጅት ሰላሳ አውቶቢሶች እንዲሠሩለት ለፊያት ካምፓኒ ያዝዛል። ከሰላሳዎቹ ግማሹ ተሠርተው አዲስ አበባ ደርሰው አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ባልተጠበቀ ሁኔታ ተመሳሳይ ችግር ያስተናግዱ ጀመር። ሕዝብን ጭነው በሚጓዙ ጊዜ የፊት ጎማቸው እየፈነዳ መገልበጥ ወይም ከመስመር እየወጡ መጋጨት ተግባራቸው ሆነ። ገናም አምስት እና ስድስቱ ተመሳሳይ አደጋ እንደደረሰባቸው፤ አቶ ማሞ ጭንቅላት ውስጥ “ለምን ይሆን?” የሚል ጥያቄ ተነሳ።

አንድ ቀን ማሞ ካቻ ከሻሸመኔ ወደ አዲስ አበባ እየነዱ ሳለ፤ አንድ አውቶቡስ ጥሩምባ ነፍቶ አለፋቸው። ይህ ጥሩምባ ነፍቶ ያለፈው አውቶቡስ አዲስ ከመጡት አንዱ በመሆኑ የማሞ ካቻን ትኩረት ሳበ። እናም ‘ለምን ይሆን?’ የሚለው ጭንቅላታቸው ውስጥ ያለው ጥያቄ ምናልባት መልሱ ቢገኝለት ብለው በማሰባቸው፤ መኪናቸውን አዙረው አውቶቢሱን መከተል ያዙ። አውቶቢሱ ሻሸመኔ ደርሶ ወደ ጎባ መንገድ ታጠፈ ተከተሉት፣ ዶዶላን አለፈ፣ ማሞ ካቻም አለፉ አውቶቢሱ ዶዶላን አልፎ ሲገሠግስ ድንገት ቁልቁለት ላይ የፊቱ ጎማ ፈነዳና ከመንገድ ወጥቶ ከአንድ ቋጥኝ ጋር ተጋጭቶ ቆመ።

ማሞ ካቻም መኪናቸውን አቁመው፤ ዱብ! ብለው ወረዱና ወደ አውቶቢሱ ተጠግተው ሁኔታውን መመርመር ጀመሩ፤ እናም ችግሩን ደረሱበት።

ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ ጊዜ ሳያ ጠፉ ወደ ጣልያን (የፊያት ኩባንያ ወደሚገኝበት ወደ ቶሪኖ) በረሩ። እንደደረሱም በቀጥታ ወደ ኩባንያው አምርተው ፕሬዚዳንቱን እንዲያገናኟቸው ጠየቁ…..።

እንግዲህ በደምቡ መሠረት ማንኛውም ባለ ጉዳይ አንድ ባለ ሥልጣንን ለማግኘት ከፈለገ ጉዳዩን አስረድቶ በቅድሚያ ቀጠሮ ማስያዝ የግድ ነው። የቀጠሮው ቀን ሲደርስ ቀድመው ተዘጋጅተው ስለሚጠብቁት በተያዘለት ቀንና ሰዓት ተስተናግዶ ይመለሳል። ዛሬ ግን የኩባንያው እንግዳ ተቀባዮች የመጣባቸው ሰው ለየት ያለ ሆነባቸው።

እንደደረሰ ምን እንደፈለገ ጠየቁት። ማሞ ካቻም

“የኩባንያውን ፕሬዚዳንት ማግኘት እፈልጋለሁ!” ብለው መለሱ።

“ለመሆኑ ቀጠሮ ይዘው ነበር?”

“ቀጠሮ እንኳን አልያዝኩም”

“እሺ ቀጠሮ ይዘው ይመለሱና በቀጠሮው ዕለት ይምጡ!”

“በፍፁም ቀጠሮ ተቀብዬማ አልመለስም! ዛሬውኑ፤ ያውም አሁኑኑ በአስቸኳይ አገናኙኝ! ለዚህ ብዬ ነው ከኢትዮጵያ ድረስ የመጣሁት!” ብለው ድርቅ አሉ።

እንግዳ ተቀባዮቹ ይሄ ከደንቡ ውጭ፣ ያለ ቀጠሮ፣ ድንገት መጥቶ ‘ከፕሬዚዳንቱ ጋር አገናኙኝ!’ ብሎ ያስቸገረ ሰው፤ ግራ አጋባቸው። ሰውዬው ጥቁር መሆኑ ደሞ የበለጠ አነጋጋሪ ሆነ። አነጋጋሪው ወሬ እያነጋገረ ሄዶ ከእንግዳ ተቀባዮቹ አልፎ ፕሬዚዳንቱ ዘንድ ደረሰ።

… … ቀጠሮ ያልያዘ፣ ጥቁር ሰው፣ ከደምቡ ውጭ ፕሬዚዳንቱን ማግኘት ይፈልጋል! 

 About | Mamo Kacha - Inspiring History

የጥቁሩ ሰው ወሬን የሰማው ፕሬዚዳንት ነገሩን ሲሰማ፤ ሊያነጋግረው ፍቃደኛ ሆነና ማሞ ካቻ እንዲገቡ ተፈቀደላቸው። ከፕሬዚዳንቱ እንደተገናኙ በቀጥታ ወደ ጉዳያቸው የገቡት ማሞ ካቻ

“ኢትዮጵያ ለሚገኘው አንበሳ አውቶቡስ ድርጅት ሰላሳ አውቶቢሶች ለመሥራት ተስማምታችሁ እስካሁን አስራ አምስቱን ወደ ኢትዮጵያ ልካችኋል!” አሉ። ፕሬዚዳንቱም

“ትክክል ነዎት!” አለና አረጋገጠላቸው።

“ወደ ኢትዮጵያ የላካችኋቸው አውቶቡሶች የፊት ጎማቸው እየፈነዳ ሕዝቡን ለአደጋ እያጋለጡት ነው። እስካሁን አምስትና ስድስት ያህሉ ይህ ነገር ገጥሟቸዋል!”

“አዎ ትክክል ነዎት። ጉዳዩን ሰምተናል። በእኛ በኩል ችግሩን እያጠናንው ነው።”

“እኔ ግን ችግሩን ተከታትዬ ደርሼበታለሁ። ካስፈለገም በቀላሉ አስተካክለዋለሁ!”

“እርስዎ አገኘሁ ያሉትን ችግር እስቲ ይንገሩኝ?”

“ኩባንያው ሲያመርታቸው የቴክኒክ ስህተት ስለሠራ ነው።”

“እሱማ በፍፁም ሊሆን አይችልም! እዚህ ኩባንያ ውስጥ እኮ ያሉት ኢንጅነሮች በትምህርትም ሆነ በልምድ በአገሪቱ አሉ የተባሉት ናቸው!”

“ሊሆኑ ይችላል። ግን ተሳስተዋል!”

“ምኑ ላይ ነው የተሳሳቱት?”

“የአውቶቡሶቹ ሞተር ከፊት ነው ያለው!”

“አዎ”

“ሞተሩ ከፊት መሆኑ ብቻ ችግር አይሆንም ነበር፤ ግን የመንገደኞች እቃ መጫኛም የሚገኘው የአውቶቡሱ የፊት አካል ላይ ነው። ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል? ሞተሩ የራሱ ክብደት አለው። የመንገደኞች ዕቃም ተጨማሪ ክብደት ነው።

“ጭነቱ ተመጣጥኖ የመኪናው ሙሉ ጎማዎች መሸከም ሲኖርባቸው የፊተኛው ክፍል ላይ ብቻ አርፏል። ይሄ ደሞ የፊት ጎማው የመኪናውን ክብደት ሁሉ እንዲሸከም ያስገድደዋል። የፊት ጎማውን ደጋግሞ የሚያፈነዳውም ምክንያቱ ይሄ ነው!” ማሞ ካቻ በእርግጠኝነት ተናገሩ።

የማሞ ካቻ ሀሳብ ስላሳመነው ፕሬዚዳንቱ በአስቸኳይ ኢንጅነሮቹን ሰበሰበ። እናም ማሞ ካቻ የተናገሩትን ነገራቸው። እነሱም ‘በፍፁም አይደለም!’ ብለው ከማሞ ካቻ ጋር ተከራከሩ። ማሞ ካቻ የሚያነሱት መከራከሪያ በመጠኑም አሳማኝ ስለሆነባቸው፤ አንዱን መኪና ብቻ እሳቸው ባሉት መንገድ አስተካክለውት እንዲሞከር ተስማሙ።

አቶ ማሞ ወደ አዲስ አበባ እንደተመለሱ አንዱን አውቶቡስ ተረክበው ፋብሪካው የሠራውን የዕቃ መጫኛ አስነሱ። በመቀጠል በላሜራ አንድ ሜትር ከሃያ ሳ·ሜ ርዝመት ያለው ዕቃ መያዣ በአውቶቡሱ የኋላና መካከለኛው ክፍል ላይ አሠርተው አስረከቡ።

ይህ ማሞ ካቻ ያስተካከሉት መኪና ክትትል ተደረገበት። እንደሌሎቹ የፊት ጎማው ሳይፈነዳ ሕዝብ ማገልገሉን ለረጅም ጊዜ ቀጠለ።

አሁንም ሌላ አውቶቡስ እንዲያስተካክሉ ተደረገና ይሄም ተጠና። ውጤቱም እንደ መጀመሪያው አጥጋቢ ሆነ። አንድ ጥቁር፣ በትምህርቱ ያልገፋ፣ ግና ብሩህ አእምሮ ያለው ኢትዮጵያዊ፤ የጣልያንን በትምህርትም በልምድም አሉ የተባሉ መሀንዲሶችን ስህተት ነቅሶ አሳየ። ጣልያኖቹም በማሞ ካቻ ችሎታ ተደነቁ! እናም ወደ ኢትዮጵያ የገቡትን አውቶቡሶች በሙሉ እንዲያስተካክሉ ኩባንያው ፈቀደላቸው።

ሥራውን ከመጀመራቸው በፊት ግን የአንበሳ አውቶቡስ ድርጅት ጣልቃ ገባና ‘እኛ ይሄን ማስተካከል የሚችሉ በቂ ቴክኒሽያኖች ስላሉን እነሱ ያስተካክሉታል!’ ብለው ማሞ ካቻን ገሸሽ አደረጓቸው። በማሞ ካቻ ዲዛይን መሠረትም አውቶቡሶቹን በሙሉ አስተካከሏቸው።

የፊያት ኩባንያ ግን ገሸሽ አላደረጋቸውም፤ ይልቅ ለፈጠራቸው ክብር ሞዴል 220 መርሴዲስ መኪና ሸለማቸው።

ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ደርግ ከተፍ አለ። እናም ያገኘውን ሁሉ መውረስ ጀመረ። እንግዲህ ደርግ አላማዬ ያለው ፦ የሰፊውን ህዝብ ንብረት አላግባብ (በግፍ) በዝብዘው ሀብት ያከማቹትን ጨቋኝ ፊውዳሎች፤ ንብረትና ሃብት ነጥቆ ለተጨቋኙ ሰፊው ሕዝብ ጥቅም ማዋል ቢሆንም፤ ‘ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ፣ አብረህ ተወቀጥ!‘ እንዲሉ አቶ ማሞን እና አንዳንድ በራሳቸው ጥረትና ድካም ለፍተው ሕዝብን በዝብዘው ሳይሆን፤ ሕዝብን አገልግለው በጥረታቸው ሀብት ያፈሩትንም ግለሰቦች አላግባብ ንብረታቸውን ወርሶባቸው ነበር።

ወላጆቻቸውን በልጅነት እድሜ አጥተው የዕለት ጉርስ ለማግኘት ኩሽኔታ በማከራየት፤ ከታች ተነስተው በጥረታቸው ሀብት ያፈሩት ማሞ ካቻም፤ ተመሳሳይ ዕጣ ደርሷቸው ንብረታቸው ተወርሶ፤ እሳቸውም ተወርሰው በወር 2500 (ሁለት ሺህ አምስት መቶ) ብር ብቻ እየተከፈላቸው እንዲኖሩ ተደረገ።

ብርቱው ማሞ ካቻም በተቻላቸው መጠን መወረስ እንደሌለባቸው ተከራከሩ። “የእኔ ሀብት የመጣው በጥረት እንጂ ከፊውዳል አባት፣ ከአያቴ የወረስኩት አይደለም! እኔ ከድህነት ተነስቼ እዚህ ደረጃ መድረሴ፤ ደርግ ቆሜለታለሁ ያለውን ሰፊውን ሕዝብ ያስተምራል ያበረታታል! ሌላውም ጥሮ፣ ግሮ፣ ሠርቶ ለማደግ እንዲፍጨረጨር ያደርጋል! የአንድን ሰው የድካም ውጤት መውረስ ግን ምንም አይነት ትምህርት ሊሰጥ አይችልም!” እያሉ ተከራከሩ። ሰሚ ጆሮ ግን አላገኙም። የማሞ ካቻ ክርክር ፍሬ አጥቶ፤ ድርጅታቸው እንደተወረሰ በሠራተኛ ማህበር መተዳደር ቀጠለ። ሠራተኛ ማህበሩ ግን ያን ማሞ ካቻ በብቃት ሲያስተዳድሩት የነበረውን ድርጅት ማስተዳደር አቃተው።

 

ገቢው እያሽቆለቆለ መጣ። ቆይቶም ለሠራተኛ ደምወዝ መክፈል ተሳነው። ቢቸግረው አንድ አውቶቡስ ሸጠና ደሞዝ ከፍሎ ተገላገለ፤ አሁንም ችግር አፍጦ መጣ! ሌላ አንድ አውቶቡስ ጆሮውን አለና ችግሩን ተወጣ። ሌላችግር፣ ሌላ አውቶቡስ ሽያጭ … … እየቀጠለ፤ ለችግር መፍቻ አውቶቡስ መሸጥ የተለመደ መፍትሄ ሆነ። አራት አውቶቡሶች ከተሸጡ በኋላ ግን የደርግ መንግሥት ነገሩን አሰበበት፤ እናም ‘ያለ ባለቤቱ፣ አይነድም እሳቱ!’ እንዲሉ ማሞ ካቻን ጠርቶ ንብረታቸውን አስረከባቸው። ድርጅታቸውን መልሰው የተረከቡት ማሞ ካቻም እስከ ህይወታቸው ፍጻሜ ድረስ በብቃት ሲመሩት ቆይተዋል።

Mamokacha PLC offers a diverse portfolio of products, including coffee produce, coffee shops, restaurants, wineries, dairy products, and hotels.

 

Joe Mamo, D.C.’s Gas-Station Masterowns half of D.C.’s filling stations

To hear him tell it, Joe Mamo’s move from Ethiopia to North Dakota in 1981 was accidental.

Mamo’s father, Yenberber Mamo, was a public transit mogul who manufactured buses and ran the first fleet to provide service across Ethiopia. The operation made his father’s Mamo Kacha bus line a household name in the East African country. 

It provided a nice life for his family. But it rendered him distinctly unpopular with the Marxist junta that ruled Ethiopia between 1974 and 1991. The elder Mamo was jailed two or three times by the regime. Some of his property was confiscated. As his son approached draft age, the patriarch looked for ways to send him overseas.

That’s how Joe, at the age of 13, found himself attending Catholic boarding school in North Dakota.

 

[ ከብርሃኑ አስረስ (የታህሳስ ግርግርና መዘዙ መጽሐፍ) የተወሰደ ]

ጭ:-- https://ethioreference.com/archives/32437 

            https://mamokachaplc.com/about-mamokacha/

            https://washingtoncitypaper.com/article/220817/joe-mamo-dc-gas-station-master/



ዓርብ, ኖቬምበር 18, 2022

አማርኛ ቋንቋ ከውጪ ቋንቋዎች የተዋሳቸው ቃላት

 አማርኛ ቋንቋ ከውጪ ቋንቋዎች የተዋሳቸው ቃላት

ምሳሌዎች፦


  • ከግሪክኛ፦ ጠረጴዛ
  • ከአረብኛ፦ ባሩድ
  • ከቱርክኛ፦ ሰንደቅ
  • ከፈረንሳይኛ፦ ባቡር
  • ከጣልኛ፦ ቡሎን
  • ከእንግሊዝኛ፦ ኢንተርናሽናል



የሀገራችን ቋንቋዎች ከውጪ ቋንቋዎች በርካታ ቃላትን ወርሰዋል፡፡ ይህም ከብሉይ ዘመን ጀምሮ ይታይ የነበረ ክስተት ነው፡፡ የመወራረሱ አድማስ ስፋቱን የጨመረው ግን በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በቀጣዮቹ አንድ መቶ ሀያ ዓመታት ውስጥ የታዩት ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ክስተቶች የሀገራችን ቋንቋዎችን ለውጪ ቋንቋዎች ተጽእኖ የበለጠ ክፍት እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል፡፡

ታዲያ ከሶስት ሺህ ከሚልቁት የውጪ ቋንቋዎች መካከል ለሀገራችን ቋንቋዎች ብዙ ቃላትን ለማውረስ የበቁት አራቱ ብቻ ናቸው፡፡ እነርሱም 

ዐረብኛ፣ 

ፈረንሳይኛ፣ 

ጣሊያንኛና 

እንግሊዝኛ ናቸው፡፡ 

የቱርክ እና የጀርመን 

ቋንቋዎችም ጥቂት ቃላትን ለሀገራችን ቋንቋዎች አበርክተዋል፡፡

*****

ዐረብኛ በሀገራችን ቋንቋዎች ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር የቻለው በዋናነት የእስልምና ሀይማኖት የአምልኮና የትምህርት ቋንቋ ስለሆነ ነው፡፡ በመሆኑም ከእስልምና እምነት ጋር በተያያዘ ለአምልኮና ለትምህርት አገልግሎት ላይ የሚውሉ ቃላት በአብዛኛው ከዐረብኛ የተገኙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ መስጊድ/መስጂድ፣ ኢማም፣ ቃዲ፣ አዛን፣ መጅሊስ፣ መድረሳ ወዘተ… የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሂደት ደግሞ የዐረብኛ ቃላት በአምልኮ ውስጥ ካላቸው አስፈላጊነት አልፈው በተራው ሰው ንግግር ውስጥም ገብተዋል፡፡ ይህ ክስተት በስፋት የሚስተዋለው ግን አብላጫው ነዋሪ ህዝብ ሙስሊም በሆነባቸው እንደ ወሎ፣ ሀረርጌ፣ ባሌ፣ ጅማ፣ ሶማሊ (ኦጋዴን)፣ ቤኒሻንጉልና አፋር አካባቢዎች ነው፡፡ በነዚህ አካባቢዎች ከሚነገሩት ቋንቋዎች “መርሐባ”፣ “አሕለን”፣ “ፉጡር”፣ “ሀድራ”፣ “ሙሐባ”፣ “መናም”፣ “ጂስም”፣ “አዛ”፣ “ኩርሲ”፣ “ማዕና”፣ “ዒልም”፣ “አስል” እና ሌሎች በርከት ያሉ የዐረብኛ ቃላትን በቀላሉ ለይቶ ማውጣት ይቻላል፡፡

ታዲያ የዐረብኛ ቃላትን የመውረሱ ተግባር በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩል ደረጃ የሚጠቀምባቸው በርከት ያሉ የዐረብኛ ቃላትንም ወርሰናል፡፡ ይህም ክስተት የተፈጠረው ከንግድ መስፋፋት ጋር ነው፡፡ በተለይ እስከ አስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ድረስ የሀገራችንን ንግድ በበላይነት ተቆጣጥረው የነበሩት ሲራራ ነጋዴዎች ዐረብኛን በንግድ ቋንቋነት በስፋት ይጠቀሙበት የነበረ ከመሆኑ የተነሳ በሀገራችን ቋንቋዎች ውስጥ መሰረት ያልነበራቸው በርካታ ቃላት እንዲወረሱ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ለምሳሌ ዛሬ የአማርኛ ቃላት አድርገን የምንጠቀምባቸው እንደ  

ሀዋላ፣ 
ጉምሩክ፣ 
ሰንዱቅ፣ 
ሱቅ፣ 
መጋዘን፣ 
ሽርክና፣ 
ወኪል፣ 
ሰነድ፣ 
ደላላ፣ 
መሃለቅ 

ወዘተ የመሳሰሉት የአማርኛ ቃላት ምንጫቸው ዐረብኛ ነው፡፡ 

እንደ 
ሐዲድ፣ 
ባቡር እና 
መኪና የመሳሰሉ ቃላትም ከዐረብኛ ነው የተወረሱት፡፡ 

ይሁንና ዐረብኛና አማርኛ ሴማዊ ቋንቋዎች በመሆናቸው የሚጋሯቸውን ቃላት እንደ ውርስ ቃላት ማየት ስህተት ነው፡፡ ለምሳሌ ሰላም፣ ደም፣ ቤት፣ ፎቅ፣ ክፍል፣ ዐይን፣ ፈረስ፣ ዘመን፣ ሐሩር፣ ሚዛን የመሳሰሉ ቃላት በሁለቱም ቋንቋዎች ውስጥ አሉ፡፡ ሁለቱም ቋንቋዎች ሴማዊ በመሆናቸው ነው እነዚህን ቃላት የተጋሩት፡፡ የነዚህ ቃላት መነሻ የሁሉም ሴማዊ ቋንቋዎች አባት እንደሆነ የሚታመንበት ግንደ-ሴማዊ ቋንቋ (Proto-Semetic Language) ነው፡፡

*****

አዲስ አበባን ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኘው የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር መስመር ሲሰራ ደግሞ ፈረንሳይኛ ወደ ሀገራችን ቋንቋዎች እየሰረገ መግባት ጀምሮ ነበር፡፡ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትም በ1910ዎቹ ውስጥ ሲከፈት የፈረንሳይኛ ተጽእኖ በጣም ተጠናክሯል፡፡ የዘመኑ የትምህርት ካሪኩለምም ከፈረንሳይ የተቀዳ በመሆኑ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና ምሩቃኑ ፈረንሳይኛን ይናገሩ ነበር፡፡ በነዚያ ምሩቃን በተሞላው ሲቪል ሰርቪስም ሆነ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ፈረንሳይኛ እንደ ሁለተኛ ቋንቋ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ለመንግሥታዊ አገልግሎት የሚያስፈልጉ ሰነዶችና የስራ መመሪያዎችም ከፈረንሳይኛ ሲተረጎሙ ነው የኖሩት (የመጀመሪያው ህገ-መንግሥትም ከፈረንሳይ የተቀዳ ነው)፡፡  በዚህም ሂደት በርካታ የፈረንሳይኛ ቃላት በአማርኛ ተወርሰዋል፡፡ 

ከፈረንሳይኛ ከወረስናቸው ቃላት መካከል 

“ኦፊሴል”፣ 
“ሞኖፖል”፣ 
“ሌጋሲዮን”፣ 
“ኮሚስዮን”፣ 
“ፔኒስዮን”፣ 
“ዲክላራሲዮን”፣ 
“ኦፕራሲዮን”፣ 
“ካሚዮን”፣ 
“ፍሪሲዮን”፣ 
“ሬኮማንዴ”፣ 
“ለገሀር (ላጋር)፣ 
“ቡፌ”፣ 
“ሌሲ ፓሴ”፣ 
“ዴኤታ”፣ 
“ ካፌ”፣ 
“ራንዴቩ”፣ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡

የኢጣሊያ ወረራ ከተወልን ማስታወሻዎች መካከል ትልቁ በሀገራችን ቋንቋዎች ውስጥ የሚታየው የጣሊያንኛ ተጽእኖ ነው፡፡ በአማርኛ፣ ኦሮምኛና ትግርኛ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጣሊያንኛ ቃላትን መቁጠር ይቻላል፡፡ በተለይም በቀድሞ ዘመናት ከተሽከርካሪ እና ትራንስፖርት እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም ከኢንዱስትሪ ጋር በተያያዘ ከሚሰራባቸው ቃላት መካከል ብዙዎቹ የጣሊያንኛ መሰረት ያላቸው ናቸው፡፡ ዛሬም ድረስ የነዚያ ቃላት ቅሪቶች በሀገርኛ ቋንቋዎች ውስጥ ይስተዋላሉ፡፡ 

ከጣሊያንኛ ከወረስናቸው ቃላት መካከል 

“ፓስታ”፣ 
“ማካሮኒ”፣ 
“ላዛኛ”፣ 
“ስፓጌቲ”፣ 
“ስልስ” (ሳልሳ)፣ 
“አሮስቶ”፣ 
“ፋብሪካ”፣ 
“ጋዜጣ”፣ 
“ሊቼንሳ”፣ 
“ፉርኖ”፣ 
“ቪያጆ” (በመኪና የሚደረግ ጉዞ)፣ 
“ላቫጆ”፣ 
“ካሮሴሪያ”፣ 
“ካምቢዮ”፣ 
“ሞቶሪኖ”፣ 
“ፍሬን”፣ 
“ፊልትሮ”፣ 
“ሳልቫታዮ”፣ 
“ፖርቶ መጋላ”፣ 
“ፒንሳ”፣ 
“ቺንጊያ” ፣ 
“ፈረፋንጎ”፣ 
“ኩሽኔታ” 
“ኪያቤ”፣ 
“ካቻቢቴ” 
“ባሌስትራ”፣ 
“ቸርኬ” 
“ፒስታ” 
“ኮማርዳሬ” 
“ጎሚኒ” 
“ሮንዴላ” 
“ዲፍረንሻሌ” 
“ስፒናታ” 
“ሳልዳሬ” 
“ቡኮ”፣ 
“ፖምፓ” (ቧንቧ)፣ 
“አውታንቲ”፣ 
“ማኖ”፣ 
“ኢሊ ጎሬ”፣ 
“ቴስታ”፣ 
“ፑንቶ”፣ 
“ቦጦሎኒ”፣ 
“ካምቦ” ወዘተ…. የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

*****

ጣሊያኖች ከተባረሩ በኋላ እንግሊዝኛ በሀገርኛ ቋንቋዎች ውስጥ ሰርጾ መግባት ጀመረ፡፡ በተለይ እንግሊዞች በኢትዮጵያ ውስጥ በነበሩባቸው አስር ዓመታት የእንግሊዝኛ ቃላት በሀገራችን ቋንቋዎች በብዛት ተወረሱ፡፡ በዚያን ጊዜ ከተወረሱት ቃላት ውስጥ እስከ አሁን ድረስ በአገልግሎት ላይ ያሉትን እንደ 

“ፖሊስ”፣ 
“ባንክ”፣ 
“ሚኒስቴር”፣ 
“ካፒታል”፣ 
“ኤሌክትሪክ”፣ 
“ኮሌጅ”፣ 
“አካዴሚ”፣ 
“ኤክስፐርት”፣ 
“ዲሬክተር” የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ 

እንዲሁም እንደ 

ፕሮፌሰር፣ 
ዶክተር፣ 
ኢንጂነር፣ 
ጄኔራል፣ 
አድሚራል፣ 
ኮሞዶር፣ 
ኮሎኔል እና 
ካፒቴን የመሳሰሉ የማዕረግ ስሞችም የተወረሱት ከእንግሊዝኛ ነው፡፡

በእንግሊዝኛ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የተነሳ ፈረንሳይኛና ጣሊያንኛ በሀገራችን ቋንቋዎች ላይ የነበራቸው ተጽእኖ በፊት ከነበረበት ደረጃ ሊያድግ አልቻለም፡፡ ነገር ግን በሀገራችን ቋንቋዎች የተወረሱት የጣሊያንኛና የፈረንሳይኛ ቃላት በዘመኑ አገልግሎት መስጠታቸውን አላቆሙም፡፡ ለምሳሌ በቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ዘመን “ኮሚሲዮን” እንጂ “ኮሚሽን” የሚባል የአማርኛ ቃል አይታወቅም፡፡ ከፈረንሳይኛና ከጣሊያንኛ የተወረሰ የሀገርና የከተማ አጠራርም ቢሆን በአማርኛ ቋንቋ አንዳች ለውጥ ሳይደረግበት ያገለግል ነበር፡፡ እንደ ምሳሌም “ቤልጅግ”፣ “ስዊስ”፣ “ሎንዶን”፣ “መስኮብ”፣ “ብሩክሴል” የመሳሰሉትን የሀገርና የከተማ ስሞች መጥቀስ ይቻላል፡፡

ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ መንግሥት ውድቀት በኋላ ግን ከፈረንሳይኛና ከጣሊያንኛ የተገኙ የሀገርና የከተማ ስያሜዎች ከእንግሊዞች በተወረሱ ስሞች ተተክተዋል፡፡ በዚህም መሰረት “ቤልጅግ” ወደ “ቤልጅየም”፤ “ስዊስ” ወደ “ስዊትዘርላንድ.፣ “ብሩክሴል” ወደ “ብራሰልስ”፣ “መስኮብ”ም ወደ “ሞስኮ” ተለውጠዋል፡፡ በመሆኑም ከልዩ ልዩ  ቋንቋዎች በተገኙ የቦታ ስያሜዎችና ቃላት ተውቦ ይታይ የነበረው አማርኛ የመኮማተር ባህሪን ለማዳበር ተገዷል፡፡

ይህ ቀደምት ውርስ ስሞችን በእንግሊዝኛ አጠራሮች የመተካቱ ሂደት ሳያቋርጥ በመቀጠሉ ከሁለቱ ቋንቋዎች (ከፈረንሳይኛና ጣሊያንኛ) የተወረሱ የሀገር ስሞችን ከማራገፍ አልፎ በጥንታዊው አማርኛ ውስጥ መሰረት የነበራቸውን የሀገር ስሞችንም በእንግሊዝኛ ስያሜዎች መለወጥ ተጀምሯል፡፡ ለምሳሌ የዓለም ትልቋ ሀገር ከጥንት ጀምሮ በአማርኛ ስትጠራ “ሩሲያ” ነው የምትባለው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን “ራሽያ” የሚለው አጠራር እያየለ መጥቷል፡፡ “ስጳኝ” የሚለው ትክክለኛ የአማርኛ አጠራር “ስፔን” በሚለው የእንግሊዝኛ ቅጂ ተቀይሯል፡፡ “አርመን” የሚለው አጠራርም በ“አርሜኒያ” ተተክቷል፡፡ “ቤልጅግም” ወደ “ቤልጅየም” ተቀይሯል፡፡ “ቆጵሮስ” የሚለውን ጥንታዊ የአማርኛና የግዕዝ አጠራር “ሳይፕረስ” በሚለው አዲስ ደራሽ የቅጂ ስም የሚለውጡ ሰዎችም እየበረከቱ ነው፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በኦፊሴል ያገለግሉ የነበሩት እንደ “ነምሳ” (አውስትሪያ) እና “ናርበጅ” (ኖርዌይ) የመሳሰሉ የሀገራት መጠሪያዎች በዚህ ዘመን በአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት መስጠታቸውን አቁመዋል፡፡

ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ የፈረንሳይኛና የጣሊያንኛ ውርስ ቃላትም ቢሆኑ የመጥፋት እጣ ደርሶአቸዋል፡፡ ለምሳሌ በዛሬው ዘመን ከፈረንሳይኛ በተወረሰው “ኮሚሲዮን” የሚገለገል ሰው የለም፡፡ በአማርኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች በስፋት ሲያገለግል የነበረው “ኦፕራሲዮን”ም በዚህ ዘመን “ቀዶ ጥገና” እና “ኦፕሬሽን” በሚሉት ስሞች ተተክቷል፡፡ “ፔኒሲዮን” የሚለው ቃልም ሙሉ በሙሉ አገልግሎቱን አቁሟል፡፡

*****

“እነዚህ ቃላት ድሮውንም የውጪ ቃላት በመሆናቸው ከአማርኛ መጥፋታቸው የሚያስነሳው አቧራ የለም” ይባል ይሆናል፡፡ ነገሩን በታሪክና በአንትሮፖሎጂ መነጽር ካየነው ግን ትልቅ ጉዳት አለው፡፡ ምክንያቱም የነዚህ ቃላት በቋንቋዎቻችን ውስጥ መኖር የ20ኛው ክፍለ ዘመን ታሪካችን የተጓዘበትን መንገድና የእኛነታችንን ህብርነት የሚያሳይ በመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው የፈረንሳይኛ ቃላት በአማርኛ ውስጥ በመኖራቸው ተገርሞ “ይህ እንዴት ተከሰተ?…” የሚል ጥያቄ ቢያቀርብ የጅቡቲው ምድር ባቡርና የተፈሪ መኮንን ትምህርት ታሪክ ይተረክለታል፡፡ በጣሊያንኛ ቃላት ላይ ጥያቄ ለሚያቀርብ ሰውም የአምስቱ ዓመቱ የኢጣሊያ ወረራና የአርበኞቻችን የተጋድሎ ታሪክ ይነገረዋል፡፡

በሌላ በኩል በአንድ ቋንቋ ውስጥ ያሉ ውርስ ቃላትና ሀረጋት የታሪካዊ ምርምር መሰረቶች የሚሆኑበት አጋጣሚም ሞልቷል፤ ቃላቱና ሐረጋቱ እንደ ታሪክ ማስረጃ የሚያገለግሉበት ሁኔታም አለ፡፡ ብዙ የታሪክ እንቆቅልሾች በቃላትና በሀረጋት መነሻነት ሊፈቱ ችለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ዛሬ በግዴለሽነት ከኦሮምኛና ከአማርኛ ቋንቋ ውስጥ እየተወገዱ ያሉት የፈረንሳይኛና የጣሊያንኛ ውርስ ቃላቶቻችን ጠሊቅ የሆኑ ኪነታዊ ስራዎች የሚወጠኑበት መሰረቶች ሆነው ሲያገለግሉ ታይተዋል፡፡ እንደምሳሌም የቴዲ አፍሮን “ሼ-መንደፈር” እና “ላምባ ዲና”ን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ቴዲ እየረሳናቸው ያሉትን አንድ የፈረንሳይኛና አንድ የጣሊያንኛ ቃላትን ወስዶ የሁለት ውብ ዜማዎች መሰረት አድርጎአቸዋል፡፡ በመሆኑም ውርስ ቃላቱን በነበሩበት ሁኔታ ማስቀጠሉ ተገቢ ነው፡፡

በዚህ ረገድ የሀገራችን ሚዲያዎችና ፕሬሶች ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ እያካሄዱት ያለውን አጥፊ ሚና መግታት አለባቸው፡፡ ፈረንሳይም ሆነ እንግሊዝ፣ ጣሊያንም ሆነ ጀርመን ሁሉም ባዕድ ነው፡፡ ፊት የመጣውንና በህዝቡ ውስጥ የቆየውን ቃል አስወግዶ በሌላ የባዕድ ቃል መተካት በምንም መልኩ የስኬት መለኪያ አይሆንም፡፡ በተለይ ግን በረጅም ዘመናት የታሪክ ጉዞአችን ያዳበርናቸውንና እኛ ብቻ የምንጠቀምባቸውን ጥንታዊ የሀገርና የከተማ አጠራሮች (ሩሲያ፣ ቆጵሮስ፣ አርመን፣ ደማስቆ፣ ስዊስ፣ ኡክራኒያ፣ ቱርክ፣ ኢጣሊያ፣ ሮማ፣ አቴና፣ ሶሪያ፣ ፍልስጥኤም፣ ሊባኖስ፣ ግብጽ ወዘተ.. የመሳሰሉትን) ከእንግሊዝኛ በተኮረጁ ስሞች (ራሽያ፣ ሳይፕረስ፣ ደማስከስ፣ ፓለስታይን፣ ኢጂፕት ወዘተ..) መተካት ይቅርታ የማይሰጠው ጥፋት ነው፡፡ ቴክኖሎጂንና የተቀላጠፈ አሰራርን መኮረጅ እንጂ ነባር ቃላትን ማጥፋት የእድገት መሰረት ሊሆን አይችልም፡፡ ዐረቦችም ሆኑ ፈረንጆች፣ ቱርኮችም ሆኑ ህንዶች እንዲህ ዓይነት ጥፋት ሲያጠፉ አይታዩም፡፡ እኛም ይህንኑ ፈለግ መከተል አለብን፡፡ ስለዚህ የሚመለከተው ሁሉ ለጉዳዩ አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል፡፡

——–

(በእንቁ መፅሔት ላይ የታተመ የዳሰሳ ጽሑፍ)

አፈንዲ ሙተቂ፣ ግንቦት 13/2006

ሐሙስ, ኦክቶበር 13, 2022

ያልተዘመረለት ታላቅ ሰዉጋዜጠኛ እሸቴ አሰፋ ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 መቆያ

 እሸቴ አሰፋ አሳምነው 

ESHETE ASSEFA ASAMNEW

እሸቴ – ከጃንሜዳ የማይዘነጋ 

ዛሬም የሚተጋ 

በሳል የሚድያ ሰው እሸቴ አሰፋ


 እሸቴ ስለራሱ ከሚናገር ይልቅ ስራው የሚናገር በሳል ባለሙያ ነው፡፡ በመጽሄት ፣ በጋዜጣ፣ በሬድዮ በቲቪ የሰራ ለወጣት ባለሙያዎች አርአያ የሚሆን የተከበረ ባለሙያ ነው፡፡ 

ትውልድና እድገት

እሸቴ አሰፋ የተወለደው ሰሜን ሸዋ መንዝ ግሼ ወረዳ ነው፡፡ ጊዜውም ሀምሌ 19 ፤1953 አ.ም ነበር፡፡ የሚድያ ባለሙያ እሸቴ፣ በተወለደበት እለት፣ታትሞ የወጣውን አዲስ ዘመን ጋዜጣን፣ አይተን እንደተረዳነው፣ በምእራብና በመካከለኛው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ግዛቶች፣ ቀኑን ሙሉ ደመና ነበር፡፡ በተለይ ጠዋት ሰማዩ በሙሉ ተሸፍኖ አንዳንድ ጊዜ አነስተኛ ዝናብ ከሰአት በኋላ መጠነኛ ዝናብ ይጥል ነበር፡፡
ጋዜጠኛ እሸቴ፣ በተወለደበት እለት ምን ጉዳይ ነበር ብለን፣ ዳሰሳ ስንሰራ፣ አዲስ ዘመን ባወጣው የፊት ለፊት ገጽ ዜና፣ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ያላት ተቀማጭ ገንዘብ፣ከ15 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ያለ ነበር፡፡ የስራ አመራር ኮርስም የተቋቋመው የዛኑ ሰሞን ነበር፡፡

የጋዜጠኝነት ጅማሮ -በወጣትነት

እሸቴ አሰፋ፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በተወለደበትና ባደገበት፣ ግሼ ወረዳ በሚገኘው ራቤል ትምህርት ቤት ያጠናቀቀ ሲሆን፣ 2ኛ ደረጃን፣ በ መሃል ሜዳ፣ በሆለታና አቃቂ ተማሪ ቤቶች ነበር ተምሮ ያጠናቀቀው፡፡፡፡
የእሸቴ የሚድያ እና የጋዜጠኝነት አፍቃሪነት የታየው፣ ገና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለ ነበር፡፡ ያንጊዜ በተማሪ ቤቱ ሚኒ ሚድያ፣ በጥዋቱ የተማሪዎች ሰልፍ ላይ የስነ-ጽሁፍ ስራዎችን በማቅረብ እጅና አንደበቱን አፍታታ፡፡
እሸቴ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በጋዜጣ ጽሁፍ የታተመለት ፣ በአዲስ ዘመን ‹‹አድማስ ገጽ›› ላይ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ፣በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እየጻፈ አቅሙን አዳብሮ፣ በፍሪላንስ ጸሀፊነት፣ በህትመት ውጤቶቹ ላይ መጻፉን ተያያዘው፡፡ በእነዚያ ጊዜያቶች፣ በአንድ በኩል የዩንቨርሲቲ ትምህርቱን እየተከታተለ፣በሌላ በኩል ፅሁፎቹን ማቅረብ ቀጠለ ፡፡ ከጋዜጣ እና መፅሄት ጽሁፍ አቅራቢነት በተጨማሪ፣ በለገዳዲ ሬዲዮ፣ እና በኢትዮ ጵያ ቴሌቭዥን ፕሮግራም ያቀርብ ነበር፡፡
እሸቴና የካቲት መጽሄት


እሸቴ ፣ በ1979 ግድም የካቲት መጽሄት ላይ በፍሪላንስ ጸሃፊነት መጻፍ ጀመረ፡፡ በጊዜው ግለ-ታሪክ ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ በሳል ፅሁፎች አቅርቧል፡፡ በጥቅምት 1980 በየካቲት መጽሄት እትም ላይ፣ የዛሬ 33 አመት ከሰራቸው ግለ-ታሪክ ጽሁፎች አንዱ፤ የአንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ የጳውሎስ ኞኞ ታሪክ ይገኝበታል፡፡ ሰፋ አድርጎ የሠራው ይህ ጽሁፍ፤ ጳውሎስ ኞኞን የሚያውቁ የቅርብ ሰዎችን ቃለ-መጠይቅ የተደረጉበት ነው፡፡
ቃለ-መጠይቅ ከሰጡት መሀልም ከፕሬስ መምሪያ ሙሉጌታ ሉሌ ፣ ከኢትዮጵያ ሬድዮ ታደሰ ሙሉ ነህ፣ ከሥራ ባልደረቦቹም እነ አጥናፍ ሰገድ ይልማ ባለቤቱ ወይዘሮ አዳነች፣ ጭምር የተካተቱበት ነበር፡፡
ስለ ብርሀኑ ዘሪሁን፣ ስለወጋየሁ ንጋቱ፣ ስለይድነቃቸው ተሰማ…. ጥልቀት ያላቸው ጽሁፎች አሳትሟል፡፡ እሸቴ በዚያን ሰሞን በመጽሄቱ ላይ ያወጣቸው የነበሩት ጽሁፎች በበቂ ጥናት እና ዝግጅት የተሰሩ ስለነበሩ አንባቢን የሚያረኩ በሰፊ ገጽ ተሰናድተው የቀረቡ ነበሩ፡፡
የዚህ ዊኪፒዲያ አሰናጆች የእሸቴን ግለ-ታሪክ ሲያጠኑ የካቲት ላይ ከጻፋቸው በርካታ ጽሁፎች ውስጥ 7 ያህሉን ጊዜ ሰጥተው አንብበዋቸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል. ስለ ‹‹ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ›› ፤ ሰለሰሜን ኮሪያ፣እንዲሁም ስለ አርበኞች እንቅስቃሴ የጻፈቸው ይገኙበታል፡፡
እሸቴ ፣ በቂ ንባብ እና የጋዜጠኝነት ፍላጎት ያዳበረ በመሆኑ ፣ የሚጽፋቸው ጽሁፎች ላይ ከፍተኛ ብስለት ይታይባቸዋል፡፡ በየካቲት መጽሄት ላይ ሲሰራ‹‹ የአጻጻፍ እውቀት ሰጥቶኛል›› ብሎ ምስጋና እና አክብሮት የሚሰጣቸው ዋና አዘጋጁን፣ አቶ ጸጋዬ ሀይሉ ተፈራን ነው፡፡ እሸቴ ስለ የካቲት መጽሄት ሲያነሳ፣ አቶ ጸጋዬ እንደቅርብ አርታኢ ትልቅ ድጋፍ ሰጥተውታል፡፡ ‹‹ምንጊዜም የማልረሳቸው መምህሬ ናቸው›› ሲል ታላቅ አክብሮቱን ይገልጻል፡፡
በአሁኑ ሰአት፣ የ78 አመት አንጋፋ የሆኑት፣ አቶ ጸጋዬ ፣ የካቲት መጽሄትን ከ10 አመት በላይ በዋና አዘጋጅነት የመሩና መጽሄቷንም ተወዳጅ እና ተነባቢ ካደረጉ በሳል የኢትዮጵያ ባለውለታዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡
አቶ ጸጋዬ ፣የእሸቴን ክህሎት ዛሬም ያደንቃሉ፡፡
‹‹…የተረጋጋ፣ በእውቀት ላይ ተመስርቶ የሚሰራ ፣ ውለታ የዋለለትን ሰው የማይዘነጋ መልካም ሰው ነው፤…››
ሲሉ ገልጸውታል፡፡


እሸቴ፣ በየካቲት መጽሄት ላይ ሲሰራ የሚያውቁት፣ አቶ ተሾመ ብርሀኑ ከማል ያላቸውን የአድናቆት ስሜት ሲገልጹ
‹‹በጥሩ ቋንቋ የሚጽፍ ታታሪ ብእረኛ.›› ብለውታል፡፡ ‹‹ከልቡ የሚጽፍ ፤ በምርምር ላይ ተመስርቶ የሚሰራ ፈጣን መጣጥፍ አቅራቢ፣ በ1970ዎቹ መጨረሻ ሀገራችን ካፈራቻቸው ጸሀፊዎች አንዱ ነው…››
ሲሉ አፋቸውን ሞልተው ይናገራሉ፡፡
ያለ አንዳች እረፍት መስራት የእሸቴ መገለጫዎች ነበሩ፡፡ በለገዳዲ ራዲዮ፣በየካቲት መጽሄትና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዝግጅቶች የሚያቀርበው በተመሳሳይ ጊዜ መሆኑ ይህንኑ ይመሰክራል፡፡
በጊዜው ፣ እሸቴን ጨምሮ ብዙዎቹ ፍሪላንስ ጸሀፊዎች ፣ ለአንድ ጽሁፍ ብር 150 ይከፈላቸው የነበረ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ጸሀፊዎች ለምርምር ስራ ከዚያ በላይ የሚያወጡበት ጊዜ ነበር፡፡
እሸቴ አሰፋ በጊዜው ውሎውን ቤተ-መጽሀፍት በማድረግ የሚመለከታቸውን ቃለመጠይቅ በማድረግ የአንባቢን የንባብ ጥም ሲያረካ የኖረ ስለመሆኑ ብዙዎች መስክረዋል፡፡
እሸቴ የአዲስ አበባ 100ኛ አመት በተከበረ ጊዜ ለክብረ- በአሉ በተዘጋጀው ልዩ መፅሄት ላይ፣ ስለ መዲናይቱ ታሪክ መጣጥፍ ጽፎም ነበር ፡፡
እሸቴና ለገዳዲ ራዲዮ
የእሸቴ የለገዳዲ ቆይታ በደስታ የተሞላ ነበር፡፡ ያኔ ከኢትዮጵያ ሬድዮ ባሻገር እንደ አማራጭ ቀርቦ የነበረው ለገዳዲ ራዲዮ ስለነበር፣ እሸቴ እና ሌሎች ለጥበብ ቅርበቱ ያላቸው በለገዳዲ የእሁድን ለአንዳፍታ ፐሮግራም ተሳትፈውበታል፡፡ እሸቴ በተለይ በሚያቀርባቸው የስነ-ቃል መሰናዶዎች በአድማጭ ዘንድ ተናፋቂ ነበሩ፡፡
ልክ የካቲት መጽሄት ላይ የግለ-ታሪክ ጽሁፎችን ሲጽፍ በበቂ ሁኔታ እንደሚዘጋጀው ሁሉ ስነ-ቃሎችንም ሲተነትን በቂ መሰናዶ አድርጎ ነው፡፡
‹‹ እሸቴ ከጃንሜዳ›› በሚል ስያሜ፣ የህዝብን ባህል የሚያሳዩ የሥነ-ቃል ስብስቦችን ለሬዲዮ ስርጭት እንዲያመች እያደረገ አስተላልፏል፡፡ በርካታ አድማጮችን ያፈራበትና በሳል መጣጥፎችን በድምጹ ያስተላልፍበት ፕሮግራም ነበር፡፡ በየአስራ አምስት ቀን ይቀርብ የነበረው፣ የሥነቃል ዝግጅቱ፣ ከ 1978 ጀምሮ ለአምስት አመታት ተሰራጭቷል፡፡
አቶ ጠንክር ገብረሰንበት ፣ እሸቴን ከ1978 ጀምሮ በለገዳዲ ሬድዮ ሲሳተፍ ያውቁታል፡፡ እርሳቸው ያኔ የስራ ሃላፊም ስለነበሩ የእሸቴን ስራዎች የመከታተል እድል ነበራቸው፡፡
‹‹….ያን ጊዜ ለገዳዲ የቅዳሜን ከእኛ ጋር እና የእሁድን ላንዳፍታ መሰናዶዎች የሚቀረጹት ሜክሲኮ ዲአፍሪክ ወረድ ብሎ በሚገኘው የትምህርት መገናኛ ዘዴዎች ስቱዲዮ ነበር፡፡ ታዲያ እሸቴ ራሱ የጻፋቸውን መጣጥፎች በራሱ አንደበት ያነባቸው ስለነበር አድማጭን የመማረክ አቅም ነበራቸው፡፡ እሸቴ፣ በተለይ የገበሬውን ውሎ አጠቃላይ የገጠሪቱን የሀገራችንን ክፍል በስነ-ቃል ለማሳየት የተቻለውን ያደርግ ነበር ፡፡እሸቴ ለገዳዲ ጽሁፍ ይዞ ሲመጣ በቂ ዝግጅት ከማድረጉ በላይ የነበረውም ትህትናዊ አቀራረብ ፍጹም አይዘነጋኝም….. የሚያቀርባቸው መጣጥፎች ብስለትን የተላበሱ በመሆናቸው ለማድመጥም የሚጋብዙ ናቸው…››
ሲሉ አቶ ጠንክር ለዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች ተናግረዋል፡፡
እሸቴ፣ለገዳዲ ራዲዮ ላይ ሲሰራ፣ ‹‹ስለሬዲዮ ዝግጅት አስተማሪዬ ናቸው›› የሚላቸውን የፕሮግራም ሀላፊ የነበሩትን አቶ ገበየሁ ደምሴን ያስታውሳል፡፡
እሸቴ እና ቴሌቪዥን
እሸቴ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በቋንቋ እና ስነ-ጽሁፍ በቢ.ኤ በዲግሪ ተመርቋል፡፡ ከ1978-1983 በለገዳዲ እና በየካቲት መጽሄት ላይ ያበረከተውን አስተዋጽኦ እንደያዘ፣ በ1979 በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ በፍሪላንስ ጋዜጠኝነት ተቀጠረ፡፡ በተለይ ደግሞ፣ በዘጋቢ ወይም በዶክመንተሪ ስራዎች አቅሙን የማሳየት ፍላጎት ስለነበረው፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ አካባቢዎችን ቦታው ድረስ ሄዶ በማየት ዘጋቢ ፊልሞችን አዘጋጅቷል፡፡
‹‹ንጋት›› በሚል ርእስ ከቀረቡት እያንዳንዳቸው አንድ ሰዐት የሚዘልቁ ፣አምስት ክፍሎች ያሉት ዘጋቢ ፕሮግራም አብዛኛውን የሸፈነው እሸቴ ነበር፡፡
እሸቴ፣ ጣና ሃይቅ ላይ ስላሉት አድባራት የሰራው ዶክመንተሪ በብዙዎች የሚታወስ ነው፡፡ እነዚህ አድባራት በወቅቱ የነበሩበትን ሁኔታ በማጥናት ለተመልካች ጥሩ የሚባል መሰናዶ አየር ላይ አውሏል፡፡ በመላ ኢትዮጵያ ባሉ ክልሎችን ተዘዋውሮ ሰርቷል፡፡
አዲስ አበባ ፣100ኛ አመቷን ባከበረችበት በ1979፣ የአዲስ አበባን ታሪክ በጊዜው ከነበረችበት እድገት ጋር አቀናጅቶ፣ የአንድ ሰዐት ተኩል ፕሮግራም ሊያቀርብ ችሏል፡፡
ኢህአዴግ በ1983 ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላም የቀይ ሽብር ተጠቂዎችን በተመለከተ ፕሮግራሞች አቅርቧል፡፡ ምን ያህል መሰናዶዎች አየር ላይ እንዳዋለ ባያስታውስም ብዙ መሆናቸውን ግን ያውቃል፡፡
እሸቴ ፣ቀደም ብሎ በየካቲት መጽሄት ላይ፣ በታሪካዊ ጽሁፎች ራሱን የቃኘና እና ንባቡም የተጠናከረ ስለነበር፣ ቴሌቭዥን ሲገባ፣ የዶክመንተሪ ስራዎችን ምርጥ አድርጎ ለማቅረብ ብዙም አዳጋች አልሆነበትም፡፡
ለ5 አመት ገደማ ኢቲቪ ሲሰራ አርታኢውን አስፋው ኢዶሳንና ነቢዩ ኢያሱን ያስታውሳል፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሚሰራበት ጊዜ በርካታ ባልደረቦቹን እና አለቆቹን አይዘነጋም፡፡
እሸቴ እና ሪፖርተር


አቶ አማረ አረጋዊ፣ በ1987 ‹‹ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ሴንተር›› ብለው ሪፖርተር ጋዜጣን ሲጀምሩ፣ ከመስራች ጋዜጠኞች አንዱ እሸቴ አሰፋ ነበር፡፡ አቶ አማረ አረጋዊ፣ ቀደም ብሎ የኢቲቪ የስራ ሃላፊ ፣በነበሩበት ጊዜ፣ የእሸቴን ችሎታ ጠንቅቀው ያውቁ ስለነበር፣ አብሯቸው እንዲሰራ፣ ግብዣ አቀረቡለት፡፡ እሸቴም አይኑን ሳያሽ፣ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ስራ ጀመረ፡፡ በወቅቱ ሰሎሞን አባተ፣ ከበደ ደበሌ ሮቢ የመሳሰሉ ጋዜጠኞች ሪፖርተርን ከመሰረቱት መካከል የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡
እሸቴ በአዘጋጅነት ለአንድ አመት ከሰራ በኋላ፣ ሰሎሞን አባተ፣ የምክትል ዋና አዘጋጅነቱን ቦታ ሲተው፣ እሸቴ ከ1989 መስከረም ወር አንስቶ የሪፖርተር ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ሆኖ ስራ ጀመረ፡፡ ጋዜጣዋን ፕሮፌሽናል በሆነ መልኩ ለመምራት የበኩሉን ጥረት አድርጓል፡፡
ዜናዎችን መዘገብ፣ የተሰሩ ዜናዎችን መከታተል፣ጋዜጠኞችን ማሰማራት፣ የአርትኦት ስራዎችን በብቃት ማከናወን… ከእሸቴ የሚጠበቅ ነበር፡፡ በጊዜው የሰው ሀይሉ በጣት የሚቆጠር ስለነበር እሸቴ ራሱ ትንታኔዎችንና ዘገባዎችን ይሰራል፡፡ በተለይ የፖለቲካ እና የነጻ አስተያየት አምዶች በአብዛኛው ተሰናድተው ለንባብ ይበቁ የነበረው በእሸቴ አማካይነት ሲሆን ጽሁፎቹንም፣ ሶስት በሚሆኑ የብዕር ስሞች ነበር የሚያቀርባቸው፡፡፡፡
ሪፖርተር ጋዜጣ፣ በወቅቱ በብዙዎች ዘንድ ተአማኒነት የነበረው የህትመት ውጤት ነበር፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው፣ እነ እሸቴ የስራ መሪ በነበሩ ጊዜ መስመር የያዘ፣ ሙያዊነትን የተላበሰና በእውቀትና በእውነተኛ መረጃ የተቃኘ ጋዜጠኝነት እንዲኖር በማድረጋቸው የተነሳ ነው፡፡
ሪፖርተር ጋዜጣ፣ ለ26 አመት አንድም ሳምንት ሳይቋረጥ እስከዛሬ ለመታተም የቻለው፣ በመጀመሪያ በእነ እሸቴ የተቃኘ እና የተገራ በመሆኑ ነው የሚሉ አሉ፡፡ እርግጥ ነው የመስራቹ የአቶ አማረ አረጋዊ በሳል አመራር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የተቀመጡት ባለሙያዎችም ብስል የሙያ ሰዎች ነበሩ፡፡

እሸቴ፣ ከሪፖርተር ጋዜጣ በተጨማሪ፣ ሪፖርተር መጽሄት በ1989 ስትመሰረት በምክትል ዋና አዘጋጅነትና በዋና አዘጋጅነት ተመድቦ፣ አቅሙን ሳይቆጥብ ሰርቷል፡፡ አቶ አማረ አረጋዊ ስለ እሸቴ ችሎታ ሲናገሩ በንባብ የደረጀ ለሚድያ የተፈጠረ ነው ይሉታል፡፡ ስነ-ምግባር የተላበሰ የጋዜጠኝነትን ሙያ ያስከበረ እና ከሪፖርተር ጋዜጣ አመርቂ ስኬት ጀርባ ያለ የማከብረው ሰው ነው ሲሉ እሸቴን በአጭሩ ገልጸውታል፡፡ በሪፖርተር መጽሄት ላይ ከእሸቴ ጋር አብሮ የሰራው ተፈሪ መኮንን በበኩሉ ከእሸቴ መስራት በጣም እንደሚያረካው ይናገራል፡፡ ለምን ቢባል እሸቴ አሰፋ እውቀትን የታጠቀ ለትጋት ምንጊዜም ራሱን ያዘጋጀ ባለሙያ ስለሆነ ነው ሲል ተፈሪ ሀሳቡን ይገልጻል፡፡
እሸቴና ሸገር ሬዲዮ
እሸቴ ፣ በሸገር 102.1 ኤፍ ኤም ሬዲዮ፣ በቅዳሜ ‹‹መቆያ›› መሰናዶው ባለፉት ዘጠኝ አመታት ባስተላለፋቸው ዝግጅቶች፣ ብዙ አድማጮችን አፍርቷል፡፡ የውጭ ሀገር፣ መሪዎችን፣ታዋቂ ሰዎችንና ተቋሞችን፣ ግለ-ታሪክ፣ በብዙ ንባብና ማስረጃዎች የደረጁና የሚደመጡ ዝግጅቶችን በማቅረብ ላይ ነው፡፡ ስለ ሞሳድ ፤ ስለ ቶማስ ሳንካራ ፤ ስለ ሁጎ ሻፌዝ ፤ ስለ ጄኔራል ደጎልና ስለ ሌሎችንም በርካታ መሰናዶዎችን አየር ላይ አውሏል፡፡
የዜና ዘገባዎችንም ይተነትናል፡፡
በሸገር ኤፍ ኤም ራዲዮ አሁንም በዋና አዘጋጅነት እያገለገለ ነው፡፡

ማጠቃለያ
ጋዜጠኛ እሸቴ አሰፋ፣ በጋዜጣና በመፅሔት ፤ በሬድዮ እና በቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት ሰርቶ የሚያውቅ በመሆኑ ሁለገብና በሙያው ላይ ከፍ ያለ የእውቀት ደረጃ ላይ መድረስ ችሏል፡፡ ከ30 አመታት ቀደም ብሎ ገና 20ዎቹ መጀመሪያ እድሜው ላይ፣ በትጋት የጀመረው የጋዜጠኝነት ሙያ፣ ዛሬ የተከበረ ባለሙያ በጥናት ላይ ተመስርቶ መስራት ልክ እንደ እሸቴ አይነት ጋዜጠኛን ይፈጥራል፡፡
ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆነው እሸቴ፣ ሙያውን በጣም ከማክበሩ የተነሳ ራሱን ከማሳወቅ ይልቅ ስራው ላይ ብቻ አተኩሮ ብዙዎችን ሲያሳውቅ አመታት ተቆጥረዋል፡፡አድርጎታል፡፡ ከጋዜጠኝነት ሙያ ውጭ አስቦም ሰርቶም አያውቅም፡፡ እሸቴ ዛሬም ይሰራል እንጂ፣ ስለ ራሱ መናገር አይወድም፡፡
ይህ ብዙ ያልነገረለት በሳል ባለሙያ ስለ ሀገራችን የ30 አመት የሚድያ ታሪክ ሲወሳ፣ የእርሱም አሻራ አብሮ መነሳቱ የግድ ነው፡፡ በመሆኑም መጪው ትውልድ በእርሱ የትጋት መስመር እንዲሄድ የእሸቴን ታሪክ በጨረፍታ አቀረብነው፡፡ 

/ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ተጽፎ የተጠናከረ ሲሆን ጊዜውም ሀሙስ ሰኔ 10 2013 ነው፡፡/

ይህ የጋዜጠኛ እሸቴ ታሪክ የተጠናቀረው በተወዳጅ ሚዲያ ነው

ሦስቱ የሸገር ኤፍ ኤም ምሰሶዎች ተፈሪ አለሙ፣መዓዛ ብሩ፣እሸቴ አሰፋ

ከመቆያ አዘጋጅ እሸቴ አሰፋ ጋር የተደረገ ቆይታ 


"የቴሌቪዥንን ተመልካች የሰረቀ ጋዜጠኛ" __ሸገር መቆያ __ እሸቴ አሰፋ  Sheger Mekoya  I Eshete Assefa





የአዲስ አድማስ ጋዜጣ እያዋዛ የሚያስተምረው ርዕሰ አንቀፅ


አዲስ አድማስ ኢትዮጵያ ዘወትር ቅዳሜ የሚታተም ሳምንታዊ ጋዜጣ ነው። ጋዜጣው የሚታተው በአድማስ አድቨርታይዚንግ .የተ.የግ.. ሲሆን የተመሰረተው ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ፲፱፻፺፪ .. ነው። 

(አዲስ አድማስ ታህሳስ 29 ቀን 1992 . የመጀመሪያው ዕለተ ቅዳሜ ለንባብ በቃ !!)

በአሁኑ ጊዜ የጋዜጣው ሥራ አስኪያጅ ገነት ጎሳዬ ስትሆን ዋና አዘጋጅ ደግሞ ነቢይ መኮንን ነው።

################################################################################

ቅዳሜ  28 ቀን 2015 .ም Saturday, 08 October 2022 

ከዕለታት አንድ ቀን ልክ እንደ ደራሲ ስብሐት ልብ ወለድ ባሕሪ፤ እንደ አጋፋሪ እንደሻው፤ ሞትን የሚፈሩና የሚሸሹ አቶ መርኔ የሚባሉ ባላባት ነበሩ፡፡ የሰፈሩ ሰው አብዬ መርኔ እያለ ነው የሚጠራቸው፡፡
አቶ መርኔ ሞትን ለማሸነፍ ሲሉ ወደፊት የሚሆነውን ነገር የሚተነብዩ ኮከብ ቆጣሪዎች ዘንድ ሄደው ያውቃሉ፡፡ ኮከባቸውን አስቆጥረዋል፡፡ የወደፊታቸው ሁኔታ፣ ፍፃሜያቸው ምን እንደሚሆን ለማወቅ ከጅለው፡፡
የመዳፍን መስመር እያዩ የሰውን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚናገሩ መዳፍ አንባቢዎች ዘንድም ሄደዋል፡፡ ዕጣዬን እዩልኝ ብለው የተለያዩ አዋቂዎችን  ጠይቀው አስነብበዋል።
ሞራ ገላጮች የሚባሉ የሰው መፃዒ ዕድል ተናጋሪዎችም ጋ ሄደው የወደፊት ፍፃሜ ሕይወታቸውን ለማረጋገጥ ሞክረዋል፡፡ የቡና ስኒ አይተው ስለ ዕድል የሚናገሩ ሰዎች ቤትም ሄደው “መጨረሻዬን ንገሩኝ እባካችሁ?” ብለው ተማጥነዋል፡፡
በየመፅሐፍ - ገላጩ ሰፈር እየዞሩ የነገ ሕይወታቸውን አላፊ ዕድሜ ሊያስጠኑ ጥረት አድርገዋል። አብዬ መርኔ ያልሄዱበት ቦታ የለም፡፡
ሁሉም አዋቂዎች የሚሞቱባትን ሣምንት ጠቅሰው፣ ”የፈለጉትን ጥንቃቄ ቢያደርጉም፤ የሚሞቱት በእሾህ ተወግተው ነው!” ሲሉ ነገሩዋቸው፡፡
አብዬ መርኔም በልባቸው፤
“እንዲያማ ከሆነ እኔ እሾክ የደረሰበት አልደርስም! እንዲያውም ከእነአካቴው ከቤቴ አልወጣም” ይሉና በነዚያ በተጠቀሱት ቀናት እቤታቸው ክትት ብለው ሰነበቱ፡፡
ከተባሉት አንድ ቀን ብቻ ነው የቀራቸው፡፡ ቤታቸው በረንዳ ላይ ተቀምጠው አላፊ አግዳሚውን የሰፈራቸውን ሰው ሰላም እያሉ፣ “እንዴት ሰነበትክ ?” ሲሉ አመሹ፡፡
ወደ ቤታቸው ሊገቡ ጥቂት ሲቀራቸው፣ የከብት እረኛቸው፣ ላሞችና በጎች እየነዳ መጣ፡፡
አብዬ መርኔ ከግልገልነቱ ጀምሮ ያሳደጉትን በግ አዩ፡፡ በጣም ደስ አላቸው፡፡ በጉ ያውቃቸዋልና እየሮጠ ወደሳቸው መጣ፡፡ እያሻሹ ሲያጫውቱት ድንገት በፀጉራም ቆዳው ውስጥ የነበረ አንድ እሾክ መዳፋቸውን ጠቅ አደረጋቸው! ደማቸው ክፉኛ ፈሰሰ፡፡ ቁስሉ አልሽር አለ፡፡ ለካ ያ እሾክ መርዝነት ያለው ኖሮ፣ ብዙም ፋታ ሳይሰጣቸው ለሞት አበቃቸው!
“ዓለም አላፊ ነው
መልክ ረጋፊ ነው
ፎቶግራፍ ቀሪ ነው!”
ይላሉ የጥንት ሰዎች፡፡ ከተፃፈልን ቀን አናልፍም፡፡ የዕጣ-ፈንታችን ነገር ነው፡፡ በሕይወት የምንኖርባትን እያንዳንዷን ደቂቃ እንጠቀምባት እንጂ ነገን አንጠብቅ፡፡ በእጃችን ያለውን ወርቅ ቀን ሳንውል ሳናድር እጥቅም ላይ እናውለው፡፡
ሀገራችን የጦር አውድማ ከሆነች አያሌ ዓመታት  ተቆጥረዋል። ስደት እንደ አዘቦት ቀን ልብስ ከተዘወተረ ከራርሟል። መፈናቀልና ቀዬን ለቅቆ መሄድ ወረት መሆን ከተወ ቆይቷል። ይሄም ያልፋል እያሉ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ሞኝነት ሆኗል። መንግሥትም፤ “የበላችው አቅሯታል፣ በላይ በላዩ ያጎርሳታል!” እንደሚባለው፤ ነጋ ጠባ የማይፈጸም ቃል መግባቱን ቀጥሎበታል። “ለምን አልፈጸምክም?” ብሎ መንግስትን አፋጥጦ ለመጠየቅ ህዝብ ወኔ አጥቷል። አሊያም በተደጋጋሚ በደረሰበት ውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ምስቅልቅል፣ ቁምስቅሉን እያየ፤ ያረገው ነገር ቸግሮታል። አንገቱን ደፍቷል!
ያውቃሉ የተባሉት ምሁራንም ዱሮ ይባል እንደነበረው፡-
“እናውቃለን። ብንናገር እናልቃለን!” የሚሉ ይመስላል። ወይም ፍርሐት ቤቱን ሰርቶባቸዋል። ረዥም ዕድሜን ከዘለዓለማዊነት እያምታቱ (They took longevity for eternity እንዲሉ)፣ ያልፍልናል እያሉ ራሳቸው ያልፋሉ! የእርግማን እስኪመስልባቸው ድረስ አድር-ባይነትን፣ ስግብግብነትን፣ ሁሉን ለእኔነትን ተያይዘውታል! የሩቅ ምስራቅ ጠበብት፤”የአንድ ህብረተሰብ ጥንካሬ በምሁሩ መዓዛ ሽታ ይለካል” የሚሉት ብሂል፣ ለሀገራችን ምሁራንም መጠቀስ ያለበት ሀቅ ነው ብንል ከማጋነን አይጣፍብንም፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ ከተፈጥሮም ጋር ትግል ይጠበቅብናል። ጎርፍ፤ ድርቅና የአየር መዛባት በተደጋጋሚ አባዜው አልለቀን ስላለ ለከባድ ቸነፈር እና ርሀብ መጋለጣችን በየአስርት ዓመቱ የምናየው ክፉ እጣ መስሎብናል፡፡ ይህን የሚቋቋም ብርቱ ጫንቃ ያለው ትውልድ ከመፍጠር ይልቅ፤ “ጦርነቱ አገርሽቷል” የሚል ዜና የሚያዳምጥ ማህበረሰብ አቅፈንና አዝለን፤ መቀመጥን ሥራዬ ብለን ረዥም መንገድ ዳክረናል!
አሁን፤ያለፈው ይበቃን ዘንድ ወደፊት ለመራመድ መቁረጥ አለብን፡፡ የመለወጥ/ድፍረቱ ሊኖረን ይገባል፡፡ ድህነትንም ሆነ ድህነትን የሚያመጣብንን ሁሉ ለመቋቋም መነሳት ግድ ነው። በአንድ በሀገር ጉዳይ ሁላችንም ተጠያቂ መሆናችንን አንርሳ። ያየነውን አይተናል ለማለትና እንከንም ካለበት ለመጠቆም፤ ለመዋጋት ወደ ኋላ አንበል፡፡ እንድፈር፤ እንነጋገር፡፡
“አሁን ለምንድነው፤ ፈሪ ማቀንቀኑ
ቅጠል አይበጠስ፤ ካልደረሰ ቀኑ!”
ያሉ አባቶች ያቆዩዋት አገር እንደሆነች አንርሣ! መንገድ ካልጀመሩት አይገፋም፤ ወንበር ካልያዙት የማንም መቀመጫ ነው! ለሁሉም በዚህ ዘመን፤ ልብና ልቦና ይስጠን!
***************************************************************************************
 26 ቀን 2015 .ም Saturday, 01 October 2022 

“ሚስት እንጃልህ ስትል፣ ባል እንጃልህ ሲል፣ ቤት ለውሻ ይቀራል!”


ከእለታት አንድ ቀን አንድ ንጉሥ በአንድ አገር ታፍረው ተከብረው ይኖሩ ነበረ። ነገር ግን ልጅ አልወለዱም ነበረና “አገሬ ሰው አልተዋጣላትም፣ ወደፊት ዘውዴን የሚረከበኝና ዙፋኔን የሚወርስ ማን ሊሆን ነው?” እያሉ ሌት ተቀን ይጨነቁ ነበር።
አንድ ቀን በሀገሪቱ ውድድር እንዲደረግና አሸናፊ የሆነ ጀግና ዙፋኑን እንደሚወርስ ሊያውጁ ይወስናሉ። ውድድሩም የፈረስ ግልቢያ ነበረ። ከብዙ ማጣራት በኋላ ጥቂት ተወዳዳሪዎች ነጥረው  ወጡ። የፍፃሜው ውድድር መቼ እንደሚሆን ተወሰነና የሚጋልቡት ርቀት ምን ያህል እንደሚሆን፣ የት ቦታም እንደሚሮጡ ቁርጡ ታወቀ። ተፎካከሩ። ሆኖም ብዙዎቹ ተወዳዳሪዎች እየተመቀኛኙ፣ አንዱ አንዱን እያሰናከለ እንዳይሳካለት ማድረግ ጀመረ። ለፍጻሜው ሦስት ቀሩ።
የመጀመሪያው ሁለተኛው እንዳያሸንፍ  ፈረሱን መርዝ ሊያበላበት ወጠነ።
ሁለተኛው ደግሞ ሦስተኛው እንዳያሸንፍ ሰውየውን ራሱን የሚያደነዝዝ መድሃኒት ሊያጠጣው መላ መታ፡፡
ሦስተኛው ደግሞ የመጀመሪያው እንዳያሸንፍ ፈረሱ የሚሮጥበትን መንገድ በመሰናክል ሊያጥርበት ወሰነ።
ሁሉም ያሰቡትን አሳኩ። ሆኖም ከመጉላላት በስተቀር ምንም ፍሬ ሳያገኙ ቀሩ!
ንጉሡ አዘኑና “ዋ አገሬ! ሰው አልዋጣ አለሽ” አሉ አሁንም።
ስለዚህም ሌላ ፈተና ሊሰጡ አሰቡ። ፈተናውም አደን ሄደው ንጉሡ ያዘዙትን ፈጽመው መመለስ ነው። ተወዳዳሪዎቹ ቀረቡ። የንጉሡ ትዕዛዝ ግን ከወትሮው የተለየ ሆኖ አገኙት። ይኸውም፤
“ሄዳችሁ የፈለጋችሁን ሦስት ነገሮች አድናችሁ ኑ። የምፈልገው ግን እንድትይዙ ወይም ገድላችሁ እንድትመጡ አይደለም። ሦስቱም የምታደርጓቸው ጥረቶች ሳይሳኩላችሁ እንድትመለሱ ነው። ሆኖም ለምን እንዳልተሳካላችሁ እያንዳንዳችሁ እንድትገልፁልኝ እሻለሁ። ይህን መልስ በትክክል ለሰጠኝ መንግሥቴን አወርሰዋለሁ” አሉ።
አዳኞቹ ወደ ጫካ ሄደው በተባሉት መሰረት ሲያድኑ ውለው የማታ ማታ ሁሉም የየግላቸውን መልስ ይዘው መጡ።
ሌሊቱን እያንዳንዳቸው ለምን አደኑ እንዳልተሳካላቸው ሲያብራሩ አደሩ። ከሦስቱ ከአንደኛው በስተቀር ሁለቱ የውሸት የፈጠራ ወሬ ነበር ያወሩት። ውሸቱንም በሚገባ አላቀረቡትም።
ያ ሦስተኛው ተወዳዳሪ ግን የሚከተለውን ተናገረ፡-
“ንጉሥ ሆይ፤ በትዕዛዝዎ መሰረት ወደ ጫካ ሄጄ ሳድን ውዬ ምሽቱ ዐይን ሲይዝ ወደ ቤተ-መንግስትዎ እየሮጥኩኝ ተመልሻለሁ።” አላቸው።
ንጉሡም፤
“እኮ ለምን አደኑ ሳይቀናህ ቀረ? አስረዳና? ለመሆኑ ምን ነበር ለማደን የፈለግኸው?” ሲሉ ጠየቁት።
አዳኙም፤
“ወፎች ለማደን ነበር ንጉሥ ሆይ”
“ሁሉም በረሩ እንዳትለኝ ብቻ?”
“ኧረ አይደለም ንጉሥ ሆይ!
“ታዲያሳ?”
“ንጉሥ ሆይ፤ በርግጥ ሦስት ወፎች ለማደን ነበር የወጣሁት። ግን ሦስቱንም ለመምታት፣ ለመግደልም ሆነ ለመያዝ አልቻልኩም”
“እኮ ለምን?”
አዳኙ ተነስቶ ቆመና፤
“ንጉሥ ሆይ! የመጀመሪያዋን ከሩቅ ነው ያየሁዋት። ሁለተኛዋን ሰማሁዋት እንጂ አላየሁዋትም። ሦስተኛውን ግን ይኼው እስከ አሁኑዋ ሰዓት ድረስ ሳባርራት ነበር። ሰዓቱ ስለመሸ ባዘዙን ሰዓት ለመገኘት ስል ወደርስዎ መጣሁ” አላቸው።
ንጉሡ በጣም ተደሰቱ። እንዲህም አሉ፡-
“ብዙዎቻችሁ ትገርማላችሁ። አንዳንዶቻችሁ ዕውነቱን መግለጽ አትችሉም፡፡ አንዳንዶቻችሁ ደግሞ ከነጭራሹ መዋሸትም አትችሉም። ሌሎቻችሁ ውሸታችሁን ማስረዳት አትችሉም። ከፊሎቻችሁ ውድድር ማለት ምን ማለት እንደሆነ አልገባችሁም። ስትመቀኛኙ እድል ያመልጣችኋል። ይሄ ተራ ሰው ግን እቅጯን ነገረኝ። ምነው ቢሉ፣ እሱ እንዳይሳካለት ያደረጉት ሦስት ዋና ዋና ችግሮች የአገራችንም ችግሮች ናቸው። ሦስቱ ችግሮችም-
1. ከሩቅ ሆነን እያየን ዝም ማለት
2. ሳናይ እየሰማን ብቻ ዝም ማለት
3. እያየንም፣ እየሰማንም ዘዴ መሻት አቅቶን እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ፤ ናቸው” አሉ ይባላል።
+++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
 14 ቀን 2015 .Saturday, 24 September 2022 

ላግዝሽ ቢሏት መጇን ደበቀች

 ከኢራቅ ተረቶች አንዱ የሚከተለውን ይመስላል፡-
ከዕለታት አንድ ቀን ንጉሥ በግዛቱ ዋና ከተማ ሳይታወቅ እየተዘዋወረ፣ ሕዝቡ ምን እንደሚያወራ ለማዳመጥ እየሞከረ ነበር። በአንድ መስኮት አጠገብ እያለፈ ሳለ ሶስት ሴቶች ሲያወሩ ሰማ።
አንደኛዋ፡- ንጉሡን ለማግባት ብችል ግዛቱን ሁሉ ሊሸፍን የሚችል ምንጣፍ (ስጋጃ እሰራለት ነበር) አለች።
ሁለተኛዋ፡- “እኔ ደግሞ ንጉሡን ለማግባት ብችል፤ መላ ሰራዊቱ በልቶ የማይጨርሰው ትልቅ ድፎ ዳቦ እጋግርለታለሁ” አለች።
ሦስተኛዋ፡- “እኔ ደግሞ ንጉሡን ባገባ፣ ሁለት ልጆች እወልድለታለሁ። አንደኛው ራሱ ላይ የብር ፀጉር፣ ሌላኛው ራሱ ላይ የወርቅ ፀጉር ያላቸው ይሆናሉ” አለች።
ንጉሡ በሚቀጥለው ቀን በአባቶቻቸው በኩል ሴቶቹን ልጆች አስጠርቶ ተራ በተራ እያስጠየቀ፣ በሉ ያላችሁትን ሰርታችሁ አሳዩኝ አላቸው። የመጀመሪያዋ ስጋጃውን መስራት አልቻለችም። ሁለተኛዋ ዳቦውን ለመድፋት አቃታት። የመጀመሪያዋም ስለ ጉራዋ ማድቤት ውስጥ እንድትቀመጥ  ፈረደባት። ሁለተኛዋን ደግሞ ኩሽና እንድትቀመጥ ቀጣት። ሦስተኛዋን ግን አገባት። ከዘጠኝ ወር በኋላ የብር ጌጥና የወርቅ ጸጉር ያላቸው መንትያዎች ተወለዱ። እነዚህን ሁለት ቆንጆ ቆንጆ ልጆች ያዩት ሁለቱም የንግስቲቱ እህቶች ቅናት ያዛቸውና፣ ከሞግዚቷ ተሟግተው ወስዳ ጫካ እንድትጥላቸው አስደረጓት። በቦታቸውም ሁለት አሻንጉሊቶች ተካች።
ንጉሡ የሆነውን ሲሰማ እቤቱ ፊትለፊት ንግሥቲቱ በቁሟ እስከ ጡቷ ድረስ ትቀበር አለ። መንገደኛው በድንጋይ እንዲወግራትም አስደረገ! ንጉሡ አንድ አሳ አጥማጅ አለው። የንጉሡ ዓሳ አጥማጅ ወንዝ ውስጥ አንድ ሳጥን ያገኛል፤ ሲይዘው ይከብዳል። ለሚስቱ ሄዶ ነገራት። ቤታቸው ወስደው ሲከፍቱት ምን የመሳሰሉ ባለወርቅና ባለብር ጸጉር ልጆች! ልጆች ስላልነበራቸው ሚስትየው በጣም ተደሰተችና ልታሳድጋቸው ወሰነች!
ንጉሡ ወደ ሩቅ ሀገር ሊሄድ አስቧል። ሁለቱንም ኩሽና ያሉ ሚስቶቹን፣ “ምን ላምጣላችሁ?” አላቸው። የመጀመሪያዋ “በእንቁ የተንቆጠቆጠ ቀሚስ!” አለች። ሁለተኛዋ፣ “ከአልማዝ የተሰራ የአንገት ሀብል!” አለች። ሁለቱ እህትማማቾች ቀጥለው፤ “እባክህ እደረቷ ድረስ የተቀበረችውንም እህታችንን ምን እንደምታመጣላት ጠይቃት?” አሉት።
“አታላኛለችና ለሷ አላመጣም!” አለ።
“ግዴለህም ሚስትህ ናት፤ለእኛም እህታችን ናት። ተባበራት!” አሉት። ወተወቱት። በመጨረሻ ተስማማና፤
“እሺ ላንችስ ምን ላምጣልሽ?” አላት።
“ምንም። በሰላም ሂድ። በሰላም ተመለስ።” አለችው።
“በጭራሽ። አንድ ነገር እዘዥኝ” አላት።
“እንግዲያው “የትዕግስት አሻንጉሊት” እና “የትዕግስት ቢላዋ” አምጣልኝ!” አለችው። “የምትሄድበት ሀገር እነዚህን ሁለቱን አታጣም። ከረሳህ የምትሳፈርበት ጀልባ እሺ ብሎ አይንቀሳቀስም።” አለችው።
ንጉሡ ሩቅ ሀገር ሄደ። ንግዱን አሳካው። ነጋዴዎቹ በእንቁ የተንቆጠቆጠ ቀሚስና የአልማዝ የአንገት ሀብል እንዲገዙለት አደረገ።
ከዚያ ወደ ሀገሩ ሊመለስ መርከቡ ላይ ወጥቶ “እንሂድ” አለ። ካፒቴኑ ግን መጥቶ “ንጉሥ ሆይ! መርከቡ አልሄድም ብሎኛል” ብሎ ሪፖርት አደረገ። ንጉሡ የረሳው ነገር ትዝ አለውና “የትዕግስት አሻንጉሊት” እና “የትዕግስት ቢላዋ” አስገዛ። የሸጠለት አንጥረኛ ግን አንድ ነገር አደራ አለውና ቃል አስገባው። ይኸውም፤ “ንጉሥ ሆይ! ለሚስትህ ስጦታዋን ስትሰጣት፤ በሩ ሥር ተደብቀህ የምታደርገውን ሁሉ እይ” ንጉሡ አንጥረኛው እንዳለው አደረገ።
ለሁለቱ ሚስቶች ስጦታቸውን ከሰጠ በኋላ ግማሽ ወደተቀበረችው ሚስቱ ሄዶ ያመጣላትን ሰጥቷት ተደብቆ የምታደርገውን ያይ ጀመር። ለአሻንጉሊቷ የሚከተለውን ተናገረች። እህቶቿ ልጆቿን እንደሰረቁባትና በቦታቸው አሻንጉሊቶችን እንድታስቀምጥ ሞግዚቷን እንዳዘዟት ገለጠች። እስከ ዛሬ ድረስም ሀዘን ላይ መሆኗን እያነባች ተናገረች።
እንዲህም አለች፡- “የትዕግስት አሻንጉሊት ሆይ! አንተ ትዕግስት ነህ! እኔም ትዕግስት ነኝ! እኔ በትዕግስት ምን ያህል ስቃይ ተሸከምኩ? ምን ያህል መከራ ተቀበልኩ?!”
አሻንጉሊቱ እየገዘፈ ሄደና ፈነዳ! ይህንን ያየችው ሶስተኛዋ ሚስት “ውይ! የትዕግስት አሻንጉሊት ሆይ ልብህ ተነካ!” አለች። ከዚያም ቢላዋውን አንስታ ራሷን ልትወጋ ስትል ንጉሡ ከተሸሸገበት ዘልሎ አዳናት! ከዚያም፤ “ምነው ለአሻንጉሊቱ የነገርሽውን ለምን ለእኔ አትነግሪኝም?” ሲል ጠየቃት።
“እህቶቼን ስላጠፉት ጥፋት እንዳትጎዳቸው ፈርቼ ነው።” ስትል መለሰች። ንጉሡ ባለሟሎቹን ጠርቶ ቆፍረው እንዲያወጧት አደረገ። ሁለቱም እህቶቿን ወደ እስር ቤት ላካቸው። ቀጥሎም፤ የጠፉትን ሁለት ልጆች እንዲፈልግ ህዝቡን በአዋጅ ጠየቀ። አዋጁ በመላ ሀገሪቱ ተሰማ። ይህን የሰሙት አሳ አጥማጁና ሚስቱ፣ ተመካክረው ልጆቹን ወደ ንጉሡ አምጥተው አስረከቡ። እንደ ሽልማትም እቤተመንግስቱ አቅራቢያ መኖሪያ ቤት ሰርቶላቸው፤ ልጆቹንም በየጊዜው እያዩ ኖሩ!
**********************-----------------------------------------------------------***************************
 7 ቀን 2015 .ም Saturday, 17 September 2022 

ቀስ በቀስ ዕንቁላል በእግሩ ይሄዳል!

ከዕለታት አንድ ቀን፣ ለንግድ ስራ ወደ ሌላ አገር ሄዶ ከርሞ ወደ ቤቱ የተመለሰ አንድ ነጋዴ በራፉ ጋ ሲደርስ የጎረቤቶቹን ሰዎች ያገኛል፡፡
የመጀመሪያውን ጎረቤት፤
“ለመሆኑ ሰፈር ደህና ነው ወይ ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ጎረቤትየውም፤
“ወዳጄ፤አንተ ከአገር ከወጣህ እኮ ከዓመት በላይ አልፏል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ፤ብዙ ልጅ ተወልዷል፡፡ ብዙ አዋቂ ሞቷል” ይለዋል፡፡
ነጋዴውም፤
 “እንዲያው ለነገሩ እህልስ እንዴት ነው? መሬቱ እንደልብ ይሰጣል?” ሲል፤ሁለተኛውን ጎረቤት ይጠይቀዋል፡፡
ሁለተኛው ጎረቤትም፤
“ምንም አይልም፡፡ መሬት እኮ በጊዜ ከመነጠሩት፤ ካለሰለሱት፤ በሰዓቱ ካረሱትና ከዘሩት መስጠቱ አይቀርም፡፡ በተለይ ባለፈው ዓመት ድርቅም ስላልነበረ፤ እህሉ መልካም ነበረ፡፡”
ነጋዴው ወደ ሶስተኛው ጎረቤቱ ሄዶ፤
 “ወዳጄ ወደ ቤቴ ከመጣሁ ቆይቻለሁ፡፡ እንደው ባለቤቴ ደህና ናት?” አለና ጠየቀው፡፡
ጎረቤትየውም ፤
“እሷስ ደህና ናት ፤ ሌላ ነገር አላውቅም ” ይለዋል፡፡
ነጋዴው የሚስቱ ደህና መሆን እያስደሰተው፤ እሱ ወደ ሩቅ አገር ሊሄድ ሲነሳ ነብሰ-ጡር እንደነበረች ያውቃልና፣ ማናቸውም ጎረቤቶቹ ስለ ልጁ ስላላነሱ ውስጡን ጭንቅ ብሎታል፡፡ ሰውን መጠየቁንም ፈራው፡፡
በመጨረሻ ግን  ቤቱ ገብቶ ሁሉንም አረጋግጦ ቢወጣለት ይሻላልና ወደ ቤቱ ገባ፡፡
ሚስቱ፤ ባላሰበችው ሰዓት በመምጣቱ እጅግ ተደስታ እልልታዋን አቀለጠችው፡፡                   ትልቅ ፌሽታ ሆነ፡፡ ጎረቤት ተሰበሰበ፡፡ ተበላ! ተጠጣ!
ለመተከዣ የሚሆን መጠጣቸውን በጅ በጃቸው እንደያዙ ፤የማይቀረውን ጥያቄ ጠየቀ- ሚስቱን፡፡
“ለመሆኑ ነብሰ-ጡር አልነበርሽ? ልጁስ እንዴት ሆነ?”
ሚስቲቱም፤
“ልጁማ ታሞ ፤ብዙ ተሰቃይቶ ፤ህይወቱ አለፈ!” አለችው ፡፡
ባል፤
“ምኑን ነበር ያመመው?”
ሚስት፤
“እንደው እንደ ትኩሳት አድርጎ ጀመረውና ፤እየቆየ ብሶበት ለሞት አበቃው”
ባል ጥቂት ተከዝ ብሎ፤
“ለመሆኑ ስሙን ማን ብለሽ አወጣሽለት?”
ሚስት፤
“ሰባጋዲስ ነበር ያልኩት፡፡ በጀግንነት እንዲያድግ ብዬ ነው!”
ባል ፤
“ተይው ተይው አሁን በምን እንደሞተ ገባኝ”
ሚስት፤
 “በምን ሞተ ልትል ነው?”
ባል ፤
 “ስሙ ከብዶት ነው የሞተው!” አላት ይባላል፡፡
++++++++++++++++++++===============================++++++++++++++++++++++++
ጳግሜ 5 ቀን 2014 .Saturday, 10 September 2022 

“መንኳኳት የማይለየው በር!”

አንዳንድ በሀገራችን እንደቀልድ የሚወሩ ወጎች ውስጠ-ነገራቸው ታሪክ-አዘል ሆኖ ይገኛል።
የሚከተለው ቀልድ ሰሞኑን ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩት የቀድሞው የሩሲያ መሪ ሚካኤል ጎርባቾቭና አሁን በኢትዮጵያ በሌሉት  በቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ  በሊቀ መንበር መንግስቱ ኃይለማርያም ዙሪያ የተቀለደ ነው።
የሩሲያ መሪ ሚካኤል ጎርባቾቭ ከዕለታት አንድ ቀን ለኢትዮጵያው መሪ ለጓድ ሊቀ መንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም የገና በዓል ሥጦታ (X-mas gift) ይልኩላቸዋል አሉ።
ሥጦታቸው አንዲት የኮርስ ብስክሌት ናት። የብስክሌቷ ልዩ ነገር፣ ምንም ዓይነት የእግር መሽከርከሪያ ወይም ፔዳል የሌላት መሆኑ ነው።
ሊቀ መንበር መንግሥቱ ፔዳል እንደሌላት ሲያዩ በጣም ተበሳጭተው፡-
“የጉምሩክ ሰራተኞች ይሆናሉ የሰረቁኝ (የበሉኝ) እሰሩና ጠይቁልኝ!” አሉና ትዕዛዝ ሰጡ። የጉምሩክ ፈታሾች በሙሉ ታሰሩ - እንደ ሕጉ። እንደ ባሕሉ። የጉምሩክ ፈታሾች በሙሉ ተከረቸሙ። በምርመራ የተገኘ ምንም ነገር አልነበረም።
በቁጣ፤ “ፓይለቶቹንም እሰሩና መርምሩልኝ” አሉ። ፓይለቶቹም ታሰሩ። ፔዳሉ ግን አልተገኘም።
ጥቂት ወራት እንዳለፈ የእስር ቤቱ መርማሪዎች፣ ምንም ፍንጭ አለመገኘቱን ሪፖርት አደረጉ።
ሊቀ መንበር መንግስቱ አማካሪዎቻቸውን ሰብስበው መላ ምቱ አሉ።
አማካሪዎቻቸውም፤
“ለምን ፕሬዚዳንት ጎርባቾቭ ዘንድ ተደውሎ፣ የላኳት ብስክሌት ፔዳል ያላት ይሁን፣ ፔዳል የሌላት አይጠየቁም?” ሲሉ ሀሳብ አቀረቡላቸው።
ተደውሎ የጎርባቾቭ የቅርብ ረዳት ተጠየቀ።
የቅርብ ረዳታቸው አረጋግጦ ያመጣው መልስ፣ ዕውነትም የተላከችው ብስክሌት ፔዳል የሌላት ናት።
መንግሥቱ ኃይለማርያም በጣም በሽቀው፤
“እኮ ለምን? ለምንድነው ፔዳል የሌላት ብስክሌት የላካችሁት?” ብለው ጠየቁ።
ከሩሲያ ወገን ያገኙት መልስ፡-
“ጓድ ሊቀመንበር፣ እርሶ ሁልጊዜ ወደ ቁልቁለት እየወረዱ ስለሚሄዱ፣ ፔዳል መምታት (መዘውሩን ማሽከርከር) አያስፈልግዎትም!” የሚል ሆነ፤ ይባላል።

//////////////////////////////////////////////=======================////////////////////////////////////////////////////////////
ነሃሴ 28 ቀን 2014 .ም Saturday, 03 September 2022 

ከሚመጣው ዓመት ዶሮ፣ እንቁላል ዘንድሮ

ከዕለታት አንድ ቀን  የቅዳሜ ሹር ለት  ቤተሰብ ተሰብስቦ፣ የፆመ የሚገድፍበት፣ ያልፆመም በግድ ተቀስቅሶ ገበታ የሚቀርብበት ሌሊት፣ አንድ አመለኛና አስቸጋሪ ልጅ፣ እንደ ሁልጊዜው ከሰው ፊት ምንትፍ ያደርጋል፡፡
የዚያን ዕለት ሌሊት በእንግድነት የተገኘ ጥቁር እንግዳ አለ፡፡
አባትና እናት፣ ያ አመለኛ ልጅ ያስቸግራል ብለው በየደቂቃው ስቅቅ ይላሉ፡፡ ዶሮው መጣ፡፡ ለየሰው በቁጥር እየለዩ እናት አወጡ፡፡ አመለኛው ልጅም ደርሶታል፡፡ ግን አመል ነውና ፋንታውን ዋጥ ስልቅጥ አድርጎ በእጁ እመር እያለ፣ የእንግዳውን ዕንቁላል ላፍ አደረገ፡፡
አባት፡-
“ኧረ ይሄ ባለጌ፣ የእንግዳውን ድርሻ ትወስዳለህ?”
እናት
(በምንተፍረት)
“ግዴለም ይብላ ተውት፣ ልጅ አደል? አለኮ፣ለእንግዳው አወጡለት፡፡”
እንግዳውም በሀፍረት ልሳን፡-
“ኧረ ግዴለም አትቆጡት! የእኛ ቤት ልጅ´ኮ ሙሉ ድስቱን ነው አንስቶ ይዞ የሚሮጠው!” አለ
ይሄኔ አባት፤
“አይ ለሱስ ደህና አድርገን ቀጥተነዋል፡፡”

============================================================================


የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ደግሞ ነቢይ መኮንን ነው።


የአዲስ አድማስ ጋዜጣ መሥራችና ባለቤት አሰፋ ጎሳዬ
+++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
የአዲስ አድማስ መሥራችና ባለቤት አሰፋ ጎሳዬ ላንተ ምን ዓይነት ሰው ነበር? (ኢዮብ ካሳ - ጋዜጠኛ፣ ተርጓሚ፣ አርታኢና ደራሲ ነው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ነው።)
እስካሁን የጠቀስኳቸውን ነገሮች ሁሉ የፈጠረልን አሰፋ ጎሳዬ ነው፡፡ በዚያን አስቸጋሪ ወቅት አዲስ አድማስን የመሰለ ጋዜጣ ለመፍጠር ብቻ ሳይሆን ጽኑ መሰረት ላይ ለማቆም፣ ምጡቅ ሃሳብና ራዕይ የነበረው ሰው ነው፡፡ በዕውቀትም በአርቆ አሳቢነትም፣ በብሩህ ራዕይና በጠንካራ ሰብዕናም የታደለ፡፡ የቅንነትና የትጋት ህያው አርአያችን ነው፡፡ የላቀ ህልምን በጥረትና በጽናት እውን የማድረግ፣ የ‹‹ይቻላል››፣ ተምሳሌት ነው ብዬ አስባለሁ፤ ለኛ ብቻ ሳይሆን ለአገርም ጭምር፡፡
በኢትዮጵያ የግል ፕሬስ ታሪክ ለ20ኛ ዓመት የምስረታ በዓል መድረስ ከባድ ነው አይደል?
በጣም እንጂ! የዛሬ 15 ዓመትና 20 ዓመት የነበሩትን ጋዜጦችና መጽሄቶች አሁን ካሉት ጋር ማወዳደር ትችላለህ፡፡ ያኔ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡ አሁን ግን ያሉት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ይሄ በራሱ የግል ፕሬሱን ፈተናዎች ያሳያል፡፡ ወደ 20 ዓመት የደረሱና የተጠጉ ጋዜጦች የኛን ጨምሮ ከአራት አይበልጡም፡፡
ባለፉት 20 ዓመታት የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ተግዳሮቶች ምን ነበሩ?
እንዴት መሰለህ --- በውጭው ዓለም 100 እና 150 ዓመት የሞላቸው ጋዜጦችን ታገኛለህ፡፡ ዘ ኢኮኖሚስትን
የመሰለ ምርጥ መጽሄትና ኒውዮርክ ታይምስን የመሰለ ድንቅ ጋዜጣ መጥቀስ ይቻላል፡፡ የአንባቢዎቻቸውን ቁጥር ደሞ አስበው፡፡ አንድ ጋዜጣ በቀን በ100ሺ በሚሊዮኖች የሚታተምበት ታሪክ ነው ያላቸው፡፡ እዚህ ጎረቤታችን ኬንያ ሳይቀር፡፡ በዚህ የረዥም ዓመታት ታሪክ ሙያው፣ አሰራሩ፣ አመራሩ፣ ቴክኖሎጂው፣ የንባብ ባህሉ ምን ያህል እንደዳበረ ማየት ይቻላል፡፡ የሙያ ሥነ ምግባር ከፖለቲካ ነጻነት ጋር አብሮ ሲሄድ እንደዚህ ነው፡፡
ወደ እኛ ስትመጣ የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኝነት ዕድሜው ለጋ ነው - በሙያ ብቃትም ሆነ በሥነ ምግባር፡፡ ፖለቲካውን ደሞ ታውቀዋለህ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የጋዜጠኝነት ትምህርት የተጀመረው በቅርቡ ነው፡፡ የንባብ ባህል ገና እንጭጭ ነው፡፡ የኢኮኖሚው ደካማ መሆን ራሱ መዓት ችግሮች አሉት፡፡ በአንድ በኩል በቂ ማስታወቂያ የማግኘት ችግር በሌላ በኩል የማተሚያ ዋጋ መናር ይፈጥራል፡፡ ይሄ ሳያንስ ደግሞ ፖለቲካው የሚያመጣቸው ጣጣዎችና የመንግስት ተጽዕኖ ይጨመርበታል፡፡

በአዲስ አድማስ ዋዜማ

____________ሰዓሊ በቀለ መኮንን (ረዳት ፕሮፌሰር) Monday, 09 March 2015 

ሁሉም ነገር የሆነበት ጊዜ ወደ ሁዋላ እየራቀ ሲሔድ ለዛሬ ሕልም መምሰሉ አይቀርም።  ጥቂት ቆይቶ ደግሞ ግማሽ ጐኑን ተረት ይበላዋል። ለእንደኛ አይነቱ ፅፎ ማስቀመጥ ብዙ  ለማይሆንለትማ ጭራሽ በመረሳት ጎርፍ  የሚጠረግበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም።
እንዲህ ሥራውን አክብሮ መሰረቱን አሳምሮ ቀና እንዳለ፣ አስራ አምስት አመታትን አስቆጥሮ ዛሬ የደረሰው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ፤ የዛሬ አስራ አምስት አመት  ረዥም ጉዞ የማይታክተው ቁምነገረኛ ጋዜጣ ጀምረን  እስቲ ሳናቋርጥ ማሳተም ያቅተንም እንደሆን፣ ሞክረን አቅማችንን ካላየን ምን ዋጋ አለው ? በሚል ወኔ  ባለቤቱ  አሴ - አሰፋ ጎሳዬ መውጣት መውረድ ከጀመረ ሰንበትበት ብሎ ነበር። ታዲያ ምንም እንኳ አብዝቶ የሚገናኘውም የሚመክረው ከቆየ የስራም የሐሳብም ባልደረባው ከጌታ መኮንን ጋር ቢሆንም በተለይ ከስራ በሁዋላ አመሻሽ ላይ በዋዛውም በቁም ነገሩም ከሚቀላቀሉት መካከል   እኔም አንዱ ነበርኩ።
 ከዚያ ቀደም ብሎ  አምስት ስድስት ዓመት በፊት ገደማ  “አዲስ አርት ፌስቲቫል” የተሰኘውን በሐገሪቱ የመጀመሪያውን  ሳምንት ሙሉ የተካሔደ ዙሪያ መለስ የስነ-ጥበብ ፌስቲቫል ለማዘጋጀት ጌታ መኮንን አሰባስቦ ካስተዋወቀን ምርጥ ሰዎች አንዱ ነበር- አሴ ። እርሱ ሰዓሊ ወይ ገጣሚ ባልሆነበት ሌሎች ታውቀው እነርሱው  በሚጠቀሙበት የሳምንት ሙሉ ትልቅ ክብረ-በዓል በአዲስ አበባ ይካሔድ ዘንድ የከሰረው የገንዘብ መጠን፣ ያባከነው የጊዜ ብዛት፣ የወጣ የወረደበት ቦታ፣ የተለማመጠው የለመነው የሰው ብዛት፣ በዚያም ያገኘውን የመንፈስ ደስታ አሁንም ድረስ ሳስበው   ካለማቸውና  ካከናወናቸው ተግባራቱ ሁሉ
 የታዘብኩት በርግጥ ሰውና ሐገሩ  መለወጥ ካማራቸው የምር መለወጫ መንገዱ ይኸው መሆኑን ነው
ርዕይ ፣ ዛሬ እንደ ብይ መጫወቻ ሳይሆን ርዕይ ከተባለ በበኩሌ የአሴ አይነት ርዕይ ያለተጨማሪ ማብራሪያ ምን እያሉ ምን ማድረግ እንደሆነ ያኔም አሁንም በቀላሉ ይገባኛል። አዲስ አርት ፌስቲቫል እስከ ዛሬ ያልደበበዘዘውን አሻራ ጥሎ እንዲያልፍ ከጌታ መኮንን ጋር ሁሉን ካደረጉ  በሁዋላ፣ አሴ በአንድ ወይ በሌላ መልክ ቋሚ የሆነ የእውቀት ወይም የጠቅላላ መረጃ መድረክ መፍጠር ወይም ከዚያም በላይ “ትልቅ የሆነ ነገር ላገራችን በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ እንችላለን ? ” ዓይነት ነገር የሁልጊዜ ጥያቄና ጨዋታው ነበር። ለራሱ
ስራ ፈጥሮ ብዙ ብዙ መንገዶችን በብዙ ሌሎች መስመሮች በኩል ደጋግሞ  እንደሞከረ
 አስታውሳለሁ። ሁሉንም የገንዘብ ትርፍ አጥቶባቸው ሳይሆን እርሱ “ሐገር” ፣ “ ወገን” ከሚለው ኅብረተሰብ ጋር አብሮ ከማደግ ፣ አውቆ ከማደግ ጋር በልቡ ያለውን ሕልም አልፈታ ስላለው ብቻ ነው ጥሎ ሌላ ለመጀመር የሚደክመው ። ይህ አይነቱ የአስተሳሰብ ሐብት ዛሬ አሰፋ ካለፈ በሁዋላ በኖርናቸው ጥቂት አመታት ውስጥ በብርሃን ፍጥነት  አሽቆልቁሎ፣ የከፋ ኪሳራ ውስጥ እንደምንገኝ አጥብቄ አምናለሁ። ከዚያ አንፃር ከተመዘንን፣ ስንቶቻችንና ማንኛችን ሞተን፣ ማንኛችን ደግሞ  የኗሪነት ቆጠራ እንደሚመለከተን አላውቅም።
ከብዙ ማውጣትና ማውረድ፣ ከብዙ ምክርና ማሰላሰል በሁዋላ  ያ የመረጃ መድረክ ጋዜጣ ቢሆን እንደሚያስኬድ ከዚያም ቀስ በቀስ የኢትዮጵያን ስነ-ጥበብ ሊያግዝ የሚችል አቅም የሚኖረው ተቋም ራሱ ይፈጥራል ተብሎ ጋዜጣው ይቅደም የሚል ውሳኔ ላይ ተደረሰ። ሁልጊዜም አሰፋ በስነ-ጥበብ ውበትና ጉልበት ላይ እምነት ነበረው። በዙሪያው በነበርነው የሙያው ሰዎች ተፅዕኖ አይመስለኝም። ዋናው ምክንያት ከገዛ ስልጣኔው የመነጨ እንደሆነ እኔ ጥርጣሬ የለኝም ። ስልጣኔው ስል  መማሩ ብቻ ማለቴ  አይደለም ። በመማርብቻ መሰልጠን እንደማይገኝ ከብዙ ምሁራኖቻችን ስለምናስተውል። ይልቁንም  አሰፋ ሲበዛ አንባቢ ፣ ምን  እንደሚያነብም የሚያውቅ ፣ በጥልቅና በፍጥነት ማንበብ የሚችልበት፣ የሚያነበው ለባላጋራ ማጥቂያ ወይም ያደባባይ  መኮፈሻ  ሳይሆን በቃ ለዕለት ተለት የአይምሮ ምግቡ  እየሰፈረ የሚመገበው ነው። ከዚያ የሚገኘውን ጉልበት እንዴት  ለሕይወት ጥያቄዎች መልስ መፈለጊያነት  እንደሚተረጉመውም አሳምሮ ያውቅበታል። እንኳን ከመፅሀፍ ከጉዋደኛ የሰማውን በራሱ እውቀትና ባካባቢው አቅምና ቋንቋ  አዋዝቶ  ያወርደዋል እንጂ አንዱንም  በደረቁ  ቃል በቃል ደግሞት አያውቅም። ለዚህ አይነቱ ሰብዕና   ስነ- ጥበብን ማወቅም ሆነ ማድነቅ፣ ማክበርም ሆነ መደገፍ እንግዳም ትርፍ ነገርም አይሆንም ።
አንድ ቀን ምሽት ጋዜጣው ሊታተም በጣም ጥቂት ቀናት ሲቀሩት፣ እነ አሰፋ በርከት ብለው ከሚያወኩበት ቦታ ስልክ ካንዳቸው ዘንድ ይደወልልኛል። ጌታ ይመስለኛል ደዋዩ። “አሁን ርዕሱ ላይ ደርሰናል። አሁን ሁላችንም  የወደድነውንና ጥሩ የመሰለንን ርዕስ እየሰነዘርን  ነው። ለምሳሌ  አዲስ ….. “ ብሎ ሳይጨርስ ካፉ ቀልቤ …” በቃ እንግዲህ  ጀመራችሁ ገብረ-ማርያም ሲባል ወልደማርያም ማለት ደስ አይልም …አዲስ ዘመን እዚያ ጋ ስለሚታተም እዚህ  ጋ የግድ አዲስ -ዓለም ፣ አዲስ-ማተብ እያልን መቀጠል አያምርብንም--”
እያልኩ  ትንሽ ተሞጣሞጥኩ። በስብሰባም ይሁን በሻይ ጨዋታ ላይ፣ ነገራችን  ሁሌም
 ከድርቀት የነፃ ነበር። “በመሰረቱ-- በዋናነት---በአዋጭነት ….” ብሎ ንግግርን ፊት ሰጥተነው አናውቅም።
በዚያ ምሽት ካልዘነጋሁ እነ ነቢይ፣ እነመስፍን እና ሌሎችም አብረው የነበሩት ሁሉ ብዙ ቀልዶችና ሐሳቦች ሰነዘሩ ።ግፋ ቢል ሁለት ቀናት ፈጀ መሰለኝ ፣ ወዲያው የመጀመሪያዋ አዲስ አድማስ ታትማ ወጥታ፣ ሁላችን በጣም ተደሰትን ። ያኔ ያሽሟጠጥኩባት “አዲስ”  እነሆ  ከዚያም በሁዋላ  ስንትና ስንት  አዲሶችን ፈለፈለች ። አዲስ ነገር ። አዲስ ጉዳይ …..እና ሌሎችንም።
******************************************
የዮሐንስ ሰ."ነፃ አስተያየት" 
የነበይ መኮንን "የኛ ሰው በአሜሪካ"
የነ አልአዛር ኬ፣
የሌሌሳ ግርማ " ልብወለድ" 
የኤፍሬም እንዳለ"እንጨዋወት"
የነእዮብ ካሣ፣
የከበደ ደበሌ ሮቤ፣
የገዛኸኝ ፀ"የመጽሐፍ ክሪቲክ" 
የሌሎችም አምደኞችን ፀሑፎች እሁድ ጧት ላይ ፓላስ ካፌ ቁጭ ብዬ 
በጥቁር ማኪያቶ የማወራራዳቸው በረከቶቸ ነበሩ....__Ethiopia First



ማሞ ካቻ (አቶ ማሞ ይንበርብሩ)

  አቶ ማሞ ይንበርብሩ (ማሞ ካቻ) እስቲ እናስታውሳቸው፣ ተቀብሮ እንዳይቀር አኩሪ ታሪካቸው  (ደረጀ መላኩ)   አቶቢሲ ማሞ ካቻ የት ትሄዳለህ? ገብረ ጉራቻ… ታዳጊው ማሞ ይንበርበሩ ገና በጨቅላ እድሜው አባቱ አቶ...