ረቡዕ, ኖቬምበር 19, 2014

“ኦሮማይ” እና በዓሉ ግርማ

ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
******************

 ኦሮማይ ከልቡ መጽሐፍ ነው፡፡ በአማርኛ ልብ-ወለድ መጻሕፍት (Novel) ታሪክ በጣም አነጋጋሪውና አከራካሪው መጽሐፍ ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ የህዝብ ፍቅር ካልተነፈጋቸው ጥቂት መጻሕፍት አንዱም ነው፡፡ በህይወቴ ብዙ ጊዜ እየደጋገምኩ ካነበብኳቸው መጻሕፍት መካከልም በመጀመሪያው ረድፍ ይሰለፋል፡፡ ይሁንና ሰዎች ለዚህ መጽሐፍ ያላቸው አድናቆት እንደየ አመለካከታቸው ይለያያል፡፡
መጽሐፉ የብዙዎቹን አትኩሮት የሳበው ታሪኩ እውነት ነው ስለተባለ እና በመጽሐፉ ሳቢያም የደራሲው ህይወት ለአደጋ በመጋለጡ ይመስለኛል፡፡ ከመጽሐፉ ዐቢይ ገጸ-ባህሪያት አንዱ የሆኑት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ “የደም እምባ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ተመሳሳይ እይታ አንጸባርቀዋል፤ እንደ ሻለቃ ዳዊት አባባል ኦሮማይ ባይታገድ ኖሮ ተወዳጅነቱ ይሄን ያህል አይገዝፍ ነበር፡፡ ሆኖም እኔ በዚህ አባባል አልስማማም፡፡ ደራሲው ባይሞት እና ታሪኩ እውነተኛ ባይሆን እንኳ “ኦሮማይ” ተደናቂ የመሆንን እድል አያጣም ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህም በርካታ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
“ኦሮማይ” በቅድሚያ ቀልብን የሚስበው በአጻጻፍ ብሂሉ ነው፡፡ ደራሲው ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው አጫጭር ዐረፍተ ነገሮችን ይጠቀማል፡፡ ይህም አንባቢው የመጽሐፉን የትረካ ቅደም ተከተል ሳይስት ድርሰቱን ያለድካም እንዲያጣጥም ያግዘዋል፡፡ ደራሲው ጠጣር ሃሳቦችን በቀላሉ ይዘረዝራል፡፡ የዘመኑ መንግሥት አሰራርን ለተደራሲው በሚገባው ቋንቋ ቀለል አድርጎ ያስረዳዋል፡፡ በሌላ በኩል መጽሐፉ ኪናዊ ውበቱን እንዳይስት ደራሲው በእጅጉ ተጠቧል፡፡ ዘይቤአዊ አባባሎችን ከዘመኑ የአነጋገር ፋሽን ጋር እየቀላቀለ አንባቢውን ያዝናናዋል፡፡ በተለይም “ኦሮማይ” ፈጠራ እየነጠፈ በዘመቻ ግርግር እና በንድፈ-ሓሳብ ዝብዘባ የሚፈበረኩ ቃላት የድርሰቱን ጎራ እያጠለሹ በመጡበት ዘመን አንባቢው በማይሰለቸው የቋንቋ ጥበብ የተጻፈ በመሆኑ የደራሲውን ልዩ ተሰጥኦ በጉልህ ያስረዳል፡፡ ሆኖም ኦሮማይ የዚያ ዘመን ድርሰት ብቻ አይደለም፡፡ በዚህ ዘመንም እንኳ ተደግመው ሊጻፉ ከማይችሉ ድርሰቶች መካከል ሊመደብ ይችላል፡፡
ይበልጥ አስደናቂው ነገር ደግሞ ወዲህ ነው፡፡ ደራሲው ያንን ውብ መጽሐፍ የጻፈው በጥቂት ወራት ውስጥ ነው፡፡ ይገርማል! ሰውዬው በወቅቱ ምክትል የማስታወቂያ ሚኒስትር ነበር (በደንበና ስሙ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ ይባል ነበረ)፡፡ የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ሆኖም ይሰራ ነበር፡፡ በአዲስ ዘመን እና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች ዝግጅትም ይሳተፋል፤ ዝግጅታቸውን በበላይነት ይቆጣጠራል፡፡ ቱባ ባለስልጣን በመሆኑ የብዙ ኮሚቴዎች አባል መሆኑም ይታመናል፡፡ በርካታ የቢሮክራሲ ስራዎችም ነበሩት፡፡ እና ከነዚህ ሁሉ የስራ ጋጋታዎች ጋር የሚታገል ሰው ያንን የመሰለ ውብ መጽሐፍ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዴት ብሎ ነው የጻፈው? ይህንን በቀላሉ ማመን ይቻላል? በትርፍ ጊዜው መጻፉ ይቅርና የሙሉ ጊዜ ደራሲ ቢሆን እንኳ አስቸጋሪነቱ መሆኑ አይቀርለትም፡፡ ሰውዬው ግን በዓሉ ነውና ቻለው! የስራ መደራረብ “ሳይበግረው” ኦሮማይን ከዘጠኝ ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንዲያ ከሽኖ አቀረበው (የቀይ ኮከብ ዘመቻ ያበቃው በየካቲት ወር 1974 ነው፤ ኦሮማይ የታተመው በታህሳስ ወር 1975 ነው)፡፡ ችሎታ ማለት እንዲህ ነው!!

ለኦሮማይ ዘመን አይሽሬነት ሁለተኛ አብነት ሆኖ የሚጠቀሰው ደግሞ የመጽሐፉ ጭብጥ ነው፡፡ በዚህ ላይ በርካታ ሰዎች የተለያየ አስተያየት ነው ያላቸው፡፡ አንዳንዶች በዓሉ ኦሮማይን የጻፈው የቀይ ኮከብ ዘመቻ ውጥረትና ውድቀትን ለመግለጽ ስለፈለገ ነው ይላሉ፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ “የመጽሐፉ ጭብጥ በርዕሱና በመጨረሻው ዐረፍተ ነገር ላይ ነው የሚገኘው” ብለው ነገር፡፡ አቶ መለስ ንግግራቸውን ሲያሰፉም “በዓሉ በመጽሐፉ “እናንተ ደርጎች በኤርትራ ላይ ሙዝዝ ካላችሁ በአዲስ አበባ ያላችሁንም ስልጣን ታጣላችሁ” የሚል መልዕክት ነው ያስተላለፈው” ብለዋል፡፡ አቶ መለስ ይህንን ትንተና የሰጡት ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የአልጀርሱን ስምምነት ፈርማ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ በምትጠባበቅበት ወቅት “የስምምነቱ አካሄድ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ነው” የሚል ሃሳብ ለሰነዘሩ ተቃዋሚዎች መልስ በሚሰጡበት ጊዜ ነው (ባልሳሳት ጊዜው የካቲት 1994 ይመስለኛል)፡፡ ሆኖም የኦሮማይ ጭብጥ በእንዲህ ዓይነቱ የፖለቲካ ዘውግ ብቻ የታጠረ አይደለም፡፡ ኦሮማይ በዘመኑ “አይነኬ” (taboo) የነበሩ በርካታ ጉዳዮችን ይነካካል፡፡ ለማስረዳት ይፈቀድልኝ፡፡
የደርግ መንግሥት በወቅቱ የሀገሪቱን ህዝብ ከአቅሙ በላይ እያሯሯጠው ነበር፡፡ ህዝቡ በየዓመቱ ከሚመጣበት የዘመቻ መአት ሳያገግም በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማያውቀው ግዙፉ የቀይ ኮከብ ሁለገብ ዘመቻ በጫንቃው ላይ ወረደ (ዘመቻው የጠየቀው የሰው ሀይልና ማቴሪያል ሳይደመር ሁለት ቢሊዮን ብር ወጥቶበታል፤ ይህም በወቅቱ ከሀገሪቷ በጀት ግማሽ ያህሉን ይሸፍናል)፡፡ ሆኖም በዘመኑ ወታደራዊው መንግሥት ያሻውን ቢያቅድና ቢፈጽም አይደፈሬ ነውና ማንም ሰው አፍ አውጥቶ አልተቃወመውም፡፡ በዓሉ ግርማ ግን ለመጪውም ዘመን ትምህርት በሚሆን መልኩ የቀይ ኮከብ ዘመቻን በግልጽ ቋንቋ ሄሶታል፡፡ ለምሳሌ በመጽሐፉ ውስጥ የጋዜጠኛ ጸጋዬ ኃይለማሪያም እጮኛ እንዲህ ትላለች፡፡
“ኤጭ እቴ! ለሁሉም ነገር ቸኩሎ መሞት! ነጋ ጠባ ዘመቻ! እድገት በህብረት ብሎ ዘመቻ! ለጦርነት ዘመቻ፡፡ የኢኮኖሚ ግንባታ ዘመቻ፡፡ ማይምነትን ለማጥፋት ዘመቻ፡፡ የቁጥጥር ዘመቻ፡፡ አሁን ደግሞ የኤርትራን ችግር ለመፍታት ዘመቻ፡፡ የዘመቻ ባህል ፈጥረናል፡፡ ያለዘመቻ ኖረን የምንሞትበት ቀን መቼ ይሆን?” (ኦሮማይ ፤ ገጽ 9)
ጋዜጠኛው የመንግሥት ባለስልጣን ሆኖ ለእጮኛው ንግግር የሰጠው ምላሽ ይበልጥ የሚደንቅ ነው፡፡ “ጊዜ ያጥረናል፤ እብዶች ነን፤ ችኩል ትውልድ፤ ያበደ ትውልድ…” ወዘተ.. ይላታል (ኦሮማይ፤ ገጽ 10)
በአንድ በኩል ጸሓፊው የዘመኑ ባለስልጣናት ለቀይ ኮከብ ዘመቻ መሳካት አኩሪ ገድል ሲፈጽሙ ያሳየናል፡፡ ወዲያው ዞር ይልና ደግሞ የመንግሥቱ የቀን ቅዠትና ሀገር አጥፊ ፖሊሲ ያስከተለውን ቀውስ በራሳቸው በባለስልጣናቱ አንደበት ይገልጽልናል፡፡ ለምሳሌ ከመጽሐፉ ዐቢይ ገጸ-ባህሪያት አንዱ የሆነው ኢኮኖሚስቱ መጽሐፈ ዳንኤል ዘመቻው በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ጫና በማስረዳት የዘመኑን አመራር እንዲህ ይሸረድደዋል፡፡
“ይህንን የቆየ ችግር በዘመቻ እንፈታለን ብለን ስንረባረብ ከአሁኑ ሌላ ችግር እየፈጠርን ነው፤ 450 ከባድ የጭነት መኪናዎች፤ 250 ሼልቶ፣ 200 ከነተሳቢያቸው ወደ ሰሜን ማዞር ምን ማለት ነው? ባጭሩ ኢኮኖሚው ተናግቷል ማለት ነው፤ ደሞ አሁን የመኸር ጊዜ መሆኑን አትርሳ” (ኦሮማይ፤ ገጽ 75)
ጋዜጠኛው በዚህ አባባል ተናዶ “ስብሰባው ላይ ምን ዘጋህ? ቅድም እንዲህ ብለህ አትናገርም ነበር፡፡ መድረኩ ለማንም ክፍት ነበር፡፡ማን ከለከለህ?” ሲለው መጽሐፈ ዳንኤል “ትቀልዳለህ ልበል?” በማለት በአጭሩ መልሶለታል፡፡ መጽሐፈ ልክ ነው፡፡ አንድ ሰው በሚፈልገው መንገድ ብቻ መደስኮር በሚፈቀድበት ስብሰባ ሐቁን እናገራለሁ ቢል የሚደርስበትን ቅጣት በደንብ ያውቀዋል፡፡ ለዚህም ነው በስብሰባና በጉባኤ ፊት እያስመሰሉ መለፍለፍ እና ለክፉ አሳልፎ የማይሰጥ ወዳጅ ሲገኝ ሐቁን መናገር የዘመኑ ወግ ሆኖ የቆየው፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ሰለሞን በትረ-ጊዮርጊስ የተባለው ገጸ-ባህሪ የያኔውን የፕሮፓጋንዳ አካሄድ እስኪበቃው ድረስ ሲወርፍ ይታያል፡፡ “እናንተ ጋዜጠኞች ጭንቀታችሁ ሁሉ ስታቲስቲክስ ነው፤ ይህን ያህል ሄክታር መሬት ታረሰ፤ ይህንን ያህል ህዝብ ተደራጀ፤ ይህን ያህል ሰዎች ከመሀይምነት ተላቀቁ፤ ነው የምትሉት፡፡ እንዲያው ወሬአችሁ ሁሉ ስታቲክቲክስ ነው፤ ዘገባችሁ ሰው ሰው አይሸትም፤ ስለ አሐዝ ስትጨነቁ ሰው ትረሳላችሁ” ይላል (ኦሮማይ ገጽ፤ 67)፡፡ እነኝህን የመሳሰሉ የስርዓቱን ጉድፍ የሚያሳዩ በርካታ አንቀጾችን መልቀም ይቻላል፡፡
የቀይ ኮከብ ዘመቻ የመጨረሻ ግብ ናቅፋ የሚገኘውን የሻዕቢያ ዋና የዕዝ ማዕከል መቆጣጠር ተደርጎ ይታሰብ ነበር፡፡ ሆኖም ናቅፋ በቀላሉ የምትደፈር ሆና አልተገኘችም፡፡ ሺዎች እንደ ቅጠል ረግፈዋል፡፡ ሺዎች ቁስለኛና ምርኮኛ ሆነዋል፡፡ ሁኔታውን በቅርበት የታዘበው ጋዜጠኛ ጸጋዬ ኃይለማሪያም ጦርነቱ ከኪሳራ ውጪ የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ተገንዝቧል፡፡ ከናቅፋ ወደ አፍአበት ሲመለስ “አይዞን! ገና ሺህ ናቅፋዎች ይጠብቁናል” ብሎ ለተናገረው ባለስልጣን “እኔ አንድ ናቅፋ ከወዲሁ በቅቶኛል፤ የጦርነትን አስከፊ ገጽታ ከአሁን በኋላ ላለማየት ቆርጫለሁ” በማለት ተቃውሞውን ገልጿል (በዓሉ ጦርነቱን ከተቃወመባቸው ዐረፍተ ነገሮች መካከል ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ይህኛው ነው)፡፡
**********************

“ኦሮማይ” ፈርጀ ብዙ የዕውቀት ድርሳን ነው፡፡ ረጅምና ውስብስብ የሆኑ እውነተኛ ታሪኮችን እጥር ምጥን አድርጎ በቀላሉ ያስነብበናል፡፡ ለምሳሌ የኤርትራ ችግር መሰረታዊ ምንጭ ምን እንደሆነ መረዳት የሚፈልግ ሰው ከሰለሞን በትረጊዮርጊስ ታሪካዊ ትንተና ብዙ ቁምነገሮችን ይጨብጣል (ኦሮማይ፡ ገጽ 78-86)፡፡ እንግሊዝ በኤርትራ ምድር የቀበረችው ፈንጂ፤ የኤርትራ ክፍለ ሀገርን ከኢትዮጵያ ጋር ለመቀላቀል የተደረገው ጥረት፤ የጀብሃና ሻዕቢያ አነሳስና በመካከላቸው የተፈጠረው ፍጭት፣ አብዮታዊ ሰራዊት ኤርትራን ከአማጺያን ለማጽዳት ያደረገው ዘመቻ ወዘተ… በሰለሞን አንደበት በሰፊው ተተንትነዋል (እርግጥ ትንተናው ሙሉ በሙሉ ትክክል ነው ለማለት አይቻልም፤ ግማሽ ያህሉ የደርግ መንግሥት በሚፈልገው መልክ የተቀናበረ ነው)፡፡
የጎሪላ እና መደበኛ የውጊያ ስልትን በተነጻጻሪ ማወቅ የሚፈልግ ሰው ከኦሮማዩ ኮሎኔል ታሪኩ ወልዳይ ትንታኔ ብዙ ነገሮችን ይማራል፡፡ ኮሎኔል በትሩ ተሰማ እና አጋዥ ቡድኑ (እነ ተክላይ ዘድንግል ያሉበት) የዘመኑ የኢንተሊጀንስ ጥበብና ስልት ምን ይመስል እንደነበር በቃልና በድርጊት ያሳዩናል፡፡ ጋዜጠኛው ጸጋዬ ኃይለማሪያም አስቸጋሪውን የናቅፋ ተራሮች የመሬት አቀማመጥ ለዓይናችን ወለል ብሎ እስኪታየን ድረስ በማይሰለቸው ብዕሩ እያጣፈጠ ይተርክልናል፡፡ ስዕላይ ባራኺ እና ጓዶቹ ደግሞ የሚያስገርሙ ጀብዶችን እየተገበሩ ሻዕቢያ በሰርጎ ገቦቹ አማካኝነት አስመራን እንዴት ያሸብራት እንደነበር ያሳዩናል፡፡ የአስመራ ነዋሪዎች የአኗኗር ወግና ማሕበራዊ ህይወት፣ የከተማዋ ታዋቂ ሰፈሮችና ሆቴሎች፤ የመንገዶቹ ውበትና አቀማመጥ ወዘተ… በመጽሐፉ ዘርዘር ብለው ተጽፈዋል፡፡ በኔ እይታ አንድ ሰው ልብ ወለድ ተብሎ የተጻፈውን “ኦሮማይ”ን ቢያነብ ከአስር መጻሕፍት የሚያገኘውን ዕውቀት ሊገበይ ይችላል፡፡
*****
እንደዚያም ሆኖ ግን “ኦሮማይ” ሙሉ በሙሉ እውነተኛ ታሪክ አይደለም፡፡ ደራሲው የመጽሐፉን ተነባቢነት ለማጉላት ምናባዊ ገጸ-ባህሪዎችንና ታሪኮችን ጨማምሯል፡፡ ለምሳሌ ደራሲው የሁለት ሰዎችን ታሪክ አዳብሎ “ስዕላይ በራኺ” የተባለ ገጸ-ባህሪ ፈጥሮልናል፡፡ እንደዚሁ ደግሞ በመጽሐፉ ውስጥ የሻዕቢያ ሰዎች በዚሁ ስዕላይ በራኺ በተባለ ገጸ-ባህሪ መሪነት የሚያካሄዱት “ኦሮማይ” የተሰኘ ስውር ኦፕሬሽን የደራሲው ፈጠራ ነው (“ቢሮክራሲ” የተባለው የስለላ ኔትወርክ ግን ትክክለኛ ነው)፡፡
ከኦሮማይ ገጸ-ባህሪያት መካከል ኮሎኔል መንግሥቱ ሀይለማሪያምና ኢሳያስ አፈወርቂን የመሳሰሉት በእውነተኛ ስማቸው ተጠቅሰዋል፡፡ አንዳንዶቹ ግን ስም የለሽ ሆነው በድርጊታቸው ብቻ ተገልጸዋል (ለምሳሌ “የቀይ ኮከብ ሁለገብ ዘመቻ ዋና ጸሐፊ” ተብለው በስራ መደባቸው ብቻ የተጠቀሱት ባለስልጣን አቶ አማኑኤል አምደሚካኤል ናቸው)፡፡ ከፊሎቹ ገጸ-ባህሪያት በእውነታው ዓለም የሚታወቁበት ስም በመጽሐፉ ውስጥ ተቀይሯል፡፡ ከነርሱ መካከል የጥቂቶቹ ትክክለኛ ስም እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
1. ኮሎኔል በትሩ ተሰማ= ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ (በደርግ መንግሥት የህዝብ ደህንነት ጥበቃ ሚኒስትር፤ ሆኖም ኮሎኔሉ “የኔ ምክትል ነው እንጂ እኔ አይደለሁም፤ እኔ በቀይ ኮከብ ዘመቻ አስመራ አልሄድኩም” በማለት አስተባብሏል)።
2. ኮሎኔል ታሪኩ ወልዳይ= ኮሎኔል ተሻገር ይማም (የአንበሳው ሶስተኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ የነበረ፤ በ1974 በናቅፋ በተካሄደው አደገኛ ጦርነት ማብቂያ ላይ ራሱን የገደለ)።
3. መጽሐፈ ዳንኤል= አቶ ፋሲካ ሲደልል (የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የማዕከላዊ ፕላን ሚኒስትር የነበረ)
4. የሺጥላ ማስረሻ= አቶ ሽመልስ ማዘንጊያ (የኢሠፓ የፖሊት ቢሮ አባልና የርዕዮተ ዓለም ጉዳዮች ሃላፊ የነበረ)
5. ጸጋዬ ሀይለማሪያም= የበዓሉ ግርማ ግርማ እና የቴሌቪዥን ጋዜጠኛው የጌታቸው ኃይለማሪያም ቅልቅል ይመስላል፡፡
6. ተድላ ረጋሳ= ሻለቃ ፍሰሓ ገዳ (የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የደርግ መንግሥት የፕሮቶኮል ሹም)
7. ሰለሞን በትረ ጊዮርጊስ= ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ (በቀይ ኮከብ ዘመን የኤርትራ ክፍለ ሀገር ኢሠፓአኮ ተጠሪ እና የክፍለ ሀገሩ የበላይ አስተዳዳሪ፣ በኋላም የእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ኮሚሽነር፤ በ1978 ከደርግ መንግሥት ተነጥሎ ወደ ውጪ ሀገር የኮበለለ)
8. ስዕላይ ባራኺ= የሁለት ሰዎችን ታሪክ በመቀላቀል የተፈጠረ ነው፡፡ አንደኛው ተስፋሚካኤል ጆርጆ ነው (አቶ ተስፋሚካኤል በሀይለስላሴ ዘመን የደቀምሐረ ወረዳ ገዥ የነበረ ሲሆን በ1963 ኢሳያስ አፈወርቂን ከሲ.አይ.ኤ ጋር በማገናኘት ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፣ ይህ ሰው በ1984 መጨረሻ ላይ በሻዕቢያ አዳኝ ኮማንዶዎች አዲስ አበባ ውስጥ ቫቲካን በሚባለው ሰፈር ተገድሏል)። ሁለተኛው ሰው ተክላይ አደን ይባላል (ተክላይ አደን የሻዕቢያ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የድርጅቱ የፖለቲካ ትምህርት ቤት ሃላፊ ነበር፤ በኋላ እጁን ሰጥቶ በሀገር ውስጥ ሲኖር ከቆየ በኋላ ደርግ ሲደመሰስ ወደ አውሮጳ ሄዷል)፡፡
9. “ቢሮክራሲ”= አፈወርቂ ተወልደ መድሕን (ደሴ የተማረ የሻዕቢያ የውስጥ አርበኛና ሰላይ፣ “ቢሮክራሲ” በሚል ስም የሚታወቀውን የስለላ ኔትወርክ የሚመራው እርሱ ነው፡፡ በኋላ ግን ድሬ ዳዋ ላይ ተይዞ ተረሽኗል)፡፡
*****
*********************************************************************************

ስለኦሮማይ ይህንን ብያለሁ፡፡ ወደፊት አዲስ ነገር ከተገኘ መመለሴ አይቀርም፡፡ እስከዚያው ሌሎቻችሁ የምታውቁትን ጨምሩበት፡፡ ሰላም!
አፈንዲ ሙተቂ
ሸገር-አዲስ አበባ
ጥቅምት 13/2006

ሰኞ, ኦክቶበር 13, 2014

ደራሲ አዳም ረታ



አዳም ረታ በ1950 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለደ። በትምህርት አለም - በጂኦግራፊ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀብሏል። ሁለተኛ (የማስተርስ) ዲግሪውን ደግሞ በውጭ ሀገር አግኝቷል። የሚፅፈው በአብዛኛው አጫጭር ልቦለዶችን ቢሆንም ግጥሞችንም ይፅፋል። በተለያዩ ጊዜያት ግጥሞቹ በተለያዩ መፅሔቶች ላይ ታትመዋል። ያልታተሙ ግጥሞችም አሉት።

ከተደራሲው ጋር የተዋወቀበት እና በኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ ተከታታዮችና አንባቢዎች ልብ ውስጥ የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጠበት “አባ ደፋር እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች” በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት የታተመው በ1977 ዓ.ም ነው። (በዚህ መድብል ውስጥ አራት ስራዎችን አዋጥቷል፡ “ድብድብ”፣ “ዕብዱ ሺበሺ”፣ “ሲሮኮ” እና “ሲፊንክስ”) ሜጋ አሳታሚ ድርጅት በ1990 ዓ.ም ባሳተመው “ጭጋግና ጠል” የአጭር ታሪኮች ስብስብ “ዘላን” የተባለው ልቦለዱ ታትሟል። እነዚህ ሁለቱ ከሌሎች ደራሲዎች ስራዎች ጋር የታተሙለት ስለሆነ እንደ ወጥ ሳይቆጠሩ ነው ከላይ የሰፈረው የተባለው። በ1981 ዓ.ም በኩራዝ አሳታሚ የታተመው “ማህሌት” የደራሲው የመጀመሪያ ወጥ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መፅሀፍ ነው። በሻማ ቡክስ በ1997 ዓ.ም የታተመው “ግራጫ ቃጭሎች” እንደ ብሉይ (classic) ሥራ ሊታይ የሚችልና የደራሲው ልዩ ብቃት የታየበት ወጥ ረጅም ልብወለድ ነው።


በ2001 ዓ.ም ሁለት ልዩ ስራዎች ይዞ የቀረበው አዳም፡ የአጫጭር ልብወለዶች ስብስብ የሆነው “አለንጋና ምስር” እና እርስ በርሳቸው በቀጭን የታሪክ ክር የሚገናኙ ልብወለዶች (ኖቬላዎች) ያካተተው “እቴሜቴ የሎሚ ሽታ” ለአንባቢያን አበርክቷል። በቀጠሉት ሦስት ዓመታት በየዓመቱ አንዳንድ መፅሐፍ ለአንባቢያ ያደረሰ ሲሆን በ2002 ዓ.ም “ከሰማይ የወረደ ፍርፍር”፣ በ2003 ዓ.ም “ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” እና በ2004 ዓ.ም “ሕማማት እና በገና” ታትመው ለንባብ በቅተዋል። “ከሰማይ የወረደ ፍርፍር” በተሰኘው መፅሀፉ ድንቅ የፋንታሲ (“ፈንጠዚያ”) ሥራዎች የተካተቱ ሲሆን በ”ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” ለመጀመሪያ ጊዜ መቼቱን ከሀገር ውጭ በማድረግ የውጭውን ሕይወት በስሱ የዳሰሰ ሲሆን ከሌሎቹ ስራዎቹ በተለየ መልኩ ስለሀገራችን ፖለቲካ ወጣ-ገባ መንገድ በታዛቢ አይን ምልከታው፣ ትውስታውን … አስፍሯል፡፡ ሕማማትና በገና የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ሲሆን ለየት ያለ ቅርፅ ያላቸው አንዳንድ ልቦለዶች ተካተውበታል። አዳም ረታ በተለየ የአፃፃፍ ስልቱ እና በስራዎቹ ጥልቀት በሃያስያን ዘንድ አዎንታዊ ሂስ እና ከፍተኛ አድናቆት ተችሮታል።
ለሕትመት የበቁ የአዳም ረታ ስራዎች
  • አባ ደፋር እና ሌሎች ታሪኮች ------------1977 ዓ.ም(“ድብድብ”፣ “ዕብዱ ሺበሺ”፣ “ሲሮኮ” እና “ሲፊንክስ”)
  • ማሕሌት - ----------------------------1981 ዓ.ም
  • ጭጋግና ጠል እና ሌሎች ----------------1990 ዓ.ም (ዘላን)
  • ግራጫ ቃጭሎች ---------------------- 1997 ዓ.ም
  • አለንጋና ምስር ------------------------ 2001 ዓ.ም
  • እቴሜቴ ሎሚሽታ -------------------- 2001 ዓ.ም
  • ከሰማይ የወረደ ፍርፍር ---------------- 2002 ዓ.ም
  • ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ ----- 2003 ዓ.ም
  • ሕማማትና በገና ---------------------- 2004 ዓ.ም
  • መረቅ---------------------------------2007 ዓ.ም
              ምንጭ:--Ethiopian Writers Association የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር

አዳም እና ሥራዎቹ - በአድናቂዎቹ አይን 



 “እኛ አገር የመፃፍ ክህሎት ያላቸው በርካታ ናቸው፤ እየፃፉልን ያሉት ጥቂቶች ቢሆኑም፡፡
እነዚህ ጥቂቶችም የመፃፍ አቅማቸውን ያህል አልሰጡንም ፤ ወይ ሰንፈዋል - ወይ ያልተመቻቸው ነገር አለ፡፡ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ፣ በዕውቀቱ ስዩም፣ አለማየሁ ገላጋይ፣ እንዳለጌታ ከበደ፣ ሰርቅ ዳ.፣ ሌሊሳ ግርማና መሰሎች ባላቸው ልክ /በዕድሜያቸው ልክ እንደማለት/ ብዙ ለማሳተምና ያላቸውን ለመስጠት የሚታትሩ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በእርግጥ ካላቸው ተሰጥኦና አቅም አንጻር ያሳተሟቸው ሥራዎች ማነሳቸው የሚከነክኑን እንዳሉበትም ልብ ይሏል፡፡ አዳምን ግን በተለየ ዓይን እንየው፤ በብቃትና በጥራት ያለውን ያለስስት እየሰጠን ነው፡፡
 /በዓሉና አዳም ከሚመሳሰሉባቸው ነገሮች አንዱ፣በተከታታይ በጥራት መፃፋቸውና ያንንም ለህዝብ ማድረሳቸው ነው፤ ከአስር ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሁለቱም ከሰባት በላይ መጻህፍት ፅፈዋል፡፡/ አዳም ወደ ራሱ አብዝቶ የሚመለከት በመሆኑ ሰቅዞ ይይዛል፡፡
ለእኔ አዕምሮ የሚያክ ደራሲ ነው፤ የትዝታ ዘመኑን /ረጅም ጊዜ ውጭ ነውና እየኖረ ያለው/ በጥፍሩ ሲቧጥጥ፣

እኛም ባልኖርንበት ዘመን ትዝታችንንና ኑሮአችንን እንድንቧጥጥ ዕድል ይሰጠናል - አገናኝ ድልድይ በመሆን፡፡ አሰላሳይ ደራሲ ስለሆነ  የቃላት ጨዋታው ሁሉ ልቡና ላይ ነው - እያነበብከው አብረኸው ታሰላስላለህ፤ ኑሮህን፣ ዘመንህን፣ አገርህን!!
አዳም <<post modernism>> አፃፃፍ የገባው ነው፡፡
ከታሪክ አወቃቀርና ከመቼት ብሎም ከሴራ በላይ በድርሰቱ ይዞት የሚመጣው ቅርፅ የሚያሳስበውና ለእሱም

አብዝቶ የሚሳሳ ይመስላል፡፡ ቅርፅና አዳም ጋብቻ ፈፅመዋል - እንደሱ ገለፃ ‹‹የእንጀራ ቅርፅን›› አስተዋውቆናል፡፡ ይህ የራሱን መንገድ ይዞ የሚፈስ ቦይ ነው እንድንል ያስችለናል፡፡ በዚያ ወንዝ ውስጥ በተለይም ከ“ግራጫ

ቃጭሎች” እስከ አሁኑ “መረቅ” ድረስ ባለው ቅርፁ እከሌን  ይመስላል ለማለት ፊት አይሰጥም - አዳም በቃ አዳምን ይመስላል፡፡
 አዳም በሰው ኮቴ ላለመራመድ ያደረገው ፣ ከ“ግራጫ ቃጭሎች” በኋላ ተሳክቶለታል - በእኔ እምነት፡፡ አዳም የሰው ዳና አላዳመጠም፣ አዳም በራሱ መንገድና በራሱ ፋና ነው የነጎደው፤ በቋንቋና በሃሳብም ቢሆን ልቀቱ

ከፍታውን ይመስክሩለታል”
          - ደመቀ ከበደ  (ገጣሚ)



“የሥነፅሁፍን ሥራ ከማንም በላይ የሚፈትሸውና  የሚያቆየው ጊዜ ባለሟሉ ነው።  የአዳም መጻህፍት  ከጊዜ ጋር ለወደፊትም በአገራችን የሥነፅሁፍ ታሪክና አፃፃፍ ዘይቤ፣ የራሳቸው  ትልቅ ድርሻና ቦታ ይኖራቸዋል።አዳም «ህጽናዊነት» የሚል ስያሜ የሰጠው የራሱ የሆነ የአፃፃፍ ዘይቤ መፍጠር የቻለ ደራሲ ነው።  ይህም ጥቃቅንንም ሆኑ ግዙፍ ነገሮችን፣ ሰዎችን (ገፀ ባህሪያት)፣ ስሜቶችን፣ ሁኔታዎችን በማያያዝና በማዛመድ አንባቢዎች አእምሮ ውስጥ ትውስታና ትዝታም የሚጭር የአፃፃፍ ዘይቤ ነው። በታሪክ ይዘታቸው በጣም መሳጭና ወደ ራሳችን ውስጥ አስገብተን፣ እራሳችንን እንድንፈትሽና እንድንጠይቅ የሚያደርጉ ናቸው።   አንዳንድ  የሴት ገፀ ባህርያቱ፣ የሴቶችን አስተሳሰብና  ባህሪያት በግልፅ (ሳይሸፋፍንና ሳያድበሰበስ)

የሚያሳዩ ናቸው።  ሴት ልጅ በወጣትነት እድሜዋ የሚያጋጥማትን  ስነልቦናዊ ፈተናዎችና ከባሕላችን ጋር ለመራመድ (ለመሄድ) የምታደርገውን ነገሮች--- አስመሳይነትን በግልፅ የምናይባቸው ገፀ ባህሪያት አሉ። ለምሳሌ “እቴሜቴ የሎሚ ሽታ” ውስጥ “ (ሽልንጓ) የመጨረሻዋ የቀበሌ 01 ድንግል” ውስጥ ያለችው የነፃነት ገፀ ባህሪ፣ የሴት ልጅን  ሥነልቦናዊ  ፈተና  በደንብ ያሳየናል። በእኛ ሕብረተሰብ ውስጥ ሴት ልጅ “ጨዋና ጭምት” መሆን አለባት ተብሎ ይጠበቃል። “ጨዋ” ማለት ምን ማለት ነው? ይህን እንድንጠይቅና እንድንፈትሽ የሚያደርጉ ገፀ ባህሪዎች ናቸው። በ“ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” ውስጥ ያሉት እትዬ ወርቄ  ደግሞ አገር ወዳድነትን፣ እናትነትን፣ እማማ ኢትዮጵያን ራሷን የሚስልበት ገፀ ባህሪ ናቸው። ለዚህም ነው ጊዜና ዘመን የማይሽራቸው መፅሐፍት የሚመስሉኝ።
እነሆ አሁን ደግሞ 600 ገጾች ያሉት  ዳጎስ ያለ አዲስ ልብወለድ፣ «መረቅ» በሚል ርዕስ ለአንባቢያን አቅርቧል።”
ሮማን ተወልደ ብርሃን ገ/ እግዚያብሄር (አድናቂ፣ ከለንደን)



አዳም ስለራሱ….
 “ስጽፍ አልለፋም!...”
 “አጣርቼ የማስወጣበት ወንፊት የለኝም!”
 (‘በስራዎችህ ከጥቃቅን ዝርዝሮች፣ የማይደፈሩ እስከሚመስሉ ነገሮች ደፍረህ ታወጣለህ፣ የገጸ ባህሪያቱን ውስጣዊ ስሜት፣ የማህበረሰቡን ህጸጾች ጨክነህ ታፍረጠርጣለህ…’ ተብሎ ሲጠየቅ፣የሰጠው ምላሽ)“ነገሮችን ማየት እወዳለሁ እንጂ አልንቀለቀልም፡፡ ጥቃቅን የሚመስሉ ነገሮችን አልንቃቸውም፡፡ አያቸዋለሁ፡፡

እረፍት ሳገኝ ደግሞ፣ ተመልሼ በደንብ አያቸዋለሁ… የሚጻፉ መስለው ከታዩኝ፣ እጽፋቸዋለሁ!...”
 “When I want to write, I write!”
 (‘ለመጻፍ የሚያነሳሳህ ምን አይነት ሁኔታ ነው?’ ለሚል ጥያቄ የመለሰው)
“ ‘ፍቅር እስከ መቃብር’ ውስጥ ያለችው ሰብለ ወንጌል፣ እንደ መልዓክ ናት - ከሰው ይልቅ ለመልዓክት የቀረበ

ባህሪ የተላበሰች፡፡ እኔ የሞከርኩት፣ ሰብለን ‘ሰው’ ሆና እንድትታይ ለማድረግ ነው!...”
.“Mezgebu is just living. He knows nothing about precision and the like.”
(ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ደራሲ አዳም ረታ፣ ከአድናቂዎቹ ጋር በተገናኘበት የቡና ስነስርዓት ላይ ከተናገረው የተወሰደ)
*******************************************************************************
ምንጭ:--http://addisadmassnews.com

ማክሰኞ, ጁን 10, 2014

ያወጣሁ ያወረድኩት ሀሳብ


Chasing Beautiful Questions 
እንዲህ አሰብኩ ። ሜኒያፖሊስ አየር መንገድ የአይሮፕላኑ መንደርደሪያ መስክ ላይ እኔን እና ብዙ ፈረንጆችን የተሳፈርንበት የብረት አሞራ ወደ ሰማይ ለመምጠቅ ሲንደረደር አንድ ሀሳብ ወደ አእምሮዮ መጣ።እሳቤውን የጫረልኝ አንድ እግሩን በቀን ጎዶሎ ያጣ ፈረንጅ ነው። ገና የ 21 ዓመት ጐረምሳ ሳለ በበጋው ወራት አሪዞና ውቅያኖስ ዳርቻ ፈረንጆቹ ዋተር እስኪንግ የሚሉትን በእኛ አገር እይታ ቅብጠት በእነሱ ደግም እስፓርት ጨዋታ ላይ እንዳለ ያልታሰበ የሞተር ጀልባ ገጭቶት እራሱን ይስታል ።
እራሱን ያወቀው እሆስፒታል ውስጥ ነበረ ። መመልከት አልፈልግም ግን ልመልከተው አለ ግራ እግሩ ተቆርጧል እጂግ ልብን የሚሰብር ሀዘን ነበር። የሆስፒታሉ ፕሮስቴቲክ ወይም የሰው ሰራሽ እግር ሞያተኞች በአሉሚኒየም የተሠራ እግር አመጡለት እናም ከብዙ ማስጠንቀቂታያ ጋር ከሆስፒታል ወጣ።
ለመጀመርያ ጊዜ በአዲሱ ሰው ሠራሽ እግር ለመራመድ ሲውተረተር እንደ ጐማ ተጠቅልሎ ነበር የወደቀው ።ከዚያች ሰከንድ በኋላ ዳግመኛ እንዲህ አይነት ቅብጠት እንደማያዋጣ ገባው ።ዶክተሮቹ በቀን ሁለት ጊዜ ያውም ብዙ ነገር እየተደገፈ እዲሞክር ቢያዙትም እርሱ አሻፈረኝ ብሎ ከደንቡ ውጪ ልራመድ ሲል ነው ዋጋውን ያገኘው። ፊሊፕ የተባለው ይህ ጀብደኛ ጕረምሳ ጭራሹኑ የእግሩን መቆረጥ አላምንም ማለቱ ነበር በጊዜው ብዙውችን ግራ ያጋባው ።የእጮኛው አባት አይዞህ ፊሊፕዬ እስክትለምደው ድረስ ነው ከትንሽ ጊዜ በኋላ ትቀበለዋለህ አለው።እርሱ ግን የእግሩን አለመኖር ማመን አልቻለም ።ከንፈሬን በንዴት ነከስኩት ይላል ፊሊፕ ።እውነቱን ነው ማንም ሰው በሚረዳበት አረዳድ ከወሰድነው እግሬ ተቆርጧል ብዬ ከማመን ውጪ አማራጭ የለኝም ግን ይህንን የማይመች የአሉሚኒየም ቱቦ አድርጌ መሮጥ መዝለል ውሃ ላይ ወጫወትን ተከልክዬ መኖርን ማመን አልፈለኩም አለ ፊሊፕ ካለ ደግሞ ምን ማድረግ ይቻላ
ል ያዋጣህ ከማለት በስቲያ።
ፊሊፕ የራሤን ቆራጣ የምቀጥለው እኔው እራሴው ነኝ አለ። ሰውን ጨረቃ ላይ ማውጣት ከቻሉ ቆንጆ የሚያስሮጥ የሚያስዘልል እግር መስራት እንዴት ያቅታል ? ብዬ ጠየኩ። ጥያቄው ግን ቆንጆ ጥያቄ አይደለም ልበል? ይህ ከፍተኛ ፈጠራን ፍጹማዊ ለውጥን በዚህ ሞያ መፍጠሩ ግልጽ ነው ግን እንዴት ይተግበር ? ቀስ በቀስ እንዴት አልቻሉም ከሚለው ጥያቄ እንዴት አልቻልኩም ወደሚል ድምዳሜ የደረሰው ፊሊፕ የራስን ቆራጣ እኔ ብቻ ነኝ የመቀጠል ጥያቄ ያለኝም መልሱን ለመመለስ መጨነቅ ያለብኝም እኔ ነኝ አለ።
የፊሊፕ እየተማረ ያለው ጋዜጠኝነት ነው የፕሮሥቴቲክ ኢንጂነሪንግ ወይም ጐዶሎ አካልን የመተካት ምህንድስና ትምህርት ቺካጐ ኖርዝዌስት ዩኒቨርስቲ ይሰጣል እንደውም ከምርጦቹ አንዱ ነው። ስለዚህም ፊሊፕ የራሡን ቆራጣ ለመቀጠል ወደዚሁ ዩንቨርስቲ ገባ።
ፊሊፕ ዩንቨርስቲ ገብቶ ለመምህርነት የመረጣቸው እንስሳትን ነበር ካንጋሮ የተባለች ልጆችዋን ሆድዋ ውስጥ የምትደብቅ የአውስትራልያ የዱር እንስሳ አቦሸማኔ የተባለው ፈጣን እሯጭ ታላላቆቹ መምህራኖቹ ሆኑ። እግር ከሰራሁ አይቀር ለምን የአቦሸማኔ እግር አልሰራም ? አለ ፊሊፕ። እንዳለውም አልቀረ ከብዙ ሙከራ በኋላ የፈጣን እንስሶች ምስጢር ተገለጠለት ፕሮፌሰር አቦሸማኔ አስተማረው።ከዚህ በኋላ የፊሊፕ ጥያቄ ለምን ከማእድናቱ መካከል ምርጥ ብረት እግርን መተካት አይችልም ? የአቦ ሸማኔ የዃላ እግር ምን አይነት ቅርጽ ነው ያለው ? ደጋን ቅርጽ ፍጥነትን ለመጨመር የተመረጠ ይሆንን ? እያለ ሲጠይቅ ሲጠይቅ ሲመልስ ሲቀልስ ብዙውን ዓመታት ጥያቄ ብቻ ተማረ።ለምን? እንዴት ይሆናል ? ብረቶችን ሁሉ ሞከረ ጠንካራው የሚለመጠው የቱ መአድን ነው? ይገርማል ፊሊፕ ሥራውን ሲጀምር የነበረው ጥያቄ ብቻ ነበር አሁን ግን ብዙ መፍግትሄዎችም አግኝቷል።
ከእለታት በአንዱ ቀን ፊሊፕ መልሱን አገኘው ቆራጣውን ቀጠለ በደጋን ቅርጽ የሰራው ፊሊፕ ሠራሽ የብረት እግር ላይ ቆመ ተራመደ ሮጠ ። ይህ አይበሬ ሰው በፕሮስቴቲክ ሞያ አብዮት አፈነዳዳ በነገራችን ላይ አብይት ማለት ያለውን ማጥፋት ሳይሆን ባለው ላይ መጨመር አዲስ ግኝት በፈልሰፍም ነው።
ፊሊፕ በልምድ ታላቅ ነገርን አግኝቷል ይኸውም ጥያቄን ነው።ለምን የሚለው ጥያቄ ችግሮችን እንድንጋፈጥ ይጠቅመናል ለምን ሰውች አልሞከሩትም? ለምን ሁኔታው አልተቀየረም ? ሌላው ጥያቄ ደግሞ እንዲህ ቢሆንስ ?ይህ ደግሞ ጥያቄውችን በተለያየ አቅጣጫ እንድንመረምር የሚያመለክት ነው። የመጨረሻው እንዴት ይሠራ የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነገሩን ከፍጻሜ ያደርሰዋል።
የሰው ልጅ መሰረተዊ እውቀቱ ጥያቄ መጠየቁ ነው። አንድ ጥናት እደጠቆመው ፧ አንዲት ሕጻን 300 ጥያቄውችን በቀን ትጠይቃለች ስለዚህ ሰውን ሰው የሚያደርገው ጥያቄ ነው እንበለውን? ፊሊፕ አንድ አስገራሜ መደምደሜያ ላይ ደርሷል።ተማሪውች ውጤት የሚያገኙት በመልሳቸው እንጂ በሚጠዬቁት ጥያቄ አይደለም ስለዚህም በዚህ ደስተኛ አይደለም። ለምንድነው ለጠያቂዎች ማርክ የማዮሰጣቸው? ይላል ።ነገሩ ግራ ቢያጋባም አስተሳሰቡን እርባና ቢስ ብለን እንዳናሽቀነጥረው ብዙ ምክንያቶችን ፊሊፕ ይደረድርልናል። በዓለማችን ላይ ያሉ ምሁራንን ጥያቄ ጠየኳቸው የሚያቁትን ሳይሆን በህይወታቸውዘመን ምን እንደጠየቁ።ስለዚህም ለፈጠራ ቅድመ አያቱ ለካ ጥያቄ ኖርዋል ሳይንቲስቶችን ፈላስፋዎችን የንድ ሞያተኞችን ነጋዴውችን የስነጥበብ ሰዎችን ሳይቀር ስለጥያቄ ጠየኳቸው በተለይ መምህራንን ተማሪዎቻቸው ጥያቄ እንዲያጐርፉ ዘንድ እንዲያበረታቱ አሳሰብኳቸው ይላል ፊሊፕ። ለምን ተብሎ ሲጠየቅ እኔ የተቆረጠ እግሬን የቀጠልኩት በጥያቄ ብዛት ነው ይላል።
የጥያቄ ሞያተኛው ቫን ፊሊፕ የተባለው ጠቡብ ዕንዺሕ ብሎ መጠየቍ ዐሥፈላጚ ነው ይላል ። ይህ ነገር ለምን ከዚህ በተላየ መንገድ አይሰራም? ለምን በተለየ መንገድ ይህ ግር አይታይም ወይም አይተገበርም ? እንዴት እንጀምረው ? ብዙ ተግባር ሙከራ ጥያቄ ።ስለዚህ ነገርችን ደረጃ በደረጃ በመጋፈጥ የሚፈልጉበት ውጤት ይደርሳሉ።
እስቲ ከዚህ ሁሉ ትንታኔ በህዋላ ወደራሳችን ቆራጣ እንመለስ እኛ ኢትዮጵያን በብዙ ነገሮች ተበልጠናል ።ግን ለምን ተበለጥን ብለን ለመጠየቅ እንኳን እንዳንበቃ በብዙ የውሸት መልሶች ተሞልተናል። የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ አንድ መስሪያ ቤት ውስጥ የእስታስቲክ ሥራ ይሠራ ነበር ።ተሰብስቦ የተሰጠንን ዳታ በተዋበ ቀለም አሳምረን ምንስቴሩ ሲመጡ አሳየናቸው ቡና እና ሻይ ተጠጥቶ ተሳስቀው ወደ የመጡበት ሲመለሱ የግራፉን ውስጠ ምስጢር የምናውቀው ደነገጥን።ባይገርማችሁ ዳታው ሁሉ የውሸት ነበረ ።የበላይ ባለስልጣናቱ መጠየቅ ስላቃታቸው የፈጠጡ ስህተቶችን ሳይቀር ሳያስተውሉ ሄዱ።
በአገራችን ጥያቄ ወንጀልም ነው። ትምህርት ቤት የሚጠይቁ ሕጻናት መምሕሩን አሳጣችሁ ተብለው ይገለላሉ። የበታች አለቃውን እንደውቃቢ እየፈራ የታዘዘውን ይፈጽማል ለህሊናው ባያስደስተው እንኳን ። ሌላው ቀርቶ ግደል የተባለውን ሳይቀር ይገድላል ። በሐሰት መስክር ሲባል ለምን ብሎ አይጠይቅም ።
የራሳችን ቆራጣ ብዙ ነው። እርሱን ለመቀጠል ግን ሌላው ቀርቶ ትምህርታችን የራሳችንን ጉድለት ለመሙላት ታቅዶ የተማርነው አይመስልም። ለምን አገራችን ማደግ ተሳናት ? ለምን መስማማት አቃተን ? ለምን ስደት በዛ ? ለምን በአስተዳደር ችግር ከላይ እስከታች ተጥለቀለቅን ? ለምን በፈጠራ አገራችን ወደኋላ ቀረች ? ለምን ተሸናፊዎች ሆንን ?
ታላቁ ሳይንቲስት አልበርአንስታይን ሲናገር ከሰው የተለየ አእምሮ ኖሮኝ ሳይሆን ጥያቄዎችን ይዤ ስለምቆይ ነው ብሏል ምን ማለቱ ነው ።አንድን ጥያቄ በተለያየ መንገድ በማገላበጥ በመጠየቅ በመመለስ በመቀለስ በመሞከር ሳይሳካ ሲቀር ደግሞ ወደኁላ በመመሰስ በተለየ አቅጣጫ በማየት በአዲስ ብርሃን በመገንዘብ ማለት ነው። ፊሉፕ የተቆረጠውን እግሩን ለመተካት የበለጠ ለማሻሻል ለአርባ ዓመታት ለፍቷል አሁንም ግን በጥያቄ ውሥጥ ነው ።
ፊሊፕ ለእራሱ እግር መፍትሔ ሲፈልግ ይህንን ጥያቄ ይጠይቅ ነበረ ። ይንን ሰው ሠራሽ እግር ለመፈጸም ምን ያህል ወጪ ያስፈልግ ይሆን ? ልክ እንደኔው እግራቸውን ያጡ በደሃ አገር ያሉ በቀላሉ ሌያሠሩ ይችሉ ይሆ? ለእነዚህ ምስኪናን ፈጠራዮን ይጠቀሙበት ዘንድ ለምን አልፈቅድላቸውም ? ለዚህም መልስ አግኝቷል ምንአልባትም በቅርብ ጊዜ በመላው ዓለም ያሠራጨው ይሆናል ።
እኛም ከሁሉ በፌት ምድነው ቆራጣችን ? ብለን እንጠይቅ ።ከዚያ በህዋላ የገዛ ጉዴለታችንን እንሙላ እንደ ፊሊፕ ለሌሎች እንተርፍ ዘንድ።
***********************

ከይልማ ኃይሉ

ምንጭ spirit southwest airlines April 2014

ረቡዕ, ሜይ 21, 2014

ጀግናው በላይ ዘለቀ



  ግናው በላይ ዘለቀ ከአባታቸው ከባሻ ዘለቀ ላቀው እና ከእናታቸው ከወ/ ጣይቱ አስኔ በወሎ ክፍለ ሐገር በቦረና ሳይንት አውራጃ በጫቃታ ወረዳ ልዩ ስሙ ጅሩ ጉጣ ከተባለው ቀበሌ 1904 . ተወለዱ። በተወለዱ በአራት ዓመታቸው አባታቸው ባሻ ዘለቀ ላቀው የልጅ እያሱ ባለሟል ሆነው የአንድ ክፍለ ጦር ኃላፊ ስለነበሩ ልጅ እያሱ በተያዙ ጊዜ ከዚያ አምልጠው በቦረና ሳይንት አውራጃ በጨቃታ ወረዳ ልዩ ስሙ ጣቀት መድሉ ከተባለው ቀበሌ ተቀምጠው እንዳሉ ከአንድ ሰው ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው በፀብ መካከል የሰው ህይወት ያልፍባቸዋል። ለዚህም ምክንያት ወሎን ለቀው ወደ ጐጃም መጡ። ጐጃምም በተለይ በቢቸና አውራጃ በእነማይ ወረዳ ልዩ ስሙ ለምጨን ከተባለው ቀበሌ ተቀመጡ።
ብቸና ውስጥም ተቀምጠው ሳለ እርሳቸውን የሚያስስ ልዩ ጦር በጥቆማ ወደ አካባቢው ተላከ። ከዚህ ጦር ጋርም ከፍተኛ ውጊያ ተደረገ። በዚህ ውጊያ ወቅት በላይ ዘለቀ እና እጅጉ ዘለቀ ልጆች ቢሆኑም ተኩሱን እያዩ የሚወድቁትን ጥይቶች ይቆጥሩ ነበር። ከውጊያው በኋላም የበላይ ዘለቀ አባት ተመተው ይወድቃሉ። ይሞታሉ። እነ በላይ ዘለቀም ካለ አባት ከእናታቸው ከወ/ ጣይቱ አሰኔ ጋር ማደግ ይጀምራሉ። ከፍ ሲሉም የአባታቸውን ገዳይ እና አስጠቁሞ እየመራ ያስገደላቸው ማን እንደሆነም ለማወቅ ማሰስ ጀመሩ።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሳሉ ፋሺስት ኢጣሊያ 1928 . ኢትዮጵያን ወረረች። በላይ ዘለቀ በወቅቱ 24 ዓመት ወጣት ነበሩ። ሀገርን የወረረውን የኢጣሊያን ጦር ለመውጋት ቆርጠው ተነሱ። በወቅቱ 200 እስከ 300 ያህል ጦር በስራቸው ሊያሰባስቡ ቻሉ። በወቅቱም የአካባቢውን ሕዝብ ሰብስበው የሚከተለውን ንግግር አደረጉ፡-
እኔ የዘለቀ ልጅ የምታዩትን የአባቴን አንድ ጥይት ጐራሽ ናስማስር ጠብመንጃዬን ይቼ በሀገር በረሃ የአላዩን ወንዝ ይዤ፣ የአለቱን ድንጋይ ተንተርሼ፣ አሸዋውን ለብሼ ዋሻውንና ተራራውን ምሽግ አድርጌ የመጣውን ጠላት እቋቋመዋለሁ፤ እንጂ እንኳንስ እናንተ የእናቴ ልጆች እጅጉ እና አያሌው ጥለውኝ ሄደው አንድ እኔ ብቻ ብቀርም ከዓላማዬ ፍንክች አልልም። እናት ሐገሬ ኢትዮጵያ ስትደፈር ከማየት ሞቴን እመርጣለሁ። የፈራህ ልቀቀኝ! ለውድ እናት ሀገርህ መስዋዕት ለመሆን የምትፈልግ ሁሉ እኔን ተከተለኝብለው ቆራጥ የሆነውን ውሣኔያቸውን ሰጡ። በዚህን ጊዜ የኒህን ጀግና ልበ ሙሉነት የተረዱት 150 ያልበለጡ አገር ወዳጆች ሲቀሩ ሌሎች ለጠላት እየሄዱ ገቡ። ስለዚህ በላይ ዘለቀም የቀሩትን ታማኝ አሽከሮቻቸውን ይዘው አባይ ለአባይ እየተዘዋወሩ በሚዋጉበት ጊዜ አብረዋቸው ያሉት አሽከሮቻቸው በካዱት ጓደኞቻቸው ላይ እንዲህ ሲሉ የእንጉርጉሮ ግጥም ገጠሙላቸው፡-

ይህንን አንበሳ ጀግናውን ከድታችሁ
ኧረ ተምን ግዜው ለጣሊያን ገባችሁ
በጣም ያሳዝናል ባንዳ መባላችሁ
ከከዳችሁ አይቀር ጀግናውን ከድታችሁ
እምትወዱት ጣሊያን እሱ ካዋጣችሁ
ልቅምቅም አድርጐ ከነጫጩታችሁ
እትውልድ ሀገሩ ሮም ይውሰዳችሁ።
እኛ ለአገራችን ለኢትዮጵያ ባንዲራ
እንታገላለን በጭብጥ ሸንኮራ።
አባይ ከጨረቻው ወድቀን እንደ ገሣ
አንድ ጭብጥ ጥሬ ይዘን በኪስ ቦርሣ
ይኸው አሁን አለን ሳንጠቁር ሳንከሣ።
ጥንት ባባቶቻችን ታፍራና ተከብራ
እንዴት በኛ ጊዜ ይውረራት አሞራ
ይህ ነጭ አሞራ ቢሽኮበኮብ ቢያልፍ
አንሰጥም ኢትዮጵያን ህይወታችን ቢያልፍ

  እያሉ ተስፋቸውን ባለመቁረጥ ትግላቸውን ቀጠሉ። በላይ ዘለቀ ጐጃም ውስጥ የጠላት ጦር
መቆሚያ እና መቀመጫ እንዳይኖረው በማድረግ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ውለታ ያበረከቱ ጀግና ናቸው። ለምሳሌ ለምጨን ከተባለ ቦታ በግንቦት ወር 1928 . ከኢጣሊያ ፋሽስት ጋር ገጥመው ሲዋጉ ከወገን በኩል በመጠኑ የቆሰለና የሞተ ሲኖር ከጠላት በኩል በብዛት ሞቶበት በመጠኑ ስለቆሰለበት በዚሁ ዕለት ድል አድርገዋል። ከዚህ ቀጥሎም ቀኛዝማች ሰማነባዋ የተባሉት የኢጣሊያ የባንዳ አለቃ ስለነበሩ በቂ መሣሪያ እና ወታደር ስጠኝ እና በላይ ዘለቀን ሲሆን ከነ ነፍሱ እጁን ይዤ አለበለዚያም አንገቱን ቆርጬ በሦስት ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አመጣዋለሁ፤ ለወንድነቱ እኔ አለሁ፤ ለበረሃውም እኔው ነኝ፤ በማለት ሊፈፅሙት ያልቻሉትን ተስፋ ለኢጣሊያ ፋሽስት ሰጥተው በትምክህተኝነት ፎክረው የተሰጣቸውን 500 ወታደር ይዘው በላይ ዘለቀን በመውጋት በቢቸና አውራጃ በሸበል በረንታ ወረዳ ልዩ ስሙ አባራ ጊዮርጊስ ከተባለው ቦታ እንደደረሱ በላይ ዘለቀ ያለበትን አሳዩኝ፤ እናንተ እያበላችሁ እያጠጣችሁ ነው ያጐለበታችሁት በማለት በሚስቱ እና በከብቱ ላይ በሚያሰቃዩበት ጊዜ በላይ ዘለቀም ከለምጨን ተነስተው በየረባቲ በተባለ ቦታ አድርገው ሲሄዱ ህዝቡን የሚቀሰቅስ ሽለላ አሸልለዋል።
 
ባላገር ተነሳ ያገር ልጅ ተነሳ ፈረንጅ ቀቅሎ ሳያደርግህ ማርሳ ያባትህን ጋሻ ጦርህን አንሳና ተነሳ ያገሬ ልጅ አገርህን አቅና። እንኳንስ ኢጣሊያ ቢመጣ ፈረንጅ አትሆንም ኢትዮጵያ ያለ ተወላጅ። ጥንት አባቶቻችን በጦር በጐራዴ ሲዋጉ በጋሻ ለኛ አውርሰውናል እስከመጨረሻ።
አድዋን አስታውሰው! የምኒልክን ቦታ እኛ አንበገር ከንቱ አትንገላታ። ከዚህ ቀጥሎ እኒሁ በላይ ዘለቀ ጉዟቸውን በመቀጠል ደብረወርቅ አለት ላይ ሲደርሱ የቀኛዝማች ስማ ነገዎን ፎክሮ መምጣትና የህዝቡን መሰቃየት በሰሙ ጊዜ ያለበትን ስፍራ ቦታ የሚያረጋግጥ ሰላይ ልከው እሳቸው አባይ ወርደው ደባሳ በተባለው መልካ ላይ ውለው ከቀኑ 12 ሰዓት ተነስተው ሌሊት በጨረቃ ከበው አድርገው ሲነጋ አደጋ ጥለው ቀኛዝማች ሶማ ነገዎን ገድለው፣ ከሞት የተረፉትን ጀሌዎቻቸውን በሙሉ ከነመሣሪያው ማርከው ካስቀሩ በኋላ በላይ ዘለቀ እንዲህ አሉ፡-

እናንተ ከኢጣሊያ ታዛችሁ ከአገራችሁ በመክዳት በዛው ቀን በተደረገው ጦርነት
ከሞት ተርፋችሁ የተማረካችሁ ኢትዮጵያዊ የሆናችሁ ወገኖቼ ሁሉ፣ አሁን በእኔ በኩል ምሬአችኋለሁ። እናት ሀገራችሁን የምትወዱ ተከተሉኝ። ወይም አርሳችሁ ብሉ። ነገር ግን ሁለተኛ ለጠላት ገብታችሁ ብትገኙ እኔ የዘለቀ ነገ እመጣለሁ 
በማለት መክረው አሰናበቷቸው።

በላይ ዘለቀ ሊወጋቸው የመጣውን የኢጣሊያ ጦር ከመመከት አልፈው ድልን በድል መቀናጀት ዋናው መለያቸው እየሆነ መጣ። ሁሌም አሸናፊ ሆኑ። የኢጣሊያ ጦር ሁሌም እየተሸነፈ በመሄዱ ተስፋ በመቁረጥ የበላይ ዘለቀን ባለቤት / ሸክሚቱ አለማየሁን እና የባለቤታቸውን እህት / ዘውዲቱ አለማየሁን ገድሎ ልጃቸው / የሻሽወርቅ በላይን ማርኮ ሄደ። ከዚህ በኋላም የበላይ ዘለቀ እልህም እያየለ በመምጣት ብዙ ባንዳዎችን እና የኢጣሊያ ወታደሮችን ድል አደረጉ። በመጨረሻም ጠላት ከበላይ ዘለቀ ጋር ታርቆ፣ ሠላም ፈጥሮ መኖር ፈለገና የሚከተለውን መልዕክት ላከላቸው።
ይድረስ ለልጅ በላይ ዘለቀ። ለኢጣሊያ መንግስት ብትገባ ጥቅም እንጂ ጉዳት አያገኝህም። ጐጃምን በእንደራሴነት ይሰጥሃል። ስለዚህ በሰላም ግባ የኢጣሊያ መንግስት መሀሪ ነውና በአጠቃላይ ሙሉ ምህረት ያደርግልሃል የሚል ነበር።"
በዚህ ግዜ ጀግናው በላይ ዘለቀም ይህንን የኢጣሊያ ደብዳቤ በሰሙ ጊዜ ለተፃፈው ደብዳቤ መልስ ሲፅፉ እንዲህ አሉ፡-

ይድረስ ለኢጣሊያ መንግሥት፣ ከሁሉ አስቀድሜ ሁልጊዜ ሰላም ላንተ ይሁን እያልኩ የማክበር ሰላምታዬን አቀርባለሁ። ከሰላምታዬ ቀጥዬ የምገልፅልህ ነገር ቢኖር ከኢጣሊያ መንግሥት የተፃፈልኝ ደብዳቤ ደርሶኛል። በአክብሮት ተቀብያለሁ። ተመልክቸዋለሁ። በደብዳቤው ላይ ያለውን ቁም ነገር ያዘለ ቃል ስመለከተው እጅግ በጣም የሚያስደስት ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ስለዚህ ልጄን ከመለስክልኝ ጐጃምን ያህል ሀገር በእንደራሴነት ከሰጠኸኝ ከዚህ የበለጠ ሌላ ምን እፈልጋለሁ። ስለዚህ የኢጣሊያ መንግስት የሚያምናቸውን ታማኞቹን ይላክልኝና በእነሱ አማካኝነት አገባለሁ 
 የሚል ደብዳቤ መልሰው ፃፉለት።
በዚህን ጊዜ የኢጣሊያን መንግስት የበላይ ዘለቀን ደብዳቤ እንደደረሰው ሲመለከተው አስደሳች ሆኖ ስለአገኘው በላይ ዘለቀን በእርቅ አታሎ በእጁ ለማስገባት የዘወትር ምኞቱ ስለነበር በጉጉት ይጠብቀው የነበረው ሃሳብ የተሳካ መስሎት የራሱ የፍርድ ቤት ዳኞች ሆነው በታማኝነት ሲያገለግሉት የነበሩትን፣ በኢትዮጵያዊያን ወገናቸው በአርበኛው ላይ ይሰቀል ይገረፍ እያሉ ሲፈርዱና አርበኛ ያለበትን ቦታ ሲጠቁሙና መርተው በማሳየት ይረዱ የነበሩትን ታማኞችን እነ ቀኛዝማች እጅጉ ለማንና እነ ቀኛዝማች አደራው የተባሉትን ከነ አስተርጓሚ ጭምር ሆነው በላይ ዘለቀን በእርቅ አታለውና አባብለው በእጁ እንዲያስገቡለት ላካቸው። በኢጣሊያ መንግሥትና በጀግናው በላይ ዘለቀ መካከል በእርቅ መልክ ለማስማማት የተላኩት ሽማግሌዎችም መድረስ አይቀርምና እንደ እመጫት ነብር ከሚያስፈራው ኮስትር ፊት ቀረቡ። በዚህ ግዜ ጀግናው በላይ ዘለቀም ከፊታቸው ለተሰለፈው ጀግና አርበኛ እንዲህ ሲሉ ስለ እንግዶቹ የሚከተለውን ንግግር አደረጉ።
ጐበዝ ያገሬ ጀግና ሆይ፣ አንድ ግዜ አዳምጠኝ፤ እነዚህ እኔንና የኢጣሊያን መንግስት ለማስታረቅ የመጡ እነ ቀኛዝማች እጅጉ ለማ የተባሉት ሐገራቸውን ከድተው እዚሁ እላይዋ ላይ ሆነው ለኢጣሊያ ፋሽስት ለማያውቁት ለማይወለዱት፣ ለማይመሳሰላቸው በገንዘብ፣ በጊዜያዊ ጥቅም በመደለል ለጠላት መሣሪያ በመሆን በሐቅና በእውነት ለውድ እናት ሀገራቸው የሚዋደቁትን ንፁህ ኢትዮጵያዊያንን ሲያሰቅሉ፣ ሲያሳስሩ፣ ሲያንገላቱና ሲያስረሽኑ ከመቆየታቸው በላይ አሁን እኔንም በዕርቅ መልክ አስገብተው ለማስረሸንና አገሪቱ ተከላካይ ልጅ እንዳይኖራት የሚጥሩ ናቸው። ስለዚህ ምን ውሣኔ ማግኘት እንደሚገባቸው ጀግናው አርበኛ ሃሳብህን ስጥበት 
 ሲሉ ተናገሩ።
በዚህ ጊዜ ጀግናው አርበኛም የመሪውን አነጋገር በጥሞና ካዳመጠ በኋላ እንደዚህ ያለውን ያገር ነቀርሳዎች ጊዜና ፋታ ሳይሰጡ አሁኑኑ ረሽኖ ማለትም በሽጉጥ ግንባር ግንባሩን ብሎ ከዛፍ ላይ ጠቅሎ የአሞራና የንፋስ መጫወቻ ማድረግ ነው ብሎ በአንድ ድምፅ ወሰነ።
በዚህ ጊዜ በአስታራቂነት የመጡት እነ ቀኛዝማች እጅጉ ለማ አትፍረድ ይፈረድብሃል እንደተባለው ሁሉ እነሱ በሌላ ሲፈርዱ ኖረው በእነሱ ላይ ይግባኝ የሌለው የአርበኛ ፍርድ በማግኘት ፅዋው ስለደረሳቸው በጥይት ተረሽነው በዛፍ ላይ ተሰቀሉ። ከዚያም በኋላ ጀግናው በላይ ዘለቀም እንዲህ የሚል ደብዳቤ ለኢጣሊያ መንግሥት ፃፈ፡-
ይድረስ ለኢጣሊያ መንግሥት፤ ሰላም ለአንተ ይሁን፤ የላክልኝን እንግዶች እነ ቀኛዝማች እጅጉ ለማን በአክብሮት ተቀብዬ በማስተናገድ ሥፍራ ወይም ቦታ ሰጥቻቸዋለሁ። ላንተ ግን ትርጁማን (አስተርጓሚ) ብለህ የላከውን ሌላ ቦታ ስትልክ እንዳይቸግርህ ልኬልሃለሁ። ልጅህን እመልስልሃለሁ ለምትለው ለአንድ ልጅ ብዬ እናት ሀገሬን ኢትዮጵያን ከድቼ ከአንተ ጋር በእርቅ መልክ አልደራደርም። ከዛሬ ጀምረህ በእኔ በኩል ያለውን ምኞትህን አንሳ። እኔን ፈልገህ ማጥፋት እንጂ አንዲት ልጅ ወስዶ ማስጨነቅና ማጉላላት ደስ የሚልህ ከሆነ እንደፈለክ አድርጋት። ሲሆን ለሷም የፈጠራት አምላክ እግዚአብሔር ፍቃዱ ከሆነ ከአንተው እጅ ላመጣት እችል ይሆናል። ጐጃምን በእንደራሴነት ልስጥህ ለምትለው አንተ የሰው ሀገር ሰው ከምትሰጠኝ እኔው ሀገሬን በሥሬ አድርጌ አስተዳድረው የለም ወይ? ስለዚህ የፖለቲካ ወሬህን ከምትነዛና የኢትዮጵያን አርበኛ እየቆማመጠ ለአሞራ በመስጠት በየዱር ገደሉ ወድቀህ ከመቅረት በመጣህበት መንገድ አገርህ ከመግባት በስተቀር አማራጭ የሌለህ መሆንህን በዚህ አጋጣሚ ልነግርህ እወዳለሁ 
 ሲሉ በላይ ዘለቀ ለኢጣሊያ መንግሥት ደብዳቤ ልከዋል።
በመጨረሻም የተማረከችውን ልጃቸውን የሻሽወርቅን እንደገና ተዋግተው ከኢጣሊያኖች እጅ ከነህይወቷ ለመማረክ ችለዋል። በአጠቃላይ በላይ ዘለቀ በአምስቱ ዓመት የነፃነት ተጋድሎ ውስጥ ከፊት የሚሰለፉ ታላቅ አርበኛ ናቸው። ታዲያ የመጨረሻው የሕይወት ፍፃሜያቸው ደግሞ ከወንድማቸው ከእጅጉ ዘለቀ ጋር በስቅላት እንዲቀጡ ተደርጓል። ቸር እንሰንብት።__
****************************************************************************
ምንጭ፡--ሰንደቅ(በጥበቡ በለጠ) 9 ዓመት ቁጥር 452 ረቡዕ ሚያዝያ 29 200 ,.


ማሞ ካቻ (አቶ ማሞ ይንበርብሩ)

  አቶ ማሞ ይንበርብሩ (ማሞ ካቻ) እስቲ እናስታውሳቸው፣ ተቀብሮ እንዳይቀር አኩሪ ታሪካቸው  (ደረጀ መላኩ)   አቶቢሲ ማሞ ካቻ የት ትሄዳለህ? ገብረ ጉራቻ… ታዳጊው ማሞ ይንበርበሩ ገና በጨቅላ እድሜው አባቱ አቶ...