“ኦሮማይ” እና በዓሉ ግርማ
ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ ****************** ኦሮማይ ከልቡ መጽሐፍ ነው፡፡ በአማርኛ ልብ-ወለድ መጻሕፍት (Novel) ታሪክ በጣም አነጋጋሪውና አከራካሪው መጽሐፍ ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ የህዝብ ፍቅር ካልተነፈጋቸው ጥቂት መጻሕፍት አንዱም ነው፡፡ በህይወቴ ብዙ ጊዜ እየደጋገምኩ ካነበብኳቸው መጻሕፍት መካከልም በመጀመሪያው ረድፍ ይሰለፋል፡፡ ይሁንና ሰዎች ለዚህ መጽሐፍ ያላቸው አድናቆት እንደየ አመለካከታቸው ይለያያል፡፡ መጽሐፉ የብዙዎቹን አትኩሮት የሳበው ታሪኩ እውነት ነው ስለተባለ እና በመጽሐፉ ሳቢያም የደራሲው ህይወት ለአደጋ በመጋለጡ ይመስለኛል፡፡ ከመጽሐፉ ዐቢይ ገጸ-ባህሪያት አንዱ የሆኑት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ “የደም እምባ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ተመሳሳይ እይታ አንጸባርቀዋል፤ እንደ ሻለቃ ዳዊት አባባል ኦሮማይ ባይታገድ ኖሮ ተወዳጅነቱ ይሄን ያህል አይገዝፍ ነበር፡፡ ሆኖም እኔ በዚህ አባባል አልስማማም፡፡ ደራሲው ባይሞት እና ታሪኩ እውነተኛ ባይሆን እንኳ “ኦሮማይ” ተደናቂ የመሆንን እድል አያጣም ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህም በርካታ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ “ኦሮማይ” በቅድሚያ ቀልብን የሚስበው በአጻጻፍ ብሂሉ ነው፡፡ ደራሲው ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው አጫጭር ዐረፍተ ነገሮችን ይጠቀማል፡፡ ይህም አንባቢው የመጽሐፉን የትረካ ቅደም ተከተል ሳይስት ድርሰቱን ያለድካም እንዲያጣጥም ያግዘዋል፡፡ ደራሲው ጠጣር ሃሳቦችን በቀላሉ ይዘረዝራል፡፡ የዘመኑ መንግሥት አሰራርን ለተደራሲው በሚገባው ቋንቋ ቀለል አድርጎ ያስረዳዋል፡፡ በሌላ በኩል መጽሐፉ ኪናዊ ውበቱን እንዳይስት ደራሲው በእጅጉ ተጠቧል፡፡ ዘይቤአዊ አባባሎችን ከዘመኑ የአነጋገር ፋሽን ጋር እየቀላቀለ አንባቢውን ያዝናናዋል፡፡ በ...