(በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሐኪም)
**************************************
በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መካከል በኖረው ታሪክ መቸም ቢሆን በማይዘነጋው የመቅደላው ግብግብ በወራሪው ወታደሮች ሳይቀር በሚገባ የተወደሰው የመይሳውን የክብር አሟሟት ባስገኘልን ልዕልና ፋንታ ከዚሕ አስደናቂ ታሪክ ጀርባ በደንብ ያልተነገሩ ብዙ እውነቶች በመኖራቸው አቅም በፈቀደ ታሪካችንን ከያለበት እያሳደድን ማቅረባችንን ስንቀጥል ክብር ይሰማናል….በዚሕ የአጭር አጭር ወግ ሁልጊዜም ቢሆን በቁጭት ከሚያንገበግበን የልዑል ዓለማየሁ ስደትና ሞት ጋር የሚዛመድ የአንድ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ግለ ታሪክ በወፍ በረር ልንቃኝ እድል ቀናን………..በአጼ ቴዎድሮስ የመጨሻዎቹ የሥልጣን ዓመታት በውስጥ ፖለቲካ ምክንያት በመቅደላ አምባ ለእስር የሚጋዙ በርካቶች ነበሩ….ከእነዚሕም መካከል የዛሬው ባለታሪካችን እናትና አባት ነጋድራስ እሸቴና ወ/ሮ ደስታ ወልደማርያም ይገኙበታል…..በ1857 ዓ/ም በጎንደር ከተማ የተወለዱት ወርቅነሕ ገና የሦስት ዓመት ጨቅላ ሳሉ ከወላጆቻቸው ጋር በመቅደላ አምባ ለእስር መደረጋቸው ምን አልባትም የወደፊቱን እጣ ፈንታቸውን ያደላደለ አጋጣሚ መፍጠሩ አልቀረም……በ1860 ዓ/ም የእንግሊዝ ጦር መቅደላን ሲይዝ በተፈጠረው እረብሻ የሞተው ሞቶ የተቀረው እግሬ አውጪኝ ሲል ከተገኙት ሕጻናት መካከል የአጼ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል ዓለማየሁና ሕጻን ወርቅነሕ በእንግሊዝ ወታደሮች ተማርከው ከወራሪው ጦር ጋር ጉዞ ጀመሩ………ከባሕር ወደብ ሲደርሱ ልኡል ዓለማየሁና ሕጻን ወርቅነሕ ሊለያዩ ግድ ሆነ....... ሮበርት ናፔር ልዑል ዓለማየሁን ይዞ ወደ እንግሊዝ ሲያቀና ሕጻን ወርቅነህ ግን ከኮሌኔል ቻርለስ ቻምበርሊን ጋር በመሆን በወቅቱ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ወደ ነበረችው ሕንድ ተጉዋዙ………
ሕጻን ወርቅነሕ በሕንድ አገር ለአራት ዓመት እንደተቀመጡ አሰዳጊያቸው ቻርለስ በሞት ስለተለዩ ኮለኔል ማርቲን የተባለው ሰው ተቀብሎ ከአንድ የሚሽን ትምህርት ቤት ገብተው ትምሕርት እንዲቀጥሉ አደረገ…ብሩሕ አእምሮ የነበራቸው ወርቅነሕ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ፑጃብ በምትባለው ከተማ ተከታትለው ሲጨርሱ ለዩኒቨርሲቲ የሚያበቃ ውጤት ስለበራቸው በፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ለማጥናት ተመዘገቡ…ከዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ጎበዝ ተማሪ እንደነበሩ የሚነገርላቸው እኝህ ሰው የሕክምና ትምህርታቸውን በሚገባ አጠናቀው ከተመረቁ በዛው በህንድ አገር እረዳት የቀዶ ጥገና ሀኪም በመሆን ለሁለት ዓመት አገለገሉ…..በሕንድ የሁለት ዓመት አገልግሎት ከሰጡ በኋላ ከፍተኛ የህክምና ትምህርት ለመከታታል እ.ኤ.አ በ1889 ዓ/ም ወደ እንግሊዝ አቀኑ……በዛም በኤደንብራና በግላስኮው ዩኑኒቨርሲቲ ሕክምና ተምረው በቀዶ ጥገና ሙያ በታላቅ ማዕረግ ተመረቁ…….በዩኒቨርሲ ቆይታቸው ባስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤት የሀኪሞች ማሕበር ‘’የበቃ ጥቁር ሀኪም ‘’ የሚል ሽልማት የተበረከተላቸው ሀኪም ወርቅነሕ እ.ኤ.አ በ1891 በሀኪምነት ተመድበው በወቅቱ በሕንድ ግዛት ስር ስትተዳደር ወደነበረችው ወደ በርማ ተላኩ…….በርማ እያሉ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የተለያዩ ጥረቶች ሲደርጉ ቆይተው በአጼ ሚኒሊክ በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት በ1891 ዓ/ም በልጅነት የተለዪዋት አገራቸውን ለማየት በቁ ከቀሪ ዘመዶቻቸውም ጋር ተዋወቁ…….ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አገራቸው ከተመለሱ በሁዋላ የተለያዩ አገልግሎቶችን ሲሰጡ ቆይተው በ1895 ዓ/ም እንደገና ወደ እንግሊዝ የተመለሱ ሲሆን ከዛን ወዲሕ በተለያዩ ጊዜያት ወደ አገራቸው በመምጣት የተለያዩ በተግባራትን ያከናወኑ ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ በመጡበት ወቅት ከወ/ሮ ቀፀላ ወርቅ ቱሉ ጋር ትዳር የመሠረቱ ሲሆን ትዳራቸው ሰምሮ አምስት ወንዶችና ስምት ሴት ልጆችን አፍርተዋል…….
በሕንድ አገር በሕክምና ሙያቸው አንቱታን ያተረፉት እኝሕ ሰው በተለይ በበርማ ከሕክምና ዳይሬክተርነት አንስቶ እስከ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን በደረሱበት አገልግሎት ከፍተኛ ተወዳጅነትን እና ከበሬታን አትርፈዋል…..በሕንድና በበርማ ለ32 ዓመታት አገልግሎት ከሰጡ በሁዋላ በ1919 ዓ/ም ጠቅልለው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ…….ሀኪም ወርቅነሕ .ወደ አገራቸው ከተመለሱ በሁዋላ ፋሺስት ኢትዮጵያን እስከወረረበት ድረስ በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሳትፈዋል ከእነዚሕም መካከል በአዲስ አበባ የሚገኘውን የፍልውሀ ድርጅት አቋቁመዋል፣ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል፣ የየካቲት 12 ሆስፒታል(የቀድሞው ቤተሳይዳ)፣ የጅማ መንገድ እና የብርሀንና ሰላም ማተሚያቤት ሲቆሙ የበላይ ተቆጣጣሪ ሆነው ሰርተዋል፣ በ1927 ዓ/ም በአባይ ወንዝ ላይ ለሚገነባው ግድብ እርዳታ ለማሰባሰብ ወደ አሜሪካ የተጉዋዘውን ቡድን መርተዋል ፣ በ1920 ዓ/ም ለቆመው ዘመናዊ ፍርድቤት አዛዥ ተብለው በተሰጣቸው ሹመት በቅንነት አገልግለዋል፣ የጨርጨር አውራጃ ገዢ በመሆን የሰሩ ሲሆን ኢትዮጵያ በነበረባት የተማረ የሰው ኃይል እጥረት የተለያዩ ሙያ ያላቸው 21 ህንዳውያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሰሩ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል…….በ1927 በጄኒቫ የመንግስታቱ ማሕበር የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው የተላኩት ሀኪም ወርቅነሕ በዛው እያሉ ኢትዮጵያ በፋሺስት እጅ በመውደቋ ወደ እንግሊዝ በማቅናት ከንጉሱ ጋር በመሆን የተለያዩ የዲፐሎማሳዊ ሥራዎችንና በማከናወን በፋሺስት ወረራ ምክንያት ጉዳት የደረሰባት አገራቸውን ለመርዳት የሚያስችሉ ዝግጅቶችን በማደራጃት በወቅቱ ከኢትዮጵያውያንና ከኢትዮጵያ ወዳጆች ከፍተኛ እርዳታ እንዲገኝ ሚና ተጫውተዋል……በዚሕ ድርጊታቸው የተቆጣው ፋሺስት አዲስ አበባ ሲኖሩ የነበሩ የሴፍና ቢንያም የተባሉ ልጆቻቸውን ቢገሉባቸውም በአላማቸው ጸንተው ኢትዮጵያ ከፋሺስት ቀንበር ነጻ እስክትወጣ የተቻላቸውን ሁሉ አደረጉ…..ከነጻነት በሁዋላ በ1934 ዓ/ም በ77 ዓመታቸው ወደ አገራቸው የተመለሱት ሀኪም ወርቅነህ በሽምግልና ዘመናቸው ሳይቀር በሙያቸውና በሌሎች አገልግሎቶች ሁሉ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን ተወጥተዋል……..በመቅደላ አምባ ላይ የተጀመረው የኝህ ሰው አስደናቂ የሕይወት ጉዞ ጥቅምት 11 ቀን 1945 ዓ/ም ሲል በሞት ተደመደመ……አዲስ አበባ በሚገኘው የየካው ሚካኤል ቀብራቸው ሲፈጸም ብዙ ኢትዮጵውያን በቦታው ተገኝተው ሽኝት አረጉላቸው፡፡
*********************************************************************************
ምንጭ-: This Day in Ethiopian History facebook page
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ