ፓንክረስት ሞተ ይላሉ
አያፍሩም ደግሞ ይዋሻሉ፤
ታሪክን እንደነዳጅ ቆፍሮ
ለቅርስ እንደ ውርስ ተከራክሮ
ላልተወለደባት ምድር ከተወላጅ በላይ ለፍቶ
በደም ከወረሷት በላይ በፍቅር ልቧ ውስጥ ገብቶ
ከእናቱ እስከ ልጁ - ለጦቢያ ልቡን ሠውቶ
በትውልድ ማማ ላይ ቆሞ የጸናውን ጌታ
ሞቷል እያለ ይዋሻል ታሪክ የጠላ ቱማታ፡፡
ኢትዮጵያዊነት ቅኔ ነው
ብርቱ እንደ ፓንክረስት የሚነጥቀው
ሞኝ እንደ ከመዳፉ የሚቀማው፡፡
ኢትዮጵያዊነት ጸጋ ነው
ልባም እንደ ዐሉላ የሚቀባው
ሞኝ እንደ ባንዳ የሚነሣው፤
ስንቱ ከማዕዘናተ ዓለም
እንደ ኦሎምፒክ ከትሞባት
ባተወለደባት ምድር
እትብቱን አምጥቶ ሲቀብርባት
ከደጁ ሞፈር ሲቆረጥ
ጅላጅል ቆሞ አንጎላጀ
ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዶ
ሐበሻ ሳይሆን አረጀ፡፡
እንዲህ ያለው ልብ አልባ
ልባሙን ሞተ ይለዋል
በትውልድ ማማ ላይ ያለ
መቼ ልብ ሰጥቶ ይሰማዋል፡፡
ፓንክረስትማ አልሞተም
በኢትዮጵያ ልብ ይኖራል
በዐጸደ ነፍስ ሆኖ
ጠላቷ ፍግም ሲል ያያል፡፡
*********************
ለፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት
(በዲያቆን ዳንኤል ክብረት_
http://www.danielkibret.com/)
*********************
የካቲት 10 ቀን 2009 ዓ.ም.