መስከረም የወራቱ ጌታ
ሔኖክ ያሬድ << መስከረም አበባ መስከረም አበባ ፣ እንቁጣጣሽ መጣ አዲስ ዓመት ገባ ፤ መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ፣ እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ ። >> የኢትዮጵያ የወራት ሁሉ መጀመሪያ መስከረም ነው፡፡ ‹‹ ኢዮሃ አበባዬ . . . መስከረም ጠባዬ ›› ዘመን በተሞሸረ ዓመት በተቀመረ ቁጥር ሰው መልካም ምኞት የሚለዋወጥበት ሐረግ ነው፡፡ ድምፃውያንም ያቀነቅኑታል፡፡ እንግዲህ ኃያሉ ክረምት ሊያበቃ፣ መሰስ እያለ ወጥቶ ለከርሞ ሊመለስ ከመስቀል በዓል በኋላ ሁለት ሳምንት ( መስከረም 25 ቀን 2012 ዓ . ም .) ቢቀረው ነው፡፡ በመጻሕፍት እንደተጠቀሰው፣ ኢዮሃ አበባዬ የደስታ ቃል ነው፡፡ ወንዶች የደመራ ለት እየዘፈኑ ድምሩን የሚዞሩበት ያበባ ዘፈን ነው፡፡ ሰኔ ግም ብሎ፣ ያምሌን ጨለማ አልፎ፣ የነሐሴን ጎርፍ ሙላትን በእኝኝ ተሻግሮና ተንተርሶ በጠንካራው ዝናብ ( ውሃ ) ምክንያት ብቅ የምትለዋ ያደይ አበባ ናትና፤ ውሃ ያደረገውን ታምር፣ ያስበቀለውን አበባ አደያዊን ተመልከት ለማለት ‹‹ ኢዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ ›› ይባላል፡፡ ታዋቂው ደራሲ በዓሉ ግርማ ‹‹ ደራሲው ›› በተሰኘው ልቦለዱ የመስከረምን ድባብ የገለፀበት አገላለጹ አዲሱ ዓመት በመጣ ቁጥር ሁሌ የሚታወስ ነው፡፡ ‹‹ መስከረም ጠባ፡፡ የመስከረም ጮራ ዕንቁጣጣሽ ብላ ተግ አለች፡፡ ልጃገረዶች ሳዱላቸውን አሳመ...