ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ጃንሆይ ምን ተናገሩ?
ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ጃንሆይ ምን ተናገሩ?
Wednesday,
04 May 2016 /በሰንደቅ ጋዜጣ የታተመ/
በጥበቡ በለጠ
ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ታሪክ ውስጥ እጅግ የተለየች ዕለት ነች። ምክንያቱም አንድ ንጉሥ በጠላት ወታደሮች ሐገሩ ተወርራ፣ የሚያደርገው ቢያጣ ከሐገሩ ውጭ በባዕድ ሀገር ተሰድዶ፣ በመጨረሻም ከአምስት ዓመታት በኋላ በውጭም በውስጥም ድል አድርጎ ወደ ሐገሩ በመምጣት፣ የጠላቶቹን ባንዲራ አውርዶ፣ የሀገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ የሰቀለ፣ ከዚያም ለሐገሩ ሕዝብ ንግግር ያደረገባት ዕለት ፈፅሞ የተለየች ነች።
ኢጣሊያ በ1888 ዓ.ም አድዋ ላይ በግማሽ ቀን ጦርነት የውርደት ማቅ መከናነቧ ሲቆጫት ሲያንገበግባት ኖሯል። እናም ከ40 ዓመታት በኋላ በ1929 ዓ.ም ቂሟን ለመወጣት ኢትዮጵያን ወረረች። ኢትዮጵያ ደግሞ ገና የሽግግር ወቅት ላይ የነበረች በመሆኑ የተደራጀ መንግሥት እና ጦር አልነበራትም። ፋሽስት ኢጣሊያ ደግሞ አሉ የተባሉ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን መርዝ ከሚተፉ አውሮፕላኖች ጋር ይዛ ኢትዮጵያን ወረረች።
ወረራው የተደራጀ ስለነበር በቀላሉ ሊቀለበስ አልቻለም። ስለዚህ ንጉሠ ነገስቱ እዚሁ ሆነው የከፉ ነገር ከሚመጣ ወደ ውጭ ወጥተው መታገልን የዘመኑ ሹማምንቶች እንደ አማራጭ መከሩ። እናም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከመንበረ ስልጣናቸው ተነስተው ኢትዮጵያን ለቅቀው ወደ እንግሊዝ ተሰደዱ። ሀገር አልባ ሆኑ።
ኢጣሊያም የኢትዮጵያን መንግሥት ተቆጣጠረች። ሮም በደስታ ተቀጣጠለች። ኢትዮጵያዊያንን ደግሞ ለሁለት ተከፈሉ። አብዛኛው በአርበኝነት ተሰማራ። ቀሪው ደግሞ ለኢጣሊያ ፋሽስቶች ባንዳ ሆነ። አርበኞቹ ፋሽስቶችን ለመፋለም በዱር በገደሉ ተሰማሩ። ጦርነቱ በየፈፋው ይካሄድ ጀመር። ኢጣሊያ በመርዝ ጋዝ አርበኞችን መፍጀት ጀመረች። ሕጻናት፣ ሴቶችና እናቶች አረጋውያን አለቁ። በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ብቻ ከ30 ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪ ፋሽስቶች ጨፈጨፉ።
በስደት ያሉት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ደግሞ “ሐገሬን አድኑልኝ” እያሉ ከአለም መንግሥታት ጋር ይሟገታሉ። ሰሚ አጡ። ነገር ግን እንደ ሲልቪያ ፓንክረስት ያሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ከኢትዮጵያው ንጉሥ ጎን ቆሙ። ሲልቪያ ፓንክረስት እንግሊዛዊት ናት። የኢትዮጵያ በፋሽስቶች መወረር ያንገበገባት ሴት ናት። እናም ስራዋን ሙሉ በሙሉ እርግፍ አድርጋ በማቆም ከኢትዮጵያው ንጉሥ ጎን በመቆም የኢትዮጵያ አርበኛ ሆነች። New Times and Ethiopian News የተሰኘ ጋዜጣ ማሳተም ጀመረች። ጋዜጣው በየሳምንቱ ለእንግሊዝ ፓርላማ አባላት የሚበተን ነው። ቀሪው ደግሞ ለሌሎች ታላላቅ ሰዎች የሚሰጥ ነው። ጋዜጣው ኢትዮጵያ ውስጥ ፋሽስቶች እየፈፀሙ ስላሉት አሰቃቂ ግፍ የሚገልጽ ነው። እንደ እንግሊዝ ያሉ ታላላቅ መንግሥታት ይህን ግፍ እንዲቃወሙ የሚቀሰቅስ ነው። በመጨረሻም የእንግሊዝ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጎን ቆሞ ፋሽስቶችን እንዲፋለም አደረገች። ሲልቪያ ፓንክረስት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ። በኢትዮጵያ የጨለማ ዘመን ወቅት ብርሃን ሆና ከወደ እንግሊዝ የወጣች ፀሐይ ናት።
እናም ጦርነቱ ተፋፋመ። አርበኞች በየጦር አውድማው ድል በድል መሆን ጀመሩ። የእንግሊዝ ጦርም ከጎናቸው ቆመ። አምስቱ የመከራ አመታት ሊያበቃ ሆነ። ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም በሱዳን፣ በኦሜድላ አድርገው ከብዙ ሺ ሰራዊት ጋር ሆነው እየተዋጉ ወደ አዲስ አበባ መጓዝ ጀመሩ። ድል በድል እየሆኑ መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም ደብረማርቆስ ከተማ ደረሱ። በዚህ ዕለት የኢትዮጵያ አርበኞች እና እንግሊዛዊው ጀነራል ካኒግሀም አዲስ አበባን ተቆጣጠረ። ይሁን እንጂ ድሉ ድል የሚሆነው ንጉሠ ነገስቱ ሲመጡ ነው።
ደብረ ማርቆስ ላይ ለ20 ቀናት ከቆዩ በኋላ ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ተደረገ። ተአምራዊ ታሪካዊ ጉዞ ነው። የተሰደደ ንጉሥ፣ ሀገር አልባው ንጉሥ ወደ ዙፋኑ ሊመጣ ነው። ጉዞው ተደርጎ አዲስ አበባ አናት ላይ፣ እንጦጦ አናት ላይ፣ ጃንሆይ ብቅ አሉ።
ጃንሆይ የሰሌዳ ቁጥሯ HA411 በሆነች አውቶሞቢል ጠቆር ያለ ካኪ ዩኒፎርም ለብሰው፣ በደረታቸውና በትከሻቸው ለይ የማርሻል መለዮአቸውን አድርገው፣ በራሳቸው ላይ የቡሽ ባርኔጣ ደፍተው በመኪናዋ ላይ ቆመዋል።
አምስት ዓመት ሙሉ በዱር በገደሉ ሲፋለም የነበረው የአበሻ ጦር የተሰደደውን ንጉሡን ሊቀበል በነቂስ ወጥቷል። በመንገዱ ዳርና ዳር የኢትዮጵያ ሕዝብ ተጨናንቋል። ሕዝቡ አምስት ዓመት ሙሉ የተለየውን ንጉሥ ለማየት በደስታ ፍካት እልልታውን ያስነካዋል።
የጃንሆይ መኪና ከፊትና ከኋላ ሆነው የሚያጅቡት ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ የእንግሊዝ ጀነራሎችና መኮንኖችም ጭምር ናቸው። ሞተር ሳይክሎች፣ ብስክሌቶች፣ ዩኒፎም ያደረጉ ወታደራዊ ሰልፈኞች፣ አርበኞች. . . ውብ በሆነ ሰልፍ ከፊትና ከኋላ አጅበዋቸዋል። የራስ አበበ አራጋይ 15ሺ ጦር በጀግንነት ወኔ እያቅራራ ሰልፉን ያደምቀዋል። ምድሯ ቀውጢ ሆናለች።
ጃንሆይን ተከትለው የመጡ በርካታ ጋዜጠኞችም ይራወጣሉ። ዶክመንተሪ ፊልም ሰሪዎች ካሜራዎቻቸውን ጠምደዋል።
ጃንሆይን የያዘችው አውቶሞቢል በዚህ ሁሉ አጀብ መሐል ስትጓዝ የሐበሻ ድምፅ ከምን ግዜውም በላይ በእልልታ አስተጋባ። ፀሐዩ ንጉሥ ከነግርማ ሞገሳቸው በፈገግታ እና በደስታ መኪናዋ ላይ ሆነው ሕዝባቸውን ሰላም ይሉታል። ምላሹ ደግሞ እጥፍ ነው። ግማሹ ያለቅሳል።
“ጃንሆይ በጣሊያን ፋሽስቶች ድል ሆነው እጅግ በመረረ ሀዘን ተኮማትረው የለቀቋትን አገራቸውን በለቀቁባትና በአለቀሱባት ቀን ድል አድርገው በደስታ ባህር ተውጠው ጠላታቸውን አስለቅቀው፣ የድል አክሊል ተቀናጅተው በድል አድራጊነት በታላቅ ደስታና ናፍቆት ተሰልፎ በሚጠብቃቸው ሕዝብ መሀል አልፈው ከታላቁ ቤተ-መንግሥታቸው ደረሱ።
የእንግሊዙ የዜና ወኪል የሆነው ጋዜጠኛ ለትየር መቅረፀ ድምፁን ለአቶ ይልማ ደሬሳ ሰጣቸው። እርሳቸውም ሲናገሩ፣ “ኢጣሊያኖች እኛን ለመግደልና ንብረታችንን ለመዝረፍ የዛሬ አምስት አመት ከከተማችን በገቡበት ዕለት በእግዚአብሔር ትክክለኛ ዳኝነትና በእንግሊዞች አጋዥነት ዛሬ ንጉሠ ነገስታችን ተመልሰው ከመናገሻ ከተማቸው ገብተዋል” አሉ።
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ንጉሠ ነገስት ዘኢትዮጵያ ስዩመ እግዚአብሔር፣ በዚህች የቀኖች ሁሉ ድንቅ ቀን፣ ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በ11 ሰዓት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በአርበኞች ብርታትና መስዋዕትነት የጣሊያን ባንዲራ አውርደው የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ሰቀሉ። አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩ ቀስተ ደመና ሰማይ ላይ ተውለበለበ። የሀበሾች የነፃነት ቀን ነው አለ። ከዚያም ጃንሆይ፣ “የሰማይ መላዕክት የምድር ሰራዊት” በሚል ርዕሰ የፃፉትን ንግግር ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሰሙ። የንግግሩ ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው።
ኢትዮጵያ ነፃ የወጣች ቀን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ያደረጉት ንግግር
ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም
የሰማይ መላዕክ የምድር ሠራዊት ሊያስቡት እና ሊያውቁት ይቻላቸው ባልነበረ፤ በዚህ በዛሬ ቀን ቸር እግዚአብሔር በመካከላችሁ ለመገኘት ስላበቃኝ በሰው አፍ የሚነገር ምስጋና የሚበቃ አይደለም። ከማናቸውም አስቀድሞ ለሁላችሁ ልነግራችሁ እና ልትረዱት የምፈልገው ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ ያዲስ ታሪክ ዘመን መክፈቻ መሆኑን ነው። በዚህም በአዲስ ዘመን ሁላችን መፈፀም ያለብን አዲስ ሥራ ይጀመራል።
በኢትዮጵያ ላይ በአለፉት ዘመናት የደረሰባትን መከራ ለማስታወስ ስንፈልግ ከዚህ ጋር የተያያዘውን ታሪኳን ብቻ በአጭር እንናገራለን። ከብዙህ ሺህ ዓመት የበለጠ ነፃነቷን ጠብቃ የምትኖር ኢትዮጵያ ኢጣሊያ ከጥንት ጀምሮ በነበራት አጥቂነት የኢትዮጵያን ነፃነት ለማጥፋት ስለ ተነሣች በ1888 ዓ.ም በአድዋ ላይ ጀግኖችዋ ጦርነት አድርገው ነፃነትዋን አዳነች። በአድዋ ላይ ለተደረገው ጦርነት ምክንያት የሆነው የውጫሌ ውል ብቻ አይደለም። ነገር ግን ከዚህ በፊት ኢትዮጵያን ለመግዛት ኢጣሊያ የነበራት ያላቋረጠ ምኞት ሲጠብቅ የነበረውን ምክንያት ያገኘ መስሎት ነበር። ኢጣሊያ በአድዋ ድል ከሆነች በኋላ እውነት ለምን ድል አደረገኝ በማለት በኢትዮጵያ ላይ በአፍ ወዳጅ መስላ ስታዘጋጀው የነበረውን ምንም የአውሮጳ ያለፈው ታላቁ ጦርነት ቢያቋርጣት በአለፉት ዘመናት ገልጣለች።
ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ የአጥቂነት ጦርነት ባደረገች ጊዜ ምንም እንኳን በጦር መሣሪያ ተወዳዳሪ አለመሆናችንን ብናውቀው በግፍ አገራችንን ለመንጠቅ የመጣብንን ጠላት መከላከል የተገባን ሥራ ስለሆነ በነበረን አቅም ተከላከልን። የዓለም ሕግ በከለከለውም መሣሪያ በጋዝ ጭስ ህዝባችንን የምትጨርስብን ቢሆን ወደ አለም መንግሥታት ለማስማትና ፍርድ ለመቀበል ሔድን። ነገር ግን ኢጣሊያ ያነሣችው ጠብ በአለም ላይ ሁሉ የሚዘረጋ ስለሆነ አለምን አሁን ከደረሰባት ጥፋት ለማዳን ለመንግስት መሪነት የተቀበሉ ሁሉ የሚጣጣሩበት ዘመን ስለነበረ ይህ እሣት እንዳይቃጠል በአለም ስምምነት እንዲገኝ ሲደክሙበት ቆዩ። በዚህ ዘመን የልብ ወዳጃችን የሆነችው ታላቂቱ ብሪታኒያ በመልካም ወዳጅነት ተቀብላን ቆየች። በዚያም ያለ ፍርድና ያለ ርሕራሄ በከንቱ ደማቸው በኢጣሊያ እጅ የሚፈሰውን ያገሬን ሰዎችና በከንቱ የሚቃጠሉትን አድባራትና ቤተ-ክርስትያናት በሰው አገር ተሰደው ባገራቸውም ላይ በዱር በገደልና በጫካ መከራና ስቃይ ያዩ የነበሩትን በአሳብ ሣንለያቸው በሥራ ቆየን። በነዚህ አመታት ውስጥ ኢጣሊያ በጭካኔ የፈጃቻቸው ወጣቶችና ሴቶች ካሕናትና መነኮሳት ስንት ናቸው? በ1929 ዓ.ም የየካቲት ሚካኤል እለት በአዲሰ አበባ ከተማ ብቻ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በሦስት ቀን ውስጥ ማለቃቸውን ታውቃላችሁ። በአካፋ እና በዶማ በቤታቸው ውስጥ እንዳሉ ከሕፃናት ልጆቻቸው ጋራ በእሣት የተቃጠሉት፣ ታስረውም በረሃብ እና በውሃ ጥም ያለቁት ደማቸውና አጥንታቸው አቤቱታውን ሲያቀርብ ቆየ። ይህ እንደዚህ ያለው የአረመኔና የጨካኝነት ሥራ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይሆን የባሰውን በቀሩት በሌሎች በኢትዮጵያ አውራጃዎች ውስጥ ሲሠራ እንደነበረ ማንም የሚያውቀው ነው። ተይዞ ያልተደበደበ ያልተረገጠና ያልተዋረደ ያልታሰረ አይገኝም።
አሁን በፊታችን ወዳለው ወደ አዲሱ ታሪክ እንተላለፋለን። የዛሬ አምስት አመት ልክ በዛሬዩቱ ቀን የፋሽስት ወታደር ከዋናው ከተማችን ገባ። ቀጥሎም ሙሶሊኒ በኛ አገር በኢትዮጵያ ውስጥ የሮማን ኢምፓየር አቁሜያለሁ ብሎ ለአለም አስታወቀ። አቀናሁላችሁ ብሎ ያስታወቀውም አገር ለዘላለም በጁ የሚኖር በመስሎት አምኖ ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀግንነት በታሪክ የታወቀ ነው። ነገር ግን ለሕዝባችን የሚያስፈልገውን የዘመኑን መሣሪያ የምናገባበት ጠረፍ ባለመኖሩ ምክንያት ለማግኝት ሳይቻለን ቀረ። ሙሶሎኒ በሠራው ሥራ 52 መንግሥታት ፈረዱበት። እርሱ ግን ይሕንን የግፍ ሥራውን ተመካበት። ፍርዳቸውን ከምንም አልቆጠረውም። የአለፉት አምስት አመታት ለእናንተ ለሕዝቦቼ የጨለማ ጊዜያቶች ነበሩ። እናንተ ግን ተስፋ ሳትቆርጡ ጥቂት በጥቂት እየጀመራችሁ በኢትዮጵያ ኮረብቶች ላይ ተሰማራችሁ። በነዚህ አምስት አመታት እናንተ የኢትዮጵያ አርበኞች ማናቸውንም መከራና ጭንቀት ችላችሁ ነፃነታችሁን ስለ ጠበቃችሁ ወደ ተሰማራችሁባቸው ተራሮች ለመምጣት ጠላታችን ከቶ ሊደፍር አልቻለም። ምንም እንኳን አገሩን ለማቅናት ባይቻል የያዘውን አሰለጥናለሁ በማለት ብዙ ሺ ሚሊዮን ሊሬ አፈሰሰ። ይህን ሁሉ ገንዘብ በማውጣቱ የታጠቀውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁኔታ ከፍ ለማድረግና ወይም የሰራውን ግፍ ለማሻሻል አልነበረም። ነገር ግን በቅድስት አገራችን በኢትዮጵያ የፋሽስት ኰሎኒ ለማቆምና እሱ እንዳሰበው የጭካኔ አገዛዝ ለመትከል ነበር። የኢትዮጵያን ዘር ለመጨረስ ተጣጣረ እንጂ ምንም ለአንድ ነፃ መንግሥት ከባድ ቀንበር ሆኖ የሚቆጠር ቢሆን የማንዳ ወይም የኘሮቴክትራ አስተዳደር እንኳ አላሰበላትም።
ነገር ግን ይህ በብዙ ሺ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብና የተዘጋጀው የጦር መሣሪያ ሁሉ ሙሶሊኒ ላሠበው መንገድ መዋሉ ቀርቶ በፍፁም ላላሠበው ጉዳይ ሆነ። ኢጣሊያ ድል ከሆነችው ከፈረንሣይ ላይ የተቻላትን ያህል ለመንጠቅ አስባ ጦርነት ለማድረግ መቁረጧን በገለጠች ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ያጓዘችው ሰው፣ የላከችው ገንዘብና መሣሪያ ከልክ ያለፈ ነበር። የሰበሰበችው ደንበኛ ጦር ቁጥር ከ150 ሺ አያንስም። የተከበብኩ እንደሆነም ብላ የብዙ አመት ስንቅ አከማችታ ነበር። በዚሁ ባዘጋጀችው የጦር መሣሪያ በመተማመን ማንም ሊያሸንፈኝ አይችልም ብላ ስለተመካች የፋሽስት መንግሥት የቶታሊታሪያን አገዛዝ ባገራችን ውስጥ ለመትከል ጀምሮ ነበር። ነገር ግን የፋሽስት መንግሥት ያላሰበው ነገር መጣ። ለዛሬው ዘመን ጦርነት ዋና አስፈላጊ የሆነው የተዋጊነት መንፈስ በናንተ ተገለጠ።
ጀግንነትና ርሕራሔ ያለው የአንድ አገር ሕዝብ ከመሆናችሁ ጋር እርስ በርሳችሁ በመረዳዳታችሁና የጦር ዕቅድ በማወቃችሁ በመሣሪያና በጦር ሠራዊት ከናንተ እጅግ ከፍ ያለውን ጠላት ለማጥፋት በቃችሁ።
ለሰው ልጅ የነፃነት መብት ሲሉ በሌላ ክፍል ይዋጉ የነበሩት የእንግሊዝ ወታደሮች ኢትዮጵያን ለመርዳትና ነፃ ለማውጣት እስኪዘጋጁና እስኪታጠቁ ድረስ ጊዜ አስፈልጓቸው ነበር። የኢትዮጵያ አርበኞች ግን በመላው ኢትዮጵያ መገናኛ መንገዱን እየቆረጣችሁ ጠላታችንን እያስጨነቃችሁ ከየምሽጉ እንዳይወጣ አደረጋችሁት። ምንም እንኳ የተማመነበት ወታደር ቁጥሩ እጅግ ብዙ ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ እሱንና አገዛዙን ከዳር እስከ ዳር እንደ ጠላው በቶሎ ተረድቶ ይህን በመሰለ አገርና ሕዝብ መካከል መኖር የማይቻለው መሆኑ ታወቀው። እንደ ልማዱም የመርዝ ጋዝ ቦምቡን እየጣለ የአረመኔነትና የጭካኔ ሥራውን እየሠራ ውስጡ በመነመነ በላይነት እኖራለሁ ብሎ ለማሰብ የማይቻል ሆነበት። በያለበት ከቦ የያዘው ወታደር ከርሱ የበለጠ ኃይለኛ ባላጋራ መሆኑን ተረዳው። ይህንንም ባላጋራውን ለመግጠም ያቺኑ ተርፉ የነበረችውን ድፍረትና ገንዘቡን ሁሉ አጠፋ። ከዚህ በኃላ በኢትዮጵያ የምጠጋበት ደህና ቦታ አገኝ እንደሆነ በማለት ሞከረ። ነገር ገን አንድም የሚጠጋበት ቦታ አላገኝም።
ጊዜው ሲደርስ የቃል ኪዳን ረዳታችን ታላቁ የእንግሊዝ መንግሥት ጠላታችንን በሚገባ ለመውጋት ተደራጀ። እኔም ይሕን እንዳውቅሁ ወታደሮቼን ይዤ በምዕራብ በኩል ከሚዋሰን እሩቅ ከሆነው አገር ከሱዳን ተነስቼ ወደ ማህል ጐጃም ገባሁ። ጠላታችን በጐጃም መሬት ብርቱ ምሽጐችና ኃይለኞች ወታደሮች' አውሮኘላኖችና መድፎችም የነበሩት የኛንና የጠላታችንን ወታደሮች ቁጥር ስንገምተው የአብላጫው ከፍተኛነት የኛ አንድ የርሱ 20 ይሆን ነበር። ከዚህ በቀር ደግሞ እንደ ፈቃዳችን የምናዝዝበት መድፍና አውሮኘላን አልነበረንም። የእኔ በአርበኞቹ መካከል መገኘት ብቻ ብዙ ሺ ሰው በአንድ ጊዜ ሣበ። የጠላታችንም ፍርሃቱና መጨነቁ በዚያው መጠን እየበዛ ሔደ። ወታደሮቼ እየገሰገሱ የጠላታችንን መገናኛ መንገድ እየቆረጡ ወታደሮቹንም እያባረሩ ከአባይ ወዲያ ማዶ አባርረው ወደ ሸዋ እና ወደ ቤጌምድር ሲከታተሉ ሣሉ የእንግሊዝ ኢምፔሪያል ወታደሮች ማንም ሊተካከለው በማይችል ሁኔታ እየገሠገሡ ዋና ከተማችንን መያዛቸውንና በስተሰሜን በኩል ወደ ደሴ፣ ከበስተ ደቡብ በኩል ወደ ጅማ፣ የመግፋታቸውን ደስ የሚያሰኝ ወሬ ሰማሁ። እንደዚሁም ከሱዳን የዘመቱት ወታደሮች እጅግ በሚያስደንቅ ኃይል የከረንን ምሽግ አፍርሰው የጠላትን ጦር በፍፁም ድል አደረጉት። እኔም ወደ ዋናው ከተማዬ የምገባበት ጊዜ ስለደረሰ ጠላታችንን ለማባረር በየቦታው ተበታትነው የነበሩትን ወታደሮቼን ሰብስቤ ዛሬ በዋናው ከተማዬ ተገኘሁ። ወታደሮቼን እየመራሁ በመንገዴ ላይ የነበረው ጠላት ድል እየሆነ እስከዚህ በመዳረስና የጋራ ጠላታችንን ኃይል በመስበሬ ደስታዬ ሳይቋረጥ ይመነጫል። የፋሽት መንግሥት ጥሎት በሸሸው ቤተ-መንግሥቴ ውስጥ ዛሬ በመካከላችሁ በመገኘቴ ሁሉን ቻይ ለሆነ አምላክ የማቀርብለት የልብ ምስጋና ሊወሰን አይችልም።
ያገሬ ኢትዮጵያ ሕዝብ፡-
ዛሬ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ እልል እያለች ምስጋናዋን የምታቀርብበት፣ ደስታዋን ለልጆችዋ የምትገልፅበት ቀን ነው። የኢትዮጵያ ልጆች ከባዕድ የመከራ ቀንበርና ከዘላለም ባርነት ነፃ የወጡበት ቀንና እኛም አምስት አመት ሙሉ ተለይተነው ከነበረው ከምንወደውና ከመንናፍቀው ሕዝባችን ጋር ለመቀላቀል የበቃንበት ቀን ስለሆነ ይህ ቀን የተከበረና የተቀደሰ፣ በያመቱም ታላቁ የኢትዮጵያ በአል የሚውልበት ነው። በዚህም ቀን ለሚወለዱት ላገራቸው ነፃነት፣ ለንጉሠ ነገስታቸውና ለሰንደቅ አላማቸው ክብር ከአባቶቻቸው የተላለፈውን ጥብቅ አደራ አናስወስድም በማለት መስዋዕት ሆነው ደማቸውን ያፈሠሡትን፣ አጥነታቸውን የከሰከሡትን ጀግኖቻችንን እናስታውሣለን። ለነዚህም ጀግኖቻችን የኢትዮጵያ ታሪክ ምስክር ይሆናል።
ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ በዝርዝር ተነግረውና ተቆጥረው የማያለቁ ያገኘናቸው መከራና ሥቃይ ትምሕርት ሆነውና ሠራተኛነት፣ አንድነት፣ ሕብረትና ፍቅር በልባችሁ ተፅፈው ለምናስበው ለኢትዮጵያ ጉዳይ ረዳቶች ለመሆን ዋና ትምሕርት የሚሰጣችሁ ነው። ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ከእንግዲህ ወዲያ የማትነጣጠሉ በሕግ ፊት ትክክለኛነትና ነፃነት ያላችሁ ሕዝቦች እንድትሆኑ እንፈልጋለን።
አገር የሚለማበትን' ሕዝብ የሚበለፅግበትን' እርሻ' ንግድ' ትምሕርትና ጥበብ የሚሰፉበትን፣ የሕዝባችን ሕይወቱና ሀብቱ የሚጠበቅበትን፣ ያገር አስተዳደርም ባዲሱ ሥልጣኔ ተለውጦ ፍፁም የሚሆንበትን ይህን ለመሰለው ለምንደክምበት ሥራ አብሮ ደካሚ መሆን አለባችሁ።
ይህንን እግዚአብሔር በቸርነቱ የሠራልንን ሥራ መጀመሪያ የቃል ኪዳን ረዳታችን የእንግሊዝ መንግሥት ያረገልንን ውለታ ለመመለስ ኢምፔሪያል ትሩኘ የተባሉት ወታደሮች ወደ ሌላ የጦር ግንባር ተዛውረው የጋራ ጠላታችንን ለማጥቃት እንዲችሉ ማድረግና፣ በጦር ሠራዊትም አንድናግዝ የሚያስፈልግ ሆኖ ሲገኝ በመርዳት፣ ሁለተኛም በአገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ሐይማኖትን የሚያስከብርና የሚጠብቅ መንግሥት በማቋቋም የሕዝብንና የሕሊናን ነፃነት በመፍቀድ ለሕዝብና ለሐገር የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት ብርቱ ምኞታችንና አሣባችን ነው።
አሁን በመጨረሻው ለናንተ ለሕዝቤ የማስታውቃችሁ ዛሬ የሁላችን የደስታ ቀን መሆኑን ነው። ዛሬ ጠላታችንን ድል የመታንበት ቀን ነው። ስለዚህ በሙሉ ልባችን ሁላችን ደስ ይበለን ስንል ደስታችን በክርስቶስ መንፈስ እንጂ በሌላ አይሁን። ለክፉ ክፉ አትመልሱ። ጠላት እንደወትሮው ልማድ እስከዚህ መጨረሻ ሰዓት ድረስ ሰራው ያለ የጭካኔና የግፍ ሥራ አትሥሩ። ተጠንቀቁ። ጠላቶቻችን በእጃቸው ያለውን መሣሪያ እንዲያስረክቡና በመጡበት መንገድ ተመልሰው እንዲሔዱ እናደርጋለን። ደራጐንን የገደለ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የእኛም የባለ ቃል ኪዳን ረዳቶቻችንም የጦር ሠራዊት ባልደረባ ነውና ይህን አዲስ የተነሣውን የሰውን ልጆች የሚያስጨንቀውን እግዚአብሔርን የማያምን ጨካኝ ዘንዶ ለመቃወም እንድንችል ለዘላለም ፀንቶ በሚኖር ወዳጅነትና ዝምድና ከባለ ቃል ኪዳን ረዳቶቻችን ጋራ እንተሳሰር። እነርሡንም እንደ ዘመድና ወዳጅ ተመልክታችሁ ደግነት እና ቸርነት እንድታሳዩዋቸው አደራ እላቸኋለሁ።
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ
ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ
ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ