ልጥፎች

ከኖቬምበር, 2022 ልጥፎች በማሳየት ላይ

አማርኛ ቋንቋ ከውጪ ቋንቋዎች የተዋሳቸው ቃላት

  አማርኛ ቋንቋ ከውጪ ቋንቋዎች የተዋሳቸው ቃላት ምሳሌዎች፦ ከግሪክኛ፦ ጠረጴዛ ከአረብኛ፦ ባሩድ ከቱርክኛ፦ ሰንደቅ ከፈረንሳይኛ፦ ባቡር ከጣልኛ፦ ቡሎን ከእንግሊዝኛ፦ ኢንተርናሽናል የሀገራችን ቋንቋዎች ከውጪ ቋንቋዎች በርካታ ቃላትን ወርሰዋል፡፡ ይህም ከብሉይ ዘመን ጀምሮ ይታይ የነበረ ክስተት ነው፡፡ የመወራረሱ አድማስ ስፋቱን የጨመረው ግን በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በቀጣዮቹ አንድ መቶ ሀያ ዓመታት ውስጥ የታዩት ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ክስተቶች የሀገራችን ቋንቋዎችን ለውጪ ቋንቋዎች ተጽእኖ የበለጠ ክፍት እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል፡፡ ታዲያ ከሶስት ሺህ ከሚልቁት የውጪ ቋንቋዎች መካከል ለሀገራችን ቋንቋዎች ብዙ ቃላትን ለማውረስ የበቁት አራቱ ብቻ ናቸው፡፡ እነርሱም  ዐረብኛ፣  ፈረንሳይኛ፣  ጣሊያንኛና  እንግሊዝኛ ናቸው፡፡  የቱርክ እና የጀርመን  ቋንቋዎችም ጥቂት ቃላትን ለሀገራችን ቋንቋዎች አበርክተዋል፡፡ ***** ዐረብኛ በሀገራችን ቋንቋዎች ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር የቻለው በዋናነት የእስልምና ሀይማኖት የአምልኮና የትምህርት ቋንቋ ስለሆነ ነው፡፡ በመሆኑም ከእስልምና እምነት ጋር በተያያዘ ለአምልኮና ለትምህርት አገልግሎት ላይ የሚውሉ ቃላት በአብዛኛው ከዐረብኛ የተገኙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ መስጊድ/መስጂድ፣ ኢማም፣ ቃዲ፣ አዛን፣ መጅሊስ፣ መድረሳ ወዘተ… የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሂደት ደግሞ የዐረብኛ ቃላት በአምልኮ ውስጥ ካላቸው አስፈላጊነት አልፈው በተራው ሰው ንግግር ውስጥም ገብተዋል፡፡ ይህ ክስተት በስፋት የሚስተዋለው ግን አብላጫው ነዋሪ ህዝብ ሙስሊም በሆነባቸው እንደ ወሎ፣ ሀረርጌ፣ ባሌ፣ ጅማ፣ ሶማሊ (ኦጋዴን)፣ ቤኒሻንጉልና አፋር አካባቢዎች ነው፡...