ማሞ ካቻ (አቶ ማሞ ይንበርብሩ)
አቶ ማሞ ይንበርብሩ (ማሞ ካቻ) እስቲ እናስታውሳቸው፣ ተቀብሮ እንዳይቀር አኩሪ ታሪካቸው
(ደረጀ መላኩ)
አቶቢሲ ማሞ ካቻ
የት ትሄዳለህ? ገብረ ጉራቻ…
ታዳጊው ማሞ ይንበርበሩ ገና በጨቅላ እድሜው አባቱ አቶ ይንበርበሩ በሥራ ምክንያት ወደ ኢሊባቦር ጎሬ ሲዛወሩ አብሮ ሄደ። ብዙም ሳይቆይ አባቱ የጣልያንን ወራሪ ኃይል ለመከላከል ዘምተው፤ በማይጨው ጦርነት የተሰው ሲሆን እናቱ በህመም ምክንያት ቀደም ብለው ሞተው ስለነበር ገና በ12 ዓመት እድሜው ያለ ወላጅ ቀረ። ወላጅ አልባውን ታዳጊ፤ ለግዜው የኢትዮጵያን ሠራዊት አሸንፈው ከገቡት የጣልያን የጦር መኮንኖች አንዱ አግኝቶት ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ይዞት መጣ።
ታዳጊው ማሞ አንበርብር አዲስ አበባ በመምጣቱ የዕለት ጉርሱን የማግኘት እድሉ ቀለል አለለት። እዛው አካባቢ የሚገኝን ሻይ ቤት ተጠግቶ ብርጭቆ እያጠበና እየተላላከ በክፍያ መልክ ምግቡን እየሰጡት ኑሮውን ጀመረ።
ብልህና ፈጣን ልጅ የነበረው ማሞ አንበርብር በሻይቤቱ ሥራ ብዙም ሳይቆይ፤ በራሱ ሠርቶ ገንዘብ የሚያገኝበትን መንገድ ማሰብ ጀመረ። አስቦም ያገኘው ዘዴ፤ አራት ኩሽኔታ የተገጠመለት መቀመጫ ያለው ተሽከርካሪ ሠርቶ፤ ህጻናትን አሳፍሮ እየጎተተ ከሠይጣን ቤት (ከቴዎድሮስ አደባባይ) እስከ ቴሌኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ድረስ እያንሸራሸረ ገንዘብ ማስከፈል ነበር። ቀስ በቀስ ሳንቲሙ እየተጠራቀመ ሲመጣ አሁንም ሌላ የሕጻናት ማንሸራሸሪያ ተሽከርካሪ አዘጋጀ። ይህ ተሽከርካሪ ሳይክል ሲሆን ፔዳልም ሆነ ካቴና የሌለው አሮጌ ነበር። በሁለቱ ጎማዎች ምትክም ማሞ ራሱ ቆራርጦ የሠራቸው ተሽከርካሪዎች ተገጥመውለት አሁንም እሱን እየጎተተ ሕጻናትን በማንሸራሸር የተሻለ ገንዘብ ማግኘት ጀመረ፡፡
ይህን ማሞን ጥረት ያስተዋለ አንድ የጣልያን ጦር መኮንን ወደ ምፅዋ በሚሄድበት ጊዜ ማሞን ይዞት ሔዶ፤ ከምፅዋ ሃያ የሚሆኑ ትክክለኛ ሳይክሎችን ገዝቶ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ረዳው።
አሁን የሃያ ሳይክሎች ባለቤት የሆነው ማሞ ሳይክሎቹን እያከራየ ከበፊቱ የተሻለ ገንዘብ ማጠራቀም ጀመረ።
በዚህ ሁኔታ ገንዘቡ እያደገለት እያለ የጣልያን ጦር በተራው ተሸነፈና እንግሊዞች ተተኩ። ለውጡን ተከትሎ ጣልያኖች ኢትዮጵያን ለቅቀው ሲወጡ መኪኖቻቸውን በችኮላ እየሸጡ ነበርና ወጣቱ ማሞም አንዲት ፎርድ ፒክ አፕ በ108 ብር ገዝቶ ከአዲስ አበባ ወሊሶ እና ወልቂጤ ሕዝብ ማመላለስ ጀመረ።
ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው እንግዲህ አቶ ማሞ አንበርብር አውቶቡስ በመግዛት የሕዝብ ማመላለስ አገልግሎታቸውን ማጠናከር የቻሉት። ከዛ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ የሶስት ቀኑን መንገድ በሁለት ቀንና በአንድ ቀን ተኩል በመግባት ሕዝቡን ማስደነቅ ጀመሩ። የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የነበረው ህብረተሰብም ለጉዞ ቀዳሚ ምርጫው የአቶ ማሞ አንበርብር አውቶቡስ ሆነ።
የዚህ አስደናቂ ስራቸው ውጤት የአባታቸውን ስም አስትቶ ከስማቸው ቀጥሎ ‘ካቻ’ በሚል ቅፅል ስም እንዲጠሩ ምክንያት ሆነ። ብሎም እጅግ ታዋቂ ሊሆኑ ቻሉ። ‘ካቻ’ ማለት የጣልያን ፈጣን መትረየስ ተኳሽ አውሮፕላን መጠሪያ ነበር። አሁን ተዋጊ ጀት እንደ ሚባለው።
ይህ ድርጅት ከሌሎቹ ሻል ያሉ መንገዶች እየተመረጡ ስለሚሰጡት አቶ ማሞና ሌሎቹም ግለሰቦች ለእነሱም እንዲህ አይነት መስመር እንዲሰጣቸው ከመጎትጎት አልፈው በየስማቸው ማህበር በማቋቋም የአውቶቡሳቸውንም ቁጥር በመጨመር በሁሉም መስመር ለመሳተፍ ጥረት ማድረጉን ቀጠሉ።
በዚህ ጊዜ የድርጅታቸውን ስም በታወቁበት ስም ‘ማሞ ካቻ’ ብለው ሰየሙት። ይህን ሁሉ ተግባር የፈፀሙት አቶ ማሞ ማንበብና መጻፍ እንኳን የማይችሉ ነበሩ።
አንድ ቀን ከእሳቸው ጋር ጭቅጭቅ የነበረው ሰው ሞቶ በመገኘቱ ተጠርጥረው ማስረጃ ባይገኝባቸውም አስራ አምስት አመታት ተፈርዶባቸው ወህኒ ወረዱ። በዛን በእስር ጊዜአቸው ነበር አብረው የታሰሩ ምሁራንን እየጎተጎቱ አማርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋ ማንበብ የቻሉት። እንዲሁም መደበኛ ሒሳብም መሥራት ቻሉ።
የሚመሩት የትራንስፖርት ድርጅት ያለው አስተዋፅኦ ታይቶ በእስር ጊዜአቸው ከእስር ቤት በሳምንት ሁለት ቀን እየወጡ ሥራቸውን አከናውነው እንዲመለሱ ተደርጎ ነበር። በ 1960 ዎቹ መግቢያ ላይ ከእስር ቤት ወጡ። እንግዲህ ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ነው አንድ አስደናቂ ተግባር ያከናወኑት። ነገሩ እንዲህ ነው ፦
የንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅት ንብረት ነው የሚባለው የአንበሳ አውቶቡስ ድርጅት ሰላሳ አውቶቢሶች እንዲሠሩለት ለፊያት ካምፓኒ ያዝዛል። ከሰላሳዎቹ ግማሹ ተሠርተው አዲስ አበባ ደርሰው አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ባልተጠበቀ ሁኔታ ተመሳሳይ ችግር ያስተናግዱ ጀመር። ሕዝብን ጭነው በሚጓዙ ጊዜ የፊት ጎማቸው እየፈነዳ መገልበጥ ወይም ከመስመር እየወጡ መጋጨት ተግባራቸው ሆነ። ገናም አምስት እና ስድስቱ ተመሳሳይ አደጋ እንደደረሰባቸው፤ አቶ ማሞ ጭንቅላት ውስጥ “ለምን ይሆን?” የሚል ጥያቄ ተነሳ።
አንድ ቀን ማሞ ካቻ ከሻሸመኔ ወደ አዲስ አበባ እየነዱ ሳለ፤ አንድ አውቶቡስ ጥሩምባ ነፍቶ አለፋቸው። ይህ ጥሩምባ ነፍቶ ያለፈው አውቶቡስ አዲስ ከመጡት አንዱ በመሆኑ የማሞ ካቻን ትኩረት ሳበ። እናም ‘ለምን ይሆን?’ የሚለው ጭንቅላታቸው ውስጥ ያለው ጥያቄ ምናልባት መልሱ ቢገኝለት ብለው በማሰባቸው፤ መኪናቸውን አዙረው አውቶቢሱን መከተል ያዙ። አውቶቢሱ ሻሸመኔ ደርሶ ወደ ጎባ መንገድ ታጠፈ ተከተሉት፣ ዶዶላን አለፈ፣ ማሞ ካቻም አለፉ አውቶቢሱ ዶዶላን አልፎ ሲገሠግስ ድንገት ቁልቁለት ላይ የፊቱ ጎማ ፈነዳና ከመንገድ ወጥቶ ከአንድ ቋጥኝ ጋር ተጋጭቶ ቆመ።
ማሞ ካቻም መኪናቸውን አቁመው፤ ዱብ! ብለው ወረዱና ወደ አውቶቢሱ ተጠግተው ሁኔታውን መመርመር ጀመሩ፤ እናም ችግሩን ደረሱበት።
ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ ጊዜ ሳያ ጠፉ ወደ ጣልያን (የፊያት ኩባንያ ወደሚገኝበት ወደ ቶሪኖ) በረሩ። እንደደረሱም በቀጥታ ወደ ኩባንያው አምርተው ፕሬዚዳንቱን እንዲያገናኟቸው ጠየቁ…..።
እንግዲህ በደምቡ መሠረት ማንኛውም ባለ ጉዳይ አንድ ባለ ሥልጣንን ለማግኘት ከፈለገ ጉዳዩን አስረድቶ በቅድሚያ ቀጠሮ ማስያዝ የግድ ነው። የቀጠሮው ቀን ሲደርስ ቀድመው ተዘጋጅተው ስለሚጠብቁት በተያዘለት ቀንና ሰዓት ተስተናግዶ ይመለሳል። ዛሬ ግን የኩባንያው እንግዳ ተቀባዮች የመጣባቸው ሰው ለየት ያለ ሆነባቸው።
እንደደረሰ ምን እንደፈለገ ጠየቁት። ማሞ ካቻም
“የኩባንያውን ፕሬዚዳንት ማግኘት እፈልጋለሁ!” ብለው መለሱ።
“ለመሆኑ ቀጠሮ ይዘው ነበር?”
“ቀጠሮ እንኳን አልያዝኩም”
“እሺ ቀጠሮ ይዘው ይመለሱና በቀጠሮው ዕለት ይምጡ!”
“በፍፁም ቀጠሮ ተቀብዬማ አልመለስም! ዛሬውኑ፤ ያውም አሁኑኑ በአስቸኳይ አገናኙኝ! ለዚህ ብዬ ነው ከኢትዮጵያ ድረስ የመጣሁት!” ብለው ድርቅ አሉ።
እንግዳ ተቀባዮቹ ይሄ ከደንቡ ውጭ፣ ያለ ቀጠሮ፣ ድንገት መጥቶ ‘ከፕሬዚዳንቱ ጋር አገናኙኝ!’ ብሎ ያስቸገረ ሰው፤ ግራ አጋባቸው። ሰውዬው ጥቁር መሆኑ ደሞ የበለጠ አነጋጋሪ ሆነ። አነጋጋሪው ወሬ እያነጋገረ ሄዶ ከእንግዳ ተቀባዮቹ አልፎ ፕሬዚዳንቱ ዘንድ ደረሰ።
… … ቀጠሮ ያልያዘ፣ ጥቁር ሰው፣ ከደምቡ ውጭ ፕሬዚዳንቱን ማግኘት ይፈልጋል!
የጥቁሩ ሰው ወሬን የሰማው ፕሬዚዳንት ነገሩን ሲሰማ፤ ሊያነጋግረው ፍቃደኛ ሆነና ማሞ ካቻ እንዲገቡ ተፈቀደላቸው። ከፕሬዚዳንቱ እንደተገናኙ በቀጥታ ወደ ጉዳያቸው የገቡት ማሞ ካቻ
“ኢትዮጵያ ለሚገኘው አንበሳ አውቶቡስ ድርጅት ሰላሳ አውቶቢሶች ለመሥራት ተስማምታችሁ እስካሁን አስራ አምስቱን ወደ ኢትዮጵያ ልካችኋል!” አሉ። ፕሬዚዳንቱም
“ትክክል ነዎት!” አለና አረጋገጠላቸው።
“ወደ ኢትዮጵያ የላካችኋቸው አውቶቡሶች የፊት ጎማቸው እየፈነዳ ሕዝቡን ለአደጋ እያጋለጡት ነው። እስካሁን አምስትና ስድስት ያህሉ ይህ ነገር ገጥሟቸዋል!”
“አዎ ትክክል ነዎት። ጉዳዩን ሰምተናል። በእኛ በኩል ችግሩን እያጠናንው ነው።”
“እኔ ግን ችግሩን ተከታትዬ ደርሼበታለሁ። ካስፈለገም በቀላሉ አስተካክለዋለሁ!”
“እርስዎ አገኘሁ ያሉትን ችግር እስቲ ይንገሩኝ?”
“ኩባንያው ሲያመርታቸው የቴክኒክ ስህተት ስለሠራ ነው።”
“እሱማ በፍፁም ሊሆን አይችልም! እዚህ ኩባንያ ውስጥ እኮ ያሉት ኢንጅነሮች በትምህርትም ሆነ በልምድ በአገሪቱ አሉ የተባሉት ናቸው!”
“ሊሆኑ ይችላል። ግን ተሳስተዋል!”
“ምኑ ላይ ነው የተሳሳቱት?”
“የአውቶቡሶቹ ሞተር ከፊት ነው ያለው!”
“አዎ”
“ሞተሩ ከፊት መሆኑ ብቻ ችግር አይሆንም ነበር፤ ግን የመንገደኞች እቃ መጫኛም የሚገኘው የአውቶቡሱ የፊት አካል ላይ ነው። ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል? ሞተሩ የራሱ ክብደት አለው። የመንገደኞች ዕቃም ተጨማሪ ክብደት ነው።
“ጭነቱ ተመጣጥኖ የመኪናው ሙሉ ጎማዎች መሸከም ሲኖርባቸው የፊተኛው ክፍል ላይ ብቻ አርፏል። ይሄ ደሞ የፊት ጎማው የመኪናውን ክብደት ሁሉ እንዲሸከም ያስገድደዋል። የፊት ጎማውን ደጋግሞ የሚያፈነዳውም ምክንያቱ ይሄ ነው!” ማሞ ካቻ በእርግጠኝነት ተናገሩ።
የማሞ ካቻ ሀሳብ ስላሳመነው ፕሬዚዳንቱ በአስቸኳይ ኢንጅነሮቹን ሰበሰበ። እናም ማሞ ካቻ የተናገሩትን ነገራቸው። እነሱም ‘በፍፁም አይደለም!’ ብለው ከማሞ ካቻ ጋር ተከራከሩ። ማሞ ካቻ የሚያነሱት መከራከሪያ በመጠኑም አሳማኝ ስለሆነባቸው፤ አንዱን መኪና ብቻ እሳቸው ባሉት መንገድ አስተካክለውት እንዲሞከር ተስማሙ።
አቶ ማሞ ወደ አዲስ አበባ እንደተመለሱ አንዱን አውቶቡስ ተረክበው ፋብሪካው የሠራውን የዕቃ መጫኛ አስነሱ። በመቀጠል በላሜራ አንድ ሜትር ከሃያ ሳ·ሜ ርዝመት ያለው ዕቃ መያዣ በአውቶቡሱ የኋላና መካከለኛው ክፍል ላይ አሠርተው አስረከቡ።
ይህ ማሞ ካቻ ያስተካከሉት መኪና ክትትል ተደረገበት። እንደሌሎቹ የፊት ጎማው ሳይፈነዳ ሕዝብ ማገልገሉን ለረጅም ጊዜ ቀጠለ።
አሁንም ሌላ አውቶቡስ እንዲያስተካክሉ ተደረገና ይሄም ተጠና። ውጤቱም እንደ መጀመሪያው አጥጋቢ ሆነ። አንድ ጥቁር፣ በትምህርቱ ያልገፋ፣ ግና ብሩህ አእምሮ ያለው ኢትዮጵያዊ፤ የጣልያንን በትምህርትም በልምድም አሉ የተባሉ መሀንዲሶችን ስህተት ነቅሶ አሳየ። ጣልያኖቹም በማሞ ካቻ ችሎታ ተደነቁ! እናም ወደ ኢትዮጵያ የገቡትን አውቶቡሶች በሙሉ እንዲያስተካክሉ ኩባንያው ፈቀደላቸው።
ሥራውን ከመጀመራቸው በፊት ግን የአንበሳ አውቶቡስ ድርጅት ጣልቃ ገባና ‘እኛ ይሄን ማስተካከል የሚችሉ በቂ ቴክኒሽያኖች ስላሉን እነሱ ያስተካክሉታል!’ ብለው ማሞ ካቻን ገሸሽ አደረጓቸው። በማሞ ካቻ ዲዛይን መሠረትም አውቶቡሶቹን በሙሉ አስተካከሏቸው።
የፊያት ኩባንያ ግን ገሸሽ አላደረጋቸውም፤ ይልቅ ለፈጠራቸው ክብር ሞዴል 220 መርሴዲስ መኪና ሸለማቸው።
ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ደርግ ከተፍ አለ። እናም ያገኘውን ሁሉ መውረስ ጀመረ። እንግዲህ ደርግ አላማዬ ያለው ፦ የሰፊውን ህዝብ ንብረት አላግባብ (በግፍ) በዝብዘው ሀብት ያከማቹትን ጨቋኝ ፊውዳሎች፤ ንብረትና ሃብት ነጥቆ ለተጨቋኙ ሰፊው ሕዝብ ጥቅም ማዋል ቢሆንም፤ ‘ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ፣ አብረህ ተወቀጥ!‘ እንዲሉ አቶ ማሞን እና አንዳንድ በራሳቸው ጥረትና ድካም ለፍተው ሕዝብን በዝብዘው ሳይሆን፤ ሕዝብን አገልግለው በጥረታቸው ሀብት ያፈሩትንም ግለሰቦች አላግባብ ንብረታቸውን ወርሶባቸው ነበር።
ወላጆቻቸውን በልጅነት እድሜ አጥተው የዕለት ጉርስ ለማግኘት ኩሽኔታ በማከራየት፤ ከታች ተነስተው በጥረታቸው ሀብት ያፈሩት ማሞ ካቻም፤ ተመሳሳይ ዕጣ ደርሷቸው ንብረታቸው ተወርሶ፤ እሳቸውም ተወርሰው በወር 2500 (ሁለት ሺህ አምስት መቶ) ብር ብቻ እየተከፈላቸው እንዲኖሩ ተደረገ።
ብርቱው ማሞ ካቻም በተቻላቸው መጠን መወረስ እንደሌለባቸው ተከራከሩ። “የእኔ ሀብት የመጣው በጥረት እንጂ ከፊውዳል አባት፣ ከአያቴ የወረስኩት አይደለም! እኔ ከድህነት ተነስቼ እዚህ ደረጃ መድረሴ፤ ደርግ ቆሜለታለሁ ያለውን ሰፊውን ሕዝብ ያስተምራል ያበረታታል! ሌላውም ጥሮ፣ ግሮ፣ ሠርቶ ለማደግ እንዲፍጨረጨር ያደርጋል! የአንድን ሰው የድካም ውጤት መውረስ ግን ምንም አይነት ትምህርት ሊሰጥ አይችልም!” እያሉ ተከራከሩ። ሰሚ ጆሮ ግን አላገኙም። የማሞ ካቻ ክርክር ፍሬ አጥቶ፤ ድርጅታቸው እንደተወረሰ በሠራተኛ ማህበር መተዳደር ቀጠለ። ሠራተኛ ማህበሩ ግን ያን ማሞ ካቻ በብቃት ሲያስተዳድሩት የነበረውን ድርጅት ማስተዳደር አቃተው።
ገቢው እያሽቆለቆለ መጣ። ቆይቶም ለሠራተኛ ደምወዝ መክፈል ተሳነው። ቢቸግረው አንድ አውቶቡስ ሸጠና ደሞዝ ከፍሎ ተገላገለ፤ አሁንም ችግር አፍጦ መጣ! ሌላ አንድ አውቶቡስ ጆሮውን አለና ችግሩን ተወጣ። ሌላችግር፣ ሌላ አውቶቡስ ሽያጭ … … እየቀጠለ፤ ለችግር መፍቻ አውቶቡስ መሸጥ የተለመደ መፍትሄ ሆነ። አራት አውቶቡሶች ከተሸጡ በኋላ ግን የደርግ መንግሥት ነገሩን አሰበበት፤ እናም ‘ያለ ባለቤቱ፣ አይነድም እሳቱ!’ እንዲሉ ማሞ ካቻን ጠርቶ ንብረታቸውን አስረከባቸው። ድርጅታቸውን መልሰው የተረከቡት ማሞ ካቻም እስከ ህይወታቸው ፍጻሜ ድረስ በብቃት ሲመሩት ቆይተዋል።
Mamokacha PLC offers a diverse portfolio of products, including coffee produce, coffee shops, restaurants, wineries, dairy products, and hotels.
Joe Mamo, D.C.’s Gas-Station Masterowns half of D.C.’s filling stations
To hear him tell it, Joe Mamo’s move from Ethiopia to North Dakota in 1981 was accidental.
Mamo’s father, Yenberber Mamo, was a public transit mogul who manufactured buses and ran the first fleet to provide service across Ethiopia. The operation made his father’s Mamo Kacha bus line a household name in the East African country.
It provided a nice life for his family. But it rendered him distinctly unpopular with the Marxist junta that ruled Ethiopia between 1974 and 1991. The elder Mamo was jailed two or three times by the regime. Some of his property was confiscated. As his son approached draft age, the patriarch looked for ways to send him overseas.
That’s how Joe, at the age of 13, found himself attending Catholic boarding school in North Dakota.
[ ከብርሃኑ አስረስ (የታህሳስ ግርግርና መዘዙ መጽሐፍ) የተወሰደ ]
ምንጭ:-- https://ethioreference.com/archives/32437
https://mamokachaplc.com/about-mamokacha/
https://washingtoncitypaper.com/article/220817/joe-mamo-dc-gas-station-master/
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ