ከመጻሕፍት ዓለም
“ዣንቶዣራ” ዓይናችንን የገለጠልን ልብወለድ!
በእርግጥ የቀዳሚ እና የተከታይ ደረጃ ለመስጠት
ያዳግተኛል፡፡ ይስማዕከ ግን በአማርኛ ልብወለድ ውስጥ ከተለመደው አብራሪነት፣ ገላጭነት፣ (ለምሳሌ በዕውቀቱ ሥዩም
እንደሚተቸው ቀኑ ደመናማ ነው ሰማዩ ብልጭ ድርግም ይላል…) እያልን ከምንወርድበት ዘልማዳዊ ጥንወት መንጭቆ
ሊያወጣን ይታትራል፡፡ የ”ዣንቶዣራ” ቁጥር አንድ እምርታ ሁነትን ከማብራራት እና ከመተረክ ይልቅ በገጸ ባሕርያት
አማካኝነት የሰላ ትችትን መሰንዘር፣ ጥልቅ ፍልስፍናን መወንጨፍ፣ የሕዝቡን ብሶት ማስተጋባት ወዘተ. ነው፡፡ በህዳሴ
እንቅስቀሴአችን ውስጥ ያላየነውን እናይ ዘንድ (ግልብ ስልጣኔአችንን እየገለበ) የሚሞግተው ኪራኮስ በተባለ ገጸ
ባሕርይ አማካኝነት ነው፡፡
ዴርቶጋዳን ለአንባቢዎቹ ባቀረበ ጊዜ የንባብን አብዮት በኢትዮጵያ ላይ የለኮሰው ይስማዕከ ወርቁ ለአማርኛ ሥነ
ጽሑፍ መዳበር፣ መታተም፣ መነበብ የራሱ የሆነ አዎንታዊ ተጽዕኖ አሳርፏል፡፡ “ዴርቶጋዳ”ን ነግደው የከበሩ መጽሐፍ
ሻጮችንም ሳንዘነጋ!
እርጅና ያልሆነ ሰንፍና ካልተጠናወተኝ በስተቀር አስታውሳለሁ!
ከአንድ ድፍን ዓመት በፊት መጽሐፍ እያሳተሙ ከደራሲ ወገን የሚሆኑ ሰዎች እንደመብዛታቸው ፖለቲካችንን እና
የአስተዳዳሪዎቻችንን የአስተዳደር ዘይቤ የሚደፍር ትጉህ ብዕረኛ እምብዛም እንደሌለ ጽፌ ነበር፡፡ በዚህኛው ጋዜጣ
አልነበረም፡፡ ያኔ በዕውቀቱ ሥዩምን ስለፖለቲካዊ ሽሙጡ፣ ይስማዕከ ወርቁን ስለ የሀገር ፍቅር ቀስቃሽ ጽሑፎቹ
መጥቀሴን ግን ኮራሁበት፡፡
በተከታታይ ያሳተማቸውን መጽሐፎቹን ብዙዎቹ በጉጉት ሲሻሟቸው አስተውለናል፡፡ በቅርቡ ያወጣው አምስተኛ ልብወለዱ ሲሆን ግጥሞቹን ስንጨምር ሰባተኛ መጽሐፉ መሆኑ ነው፡፡ የአሁኑ መጽሐፉ “ዣንቶዣራ” ይስማዕከ ሁለገብ በሆነ መልኩ እምርታ ያሳየበት መሆኑን አምናለሁ፡፡ በዘመኔም ይህን መጽሐፍ በማንበቤ ራሴን እድለኛ አድርጌ እቆጥረዋለሁ|፡፡ ለመሆኑ ይህን ለምን እላለሁ?
ከታክሲ ግፊያ፣ ከኑሮ ጥድፊያ፣ ከሽሮ ጥልፊያ፣ ከጤና መጠበቂያ ጋር እልህ አስጨራሽ ግብግብ እየገጠምን በምንቆጥበው ሳንቲም የምንገዛቸው ብዙ መጻሕፍት ማጠንጠኛቸው በቀል፣ ውርስ፣ ተረት ከዚህ ሲያልፍ ወሬ፣ ወሲብ፣ ቅንዝረኝነት፣ ብልግና እና መሰል አርቲቡርቲ እየሆነ ተረብሸናል፡፡ የመጽሐፉን ገበያ የሚጋፉት ‹‹ፀሐፊዎች›› ትርኪ ምርኪ ትርጉሞችን ሲያስነብቡን አሜን ብለን የተቀበልናቸው እንመስላለን፡፡ በዚህ የሰቆቃ ጭስ እተጨናበስን ስንማትር “ዣንቶዣራ” ከሰማይ እንደተምዘገዘገ መብረቅ ብልጭ ሲል ውስጥህ ከምን ብለን ጓጓንለት፡፡
የሚያስተምሩን ሲያስተምሩን፣ ልምድ የሚያካፍሉን ሲያወጉን፣ ወገኞች ወግ ሲጠርቁልን፡- ሀዲስ ዓለማየሁ በዘመናቸው የነበረውን የአጼ ሥርዓት መጃጃት በ”ፍቅር እስከመቃብር” አጋለጡ፡፡ ወይም ጥቆማቸውን አደረሱ፡፡ በዓሉ ግርማ የዘመኑን እንቅልፋም ምሁራን በ”አድማስ ባሻገር” ንቁ! ብሎ የደርግን ቦርጫም ባለስልጣናት በኦሮማይ አጋልጦ ተሰዋ፡፡
ፖለቲካንና አስተዳደርን የሚነኩ፣ የሀገር ቁስልን የሚያኩ ምሳሌ ሆነው ብዙ ጊዜ የሚጠቀሱልንን መጥቀሴ ነው፡፡ እኔም እላለሁ፡፡ “ዣንቶዣራ” በሕይወት ላለን፣ ሩጠን ላልጠገብን የጽሑፍ ቤተሰቦች ዐይን ገላጭ ነው፡፡ የዘመናችንን የሀሳብ ስስት፣ አድርባይነትና ሆዳምነት፣ የፍርሃት ብዕረኝነት፣ ደኅና ይሰንብት፣ ሀገር ሕዝብ ሞራል ይቅደም አለን፡፡
በ304 ገጾች የተቀነበበው “ዣንቶዣራ” ለአያያዝና ለዕይታ በሚያመች የመጽሐፍ ቅርጽ ተደጉሷል፡፡ በአርባአምስት ብር ዋጋ ነው ለአንባቢው የቀረበው፡፡ የመነሻው ገጽ እንዲህ ይላል፡-
‹‹ግልቡን ስልጣኔ መግልብ››
ግልቡን ስልጣኔ የሚገልብልን ደራሲ እንፈልግ ነበር፡፡ በእርግጥ ግልቡን ስልጣኔ ገልበን እናሳያለን ያሉ ጋዜጠኞች መልካም እጣ እንዳልገጠማቸው ሳናስብ አንቀርም፡፡ መሰልጠናችን ከነአሻሚነቱ ቢያስማም እንኳ ስልጣኔአችን ግልብ እንዳልሆነ ልንሟገት አቅም አይኖረንም፡፡ ይህን ግልብ ስልጣኔ ይስማዕከ በ”ዣንቶዣራ” ገጽ 80 ጀምሮ እንዲህ ይገልጠዋል፡-
‹የኢትዮጵያን ዳግም ልደት ለመጠንሰስ፣ እውነተኛውን ዳግም ልደት ለመጽነስ ከየት መጀመር አለበት?›› ሲል አሰበ፡
‹‹ከአብርኾት መሆን አለበት! Enlightenment የጥንቱን ስልጣኔ አሁን ካለው ነባራዊ የዓለም እርምጃ ጋር ማዛመድ አለብን፡፡ መጀመርያ የተበላሸውን ከመወርወር ጠግኖ ወደ መጠቀም፣ ያለፈውን ከማዳፈን አራግፎ መልካም መልካሙን ወደመጠቀም መመለስ አለብን፡፡ መጀመርያ ጥበባችን ማበብ አለበት፡፡ ከአብርኾት Enlightenment ያልተነሣ ሕዳሴ (renaissance) ምንጭ እንደሌለው ወንዝ ነው፡፡ ጎርፍ የፈጠረው የክረምት ወንዝ፡፡ ጎርፉ ሲቆም ወንዙም መቆሙ አይቀርም፡፡
‹‹ሥነ ልቦናችን ራሱ የእኛ አይደለም፡፡ ሁለነገራችን የለማኝ አዝመራ ሆኗል፡፡ ታዲያ ለዚህ ምሱ ምንድን ነው?››
‹‹… ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዳሴ ከሚለው የኢህአዴግ እንቅስቃሴ ጋር አነጻፅረው፡፡ ‹ግማሽ ተሠርታ ግማሽ ተላጭታ› የሚለውን ብሂል አስታውሶት ፈገግ አለ፡፡ ሁለንተናዊ ያልሆነ ሕዳሴ እንደ ተልባ ስፍር በዚህ ሲቆልሉት በዚያ የሚናድ ነው፡፡ (82)
በእርግጥ የቀዳሚ እና የተከታይ ደረጃ ለመስጠት ያዳግተኛል፡፡ ይስማዕከ ግን በአማርኛ ልብወለድ ውስጥ ከተለመደው አብራሪነት፣ ገላጭነት፣ (ለምሳሌ በዕውቀቱ ሥዩም እንደሚተቸው ቀኑ ደመናማ ነው ሰማዩ ብልጭ ድርግም ይላል…) እያልን ከምንወርድበት ዘልማዳዊ ጥንወት መንጭቆ ሊያወጣን ይታትራል፡፡ የ”ዣንቶዣራ” ቁጥር አንድ እምርታ ሁነትን ከማብራራት እና ከመተረክ ይልቅ በገጸ ባሕርያት አማካኝነት የሰላ ትችትን መሰንዘር፣ ጥልቅ ፍልስፍናን መወንጨፍ፣ የሕዝቡን ብሶት ማስተጋባት ወዘተ. ነው፡፡ በህዳሴ እንቅስቀሴአችን ውስጥ ያላየነውን እናይ ዘንድ (ግልብ ስልጣኔአችንን እየገለበ) የሚሞግተው ኪራኮስ በተባለ ገጸ ባሕርይ አማካኝነት ነው፡፡
በ”ዴርቶጋዳ” ተነስቶ በ”ራማቶሐራ” ሸለቆ አቋርጦ ወደ “ዣንቶዣራ” የሚምዘገዘገው የይስማዕከ ምናብ፣ መሠረታዊ ዓላማ የሰለጠነ ትውልድ ማምጣት፤ ስልጣኔን ከውጭ ሳይሆን ከሀገር ውስጥ የማብቀል ከብሔር፣ ከሃይማኖት፣ ከዘር መለያየት እና መቋጠር፤ ፍጹማዊ ንጽህናን ወርሶ ‹‹ሀገር›› ለተባለችው ‹‹ህዝብ›› ሆኖ ስለመገኘት ለመስበክ ነው፡፡
‹‹ከሆድ ያለፈ ዓላማ፤ ከዳቦ ያለፈ ሕልም ያለን ሰዎች ነን›› የሚለውን ቅቡል ንግግር ሚራዥ በገጽ 252 ላይ ይናገራል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው? በእኔና በእናንተ ልብ ውስጥ ብዙ መከፋት አለ፡፡ ከቀበሌ እስከ ፌደራል የተቀመጡ የሥራ ኃላፊዎች፣ የፖለቲካ ሰዎች፣ ሠራተኞች መካከል ሀገር ከምትጥልባቸው አደራ ባለፈ የግል ጥቅም ቀድሞ ትዝ የሚላቸው፣ ይህን ሒሳብ እየሠሩ የሚንቀሳቀሱም ጥቂት አይደሉም፡፡
እነዚህ ነቀዞች ሀገር ለእነሱ ምንም ናት፡፡ አደራ ለእነሱ ተራ ነገር ነው፡፡ ጥቁር ጋዎን ለብሰው የሚገቡት ቃልኪዳን በጥቂት ብሮች የሚደረመስ የሸንበቆ ድልድይ ነው፡፡ በምርጫ ካርድ ያገኙት ያደራ ስልጣን በሰው ላይ ምራቅ ጥቂ ብሎ እስከመትፋት የሚያደርስ ትእቢትን ያዋድዳቸዋል፡፡ እነዚህን ነቀዞች መደራደር ያላማረው ሚራዥ፤ ከሆድ ያለፈ ዓላማ ከዳቦ የበለጠ ህልም ያለው ትውልድ መምጣት እንዳለበት ተናገረ፡፡ ታዲያ ይህ ማንን አያሳምንም? ከአንገት ሳይሆን ከአንጀት ሀገሩን ለሚወድ ስለዚህ ቃሉ ብቻ መጽሐፉ የእውነት መጽሐፍ ነው፡፡
ከፍ ብዬ እንደጠቀስኩት ደራሲዎቻችን በፍርሃት ሸምቀቆ በተቀረቀቡበት በአሁኑ ወቅት፣ የጋዜጦች መዘጋት ተራ ጨዋታ በሆነበት በዚህ ሰሞን፣ እጅን በአፍ የሚያስጭን ድፍረት በ”ዣንቶዣራ” እናያለን፡፡
‹‹ ጤፍ ተወደደ ብሎ ማማረር ሽብርተኛ የሚያስብልበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡ ለተገቢው ስራ ክፍያ ይከፈለኝ ብሎ መጠየቅ ሽብርተኛ የሚያስብልበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡ ስርዓቱ ላለፉት ሃያ ዓመታት በላይ ያልመለሳቸውን ጥያቄዎች ማንሳት ሽብርተኛ የሚያስብልበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡ ቋንቋን መሠረት ያደረገው ፌደራላዊ ሥርዓት ጸረ አንድነት እና ጸረ እድገት ነው ብሎ መከራከር ሽብርተኛ የሚያስብልበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡ የተናገርኩትን ሁሉ መናገርም በሽብርተኝነት እንደሚያስጠይቅ አለመጠርጠር አይቻልም፡፡›› ይህ የተሟጋቹ የዣንጊዳ ንግግር ነው፡፡ (ገፅ 110)
‹‹ልብወለድ›› ከፕሮፌሰር አፈወርቅ ገ/ኢየሱስ የወረስነው ቃል ይሁን እንጂ ልብ የወለደውን ብቻ ትረካ የሚገልጽ እንዳልሆነ የሙያው ሰዎች ይናገራሉ፡፡ “የገሀዱ ዓለም ነጸብራቅ ነው ነው” የሚለውን ንድፈ ሐሳብ ሊያብራራ ቢያሻው፣ ከዚህ በላይ የተቀመጠውን የመፅሃፉን ክፍል ማንበብ እና ካለንበት ነባራዊ ሀቅ ጋር ማነጻጸር በቂ ነው፡፡ እንግዲህ የደራሲው እምርታ ሆኖ እንዳይመዘገብለት ማን ይቃወማል፡፡
ሃይማኖትን ወይ ቋንቋን ወይም ብሔርን ሽፋን በማድረግ ዜጎችን የማለያየት ዓላማ ያነገቡ የገዥው ይሁኑ የተቃዋሚ ፓርቲ ብልጣብልጥ አባላት፣ ጻፍን ያሉትን ክርታሳቸውን ባስነበቡበት የመጻሕፍት መድረክ ላይ ስለሀገር የተዘመረ ድርሳን በዚህኛው ዘመን የስነ ጽሑፍ ታሪክ ትልቁን ስፍራ ቢይዝ አይገርምም ፡፡ አንባቢዎች ተሻምተው ቢገዙት ምክንያቱ ይህ ነው፡፡ መጽሐፍ መሸጥ መተዳደርያቸው ያልሆኑ የሱቅና የጎዳና ነጋዴዎች “ዣንቶዣራን” ቆልለው ሲቸበችቡ መታዘባችንም በልባችን የሚፈላውን የአንድነት፣ የኅብርና የፍቅር ስሜት የሚጠቁም ነው፡፡
ዙርያ ገባውን ያሁኑን ዘመን ህዝብ እና መንግስት ብሎም ሀገሪቱን ለታሪኩ ማጠንጠኛ ያደረገው መፅሃፉ፤ በየገጸባህርያቱ የሚንቀለቀል ወኔ አንድነትን እንደሚያሳየን ሁሉ ቀንጠፋውን እና አክሎግን በመሰሉ ገጸባህርያት ደግሞ ገዥውን ፓርቲ ጥግ አድርገው ፓርቲውንና ህዝቡን የሚመጠምጡ መዥገሮችን ያጋልጣል፡፡
በገዥው ፓርቲ ብዙ እምነት ተጥሎበት ከፍተኛ የደህንነት ሃላፊነት የተሰጠው ቀንጠፋው ለገንዘብ ሲል የሀገሩን አደራ ይዘነጋል፡፡ መዘንጋቱ ሳይሆን አደራውን ሊበላበት ያለው መንገድ ይበልጡን ይሰቀጥጣል፡፡ የሀገሩ አንጡራ ሀብት የሆነውን ኢንጅነር ከነነፍሱ ለሲአይኤ ሊሸጥ ሲዳረደር ማየት እንባን የሚያስመጣ አሊያም በቁጣ የሚያገረጣ ክስተት ነው፡፡
ታዲያ ቀንጠፋውንና አክሎግን ለመሳሰሉ ሀገርና ህዝብ ለሚቸረችሩ ብኩኖች ተስፈኞቹ፣ አዲሶቹ፣ ሀገርን በቅንነት ሊረከቡ ያሉቱ ‹‹ሴቶቿን ለአረብ ምሁሮቿን ለምዕራብ ከእንግዲህ አትሸጡም›› ብለው ሲቋቋሟቸው ማየት፣ በሆነ ከሚለው ምኞት ጋር ቀውቤ መጠጣት ነው፡፡ ሞራልን ስነምግባርን እና ብጽዕናን ለአንባቢ ማቀናጀት የሥነ ጽሑፍ ትልቁ ጥቅም ነው፡፡ ይህን ማድረግ የቻለው ይስማዕከ ዕምርታ ሆኖለታል እላለሁ፡፡
ይስማዕከ በ”ዣንቶዣራ” ብዙ አዲስ ነገሮችን አምጥቷል፡፡ በ”ዴርቶዳጋ” እና በ”ራማቶሐራ” ከታየው ይበልጥ በበረሃ እንዳለ ምንጭ ኮለል የሚል የቋንቋ አጠቃቀምን እናይበታለን፡፡ የመጽሐፉ ሕትመት በራሱ ለማንበብ ምቹ መሆኑን መመስከር የቀደመውን ማጣጣል ይመስላል ብዬ አልገምትም፡፡ ሰላም ለአንባቢያን!
*********************************************************************************
ምንጭ:--አዲስ አድማስ ጋዜጣ
Saturday, 22 September 2012
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ