ከፊልም መንደር
“የኢትዮጵያን ፊልም እንደ ዥዋዥዌ ነው የማየው”
- Written by አበባየሁ ገበያው
- ***********************
አብዛኞቹ የፊልም አድናቂዎች ከ‹‹ሄርሜላ›› ፊልም ጀምሮ ያውቁታል፡፡ በፊልም ትወና ሙያ ለ11 ዓመታት የሰራው አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ፤ በየጊዜው በርካታ የፊልም ፅሁፎች ቢቀርቡለትም እስካሁን በዓመት ከአንድ በላይ ፊልም አልሰራም፡፡ መስራት ሳይፈልግ ቀርቶ አይደለም፡፡ የሚመጥነው እያጣ መሆኑን አርቲስቱ ይናገራል። ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ‹‹የዓመቱ ምርጥ የወንድ የፊልም ተዋናይ›› በሚል የተሸለመው አርቲስቱ፤ የዛሬ ሶስት ዓመትም በተመሳሳይ ዘርፍ ተሸላሚ ነበር፡፡ የ‹‹ሜተድ አክቲንግ›› የትወና ዘይቤ ገፀ ባህርይው መስሎ ሳይሆን ሆኖ መጫወት እንደሚፈልግ ያስረዳል፡፡ ለዚህ ነው የሚተውነውን ገፀ ባህሪ ለማጥናት ሰፊ ጊዜ የሚወስደው፡፡ ዘንድሮ በተሸለመበት በ‹‹400 ፍቅር›› ፊልም ላይ ቦክሰኛውን ሆኖ ለመጫዎት ለስምንት ወር የቦክስ ስልጠና እንደወሰደ ይናገራል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ከግሩም ኤርሚያስ ጋር ባደረገችው ቆይቶ ስለ ህይወቱና ስለ ሙያው፣ ስለ ኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪና ተያያዥ ጉዳዮች አነጋግራዋለች፡፡
በቅርቡ ሁለተኛ ልጅ አግኝተሃል፡፡ ባለፈው ሳምንት ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል “የዓመቱ ምርጥ የፊልም ተዋናይ” በሚል ተመርጠሃል፡፡ ሽልማት በሽልማት ሆነሃል ልበል…
አዎ.. ሁለቱም ሽልማቶች ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ልጄ ወንድ ነው..አምስት አመቱ ነው፡፡ ሁለተኛ ልጄ ደግሞ ሴት ናት፡፡ ይህ የእግዚአብሄር ሽልማት ነው። አዲስዋ ልጄ ከተወለደች ሃምሳ አምስተኛ ቀንዋ ነው። ሌላው በ”የኢትዮጵያ ኢንተርናሽና ፊልም ፌስቲቫል” ሁለት ጊዜ ማለትም በአምስተኛውና በስምንተኛው ዙር ውድድር “ምርጥ የወንድ ፊልም ተዋናይ” ሆኜ ተመርጫለሁ፡፡ ይሔኛው ሽልማት ደግም ሰዎች ለሰራሁት ስራ እውቅና ሰጥተው አክብሮታቸውን ያሳዩበት ነው፡፡ ሁለቱም ለእኔ ብርቅ ናቸው፡፡
እስቲ አሸናፊ ስለሆንክባቸው ስራዎችህ ንገረኝ?
በአምስተኛው ዙር ‹‹ትዝታ›› እና ‹‹ይሉኝታ›› በተሰኙት ፊልሞች በእጩነት ቀርቤ ነው በአንዱ የተሸለምኩት፡፡ ባለፈው ሳምንት በስምንተኛው ዙር ውድድር ደግሞ ‹‹400 ፍቅር›› በተባለው ፊልም “ምርጥ የዓመቱ የወንድ ፊልም ተዋናይ” ሆኜ ተሸልሜአለሁ፡፡
‹‹ትዝታ›› እና ‹‹ይሉኝታ›› ፊልሞች..ጭብጣቸው ምን ነበር?
ሁለቱም በተለያየ ዘውግ የተፃፉ የተለያየ ባህሪ ያላቸው ፊልሞች ናቸው፡፡ ‹‹ይሉኝታ››ን ካየነው ዳርክ ኮሜዲ ከሚባለው የፊልም ዘውግ የሚመደብ ነው፡፡ ‹‹ትዝታ›› ደግሞ ሙሉ በሙሉ ድራማ ነው። ሁለቱ ውስጥ የተለያዩና ፅንፍ ለፅንፍ ያሉ ገፀ ባህሪያት ናቸው ያሉት፡፡ ‹‹ይሉኝታ›› ላይ ያለው ዋና ገፀ ባህሪ ጥግ ድረስ ሄዶ ሰዎችን የመረዳት ባህሪ ያለው..ለእኔ ጂኒየስ የምለው ዓይነት ሰው ነው፡፡ በቅርብ የማውቀውን ሰው ነው አክት ያደረግሁት። ለእኔ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ለፍፁምነት እጅግ የቀረቡ ናቸው፡፡ በምድር ላይ ብዙ አይደሉም። ክርስቶስ እንዳደረገው፤ ሁሉነገራቸውን ለሰው የሰጡ ዓይነት ናቸው፡፡ ከውጭ ስናያቸው ሞኝ፣ የዋህ ሊመስሉ ይችላሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች በርከት ቢሉ አለማችን ትቀየራች ብዬ አስባለሁ፡፡
‹‹ትዝታ›› ፊልም እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ ዳሬክተሩ ሃብታሙ አሰፋ፤ የአባቱን እውነተኛ ታሪክ ነው የጻፈው፡፡ ያልኖርኩበትን የ60ዎቹን ወጣትነትና በእርጅና ውስጥ ያለ ህይወት ነው የዳሰስኩበት፡፡ የሚገርመው ሁለቱንም አልኖርኩበትም፡፡ ሁለቱም ጽንፍ ያላቸው ግን ወድጃቸው የተጫወትኳቸው ናቸው፡፡ ዘንድሮ በስምንተኛው ዙር ያሸለመኝ ደግሞ ‹‹400 ፍቅር›› ፊልም ነው፡፡ የሁለት መንታዎች ታሪክ ነው፡፡ በመጀመሪያ ‹‹ምን ዓይነት መንታዎች አሉ?›› የሚል ሰፊ ጥናት አደረግሁ፡፡ ብዙ ዓይነት የመንታ ዓይነቶች አሉ፡፡ በፊልሙ ላይ ያሉት ግን ‹‹ሚረር ኢሜጅ አይዴንቲካል ትዊንስ›› የሚባሉ የመንታ ዓይነቶች ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት መንታዎች ከሌሎች መንታዎች የሚለዩት፣ ራሳችንን በመስታወት በምናይ ጊዜ መስታወት ውስጥ ላለው ምስል ሁሉ ነገራችን ተቃራኒ ነው። ቀኛችን ግራ ነው፣ ግራችን ቀኝ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት መንታዎችም መልካቸው አንድ ዓይነት ይሆናል እንጂ ሁሉ ነገራቸው የተለያየ ነው፡፡ ለምሳሌ አንደኛው ግራኝ ከሆነ፣ አንደኛው ቀኝ ይሆናል፡፡ ፍፁም የተለያዩ ናቸው፡፡ አንደኛው ቦክሰኛ ነው፣ አንደኛው ደግሞ ዲዛይነር ነው፡፡
በዚህ ፊልም ውስጥ ቦክሰኛውን ሆነህ ለመጫወት ቦክስ ተለማምደሃል?
ያውም ስምንት ወር ነዋ የፈጋሁት! ከቦክሰኞች ጋር በመዋል..ሙሉ በሙሉ የቦክስ ልምምዱን ወስጄ ነው የወጣሁት፡፡ ቦክሱን ያስተማሩኝን አሰልጣኝ ከድር ከማልን እና ካሳዬ ከፋን በጣም አመሰግናለሁ። በስምንት ወር ውስጥ ፕሮፌሽናል ቦክሰኛ ነው ያደረጉኝ፡፡
አሁን መዘረር ነው በለኛ...
/ሳቅ/ የሚገጥመኝ ካለ ዝግጁ ነኝ። እና በፊልሙ ላይ የመንትዮችን ባህሪ ሳጠና፣ ከእናትና ከአባታቸው የወረሱት ጂን ምንድን ነው? ለምሳሌ አንደኛው ከእናቱ የድፍረትን ጂን ወስዷል። አንደኛው ደግሞ አባታቸው ፈሪ ስለነበረ የአባታቸውን ጂን ወስዷል። የዚህን ያህል ነው የካራክተሮችን ባህሪ ያጠናሁት። የዚህ ልፋት ዋጋ ነው በሰዎች ዘንድ ዋጋ አሰጥቶኝ ያሸለመኝ፡፡
ወደ ሙያው ከገባህ ጀምሮ ስንት ፊልሞች ሰራህ?
አስራ አንድ ፊልሞች ነው የሰራሁት፡፡ “መስዋዕት”፣ “ሄርሜላ”፣ “ልዕልት”፣ “ስርየት”፣ “የሞረያም ምድር”፣ “862”፣ “ትዝታ”፣ “ይሉኝታ”፣ “አማላዩ” እና “400 ፍቅር” ናቸው፤ ባለፉት አስራ አንድ ዓመታት የሰራኋቸው፡፡ ይሄ እንግዲህ በዓመት አንድ ፊልም ማለት ነው፡፡
ፊልሞች በበዙበት ወቅት እንዴት በዓመት አንድ ብቻ በመስራት ተወሰንክ?
ሁሉጊዜ የሚስበኝ የምሰራበት ፊልም ያለው ታሪክ ምንድን ነው የሚለው ነው፡፡ ለማህበረሰቡ በተወሰነ መልኩ መልዕክት ማስተላለፍ የሚችል ታሪክ ሲሆን ደስ ይለኛል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ፣ የምጫወተው ካራክተር (ገፀባህሪ) ነው የሚመስጠኝ፡፡ የእኔ መስፈርት፣ እስከዛሬ ከተጫወትኳቸው ካራክተሮች በጭራሽ የማይመሳሰል መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ ለምሳሌ ሰዎች ‹‹አማላዩ››ን ፊልም አይተው ‹‹አማላዩ›› ላይ ያለውን አይነት ካራክተር..ይዘቱም ቅርፁም ተመሳሳይ የሆነ የፊልም ታሪክ ይዘውልኝ ይመጣሉ.. ግን አልቀበልም፡፡ ምክንያቱም ያ በቃ ሞተ፤ ለእኔ ያ ሰው እንደተቀበረ ሰው ማለት ነው። አንድ ካራክተር ከሰራሁት በኋላ እንሰነባበታለን፡፡ ከዛ ደግሞ ያልሰራሁት፣ ያልዳሰስኩት፣ ያልነካሁት ገፀ ባህሪ መጫወት እፈልጋሁ፡፡ የተወሰነ ጊዜ እጠብቃለሁ፤ አሪፍ አሪፍ ነገር እስኪመጣልኝ፡፡ ለዛ መሰለኝ..
ለአምስት ዓመት በማረሚያ ቤት ታስረህ ነበር፡፡ እንዴት ነው ያሳለፍከው?
ብዙ መፃህፍትን “ቁርጥም አድርጌ የበላኋቸው” የዛን ጊዜ ነው፡፡ ልቦለድ፣ ፍልስፍና፣ ስለላ.. ብዙ ታሪኮችን አንብቤያለሁ፡፡ የማንዴላን “Long walk to Freedom”፣ “ፍቅር እስከ መቃብር” ወዘተ.. ትምህርቴን አቋርጬ ስለነበር፣ እንደ አዲስ ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሬ እዚያው ተማርኩ፡፡ የቋንቋ ችሎታዬን በተወሰነ መልኩ ለማዳበርም ሞክሬያለሁ፡፡ ማረሚያ ቤት ለእኔ ዩኒቨርስቲ ነበር፣ ህይወትን “ግራጅዌት” አድርጌ እንደወጣሁ ነው የምቆጥረው፡፡ ራስን የመፈለግ ጉዞ ነበር የሆነልኝ፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን በማረምያ ቤት ጨረስክ፡፡ ከዚያ በኋላስ አልቀጠልክም?
ከሆሊላንድ አርት አካዳሚ በትያትሪካል አርት ተመርቄአለሁ፤ ሁለት ዓመት ተምሬ፡፡
አንዳንድ ባለሙያዎች ‹‹ሜተድ አክቲንግ” እንደምትከል ይናገራሉ፡፡ እስቲ ስለእሱ አብራራልኝ…
እንደ ስታይል የሜተድ አክቲንግ ስታይል ተከታይ ነኝ፡፡ የሩሲያዊውን አክተርና ዳይሬክተር የስታኒላቭስኪን የሜተድ አክቲንግ መፅሃፍ አግኝቼ አንብቤዋለሁ፡፡ እሱን ከአነበብኩ በኋላ ነው የሜተድ አክቲንጉ ተከታይ መሆን የጀመርኩት፡፡ በዚህ ስታይል መሰረት፤ የምትጫወችውን ካራክተር መምሰል ሳይሆን መሆን አለብሽ፡፡ አንቺ ወደ ካራክተሩ እንድትሄጂ እንጂ ካራክተሩ ወደ አንቺ እንዲመጣ አይጠበቅም፡፡ ወደ አንቺ የሚመጣ ከሆነ “ታይፕ አክተር” ነው የምትሆኝው፡፡ ያ ከሆነ ደግሞ የምሰራቸው ፊልሞች ተመሳሳይ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ካራክተሩ ወደ አንቺ እንዲመጣ በጋበዝሽው ቁጥር ሌሎች ሰዎችን ነው የምትሆኝው፡፡ ሜተድ አክቲንግ የሚጠቅመው ካራክተሮችን እንዳትደግሚ በማድረግ ነው፡፡ እኔ ደግሞ የዚህ ውጤት ነኝ፡፡
የተለያዩ ባህሪያትን እያጠኑ ሆኖ መጫወት ትክክለኛው የራስህ ባህሪ ላይ ተጽዕኖ አያሳድርም?
እውነት ነው፤ በጣም ተፅዕኖ (ኢንፍሉዌንስ) አለው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ዲፕሬሽን (መደበት) ሊያጋጥምሽ ይችላል፡፡ የተጫወትኩት ባህሪ ከደሜ ውስጥ ሙልጭ ብሎ እስኪወጣ ድረስ ይዞኝ ይጠፋል፡፡ ይሁነኝ ብለሽ አይደለም የሚመጣብሽ። በሰብኮንሸስ ማይንድ (ንቁ ባልሆነው የአዕምሮአችን ክፍል) ነው የሚሰራው። ብዙዎቻችን የምንኖረውም በሰብኮንሼስ ማይንዳችን ነው፡፡ ሰብኮንሸስ ማይንድ በነገርሽው መጠን፣ ያንን ነገር ቅርጽ አስይዞ ያስቀምጥና ይመነዝረዋል፡፡ ከዚያም አሳልፎ ለኮንሸስ ማይንድ (ለንቁው የአዕምሮአችን ክፍል) ይሰጣል፡፡ ‹‹400 ፍቅር››ን ስሰራ አነበብኩ፤ ሪሰርች አደረግሁ፡፡ ቦክስ ተማርኩ…ከቦክሰኞች ጋር ተገኘሁ..ራሴን ‹‹ቦክሰኛ ነኝ›› ብዬ አሳመንኩ፡፡ ቦክስ ቦክስ ስል ሳላውቀው…ሰውነቴም ሪአክት ማድረግ ጀመረ… ክብደት ጨመርኩ..ጡንቻዬ ይሳሳብ ጀመር፡፡ አሁን ደግሞ የሃሺሽ ሱስኛ (ድራግ አዲክትድ) የሆነ ገፀ ባህሪ ያለበትን የፍጹም አስፋውን ፊልም ለመስራት ጥናት ላይ ነኝ፡፡ ሪሰርች ጀምሬያለሁ፤ ሰውነቴ ሲከሳ ይታወቀኛል፡፡
እንዴት ነው በሱስ የተያዘ ሰው ባህሪን የምታጠናው?
/ሳቅ/…ድራግ አዲክትድ ወይም የሀሺሽ ሱስኛ ሰውን ባህሪ ነው የማጠናው፡፡ በተደጋጋሚ ጳውሎስ ሆስፒታል “ሪሃብሊቴሽን ሴንተር” እየተመላለስኩ ነው፡፡ የድራግ ሰብስታንሶች ያሉባቸው ሰዎች ከሱሳቸው የሚነፁበትን መንገድ ለምሳሌ ከመጠጥ፣ ሲጋራ፣ አልኮልና፣ አደንዛዥ ዕፅ... ለማጥናት ሰሞኑን ያለሁት ጳውሎስ ነው..ብዙ የተሰሩ ጥናቶችን ከኢንተርኔት እያወጣሁ አነባለሁ፡፡ በሽተኞች፣ ዶክተሮች፣ ሳይካትሪስቶች…አግኝቻለሁ፡፡ እነሱን ሳገኝ ሳላውቀው ምን እንደሆንኩ ታውቂያለሽ? በየቀኑ የማዘወትረው ስፖርት አስጠላኝ፡፡ ብታምኝም ባታምኝም የምግብ ፍላጐቴ ሁሉ እየተዘጋ መጣ፡፡ ኪሎዬም እየቀነሰ ነው፡፡ ለምን መሰለሽ? ከህመምተኞች ጋር ሳወራ፤ የምግብ ፍላጎት እንደሚያጡና ክብደታቸው እንደሚቀንስ ሰማሁ፤ አሁን ሰውነቴ በዛ ነገር ውስጥ እየገባ ነው ያለው፡፡
ከአምስት ወር በፊት ወታደር ገፀባህሪ ያለው ፊልም ለመስራት ለሶስት ወር የወታደር ካምፕ ውስጥ ልትገባ በዝግጅት ላይ እንደነበርክ ነግረኸኛል፡፡ ምን ደረሰ?
ገና ነው፤ በሆነ ምክንያት እንዲቆይ ተደርጓል። ነገር ግን ከአምስት ወር በፊት እንዳልሽው ወታደር ወታደር ሸትቼ ነበር፡፡ በዛን ወቅት የማያቸው ፊልሞች በጠቅላላ የጦርነት “ዋር ሙቪ” ነበሩ። ማንበብ የምፈልገው መፃህፍት ሁሉ ከውትድርና ጋር የተገናኙ ነበረ፡፡ ማየት የምፈልገው ወታደር ነው፡፡ ከሚሊተሪ ነክ ሰዎች ጋር መዋል ጀምሬ ነበር። እነሱን መስማት ማድመጥ ነበር ስራዬ፡፡ ለሶስት ወር ስልጠና ልንገባ ወደ አዋሽ አካባቢ ካምፕ ሁሉ ተዘጋጅቶልን ነበር፡፡ ይህን ማድረጌ ካራክተሩን በቀላሉ ማግኘት እንድችል ይረዳኛል፡፡ ጊዜው ሲደርስ እሱንም እሰራዋለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡
ስታንቶች የሚያስፈለጉት ታዲያ መቼ ነው?
ለምሳሌ እኔ ሞተር ሳይክል መንዳት ባልችል ወይም መኪና ከኋላ የሚከተለው የ”ካር ቼዚንግ” ካራክተር ያለው ፊልም ልስራ ብል..ስታንቶች ያኔ ይመጣሉ፡፡ ስታንቶች ለአክተሩ በጣም ከባድ የሆኑ ልዩ ክህሎት የሚጠይቅበት ቦታ ላይ ነው የሚያስፈልጉት፡፡ ካልሆነ ራስሽ ብትሰሪው ይመረጣል፡፡ እኔ ራሴ ብሰራው እመርጣለሁ፡፡ ደስ የሚለውን…እስከ አሁን በስታንት የተሰራ የለም..ራሴ ስታንት ሆኜ ነው የምሰራው /ሳቅ/
እስከ አሁን ከሰራኋቸው ፊልሞች ምርጥ “ማስተርፒስ” የምትለው ፊልም የትኛው ነው?
ሁሉም በቂ ዝግጅትና ጊዜ ተወስዶባቸው..ወድጃቸው..በጥናትና በፍቅር.. ተለፈቶባቸው፣ በተለያየ መንፈስና ከአካባቢ የተሰሩ ናቸው፡፡
ፊልም የሙሉ ጊዜ ስራህ ይመስለኛል..
አዎ፡፡ ፊልም ብቻ ነው የምሰራው /ሳቅ/
የምትጠይቀው ክፍያ አይቀመስም ይባላል፡፡ ለአንድ ፊልም ስንት ትላለህ?
ክፍያ ላይ ደህና ነኝ፡፡ ከመቶ ሺ በላይ ነው። የዓመት ቀለብ ናት፤ እሷን እየቆረጠምኩ.. ሌላ የሚመጥነኝ ፊልም እስኪመጣ እጠብቃለሁ፡፡
ለፊልም ብለህ በምትለማመዳቸው አንዳንድ ነገሮች ለምሳሌ መጠጥ፣ ሲጋራ ሱስ ተይዘህ ለመላቀቅ የተቸገርክበት ሁኔታ የለም?
/ሳቅ/ ከጫቱም፣ ከሲጋራውም፣ ከድራጉም.. ባጠቃላይ ከየትኛውም ሱስ የለሁበትም፤ እግዚአብሄር ይመስገን፡፡ ሱስ ካልሽው ግን የስፖርት ሱስ አለብኝ..ስራ ከሌለኝ አብዛኛውን ጊዜዬን ጂም ነው የማሳልፈው፡፡ ምክንያቱም ትወና ለእኔ የማይንድ ስቴትና (አዕምሮአችን) የፊዚካል ባዲያችን (አካላችን) ሃርመናይዤሽን ነው ብዬ ነው የማስበው። የሁለቱም ጥምረት ነው፡፡ ሁለትም እኩል መገንባት (መታነፅ) አለባቸው፡፡ ሁለትን ቢውልድ አፕ የሚያደርግ ተዋናይ አሪፍ ተዋናይ ይሆናል ይባላል፡፡ በትርፍ ጊዜዬ መፅሃፍ አነባለሁ። ድሮ ፊክሽን ነበር፤ አሁን የህይወት ታሪኮች (ባዮግራፊ) ፍልስፍና፣ (ሳይኮሎጂ) መፃህፍትን አነባለሁ፡፡ የግጥም መፃሃፍትም እሞካክራለሁ፡፡
መፃፍ ላይስ እንዴት ነው?
አጫጭር ልቦለዶችን እፅፋለሁ.. እሞክራለሁ፡፡ በፍቅር ነው የምወደው፡፡
ወደፊት በመፅሃፍ መልክ ይወጣሉ?
አዎ አስባለሁ፡፡ የተወሰኑ አሉኝ.. በቅርቡ ይታተማል፡፡
የፊልም ስክሪፕት መፃፍና ዳይሬክት ማድረግስ?
“የፕሬዚደንቱ ምስጢሮች” የሚለውን አጭር ታሪክ ዳይሬክት አድርጊያለሁ፡፡ በ2000 ዓ.ም. አካባቢ የአጭር ልቦለዶችን የአረትኦት ስራ ሰርቻለሁ፡፡ ሁለት ፊልሞችን ፅፌያለሁ.. ‹‹ልዕልት” እና “የሞሪያም ምድር›› የእኔ ድርሰቶች ናቸው። አሁን ግን ሙሉ በሙሉ በትወና ስራ ውስጥ ተመሰጥኩ፡፡
በተለይ በእኛ አገር በፊልም ውስጥ ለመተወን የሚያስቸግሩ አንዳንድ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ከንፈር ለከንፈር መሳሳም አንተ ይሄን ትደፍራለህ?
እንደነዚህ አይነት ነገሮች በርግጥ ትንሽ ከባድ ናቸው፡፡ ከባህላችን ጋር አይሄዱም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን አልሞክርም፡፡ ብዙ ነገር በካሜራ ይሸወዳል እንጂ ይከብዳል፡፡ የቆምኩበት መሬት ወይም ባህላዊ መሰረት (ግራውንድ) ማን ነው ብዬ ነው የማስበው። የቆምኩበት ግራውንድ አሜሪካኖች ናቸው… ኢትዮጵያውያኖች? የምሰራው በኢትዮጵያውያን ግራውንድ ነው፡፡ አበሾች ነን። እኔም የዚህ ማህበረሰብ ውጤት ነኝ፡፡ ያደግሁት ሁሉ ነገር ሽፍንፍን ባለበት ማህበረሰብ ውስጥ ነው። እንደ አርት ግን ትክክል ነው፤ መሰራት አለበት፡፡
ፖለቲካ ላይ እንዴት ነህ? ብዙ አርቲስቶች “ፖለቲካና ኤሌክትሪክ በሩቁ” የሚሉ ይመስላል፡፡ አንተስ?
ፖለቲካ ከባድ ነገር ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እኛ እንደምናስበው ዓይነት ጨዋታ ላይሆን ይችላል፡፡ ሁሉም ለሆነ ነገር ይፈጠራል፡፡ አርቲስት፣ እግር ኳስ ተጫዋች.. አንዳንዱ ደግሞ ለፖለቲካ ይፈጠራል። ለዛ የተፈጠሩ ሰዎችን አከብራለሁ፤ አደንቃለሁ። እንደሌላው ሞያ ማለት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እኛ አድናቆት የሚኖረን ለአርት ለተፈጠረ ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ ለምንድን ነው ለፖለቲካ የተፈጠረን ሰው የማናደንቀው? አንዳንድ ሰዎች ለፖለቲካ ተፈጥረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎችን ከልቤ አደንቃለሁ፡፡
በአኗኗርህ ምን አይነት የህይወት ስታይል ትከተላለህ?
ቀለል ያሉ አለባበሶች ይማርኩኛል፡፡ ህይወቴ በራሱ ሲምፕሊ ሲቲ የተከተለ ነው፡፡ በግል ህይወቴ የተወሳሰበ ነገር የለኝም፡፡ በኑሮዬም.. በብዙ ነገር… ስለብስም ቀለል ማለት ይመቸኛል፡፡ ግን ራሴን ሳጠናው ደግሞ አንድ ካራክተር አግኝቼ በልምምድ ላይ ከሆንኩ የዛ ካራክተር ስታይል ሲንፀባረቅብኝ አስተውላለሁ፡፡ እስከ አሁን በዲዛይነር የመልበስ ባህላችን ገና ነው፤ የሚያለብሰኝ ካገኘሁ ግን አልጠላም፡፡
አንተ አሪፍ የምትላቸው አሉ? እንደተመልካች ባለሙያ ማለቴ ነው…
ተይ! ከጓደኞቼ ጋር ታጣይኛለሽ፡፡ ግን ካስገደድሽኝ ከአስር አይበልጡም፤ እስከ አሁን ከአየሁዋችው፡፡
የኢትዮጵያ ፊልሞች የእድገት ደረጃ እንዴት ታየዋለህ?
የኢትዮጵያን ፊልም ኢንዱስትሪ እንደዥዋዥዌ ነው የማየው፡፡ በጣም ወደፊት የተራመደ ፊልም ታያለሽ፡፡ በተራመደበት ፍጥነት ተመልሶ ደግሞ ወደ ኋላ ይሄዳል፡፡ ብዙ ጊዜ ከጓደኞቼ ጋር ሳወራ ይህንኑ ነው የምለው፡፡ የሆኑ ፊልሞች ይዘውት ይወጣሉ፤ የሆኑ ፊልሞች ወደላይ ይዘውት ይወርዳሉ፡፡
ፕሮፌሽናል የፊልም ሃያስያን አለመኖራቸው ለዚህ አስተዋፅኦ አድርጓል ትላለህ?
በጣም ቆንጆ ጥያቄ ጠየቅሽኝ፡፡ በርካታ ሃያሲያንን እንፈልጋለን፡፡ በነገራችን ላይ ሃያሲው ከፊልም ባለሞያዎቹ የተሸለ እውቀት ያለው መሆን አለበት፡፡ እንጂ ዘለፋ ሂስ ሊሆን አይችልም፡፡ በዘለፋ ምንም ማስተማር አትችይም፡፡ ፖዘቲቭና ኔጌቲቭ ጎኑን የሚነግረን፣ ሞያዊ አስተያየት የሚሰጠን ነው የእውቀት ሰው፡፡ እንደዚህ አይነት ሃያሲያን ቢኖሩን ጥሩ ነበር፡፡ ማርክ ትዌይን ስለሃያሲ ያለው አንድ አባባል አለ፡- “ከፊት ከፊት እየሄደ ለደራሲው መንገድ የሚያሳይ ትክክለኛ ሃያሲ ነው” ይላል፡፡ ቀሽም ሃያሲ ከኋላ ከኋላ እየተከተለ ባለሙያውን የሚገፋው ነው። ለእኛ የሚያስፈልገን ከፊት ለፊት እየሄደ መንገዱን የሚጠርግልን ሃያሲ ነው እንጂ የሚገፋ ምን ያደርጋል። የፊልም ኢንዱስትሪው እንዲያድግ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች የግድ ያስፈልጋሉ፡፡ ራሱ ሂስ ‹‹ሞያዊ አስተያየት›› ስለሆነ ማለት ነው፡፡
ምን አዲስ ስራዎች እንጠብቅ?
ሁለት ስራዎች አሉ፡፡ ከቶም ፊልም ፕሮዳክሽን ጋር የሰራሁት አንድ ፊልም አለ፡፡ ታሪኩ ስለ አንድ ሃብታም ወጣት ነው፡፡ የተለየ አይነት ባህሪ ያለው ነው.. ትወድታላችሁ፡፡ ሁለተኛው እኔና ሰለሞን ቦጋለ የሰራነው ‹‹የፀሃይ መውጫ ልጆች›› የተሰኘ ፊልም ሲሆን የቢንያም ወርቁ ድርሰት ነው፡፡ በዓይነቱም በይዘቱም ለየት ያለ ነው፡፡ ..ለመስራት በጥናት ላይ ነኝ ያልኩሽ የድራግ አዲክትድ ካራክተር ደግሞ የፍፁም አስፋው ፊልም ነው፡፡ ለጊዜው እነዚህ ናቸው፡፡
ሃሳብ የለህም?
በማውቀው ቋንቋና በለመድኩት ባህል ላይ ስሰራ ደስ ይለኛል፡፡ በትምህርት በኩል ግን በተለይ ከትወና ጋር በተገናኘ ስኮላርሽፖችን ለማግኘት ሁልጊዜ ራሴን ማሳደግ እፈልጋለሁ፡፡ ለራሴ ብቻ ሳይሆን በአገሬም የትወና ፍላጎትና ጥማት ያላቸውን ሰዎች ማስተማር እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህ ነው ከዚህ በፊት ተዋናይ ለመሆን ለሚፈልጉ ሰዎች መፅሃፍ ተርጉሜ ያሳተምኩት፡፡
የመፅሃፉ ርዕስ ምንድን ነው?
‹‹መሰረታዊ የትወና መማሪያ›› የሚል መፅሃፍ ነው፡፡ ወደ ትወና በስፋት እየገባሁ በመጣሁ ጊዜ ሙያው ባህር እየሆነና ብዙ ልፋት የሚጠይቅ እየሆነ መጣብኝ.. ያኔ በመሃይም ዕውቀቴ ትወና የጀመርኩ አካባቢ ያወቅሁ መስሎኝ ነበር፡፡ እየሰራሁ በመጣሁ ቁጥር እየሰፋብኝ ነው የመጣው፡፡ ስፋቱን ለማጥበብ መማር አለብኝ፡፡ እድሉን ባገኝ ደስ ይለኛል፤ እስከዚያው በአጠገቤ ያሉትን መፅሃፍት እያነበብኩ እቆያለሁ፡፡
የውጭ ፊልሞችን ትመለከታለህ? የትኞቹን ዘውጐች ትመርጣለህ? የትኞቹን የሆሊውድ አክተሮችስ ታደንቃለህ?
የውጪ ፊልሞች በጣም አያለሁ፡፡ አንድ መፅሀፍ ላይ እንዳነበብኩት አንድ ሰው ፊልም ሰሪ ለመሆን ከፈለገ ፊልም ማየት ነው የሚያስፈልገው። የፊልም ሜከር ትምህርት ቤቱ ራሱ ፊልም ማየት ነው፡፡ የአሜሪካ ፊልሞች እጅግ ይመስጡኛል። የድራማ ዘውግ ፊልሞች አድናቂ ነኝ፡፡ ድራማ የሚያነጣጥረው ሪያሊስቲክ በሆኑ ነገሮች ላይ ነው፡፡ ንፅፅሩም በሁለት መሃል ያሉ እውነቶችን እንድትመርጪ ነው የሚያደርገው፡፡ ድራማ ለተዋናዩም፣ ለአዘጋጁም፣ ለፀሃፊውም ከባድ ነው ይባላል፡፡ ከሆሊውድ አክተሮች የማደንቀው… ከወጣቶቹ ኩባ ጉዲንግ፣ ኤድዋን አልበርተን፣ ማትዴመንን ሲሆን ከፊልም “ሮሚዬዝ ብሊዲንግ” አደንቃለሁ፡፡ ጋሪአልድ ማን የተጫወተበት… ከአውሮፓ ፊልሞች “ሲኒማ ፓራዲዞ” የተባለውን የጣሊያኖች ፊልም አደንቃለሁ። በነገራችን ላይ የአውሮፓ ፊልምም አያለሁ፡፡ ብዙዎቹ የእንግሊዝኛ ሰብታይትል ስላላቸው ቋንቋ ላይ ችግር የለም። የኢራን ፊልሞች በጣም ነው የምወዳቸው። የሚገራርሙ ናቸው፡፡ የአውሮፓ ፊልሞች ለጥበብ አዳኞች ነው የሚሰራው፡፡ ለእኔ አንደኛ ፊልሜ ግን “ሲኒማ ፓራዲዞ” ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለአንባቢያን ይህንን ፊልም እጋብዛለሁ፡፡ የፊልም ትምህርት በጣም እየተሰጠ ያለው በአሜሪካ ነው። አውሮፓዎችም አላቸው፡፡ ግን ብማር ብዬ የማስበው አውሮፓ እንግሊዝ አገር ነው፡፡ የእነሱ ፊልሞች በጣም ጠንካራ ናቸው፡፡ ለጥበብ አዳኞች የሚሰራ ነው፡፡ ስኬፒስት ኦዴንሶች አይደለም የሚበዙት፡፡ የሚሰሩት ፊልሞች “ጥበብ ..ለጥበብ ደንታ” የሚባሉ አይነት ናቸው። እነሱ ሲያሾፉ ምን ይላሉ? “ኮሜርሺያል የሆነ የአውሮፓ ፊልም ሆሊውድ ውስጥ ቢሄድ የጥበብ ፊልም ይሆናል” ይላሉ፡፡ እንደዚህ ነው አውሮፓውያን አሜሪካኖቹን የሚንቋቸው፡፡ የሆሊውድ ዳይሬክተሮች ራሳቸው ፊልም የአውሮፓውያንን ፊልም ነው የማያዩት፡፡
ትያትር ላይ ስትተውን አተታይም፡፡ ለምንድነው?
መድረክ ላይ ሰርቼ አላውቅም፡፡ ትያትር የማከብረው ሞያ ነው፤ ዘልዬ መግባት አልፈልግም። ምናልባት ወደ ትያትር ብመጣ እንኳን ስለቲያትር የተወሰኑ ነገሮች በደንብ አውቄ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም የፊልም አክቲንግ እና የመድረክ አክቲንግ የተወሰነ ልዩነት አላቸው፡፡ ልዩነቱን አጥብቤ ነው ወደ ቲያትር መግባት የምፈልገው፡፡ ለአንድ የፊልም አክተር ከዘጠና ፐርሰንት በላይ ያለው የስሜት ጨዋታ አይን ውስጥ ነው፡፡ ወደ ትያትር ስትመጪ ግን ሰፊ ነው፡፡ ብዙ ሰው ነው ያለው፡፡ ለዛ ሁሉ ሰው ስሜትሽ እንዲጋባበት የምታደርጊው በአይንሽ አይደለም፤ የእጅ እንቅስቃሴዎችን፣ የፊት ገፅታዎችን ትጠቀሚያለሽ …የፊልም ትወና በካሜራ ክሎዝ አፕ እየታየ ነው ጨዋታው፡፡
ፊልም አክት አይደረግም ኑሮ ነው የሚኖረው። “ኖ ፌስ አክቲንግ” ይባላል፡፡ ፊትሽ ላይ አክት አያስፈልግም፡፡ አይን ውስጥ ነው ብዙ ስሜቶች የሚያልቁት፡፡ በጥቅሉ ግን እኔ ቅኝቴም፣ የተጠመቅሁበትም ፊልም ነው፡፡
***********************************************************************
ምንጭ:--http://www.addisadmassnews.com
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ