ጀግናው በላይ ዘለቀ



  ግናው በላይ ዘለቀ ከአባታቸው ከባሻ ዘለቀ ላቀው እና ከእናታቸው ከወ/ ጣይቱ አስኔ በወሎ ክፍለ ሐገር በቦረና ሳይንት አውራጃ በጫቃታ ወረዳ ልዩ ስሙ ጅሩ ጉጣ ከተባለው ቀበሌ 1904 . ተወለዱ። በተወለዱ በአራት ዓመታቸው አባታቸው ባሻ ዘለቀ ላቀው የልጅ እያሱ ባለሟል ሆነው የአንድ ክፍለ ጦር ኃላፊ ስለነበሩ ልጅ እያሱ በተያዙ ጊዜ ከዚያ አምልጠው በቦረና ሳይንት አውራጃ በጨቃታ ወረዳ ልዩ ስሙ ጣቀት መድሉ ከተባለው ቀበሌ ተቀምጠው እንዳሉ ከአንድ ሰው ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው በፀብ መካከል የሰው ህይወት ያልፍባቸዋል። ለዚህም ምክንያት ወሎን ለቀው ወደ ጐጃም መጡ። ጐጃምም በተለይ በቢቸና አውራጃ በእነማይ ወረዳ ልዩ ስሙ ለምጨን ከተባለው ቀበሌ ተቀመጡ።
ብቸና ውስጥም ተቀምጠው ሳለ እርሳቸውን የሚያስስ ልዩ ጦር በጥቆማ ወደ አካባቢው ተላከ። ከዚህ ጦር ጋርም ከፍተኛ ውጊያ ተደረገ። በዚህ ውጊያ ወቅት በላይ ዘለቀ እና እጅጉ ዘለቀ ልጆች ቢሆኑም ተኩሱን እያዩ የሚወድቁትን ጥይቶች ይቆጥሩ ነበር። ከውጊያው በኋላም የበላይ ዘለቀ አባት ተመተው ይወድቃሉ። ይሞታሉ። እነ በላይ ዘለቀም ካለ አባት ከእናታቸው ከወ/ ጣይቱ አሰኔ ጋር ማደግ ይጀምራሉ። ከፍ ሲሉም የአባታቸውን ገዳይ እና አስጠቁሞ እየመራ ያስገደላቸው ማን እንደሆነም ለማወቅ ማሰስ ጀመሩ።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሳሉ ፋሺስት ኢጣሊያ 1928 . ኢትዮጵያን ወረረች። በላይ ዘለቀ በወቅቱ 24 ዓመት ወጣት ነበሩ። ሀገርን የወረረውን የኢጣሊያን ጦር ለመውጋት ቆርጠው ተነሱ። በወቅቱ 200 እስከ 300 ያህል ጦር በስራቸው ሊያሰባስቡ ቻሉ። በወቅቱም የአካባቢውን ሕዝብ ሰብስበው የሚከተለውን ንግግር አደረጉ፡-
እኔ የዘለቀ ልጅ የምታዩትን የአባቴን አንድ ጥይት ጐራሽ ናስማስር ጠብመንጃዬን ይቼ በሀገር በረሃ የአላዩን ወንዝ ይዤ፣ የአለቱን ድንጋይ ተንተርሼ፣ አሸዋውን ለብሼ ዋሻውንና ተራራውን ምሽግ አድርጌ የመጣውን ጠላት እቋቋመዋለሁ፤ እንጂ እንኳንስ እናንተ የእናቴ ልጆች እጅጉ እና አያሌው ጥለውኝ ሄደው አንድ እኔ ብቻ ብቀርም ከዓላማዬ ፍንክች አልልም። እናት ሐገሬ ኢትዮጵያ ስትደፈር ከማየት ሞቴን እመርጣለሁ። የፈራህ ልቀቀኝ! ለውድ እናት ሀገርህ መስዋዕት ለመሆን የምትፈልግ ሁሉ እኔን ተከተለኝብለው ቆራጥ የሆነውን ውሣኔያቸውን ሰጡ። በዚህን ጊዜ የኒህን ጀግና ልበ ሙሉነት የተረዱት 150 ያልበለጡ አገር ወዳጆች ሲቀሩ ሌሎች ለጠላት እየሄዱ ገቡ። ስለዚህ በላይ ዘለቀም የቀሩትን ታማኝ አሽከሮቻቸውን ይዘው አባይ ለአባይ እየተዘዋወሩ በሚዋጉበት ጊዜ አብረዋቸው ያሉት አሽከሮቻቸው በካዱት ጓደኞቻቸው ላይ እንዲህ ሲሉ የእንጉርጉሮ ግጥም ገጠሙላቸው፡-

ይህንን አንበሳ ጀግናውን ከድታችሁ
ኧረ ተምን ግዜው ለጣሊያን ገባችሁ
በጣም ያሳዝናል ባንዳ መባላችሁ
ከከዳችሁ አይቀር ጀግናውን ከድታችሁ
እምትወዱት ጣሊያን እሱ ካዋጣችሁ
ልቅምቅም አድርጐ ከነጫጩታችሁ
እትውልድ ሀገሩ ሮም ይውሰዳችሁ።
እኛ ለአገራችን ለኢትዮጵያ ባንዲራ
እንታገላለን በጭብጥ ሸንኮራ።
አባይ ከጨረቻው ወድቀን እንደ ገሣ
አንድ ጭብጥ ጥሬ ይዘን በኪስ ቦርሣ
ይኸው አሁን አለን ሳንጠቁር ሳንከሣ።
ጥንት ባባቶቻችን ታፍራና ተከብራ
እንዴት በኛ ጊዜ ይውረራት አሞራ
ይህ ነጭ አሞራ ቢሽኮበኮብ ቢያልፍ
አንሰጥም ኢትዮጵያን ህይወታችን ቢያልፍ

  እያሉ ተስፋቸውን ባለመቁረጥ ትግላቸውን ቀጠሉ። በላይ ዘለቀ ጐጃም ውስጥ የጠላት ጦር
መቆሚያ እና መቀመጫ እንዳይኖረው በማድረግ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ውለታ ያበረከቱ ጀግና ናቸው። ለምሳሌ ለምጨን ከተባለ ቦታ በግንቦት ወር 1928 . ከኢጣሊያ ፋሽስት ጋር ገጥመው ሲዋጉ ከወገን በኩል በመጠኑ የቆሰለና የሞተ ሲኖር ከጠላት በኩል በብዛት ሞቶበት በመጠኑ ስለቆሰለበት በዚሁ ዕለት ድል አድርገዋል። ከዚህ ቀጥሎም ቀኛዝማች ሰማነባዋ የተባሉት የኢጣሊያ የባንዳ አለቃ ስለነበሩ በቂ መሣሪያ እና ወታደር ስጠኝ እና በላይ ዘለቀን ሲሆን ከነ ነፍሱ እጁን ይዤ አለበለዚያም አንገቱን ቆርጬ በሦስት ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አመጣዋለሁ፤ ለወንድነቱ እኔ አለሁ፤ ለበረሃውም እኔው ነኝ፤ በማለት ሊፈፅሙት ያልቻሉትን ተስፋ ለኢጣሊያ ፋሽስት ሰጥተው በትምክህተኝነት ፎክረው የተሰጣቸውን 500 ወታደር ይዘው በላይ ዘለቀን በመውጋት በቢቸና አውራጃ በሸበል በረንታ ወረዳ ልዩ ስሙ አባራ ጊዮርጊስ ከተባለው ቦታ እንደደረሱ በላይ ዘለቀ ያለበትን አሳዩኝ፤ እናንተ እያበላችሁ እያጠጣችሁ ነው ያጐለበታችሁት በማለት በሚስቱ እና በከብቱ ላይ በሚያሰቃዩበት ጊዜ በላይ ዘለቀም ከለምጨን ተነስተው በየረባቲ በተባለ ቦታ አድርገው ሲሄዱ ህዝቡን የሚቀሰቅስ ሽለላ አሸልለዋል።
 
ባላገር ተነሳ ያገር ልጅ ተነሳ ፈረንጅ ቀቅሎ ሳያደርግህ ማርሳ ያባትህን ጋሻ ጦርህን አንሳና ተነሳ ያገሬ ልጅ አገርህን አቅና። እንኳንስ ኢጣሊያ ቢመጣ ፈረንጅ አትሆንም ኢትዮጵያ ያለ ተወላጅ። ጥንት አባቶቻችን በጦር በጐራዴ ሲዋጉ በጋሻ ለኛ አውርሰውናል እስከመጨረሻ።
አድዋን አስታውሰው! የምኒልክን ቦታ እኛ አንበገር ከንቱ አትንገላታ። ከዚህ ቀጥሎ እኒሁ በላይ ዘለቀ ጉዟቸውን በመቀጠል ደብረወርቅ አለት ላይ ሲደርሱ የቀኛዝማች ስማ ነገዎን ፎክሮ መምጣትና የህዝቡን መሰቃየት በሰሙ ጊዜ ያለበትን ስፍራ ቦታ የሚያረጋግጥ ሰላይ ልከው እሳቸው አባይ ወርደው ደባሳ በተባለው መልካ ላይ ውለው ከቀኑ 12 ሰዓት ተነስተው ሌሊት በጨረቃ ከበው አድርገው ሲነጋ አደጋ ጥለው ቀኛዝማች ሶማ ነገዎን ገድለው፣ ከሞት የተረፉትን ጀሌዎቻቸውን በሙሉ ከነመሣሪያው ማርከው ካስቀሩ በኋላ በላይ ዘለቀ እንዲህ አሉ፡-

እናንተ ከኢጣሊያ ታዛችሁ ከአገራችሁ በመክዳት በዛው ቀን በተደረገው ጦርነት
ከሞት ተርፋችሁ የተማረካችሁ ኢትዮጵያዊ የሆናችሁ ወገኖቼ ሁሉ፣ አሁን በእኔ በኩል ምሬአችኋለሁ። እናት ሀገራችሁን የምትወዱ ተከተሉኝ። ወይም አርሳችሁ ብሉ። ነገር ግን ሁለተኛ ለጠላት ገብታችሁ ብትገኙ እኔ የዘለቀ ነገ እመጣለሁ 
በማለት መክረው አሰናበቷቸው።

በላይ ዘለቀ ሊወጋቸው የመጣውን የኢጣሊያ ጦር ከመመከት አልፈው ድልን በድል መቀናጀት ዋናው መለያቸው እየሆነ መጣ። ሁሌም አሸናፊ ሆኑ። የኢጣሊያ ጦር ሁሌም እየተሸነፈ በመሄዱ ተስፋ በመቁረጥ የበላይ ዘለቀን ባለቤት / ሸክሚቱ አለማየሁን እና የባለቤታቸውን እህት / ዘውዲቱ አለማየሁን ገድሎ ልጃቸው / የሻሽወርቅ በላይን ማርኮ ሄደ። ከዚህ በኋላም የበላይ ዘለቀ እልህም እያየለ በመምጣት ብዙ ባንዳዎችን እና የኢጣሊያ ወታደሮችን ድል አደረጉ። በመጨረሻም ጠላት ከበላይ ዘለቀ ጋር ታርቆ፣ ሠላም ፈጥሮ መኖር ፈለገና የሚከተለውን መልዕክት ላከላቸው።
ይድረስ ለልጅ በላይ ዘለቀ። ለኢጣሊያ መንግስት ብትገባ ጥቅም እንጂ ጉዳት አያገኝህም። ጐጃምን በእንደራሴነት ይሰጥሃል። ስለዚህ በሰላም ግባ የኢጣሊያ መንግስት መሀሪ ነውና በአጠቃላይ ሙሉ ምህረት ያደርግልሃል የሚል ነበር።"
በዚህ ግዜ ጀግናው በላይ ዘለቀም ይህንን የኢጣሊያ ደብዳቤ በሰሙ ጊዜ ለተፃፈው ደብዳቤ መልስ ሲፅፉ እንዲህ አሉ፡-

ይድረስ ለኢጣሊያ መንግሥት፣ ከሁሉ አስቀድሜ ሁልጊዜ ሰላም ላንተ ይሁን እያልኩ የማክበር ሰላምታዬን አቀርባለሁ። ከሰላምታዬ ቀጥዬ የምገልፅልህ ነገር ቢኖር ከኢጣሊያ መንግሥት የተፃፈልኝ ደብዳቤ ደርሶኛል። በአክብሮት ተቀብያለሁ። ተመልክቸዋለሁ። በደብዳቤው ላይ ያለውን ቁም ነገር ያዘለ ቃል ስመለከተው እጅግ በጣም የሚያስደስት ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ስለዚህ ልጄን ከመለስክልኝ ጐጃምን ያህል ሀገር በእንደራሴነት ከሰጠኸኝ ከዚህ የበለጠ ሌላ ምን እፈልጋለሁ። ስለዚህ የኢጣሊያ መንግስት የሚያምናቸውን ታማኞቹን ይላክልኝና በእነሱ አማካኝነት አገባለሁ 
 የሚል ደብዳቤ መልሰው ፃፉለት።
በዚህን ጊዜ የኢጣሊያን መንግስት የበላይ ዘለቀን ደብዳቤ እንደደረሰው ሲመለከተው አስደሳች ሆኖ ስለአገኘው በላይ ዘለቀን በእርቅ አታሎ በእጁ ለማስገባት የዘወትር ምኞቱ ስለነበር በጉጉት ይጠብቀው የነበረው ሃሳብ የተሳካ መስሎት የራሱ የፍርድ ቤት ዳኞች ሆነው በታማኝነት ሲያገለግሉት የነበሩትን፣ በኢትዮጵያዊያን ወገናቸው በአርበኛው ላይ ይሰቀል ይገረፍ እያሉ ሲፈርዱና አርበኛ ያለበትን ቦታ ሲጠቁሙና መርተው በማሳየት ይረዱ የነበሩትን ታማኞችን እነ ቀኛዝማች እጅጉ ለማንና እነ ቀኛዝማች አደራው የተባሉትን ከነ አስተርጓሚ ጭምር ሆነው በላይ ዘለቀን በእርቅ አታለውና አባብለው በእጁ እንዲያስገቡለት ላካቸው። በኢጣሊያ መንግሥትና በጀግናው በላይ ዘለቀ መካከል በእርቅ መልክ ለማስማማት የተላኩት ሽማግሌዎችም መድረስ አይቀርምና እንደ እመጫት ነብር ከሚያስፈራው ኮስትር ፊት ቀረቡ። በዚህ ግዜ ጀግናው በላይ ዘለቀም ከፊታቸው ለተሰለፈው ጀግና አርበኛ እንዲህ ሲሉ ስለ እንግዶቹ የሚከተለውን ንግግር አደረጉ።
ጐበዝ ያገሬ ጀግና ሆይ፣ አንድ ግዜ አዳምጠኝ፤ እነዚህ እኔንና የኢጣሊያን መንግስት ለማስታረቅ የመጡ እነ ቀኛዝማች እጅጉ ለማ የተባሉት ሐገራቸውን ከድተው እዚሁ እላይዋ ላይ ሆነው ለኢጣሊያ ፋሽስት ለማያውቁት ለማይወለዱት፣ ለማይመሳሰላቸው በገንዘብ፣ በጊዜያዊ ጥቅም በመደለል ለጠላት መሣሪያ በመሆን በሐቅና በእውነት ለውድ እናት ሀገራቸው የሚዋደቁትን ንፁህ ኢትዮጵያዊያንን ሲያሰቅሉ፣ ሲያሳስሩ፣ ሲያንገላቱና ሲያስረሽኑ ከመቆየታቸው በላይ አሁን እኔንም በዕርቅ መልክ አስገብተው ለማስረሸንና አገሪቱ ተከላካይ ልጅ እንዳይኖራት የሚጥሩ ናቸው። ስለዚህ ምን ውሣኔ ማግኘት እንደሚገባቸው ጀግናው አርበኛ ሃሳብህን ስጥበት 
 ሲሉ ተናገሩ።
በዚህ ጊዜ ጀግናው አርበኛም የመሪውን አነጋገር በጥሞና ካዳመጠ በኋላ እንደዚህ ያለውን ያገር ነቀርሳዎች ጊዜና ፋታ ሳይሰጡ አሁኑኑ ረሽኖ ማለትም በሽጉጥ ግንባር ግንባሩን ብሎ ከዛፍ ላይ ጠቅሎ የአሞራና የንፋስ መጫወቻ ማድረግ ነው ብሎ በአንድ ድምፅ ወሰነ።
በዚህ ጊዜ በአስታራቂነት የመጡት እነ ቀኛዝማች እጅጉ ለማ አትፍረድ ይፈረድብሃል እንደተባለው ሁሉ እነሱ በሌላ ሲፈርዱ ኖረው በእነሱ ላይ ይግባኝ የሌለው የአርበኛ ፍርድ በማግኘት ፅዋው ስለደረሳቸው በጥይት ተረሽነው በዛፍ ላይ ተሰቀሉ። ከዚያም በኋላ ጀግናው በላይ ዘለቀም እንዲህ የሚል ደብዳቤ ለኢጣሊያ መንግሥት ፃፈ፡-
ይድረስ ለኢጣሊያ መንግሥት፤ ሰላም ለአንተ ይሁን፤ የላክልኝን እንግዶች እነ ቀኛዝማች እጅጉ ለማን በአክብሮት ተቀብዬ በማስተናገድ ሥፍራ ወይም ቦታ ሰጥቻቸዋለሁ። ላንተ ግን ትርጁማን (አስተርጓሚ) ብለህ የላከውን ሌላ ቦታ ስትልክ እንዳይቸግርህ ልኬልሃለሁ። ልጅህን እመልስልሃለሁ ለምትለው ለአንድ ልጅ ብዬ እናት ሀገሬን ኢትዮጵያን ከድቼ ከአንተ ጋር በእርቅ መልክ አልደራደርም። ከዛሬ ጀምረህ በእኔ በኩል ያለውን ምኞትህን አንሳ። እኔን ፈልገህ ማጥፋት እንጂ አንዲት ልጅ ወስዶ ማስጨነቅና ማጉላላት ደስ የሚልህ ከሆነ እንደፈለክ አድርጋት። ሲሆን ለሷም የፈጠራት አምላክ እግዚአብሔር ፍቃዱ ከሆነ ከአንተው እጅ ላመጣት እችል ይሆናል። ጐጃምን በእንደራሴነት ልስጥህ ለምትለው አንተ የሰው ሀገር ሰው ከምትሰጠኝ እኔው ሀገሬን በሥሬ አድርጌ አስተዳድረው የለም ወይ? ስለዚህ የፖለቲካ ወሬህን ከምትነዛና የኢትዮጵያን አርበኛ እየቆማመጠ ለአሞራ በመስጠት በየዱር ገደሉ ወድቀህ ከመቅረት በመጣህበት መንገድ አገርህ ከመግባት በስተቀር አማራጭ የሌለህ መሆንህን በዚህ አጋጣሚ ልነግርህ እወዳለሁ 
 ሲሉ በላይ ዘለቀ ለኢጣሊያ መንግሥት ደብዳቤ ልከዋል።
በመጨረሻም የተማረከችውን ልጃቸውን የሻሽወርቅን እንደገና ተዋግተው ከኢጣሊያኖች እጅ ከነህይወቷ ለመማረክ ችለዋል። በአጠቃላይ በላይ ዘለቀ በአምስቱ ዓመት የነፃነት ተጋድሎ ውስጥ ከፊት የሚሰለፉ ታላቅ አርበኛ ናቸው። ታዲያ የመጨረሻው የሕይወት ፍፃሜያቸው ደግሞ ከወንድማቸው ከእጅጉ ዘለቀ ጋር በስቅላት እንዲቀጡ ተደርጓል። ቸር እንሰንብት።__
****************************************************************************
ምንጭ፡--ሰንደቅ(በጥበቡ በለጠ) 9 ዓመት ቁጥር 452 ረቡዕ ሚያዝያ 29 200 ,.


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

የገጣሚ ነብይ መኮንን እማይነትበዉ ስዉር-ስፌት

ሞክሼ የአማርኛ ፊደላት እና የባለሙያዎች ማብራሪያ

ንባብ ለሕይወት!