ያወጣሁ ያወረድኩት ሀሳብ


Chasing Beautiful Questions 
እንዲህ አሰብኩ ። ሜኒያፖሊስ አየር መንገድ የአይሮፕላኑ መንደርደሪያ መስክ ላይ እኔን እና ብዙ ፈረንጆችን የተሳፈርንበት የብረት አሞራ ወደ ሰማይ ለመምጠቅ ሲንደረደር አንድ ሀሳብ ወደ አእምሮዮ መጣ።እሳቤውን የጫረልኝ አንድ እግሩን በቀን ጎዶሎ ያጣ ፈረንጅ ነው። ገና የ 21 ዓመት ጐረምሳ ሳለ በበጋው ወራት አሪዞና ውቅያኖስ ዳርቻ ፈረንጆቹ ዋተር እስኪንግ የሚሉትን በእኛ አገር እይታ ቅብጠት በእነሱ ደግም እስፓርት ጨዋታ ላይ እንዳለ ያልታሰበ የሞተር ጀልባ ገጭቶት እራሱን ይስታል ።
እራሱን ያወቀው እሆስፒታል ውስጥ ነበረ ። መመልከት አልፈልግም ግን ልመልከተው አለ ግራ እግሩ ተቆርጧል እጂግ ልብን የሚሰብር ሀዘን ነበር። የሆስፒታሉ ፕሮስቴቲክ ወይም የሰው ሰራሽ እግር ሞያተኞች በአሉሚኒየም የተሠራ እግር አመጡለት እናም ከብዙ ማስጠንቀቂታያ ጋር ከሆስፒታል ወጣ።
ለመጀመርያ ጊዜ በአዲሱ ሰው ሠራሽ እግር ለመራመድ ሲውተረተር እንደ ጐማ ተጠቅልሎ ነበር የወደቀው ።ከዚያች ሰከንድ በኋላ ዳግመኛ እንዲህ አይነት ቅብጠት እንደማያዋጣ ገባው ።ዶክተሮቹ በቀን ሁለት ጊዜ ያውም ብዙ ነገር እየተደገፈ እዲሞክር ቢያዙትም እርሱ አሻፈረኝ ብሎ ከደንቡ ውጪ ልራመድ ሲል ነው ዋጋውን ያገኘው። ፊሊፕ የተባለው ይህ ጀብደኛ ጕረምሳ ጭራሹኑ የእግሩን መቆረጥ አላምንም ማለቱ ነበር በጊዜው ብዙውችን ግራ ያጋባው ።የእጮኛው አባት አይዞህ ፊሊፕዬ እስክትለምደው ድረስ ነው ከትንሽ ጊዜ በኋላ ትቀበለዋለህ አለው።እርሱ ግን የእግሩን አለመኖር ማመን አልቻለም ።ከንፈሬን በንዴት ነከስኩት ይላል ፊሊፕ ።እውነቱን ነው ማንም ሰው በሚረዳበት አረዳድ ከወሰድነው እግሬ ተቆርጧል ብዬ ከማመን ውጪ አማራጭ የለኝም ግን ይህንን የማይመች የአሉሚኒየም ቱቦ አድርጌ መሮጥ መዝለል ውሃ ላይ ወጫወትን ተከልክዬ መኖርን ማመን አልፈለኩም አለ ፊሊፕ ካለ ደግሞ ምን ማድረግ ይቻላ
ል ያዋጣህ ከማለት በስቲያ።
ፊሊፕ የራሤን ቆራጣ የምቀጥለው እኔው እራሴው ነኝ አለ። ሰውን ጨረቃ ላይ ማውጣት ከቻሉ ቆንጆ የሚያስሮጥ የሚያስዘልል እግር መስራት እንዴት ያቅታል ? ብዬ ጠየኩ። ጥያቄው ግን ቆንጆ ጥያቄ አይደለም ልበል? ይህ ከፍተኛ ፈጠራን ፍጹማዊ ለውጥን በዚህ ሞያ መፍጠሩ ግልጽ ነው ግን እንዴት ይተግበር ? ቀስ በቀስ እንዴት አልቻሉም ከሚለው ጥያቄ እንዴት አልቻልኩም ወደሚል ድምዳሜ የደረሰው ፊሊፕ የራስን ቆራጣ እኔ ብቻ ነኝ የመቀጠል ጥያቄ ያለኝም መልሱን ለመመለስ መጨነቅ ያለብኝም እኔ ነኝ አለ።
የፊሊፕ እየተማረ ያለው ጋዜጠኝነት ነው የፕሮሥቴቲክ ኢንጂነሪንግ ወይም ጐዶሎ አካልን የመተካት ምህንድስና ትምህርት ቺካጐ ኖርዝዌስት ዩኒቨርስቲ ይሰጣል እንደውም ከምርጦቹ አንዱ ነው። ስለዚህም ፊሊፕ የራሡን ቆራጣ ለመቀጠል ወደዚሁ ዩንቨርስቲ ገባ።
ፊሊፕ ዩንቨርስቲ ገብቶ ለመምህርነት የመረጣቸው እንስሳትን ነበር ካንጋሮ የተባለች ልጆችዋን ሆድዋ ውስጥ የምትደብቅ የአውስትራልያ የዱር እንስሳ አቦሸማኔ የተባለው ፈጣን እሯጭ ታላላቆቹ መምህራኖቹ ሆኑ። እግር ከሰራሁ አይቀር ለምን የአቦሸማኔ እግር አልሰራም ? አለ ፊሊፕ። እንዳለውም አልቀረ ከብዙ ሙከራ በኋላ የፈጣን እንስሶች ምስጢር ተገለጠለት ፕሮፌሰር አቦሸማኔ አስተማረው።ከዚህ በኋላ የፊሊፕ ጥያቄ ለምን ከማእድናቱ መካከል ምርጥ ብረት እግርን መተካት አይችልም ? የአቦ ሸማኔ የዃላ እግር ምን አይነት ቅርጽ ነው ያለው ? ደጋን ቅርጽ ፍጥነትን ለመጨመር የተመረጠ ይሆንን ? እያለ ሲጠይቅ ሲጠይቅ ሲመልስ ሲቀልስ ብዙውን ዓመታት ጥያቄ ብቻ ተማረ።ለምን? እንዴት ይሆናል ? ብረቶችን ሁሉ ሞከረ ጠንካራው የሚለመጠው የቱ መአድን ነው? ይገርማል ፊሊፕ ሥራውን ሲጀምር የነበረው ጥያቄ ብቻ ነበር አሁን ግን ብዙ መፍግትሄዎችም አግኝቷል።
ከእለታት በአንዱ ቀን ፊሊፕ መልሱን አገኘው ቆራጣውን ቀጠለ በደጋን ቅርጽ የሰራው ፊሊፕ ሠራሽ የብረት እግር ላይ ቆመ ተራመደ ሮጠ ። ይህ አይበሬ ሰው በፕሮስቴቲክ ሞያ አብዮት አፈነዳዳ በነገራችን ላይ አብይት ማለት ያለውን ማጥፋት ሳይሆን ባለው ላይ መጨመር አዲስ ግኝት በፈልሰፍም ነው።
ፊሊፕ በልምድ ታላቅ ነገርን አግኝቷል ይኸውም ጥያቄን ነው።ለምን የሚለው ጥያቄ ችግሮችን እንድንጋፈጥ ይጠቅመናል ለምን ሰውች አልሞከሩትም? ለምን ሁኔታው አልተቀየረም ? ሌላው ጥያቄ ደግሞ እንዲህ ቢሆንስ ?ይህ ደግሞ ጥያቄውችን በተለያየ አቅጣጫ እንድንመረምር የሚያመለክት ነው። የመጨረሻው እንዴት ይሠራ የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነገሩን ከፍጻሜ ያደርሰዋል።
የሰው ልጅ መሰረተዊ እውቀቱ ጥያቄ መጠየቁ ነው። አንድ ጥናት እደጠቆመው ፧ አንዲት ሕጻን 300 ጥያቄውችን በቀን ትጠይቃለች ስለዚህ ሰውን ሰው የሚያደርገው ጥያቄ ነው እንበለውን? ፊሊፕ አንድ አስገራሜ መደምደሜያ ላይ ደርሷል።ተማሪውች ውጤት የሚያገኙት በመልሳቸው እንጂ በሚጠዬቁት ጥያቄ አይደለም ስለዚህም በዚህ ደስተኛ አይደለም። ለምንድነው ለጠያቂዎች ማርክ የማዮሰጣቸው? ይላል ።ነገሩ ግራ ቢያጋባም አስተሳሰቡን እርባና ቢስ ብለን እንዳናሽቀነጥረው ብዙ ምክንያቶችን ፊሊፕ ይደረድርልናል። በዓለማችን ላይ ያሉ ምሁራንን ጥያቄ ጠየኳቸው የሚያቁትን ሳይሆን በህይወታቸውዘመን ምን እንደጠየቁ።ስለዚህም ለፈጠራ ቅድመ አያቱ ለካ ጥያቄ ኖርዋል ሳይንቲስቶችን ፈላስፋዎችን የንድ ሞያተኞችን ነጋዴውችን የስነጥበብ ሰዎችን ሳይቀር ስለጥያቄ ጠየኳቸው በተለይ መምህራንን ተማሪዎቻቸው ጥያቄ እንዲያጐርፉ ዘንድ እንዲያበረታቱ አሳሰብኳቸው ይላል ፊሊፕ። ለምን ተብሎ ሲጠየቅ እኔ የተቆረጠ እግሬን የቀጠልኩት በጥያቄ ብዛት ነው ይላል።
የጥያቄ ሞያተኛው ቫን ፊሊፕ የተባለው ጠቡብ ዕንዺሕ ብሎ መጠየቍ ዐሥፈላጚ ነው ይላል ። ይህ ነገር ለምን ከዚህ በተላየ መንገድ አይሰራም? ለምን በተለየ መንገድ ይህ ግር አይታይም ወይም አይተገበርም ? እንዴት እንጀምረው ? ብዙ ተግባር ሙከራ ጥያቄ ።ስለዚህ ነገርችን ደረጃ በደረጃ በመጋፈጥ የሚፈልጉበት ውጤት ይደርሳሉ።
እስቲ ከዚህ ሁሉ ትንታኔ በህዋላ ወደራሳችን ቆራጣ እንመለስ እኛ ኢትዮጵያን በብዙ ነገሮች ተበልጠናል ።ግን ለምን ተበለጥን ብለን ለመጠየቅ እንኳን እንዳንበቃ በብዙ የውሸት መልሶች ተሞልተናል። የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ አንድ መስሪያ ቤት ውስጥ የእስታስቲክ ሥራ ይሠራ ነበር ።ተሰብስቦ የተሰጠንን ዳታ በተዋበ ቀለም አሳምረን ምንስቴሩ ሲመጡ አሳየናቸው ቡና እና ሻይ ተጠጥቶ ተሳስቀው ወደ የመጡበት ሲመለሱ የግራፉን ውስጠ ምስጢር የምናውቀው ደነገጥን።ባይገርማችሁ ዳታው ሁሉ የውሸት ነበረ ።የበላይ ባለስልጣናቱ መጠየቅ ስላቃታቸው የፈጠጡ ስህተቶችን ሳይቀር ሳያስተውሉ ሄዱ።
በአገራችን ጥያቄ ወንጀልም ነው። ትምህርት ቤት የሚጠይቁ ሕጻናት መምሕሩን አሳጣችሁ ተብለው ይገለላሉ። የበታች አለቃውን እንደውቃቢ እየፈራ የታዘዘውን ይፈጽማል ለህሊናው ባያስደስተው እንኳን ። ሌላው ቀርቶ ግደል የተባለውን ሳይቀር ይገድላል ። በሐሰት መስክር ሲባል ለምን ብሎ አይጠይቅም ።
የራሳችን ቆራጣ ብዙ ነው። እርሱን ለመቀጠል ግን ሌላው ቀርቶ ትምህርታችን የራሳችንን ጉድለት ለመሙላት ታቅዶ የተማርነው አይመስልም። ለምን አገራችን ማደግ ተሳናት ? ለምን መስማማት አቃተን ? ለምን ስደት በዛ ? ለምን በአስተዳደር ችግር ከላይ እስከታች ተጥለቀለቅን ? ለምን በፈጠራ አገራችን ወደኋላ ቀረች ? ለምን ተሸናፊዎች ሆንን ?
ታላቁ ሳይንቲስት አልበርአንስታይን ሲናገር ከሰው የተለየ አእምሮ ኖሮኝ ሳይሆን ጥያቄዎችን ይዤ ስለምቆይ ነው ብሏል ምን ማለቱ ነው ።አንድን ጥያቄ በተለያየ መንገድ በማገላበጥ በመጠየቅ በመመለስ በመቀለስ በመሞከር ሳይሳካ ሲቀር ደግሞ ወደኁላ በመመሰስ በተለየ አቅጣጫ በማየት በአዲስ ብርሃን በመገንዘብ ማለት ነው። ፊሉፕ የተቆረጠውን እግሩን ለመተካት የበለጠ ለማሻሻል ለአርባ ዓመታት ለፍቷል አሁንም ግን በጥያቄ ውሥጥ ነው ።
ፊሊፕ ለእራሱ እግር መፍትሔ ሲፈልግ ይህንን ጥያቄ ይጠይቅ ነበረ ። ይንን ሰው ሠራሽ እግር ለመፈጸም ምን ያህል ወጪ ያስፈልግ ይሆን ? ልክ እንደኔው እግራቸውን ያጡ በደሃ አገር ያሉ በቀላሉ ሌያሠሩ ይችሉ ይሆ? ለእነዚህ ምስኪናን ፈጠራዮን ይጠቀሙበት ዘንድ ለምን አልፈቅድላቸውም ? ለዚህም መልስ አግኝቷል ምንአልባትም በቅርብ ጊዜ በመላው ዓለም ያሠራጨው ይሆናል ።
እኛም ከሁሉ በፌት ምድነው ቆራጣችን ? ብለን እንጠይቅ ።ከዚያ በህዋላ የገዛ ጉዴለታችንን እንሙላ እንደ ፊሊፕ ለሌሎች እንተርፍ ዘንድ።
***********************

ከይልማ ኃይሉ

ምንጭ spirit southwest airlines April 2014

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

የገጣሚ ነብይ መኮንን እማይነትበዉ ስዉር-ስፌት

ሞክሼ የአማርኛ ፊደላት እና የባለሙያዎች ማብራሪያ

ንባብ ለሕይወት!