ዓርብ, ማርች 10, 2017

ባለቅኔው ደበበ ሰይፉ ከ1942 - 1992

ጠብቄሽ ነበረ
መንፈሴን አንጽቼ
ገላዬን አጥርቼ
አበባ አሳብቤ
አዱኛ ሰብስቤ
ጠብቄሽ ነበረ፤
ብትቀሪ ጊዜ፣
መንፈሴን አሳደፍኩ
ገላዬን አጎደፍኩ
አበባው ደረቀ
አዱኛው አለቀ፤
ብትቀሪ ጊዜ፣
የጣልኩብሽ ተስፋ
እኔን ይዞ ጠፋ፡፡
(ደበበ ሰይፉ፣ ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ፣ 1992)



በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ዓለም ውስጥ በሥነ-ግጥም ችሎታቸው አንቱ ተብለው ባለቅኔ ወደመባል ደረጃ ከደረሱ ልሒቃን /elites/ መካከል አንዱ ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውሰጥ ለረጅም ዓመታት ከማስተማሩም በላይ የኢትዮጵያን ቋንቋ በተለይም አማርኛን የሥነ-ጽሑፍና የመደበኛ ትምህርት ማካሄጃ ለማድረግ በነበረው እንቅስቃሴ ውስጥ ያበረከተው አስተዋፅኦ በእጅጉ ግዙፍ ነው። የኢትዮጵያን የሥነ-ጽሑፍ፣ የሥነ-ግጥም እና የቴአትር ጥበብን ታሪክ በማጥናትና በመመራመር ረገድ ለትውልድ አቆይቶት ያለፈው መረጃ ለዘላለም ስሙ እንዲነሳ ያደርገዋል። የአያሌ ታላላቅ ሰብዕናዎች ባለቤት የሆነውን ምሁር ዛሬ በጥቂቱ እናነሳሳዋለን። መምህሩን፣ ገጣሚውን፣ ፀሐፌ-ተውኔቱን፣ ተመራማሪውን ሰው ደበበ ሰይፉን!
ደበበ ሰይፉ ሐምሌ 5 ቀን 1942 ዓ.ም የተወለደባት እና ያደገባት ከተማ ይርጋለም ትባላለች። ይርጋለም በደቡብ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ጥንታዊ ከተሞች መካከል አንዷ ነች። ከአዋሳ ከተማ በአጭር ርቀት ውስጥ ያለችው ይርጋለም ሲዳማ ውስጥ ዝነኛ ከሆኑ ከተሞች መካከል ግንባር ቀደሟ ናት። ይርጋለም ጥንታዊት ናት። ከዚያም አልፎ ጥንት የደቡብ ኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና የልዩ ልዩ ህዝቦች መናሃርያ ነበረች። ይህች ከተማ በ1940ዎቹ፣ 50ዎቹ እና 60ዎቹ ውስጥ ከልዩ ልዩ የደቡብ ከተሞች ተማሪዎች እየመጡ የመካከለኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚከታተሉባት ማዕከል ሆና ቆይታለች። ይርጋለም ኅብረ ህዝብ ያለባት የኢትዮጵያ ምሳሌ ነች። እናም በዚህች ከተማ ውስጥ ተወልዶ ያደገው ደበበ ሰይፉ ለኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ሰፊ ብርሃን ሰጥቶ ያለፈ የኪነት ፀሐይ ነበር።

ደበበ ሰይፉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ በኮከበ ጽባሕ ት/ቤት ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ቀድሞ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ከሚታወቀውና በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት ሥነ-ጽሑፍን መማር ጀመረ። ከዚያም በ1965 ዓ.ም ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ማዕረግ ተመረቀ። ቀጥሎም በዚያው በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሥነ-ጽሑፍን ማስተማር ጀመረ።
እንደ ደበበ ሰይፉ ያሉ መምህራን በዚህ ትምህርት ክፍል ውስጥ መቀላቀል ሲጀምሩ ዲፓርትመንቱም እያደገና እየተስፋፋ የመጣበት ዘመን እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ምክንያቱም የጥናትና የምርምር ውጤቶች በስፋት መሠራት ጀመሩ።
ለምሳሌ ደበበ ሰይፉ የኢትዮጵያ የሥነ-ግጥም እና የሥነ-ጽሁፍ ታሪክን እና በዚህ ታሪክ ውስጥ ደግሞ ኪነታዊ አስተዋፅኦዋቸው ሰፊ የሆነውን ጐምቱ አበው ፀሐፊያንን ታሪክና የአፃፃፍ ቴክኒካቸውንም ጭምር እያጠና ማቅረብ ጀመረ። ያለፈው የጥበብ አሻራ ለመጪው ጥበብ የሚያቀብለውን መረጃ እየወሰደ ትውልድን በጥበብ ማስተሳሰር አንዱ ተግባሩ ነበር።
የአንዲት ሀገር ማንነት ተቀርጾ ከሚኖርባቸው ጉዳዮች ዋነኛው ሥነ-ጽሁፍ ነው። በሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ደግሞ ታሪክ አለ፣ ሥነ-ግጥም አለ፣ ቴአትር አለ፣ ፍልስፍና አለ፣ አስተሳሰብ አለ፣ ፖለቲካ አለ፣ ህዝብ አለ፣ ኧረ ብዙ ብዙ ነገሮች አሉት። ደበበ ሰይፉ ደግሞ እነዚህን የኢትዮጵያን የማንነት መገለጫዎች ከጥንታዊ ሰነዶች ውስጥ እየፈተሸ በማውጣት ትውልድ እንዲህ ነበር፣ እንዲህም ኖሯል፣ እንዲህም አስቧል …. እያለ የዘመን ርቀታችን እንዳያለያየን ከትውልዶች ጋር ያገናኘን ነበር። ደበበ በስነ-ጽሁፍ ውስጥ የትውልድ የመሸጋገሪያ ድልድይ ሆኖ አገልግሏል።
ደበበ ሰይፉ በቀላል አነጋገር ሐያሲ ነበር። ሐያሲ ታሪክ አዋቂ ነው። ያለፈውን ከአሁኑ ጋር እያነፃፀረ የሚያስረዳ፣ የሚተነትን ባለሙያ ነው። የሒስ ጥበብን ደግሞ እንደ ሙያ ከታደሉት ሰዎች መካከል ደበበ ሰይፉ አንዱ ነው። በኢትዮጵያ የዘመናዊ ሂስ ጥበብ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ሰው ቢኖር አንዱ ደበበ ሰይፉ ነው።
ደበበ ገጣሚ ነው። በአገጣጠም ችሎታው ውብ እና ማራኪነት የተነሳ ብዙዎች ባለቅኔው ደበበ ሰይፉ እያሉ ይጠሩታል። ይህ በስነ-ግጥም ዓለም ውስጥ የተሰጠው ፀጋ ከሌሎች ጉዳዮች ሁሉ ገዝፎ የሚነገርለትም ነው። ደበበ ሲነሳ ገጣሚነቱ አብሮ ብቅ የሚልለት የጥበብ ሰው ነው። እነዚህን የግጥም ትሩፋቶቹን በ1980 ዓ.ም የብርሐን ፍቅር በሚል ርዕስ ሰብስቦ አሳትሟቸዋል። በዚህች የብርሐን ፍቅር በተሰኘችው የሥነ-ግጥም ስብስቡ መፅሐፍ ውስጥ ቀደም ሲል በተማሪነት እና በአስተማሪነት ዘመኑ ሲፅፋቸው የነበሩትን ግጥሞች የምናገኝበት ድንቅ መፅሐፉ ነች።
ከዚህች መፅሐፉ በተጨማሪ በ1992 ዓ.ም በሜጋ አሳታሚ ድርጅት አማካይነት ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ በሚል ርዕስ ሁለተኛዋ የሥነ-ግጥም መፅሐፉ ለንባብ በቃች። ነገር ግን በዚህ ወቅት ደበበ በሕይወት የለም ነበር። ስራዎቹ ዘላለማዊ ናቸውና እርሱ በህይወት በሌለበት ወቅትም የትውልድ ሀሴት በመሆናቸው ይታተሙለታል። እናም ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ በምትሰኘው መፅሐፉም የደበበን የሥነ-ግጥም ርቀት እና ጥልቀት የምናይበት ሥራ ነው። ለዚህች ለደበበ መፅሐፍ አጠቃላይ ገፅታዋን በተመለከተ አስተያየት የፃፈው ታዋቂው ወገኛ እና የደበበ ጓደኛ የሆነው መስፍን ኃብተማርያም ነው። መስፍንም ስለዚህችው መፅሐፍ የሚከተለውን ብሏል።
“ደበበ ሰይፉ በርዕስ አመራረጡና በሚያስተላልፋቸው ልብ የሚነኩ መልዕክቶች ብቻ ሳይሆን በስንኞቹ አወራረድና የቤት አመታቱ በአጠቃላይ በውብ አቀራረቡ ተደራሲያንን የሚመስጥ ገጣሚ ነው። ስለ ተፈጥሮ ሲገጥም ፀሐይና ጨረቃ፣ ቀስተ ደመናና የገደል ማሚቶ ያጅቡታል። ስለ ፍቅር ስንኞች ሲቋጥር የፍቅረኞችን ልብ እንደ ስዕል ቆንጆ አድርጐ በቃላት ቀለማት ያሳያል። ክህደት ላይ እንደ አንዳንድ ገጣሚያን አያላዝንም። ይልቁንም ውበትና ህይወትን አገናዝቦ ያውላችሁ ስሙት፣ እዩት፣ ማለትን ይመርጣል። ….. እኔ እንደማውቀው ደበበ ሰይፉ በገጣሚነቱ ሁሌም ዝምተኛ ነው። አይጮህም። ጮሆም አያስበረግግም። ይልቁንስ ለዘብ ለስለስ አድርጐ “እስቲ አጢኑት” ይለናል። ደግመን እንድናነብለት የሚያደርገንም ይኸው ችሎታው ነው።” በማለት የወግ ፀሐፊውና ጓደኛው መስፍን ሐብተማርያም ደበበን ይገልፀዋል።
ደበበ ሰይፉ በስነ-ግጥም ተሰጥኦው እና በሚያነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ጐልቶ ከሚነሱ ከያኒያን መካከል አንዱ መሆኑን ቀደም ያሉት ሃያሲያን ጽፈውታል።

የደበበ ችሎታ በዚህ ብቻም አያበቃም። ደበበ የቴአትር ጥበብ መምህር ከመሆኑም በላይ በዘርፉ ውስጥ ግዙፍ የሚባል አስተዋፅኦ አበርክቶ አልፏል። ደበበ በመድረክ ላይ የሚሰሩ ቴአትሮችን እና የቴአትር ፅሁፎችን የያዟቸውን ሃሳቦች በመተንተን እና ሒስ በመስጠት ለዘርፉ እድገት የበኩሉን ሚና ተጫውቷል። ደበበ የቃላት ፈጣሪም ነው። ለምሳሌ በቴአትር ዓለም በአጠቃላይ በሥነ-ጽሑፉ ዓለም ውስጥ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መጠሪያ የሆኑ ሙያዊ ቃላትን ወደ አማርኛ በማምጣት አቻ የሆነ የአማርኛ ትርጉም በመስጠት ይታወቃል። በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ እስከ አሁን ድረስ መጠሪያ የሆኑትን ለምሳሌ ገፀ-ባህሪ፣ ሴራ፣ መቼት፣ ቃለ-ተውኔት ወዘተ እየተባሉ የሚገለፁትን መጠሪያዎች የፈጠረው ደበበ ሰይፉ ነው።
-    Character የሚለውን የእንግሊዝኛ መጠሪያ “ገፀ-ባህሪ” በማለት አቻ ትርጉም ሰጥቶታል፣
-    Sefting የሚለውን የእንግሊዝኛ መጠሪያ በውስጡ ጊዜ እና ቦታን መያዙን በመረዳት ወደ አማርኛ ቋንቋ ‘መቼት’ ብሎ ደበበ ተረጐመው። መቼት ማለት ‘መች’ እና ‘የት’ ማለት ሲሆን፤ ጊዜንና ቦታን ይገልፃል።
-    Dialogue የሚለው የእንገሊዝኛ ቃል ተዋናዮች በትወና ወቅት የሚናገሩት ሲሆን፤ ይህን Dialogue የተሰኘውን ቃል ወደ አማርኛ አምጥቶት ቃለ-ተውኔት በማለት የተረጐመው ደበበ ሰይፉ ነው።
ደበበ እነዚህንና ሌሎችንም ሥነ-ጽሑፋዊ ቃላትን በመፈጠር በትውልዶች አንደበት፣ አእምሮ እና ብዕር ውስጥ ለዘላለም እንዲኖር ያደረገ ጥበበኛ ነው።
ደበበ ሰይፉ ለዚሁ ለቴአትር ትምህርት ዘርፍ ካበረከታቸው አስተዋፅኦዎች መካከል ለትምህርቱ መጐልበት ይረዳ ዘንድ በ1973 ዓ.ም መፅሐፍም አሳትሟል። መፅሐፏ የቴአትር ጥበብ ከፀሐፌ-ተውኔቱ አንፃር የምትሰኝ ርዕስ የያዘች ሲሆን፤ ለሀገራችን የቴአተር ሙያተኞች እንዲበራከቱ እና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ሰፊ ድርሻ አበርክታለች። ደበበ በዚሁ በቴአትር ዘርፍ ውስጥ የተፃፉ የንባብ መፅሐፍት ያለመኖራቸውን ክፍተት ተገንዝቦ ያንን ክፍተት ለመሙላት ሙያዊ ጥሪውን የተወጣ ባለሟል ነው።
ደበበ ሰይፉ ፀሐፌ - ተውኔትም ነው። በርካታ ተውኔቶችን ፅፎ ለመድረክ አብቅቷል። አንዳንዶቹ ደግሞ ለምሳሌ ክፍተት የተሰኘው ተውኔቱ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለበርካታ ጊዜያት ታይቶለታል። በዚህ ክፍተት በተሰኘው የደበበ የቴሌቭዥን ድራማው ላይ በመተወን ተፈሪ ዓለሙ፣ አለማየሁ ታደሰ እና ሙሉአለም ታደሰ ድንቅ የሆነ ብቃታቸውን አሳይተውበታል።
ደበበ ሰይፉ ከፃፋቸውና ከተረጐማቸው ተውኔቶች መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡-
  1. ከባህር የወጣ ዓሣ
  2. እናትና ልጆቹ
  3. እነሱ እነሷ
  4. ሳይቋጠር ሲተረተር
  5. የህፃን ሽማግሌ
  6. ማክቤዝ እና
  7. ጋሊሊዮ ጋሊሊ ይገኙበታል።
ከእነዚህ ሌላም በ1973 ዓ.ም ማርክሲዝምና የቋንቋ ችግሮቹ የሚል መፅሐፍ ከማሳተሙም በላይ በ1960 ዓ.ም ያዘጋጃት የሦስት አጫጭር ልቦለዶች መድብል የሆነችው ድርሳኑ ትጠቀሳለች።
ደበበ ሰይፉ ከእነዚህ ከረቀቁ እና ከመጠቁ ምሁራዊ አስተዋፅኦው በተጨማሪ በበርካታ ኪነ-ጥበባዊ ጉዳዮች ላይም አሻራውን ያሳረፈ ነው። ለምሳሌ በቀድሞው ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ መስፋፋት እገዛው ሰፊ ሆኖ ኖሯል። በኢትዮጵያ ሬዲዮ ውስጥም የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ውስጥ ያሉትን ፕሮግራሞች አማካሪ ሆኖ ሰርቷል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የቋንቋዎች ተቋም ጆርናል አሳታሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆኖ አገልግሏል። ደበበ ሰይፉ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዚደንት ሆኖ ሰፊ ድርሻ አበርክቷል። ደበበ ሰይፉ በኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ዓለም ውስጥ ትልቅ ድርሻውን አበርክቶ ያለፈ የትውልድ ምሳሌ ነው።
ግን ሁሉም ነገር እንዳማረበት እስከ መጨረሻው አይሄድም፤ እናም ደበበ በዙሪያው ባሉ ሰዎች በሚያውቃቸው ሰዎች ተበሳጨ። ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ ከቤት ዋለ። ታመመ። መናገርም አቆመ። ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ በአጠቃላይ ለኪነ-ጥበቧ እድገት የአንበሳውን ድርሻ ያበረከተው ደበበ ሰይፉ ሚያዚያ 16 ቀን 1992 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ቀብሩም ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ-ክርስትያን ተፈፀመ።
ስለ ደበበ ሰይፉ ምን ተፃፈ?
“ደበበ ሰይፉ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዝዳንት ሆኖ ከ1978 እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ሰርቷል። ከዚህም በላይ በወቅቱ አያሌ የሙያው ባለቤቶች እንዲሰባሰቡ አድርጓል። ከውጭ ሀገር በተለይም ከሶቭዬት ኅብረት ጋር ሙያዊ ድጋፍና ትብብር እንዲደረግ አድርጓል። አንጋፋው ደራሲና ሃያሲ አቶ አስፋው ዳምጤ በአንድ ወቅት ስለ ደበበ የህይወት ታሪክ ለሚያጠናው ተማሪ፣ ለተክቶ ታደሰ በሰጡት ቃለ-ምልልስ እንዲህ ብለዋል።
“ደበበ ስራ ይወዳል ስራው ጥንቅቅ ያለ ነው። ግን ሰዎችን ለመጋፈጥ ድፍረት ያንሰዋል። ለቴአትር ዲፓርትመንት ከመከፈቱ ጀምሮ መጽሐፍ ጽፎላቸዋል። ፅንሰ ሃሳቡን እንዲረዱት አድርጓል። ስለ ደበበ ካስደነቁኝ አንዱ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታው ነው። የደራሲያን ማኅበር ሊቀመንበር ሆኖ እኔ ስራ አስፈፃሚ ሆነን ሠርተናል። ቀድሞ ከነበረው የማኅበሩ የሥራ ዘመን ያልታየ እንቅስቃሴ ደረገ” የሚሉት አቶ አስፋው “እነሆ” የምትሰኘው የአጫጭር ልቦለዶች መድብልና “ብሌን” የተሰኘችው መጽሔትም መታተሟን ያስረዳሉ። “የጽጌረዳ ብዕር” የሚል የግጥም መድብል መታተሙንም አስረድተው የደበበን ጥንካሬ ገልፀዋል።
ታዋቂው የወግ ፀሐፊ መስፍን ኃ/ማርያም ደግሞ ለአጥኚው እንዲህ ብሎ ነግሮታል። “ደበበ በጣም ጠንካራ፣ ትጉህ ሠራተኛ፣ ለተሰለፈበት ዓላማ ወደኋላ የማይል፣ በማስተማር ደበበ innovator /ፈጣሪ/ አይነት ነበር። የምናስተምረውን ኮርስ እንዲህ ብናደርገው፣ እንዲህ ብንለው እያለ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንድናሻሽል በማድረግ በኩል ፈር ቀዳጅ ነበር።…. ደበበ ደራሲ ብቻ አይደለም። ጥሩ የማስተማር ችሎታ ነበረው” ብሏል።
ደራሲ ታደለ ገድሌም ሚያዚያ 29 ቀን 1992 ዓ.ም በወጣው “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ላይ “ደበበ ሰይፉና ስራዎቹ ሲታወሱ” በሚለ ርዕስ ስለዚሁ ታላቅ ሰው አስነብቦናል።
ይህች ከተማ ነሐሴ 5 ቀን 1942 ዓ.ም ደበበን ያህል ታላቅ የኪነ-ጥበብ ሰው አፍርታለች። አባቱ በጅሮንድ ሰይፉ አንተን ይስጠኝ እና እናቱ ወ/ሮ የማርያምወርቅ አስፋው የኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ዋልታ ያቆሙት በዚህች ምድር ነው። ደበበ ሰይፉን! ይርጋለም ከተማ ውስጥ።
“ይርጋለም
ዋ… ይርጋለም
የልጅነቴ ህልም ቀለም
ዓይኔን የከፈትሽው ጨረር
ወርቃማይቱ ጀንበር” ብሎ ደበበ ፅፎታል።
ዛሬ በህይወት የሌለው የስነ-ጽሁፍ መምህሩ ብርሃኑ ገበየሁ ትዝ አለኝ። ስለ ደበበ ሰይፉ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ሲፅፍ እንዲህ ብሏል። “የደበበ አቀራረቡ ቀላልና የማያሻማ ነው። ድምፀቱ ደግሞ ሐዘን ከሰበረው ልብ የሚፈልቅ እንጉርጉሮ። የአቀራረብ ቀላልነት ውበቱ ነው። ይርጋለምና ልጅነቱ በተናጋሪው ህሊና አንድም ሁለትም ናቸው፤ የማይፈቱ” ብሏል። እናም ይርጋለም ደበበ ሰይፉ ናት!
ሌላኛው የስነ-ጽሁፍ መምህር የሆነው ወዳጄ ገዛኸኝ ጌታቸው፣ ደበበ ሰይፉ እንዳረፈ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር። “ዛሬ የኢትዮጵያ ስነ-ጽሁፍ አንድ ለጋ ብዕር አጣ፤ ነጥፎ አይደለም ታጥፎ ነው። ዛሬ የኢትዮጵያ ስነ-ጽሁፍ የዋህ ሃሳብ አጣ። ከፍቶ አይደለም በኖ ተኖ እንጂ። ዛሬ ብዙዎቻችን ካወቅነው ብዙ ነገር አጣን። ካላወቅንም እሰየው፤ ከእንጉርጉሮና ከፀፀት ተረፍን” ብሏል።
ጋዜጠኛ መሠረት አታላይ በፈርጥ መጽሔት ላይ “ለኪነ-ጥበብ ተፈጥሮ ለኪነ-ጥበብ የሞተ” በሚል ርዕስ የደበበን ጓደኞች ዶ/ር ፍቃደ አዘዘን፤ መስፍን ኃ/ማርያምን እና አስፋው ዳምጤን ቃለ መጠይቅ አድርጐ ጽፏል። ሁሉም የኪነ-ጥበብ ጋዜጠኞች ማለት ይቻላል ስለ ደበበ ጽፈዋል። በ1995 ዓ.ም ደግሞ በጀርመን የባህል ተቋም ውስጥ በወ/ሮ ተናኘ ታደሰ አስተባባሪነት ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ፣ ዶ/ር ዮናስ አድማሱ እና ገዛኸኝ ጌታቸው “የደበበ ሰይፉ ምሽት” ብለው እጅግ የደመቀ ዝግጅት አድርገዋል። ነብይ መኮንን፣ አበራ ለማ እና አብርሃም ረታ ቅኔዎች ዘርፈውለታል። የወንዙ ልጅ አብርሃም ረታ እንዲህ ገጥሞለታል፡-
ብናቀጣጥለው ኪነትክን እንደጧፍ
ስምህ ርችት ነበር
ላውዳመት እሚተኮስ
ሰማይ ላይ የሚጣፍ
ሰማይ ላይ የሚጦፍ
ሰማይ ላይ የሚጥፍ።
https://www.youtube.com/watch?v=omZPWPyU1uQ
*************************************************************
http://www.sendeknewspaper.com/arts-sendek/item/486_በጥበቡ በለጠ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ማሞ ካቻ (አቶ ማሞ ይንበርብሩ)

  አቶ ማሞ ይንበርብሩ (ማሞ ካቻ) እስቲ እናስታውሳቸው፣ ተቀብሮ እንዳይቀር አኩሪ ታሪካቸው  (ደረጀ መላኩ)   አቶቢሲ ማሞ ካቻ የት ትሄዳለህ? ገብረ ጉራቻ… ታዳጊው ማሞ ይንበርበሩ ገና በጨቅላ እድሜው አባቱ አቶ...