አማርኛችን ወዴት እየሔደ ነው?
ቋንቋ መግባቢያ ነው፡፡ ከመግባቢያነቱ ባለፈ ቋንቋ የራሱ የሆነ የአነጋገርና የአጻጻፍ ሥርዓት አለው፡፡ አንድ ቋንቋ በራሱ ለተናጋሪው ምሉዕ (የተሟላ) እንዲሆን ዘመኑን የሚዋጁ (ዘመኑ የሚወልዳቸው) ቃላት ሊኖሩት ይገባል፡፡ እኔ ምንም እንኳ የቋንቋ ተመራማሪ ባልሆንም አንድ ቋንቋ ምን ማሟላት እንዳለበት ግን እረዳለሁ፡፡ የሰው ልጅ በበርካታ ነገሮች ሊግባባ ይችላል፡፡ የሚግባባበት ሁሉ ግን ቋንቋ አይደለም፡፡ ወፎችም፣ እንስሳትም ሁሉም ይግባባሉ (የራሳቸው የሆነ መግባቢያ አላቸው) ነገር ግን ቋንቋ የላቸውም፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ሥልጣኔ ውስጥ አብራ የሰለጠነች በዘመናት መካከልም አብራ የዘመነች እንደሆነች በርካታ ማስረጃዎችን ማንሣት እንችላለን፡፡ አክሱም ሐውልትን የመሰለ ልዩ ምህንድስና ያለበት፣ ላሊበላን የመሰለ ልዩ ጥበብ የፈለቀበት፣ ልዩ የሆነውን 13 ወራት የሚይዘው የቀን አቆጣጠር ሃብታችን፣ የራሳችን የሆነው የፊደል ገበታችን ስልጣኔያችን ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር በቂ ማሳያዎቻችን ናቸው፡፡ በርካታ አገራት ፊደላትን ከሌሎች እየተዋሱ ሲጠቀሙ በነበረበት ዘመን ኢትዮጵያ ይህንን የመሰለውን የራሷ የሆነውን ብርቅየ ቋንቋ ከነፊደሉ ማዘጋጀቷ ትልቅ እና የጥበብ መፍለቂያ አገር እንደነበረች ያስረዳናል፡፡
የግዕዝ ፊደላት አማርኛ ቋንቋ ውስጥ የምንጠቀምባቸው ብቸኛ ፊደላት ናቸው፡፡ ቃላት እንደዘመናት መፈራረቅ ሁሉ ይወለዳሉ፣ ያድጋሉ፣ ይሞታሉ፡፡ ይህ ተፈጥሮአዊ የቃላት ዑደት በማንኛውም ቋንቋ ዘንድ እንደሚኖር አልጠራጠርም፤ በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ ግን አለ፡፡ አሁን አሁን ግን እየተወለዱ ያሉት ቃላት አማርኛ አማርኛ የማይሸቱ እየሆኑ በመምጣታቸው ለአማርኛ ቋንቋችን ከፍተኛ ተጽእኖን እያሳደሩ ናቸው፡፡ በቋንቋችን አፍረን ለሌላ ቋንቋ ልባችንን ከፍተን የማንነታችን መታወቂያ የሆነውን ቋንቋ በርዘነዋል፡፡ የተወሰነውን የቋንቋ ባህሪ ለሌላው በማውረስ ቃላትን የምንፈጥር አለን፡፡ ለምሳሌ እንመልከት፡- ኮምፒዩተር የሚለው ቃል እንግሊዝኛ ነው እኛ እንደአማርኛ ኮምፒዩተሮች እያልን አናረባዋለን፡፡ አበበ የኮምፒዩተርና ኤሌክትሮኒክስ መሸጫ መደብር ብለንም ማስታወቂያ እንሰራለን፡፡ የእንግሊዝኛ ቃላትን ከአማርኛ ቃላት ጋር በማጣመርም ቃል የፈጠርን የሚመስላቸው ሞኞች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡ መስከረምባርና ሬስቶራንት፣ ፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ፣ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ፣ ሬጅስትራር ጽ/ቤት፣አርቲስት እገሌ፣ ኢንጅነር እገሌ፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የፋይናንስ አስተዳደር፣ የኮምፒዩተርናኤሌክትሮኒክስ መሸጫ መደብር አረ ስንቱ፡፡
በአማርኛ ፊደል መጻፉ ብቻ አማርኛ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ ይኼ ደግሞ በፍጹም ኢትዮጵያዊነት ባህሪ የጎደለው ግድየለሽነት ነው፡፡ በዚህ የምንቀጥል ከሆነ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ፊደላችን ብቻ ሊቀር እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ እንግሊዝኛን ከአማርኛ ጋር ቀላቅሎ መናገር ትልቅነት የሚመስላቸው በርካታዎች ናቸው፡፡ እንግሊዝኛ ማለት አማርኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ፣ ጣልያንኛ ወዘተ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ቋንቋዎች፣ መግባቢያዎች ስለሆኑ፡፡ አለቀ፡፡ ማግባባት ከቻለ የእኛው አማርኛ ምኑ ላይ ነው ድክመት ያለበት? የተለያዩ ቋንቋዎችን መቻል በጣም ጥሩ ነው ደስም ይላል፡፡ ምክንያቱም ብዙ እውቀት ልናገኝበት የምንችልበትን እድል ስለሚከፍቱ፡፡ ነገር ግን አንዱን ከአንዱ ጋር እየቀላቀሉ መናገርም ሆነ መጻፍ አላዋቂነት ነው፡፡
በተለያዩ ቦታዎች የተጻፉ ማስታወቂያዎችን ልብ ብላችሁ ታውቃላችሁ? አንድ ከተማ ውስጥ ግቡ እና ማስታወቂያዎችን ተመልከቱ ሙሉ አማርኛ አታገኙም፡፡ እኔ ባለሁበት አካባቢ ጥቂቶችን ልግለጽላችሁ፡፡ ጎዛምን ሆቴል፣ ኤፍ. ኤም ኢንተርናሽናል ሆቴል፣ ስታር ቢዝነስ ግሩፕ፣ ፎቶ ስታር፣ ፓራዳይዝ ሕንጻ፣ አበበ የኮምፒዩተርና ኤሌክትሮኒክስ መሸጫ መደብር፣ማርታ ጁስ መሸጫ ወዘተ ዘርዝሬ መግለጽ አልችልም በእርግጥ፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም የዚህ ሰለባዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ፋይናንስና ግዥ አስተዳደር፣ የታክስናኦዲት ባለስልጣን፣ የፌዴራል ኦዲተር፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት፣ ዳይሬክተር፣ ዲፓርትመንት ሄድ፣ ምርጫ ቦርድ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ወዘተ … እነዚህ ሁሉ በአማርኛ የተጻፉ በአማርኛ የቃላት እርባታ እንደአስፈላጊነቱ እየረቡ ያሉ ናቸው፡፡ ለነገው ትውልድ ምንድን ነው የምናወርሰው? ይህን የተበረዘ አማርኛችንን ነው? የመንግስት ተቋማትስ ምን እየሰሩ ነው? የአማርኛ ትምህርት ክፍልስ ምን አይነት መምህራንና ተማሪዎችን እያፈራ ነው? መቼ ይሆን በራሳችን ፊደል የራሳችንን ቋንቋ ብቻ የምንጽፍበት? ሁኔታው አሳሳቢ ነው፡፡ አንድ ደብዳቤ ምን ያህል የእንግሊዝኛ ቃላትን በአማርኛ ፊደላት እንደተጠቀመ በየአጋጣሚው የሚጻፉ ደብዳቤዎችን ተመልከቱ፡፡ በውኑ የአማርኛ ቋንቋ መግለጽ የማይችለው ነገር አለን? ካለስ የአማርኛ ምሁራን ሰብሰብ ብለው ለዚያ ነገር አዲስ የአማርኛ ቃልን መውለድ (መፍጠር) እንዴት ተሳናቸው? በዚህ ችግር እስከመቼ እንቆይ ይሆን?
ታዲያ መፍትሔው ምን ሊሆን ይችላል? በመጀመሪያ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ተናጋሪው በራሱ ትክክለኛውን አማርኛ መናገር አለበት፡፡ ሁለተኛም የአማርኛ ምሁራን ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በመጨረሻ መንግሥትም ትኩረት ሊያደርግበት ይገባል፡፡ ከራሱ መሥሪያ ቤቶች ስያሜ በመጀመር፡፡ የሥራ ቋንቋ አማርኛ እንዲሆን የወሰነ መንግስት የመገናኛ ብዙኃኑን (EBC) ማለቱ በጣም የሚያናድድና የሚያበሳጭ ነው፡፡ ኢብኮ- የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ‹‹ብሮድካስቲንግ - ኮርፖሬሽን›› የትኛው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ላይ ነው እነዚህ ቃላት የሚገኙት? ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት ትልቁን ድርሻ ሊወስድ ይገባዋል፡፡ ማደግ የምንችለው በራሳችን ሃብት መጠቀም ስንችል ብቻ ነው፡፡ ቋንቋችን ደግሞ ትልቁ ሃብታችን ነው፡፡ ቻይና ለማደጓ ምሥጢሩ የራሷን ቋንቋ መጠቀሟ ነው፡፡ እኛም ማደግ የምንችለው በራሳችን ቋንቋ መጠቀም ስንችል ብቻ ነው፡፡
*******************************************************************************
Melkamu Beyene/ መልካሙ በየነ _ http://melkamubeyene.blogspot.com/2015/05/blog-post_20.html
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ