ብዝኃ ጠቢቡ ነቢይ
ነቢይ ከጀርመናዊቷ ሪካ ጋር የፈጠረው ግጥማዊ ጥምረት
በዕውቀት አደባባይ ውስጥ ከዚያ ‹የግሪክ ጥበባት›› ከዚህ ‹የግእዝ ጥበባት› የሚባሉ በሰባት መደብ የተከፈሉ የትምህርትና የአዕምሮ ዕድገት መሠረት የሆኑ ትሩፋቶች አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል ለሥነ ጽሑፍ ከነጓዙ መሠረት የሆነው የቋንቋ ጥናትና አወቃቀሩ (ሰዋስው)፣ በመናገርና በመጻፍ የማሳመን ንግግራዊ ዘይቤ (ሪቶሪክ)፣ የማመዛዘንና የክርክር መርሆችን የያዘው ሎጂክ (ተጥባበ ነገር) ይገኙበታል፡፡
እነዚህ ጥበባት በኢትዮጵያ የትምህርትና የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የተዋሃዱ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ትውልዶችም እያበለፀጉ ተጉዘውበታል፡፡ በየዓረፍተ ዘመኑ የሚነሱ ሥነ ጠቢባንም ታይተዋል፡፡ በብዝኃ ጥበባት ካለፉት መካከል ከሰሞኑ ዜና ዕረፍቱ የተሰማው ገጣሚ፣ ጸሐፌ ተውኔት፣ ተርጓሚ፣ ወጋዊ ንግግር አዋቂ፣ ዜናዊ ሆኖ ያለፈው ነቢይ መኰንን ይገኝበታል፡፡ የሥዕል ሥራዎችም አሉት፡፡
ነቢይ፣ ዜናዊ ሲሉት በመጽሔትም (ፈርጥ) ሆነ በጋዜጣ (አዲስ አድማስ) በዋና አዘጋጅነት መሥራቱ ነው፡፡ ‹‹ሰው በዜና ውኃ በደመና›› እንዲሉ ዜናዊ ሆኖ ከሐበሻ ሥነ ልቡና ጋር የተያያዘውን፣ ሠርክ የማይለየውን ተረትና ምሳሌ ከነ ብሂሉ እየዘገነ የርዕሰ አንቀጽ ማንደርደሪያው ማድረጉ ከአገሩ በልዩነት የሚያስቀምጠው ነው፡፡
‹‹መጽሐፍ ከነገረው ተረት የነገረው›› የሚለውን ነባር ብሂልን ዘመኑ አሻግሮ ያመጣ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የጉዞ ማስታወሻ (ትራቭሉግ) በመጻፍና በማሳተም የሚታወቁት በጣሊያን ያደረጉትን ጉዞ በ19ኛ ምዕት ዓመት ‹‹ጦብላህታ›› ብለው በትግርኛ ባሳተሙት ደብተራ ፍሥሐዬ የተጀመረውን የጽሑፍ ዘውግ ከኢትዮጵያ እስከ አሜሪካም ሆነ በአገር ቤት የተለያዩ አካባቢዎች የቃኛቸውን በመጽሐፍ በማሳተም ነቢይ መኰንን ተጠቃሽ ነው፡፡
ነቢይ በተርጓሚነቱ በግዝፈት እንዲታይ ያደረገው በአሜሪካዊቷ ማርጋሬት ሚሸል የተጻፈውን ጎን ዊዝ ዘዊንድ (Gone With the Wind) መጽሐፉ በአቻ አማርኛ የተረጐመውና ‹‹ነገም ሌላ ቀን›› የሚል ርዕስ የሰጠው መጽሐፍ ነው፡፡ በ1970ዎቹ መገባደጃ የታተመው ይህ መጽሐፍ ቅጽ ፩ ሲሆን ተከታዩ ግን እስካሁን የኅትመት ብርሃን አላየም፡፡
መጽሐፉን የተረጐመው በኢሕአፓ (የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ) አባልነቱ ዘብጥያ ወርዶ ለ10 ዓመታት ያህል በኖረበት ከርቸሌ ነው፡፡ ገጸ ታሪኩ እንደሚያሳየው ይጽፍ የነበረው በሲጃራ ፓኮዎችና በብጥስጣሽ ወረቀቶች ላይ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ይታይ የነበረው የ18ኛው ምዕት ዓመት ጀርመናዊ ደራሲ ጎትሆልድ ኤፍሬም ሌሲንግ የእንግሊዝኛውን ‹‹Nathan the Wise›› ወደ አማርኛ ‹‹ናትናኤል ጠቢቡ›› ብሎ የተረጐመው ነቢይ ነው፡፡
በ1779 የተጻፈው የሌሲንግ ናታን ዴር ዋይዝ›› (ጠቢቡ ናታን) በብዙ ቋንቋዎች የተተረጐመና ተደናቂነትን ያተረፈ፣ ሦስቱ አብርሃማውያን የአንድ አምላክ አማኞች (አይሁድ፣ ክርስትና እና እስልምና) በአምላክ ፊት በእኩልነት የቀረቡበት የመቻቻል አስፈላጊነት የተንፀባረቀበት እንደሆነ ይወሳል፡፡
ሌላው ለንባብ የበቃው የነቢይ መጽሐፍ ‹‹የመጨረሻው ንግግር›› የተሰኘ ሲሆን ‹‹ዘ ላስት ሌክቸር›› የሚለው መጽሐፍ ትርጉም ነው።
ነቢይን ያስተዋወቀው ሌላው ትልቁ ሥራው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተላለፈው ‹‹ባለ ጉዳይ›› የተሰኘው አስቂኝ አሽሙር ተውኔት ነው፡፡
ተውኔቱ በአገሪቱ የተንሠራፋውን የቢሮክራሲ ውጣ ውረድና ጉቦኝነትን ያሳያል፡፡ ዋና ገጸ ባሕሪው ‹‹ቀናው ተበጀ››ን ሁኖ የተወነው ፍቃዱ ተክለማርያም ከነአበበ ባልቻ፣ ፍቅርተ ጌታሁን ጋር ነበር፡፡ የብዙዎችን ቀልብ የገዛ በተደጋጋሚ የታየ ተውኔት ሆኖ ባጅቷል እሱም በተዋናይነት ተሳትፎበታል፡፡ በባለካባና ባለዳባ ተውኔትም እንዲሁ፡፡
በምድረ ዓለም ተስፋፍቶ የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈው ኤችአይቪ ኤድስ፣ በኢትዮጵያ በአሳሳቢ ደረጃ በነበረበት ጊዜ ኅብረተሰቡን ማስገንዘቢያ ‹‹ማለባበስ ይቅር›› የተሰኘ የኅብረ ዝማሬ ግጥም ነቢይ ደርሷል፡፡ በሬዲዮም ሆነ በቴሌቪዥን በታዋቂ ወጣት ድምፃውያን አማካይነት ቀርቧል፡፡
ነቢይ ተርጓሚነቱ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ብቻም አይደለም፡፡ ከአማርኛ ወደ እንግሊዝኛ የተረጐማቸው ከሥነ ቃል እስከ ታዋቂ ገጣሚዎች (ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ ከበደ ሚካኤል፣ ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ፣ ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ (ገሞራው)፣ በዕውቀቱ ሥዩም፣ በፍቃዱ ሞረዳ ወዘተ) ሥራዎች ይገኙበታል፡፡ ለዓይነት ያህል እነሆ፡-
‹‹ልዩ ኃይል አግኝቶህ፣ እስክታገኝ ዋጋ
በነፍስ አትጫወት፣ ተው ሥጋ ተው ሥጋ››
– (ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ/ ገሞራው)
O fleshy flesh!
Till some unique force comes,
that can make you worthy;
Play not on your soul
till change engulfs thee.
***
ድህነት ይገልበጥ
ባፍጢሙ ይደፋ
ደኻ ግን ይበርክት
ፍቅር እንዳይጠፋ።
– (በፈቃዱ ሞረዳ)
Down with poverty
be it crushed to ash
But let the poor flourish
so that their love cherish!
so that their love nourish!
***
ወንድሙን ሲገድሉት፣ ወንድሙ ካልከፋው
ደጁ ላይ ቅበረው፣ ደሙ እንዲከረፋው።
– (ሥነ ቃል)
If he pays no hid
nor if he is not dismayed
when his brother is slaughtered and killed.
Bury the dead affront, right there at his gate
so that it stinks
and irritates him straight!
በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ የማዘጋጃ ቤት ‹‹ጁሊያስ ቄሳር›› የተሰኘ ትርጉምና በዚያው መድረክ ‹‹ማደጎ›› የተሰኘ ወጥ ሥራው ቀርቦለታል፡፡
ነቢይ ከሁሉም የጥበባት ዘርፎች ‹‹የድርሰት ንጉሥ›› የሚያደርገው ግጥም ነው፡፡ በርካታ ግጥሞች አሉት፡፡ በመጽሐፍም በጋዜጣም፣ በመጽሔትም በየመድረኩ ያቀረባቸው፡፡ ከታተሙት መድበሎቹ ‹‹ሥውር ስፌት›› በዓቢይነት ይጠቀሳል፡፡
ስለ ሥውር ስፌት ሒስ ያቀረበው አብደላ ዕዝራ፣ ነቢይ መኰንን ከአማርኛ ገጣሚያን የሚለየው አንድ ሁለት ሳይሆን በአገር ጉዳይ ከሃያ ግጥሞች በላይ መቀኘቱ ነው ይለዋል፡፡ ‹‹ሀገርህ ናት በቃ!›› ላይ እንዲህ ተቀኝቷል ነቢይ፡-
ይቺው ናት ኢትዮጵያ…
ይቺው ናት ዓለምህ፣
ብቻዋን የተኛች ከዓለም ተደብቃ!!
አኪሯ ቀዝቅዞ፣
‹‹ያንቀላፋች ውቢት›› ያንተው የክት ዕቃ…
ምን ትሆን እንግዲህ ሀገርህ ናት እሷ!
ልቧን አታውልቃት አትጨቅጭቃት በቃ፣
አብረህ አንቀላፋ፣ ወይ አብረሃት ንቃ!
ነቢይ ኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮናዎች በመጡ ቁጥር ኢትዮጵያውያን ድልን ሲቀዳጁ ውዳሴ ከማቅረብ፣ ከመቀኘት አልተቆጠበም፡፡ የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮኗ ጥሩነሽ ዲባባ ድርብ ድል በተቀዳጀች ጊዜ ‹‹ነገር የገባት ሰጎን›› የተሰኘ በተለያዩ ዓመቶች ቁጥር 1 እና 2 አድርጎ አስነብቧል፡፡
ግጥሞቹ በተለያዩ ቋንቋዎች የተተረጎሙለት ነቢይ በጀርመን በተዘጋጀ የግጥምና ጃዝ ፕሮግራም ላይ ሥራውን አቅርቧል፡፡ በተለይ ከጀርመናዊቷ ሪካ ጋር የፈጠረው የጥበብ ጥምረት እሷን ጨምሮ ብዙዎችን እንዳስደመመ ሠዓሊና ገጣሚዋ ምሕረት ከበደ በማኅበራዊ ገጿ ገልጻለች፡፡
ከአባቱ ከአቶ መኰንን ወንድምና ከእናቱ ከወ/ሮ በለጤ በድሉ በነሐሴ ወር 1946 ዓ.ም. በናዝሬት ከተማ በአሁኑ አጠራሩ በአዳማ የተወለደው ነቢይ መኰንን፣ በቄስ ትምህርት ቤት ዳዊት እስከመድገም ደርሷል፡፡
የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በዚያው ናዝሬት (አዳማ) አፄ ገላውዴዎስ ትምህርት ቤት ሲሆን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲን በተጎራበተው ልዑል በዕደ ማርያም ተማሪ ቤት ነው፡፡
በ1966 ዓ.ም. የከፍተኛ ትምህርቱን በዚያው ዩኒቨርሲቲ በሳይንስ ፋኩልቲ በመግባት ኬሚስትሪን በዋናነት ሲያጠና፣ በሁለተኛ በንዑስ (ማይነር) ደግሞ ሒሳብን ተከታትሏል፡፡
ነቢይ፣ ትምህርቱ ኬሚስትሪ ቢሆንም በሥራ ዓለም ያሳለፈው በተርጓሚነት፣ በደራሲነት፣ በኮሚኒኬሽን አማካሪነትና በጋዜጠኝነት ነው፡፡
ገጸ ታሪኩ እንደሚያሳየው፣ ሜጋ ኪነ ጥበባት ማዕከል በ1984 ዓ.ም. ሲቋቋም ከመሥራቾች አንዱ የነበረው ነቢይ፣ በጊዜው በማዕከሉ አሳታሚነት ትወጣ የነበረችውን ‹‹ፈርጥ›› የኪነ ጥበብ መጽሔትን ዋና አዘጋጅ ነበር፡፡ በተጓዳኝም በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ኮሚኒኬሽን በአማካሪነት ሠርቷል፡፡
በሕይወት ታሪኩ ላይ ነቢይ እንዲህ ተገልጿል፡-
‹‹የማይሰለች፣ ጨዋታ አዋቂው፣ ፈገግታ የማይታጣበት ነቢይ ጋዜጠኛ ብቻ አልነበረም፣ የእውነትና የግልጽነት ድምፅ ጭምር እንጂ። ጥልቅ የሆኑት የዘገባና የትንተና ሥራዎቹ የተወሳሰበውን ባህል፣ ታሪክና ፖለቲካችንን መልክ አስይዞ ፍንትው አድርጎ የማሳየት ብቃቱ ምስክሮች ናቸው። በሕይወት ዘመኑ ከፍትሕና ከእውነት ጋ ቆሞ፣ መስዋዕትነትንም ከፍሎ በመረጃ የዳበረ፣ በውይይት የጎለበተ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ነቢይ የበኩሉን ጥሯል።
‹‹ሥራዎቹ የአገራችንን ሥነ ጽሑፍ አንድ ዕርምጃ ወደፊት ለማራመድ ካገዙ ምጡቅ ሥራዎች ውስጥ የሚመደቡ ናቸው። ነቢይ አስተምሮናል፣ አዝናንቶናል፣ የውስጣችንን እሬት በማር ለውሶ አውጦናል፣ ማኅበራዊ ስንክሳሮቻችንን፣ የተሰወሩ ጉድፎቻችንን በጥበብ ብርሃን አሳይቶናል። ፀጋና ውበታችንን፣ ባህልና ትውፊቶቻችንን፣ ታሪክና አገራችንን በውብ ሥራዎቹ ከሽኖ እንደምቅባቸው ዘንድ አጎናጽፎናል። ብዙ ከያንያንንም ፈለጉን ይከተሉ ዘንድ የተምስጦ ሻማን ለኩሶላቸዋል።››
ባደረበት ሕመም ምክንያት ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በተወለደ በ70 ዓመቱ (69 ዓመት ከ11 ወር) ያረፈው ነቢይ መኰንን፣ ሥርዓተ ቀብሩ በማግሥቱ በአዳማ ናዝሬት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡ ከሥርዓተ ቀብሩ አስቀድሞ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የክብር አሸኛኘት ተደርጎለታል፡፡
ባለትዳር የነበረው ነፍስ ኄር ነቢይ መኰንን የሁለት ሴት ልጆች አባት የነበረ ሲሆን፣ ሰባት የልጅ ልጆችን አይቷል፡፡
ሞትን እናስጎምዠው!
በአንድ መድረክ ላይ ነቢይ ትውስታውን ሲወጋ እንዲህ ማለቱ ተጠቅሷል፡፡
‹‹ባንድ ወቅት ነቢይ መኰንንና ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ወጣ ብለው ለመዝናናት ወሰኑ። ታዲያ የመረጧት ቤት አንዲት አነስ ያለች ግሮሰሪ ነች፣ ከቤቱ አጠገብ የሬሳ ሳጥን መሸጫ አለ። ስብሐት አንድ አሳብ መጣበት። ሁለቱም ያዘዙትን መጠጥ የሬሳ ሳጥን መሸጫው ቤት ቁጭ ብሎ መጠጣት!
ሁለቱም በሐሳቡ ተስማምተው እየጠጡ ጨዋታ ቀጠሉ፡፡ ታዲያ ነቢይ ስብሐትን ለምን ይሄንን ቤት እንደመረጠ ጠየቀው፣ ስብሐትም መለሰለት ‹‹ሞትን እስቲ እናስጎምዠው ብዬ ነው›› አለው።››
የነፍስ ኄር ነቢይ መኰንን ዜና ዕረፍት ተከትሎ ሰይፉ ወርቁ በገጹ እንዲህ ገጠመ፡-
‹‹ግጥምም ዝም አለ። ጨዋታም ዝም አለ።
ሰው መውደድ ዝም አለ። ትሕትና ዝም አለ።
ነቢይ ያልነው ዋርካ፥ በአገሩ የት አለ!›
ነቢይ በሥውር ስፌት መድበሉ ውስጥ ‹ከሞት ጋር ተቃጥረን› የምትል ግጥም አለችው፡፡
‹‹ወትሮም እንዲህ ነው የአበሻ ቀጠሮ!
ሞት ለካ አበሻ ነው?!
ግና ምን ሆኖ ነው?
እንዴት ቢንቀኝ ነው?
እንዴት ቢፈራኝ ነው?
መንገዱ ረዘመ ወይ መንገዱ ጠፋው?
የሕይወትን አጥር፣ ዳር ዳሩን ይዞራል!
ዕድሜን ደጅ ይጠናል፡፡
ሞትም እንደ ሰው ልጅ ቀን ይጎድልበታል?
በለስ የቀናት ‘ለት
ሕይወት እንደዚህ ናት
ሞትን መገነዣ፣ ሥውር ስፌት አላት!››
***********************
ብዝኃ ጠቢቡ ነቢይ - ሪፖርተር - Ethiopian Reporter - #1 Best And Reliable News Source In Ethiopia
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ