ኢትዮጵያን ከእግዚአብሔር እጅ እንሻት
(ሰኔ ፲፱፻፺፯ ዓ. ም.) በ፲፱፻፹፫ ዓ.ም. ብዙ ሆነን ከአሰብ ተሰድደን በጅቡቲ በኩል ለማለፍ ስንሞክር የፈረንሳይ ወታደሮች አንድ ሜዳ ላይ አገቱን። እጅግ በጣም ሐሩር ስለነበር ከመንገላታት ጋር አንዳንዶቻችን በብርቱ ታመን ነበር። ከፊት ለፊቴ ቆሞ በጠላትነት አይን እያየ፣ በመሣሪያው እያስፈራራ፣ አንዳንዴም እየገፈተረ፣ መተላለፊያ የሚከለክለኝን ወጣት ፈረንሳዊ እያየሁ በሃሳብ ሰመጥኩ። እኔን የሚመስሉ ዘመዶቸ በሚኖሩበት መሬት እንዳላልፍ ከፈረንሳይ አገር መጥቶ ከለከለኝ ። መሰደዴ ደግሞ እሱን የሚመስሉ ሰዎች ባዘጋጁት ውጥን ነው። ይህ ወጣት ከሩቅ አገር መጥቶ በሰፈሬ እንዳላልፍ የከለከለኝ በጠማማ መንገድ ከሚሄድ ባለጠጋ ያለነውር የሚሄድ ደሀ ይሻላል ተብሎ እንደተጻፈው አባቱ ከሩቅ አገር መጥተው በአራጣ ብዛትና በቅሚያ የአባቴን ስለወሰዱ አይደለምን? ታዲያ ይህ ፈረንሳዊ ካባቱ አንድ ጊዜ ባገኘው አስነዋሪ ትርፍ ምክንያት የሱ ልጅ ከሩቅ አገር መጥቶ የሰው መብት ከልካይ፤ የኔ ልጅ ደግሞ በራሱ ሰፈር መብቱ የተዋረደ መሆኑ አይደለምን? ብየ አሰብኩ። ብዙ ሰው እንደዚህ አለማሰቡ መልካም ሆነ እንጂ ነገሩ መንፈስን የሚያውክ ነገር ነው። ከዚህ በሁዋላ ብዙወችን ነገሮች ሳያቸው ስለማናውቀው ነው እንጂ እኛ ፈልገን የምናመጣው የስብእና ውርደት በብዙ መልክ እንዳለ ተገነዘብኩ። እባካችሁ አገራችን ውስጥ ያለውን መንግሥት ቀይሩልን ብሎ ሌሎችን አገሮች ደጅ መጥናት እራሱ ውርደት ነው። በአገር ውስጥ፣ በቤተመንግሥቱ፣ በየመንገዱ፣ በየምግብ ቤቱ፣ በየመጠጥ ቤቱ፣ በየህዝብ አገልግሎት ተቅዋሙ የውጭ አገር ሰው ሲከበር ኢትዮጵያዊ ግን በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተንቆ ማየት ውርደት ነው። ከኢትዮጵያዊ አዋቂወች ወ...