ኢትዮጵያን ከእግዚአብሔር እጅ እንሻት


 (ሰኔ ፲፱፻፺፯ ዓ. ም.)
 
በ፲፱፻፹፫ ዓ.ም. ብዙ ሆነን ከአሰብ ተሰድደን በጅቡቲ በኩል ለማለፍ ስንሞክር የፈረንሳይ ወታደሮች አንድ ሜዳ ላይ አገቱን። እጅግ በጣም ሐሩር ስለነበር ከመንገላታት ጋር አንዳንዶቻችን በብርቱ ታመን ነበር። ከፊት ለፊቴ ቆሞ በጠላትነት አይን እያየ፣ በመሣሪያው እያስፈራራ፣ አንዳንዴም እየገፈተረ፣ መተላለፊያ የሚከለክለኝን ወጣት ፈረንሳዊ እያየሁ በሃሳብ ሰመጥኩ። እኔን የሚመስሉ ዘመዶቸ በሚኖሩበት መሬት እንዳላልፍ ከፈረንሳይ አገር መጥቶ ከለከለኝ ። መሰደዴ ደግሞ እሱን የሚመስሉ ሰዎች ባዘጋጁት ውጥን ነው። ይህ ወጣት ከሩቅ አገር መጥቶ በሰፈሬ እንዳላልፍ የከለከለኝ በጠማማ መንገድ ከሚሄድ ባለጠጋ ያለነውር የሚሄድ ደሀ ይሻላል ተብሎ እንደተጻፈው አባቱ ከሩቅ አገር መጥተው በአራጣ ብዛትና በቅሚያ የአባቴን ስለወሰዱ አይደለምን? ታዲያ ይህ ፈረንሳዊ ካባቱ አንድ ጊዜ ባገኘው አስነዋሪ ትርፍ ምክንያት የሱ ልጅ ከሩቅ አገር መጥቶ የሰው መብት ከልካይ፤ የኔ ልጅ ደግሞ በራሱ ሰፈር መብቱ የተዋረደ መሆኑ አይደለምን? ብየ አሰብኩ። ብዙ ሰው እንደዚህ አለማሰቡ መልካም ሆነ እንጂ ነገሩ መንፈስን የሚያውክ ነገር ነው። ከዚህ በሁዋላ ብዙወችን ነገሮች ሳያቸው ስለማናውቀው ነው እንጂ እኛ ፈልገን የምናመጣው የስብእና ውርደት በብዙ መልክ እንዳለ ተገነዘብኩ። እባካችሁ አገራችን ውስጥ ያለውን መንግሥት ቀይሩልን ብሎ ሌሎችን አገሮች ደጅ መጥናት እራሱ ውርደት ነው። በአገር ውስጥ፣ በቤተመንግሥቱ፣ በየመንገዱ፣ በየምግብ ቤቱ፣ በየመጠጥ ቤቱ፣ በየህዝብ አገልግሎት ተቅዋሙ የውጭ አገር ሰው ሲከበር ኢትዮጵያዊ ግን በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተንቆ ማየት ውርደት ነው። ከኢትዮጵያዊ አዋቂወች ወይም ከአዛውንቶችዋ ምክር ይልቅ ኢትዮጵያን ጥቂት ቀን ጎብኝቶ ወይም በቴሌቪዢን አይቶ "ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሔው ይሄ ነው" ብሎ የውጭ አገር ሰው የሚጽፈውን እያስተጋቡ መኖር ውርደት ነው። ከሊህቅ እስከ ደቂቅ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ የውጭ አገር ሰው መምሰልን መፈለግ ውርደት ነው። ስለኢትዮጵያ ችግር፣ ለችግሮችዋም መፍትሄ ይሆናል የሚለውን መልዕክቱን ሁሉም ሰው ሊያሰማ የሚፈልገው ለውጭ አገር ሰወች እንጅ ለኢትዮጵያውያን አለመሆኑ ውርደት ነው። ተማሪው እስከ መምህሩ፣ ልጅ እስከ አባቱ፣ ዲያቆኑ እስከ ጳጳሱ ድረስ አገርን ለቆ መሄድን መሻታቸው ለኢትዮጵያውያን ውርደት ነው።  አገርን ለቆ በውጭ አገር ለመኖር ከመፈለግ ብዛት ካህናት እንኩዋን ሳይቀሩ በየኤንንባሲው የሃሰት ምክንያትና ኑዛዜን ማቅረባቸው ውርደት ነው።  

በህሊና አስቦ በውን አመዛዝኖ መሥራትም ከቀረ ውሎ አድሮአል። የውጭ አገር ሰዎች ያሉትን እንደገደል ማሚቶ መልሶ መላልሶ ከማስተጋባት ብዛት እግዚአብሔር ያለጭንቅላት የፈጠረን እያስመሰልነው ነው። አንድ ጊዜ በውጭ አገር የቲዮሎጅ ትምህርት የማስትሬት ዲግሪ አግኝቻለሁ ብለው ኢትዮጵያ ካገኙት የክህነት ትምህርት ይልቅ በማስትሬቱ ዲግሪ የሚኮሩ አንድ ካህን "ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መጀመሪያ የተገኘባት መሆንዋ በሳይንስም ተረጋግጥዋል" ብለዉ ስብከታቸውን "በሉሲ" ታሪክ ሲጀምሩ ትዝ ይለኛል። የፈረንጆቹ ትምህርት "ሉሲ ሰው መሆን የጀመረች ዝንጆሮ ናት" እንደሚል ካህኑ አላወቁም። ፈረንጅ የተናገረውን ያለጥያቄ ማስተጋባት ባህል እየሆነ ስለመጣ ፈረንጅ ከተናገረው እሱኑ መውሰድ እንጅ እሳቸው ምን በወጣቸው ምስጢሩን ይመርምሩ? ይህ ምሳሌ ነው፤ ይሁን እንጂ ከመቶ አመት ወዲህ የተወለደ ኢትዮጵያዊ እንደካህኑ "የምሠራውን፣ የምበላዉን፣ የማስበውንና የምናገረውን ነገር ፈረንጅ አዘጋጅቶ ይስጠኝ" የሚል ነው።
የራሳችን የሆነውን ማን ወሰደው?

የችግሩን ተፈጥሮ ለመንገር በሺህ የሚቆጠሩ ጽሁፎች በመቶ የሚቆጠሩ ጉዳዮችን በማንሳት ተግሣጽና ወቀሳን ሲያደርጉ ይሄው ሃምሳ አመት ሊሞላ ነው። ሁሉም በየተራው የችግሩ ምንጭ "ንጉሣዊ አገዛዝ፣ መሬት ያራሹ አለመሆን፣ ፊዩዳሊዝም፣ ቡርዥዋወች፣ ኢምፔሪያሊዝም፣ ወታደራዊ አገዛዝ፣ የዘር አገዛዝ፣ የዲሞክራሲ አለመኖር፣ የመብት መጥፋት፣ እገሌ የሚባለው ጎሣ ጨቁዋኝ መሆን፣ እገሌ የሚባለው ጎሣ ጦረኛ መሆን፣ ወዘተረፈ" እያሉ ጽፈዋል። የሚደማመጥ የለም እንጅ የሚጻጻፍ ሞልቶ ነበር። በመጻጻፍ የተግባባ እስካሁን አላየንም። በመጻጻፍ መበሻሸቅ ግን በየቀኑ የምናየው ትዕይንት ነው። ተጽፈው የምናነባቸው መፍትሄወችም "የትጥቅ ትግል ማድረግ፣ ተጨማሪ የሚወነጅሉ ጽሁፎችን መጻፍ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ፣ ጉልበት ላላቸው መንግሥታት ማመልከቻ ማቅረብ፣ ወዘተረፈ" የሚሉ ናቸው። ሁሉም ተደረጉ፤ መልካም ቀን አልመጣም። በጦር ብልጫ ወይም በተቃውሞ ብዛት አንዱ አሽናፊ ከሆነ ሌላው ደግሞ ጠመንጃ አንስቶ የተዋጊነት ዙር ይደርሰዋል። ኢትዮጵያን ከጦር ሜዳ፣ ወይም ከሰላማዊ ሰልፍ መንበር፣ ወይም ከኃያላን መንግሥታት ችሮታ ለማግኜት መሞከር ሞኝነት ነው። መልካምዋ ኢትዮጵያ ከኃያላን መንግሥታት ጀርባ አልተደበቀችም። በጦርነትና በሰላማዊ ሰልፍ ማህደር ውስጥም አልተሸሸገችም። በክፉ ሥራችን ከኛ ጠፍታለች፤
እንድናገኛት ከእግዚአብሔር እጅ እንሻት

የእግዚአብሔር ፍርድ ሳይዉል ሳያድር የሚፈጸምባት ወይም የሚፈጸምላት ክፉ ሥራችን ያጠፋት ኢትዮጵያ በእግዚአብሔር የተለየች ሀገር መሆንዋን ያልተገነዘቡ መልሰው መላልሰው ቢያስተዉሉ መልካም ነው። እንደራስ መሆንን ትቶ ሌሎችን ለመምሰል መጣር ይህን ካለማስተዋል የመነጨ ፍላጎት ነው።         

ልጅ እያሱ በግርማዊነታቸው በአፄ ኃይለሥላሴ ትእዛዝ እስር ቤት እያሉ ጣሊያን ኢትዮጵያን መውረር ጀመረ። ጣሊያን እየገሠገሠ ሲመጣ ግርማዊነታቸው ወደዉጭ አገር ገለል ብለው በውጭ ለመታገል ከመውጣታቸው በፊት የልጅ እያሱን ሁኔታ በተመለከተ ከቅርብ አማካሪወቻቸው ጋር ተነጋገሩ። ጣሊያን ሲገባ ህዝብን ለማሳመንና የፖለቲካ መጠቀምያ ለማድረግ ልጅ እያሱን "ንግሥና የሚገባው ንጉሥ ይሄዉና" ብሎ ንጉሥ አድርጎ ያነግሣል የሚል ፍራቻ በንጉሡና በአማካሪወቻቸው አደረ። ይህ ከሚሆን ብንገንድለውስ ብለው ተማከሩ። አፄ ኃይለሥላሴም "ንስኃውን እንዴት እንችለዋለን?" ሲሉ የነብስ አባታቸው አባ ሃና ጅማ "እንጾመዋለን" አሉዋቸው። ልጅ እያሱ በእስር ቤት ውስጥ ስንቅ ከሚያቀብላቸው ሠራተኛ ጋር እያወሩ የሚገድሉዋቸው ሰወች ከነሱም አንዱ የአባ ሀና ወንድም ኃይሌ ጅማ ሲመጡ ከሩቅ አዩና "ሊገድሉኝ እየመጡ ነው" ደህና ሰንብት ብለው ስንቅ አቀባያቸውን ተሰናበቱት። ከዚህ በሁዋላ የልጅ እያሱ አስከሬን የት እንደደረሰ አይታወቅም። [፩]  

ግርማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በደርግ ትእዛዝ እስር ቤት እያሉ የደርግ አባሎች ምን እናድርጋቸው እያሉ መከሩ። እሳቸው በህይወት እያሉ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዴት ሊገዛልን ይችላል ብለው አዲሶቹ የሀገር መሪ ወጣት የጦር መኮንኖች ንጉሡ በእስር ቤት እንዳሉ ለመግደል አቀዱ። አፄ ኃይለሥላሴ በእስር ቤት ዉስጥ ስንቅ ክሚያቀብላቸው ሠራተኛ ጋር ሲያወሩ ዛሬ ከእርስዎ ጋር እንደማላድር ተነግሮኛል አላቸው። አዝነው አለቀሱ። ወዲያውም የሚገድሉዋቸው መኮንኖች ሲመጡ ከሩቅ አዩና አወቁ። ከዚህ በሁዋላ አስከሬናቸው የት እንደደረሰ ሳይታወቅ ከደርግ መውደቅ በሁዋላ አጥንታቸው ተፈልጎ ተቀበረ ተባለ። የነብስ አባታቸው አባ ሃናም በሰው እጅ ነበር የጠፉት።  [፪]

ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ ግርማዊ አፄ ኃይለስላሴ ሊግ ኦፍ ኔሽንስ በተባለው የዓለም መንግሥታት ማህበር ስብሰባ "ጉልበተኛ ጉልበት የሌለውን በግፍ ሲያጠቃ ዝም ብላችሁ አትዩ፤ ነገ በናንተ ላይ ይደርሳልና" ብለው ጣልያን ከኢትዮጵያ ለቆ እንዲወጣ አቤቱታ አሰሙ። በጉባኤው የነበሩ የአውሮጳ ሃያላን መንግሥታት ተሳለቁባቸው።

ጣሊያን በኢትዮጵያ ዉሎ ሳያድር የጣሊያን ጉዋደኛ የሆነው ጀርመን የአውሮጳን ኃያላን በእግሩ እየረገጠ ማንበርከክ ጀመረ። አንድ ባንድ አውሮጳን ይወርም ጀመረ። በአፄ ኃይለሥላሴ አቤቱታ የተሳለቁት መንግሥታት በኢትዮጵያ ላይ የደረሰው በራሳቸው ላይ እየደረሰ በመምጣቱ ተደናገጡ። ከኢትዮጵያ ጎን በወታደርነት ተሰልፈው ጣልያንን እስኪአስወጡ ድረስ በኢትዮጵያ ላይ መሳለቃቸውን ረገሙ። የእግዚአብሔር ፍርድ እንዲህ ነው።

የጣልያኑ መሪ ቤኒቶ ሙሶሎኒ ኢትዮጵያን በወረሩበት ጊዜ ብዙ ግፎችን ሠርተው፣ አሰቃቂ ፍርዶችንም ፈርደው ነበረ። መነኮሳትን በየገዳሙ በጥይት ጨፍጭፈው ገድለዋል፤ በመርዝ ጋዝና በኬሚካል መሣሪያወች የኢትዮጵያን ህዝብ ጨፍጭፈዋል፤ አርበኞችን ከአውሮፕላን ከሰማይ ወደምድር ዘቅዝቀው ወርውረዋል። ቤኒቶ ሙሶሎኒ ከሠሩዋቸው ግፎች ዉስጥ አንዱ የእግዚአብሔርን ሰው አቡነ ጴጥሮስን አዲስ አበባ ላይ አስረው በተጣደፈ ችሎት የሞት ፍርድ አስፈርደው በጥይት አስደብድበው መግደላቸው ነው።

የጣሊያን ጦር ከኢትዮጵያ ከተባረረ በሁዋላ ትልቁ የጣሊያን ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒቶ ሙሶሎኒ ከአገራቸው ሊወጡ ሲገሠግሱ የጣልያን ሶሻሊስቶች ይዘው በተጣደፈ ችሎት የሞት ፍርድ በየኑባቸው። በፍርዱ መሠረት ወዲያውኑ ቤኒቶ ሙሶሎኒ እንደ አቡነ ጴጥሮስ በጥይት ተደብድበው ተገደሉ። በሚላን ከተማ ሬሳቸው ተዘቅዝቆ ተሰቀለ። ከዚህ በኢትዮጵያ ላይ ከተፈፀመ የግፍ ወረራ ዘመን በሁዋላም ጣልያን ከአውሮጳ ጅራቶች ዉስጥ አንድዋ ሆና ቀረች።

የዛሬ አራት መቶ ሃምሳ አመት አካባቢ ኦስማኒየ ወይም ኦቶማን ኢምፓየር የተባለ ማእከሉ ቱርክ የሆነ በዘመኑ በዓለም ላይ አቻ የሌለው መንግሥት የውስጥ አመፀኛን በማስታጠቅ እንዲሁም ወታደሮቹን በአካል መሣሪያ አስይዞ ክርስትናን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ወደኢትዮጵያ መጣ። ትልቅ ጥፋትንም አደረሰ። አብያተክርስቲያናት ተቃጠሉ፣ መነኮሳት ታረዱ።

ለሁለት መቶ አምሳ አመታት በኃያልነት በማንም ሳይደፈር ከቆየ በሁዋላ የኦቶማን ኢምፓየር በኢትዮጵያ ላይ ጥፋትን አድርሶ ብዙ ሳይቆይ ለመጀመሪያ ጊዜ በላፔንቶ ጦርነት ተሽንፎ የሜዲትራንያንን ባህር መቆጣጠር አቃተው። ቀስ በቀስም እንደጉም በኖ ጠፋ። 

በተለይ የኦቶማን ኢምፓየር ቅሬታወች ነን የሚሉ መንግሥታት ባለፉት አምሳ አመታት ኢትዮጵያን በጦርነት አደህይተው፣ ወደቦችዋን ነጥቀው፣ የንግድ በርዋን ዘግተውና ህዝቦችዋን አናክሰው ህልውናዋን በማጥፋት ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚፈልጉትን እስከሚችሉት አከናወኑ። እነዚህ መንግሥታት እንደአባቶቻቸው ኦቶማኖች የውስጥ አመፀኛን በማስታጠቅ ይህ ነው የማይባል ጥፋትን አድርሰዋል። አንድ ጊዜ መንፈሰ መራራ እንዲሆኑ በውጭ አገር ሰወች የተሰበኩ ኡስማን ሳልህ ሳቤ የተባሉ ሰዉየ ኢትዮጵያውያን ሱዳን አገር በሚገኝ የመዳህኒዓለም ቤተክርስትያን አብረው በመፀለይ ላይ እንዳሉ "ኤርትራውያን የተለያችሁ ናችሁ፤ ለናንተ እኔ ቤተክርስቲያን ለብቻችሁ እገዛላችሁዋለሁ" በማለት ከነዚህ መንግሥታት ባገኙት ገንዘብ ህንፃ ገዝተው የኤርትራውያን ሚካኤል ቤተክርስቲያን ብለው ሰየሙና ኢትዮጵያውያንን ከፋፈሉዋቸው። [፫] በተለይ የባዝ ፓርቲ ተብሎ የሚጠራው የኢራቅ ፓርቲ ቀይ ባህርን አረቦች ብቻ ይቆጣጠሩት ዘንድ ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠልና ኢትዮጵያ ተቆራርጣ የንግድ በር እንድታጣ ለአረቦች ጥሪ አደረገ። የነዚህ መንግሥታትም ገንዘብ  እንደ ጥፋት ልኡክ ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ደም ፈሰሰ።

እነሆ ለነዚህ መንግሥታት በጦርነት አደህይቶ፣ የንግድ በራቸውን ተቆጣጥሮ፣ ህዝባቸውን አናክሶ የሚፈልገውን የሚያከናውን ኃይለኛና የሚረግጥ የበላይ ሰጣቸው። አንዳቸው ብቻ አይደሉም - ሁሉም የሠሩትን ግፍ የሚያህል ፅዋ እየተጎነጩ ነው። ማን ያውቃል - እስላም ያልሆነው ኃይለኛው መንግሥት በመካከላቸው ባስቀመጠው ወኪል አማካኝነት ለአንዱ ዘር የተለየ መስጊድ ይገዛለት ይሆናል። 

አምባሳደሮችዋን ክንፍ ባላቸው መርከቦች በዓለም ላይ የምታሰማራው የአሜሪካ ልኡክ የሆኑ የመጣሁት አረቦች ኤርትራን ገንጥለው የራሳቸው ለማድረግ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለማጨናገፍ ነው እያሉ ከኤርትራው ጠቅላይ ገዥ ጋር በመሆን ከአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ለመገናኘት በቀጠሮ ወደቃኘው ሻለቃ አመሩ። ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ቢታገሉ እንደማይቃወሙ እንደሚረዱዋቸውም ከጠቅላይ ገዢው ዘወር አርገው ለአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ማበረታቻ ሰጡዋቸው። [፬] ከዚህ ጊዜ በሁዋላ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ትገነጠል ዘንድ የኢትዮጵያን ሀገርነትና ኃይማኖትዋን የሚያጥላሉ ሚሽነሪወችን በማሰማራት፣ እንዲሁም ከሰላይ እስከ ደላይ፤ ከጋዜጠኛ እስከ ጎብኝ፣ ከስነፅሁፍ እርዳታ እስከገንዘብ ድረስ በማቅረብ ኢትዮጵያን አዳከሙ። ኢትዮጵያ ትከፋፈል ዘንድ፣ የንግድ በርም ታጣ ዘንድ ከአረቦች ጋር አላማቸው አንድ ሆነ። ሶስት መቶ ስልሳ አንድ ወደቦች ያላት ታላቁዋ አገር አሜሪካ አንድ ብቻ ያላትን የተራበችዉን፣ የደሃዋን አገር በር ለመንሳት አምባሳደርዋን ላከች። ፈፀመችም። ኢትዮጵያን ለመክፈል፣ የንግድ በርዋንም ለመዝጋት በሌላ አገር ላይ ተደርጎ የማይታወቅ ኢትዮጵያን ያለ በር ማስቀረት የሚያስችል የመንግሥታት ማህበር ድንጋጌ በልዩ ዘዴ ተነደፈ። ተጨበጨበ። ተፈጸመም።

ለምልክት እንዲሆን በኢትዮጵያ አዲስ አመት እለተ ቀን፣ ኢትዮጵያን ለማጎሳቆል አላማ  ከተወዳጀቻቸው ወገኖች የተሰነዘረ ጥቃት በአሜሪካ ላይ ደረሰ። በስማይም በባህርም ብዙ ሺ መንገድ ያላት አገር በሮችዋ እንደ አንድ በር ሆኑና ሰማዩም ባህሩም የስጋት ሆነባት። በአንድ እለተ ቀን የተፈፀመ ጥቃት አጥቂወቹም ተጠቂወቹም በማያውቁት መንገድ የእያንዳንዱን ሰው ኑሮ ዳሰሰ፤ አቃወሰ። የተጠቂዋ ንግድ በጥቃቱ ተጎዳ፣ ደስታዋም አነሰ። በሰማይዎችዋና በባህሮችዋ ያለባትን ስጋት ለመሸፈን በየቀኑ ቁጥር ስፍር የሌለው ኃብትዋን በመድፋት ላይ ትገኛለች።  

ኢትዮጵያን የበደለ ይበደላል። እነ ታላቅዋ ብሪታንያ፣ እነ ዩ ኤስ ኤስ አር፣ እነ ፖርቱጋል ወዘተረፈ የሚመጣጠነውን ዋጋቸውን አግኝተዋል። አንድ የእግዚአብሔር ሰው አንድ ጊዜ "ኢትዮጵያን አይነኩ፤ ቢነኩ ያድርዋል ሲታወኩ" ብለው የተናገሩት ያለምክንያት አይደለም። ትናንትናም ዛሬም ነገም አይቀየርም - የነካት ይነካል። በኢትዮጵያውያን የተሠራ ኃጢአትም ወዲያዉኑ ፍርድ ያገኛል። አሁን እየተጎነጨን ያለነው ፅዋ ለሠራነው ኃጢአት የሚመጣጠነውን ነው። ፍቅር የለን፤ እንዴት አንድ እንሁን? ምቀኝነት ምግባራችን፤ እንዴት እንበልጽግ? የውጭ የምናይ፤ እንዴት የራሳችን ይክበር? አጉል ምግባራችን ያጠፋት መልካምዋ ኢትዮጵያ በእግዚአብሔር እጅ ተይዛለች። የምትገኘው በሱ ነውና እሱን እንፈልገው።
እንድናገኘውም ከፍቅር ማህበር እንጥራው
 
እገሌ እንዲህ አድርጎ ስለበደለን እንዲህ ሆነናል እያልን ከዘመን ዘመን የተለያዩ ሰወችን እያማረርን፣ ተጠያቂወቹ እነሱ ናቸው እያልን እንኑር ወይ? ውድቀታችን ያመካኘንባቸው ሰወች ከየት መጡ? የውድቀት ተጠያቂወች የሚቀያየሩ ከሆነስ ውድቀት እንዴት ሊቆም ይችላል? ጨቁዋኞችስ ለምን መጡ? ሁከተኞች ለምን መጡ? አገር መገንጠል የሚፈልጉ ለምን መጡ? ያልተሰጣቸውን የሚነጥቁ ለምን መጡ? ዘጠና ስምንት ከመቶ በላይ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ በእግዚአብሔር ያምናል። ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የንግሥና ዘመን ማለፍ በሁዋላ የተሰየሙት እግዚአብሔር የለም የሚሉ ሁለት መንግሥቶች በእግዚአብሔር ከሚያምን ህዝበ-ውቅያኖስ መካከል ወጥተው እንዴት መሪ ሊሆኑ ቻሉ? ልብ ላደረገው መልሱ እራሱ ከጥያቄው ዉስጥ ይገኛል።      

እግዚአብሔር ጭቆና አይወድም። ወንድሙን እና እህቱን የሚወድ ወንድሙንና እህቱን አይጨቁንም። ጉዋደኛዉን የሚወድ ጉዋደኛውን አያጭበረብርም። የተጨቆነ ወንድም ለመውደድ ይቸገራል። የተታለለ ባልንጀራ ግዋደኝነትን አይሻም። ክፉ አመልን እንደያዝን የምንገነባው ይፈርሳል። የምናደርገው ነገር ሁሉ ዉኃ ቢወግጡት ይሆናል። ባለዘመን ቢገነባ የሚከተለው ያፈርሰዋል። ዘንድሮ የተወደሰው ከርሞ ይረክሳል። ኢትዮጵያን ከክፉ ቀን ለማዳን የሚያስፈልገን አንድ ነገር ብቻ ነው። እሱም ፍቅር ነው። ፍቅር ካለ ጭቆና የለም። ፍቅር ካለ ማጭበርበር የለም። ፍቅር ካለ አመፅ የለም። በፍቅር የተገነባ በበቀል አይፈርስም። ፍቅር ካለ እንገነጣጠል የሚል ዛቻ የለም። ፍቅር ካለ ስብሰባውም ሆነ ስነፅሁፉ ስለ መገንባት ጉዳይ እንጂ ስለ ጦርነት ጉዳይ አይሆንም። እግዚአብሔር ፍቅር ነውና ስንፋቀር እግዚአብሔርን እናገኘዋለን። እግዚአብሔርም መዳብ መስሎን የነበረው እኛነታችን አይናችን ገልጦ ወርቅ መሆኑን ያሳየናል። የምንበላውና የምንጠጣው የሌለ የመሰለው ልቦናችንን አንቅቶ በኤደን ገነት ውስጥ እንደምንኖር ይስመለክተናል። የውጩ የሚያስጎመጅ የመሰለው አዕምሮአችንን ብሩህ አድርጎ በእጃችን ያለው እንቁ መሆኑን ያሳየናል። ስለዚህ የፍቅርን ሥራ እንጀምር።

**********************************************************************************
፩ ይህን ያሪክ ያጫወቱኝ በጊዜው ጉዳዩን የሚያውቁ አረጋዊ ናቸው።
፪ ይህን ያሪክ ያጫወቱኝ በጊዜው ጉዳዩን የሚያውቁ አረጋዊ ናቸው።
፫ ይህን ታሪክ ያጫወቱኝ በሱዳን አገር በስደት የኖሩና ጉዳዪን በአይናቸው ያዩ የባህረ ነጋሽ ተወላጅ ናቸው። 
፬ ሲ አይ ኤ በአፍሪካ፣ በአለሜ እሸቴ፣ ፲፱፻፺፬ ዓ.ም.

****************************************
 ምንጭ:--http://www.oftsion.org/SeektheLord.html

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

የገጣሚ ነብይ መኮንን እማይነትበዉ ስዉር-ስፌት

ሞክሼ የአማርኛ ፊደላት እና የባለሙያዎች ማብራሪያ

ንባብ ለሕይወት!