የሸገር ሬዲዮ መዓዛ
ክፍል --፪
**************
እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ የሬዲዮ መቀበያችንን መስመር በኤፍ ኤም በኩል ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ ብንዘውረው ሰባት ያህል የሬዲዮ ጣቢያዎችን ማግኘት እንችላለን፡፡
ሬዲዮ ጣቢያዎቹ የተለያዩ ቢሆኑም አብዛኞቹ የሚያቀርቡት ተመሳሳይ “ዝግጅት” ነው፡፡
አንዱን ጣቢያ ከሌላው ለመለየት የሚያስችል የራሳቸው የሆነ መለያ ቀለም ስለሌላቸው፤ የአንዱ ሬዲዮ ፕሮግራም በሰባት የሬዲዮ መስመሮች ውስጥ ተከፋፍሎ የሚሰማ እስኪመስል ድረስ ምንም ዓይነት ልዩነት አይታይባቸውም፡፡ የሚያቀርቧቸው ፕሮግራሞች በክሊሼ የታጀሉና ኦና ከመሆናቸው የተነሳ አድማጭን ያንገፈግፋሉ፡፡ መስፍን ሀብተማርያም በአንድ የወጐች መድበሉ ላይ እንዳለው፤ ለአንዳንዶቹ ሬዲዮኖች ሲባል “ምነው ጆሮም እንደ ዓይን ቆብ በኖረው” ያሰኛል፡፡
ለመሆኑ ጥሩ የሬዲዮ ፕሮግራም እንዴት ያለ ነው? ጥሩ የሬዲዮ ፕሮግራም፤ ባለሙያ መጥናና ቀምማ ባሰናዳችው መልካም ወጥ ሊመሰል ይችላል ይባላል፡፡
**************
እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ የሬዲዮ መቀበያችንን መስመር በኤፍ ኤም በኩል ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ ብንዘውረው ሰባት ያህል የሬዲዮ ጣቢያዎችን ማግኘት እንችላለን፡፡
ሬዲዮ ጣቢያዎቹ የተለያዩ ቢሆኑም አብዛኞቹ የሚያቀርቡት ተመሳሳይ “ዝግጅት” ነው፡፡
አንዱን ጣቢያ ከሌላው ለመለየት የሚያስችል የራሳቸው የሆነ መለያ ቀለም ስለሌላቸው፤ የአንዱ ሬዲዮ ፕሮግራም በሰባት የሬዲዮ መስመሮች ውስጥ ተከፋፍሎ የሚሰማ እስኪመስል ድረስ ምንም ዓይነት ልዩነት አይታይባቸውም፡፡ የሚያቀርቧቸው ፕሮግራሞች በክሊሼ የታጀሉና ኦና ከመሆናቸው የተነሳ አድማጭን ያንገፈግፋሉ፡፡ መስፍን ሀብተማርያም በአንድ የወጐች መድበሉ ላይ እንዳለው፤ ለአንዳንዶቹ ሬዲዮኖች ሲባል “ምነው ጆሮም እንደ ዓይን ቆብ በኖረው” ያሰኛል፡፡
ለመሆኑ ጥሩ የሬዲዮ ፕሮግራም እንዴት ያለ ነው? ጥሩ የሬዲዮ ፕሮግራም፤ ባለሙያ መጥናና ቀምማ ባሰናዳችው መልካም ወጥ ሊመሰል ይችላል ይባላል፡፡
የባለሙያዋን ቅመም ዓይነትና መጠን እንዲሁም የአበሳሰል ዘዴ ባናውቀውም፣ በማድመጥ ግን ጥሩው የቱ እንደሆነ እናውቀዋለን፡፡ ለምሳሌ ለእኔ መልካም የሬዲዮ ፕሮግራም ማለት እንደ ቢቢሲ፣ እንደ ዶቼ ቬሌ፣ እንደ ቪኦኤ ወይም እንደ ሸገር ሬዲዮ ፕሮግራም ያለ ነው፡፡
የሬዲዮ ፕሮግራም ዝግጅት የማያቋርጥ መሰናዶ እንደሚሻ የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡ በተጨማሪም ሙያው ከማንኛውም የጋዜጠኝነት ዘርፍ ያላነሰ ምርምር፣ ሐቀኛ መረጃ እና እንደ ጥበብ ደግሞ የፈጠራ ሥራ ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ ላይ ተመስርቶ ቀላል፣ የተመጣጠነ ሆኖም አዝናኝ ወይም አስተማሪ የሆነ ፕሮግራም ከሙዚቃ ጋር ተዋህዶ ለዛ ባልተለየው ዘዴ ሲቀርብ የአድማጩን የዕውቀት አድማስ ያሰፋል ወይም ያዝናናል፡፡ በዚህ ረገድ በሀገራችን የተሻለ ሥራ በማከናወን የአድማጩን ስሜት ለማርካት የቻለው ሸገር 102.1 ኤፍ ኤም ሬዲዮ ነው፡፡
ይህ ሬዲዮ በተመሠረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሳየው ብቃት በአገራችን የሬዲዮ ሥርጭት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራን እንዲያገኝ አድርጐታል፡፡ የጣቢያው ብቃትና ችሎታም ምንጭ የአዘጋጆቹ የዓመታት የሬዲዮና የጥበብ ሥራ ቅምር ውጤት ነው፡፡ ሸገር ሬዲዮ የተፀነሰው፤ አንጋፋው የኢትዮጵያ ሬዲዮ በመሠረተውና የአገሪቱ የመጀመሪያው የኤፍኤም ሬዲዮ በሆነው በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ስቱዲዮ ውስጥ ከአስራ ሶስት ዓመታት በፊት በ1992 ዓ.ም ነበር፡፡
በአንድ ወቅት የሸገር ሬዲዮ አስኳል የሆነው የ“ጨዋታ” ፕሮግራምን ጅማሮ አስመልክተው የፕሮግራሙ ፕሮድዩሰር አቶ አበበ ባልቻ ሲገልጹ፤ የኤፍኤም አዲስ 97.1 ሥራ አስኪያጅ የነበሩ ሰው፤ ሬዲዮ ጣቢያቸው ለተባባሪ አዘጋጆች የአየር ሰዓቱን ክፍት ሊያደርግ እንዳሰበ እንዳጫወቷቸው አስታውሰው፤ “ስለዚህም በሬዲዮ ላይ የመሥራት ልምድም ሆነ ፍላጐትም ከነበራቸው ከወይዘሮ መዓዛ ብሩ እና ከአቶ ተፈሪ ዓለሙ ጋር በመሆን ቅዳሜ ከቀትር በኋላ ባለው ጊዜ የሚቀርብ ዝግጅት ለማቅረብ መሰናዶ ጀመርን” ብለው ነበር፡፡
በዚህም መሠረት ወይዘሮ መዓዛ ብሩ ቀደም ብለው ያቋቋሙት “አደይ ፕሮሞሽን” እና የአቶ ተፈሪ ዓለሙ “ትንሣኤ ኪነጥበባት” ተጣምረው “ጨዋታ” ሲሉ የሰየሙትን ዝግጅት ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር በመተባበር፣ ቅዳሜ ሐምሌ 1 ቀን 1992 ዓ.ም በአየር ላይ በማዋል ፕሮግራማቸውን በይፋ ጀመሩ፡፡ የጨዋታ ፕሮግራም ዘወትር ቅዳሜ ከሰባት ሰዓት ተኩል እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ተኩል ለ420 ደቂቃዎች ያህል የቃለመጠይቅ፣ የድራማና የግጥም፣ የስፖርትና የሙዚቃ ዝግጅቶችን ያቀርብ ጀመር፡፡ ፕሮግራሙ የአዘጋጆቹ ልምድ፣ ችሎታ፣ ጥረትና ለዛ የታከለበት በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ከሚቀርቡ ዝግጅቶች በተወዳጅነት ቀዳሚው ለመሆን በቃ፡፡
በዚህ ጊዜ በተለይ የማይዘነጋውና በጨዋታ ፕሮግራም ከሚቀርቡት ዝግጅቶች ሁሉ ተወዳጁ መጀመሪያ በደረጄ ኃይሌ፣ በኋላ በመዓዛ ብሩ ይቀርብ የነበረው “የጨዋታ እንግዳ” የተሰኘው የቃለመጠይቅ ፕሮግራም ነበር፡፡ በዚህ ፕሮግራም በርካታ የአገር ባለውለታ የሆኑ እንግዶች ቀርበው የሥራ እና የሕይወት ትውስታቸውን አካፍለው አድማጩን አስደስተውታል፡፡
በተጨማሪም አንደ ፍቃዱ ተክለማርያም ያሉ ስም ያላቸው ታዋቂ የጥበብ ባለሙያዎች የሚያቀርቧቸው ትረካዎችና የሬዲዮ ድራማዎች ለጨዋታ ፕሮግራም ውበት የሰጡ ፈርጦች ሆነውለት ነበር፡፡ የቅዳሜ ጨዋታ ተቀባይነት እየጨመረ ወደ ሸገር ሬዲዮ እስከተዘዋወረ ድረስ ቀጥሏል፡፡
ለመሆኑ ሸገር ሬዲዮ እንዴት ተመሠረተ? ባለቤቱስ ማን ነው የሚለው ጥያቄ የሬዲዮው ወዳጆችና አድናቂዎች ሁሉ ይመስለኛል፡፡ የዚህ ሬዲዮ መስራች፣ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ መዓዛ ብሩ ትባላለች፡፡
መዓዛ የተወለደችው እዚህ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሲሆን ዘመኑም 1951 ዓ.ም ነበር፡፡ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ክፍል በሐረርጌ ክፍለ ሀገር በሒርና ከተማ ተምራ፣ ከአራተኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርቷን ደግሞ በቅድስት ማርያም ትምህርት ቤት (Saint Mary School) ተከታትላ ፈጽማለች፡፡ መዓዛ በትምህርት ቤቷ በክፍል ውስጥ አጫጭር ታሪኮችን ለተማሪዎች በማንበብ ከመታወቋም ሌላ ከፍ ያለ የሥነ - ጽሑፍ ዝንባሌ እንደነበራት የሚያስታውሱት መምህራኗ “አንድ ቀን ታላቅ የጥበብ ሰው እንደሚወጣት እናውቅ ነበር” ይላሉ፡፡
መዓዛ በ1971 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ - ቋንቋ ጥናት ተቋም ውስጥ በሥነ -ልሣን (Linguistics) ትምህርት ክፍል ተመደበች፡፡ ሥነ - ልሣን መዓዛ የምትፈልገው ጥናት ባለመሆኑ በምደባው ቅር ብትሰኝም፤ በንዑስ ትምህርት ደረጃ (minor study) የምትወስደው የውጭ ቋንቋና ሥነ - ጽሑፍ በመሆኑ ለነበራት ቅሬታ እንደማካካሻ ሆኖላታል፡፡ በዚህ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ሳለች የተፈጠረ አንድ አጋጣሚ ደግሞ መዓዛንና ሬዲዮንን የሚያስተሳስር ይሆናል፡፡ ይኸውም የኢትዮጵያ ሬዲዮ የፕሮግራሞች ኃላፊ የነበረው አቶ ታደሰ ሙሉነህ ለሚያዘጋጀው የእሁድ የሬዲዮ ፕሮግራም ድራማ የሚጫወቱ ሸጋ ድምጽ ያላቸው ወጣቶችን ሲያፈላልግ ከመዓዛ ጋር ይተዋወቃል፡፡ ድራማው አስታጥቃቸው ይሁን ያሰናዳው ሲሆን የመዓዛ ድምጽ ለሙከራ በስቱዲዮ ተቀርጾ ሲሰማው፣ ታደሰ ሙሉነህ የሚፈልገውና የሚወደው ድምጽ ሆኖ ስላገኘው ይደሰታል፡፡ ከዚህ በኋላም ለእሁድ ፕሮግራም የሚሆኑ ጽሑፎችን በየሳምንቱ እንድታነብለት ያግባባትና የመዓዛና የሬዲዮ ፍቅር በኢትዮጵያ ሬዲዮ ይወለዳል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የመዓዛ ድምጽ በእሁድ የሬዲዮ ፕሮግራም አድማጮች ዘንድ የተለመደና የተወደደ ሆነ፡፡ መዓዛም የሌሎችን ጽሑፎች በማንበብ ብቻ ሳትወሰን የራሷን ጽሁፎች እያዘጋጀች የምታቀርብ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ከሬዲዮ ፕሮግራሙ ቤተሰቦች እንደ አንዱ ሆነች፡፡ በ1974 ዓ.ም ከዩኒቨርሲቲ ተመርቃ ትምህርቷ ፍጻሜውን እስካገኘ ድረስም መዓዛ ሬዲዮና ትምህርትን ጎን ለጎን ስታስኬድ ቆይታለች፡፡
የመዓዛ የሥራ ዓለም የተጀመረው ግን በምትወደውና በምትፈልገው በኢትዮጵያ ሬዲዮ ውስጥ ሳይሆን መንግስት በመደባት በባህል ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ ነበር፡፡ ስራዋም ባህልና ስፖርት የተባለው የመስሪያ ቤቱ መምሪያ በሚያሳትመው “መርሐ ስፖርት” የተሰኘ ወርሃዊ የስፖርት መጽሔት (በኋላ ጋዜጣ) ላይ ሆነ፡፡ ምንም እንኳ አዲሱ ስራዋ ከራዲዮ የሚያርቃት ቢሆንም መዓዛ ግን ሳትሸነፍ ሬዲዮን በትርፍ ጊዜ ሥራነት ተያያዘችው፡፡ ሬዲዮ ጣቢያው የሚሠጣትን አነስተኛ ክፍያ እየተቀበለችም ልዩ ልዩ ጭውውቶችን እና መጣጥፎችን በግልና በጋራ በማቅረብ ተወዳጅ ሥራዎቿን ለሕዝብ አበርክታለች፡፡
መዓዛ በእሁድ የሬዲዮ ፕሮግራም ታቀርባቸው የነበሩት ሥራዎች ይዘት ማህበራዊ ሕይወት እንዲሠምር በመጣር ላይ ያተኮሩ ሆነው ግልጽ፣ ቀላልና ለዛ ያልተለያቸው ስለነበሩ ከሶስት አሥርት ዓመታት በኋላም ትውስታቸው ከአድማጭ ህሊና አልጠፉም፡፡ በዚሁ ፕሮግራም ላይ መዓዛ ካበረከተቻቸው የፈጠራ ሥራዎቿ ውስጥ ጎልቶ የሚታወሰው “የአዲሱ ቤተሰብ” የተሰኘ ባለ ሰማንያ ስድስት ክፍል ድራማ ሲሆን በዘመኑ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉም የሚያደምጠው ተወዳጅ የቤተሰብ ድራማ ነበር፡፡
መዓዛ በ “መርሀ ስፖርት” እና በሬዲዮ መካከል ሆና ከአራት ዓመት በላይ ከቆየች በኋላ በ1979 ዓ.ም የባህል ሚኒስቴርን ለቅቃ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቀጠረች፡፡
አዲሱን መስሪያ ቤቷን ከተቀላቀለችበት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከሬዲዮ እየራቀች መጣች፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የቆየችው ለሶስት ዓመታት ያህል ሲሆን ከዚያ በኋላ የግሏን የማስታወቂያ ሥራ ድርጅት መሥርታ የራስዋ ተቀጣሪ ሆናለች፡፡ ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1992 ዓ.ም ባሉት የአስራ ሶስት ዓመታት ጊዜ ግን መዓዛና ሬዲዮ ተራራቁ፡፡
መዓዛና ሬዲዮ ዳግም የተዋደዱት ከላይ እንደተገለጸው በ1992 ዓ.ም ሳምንታዊውን የ “ጨዋታ” ፕሮግራም በኤፍ ኤም 97.1 ከተፈሪ ዓለሙ ጋር በጋራ ማቅረብ ሲጀምሩ ነበር፡፡ የ “ጨዋታ” ፕሮግራም እስከ 1999 ዓ.ም ድረስ በአድማጮቹ እንደተወደደ በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ላይ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት የኤፍ ኤም ሬዲዮ ፈቃዶችን ለግሉ ዘርፍ ለመስጠት ሲዘጋጅ፣ ዝርዝር የሥራ እቅድ አቅርባ ባመለከተችው መሠረት፤ ከረጅም ጊዜ ቆይታ በኋላ ከአስር አመልካቾች መካከል አንዷ ሆና የመጀመሪያ የግል የኤፍ ኤም ሬዲዮ ባለቤት ያደረጋትን ፈቃድ ተቀበለች፡፡
መዓዛ የሬዲዮ ማሰራጫ መሳሪያዎችን ውድነት፣ የማሰራጫ ቦታ እና የባለሙያ እጦትን ተቋቁማ ሸገር 102.1 ኤፍ ኤም ሬዲዮን በታህሳስ 2009 ዓ.ም አበረከተችልን፡፡
ባለትዳርና የሶስት ልጆች እናት የሆነችው መዓዛ እንደ ባለቤት፣ ሥራ አስኪያጅና ጋዜጠኛ በመሆን በኢትዮጵያ ተወዳጁንና የመጀመሪያውን የግል የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ትመራለች፡፡ በመዓዛ ህይወትና ሥራዎችዋ ላይ የመመረቂያ ጥናቱን ለሠራው ለኤርምያስ ወሌ በሚያዝያ ወር 2002 ዓ.ም በሰጠችው ቃለምልልስ “የማይክራፎን ፍቅር አይለቀኝም፤ እስካሁን ድረስ ከሬዲዮ ባለመለየቴም እጅግ ደስተኛ ነኝ” በማለት ስለ ስራዋ ያላትን ስሜት ተናግራለች፡፡
ሸገር በዚህ ዓመት የተመሠረተበትን የአምስተኛ ዓመት የልደት በዓሉን ያከብራል፡፡ ሸገር ደካማውን ጎኑን አጠንክሮ፣ ጠንካራውን እያጎለበተ ገና ብዙ ሻማዎች እንደሚለኩስ የአድማጮቹ ተስፋ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ወይዘሮ መዓዛ ብሩን፣ አቶ ተፈሪ ዓለሙን እና መላውን የሸገር ሬዲዮ ጣቢያ ሠራተኞችና ጋዜጠኞች እንኳን ለሸገር ሬዲዮ የአምስተኛ ዓመት የልደት በዓል አደረሳችሁ እላለሁ፡፡
“ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!”
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ