ኪነ ጥበብ
ፊልም፣ "ሰባተኛው ስነ-ጥበብ"
በሰሎሞን ተሠማ ጂ. (semnaworeq.blogspot.com)
![](https://blogger.googleusercontent.com/img/b/R29vZ2xl/AVvXsEg_S5ehGOpstH2LYIaqyvz3D6OwwES5bQnRlDF6NxxniNnVQs_G8PJm8Aj_Ps8O6qSNuQ3ZWYlbVL0JhTjUvZAW5ASvAgsRXcEgY1ZHvS1Ju3Ut9PWwfLu8tqzu42RLElz9q5389Mytc6Qs/s400/images0.jpg)
ኢትዮጵያዊያንም የአድዋንና የአምስቱን
ዓመት የፀረ-ወረራ ትግል ካካሄዱ በኋላ ታሪካቸውንና ባህላቸውን እንዲዘነጉ የጣሊያን ወራሪዎችም ሆኑ ቆንስላዎቹ ያልተቆጠበ ጥረት
አድርገዋል፡፡ ፕሮፌሰር ሥርግው ኃብለ ሥላሴ “ዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ፣
የአዲሱ ሥልጣኔ መስራች” በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት “የመጀመሪያው የሲኒማ ቤት በአንድ የፈረንሳይ ተወላጅ በ1890ዎቹ
ተከፍቶ የነበረ ቢሆንም ቅሉ፣ በዚያን ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ የነበሩት የውጭ አገር ሰዎች ቁጥር መጠነኛ ስለነበረ፣ ያሉትም ሲኒማ
ለማየት ስላልፈለጉ፣ ኢትዮጵያዊያኑም ቶሎ ስላልለመዱ ኪሳራ ላይ ወደቀ፡፡ የሲኒማ ቤቱ ባለቤትም ይህ ንግድ እንደማያዋጣው ስላወቀ
መሣሪያውን ለኢጣሊያው ሚኒስትር ቺኮዲኮሳ ሸጠለት” (ገጽ 444)፡፡ ቺኮዲኮሳም የሲኒማ ማሳያውን፣ አፄ ሚኒሊክ ለአዲስ ግኝት የነበራቸውን
ጉጉት ስለሚያውቅ ገጸ በረከት አቀረበላቸው፡፡ በደስታም ተቀበሉት፡፡ አንድ የአርመን ተወላጅ እያንቀሳቀሰው ለብዙ ጊዜ ንጉሱና ንግስቲቱ
ሲኒማ ሲያዩ ከቆዩ በኋላ በድንገት ተሰናከለ፡፡ አውቶሞቢል ይዞ የመጣው እንድሊዛዊው ቤንትሌይ ጠግኖት እንደገና መታየቱ ቀጠለ
(ፕ/ር ሥርግው፤ ገጽ 444)፡፡
በ1902 ዓ.ም የመጀመሪያው ሲኒማ
ቤት ቴድሮስ አደባባይ አጠገብ “ፓቲ” የሚሰኘው ሲሆን (የዛሬው ሜጋ አምፊ ቴያትር ያለበት ቦታ ላይ) የተከፈተ ሲሆን ያቋቋሙትም
ሁለቱ ወንድማማቾች ነበሩ፡፡ ምንም እንኳን የፈረንሳይ ተወላጆች ቢሆኑ፣ የጣሊያን ዜግነት ነበራቸው፡፡ ሕዝቡም ሲኒማ ቤቱን “የሰይጣን
ቤት” እያለ ነበር የሚጠራው፡፡ ከ1908 እስከ 1926 ዓ.ም ድረስም አምስት ሲኒማ ቤቶች ተከፍተው ሲኒማ ያሳዩ ነበር፡፡ የኢጣሊያ
ወራሪዎች ወደአዲስ አበባ ሲገቡ ከሰይጣን ቤት በስተቀር ሁሉም ሲኒማ ቤቶች ተቃጠሉ (የፊልም ማዳበሪያና መቆጣጠሪያ ዋና ክፍል፣ ገጽ 4-7)፡፡
ሆኖም ወራሪው ኃይል የሲኒማን ጠንከራ
የፕሮፓጋንዳ መሣሪያነቱንና ኃይሉን ስለተረዳ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተቃጠሉትን ሲኒማ ቤቶች አድሶ፤ ሲኒማ ኢታሊያ (የዛሬው ሲኒማ
ኢትዮጵያ ነው)፣ ሲኒማ አምፒር (አሁንም በቦታው ላይ አለ)፣ ሲኒማ ማርኮኒ (አሁን የብሔራዊ ቲያትር ሕንፃ ያረፈበት ቦታ ላይ
ነበር)፣ ሲኒማ ቺንኮ ማጆ (አራት ኪሎ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሣይንስ ፋኩሊቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ ይገኝ ነበር)፣ ሲኒማ ዲ መርካቶ
(የዛሬው ራስ ቴያትር ነው)፣ ሲኒማ ዲፖላቮሮ (የተግባረ ዕድ ት/ቤት የፊት ለፊቱ ህንፃ ወስጥ) እና በድሬዳዋ ሲኒማ አምፒርና
ሲኒማ ማጀስቲ የተባሉትን፤ በሐረር ሲኒማ ዲ ሮማን፣ በጅማና በጎንደር እንዲሁም በደሴ ሲኒማ ቤቶችን የወራሪ ኢጣሊያን ሹማምንትና
ዜጎቻቸው ከፍተው ነበር (የፊልም ማዳበሪያና መቆጣጠሪያ ዋና ክፍል፣
ገጽ 4-7)፡፡
![](https://blogger.googleusercontent.com/img/b/R29vZ2xl/AVvXsEgz-j-dYGlBf_ecdLs8qEfbE3zLQIfT7Vkrt0RrDWv7UxDnKzcIEcdYZCetq_YrGy24RtwuxY8ALdUJwvUGBDgB43lECqgRny1JY2a0KxVVWefUG3P_An79sTX509Y5z4Bz7O9lcHsnJrXP/s320/images9.jpg)
***************************************
![](https://blogger.googleusercontent.com/img/b/R29vZ2xl/AVvXsEjRqhXAZxOmk_DYoaAIN3NRXd0eno8ed0sc6ImwIA3diIjbTGBtTz9coQDkS8U-NxPCMyqEjjbwmxDOgnfDC8_TEYL_zhstGZXyYbF32dyhJiw0X0ZMiKeEU3pEYdxieZCxVNu0ZdhGgnUC/s1600/images.jpg)
የሲኒማነት
ደረጃ ላይ የደረሱ ፊልሞች ሊያሟላቸው የሚገባቸው አራት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛ፣ የመተረክ ዕውቀትና ክህሎት ነው፡፡ ለመተረክ ደግሞ የራስን ታሪክ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰው የራሱን ታሪክ
ሳያውቅ አንደምን አድርጎ የሌሎችን ታሪክ ለመተረክ ይችላል? የራስን ታሪክ ማወቁ ሁለት ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ በመጀመሪያ፣ በራስ
ታሪክ ላይ እምነት ለማሳደር ማስቻሉ ነው፡፡ የራስን ታሪክ አውቆና አቀላጥፎ መተረክ የሚችል፣ የሌሎችም ታሪክ ለመተረክ ይችላል
(ሃይሌ ገሪማ፣ 1996)፡፡ ቀጥሎም፣ የራስን ታሪክ ካለማወቅና ካለመተረክ የሚመነጩ ችግሮች ዞሮ ዞሮ ወደ ኩረጃና ወደ ጥራዝ-ነጠቅነት
ስለሚከቱ ውጤቱ አደገኛ ነው የሚሆነው፡፡
የሲኒማነት
ደረጃ ላይ የደረሱ ፊልሞች በሁለተኛነት ሊያሟሉ የሚገባቸው ነጥብ አለ፤ እርሱም ብሔራዊ እውነትና ውበት እንዴት እንደሚሰምር መረዳት
ነው፡፡ “እውነት” ሲባልም የከያኒው ውስጣዊ እምነትና አቋም ከከያኒው ውጫዊና ከባቢያዊ እውነታ ጋር የታረቀና ስምም እንዲሆን ማድረግ
ነው፡፡ ራሱ የማያምንበትን ነገር ለሌሎች መናገርም ሆነ፣ የሌሎችን እውነት ክዶ መሟገት ትርፉ ባዶ ልፈፋ ነው፡፡ ብሎም ለፕሮፓጋንዳና
ለወቅታዊ ፍጆታ ሰልፈኛ ከመሆን አያድንም፡፡ መገናኛ ብዙኃን ዓባይ-ዓባይ እያሉ ሲያላዝኑ ሰምቶ፣ “ዓባይ” ወይም ናይል ብሎ መስገብገብ
ትርፉ ባዶ ነው፡፡ ስለባህር በር ጉዳይ ወቅታዊ አጀንዳ ሲሆንም “የባህር በር” ብሎ መጣደፍ ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡ እነዚያን
“ፊልሞች” ከጥቂት አመታት በኋላ ዞር ብሎም የሚያየው ተመልካች አይገኝም፡፡ የፊልም ሰሪውንም ለእውነት ያልቆመና ሸቃይ መሆኑን
ያጋልጣል፡፡
በወቅታዊ
ጉዳይ ላይ በስገብገብም የፊልም ስራውን በተለይ፣ የስነ-ጥበቡን ዘርፍ ባጠቃላይ ቅጥ የለሽ (Formless) ያደርገዋል፡፡ ከአርስቶትል
ጀምሮ እስካሁን ድረስ የተነሡት የስነ-ውበት ሊቃውንት እንደሚያስገነዝቡት ከሆነ፣ ያለቅርጽ ምንም ዓይነት ውበት መግለጫ መንገድ
የለም፡፡ “ሲያዩት ያላማረ….” የሚለው የሃገራችን አባባል ከንጽሕና ጋር ባቻ ሳይሆን ከቅርጽ ጋርም ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡
ስለሆነም፣ ስነ-ውበትን መረዳትና ለኪነ-ጥበባዊ ስራውንም ተስማሚ ቅርጽ መስጠት የአንድ ከያኒ ግዴታው ነው፡፡ “የፊልም ይዘቱና
የአቀራረብ ስልቱም ስነ-ጽሑፋዊ ነውና ቅርጽና ቅጥ ያስፈልገዋል፤” ይላል በርናርድ ዲክ Anatomy of Film በተባለው መጽሐፉ ውስጥ፣ ገጽ 254-6 ይመልከቱ)፡፡
በሦስተኛ
ደረጃም፣ አንድ የፊልም ሠሪ ስለቋንቋውና በቋንቋው አማካይነት ሊያስተላልፈው ስለሚፈልገው እውነትና ውበት ትክክለኛ አቋም ሊኖረው
ይገባል፡፡ የብዙኃኑን ሕይወትና አኗኗር ለማሳየት ተነስቶ የተንጣለለ የተውሦ ቪላና ፎቅ ቤት ውስጥ መንከላወስ የቋንቋ እጥረትን
ያስከትላል፡፡ ስለሆን፣ ከያኒው ስለሚያውቀውና እየኖረበት ስላለው ሕያወት ቢተርክ ያዋጣዋል፡፡ እውነታውን በሚያውቀውና በገባው መልኩ
ሌሎች እንዲያውቁትና እንዲገባቸው ለማድረግ ቋንቋና እውነታ እንደሰልባጅ አያጥረውም፡፡ የፈረደባቸው የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮችና ፖለቲከኞች፣
ቀሳውስትና ባለጸጐች ላይ ፊጥ ከማለቱ በፊት የራሱን ኑሮና ሕይወት፣ ታሪክና እምነት መርምሮና ተፈላልጎ መጻፍ ከግልብነት ያድናል፡፡
የፕሮፌሰሩን የመነጽር አደራረግና አስተያየት ሳይመረምሩ፣ ወይም የኢንቨስተሩን ሚስት የመዋቢያ ቁሳቁስ አጠቃቀምና አኳኋን ሳያጠኑ፣ የአዛውንቱን
የእጅና የፊት እንዲሁም የሰውነት እንቅስቃሴዎች ከነለዛቸው ሳይረዱና ሳያውቁ የተዋናዩ ላንቃና መንጋጋ ውስጥ ለመጠቅጠቅ
መጀል አጉል ነው፡፡ የፊልም ሠሪ መጀመሪያውኑ ስለባለታሪኮቹ ማንነትና ስለሚናገሩት ቋንቋም በቅጡ ሊያውቅ ይገባዋል፡፡
በአራተኛ
ደረጃም፣ አንድ የፊልም ሠሪ የፈጠራቸው ገጸ-ባህሪያት ባለው ህብረሰብ፣ ባህል፣ ተፈጥሮና በስርዓቱ ጉድፎች ላይ የሚያምጽ መሆን አለበት፡፡ ዓመፁም ለበጎ
ነው፡፡ ለለውጥ ነው፡፡ ወደ ለውጥ ነው፡፡ የሰው ልጅ ታሪክ የማያቋርጥ የለውጥ ሂደትና ትግልም ነው፡፡ የለውጥ ትግሉና መፍጨርጨሩም
ስልጣኔን ለማወጅ ነው፡፡ ሥልጣኔ፣ የብዙ እሴቶች ድምር ነው፡፡ ሰው ወደ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ሠላም፣ ፍቅር፣ እውነት፣ ነፃነትና
ሌሎችም ረቂቅ እሴቶች ዝንት ዓለም ሲፍገመገም ይኖራል፡፡ በፊልም ወስጥ ያሉት ገጸ-ባህሪያትና ፊልሙም ሰብዓዊ ውበትንና እውነትን
ለማምጣት ስለሚታገሉና ስለሚያምጹ ሰዎች መሆን ይገበዋል፡፡ ሲረገጡና ሲበደሉ፣ “በጄ!.....እሺ!....አሜን!....ወይም ተመስጌን!”
የሚሉ ልፍስፍስ ባለታሪኮችን ይዞ የሚነሳ ፊልም ሠሪ ሁለት ግድፈቶችን ፈጽሟል፤ አንደኛ፣ የሰው ልጅ በለውጥ ጅረት ውስጥ ወደ ስልጣኔ
የሚያደርገውን በውጣ ውረድ የተሞላ ትግልና፤ ሁለተኛም፣ ከያኒው ለሰብዓዊ ውበትና ክብርም ያለውን ዝቅተኛ ግንዛቤ ያሳያሉ፡፡
ከላይ
የጠቀስኳቸውን አራት ነጥቦች ቸለል ካልናቸው ወደብሔራዊ የፊልም ግብና ዓላማ መቼውንም አንደርስም፡፡ ዛሬ በተስፋና በጉጉት ለሰዓታት
ፊልም ቤቶች ደጃፍ ላይ ተሰልፎ ለማየት የተነቃነቀው ተመልካቸም ደብዛው የጠፋል፡፡ የተመልካቹ ንቃተ-ሕሊናም እያደገና እየጎለበተ
ነው፡፡ በTV-Africa ፋንታ፣ ደህና ደህና ፊልሞችን በተለያዩ Channels በማየት ላይ ነው፡፡ በተንቀሳቃሽ ምስሎች በኩል
ንቃተ-ሕሊናው እያደገ ነው፡፡ ዓይኖቹንና ቀልቡን ከተንቀሳቃሽ ምስልና ከቴክኖሎጂ ጋር እያለማመደ ነው፡፡ አንድ ቀን፣ ዛሬ ላይ
የተሠሩለትንና የተሠሩበትን “ነገሮች” አሽቀንጥሮ ይጥላቸዋል፡፡
***************************************
![](https://blogger.googleusercontent.com/img/b/R29vZ2xl/AVvXsEh42wPKd6xaA-viR87RT1HX_891IK0599AJKwIxrjYFq22sYFVm2URietHI94e4952zJBo3KjUffiklZOprrVzPiuZeIf6Avfe-A8p12tB2gZWRZ85ax_rxxjMM7tBMZQwl97qN-SYX3m4i/s1600/images2.jpg)
![](https://blogger.googleusercontent.com/img/b/R29vZ2xl/AVvXsEjB_zgMmHwmnWPckKWWX4BRljJLGTvMjy_eOoRYlCfa6qKPBlTn44qhaxyBUcJx1nmBIG2kyUu0kmuejNsGINRWfpNy9BXoY7dlKsfE-4_0row5ovhgmVaMUqjCBGJiAfhYv_fwAYSAar6G/s1600/images5.jpg)
![](https://blogger.googleusercontent.com/img/b/R29vZ2xl/AVvXsEiopp_tEqnFw_IkAhwcXWrLjuiZwnbTFwsoVtUEC76NYTkcNKCYGi53zgokbrrZLBVWV4JiN6dr7G06VabX7wEeskVUuJRRCXYITOanuc6ivxxG0WeDDIzQa4ltFa_ThxKS_a8g2B8cUX8-/s1600/images1.jpg)
ይህ
እውነት ነው፡፡ ምክንያቱም ፊልም፤ የስነ-ጽሑፍን፣ የፎቶግራፊን፣ የሙዚቃንና የዳንስን፣ የቲያትርንና የሰርከሥን፣ የስዕልን፣ የምትሃትን
(የአስማትን)ና የሌሎችንም ጥበባዊ ዘርፎች ባንድነት አዋሕዶ የያዘ በመሆኑ “ሰባተኛው ስነ-ጥበብ” ብለው የሚጠሩትም አልጠፉ (ሲን ኩቢት፣ History of Ideas በተባለው መጽሐፍ ውስጥ በገጽ 327 ላይ እንደገለጸው) ነው፡፡ በተመልካቹም ዘንድ
ከፍተኛ የሆነ ግምት አለው፡፡ የፊልም ስራ ንግድን ብቻ ሳይሆን፣ ስነ-ጥበባዊ በሆነ አቀራረቡ ከዋነኛዎቹ የመገናኛ ብዙኃን ዘዴዎች
መሃከልም አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም፣ “የፊልም ሠሪው ከባድ ሕዝባዊ ኃላፊነት ያለበት ነው” ይላሉ የማርክሲስት ፈለግ አቀንቃኝ ሊቃውንት፡፡
![](https://blogger.googleusercontent.com/img/b/R29vZ2xl/AVvXsEisdWIci-HbgglJReojl7BsjrXAuNFV4icz6s4Wz8iYIUf3xXz-uB0oD9OOWCojgaYhnID2mgSktykYrYuM6rniJ-N5Eq35-lBKqe4O8bgdWrOiToIH8Eb63qq3-QhD-rj-e7hPc4WRzDwS/s1600/images3.jpg)
![](https://blogger.googleusercontent.com/img/b/R29vZ2xl/AVvXsEgnNVmB8PPpQL1lgZrhOQEyoHzPIKVHJkmWmXCd7zXoMgVhCV6dcgEh5zQHvvLeMs2P59hSrwO6KVBm8mt_4tLJDWp5QcK42CZ7min2U0LWMvub-7sn4myLcANhVmyAcDHRk-P0L9BOjzPJ/s400/images4.jpg)
****************************
ምንጭ፡-http://semnaworeq.blogspot.com
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ