ሰኞ, ሜይ 20, 2013

ከስፖርቱ ዓለም

ጃፓናዊያን ሴቶች በፍቅር ያበዱለት የማራቶን ጀግና

                                            በ ፍስሃ ተገኝ
***************************************************
በአንድ ወቅት ጃፓናውያን ሴቶች አብረውት ለመሆን በቁጥር አንድነት የሚመኙት ጎረምሳ ነበር። እሱ ያለበትን ሁኔታ በንቃት ይከታተላሉ፣ ባዩት ቁጥር በደስታ ይጮሀሉ። ስለ ብራድ ፒት ወይም ዴቪድ ቤካም እያወራሁ አይደለም፤ ስለ አበበ ቢቂላ እንጂ። እ.አ.አ በ1961 ዓ.ም በጃፓኗ ኦሳካ ከተማ በተካሄደው የማራቶን ውድድር ላይ ተሳትፎ  በአሸናፊነት ካጠናቀቀ በኋላ በጃፓናውያን ሴቶች ልብ ውስጥ መግባት የጀመረው አበበ ቢቂላ በ1964ቱ የቶኪዮ ኦሎምፒክ ለመሳተፍ ወደጃፓን ሲሄድ በሰውነት አቋማቸው ከሚበልጡትና በእድሜ ከሱ ከሚያንሱት ፈርጣማና ጡንቸኛ አሜሪካዊን የኦሎምፒኩ ተሳታፊዎች ቦክሰኛው ጆን ፍሬዠርና ዋናተኛው ዶናልድ አርቱር ሾላንደር ይልቅ የሀገሪቷን ሴቶች ቀልብና ልብ መስረቅ ችሏል።
እ.አ.አ በ1932 ዓ.ም ሰሜን ሸዋ ጃቶ ውስጥ የተወለደው አበበ፤ ከእናቱ ጋር ለመኖር በሚል የትውልድ ቦታውን ትቶ ወደ አዲስ አበባ ከሄደ በኋላ በቅድሚያ ከከተማዋ የወደደው ነግር ቢኖር ጥርት ያለና ስርአት ያለው የደንብ ልብስ የሚለብሱት የአጼ ኃይለ ስላሴ ክቡር ዘበኛ አባሎች ነው። እናም በ1956 ዓ.ም አበበ ክቡር ዘበኛን ተቀልቀለ። ክቡር ዘበኛ ውስጥ በጥሩ ዋናተኛነት፣ በጎበዝ ፈረስ ጋላቢነትና በገና ተጨዋችነት ከመታወቁ በስተቀር በሩጫ ማንም ግምት አይሰጠውም ነበር።
በጊዜው የአበበ ቢቂላ አሰልጣኝ የነበሩት ሲውዲናዊው ኦኒ ኒስከነን አበበን አስመልክተው ሲናገሩ “ከ1959 ዓ.ም በፊት አበበን በጭራሽ አላውቀውም ነበር። የኦሎምፒክ የመጀመሪያ ማጣሪያ ውድድር ላይ ሶስተኛ ቢወጣም የሩጫ ብቃቱ አሳማኝ አልነበረም። ምክንያቱም እጆቹ እዛና እዚህ ሲወራጩ ማየትና የሚዛን አጠባበቅ ችግር አበበ ላይ ማየት የተለመደ በመሆኑ አንዳንድ ጊዜ እጮህበት ነበር። በርግጥ መስዋእትነት መክፈልንና ጠንክሮ መስራትን ከእሱ ጋር የሚስተካከል ማንም አልነበረም። ታላቁ አበበን የፈጠረው እራሱ አበበ ነው። እኔ ለእርሱ ታላቅነት ምንም አስተውጾ አላበረከትኩም” አሉ።
ወደሮም ለ1960ው ኦሎምፒክ ከመሄዱ በፊት ከኢትዮጵያ ውጪ አንድም ውድድር ያላደረገውና ሩጫን ዘግይቶ የጀመረው አበበ፤ ለኦሎምፒኩም የመጀመሪያ ተመራጭ አልነበረም። የመጀመሪያ ተመራጭ የነበረው ዋሚ ቢራቱ ጉዳት ደረሰበትና አበበ ዋሚን ተክቶ ቡድኑን ተቀላቀለና ጉዞ ወደ ሮም ሆነ።
የኦሎምፒኩ የማራቶን ውድድር ከመጀመሩ ሁለት ሰአታት በፊት አበበ ሌላ አስገራሚ ክስተት አጋጣመው። በውድድሩ ለአትሌቶች ጫማዎችን ሲያቀርብ የነበረው አዲዳስ በቂ ጫማዎች ስላልነበሩት ለአበበ እግር ይበቃሉ ተብለው የተገመቱ የተለያዩ ጫማዎች ቢሞከሩም ሊገኙ አልቻሉም፤ የተቃረቡትም ያበረከቱት አስተዋጾ ቢኖር አለመመቸትና እግሩን ማቁሰል ነበር። ሀገሩ በልምምድ ወቅት በአብዛኛው ያለጫማ ይሮጥ የነበረው አበበም “በባዶ እግሬ እሮጣለሁ” የሚል ሀሳብ አቀረበና አሰልጣኙም በሀሳቡ ተስማሙ።
ውድድሩ ተጀመሮ የርቀቱን ሩብ ያህል እንደሮጡ ከመሪዎቹ በትንሽ የሚርቀው አበበ ፍጥነቱን ጨመረና ቤልጄማዊው ኦውሬል ቫን ዴን ሬሽኽ፣ ብሪታኒያዊው አርቱር ኬሊ እና ሞሮኳዊው ራህዲ ቤን አብዲሰላም የሚገኙበትን የመሪዎቹን ቡድን ተቀላቀለ። የ42.196 ኪሎ ሜትሩን ግማሽ ካለፉ በኋላ አበበና ራህዲ ከሌሎች ተገንጥለው በመውጣት መሪነቱን ለብቻቸው ተቆጣጠሩ።

አበበ በሮም ጎዳናዎች ላይ በባዶ እግሩ ሲገሰግስ
ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት አሰልጣኝ ኦነኒስከን የአበበ ተፎካካሪ 26 ቁጥር የተጻፈበት መለያ የሚለብሰው ሞሮኳዊው ራህዲ ሊሆን እንደሚችል በመገንዘባቸው ለአበበ “26 ቁጥር የለበሰው አትሌት ላይ ትኩረትህን አድርግ” የሚል መለክት አስተላልፈው ነበር። በሚገርም ሁኔታ ታዲያ ውድድሩ ከተጀመረ በኋላ ራህዲ የለበሰው 26 ቁጥር ሳይሆን 10 ሺህ ሜትር ሲሮጥ የለበሰው 185 ቁጥር የተጻፈበት ማሊያን መሆኑ ነው። ውድድሩ እየተጋመሰ ሲሄድ አበበ ወደ ግራና ቀኝ፣ እንዲሁም ወደኋላ ዘውር እያለ 26 ቁጥር የለበሰ ሲፈልግ ሊያየውና ሊያገኘው አልቻለም። ለካ ራህዲ አብሮት ከአበበ ቢቂላ አጠገብ በመሪነት እየሮጠ የነበረው 185 ቁጥር የለበሰው አትሌት ሆኗል።
ማራቶኑ ሊጠናቀቅ ሶስት ኪሎ ሜትሮች ያህል እስኪቀሩት ድረስ አበበና ራህዲ ጎን ለጎን አብረው ከሮጡ በኋላ፤ አበበ ፍጥነቱን ጨመረና ራህዲን በ200 ሜትሮች ያህል በመቅደም አንደኛ ወጥቶ ለኢትዮጵያና ለጥቁር አፍሪካ በኦሎምፒክ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኘ። በስታዲዬሙ የተገኘውን ተመልካችና አለም አቀፉን መገነኛ ብዙሃን ያስገረመው ሌሎቹ ሯጮች ሲያለክልኩና ጥቂቶቹም ራሳቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ሲውድቁ፤ በባዶ እግሩ ማራቶኑን የሮጠው አበበ ስታዲየሙ ውስጥ ሲያሟሙቅና ሰውነቱን ሲያፍታታ ማየታቸው ነበር።
ከውድድሩ በኋላ የአበበ በባዶ እግር ሮጦ ማሸነፍ ያስገረማቸው ጋዜጠኞች አሰልጣኝ ኦኒ ኒስካነን ሁኔታውን እንዲያብራሩላቸው ሲጠይቋቸው “በባዶ እግሩ መሮጡ ምንም አያስገርምም። ልምምድ ላይ በባዶ እግሩ ሲሮጥ አንድ ደቂቃን በ98 ርምጃዎች ሲሸፍን፤ በጫማ ሲሮጥ ደግሞ ደቂቃን በ96 ርምጃዎች ሲሸፍን አይቻለሁ። እናም ብዙ ልዩነት አይኖረውም ብዬ ስላሰብኩ በባዶ እግሩ ተመችቶት እንዲሮጥ ወሰንን። ምን አልባት ጫማ በኮረኮንቻማ ቦታዎች ላይ ሊጠቅምህ ይችላል፤ ብዙ እግርህን ሊያቆስሉህ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉና። የሮም ጎዳናዎች ግን እንደዛ አይደሉም። ስለዚህ አበበ ‘በባዶ እግሬ ልሩጥና ለአፍሪካ ታሪክ እንስራ አለኝ፤ እኔም ተስማማሁ።’ በጣም አርበኝነት የሚሰማው ሰው ነው” የሚል ነበር መልሳቸው።
የአበበ ቢቂላ ወርቅ ሜዳሊያና የሞሮኳዊው ራህዲ ብር ሜዳሊያ በወደፊት የኦሎምፒክና የተለያዩ አለም አቀፍ ውድድሮች ላይ አፍሪካዊያን ሩጫን በበላይነት ሊቆጣጠሩ እንደሚችሉ ምልክት የሰጠ ነበር።

ቁጥር አንዱ አበበ ቢቂላ
በሮም የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ከሆነ በኋላ በግሪክ፣ ጃፓንና ቼኮዝሎቫኪያ ላይ የተካሄዱ የማራቶን ውድድሮችን ያሸነፈው አበበ ቢቂላ እስከ ቶኪዮ ኦሎምፒክ መቃረቢያ ድረስ ያሉትን ጊዜያት በጥሩ ሁኔታ አላሰለፈም ማለት ይቻላል። የአበበን በጥሩ አቁም ላይ አለመገኘት የተገነዘቡት በርካታ የዘርፉ ባለሞያዎችና መገናኛ ብዙሀን ከኦሎምፒኩ መጀመር አራት ወር ቀደም ብሎ አዲስ የአለም የማራቶን ክብረወሰንን 2 ሰአት ከ13 ደቂቃ 55 ሰከንድ በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው ብሪታኒያዊው ቤንጃሚን ባሲል ሄትሊ የቶኪዮው ኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ይሆናል የሚል ግምት ሰጡ። ይባስ ብሎ አበበ ጠንካራ ልምምዶችን በማድረግ ድክመቱን ለማካካስ ጥረት እያደረገ እያለ የትርፍ አንጀት ህመም አጋጠመውና ኦሎምፒኩ ከመጀመሩ ከአራት እስከ ስድስት ሳምንታት ቀደም ብሎ የቀዶ ጥገና ህክምና በማድረጉ ልምምዱ ተሰናከለ። ሆኖም ልክ ሀኪሞቹ ለአሰልጣኝ ኒስከነን እንደነገሯቸው አበበ በቶሎ አገገመና የቀዶ ጥገና ህክምናውን ካደረገ ከሁለት ሳምንታት ቆይታ በኋላ ልምምድ መስራት ጀመረ።
ለኦሎምፒኩ ማሟሟቂያና ማጣሪያ እንዲሆን አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደ የማራቶን ሩጫ ውድድር ማሞ ወልዴን በአንድ ሰከንድ ቀድሞ አንደኛ የወጣው አበበ ያስመዘገበው 2 ሰአት ከ16 ደቂቃ 18.8 ሰከንድ የሆነ ጊዜ ምን አልባትም ሁለተኛ የወርቅ ሜዳሊያውን ለማግኘት እድል እንዳለው ያሳየ ነበር።
64 ተወዳዳሪዎች በተሳተፉበት የ1964ቱ የቶኪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር ሻምበል አበበ ቢቂላ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 10 ኪሎ ሜትሮች እስኪቀሩ ድረስ መሪነቱን በተረጋጋ ሁኔታ ለመያዝ ቻለ። ብዙም ሳይቆይ ታዲያ አበበ ከሌሎቹ አትሌቶች ተገንጥሎ ወጣና ለብቻው መሪነቱን በመቆጣጠር ብሪታኒያዊውን የአለም ክብረወሰን ባለቤት ባሲል ሄትሊን በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ቀድሞ 2 ሰአት ከ12 ደቂቃ 12.2 ሰከንድ በሆነ ጊዜ የአለም ክብረወሰንን በመስበር አንደኛ ወጥቶ ለሁለተኛ ጊዜ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆነ።
አሶሺዬትድ ፕሬስ ሁኔታውን እንዲህ በማለት ነበር የዘገበው። “አበበ ተከታዩን በሰፊ ልዩነት በመቅደም ወደቶኪዮ ስታዲዬም ከገባ በኋላ ሁለት እጆቹን ወደላይ አንስቶ የመጨረሻውን ገመድ በደረቱ በጥሶ አንደኛ ወጣ። ከዛም ወደሜዳው መሀል ገባና ሳሩ ላይ በጀርባው ተኝቶ እግሮቹን ልክ የብስክሌት ፔዳል እንደሚመታ ሰው አይነት እያወራጨ በማፍታታት ስታዲዬም የተገኘው ተመልካችን አስደመመ።”
ከቶኪዮው ወርቅ ሜዳሊያ በኋላ አበበ በ1965 ዓ.ም ወደ ጃፓን በመመለስ የኦትሱ ማራቶንን አሸነፈ። በቀጣዩ አመት ደግሞ የባርሴሎናው ዛራውትዝ ማራቶንን በማሸነፍ ለ1968ቱ የሜክሲኮ ኦሎምፒክ ዝግጁ መሆኑን ለአለም አረጋገጠ። የ36 አመቱ አበበ ቢቂላ ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ የማራቶን ወርቅ ሜዳሊያን ለማግኘት ሜክሲኮ ሲገባ በጥሩ አቋም ላይ ይገኝ ነበር። እሱ እራሱ በጊዜው በሰጠው አስተያየት “በጣም በጥሩ አቋም ላይ ስለምገኝ አሸንፋለሁ ብዬ እጠብቃለሁ። ነገር ግን በእንደዚህ አይነት ረጅም ሩጫ ያልተጠበቀ ነገር ሊፈጠር ይችላል። ያልተጠበቀው ተከስቶ የምሸነፍ ከሆነ በሀገሬ ልጆች ማሞ ወልዴና መርሀዊ ገብሩ ብሸነፍ ይሻለኛል” አለ።
የሜክሲኮው ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር ከመጀመሩ በፊት የነበሩት አራት ቀኖች ለአበበ መጥፎ ጊዜዎች ነበሩና ቀናቶቹን በህመም አሳለፈ። ውድድሩ ተጀምሮ 10 ኪሎ ሜትሮች ያህል እንደሮጠ ታላቁ አትሌት ውድድሩን አቋርጦ ወጣና ሌላው ኢትዮጵያዊ ማሞ ወልዴ አንደኛ በመውጣት አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት በመሆን ለኢትዮጵያ ሶስተኛውን ተከታታይ የማራቶን ወርቅ ሜዳሊያዎች አገኘ።

ቀስተኛው አቤ ለድል ሲያነጣጥር
መጋቢት ወር አጋማሽ 1969 ዓ.ም ላይ ይነዳት የነበረችው ፎልስቫገን መኪና ተገልብጣ አደጋ የደረሰበትና እግሮቹ ፓራላይዝ የሆኑት ሻምበል አበበ ቢቂላ፤ እነዛ የወርቅ ሜዳሊያዎች ያስገኙለት አስደናቂ እግሮቹን ወደስራ እንደገና ለመመለስ ህክምናዎችን ቢያደርግም የተደረገው የህክምና ጥረት ውጤታም አልሆነም። የመጨረሻ አማራጭና ተስፋ በሚል ወደእንግሊዝ ተወስዶ በስቶክ ማንዴቪል ሆስፒታል ህክምና ቢደረግለትም አበበን እንደገና ወደሩጫው መመለስ ሳይቻል ቀረ። ታዲያ ተስፋ የማይቆርጠው አበበ “መሮጥ አልችልም” ብሎ ከስፖርቱ አለም ከመራቅ ይልቅ ራሱን ወደቀስት ወርዋሪነት አሸጋገረና በእግሮቹ ያገኛቸውን ድሎች በእጆቹም ለመድገም ወሰነ። ምንም እንኳን እንዳሰበው ውጤታማ ባይሆንም በ1969 ዓ.ም በተካሄደው የዊልቸር ኦሎምፒክ በጀማሪ ቀስት ወርዋሪዎች ክፍል ተወዳድሮ ዘጠነኛ ደረጃን አግኝቶን ጨረሰ።
የሚያሳዝነው ነገር ታላቁ አበበ ቢቂላ ገና በ41 አመቱ በ1973 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለየና የአትሌቲክስ ስፖርት አፍቃሪው አለምና ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው አጡ።
በቅርቡ የአለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር መቶኛ አመት ምስረታን አስመልክቶ የስፖርቱ የታላቆች ታላቅ ተብለው ከተመረጡት ቀዳሚ 12 አትሌቶች መካከል ኢትዮጵያዊው ጀግና አበበ ቢቂላ አንዱ ነበር። ወረቀት ላይ ከተነደፉ እቅዶች ይልቅ የራሱን የተፈጥሮ የሩጫ ችሎታን እና ነገሮችን እንደየአመጣጣቸው የማንበብ ብቃቱን በመጠቀም ታላቅ ታሪክን የሰራው የአበበ ቢቂላን ሩጫዎች ያላዩ ታሪኩን ሲሰሙ የአፈታሪክ ያህል ነው የሚሆንባቸው። “ማራቶንን በባዶ እግሩ ሮጦ መጨረስ ብቻ ሳይሆን አንደኛ ወጥቶ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነ አትሌት አለ” ብሎ አንድ ሰው ጎዳና ላይ ላገኘው ሰው ቢያወራ “አብደሀል ወይ፤ ለምን የማይሆን ነገር ታወራለህ” ነው የሚባለው። አበበ ግን ተአምረኛ ነበርና አድርጎታል፤ ለሰሚ እውነት የማይመስል እውነትን ያውም በታላቁ ኦሎምፒክ ላይ ፈጽሟል።
******************************************************************************
ምንጭ:---http://www.total433.com

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ማሞ ካቻ (አቶ ማሞ ይንበርብሩ)

  አቶ ማሞ ይንበርብሩ (ማሞ ካቻ) እስቲ እናስታውሳቸው፣ ተቀብሮ እንዳይቀር አኩሪ ታሪካቸው  (ደረጀ መላኩ)   አቶቢሲ ማሞ ካቻ የት ትሄዳለህ? ገብረ ጉራቻ… ታዳጊው ማሞ ይንበርበሩ ገና በጨቅላ እድሜው አባቱ አቶ...