መንትያ ጥበባት፤ ግጥምና ሙዚቃ!
መንትያ ጥበባት፤ ግጥምና ሙዚቃ!
ሰሎሞን ተሠማ ጂ.
******************


ድጓ ቤት፣ ዝማሬና መዋሲት፣ እንዲሁም ቅዳሴና ሰዐታት የዜማ ተማሪው በተናጠል የሚያዜማቸው ናቸው፡፡ አራተኛውና የመጨረሻው ደግሞ፣ “አቋቋም” ይባላል፡፡ አቋቋም፣ በዜማ ቤት ውስጥ የወረብ፣ ዝማሜና ማሕሌት መማሪያ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ስልት ያለው ውዝዋዜ (ዳንስ) ነው፡፡ ይህ ክፍል በህብረት ጽናጽልና መቋሚያ ተይዞ ንፋስ ከንበል-ቀና እንደሚያደርገው ሰንበሌጥ በስልት ይወዛወዛሉ (ኃይለ ገብርኤል ዳኜ፤ 1970፣ ገጽ 91)፡፡ የነዚህ የዜማ ቤት ሊቃውንት የቀለምና የሙዚቃ ዕውቀታቸውን በሃይማኖታዊውም ሆነ በዓለማዊው ምግባራቸው ሲገለጥ ኖሯል፡፡

ከዜማ ቤት ቀጠሎም በቅኔ
ቤት ቆይታቸው ዘጠኝ ዓይነት አቀኛኘቶችን ያጠናሉ፤ ይለማመዳሉም፡፡ ከባለሁለት ስንኝ (ጉባኤ ቃና) ጀምረው ባለሦስት፣ አራት እስከ
ዕጣነ-ሞገር ወይም መወድስ ድረስ (ባለሰባት ወይም ስምንት ስንኝ ያላቸው ሰምና ወርቅ ግጥሞችን) መግጠም ያጠናሉ፡፡ ይጽፋሉም፡፡
የቅኔን አዝመራ የቆረጠመ ምናቡና ምርምሩ የላቀ መሆኑ አይጠረጠርም፡፡ የቅኔ ቤትን ያጠናቀቀ ሙያተኛ አርዕስታዊ የሆነ ርዕሰ-ጉዳይ
ላይ እንደልቡ ሃሳቡን በቃላት አማካኝነት ትርጉም መስጠት አያቅተውም፡፡ እርግጡን ለመናገር፣ የምርምርን ክህሎት ብቻ ሳይሆን የፈጠራ
ችሎታንም ያዳብል፡፡ ቅኔን ያወቀና ያጠናቀቀ ኩረጃን (Hates an imitation of an imitation) ይጠየፋል::
በተመሳሳይ ሁኔታም፣ ለምዕራባውያንም
ሙዚቃ ማለት ግጥም ነው፡፡ ግጥምና ሙዚቃ ትርጓሜያቸው አንድ ነው፡፡ በሌላ አነገገር፣ ሙዚቃ ሥነ-ጸሑፍ ነው፡፡ ዕውቀት ነው፡፡
ምናብ ነው፡፡ ፈጠራ ነው፡፡ ጥበባዊ ክህሎትን የሚጠይቅም ነው፡፡ ከሁሉም በላይ አዕምሮአዊ ነው፡፡ በመሆኑም ምዕራባዊያኑ ሊቃውንት፣
“አዕምሮአዊ አረዳዱ ዝቅተኛ የሆነ ሰው ሥነ-ጽሑፍም ስለማይገባው፣ ጥበባዊ (ክላሲክ) ሙዚቃም ምን እንደሆነ በግልፅ አይታየውም፤”
ይላሉ፡፡ ስለሆነም፣ ምዕራባውያን ዜማንና ሥነ-ጽሑፍን ጎን ለጎን ለታዳጊዎቻቸው ያስተምራሉ፡፡ የታዳጊው አዕምሮ በዜማና በሥነ-ጽሑፍ
ረገድ መንትያ ዕድገት እንዲኖረው ይደረጋል፡፡ በመጨረሻም፣ ታዳጊው ወደሚያዘነብልበት በኩል እንዲያተኩር ይደረጋል፡፡
በኢትዮጵያ ባህላዊ አስተምህሮት
ግን ነገሩ የተለየ ነው፡፡ አንድ ሰው የዜማ ቤትን ሲያጠናቅቅ ወደ ቅኔ ቤትና ወደ መጽሐፍት ቤት ያመራል፡፡ ዜማ ማለዘቢያ ነው፡፡
ዜማ የቅኔና የመጽሐፍት ቤቶች መንደርደሪያ ነው፡፡ አዕምሮን ለጥልቁና ረቂቁ የቅኔና የመጽሐፍት እንዲሁም የሊቃውንት ጥናት የሚያዘጋጀው
ዜማ ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ፣ ዜማና ሥነ-ጽሑፍ በኢትዮጵያም ሆነ በአውሮፓውያን አስተምህሮቶች ዘንድ የአንድ አላድ ሁለት ገፅታዎች
ናቸው፡፡ ይህንን መረዳትና መገንዘብም የተገባ ነው፡፡
ከላይ እንዳወሳነው፣ መዚቃና
ሥነ-ጽሑፍ በተለይም ሙዚቃና ግጥም መንትያ ናቸው፡፡ ግጥምና ሙዚቃ የሚከወኑት ለጆሮ ነው፡፡ ለዕዝነ-ልቦና ነው፡፡ ግጥም በአሰኛኘቱ
በስድስት ቤቶች ይከፈላል፡፡ ማለትም፤ የቡሄ በሉ ቤት፣ የሠደፌ ቤት፣ የወል ቤት፣ የሰንጎ መገን ቤት፣ የወዳጄ ዘመዴ ቤትና የመዲና
ቤት ናቸው (ተሾመ ይመር፣ የኢትዮጵያ ጥናት መጽሔት፡፡ ሐምሌ
1997፡፡ ገጽ 89-123)፡፡ እንደግጥም ሁሉ፣ ሙዚቃም ብዙ ዓይነቶች አሉት፡፡ በድምፅ አሳክቶና
አቀናብሮ የታቀደውን ሃሳብ በሰሚው መንፈስና ስሜት፣ እንዲሁም በሰሚው አእምሮ ላይ ትርጉም እንዲያገኝ ለማድረግ ዘዴውንና እውቀቱን
ከችሎታ ጋር መጠየቁን ማወቅ የሙዚቃ ባለሙያው ግዴታ ነው፡፡ አድማጩም ቢሆን ለዚህ ዓይነቱ የሙዚቃ ዝግጅት የሠለጠነ መሆን ያስፈልገዋል፡፡
ከይዘት አንጻር ግጥም
በሁለት ይከፈላል፡፡ ኃይማኖታዊና ዓለማዊ ይዘት ያላቸው ግጥሞች ይባላሉ፡፡ ለአንባቢውና ለአድማጩ ዕዝነ-ልቦና ባላቸው የመደመጥና
የመነበብ ኃይላቸው በሁለት ይከፈላሉ፡፡ የዱሮውንም የአሁኑንና የመጪውን ትውልድ ዓይንና ጆሮ በመያዝና ባለመያዝ አቅማቸው በሁለት
ይከፈላሉ፡፡ እነርሱም ጥበባዊ (Classical) ኃይል ያላቸው እና ጊዜያዊ (popular) ስሜትን ለማጫር ሲባል የሚገጠሙ ግጥሞች
ናቸው፡፡ አከፋፈሉ ከአድማጩ አንፃር መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡
በተመሳሳይ ሁናቴም ከይዘት
አንፃር፣ “ማንኛውም ሙዚቃ ሁለት ታላላቅ የዓይነት መክፈያዎች አሉት፡፡ እነርሱም 1ኛ/ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ሙዚቃዎችና 2ኛ/
ዓለማዊ ይዘት ያላቸው ሙዚቃዎች ተብለው ነው፡፡ እንደግጥም ሁሉ ሙዚቃዎችም በአድማጩ ዕዝነ-ልቦና ላይ ባላቸው የመደመጥ ኃይልና
እንደወይን እያደር በቀማሹ ላይ በሚኖራቸው የማምጠቅ ቃና በሁለት ታላላቅ ክፍሎች ይከፈላሉ፡፡ 1ኛ/ ጥበባዊ (Classical
music) ሙዚቃ የሚባሉት ሲሆኑ 2ኛ/ ደግሞ ጊዜያዊ (popular music) ሙዚቃ ተብለው ነው፡፡ ጥበባዊና ጊዜያዊ ሙዚቃዎች
በአቀራረብ ስልታቸው መሰረት በሦስት ንዑስ ክፍሎችና ዓይነቶች ይከፈላሉ፡፡ 1ኛ/ ድምፃዊ ሙዚቃ 2ኛ/ መሳሪያዊ ሙዚቃ ሲሆኑ 3ኛ/
የድምጻዊና የመሳሪያዊ ሙዚቃዎች ውሁድነት የሚቀርቡና የሚቀርቡበት ስልት ነው” (ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ፡፡ የካቲት 8 ቀን 1960 ዓ.ም፤ ገጽ
5)፡፡

3ኛ/ የፕሮፌሰር አሸናፊ
ከበደ “እረኛው ባለዋሽንት”ና ወይም “ኒርቫናህ” የተባሉት ሙዚቃዎች፣ ወይም የሙላቱ አስታጥቄ “የልቤ ትዝታ” እና ሌሎቹም ቅንብሮቹ
ደግሞ ጥበባዊ ናቸው፡፡ ዓለማዊም ናቸው፡፡ መሳሪያዊ ብቻ ናቸው፡፡ ..... “ጥበባዊ ሙዚቃ” ናቸው ስልም፤ “የታቀደውን የሙዚቃ
አርእስትና ሃሳብ በድምፅ አሳክቶ፣ አዳብሮና አስፋፍቶ ለአድማጩ መንፈስ፣ አእምሮና ስሜት እንደታቀደው ለማስተላለፍ የሚችለውን ዓይነት
ሙዚቃዎች ናቸው” ለማለት ነው፡፡ እነዚህ ሙዚቃዎች የደራሲውን የጥበባዊ ሙዚቃ ቅመራ ችሎታ ብቻ ሳይሆን የአድማጩንም የአእምሮ ጉልምስና
ይጠይቃሉ፡፡ ጆሮና ዕዝነ-ልቦናው ያልተገራውን አድማጭ ጨርሶ ላይወዘውዙትም ይችላሉ፡፡
ጊዜያዊ (Popular
Music) ሙዚቃ የሚባለው ዓይነት ብዙው ጊዜ የስሜት ብቻ ማስደሰቻ፣ የዳንኪራ መምቻ፣ የሽለላና የፉከራም ማሰሚያ ነው፡፡ ግጥሙም
ሆነ ሙዚቃው ያልተያያዘና ያልተገጣጠመ፣ በመሳሪያና በድምፅ ጩኸትና ኳኳታ ብቻ የተሸፋፈነ ሲሆን ጠለቅ ብለው የማይመራመሩና ጊዜያዊ
ጭፈራዎችን የሚሹትን አድማጮች ስሜት ቀስቃሽ ነው፡፡ በብዙ መልኩ ከንግድና ከትርፍ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ጊዜያዊ (Popular
Music) ሙዚቃ ብዙውን ጊዜ የአድማጮችን “ጊዜያዊ ደስታ” ብቻ ዓላማው ስለሚያደርግ በጥበባዊ ዝግጅት በኩል በብዛት “ባዶ” መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ “ባዶ ጩኸት ብቻ ነው፡፡” ምክንያቱም
1ኛ/ ተጫዋቾቹ የመዚቃ ችሎታ ስለሌላቸውና ችሎታቸውንም ለማሻሻል ስለማይጥሩ፤ ሲሆን 2ኛ/ የሚበዛው የዓለም ሕዝብ የሚወደው ይሄንኑ
ዓይነት ጩኸትና አደንቋሪ ስልት ስለሆነ ነው፡፡ ተለይም በትንሽ ድካም ብዙ ገንዘብ የሚተረፍበት የሙዚቃ ዓይነት ስለሆነ ነው ጥበባዊ
ይዘቱ ኦና ነው፡፡ 3ኛ/ ሙዚቃውና ግጥሙም በትንሽ ድካምና ልምምድ (የውጭ አገሩን ዜማ በመመንዘርና በመኮረጅ የጊዜውን ትኩሳት
ለመቀስቀሻነት የሚሆኑትን ቃላት በግጥም መልክ በማሳካት) ተዘጋጅቶ የሚቀርብበት ስልት ነው፡፡
4ኛ/ የተጫዋቾች የቀለምና
የሙዚቃ ትምህርት ደረጃቸው በጣም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ መጥፎውንና ጥሩውን ግጥምና ዜማም ስለማይዩት የለብ ለብ ስራ ይሰራሉ፡፡ የሆነው
ሆኖ፣ ባላቸው አቅምና ችሎታ ሕዝብን ለማስደሰት ከመጣጣር አላቋረጡም፡፡
የቀለም ትምህርቱንና የሙዚቃ ትምህርቱን ያጣመሩ
ባለሙያዎች ያስፈልጉናል፡፡ የኢትዮጵያን ቅኔና ዜማ ስልት ጠንቅቀው ያጠኑና የሚያውቁ የባሕላዊና ዘመናዊ መሣሪያዎችን ለመጫወት የሚችሉ፣
የሙዚቃ ሰዋሰውንና አገባብን በቅጡ የሚያውቁ፣ ድምፅንና ሙዚቃን በአንድነት የሚያቀናብሩና የሚያቀርቡ የሙዚቃ ደራሲዎች ያስፈልጉናል፡፡
ጊዜያዊው ሙዚቃም በነርሱ ምሳሌነት ይሻሻላል፡፡ የምዕራብ አፍሪካን ወይም የሱዳን፣ የደቡብ አፍሪካን ወይም የመካከለኛው አፍሪካን
ስልቶችና ዜማዎች በመኮረጅ የትም አንደርስም፡፡ የምዕራባዊያኑንም ሆነ የአረቦቹን ስልት ከኦሪጂናል ድምፃዊያኑ ልሳንና አልበሞች
ልንሰማው እንችላለን፡፡ ወደ አማርኛ ወይም ኦሮምኛ ቋንቋ የሚተረጉምልን ቱርጁማን አያስፈልገንም፡፡ ምክንያቱም ሙዚቃ ዓለም አቀፋዊ
ቋንቋ ነው፡፡ የቃላቱን ፍቺ ባናውቀው ግድ አይሰጠንም፤ ወይም ሙዚቃ ውስጥ የቃላቱ ረብ ሳየሆን የአርዕስቱ ጉልበት ነው ዕዝነ-ልቦናን
የሚገዛው፡፡
አድማጩን አያውቅም ብሎ መናቅ ወይም ለመሸወድ
መሞከር ይቅር፡፡ አድማጭ ከሌለ ማንኛውም ሙዚቃ ሊዳብርም ሆነ ሊሻሻል አይችልም፡፡ ጊዜያዊ ሙዚቃና ግጥሙ (ጥሩም ሆነ መጥፎ) አሁን
ብዙ አድማጭና ፈላጊ እንዳለው እናውቃለን፡፡ ሆኖም፣ በኢትዮጵያ ጥበባዊ ሙዚቃ ከቤተ - ክህነት ውጪ ገና አልተጀመረም ለማለት ያስደፍራል፡፡
ቢኖሩም ከሦስትና አራት የማይበልጡ የተናጠል ጥረቶች ናቸው የሚስተዋሉት፡፡ በ1960ዎቹ ከቤተ-ክህነት ውጭ ጅምሮች ነበሩ፡፡ በብሔራዊ
ቴያትር ነርሲስ ናልባንዲያን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ - የባሕል ማዕከል ውስጥ አቶ ተስፋዬ ለማ እና በተፈሪ መኮንን ት/ቤት
እንዲሁም በናዝሬት የአፄ ገላውዲዮስ ትምህርት ቤት ሕብረ-ዝማሬዎች ብቅ-ብቅ ማለት ጀምረው ነበር፡፡ ግን ወዲያው ጠፉ፡፡ በደርጉ ዘመን፣
ኪነት ለጥበባዊነቷ ሳይሆን በጊዜያዊ የፕሮፖጋንዳ ተግባር ላይ ተጠምዳ ኖረች፡፡ አሁንም ቢሆን ያው ነው፡፡ ጊዜያዊ ነው! ጊዜያዊ
ሆያ ሆዬ የተጠናወታት ነች! በአንድ ሙዚቃ ውስጥ የሰባት ስምንት ብሔረሰቦችን ችፋሮ ማየት ልማድ ሆኗል፡፡ ጥበባዊነት ቀርቶ ስልቱ
የሰመረ መሆኑ እንኳን ግር ያሰኛል፡፡ በልዩነት ውስጥ አንድነትን እናሳያለን የሚሉት ቀማሪዎች የወቅቱ ፖለቲካ ደራሽ ጎርፍ ሆኖ
እብስ አደረጋቸው፡፡ የከያኒ ነፍሳቸው በፖለቲካ አሸብሻቢነት ተዋጠች፡፡ ጥበባዊት ቆሌያቸውን የወቅቱ ሁናቴ አስደነበረባቸው፡፡ሙዚቃዊ
ምቱ፣ ስልቱም ሆነ ጭፈራው ሚስቶ ሆነ፡፡...በቃ ይሄው ነው! ይሄንን ነው በየቴሌቪዥኑ መስኮት የምናየው፡፡ “አፍሪካ! አፍሪካ! አፍሪካ! አገራችን!” የምትለውን የነርሲስ
ናልባንዲያንን ሕብረ-ዝማሬ የሚተካከል ሙዚቃ አቀናባሪ ጠፍቶ ሌት ከእንቅልፍ እንደሚቀሰቀስ አረሆ ጯሂ ተራ ስልት ያለ ድብልቅልቅ
ነው የሚሰማው፡፡.....

ሙዚቃ በቃላት (ወይም በጽሑፍ) የሚገለጥና
የሚከራከሩበት ጉዳይ አይደለም፡፡ ሙዚቃ በድምፅ የሚደረስ ወይም የሚጫወቱት፣ በሰሚውና በተጫዋቹ መካከል የሚደረግ የመንፈስ ግንኙነትና
መግባባትን የሚፈጠር አስቸጋሪ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ነው፡፡ ስለዚህም፣ ለሙዚቀኛ በቃላት ኃይል መጠቀምና መልዕክቱን ማስተላለፍ ቅር
ያሰኘዋል፡፡ ትንሽም ሆነ ትልቅ በሙዚቃ ምሳሌነት ያለው ሙዚቃዊ በረከት፣ ፍሬያማ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል፡፡ ስለሙዚቃ ሰው ማወቅ
የሚችለው በሙዚቃ ትምህርት ውስጥ ገብቶ ሲማር ነው፡፡ ያን ጊዜ፣ ብዙ ብዙ አሸናፊ ከበደዎች፣ ነርሲስ ናልባዲያኖች፣ ሙላቱ አስታጥቄዎችና
ግርማ ይፍራሸዋዎች እናገኛለን፡፡ እነርሱም፣ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ጥበባዊ ያደርጉታል፡፡ ዳግማዊ የሆኑ ያሬዶችን በጉጉት እንጠባበቃለን፡፡
የዚያ ሰው ይበለን!
*********************************************************************************
ምንጭ:--http://semnaworeq.blogspot.com
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ