ዓድዋ ሲታሰብ
. . . አሁንም አገር የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል . . . . በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ . . . ያገሬ ሰው . . . ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፡፡ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በኀዘን እርዳኝ፡፡ . . . ይህ ኃይለ ቃል ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ሕዝቡንና የየአካባቢውን መኳንንትና ገዢዎች በኢጣሊያ ላይ ያነሳሱበት የክተት አዋጅ ነበር፡፡ በዚህም አዋጅ መሠረትም የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ዓድዋ ላይ የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት ድል ተመቶበታል፡፡ ኢትዮጵያውያን አርበኞች በጠቅላይ አዝማቹ በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ አማካይነት ሕያው ታሪክ ያስመዘገቡበት ዓድዋ፡፡ የካቲት 23 ቀን በመላው ኢትዮጵያ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ይከበራል፡፡ ታሪኩ በ1888 ዓ.ም. ኢጣሊያ የቅኝ ግዛት ሕልሟን እውን ለማድረግ በተነሣች ጊዜ ሰበበ ጦርነት የሆነው የውጫሌው ውል ነበር፡፡ በአንቀጽ 17 በኢጣሊያንኛ ትርጉሙ ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ጥብቅ ግዛት ነች፤ የውጭ ግንኙነቷ በርሷ በኩል ይሆናል የሚለው የተጭበረበረ ሐረግ ነበር ፍልሚያ ውስጥ የከተታቸው፡፡ ኢትዮጵያውያንም የውስጥ ችግራቸውን ወደጎን ትተው ከየማዕዘኑ ተጠራርተው በአፄ ምኒልክ መሪነት ከፍልሚያው አውድማ ተሰለፉ፡፡ በታሪክ ጸሐፊው በአቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ አገላለጽ፣ የኢጣሊያንንም ወታደር ከበው እየተፏከሩ በጥይትና በጎራዴ ሲደበድቡት የኢጣሊያ ጦር አራት ሰዓት ከተዋጋ በኋላ ሽሽት ዠመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያውያን እየተከታተሉ ሲወጉት፣ አዝማቹ ጄኔራል አልቤርቶኒ ተቀምጦበት የነበረው በቅሎ ተመቶ ወደቀ፡፡ ወዲያው ተነሥቼ አመልጣለሁ ብሎ ለመነሣት ሲ...