ብዝኃ ጠቢቡ ነቢይ
ነቢይ ከጀርመናዊቷ ሪካ ጋር የፈጠረው ግጥማዊ ጥምረት ሔኖክ ያሬድ በዕውቀት አደባባይ ውስጥ ከዚያ ‹የግሪክ ጥበባት›› ከዚህ ‹የግእዝ ጥበባት› የሚባሉ በሰባት መደብ የተከፈሉ የትምህርትና የአዕምሮ ዕድገት መሠረት የሆኑ ትሩፋቶች አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል ለሥነ ጽሑፍ ከነጓዙ መሠረት የሆነው የቋንቋ ጥናትና አወቃቀሩ (ሰዋስው)፣ በመናገርና በመጻፍ የማሳመን ንግግራዊ ዘይቤ (ሪቶሪክ)፣ የማመዛዘንና የክርክር መርሆችን የያዘው ሎጂክ (ተጥባበ ነገር) ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ጥበባት በኢትዮጵያ የትምህርትና የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የተዋሃዱ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ትውልዶችም እያበለፀጉ ተጉዘውበታል፡፡ በየዓረፍተ ዘመኑ የሚነሱ ሥነ ጠቢባንም ታይተዋል፡፡ በብዝኃ ጥበባት ካለፉት መካከል ከሰሞኑ ዜና ዕረፍቱ የተሰማው ገጣሚ፣ ጸሐፌ ተውኔት፣ ተርጓሚ፣ ወጋዊ ንግግር አዋቂ፣ ዜናዊ ሆኖ ያለፈው ነቢይ መኰንን ይገኝበታል፡፡ የሥዕል ሥራዎችም አሉት፡፡ ነቢይ፣ ዜናዊ ሲሉት በመጽሔትም (ፈርጥ) ሆነ በጋዜጣ (አዲስ አድማስ) በዋና አዘጋጅነት መሥራቱ ነው፡፡ ‹‹ሰው በዜና ውኃ በደመና›› እንዲሉ ዜናዊ ሆኖ ከሐበሻ ሥነ ልቡና ጋር የተያያዘውን፣ ሠርክ የማይለየውን ተረትና ምሳሌ ከነ ብሂሉ እየዘገነ የርዕሰ አንቀጽ ማንደርደሪያው ማድረጉ ከአገሩ በልዩነት የሚያስቀምጠው ነው፡፡ ‹‹መጽሐፍ ከነገረው ተረት የነገረው›› የሚለውን ነባር ብሂልን ዘመኑ አሻግሮ ያመጣ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የጉዞ ማስታወሻ (ትራቭሉግ) በመጻፍና በማሳተም የሚታወቁት በጣሊያን ያደረጉት...