ማክሰኞ, ኦክቶበር 09, 2012

ሲልቪያ ፓንክረስት - የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ

በፍቅር ለይኩን

እንግሊዛዊቷ ሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስት በ1953 ዓ.ም. በወርሀ መስከረም በመስቀል በዓል ዕለት  አርፈው የቀብራቸው ሥነ ስርዓት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተፈጸመው በማግስቱ መስከረም 18 ቀን ነበር፡፡
ሲልቪያ ፓንክረስት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ፣ የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ ኢትዮጵያ በኢጣሊያን በተወረረችበት ጊዜም ወረራውን በመቃወም የፀረ ፋሽስት ዘመቻን በአውሮፓ ያስፋፉ፣ የፋሽስትን ኢሰብአዊ የሆነ ጭፍጨፋና ግፍ ያጋለጡ፣ የሰው ልጆች መብትና ነፃነት ተቆርቋሪ የሆኑ በታሪክ ትልቅ ስፍራ የተሰጣቸው ታላቅ ሴት ናቸው፡፡ ሲሊቪያ ፓንክረስት ታጋይ ብቻ ሳይሆኑ የታሪክ ተመራማሪና ጸሐፊም ናቸው፡፡ እኚህን የኢትዮጵያን የቁርጥ ቀን ወዳጅ የሞቱበትን 52ኛ ዓመት በማስመልከት ታሪካቸውን በጥቂቱ ልንዘክረው ወደድን፡፡

ሲልቪያ ፓንክረስት የተወለዱት ሚያዝያ 27 ቀን 1874 ዓ.ም. በእንግሊዝ አገር ማንችስተር በተባለው ከተማ ነው፡፡ ለሲልቪያ ፓንክረስት የወደፊት ሕይወት ላይ ደማቅ አሻራን ያኖሩት አባታቸው ዶ/ር ሪቻርድ የእንግሊዝ ሌበር ፓርቲ ንቁ ተሳታፊ፣ ለድሆች ተሟጋችና መብታቸውን ለተነፈጉ ሁሉ ድምፅ ነበሩ፡፡ እናታቸው ኤምሊ ፓንክረስትም ሴቶች  በእንግሊዝና በአውሮፓ ፖለቲካና ምርጫ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ትልቅ ሚና የተጫወቱና ብርቱ ትግል ያደረጉ ሴት ነበሩ፡፡

ሲልቪያ የአባታቸውንና እናታቸውን አርአያ በመከተል ዕድሜ ዘመናቸውን ሁሉ ለሰው ልጆች መብትና ነፃነት በመታገል አሳልፈዋል፡፡ በ1928 ዓ.ም. ወራሪው ፋሽስት ኢጣሊያ የኢትዮጵያን ሕዝብ በመርዝ ቦምብ ሲፈጅና የፍትሕ ያለህ እያለ በሚጮኽበት፣ ኢትዮጵያውን አርበኞች በዱር በገደል ለአገራቸው ነፃነት ደማቸውን በማፍሰስ ላይ በነበሩበት ጊዜ ሲልቪያ ፓንክረስት ማንንም ሳይፈሩ የፋሽስት ወራሪውን ኃይል ግፍን በድል በግልፅ በአደባባይ በመቃወም ድምፃቸውን ለዓለም ሁሉ ሕዝብ ያሰሙ የነፃነት አርበኛና የጭቁን ሕዝቦች አለኝታ ነበሩ፡፡

የኢጣሊያ ወታደሮች አዲስ አበባን ከያዙበት ከ1928 ዓ.ም. ጀምሮ በእንግሊዝ ‹‹The New Times and Ethiopian News›› የተባለውን ጋዜጣ አቋቁመው ያለ ማቋረጥ በየሳምንቱ በማሳተም ለኢትዮጵያውያን ነፃነት፣ ክብርና ልዑላዊነት ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡ በዚህ ጋዜጣም ፋሽስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እያደረስ ያለውን ግፍ በመግለፅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነትን ሊያገኙ ችለው ነበር፡፡

በዚህም እንቅስቃሴያቸው ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች ገንዘብ በመሰብሰብና በመላክ ታላቅ የሆነ ሰብአዊ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ ከኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ሥልጣኔ፣ ታሪክ፣ ባህል፣ የሕዝቦቿ የነፃነት ተጋድሎና ኩራት እጅግ የተማረኩት ሲልቪያ ፓንክረስት ከነፃነት በኋላ በቀሪው ዕድሜያቸው በሩቅ የሚያውቋትን ኢትዮጵያን በአካል በመገኘት ስለ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያውያን ለማጥናት ሲሉ በ1948 ዓ.ም. ከወንድ ልጃቸው ከሪቻርድ ፓንክረስት ጋር ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡

በኢትዮጵያም ውስጥም ‹‹Ethiopian Observer›› የተባለውን መጽሔት በማዘጋጀት በየወሩ ያሳትሙ ነበር፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ ጋር የነበራትን ግንኙነት በተመለከተ፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ በኩል ስላለው ታሪካዊ ግንኙትና ፖለቲካዊ ቀውስ ሰፊ የሆነ ጥናትና መልካም ተሳትፎ ያደርጉ እንደነበር በዘመኑ ካስነበቧቸው ጽሑፎች መረዳት ይቻላል፡፡ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ መስከረም 18 ቀን 1953 ዓ.ም. እትሙ በሲልቪያ ፓንክረስት የቀብር ሥነ ሥርዓት የአገር ግዛት ሚኒስትር የነበሩት ራስ አንዳርጋቸው መሳይ ለእኚህ የኢትዮጵያ ወዳጅ ያደረጉትን ንግግር እንዲህ ዘግቦት ነበር፡-

‹‹… ሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስት በኢትዮጵያ ገና ብዙ ለማገልገል ከፍ ያለ ምኞት ስለነበራቸው በዛሬው ቀን የቀጠሩን እዚህ ሳይሆን ሌላ ስፍራ ነበር፡፡ በእውነት እላችኋለሁ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ መከራ፣ ግፍና ስደት አልቆ ውጤቱ እስኪደርስ ድረስ ሚስ ሲልቪያ የሠሩት ሥራ በሽማግሌ ጉልበታቸውና ላባቸው ብቻ ሳይሆን ጤናቸውን እስኪያጡ፣ ርስታቸውን ሽጠው እስኪደኸዩ፣ በግል ገንዘባቸው ጭምር ለኢትዮጵያ የሠሩ ሰው ናቸው፡፡ ስለዚህ ታላቋ እንግሊዛዊት ሚስ ሲልቪያ ፓንክረስት የኢትዮጵያ ወዳጅ፣ እውነተኛዋ ኢትዮጵያዊ አርበኛ መባል የሚገባቸው ናቸው፡፡

ክቡር ራስ አንዳርጋቸው ንግግራቸውን በመቀጠልም፡-
‹‹… ወዳጃችን ሲልቪያ ፓንክረስት ሆይ 25 ዓመት ሙሉ ያለ ዕረፍት የዕድሜዎን ሸክም ሳያስቡ በእውነትና በታማኝነት የረዱዋቸው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትና ሕዝብ አሁን በዙሪያዎ ቆመው ያለቅሱልዎታል፡፡ ወዳጆችዎ አርበኞችና ስደተኞች እዚሁ ባጠገብዎ ቆመዋል፡፡ ያንንም የመከራ ዘመን ያስባሉ፡፡ ታሪክዎ ከታሪካቸው በደም ቀለም ተጽፎ ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡ እርስዎም በዚህች በኢትዮጵያ ምድር ላይ በሰላም አርፈው እንዲኖሩ የግርማዊነታቸው መልካም ፈቃድ ስለሆነ እንደ ኢትዮጵያዊት ዜጋ ቆጥረን በክብር እናሳርፍዎታለን፡፡ እግዚአብሔር በምድር ላይ ሳሉ የሠሩትን በጎ ሥራ ሁሉ ቆጥሮ በሰማይ ቤት የክብር ቦታ እንዲያድልዎ እንመኛለን፡፡›› በማለት ነበር እኚህ ታላቅ የኢትዮጵያ ባለውለታ በጥልቅ ሐዘን ስሜት ውስጥ ሆነው የተሰናበቷቸው፡፡

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም በሚስ ሲልቪያ ፓንክረስት የቀብር ዕለት ባደረጉት ንግግራቸው፡-

‹‹…ሚስስ ሲሊቪያ ፓንክረስት ኢትዮጵያን ለማገልገል ቆርጠው ከተነሱበት ጊዜ ጀምሮ የመጨረሻው ድል እስኪገኝ ድረስ ያደረጉትን የአሳብና የሥራ ተጋድሎ ሰፊ የታሪክ መስመር የያዘ ነው፡፡ ምኞታቸውና እምነታቸው የማይበገር የምሪት ምሽግ ነበር፡፡ የመንፈሳቸው ጽናት በፊታቸው የተጋረደውን እንቅፋት አስወግዶ ለማለፍ የተለየ ሥልጣን ነበረው፡፡ የኢጣሊያ ፋሽስት ጦር በዓለም መንግሥታት የተከለከለ የመርዝ ጢስ እየጣለ ሰላማውያኑን ሕዝብ ሴቱንና ሽማግሌውን ሕጻኑን ለመጨረስ ስለተነሳ ይህን ግፍ ለዓለም ሸንጎ ለማሰማት ወደ ጄኔቭ መሄዳችንን ሲከታተሉ የቆዩት ሚስስ ሲልቪያ በዓለም ላይ ከዚህ የባሰ ምን በደል ይድረስ በማለት ለእውነተኛው ፍርድ በመቆርቆር ተነሱ፡፡

‹‹ፋሽስቶች የኢትዮጵያን ሕዝብ ያለ ፍርድ ፈጁት፡፡ ሚስስ ፓንክረስትም የጽሑፍና የፎቶግራፍ ማስረጃዎች እያሰባሰቡ ዓለም ይህን ሰምቶና አይቶ ካልፈረደ ለራሱ ወዮለት እያሉ ጮኹ፡፡ የኢትዮጵያን አርበኞች ተስፋ ለማስቆረጥ ፋሽስቶች  በመርዝ ጢስና ቦምብ ያደረጉባቸውን የጭካኔ ውጊያ ሴቱንና ሕጻኑን ያለ ምክንያት እየሰበሰቡ በመትረየስ መፍጀታቸውን ማስረጃ አቀረቡ፡፡

‹‹ሚስስ ፓንክረስት በባሕርያቸው እውነተኛ ፍርድ ለማግኘት ሲታገሉ፣ የዚህችን ጥንታዊ አገር ታሪክ፣ ሥልጣኔና ቅርስ የሕዝቦቿን ጀግንነትና ፍቅር እየማረካቸው ሄደ፡፡ ከኢትዮጵያና ከሕዝቦቿ ጋር በፍቅር የወደቁት ሲልቪያ ፓንክረስት ለሀገራቸው ነፃነትና አንድነት ክቡር ሕይወታቸውን ከከፈሉት ኢትዮጵያን አርበኞች የሚደመሩ ናቸውና በዚህ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ያርፉ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ሆኗል፤›› በማለት ነበር እኚህን ታላቅ የኢትዮጵያ ወዳጅ መቼም ቢሆን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሁሌም ሥራቸው ሲታወስ እንደሚኖር በትልቅ አድናቆትና አክብሮት የተሰናበቷቸው፡፡

ሚስስ ፓንክረስት በሁለተኛ ዓለም ጦርነት ባሎቻቸውን ያጡትን ባልቴቶችና እንዲሁም ድኃ አደግ የሆኑትን ልጆች በመሰብሰብ ከፍ ያለ ዕርዳታ አድርገዋል፡፡ ትምህርት ቤትና ክሊኒኮችንም ከፍተው ገቢው ለሠራተኞች በተለይም ለመርከበኞችና ለወታደሮች ሚስቶች ጉዳይ እንዲውል በማድረግ ራሳቸው ጸሐፊ በመሆን ታላቅ ሥራ ሠርተዋል፡፡ በአምስቱ ዓመት የፋሽስት ወረራ ዘመን ማቲዎቲ የሚባለው የፋሽስት ተቃዋሚ ድርጅት መሥራችና ዋና ጸሐፊ ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሰፊ የሆነ ጥናትና ምርምር ያደረጉም ሴት ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ከጻፏቸው መጻሕፍት መካከልም፡- የኢጣሊያ ጦርነት ወንጀል በኢትዮጵያ፣ የእንግሊዝ አመራር በኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች መብታቸውና ዕርምጃቸው፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ፣ ‹‹The Cultural History of Ethiopia›› የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በቅርቡም በርካታ ኢትዮጵያንን በግፍ ለፈጀውና ላስገደለው ለፋሽስቱ የጦር ጄኔራል ለፊልድ ማርሻል ግራዚያኒ በደቡብ ኢጣሊያ አፊላ በተባለችው መንደር ለቆመው መታሰቢያ ሐውልትና ፓርክ በዓለም ዙሪያ የተቃውሞ ድምፃቸውን ካሰሙት መካከል የሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስት ልጅ የሆኑት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትና ባለቤታቸው ሪታ ፓንክረስት ይገኙበታል፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ ወዳጆች የሆኑ ምሁራን የኢትዮጵያን የቁርጥ ቀን ወዳጅ የሆኑትን የሲልቪያ ፓንክረስትን መንገድ በመከተል ከሌሎች ኢትዮጵያን ጋር በመተባበር ለጦር ወንጀለኛው ለግራዚያኒ መታሰቢያ በኢጣሊያ የተሠራውን መታሰቢያ በመቃወም በለንደን ከተማ ተቃውሞአችውን ማስማታቸው በልዩ ልዩ የመገናኛ ብዙኃን ተገልጾ ነበር፡፡

እነዚህ የኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ የረጅም ዘመንና የቁርጥ ወዳጅና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ነጻነት ቀናኢ የሆኑትን ሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስትን ምንም እንኳን በሞት ቢለዩንም ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የከፈሉት መስዋእትነት፣ ያሳዩት ፍቅርና ክብር መቼም ቢሆን በሁላችን ልብ ውስጥ ሕያው ሆኖ የሚዘልቅ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ያደረጉትን መልካም ሥራና በጎ ውለታ ዳግም እንደገና በልጃቸው በፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትና በቤተሰቦቻቸው አሁንም ድረስ ቀጥሏል፡፡

እነኚህ የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑ እንግሊዛውያን  ቤተሰቦች በየዓለም አቀፉ መድረክ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ያላቸውን ወዳጅነት በተለያየ አጋጣሚ አሳይተዋል፣ እያሳዩም ነው፡፡ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ በዓለም አቀፍ መድረክ ከማስተዋወቅ በተጨማሪ በፋሽስት ኢጣሊያ ተዘርፎ የሄደውን የአክሱም ሐውልት እንዲመለስ በዓለም አቀፍ መድረክ ከሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ታላቅ ሥራን ሠርተዋል፡፡ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመንም በእንግሊዛውያን የተዘረፉ የኢትዮጵያ ቅርሶችን በማስመለስ ረገድም ጉልህ ሚና ነበራቸው፡፡ የሚስስ ሲልቪያና የቤተሰቦቻቸው ለኢትዮጵያ ያላቸው ፍቅር፣ ክብርና ያደረጉት ውለታ ሁሌም ሕያው ሆኖ የሚዘከር ነው፡፡

የሲልቪያ ፓንክረስትን ታላቅ ታሪክና መልካም ሥራቸውን ለመዘከር ሲባል ከሁለት ዓመት በፊት በስማቸው መታሰቢያ ለማቋቋም እንቅስቃሴ ተጀምሮ እንደነበር ይታወሳል፤ ይህ እንቅስቃሴ የት እንደደረሰና ምን ያህል እንደተጓዘ ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቋም ያሉ በተለይም ደግሞ በዚህ ተቋም ውስጥ ያሉ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ወዳጆች ማኅበር የእኚህን ታላቅ የኢትዮጵያ ወዳጅ ሥራና ታሪክ የሚዘክር ዐውደ ጥናት /Public Lecture  ለማካሄድ ቢታሰብበት መልካም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

የኢትዮጵያን ጥናትና ምርምር ተቋም ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ተቋሙን በመምራትና በማደራጀት ሰፊ የሆነ ተሳትፎ የነበራቸው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትና ባለቤታቸው ሚስስ ሪታ ፓንክረስት ከተቋሙ የሥራ ባልደረቦችና ከተቋሙ ወዳጆች ጋር በመሆን በእኚህ ታላቅ ሴት ስም ለማቋቋም የታሰበው መታሰቢያ ጅምር እቅድ ወደፊት መጓዝ ይችል ዘንድ እንዲህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በኩል ቢጀመር መልካም እንደሆነ ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡ ፍቅርና ክብር ለኢትዮጵያ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝቦችና ወዳጆች ሁሉ!
ሰላም! ሻሎም!
***********
ምንጭ:---http://www.ethiopianreporter.com

 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ማሞ ካቻ (አቶ ማሞ ይንበርብሩ)

  አቶ ማሞ ይንበርብሩ (ማሞ ካቻ) እስቲ እናስታውሳቸው፣ ተቀብሮ እንዳይቀር አኩሪ ታሪካቸው  (ደረጀ መላኩ)   አቶቢሲ ማሞ ካቻ የት ትሄዳለህ? ገብረ ጉራቻ… ታዳጊው ማሞ ይንበርበሩ ገና በጨቅላ እድሜው አባቱ አቶ...