የአማርኛ ፊደል ክርክር በታይፕራይተር ዘመን
ዮናስ ብርሃኔ
በንጉሡ ዘመን ነው፡፡ ታይፕራይተር ወደ አገራችን እንደገባ ሰሞን በአጠቃቀም ዙሪያ ውዝግብ ተነስቶ
የነበረ ሲሆን እነ መንግሥቱ ለማም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አደባባይ መድረክ ብቅ ያሉበት አጋጣሚም ነበር፡፡ መንግሥቱ
ለማን ጨምሮ ሌሎች ወጣት ተማሪዎች የትምህርት እድል አግኝተው ወደ እንግሊዝ ለመሄድ እየተዘጋጁ በነበረበት ወቅት፣
በአራት ኪሎ ቅድስት ሥላሴ ግቢ ደግሞ በአማርኛ ፊደል ዙሪያ ቅልጥ ያለ ክርክር እየተካሄደ ነበርና ወጣቶቹ
ተማሪዎቹም እዚያ ላይ እንዲገኙ በትምህርት ሚኒስቴር ተጋብዘው ይሄዳሉ፡፡
ነገሩን ራሳቸው መንግሥቱ ለማ እንደገለፁት በማለት ንቡረ እጽ ኤርምያስ ከበደ ስለ ሁኔታው ሲያትቱ፤ ..መንግሥቱ
ከሌሎች ወዳጆቹ ጋር ወደ ጉባኤው ሲገቡ ሁለቱ ቀንደኛ ተከራካሪዎች የወቅቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር አቶ አበበ ረታ እና
በቤተመንግሥት የታሪክና የመጻሕፍት ሹም የነበሩት ብላታ መርሰዔ ሀዘን ወልደ ቂርቆስ የጉባኤው ሊቀመንበር እና
በጊዜው የሥራ ሚኒስትር ከነበሩት ብላታ ዘውዴ በላይነህ ግራ እና ቀኝ ተቀምጠው ነበር፡፡ እነሱ በገቡበት ሰዓት
የነበረው ድባብ ..በላቲኑ ሥርዓት፣ በላቲኑ ፊደል እንጻፍ.. የሚለው የብላታ መርስዔ ኅዘን ሃሳብ ወደመሸነፉ
አጋድሎ፣ ቅጥሉን አንድ አይነት አድርገን አሻሽለን በራሳችን ፊደል እንጠቀም የሚለው የአቶ አበበ ረታ ሃሳብ
ሳያሸንፍ፣ ታዳሚው የአቶ አበበን ሃሳብ እንቀበለው አንቀበለው እያለ በማመንታት ላይ እንደነበር የሚገልፁት መንግሥቱ
ለማ፤ እሳቸው የሚደግፏቸው የነበሩትና ቀደም ሲል በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በዚሁ ዙሪያ ሲደረግ በነበረው የጦፈ
ክርክር፤ የአገራችን ፊደል መነካት የለበትም በማለት ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ የነበሩት አቶ ብርሃኑ ድንቄም
ስብሰባው ላይ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ ..ፊደላችን ይለውጥና በፈረንጆቹ መንገድ እንሥራ.. የሚለውን የራስ እምሩን
ሃሳብ የሚያቀነቅኑት ኮሎኔል ታምራት ይገዙም እዚሁ ስብሰባ ላይ ነበሩ፡፡ የአማርኛ መጻፊያ ፊደል ይሻሻል የሚለው
ሃሳብ በወቅቱ የተነሳበት ዋነኛ ምክንያት የአማርኛው ፊደላት ለታይፕራይተር መጻፊያ አያመችም በሚል ነበር፡፡ በዚህ
ጉዳይ ላይ የተለያየ አቋም የነበራቸው ተከራካሪዎች በሃሳብ እየተፋጩ በነበረበት በዚህ ጉባዔ ላይ በርካታ የመንግስት
ባለስልጣናት እና ታላላቅ ሰዎች የነበሩ ሲሆን በወቅቱ ታዲያ ..ቱርክ ፈረንጅ ሆናለችና እኛም ፈረንጅ እንሁን..
የሚለው የመርስዔ ኅዘን ሃሳብ መረታቱ ቢሰማኝም አልሸሹም ገለል አሉ (አይነት ነገር) የሆነው የራስ እምሩ ሃሳብ
ወድቆ አይቀርም ብዬ ደስ ብሎኝ ነበር፡፡ ከሁለቱም ይብሱን አደገኛ የሆነው የአቶ አበበ ረቂቅ የማባበያ ሃሳብ
አልወድቅም ብሎ ሲንገዳገድ፣ አንዳንዴም የመርስዔ ኅዘንንም የራስ እምሩንም ማየቴ፣ የኔም የጥንታዊ ፊደል ጠበቃነት
ወኔን ነሸጥ አድርጐት ነበር፡፡ ግን ያ ሁሉ ሰው በተሰበሰበበት መሀል ተነስተው ለመናገር ድፍረቱን ስላጡ ዝም ብሎ
ተቀምጠው እንደነበር ይነግሩናል፡፡ - መንግሥቱ ለማ፡፡ይሁንና በኋላ ላይ በጓደኞቻቸው ግፊት ሳይወዱ በግድ ወደ
መድረኩ መውጣታቸው አልቀረላቸውም፡፡ በነገራችን ላይ መንግሥቱ ለማ ቀደም ሲል ፊደላችን መነካት የለበትም የሚለውን
የአቶ ብርሃኑ ድንቄን ሃሳብ በመደገፍ ሰፋ ያለ መጣጥፍ አዘጋጅተው ለአዲስ ዘመን ጦማር (ጋዜጣ) አዘጋጅ ልኮ
የነበረ ሲሆን በአንዳንድ የውስጥ ችግሮች ሳቢያ ግን ጽሑፉ አልወጣም ነበር፡፡ ይህንን ታሪክ ራሳቸው መንግሥቱ ለማ
ናቸው በኋላ ላይ የተናገሩት፡፡ በመጨረሻ ወደ መድረኩ ተገፍተው የወጡት መንግስቱ ለማ፤ ቱርክ የራሷን ፊደል ትታ
የፈረንጆቹን ስለተቀበለች በስልጣኔ ምንም ያህል እንዳልተራመደች፣ በተቃራኒው ግን ጃፓን ለመጻፍ ከእኛ በበለጠ በጣም
የሚያስቸግረውን የራሷን ፊደላት ጠብቃ እንደያዘች በስልጣኔ የትና የት መራመድ እንደቻለች በመግለጽ፣ የቱርክን
መንገድ እንከተል የሚሉትን ሃሳብ ድባቅ መተውታል፡፡ ከዚያም ቀጠል አደረጉና የፈረንጁ የፊደል ገበታ ሃያ ስድስት
ፊደላት ብቻ ነው ያሉት ቢባልም በፈረንጁ እትም መጻፊያ መኪና ላይ የሰፈረው ሁለት የተለያየ የፊደል ገበታ ትልቅና
ትንሽ Small & capital Letters መሆኑን በመጥቀስ የእንግሊዝኛው ፊደላት ቁጥር በድምሩ 26
ሳይሆን 52 እንደሆነና የእኛንም ቅጥሎቹን ከፊደላቱ ለይተን በመኪናው ላይ ብናሰፍራቸው፣ ቅጠላቸው ተለይቶ ለብቻው
ቢሠፍር፣ የማይቻሉትን ፊደላት /ደግሞ/ እንዳለ ብናስቀምጣቸው፤ እንዲሁም እነ ..ቸ..፣ ..ጀ..፣ ..ዠ..፣
..ጰ.. ፣ ..ቷ..፣ ..ጓ.....ወዘተን በዋና ፊደላቸው ብቻ ብንተካቸውና ተጨማሪውን ምልክት ለብቻው ብናሳፍረው
ለጽሕፈት መኪና የማያስቸግሩ መሆናቸውን በጥቁር ሰሌዳ ላይ እየጻፉ በማስረዳት ..ፊደላችን ለእጅ መኪና ጽሕፈት
አይመችም.. የሚለውን የእነ አቶ አበበ ረታን ሃሳብ ፉርሽ አድርገው ቁጭ አሉ፡፡ መንግሥቱ ለማ ባቀረቡት ሃሳብ
የተደመመው በጉባዔው ላይ ተገኝቶ የነበረው ህዝብም አድናቆቱን በሚገልጽ ሞቅ ያለ ጭብጨባ ተቀበለው፡፡ ነገሩም
በመንግሥቱ ለማ ድል አድራጊነት የአማርኛ ፊደል የያዘውን ቅርጽ እንደያዘ ለዘመናት በታይፕራይተር ስንገለገልበት
ቆይተን አሁን ደግሞ ኮምፒዩተር መጣ፡፡ በኮምፒዩተርም ላይ በአማርኛ መጻፍ የምንችልበት ሶፍትዌር ተሰራ፡፡ ይሁንና
ለጽሑፍ ስራው ጥራት መሻሻል ወሳኝ የሆነው የቃላት (አጻጻፍ) ማረሚያ ገና ይቀረናል፡፡ በቅርቡ ጥቅም ላይ
እንደሚውል ተስፋ እናድርግ፡፡*******
ምንጭ:---http://www.addisadmassnews.com
በኮምፒዩተርም ላይ በአማርኛ መጻፍ የምንችልበት ሶፍትዌር ተሰራ፡፡ ማን፣ እንዴት፣ መቼ? https://muse.jhu.edu/article/872061
ምላሽ ይስጡሰርዝ