«...ኢትዮጵያ ልዩና ታሪካዊ አገሬ ናት...»
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረትስ
*********************
የለንደኑ ትንታግ ወጣት ለኢትዮጵያ በመወገን እንደ አርበኛዋ እናታቸው ፀረ- ፋሽስት ጽሑፎችን በጋዜጣ በማውጣት ትግል የጀመሩት ገና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያሉ ነበር። ይህም በመሆኑ የሥነ ጽሑፍ ክህሎታቸውን በንድፈ ሐሳብ እውቀትና በምርምር አዳብረው ለህትመት ካበቋቸው ከሃያ በላይ መጻሕፍት የተወሰኑት ለአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች የመማሪያና የምርምር ሰነዶች ለመሆን በቅተዋል።
በልጅነት ዕድሜያቸው የኢትዮጵያን ጉዳይ በደማቸው ያሰረፁትና በሃያ ዘጠኝ ዓመታቸው የዶክትሬት (PHD) ዲግሪያቸውን በከፍተኛ ማዕረግ አግኝተዋል። የለንደኑ ዩኒቨርቲቲ የዕውቀት ቀንዲል ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሃምሳ ዓመት በላይ የሰጡት ምሁራዊ ተልዕኮ ተቋሙ ዛሬ ለደረሰበት የዕድገት ምዕራፍ የታሪክ ባለድርሻ አድርጓቸዋል።
በወጣትነት ዕድሜያቸው ከጀመሩት ክቡር የመምህርነት ሙያ ባለፈ በኢትዮጵያ ላይ የላቀ ምርምርና ጥናት ለማካሄድ ያስቻለ፣ ታሪካዊ ቅርሶችን አሰባስቦ ለመያዝ ያገዘ እና አገራችንን ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ያስተዋወቀ፣ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩትን በመመስረት እንደእናታቸው የዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ባለቤት ለመሆን ችለዋል።
በቅኝ ገዥዎችና በፋሽስት ኢጣሊያ የተዘረፉ ታሪካዊ ቅርሶችን ለማስመለስ ከኢትዮጵያውያን ባልንጀሮቻቸው ጋር በመሆን በአደረጉት ዓለም አቀፋዊ ትግል የአክሱም ሐውልትን፣ የአፄ ቴዎድሮስ ክታብንና ሌሎችንም ቅርሶችን በአገራቸው ከወገናቸው ጋር ደምቀው እንዲታዩ በማድረግ ሕዝባችን ለዘመናት ከነበረበት ፀፀትና ቁጭት እንዲላቀቅ አድርገዋል።
የእናታቸውን የአርበኝነት የተጋድሎ ገድል የሕይወት ዘመን ስንቅና መመሪያ አድርገው በተለይም ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ኮሌጅ ጀምረው ተቋሙ ዩኒቨርሲቲ ከሆነም በኋላ ለአበረከቱት ምሁራዊ አስተዋፅኦ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመርጌታነትና የተመራማሪነት ብቃታቸውን በማረጋገጥ የፕሮፌሰርነትና የክብር ዶክትሬት (PHD) ዲግሪ ማዕረግ አጐናፅፏቸዋል።
በብሔራዊም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱታን ያተረፉት እኒሁ ምሁር በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ባደረጉት ጥልቅ ጥናትና ምርምር ከአፄ ኃይለሥላሴ ሽልማት ድርጅትና ከእንግሊዝ መንግሥት የወርቅ ሚዳሊያና ኒሻን ለመሸለምም በቅተዋል።
የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩትን ከመመስረት ባለፈ በሰጡት ያልተቆጠበ አመራርና ድጋፍ ለእኒሁ የአገር ባለውለታ ምሁር የሃምሳ ዓመት ወርቃማ አገልግሎት ለመዘከር በተዘጋጀ ልዩ ሥነ ሥርዓት ላይ በብር የተሰራ የአክሱም ሐውልት ምስል ተሸላሚ ሆነዋል።
የእነዚህና የሌሎችም እውነታዎች ባለቤት የምጣኔ ሀብት ታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ኬር ፔቲክ ፓንክረስት ይባላሉ። እኒህ የዛሬው እውቅ ዓለም አቀፍ ምሁርና የዚያን ጊዜው እምቦቀቅላ ሕፃን የተወለዱት እ.አ.አ በወርሐ ታህሣሥ 1927 በአገረ እንግሊዝ ለንደን ከተማ በሚገኘው ሐምስቴድ ሆስፒታል ነው። የዚያን ጊዜው ብላቴና የዛሬው አዛውንት እናት የኢትዮጵያ ሕዝብ የቁርጥ ቀን የልብ ወዳጅ፣ የሴቶች መብት ተሟጋች ፣ አርቲስት፣የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኝ፣ የፀረ - ፋሽዝም ንቅናቄ ፈር ቀዳጅ፣ ጋዜጠኛና ደራሲ የሆኑት ሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስት ይባላሉ። አባታቸው ሚስተር ሲልቪዮ ኮርዮም ሰዓሊና ጋዜጠኛ፣ እንዲሁም ፀረ ፋሽስት አቋም የነበራቸው እንግሊዝ አገር የሚኖሩ ኢጣሊያዊ ስደተኛ ነበሩ።
የዚያን ጊዜው የለንደኑ ቡቃያና የዛሬው ፕሮፌሰር የተወለዱት አንደኛው እና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በተጠናቀቀበት ማግሥትና ዋዜማ በመሆኑ ጦርነቶቹ የፈጠሩአቸው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መመሰቃቀሎች በዕድገታቸው ላይ አንፃራዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ ባይቀርም ወላጆቻቸው ዕቅፍ ድግፍ አርገው በማሳደጋቸው እነሆ ከዚያ ዘመን የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ተርፈው ዛሬ የሰማንያ አምስት ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ ለመሆን በቅተዋል።
በጦርነቶች መካከል የለመለመች ሕይወት
ምንም እንኳን የያኔው ሕፃን ሪቻርድ ከልደት እስከ ልጅነት የነበራቸው የሕይወት ጉዞ ጦርነት ባስከተለውና በፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ የታጀበ ቢሆንም አንድ ለእናቱ የሆኑት የሚስስ ሲልቪያ የስስት ልጅ በሰባት ዓመታቸው ከእናታቸው ጉያ ወጥተው ችክዌል በሚባለው ትምህርት ቤት ይገባሉ። ሆኖም ግን የገቡበት ትምህርት ቤቱ የሚመላለሰው የባቡር ሀዲድ በመጐዳቱ ሕፃኑ ተማሪ በእግራቸው ተመላልሰው መማር እንደማይችሉ ታመነበት። እናም አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ መኖሪያቸው አካባቢ በነበረው ወደ ባንክራፍት ትምህርት ቤት ይዛወራሉ።
የዚያን ጊዜው ሕፃንና ተማሪ ሪቻርድ ፓንክረስት ትምህርት ቤታቸውን የዕውቀት ማዕከል በማድረግ ከክፍል ወደ ክፍል ከፍተኛ ውጤት እያገኙ መዘዋወረ ሲጀምሩ የብሩህ አዕምሮ ባለፀጋ መሆናቸውን ያመላክታሉ። ይሁን እንጂ 'በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ውሃ ይጠጣል' እንዲሉ ገና የሰባተኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ይጀመራል። ወቅቱ እንኳንስ ለመማር ቀርቶ በህልውና ለመትረፍም አስፈሪ ቢሆንም ትምህርት ቤቶች ባለመዘጋታቸው ተማሪ ሪቻርድ ፓንክረስት እንደሌሎቹ አቻዎቻቸው የመማር ማስተማሩን ሂደት በሚገባ መከታተላቸውን ይቀጥላሉ። ምንም እንኳን ጦርነቱ የፈጠረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በሁሉም እንግሊዛዊ ላይ የሚታይ ነበር። የአርበኛዋ የወይዘሮ ሲልቪያ ልጅ በትምህርት አቀባበላቸውና ዘወትር ከማይለያቸው ትጋታቸው ላይ ተፅዕኖ እንዳልፈጠረባቸው ዛሬ ላይ ሆነው ያስታውሳሉ።
ይህም በመሆኑ ወጣቱ ፓንክረስት ለመማር የነበራቸው ሩጫ ባይጠናቀቅም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመጠናቀቁ በፊት ማለትም እ.አ.አ 1944 በአስራ ስምንት ዓመታቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቅ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት መንፈሳዊ ዝግጅት ያደርጋሉ። ግን ደግሞ የእንግሊዝ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች አገራዊ ግዳጃቸውን ተወጥተው ከግንባር ለሚመለሱ ወጣቶች ቅድሚያ የትምህርት ዕድል እንዲሰጣቸው የሚል አዲስ መመሪያ በማውጣቱ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ቀን ይቆጥሩ የነበሩት ወጣቱ ሪቻርድ በሚፈልጉት ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለመግባት እንቅፋት ይገጥማቸዋል።
ይሁን እንጂ የልጃቸውን ጭንቀት በሚገባ የተረዱት እናታቸው ወይዘሮ ሲልቪያ ጓደኛቸው የሆኑትንና የፖለቲካል ሳይንቲስት የነበሩትን ፕሮፌሰር ላስኬን ያማክሯቸዋል። ምሁሩም የተለያዩ በጐ ምክንያቶችን በመደርደር ወጣቱ ሪቻርድ ለንደን ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ ይደረጋሉ። የሚስስ ሲልቪያ ብቸኛ ልጅ ሩቅ አስበው ቅርብ አዳሪ አልሆኑም። እናም ለንደን ዩንቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት በመግባት ትምህርታቸውን በትጋት መከታተሉን ይቀጥላሉ። ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ አስተውሎ መራመድንና ጊዜን በዋዛ ፈዛዛ ማሳለፍን የማይወዱት የዚያን ጊዜው የለንደን ዩኒቨርስቲ ተማሪና የዛሬው እውቅ የታሪክ ምሁር የሦስት ዓመት የዩኒቨ ርሲቲ ቆይታቸውን አጠናቀው በሃያ አንድ ዓመታቸው በምጣኔ ሀብት (Economics) የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማዕረግ ያገኛሉ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ወጣቱ ፓንክረስት በተቀዳጁት ውጤት ቢደሰቱም ወደ ሥራ ዓለም ከመግባት ይልቅ ጊዜ ሳያጠፉ ትምህርታቸውን መቀጠል እንዳለባቸው ይወስናሉ ። የትና ምን መማር እንዳለ ባቸው ማሰላሰል በያዙበት ወቅት ታላቅ የምስራች ይደርሳቸዋል። በመጀመሪያ ዲግሪያቸው ያስመዘገቡት ውጤት በቀጥታ ለዶክትሬት (PHD) ዲግሪ የሚያበቃቸውን ትምህርት እንዲማሩ ለንደን ዩኒቨርሲቲ የነፃ ትምሀርት ዕድል ይሰጣቸዋል።
አንብበው የማይሰለቹት፣ ፅፈው የማይደክሙት የዚያን ጊዜው ሪቻርድ ፓንክረስት ጀንበር ወጥታ እስከምትጠልቅ ብቻ ሳይሆን የእንቅልፍ ጊዜያቸውን ሳይቀር ለጥናታቸውና ለትምህርታቸው በመስጠታቸው በአስተማሪዎቻቸው ሳይቀር አንቱታን ያተርፋሉ። እናም በሃያ ዘጠኝ ዓመታቸው በምጣኔ ሀብት ታሪክ (Economic History) የዶክተሬት (PHD) ዲግሪያቸውን እ.አ.አ በ1954 በከፍተኛ ውጤት በመመ ረቅ እነሆ ዛሬ ድረስ ያች በሁለት ዓለም አቀፍ ጦርነቶች መካከል የተፈጠረች ነፍስ በዕውቀትና በክህሎት ገዝፋ ዓለም ዕውቅና የቸራት ለመሆን ችላለች።
በዘር የተላለፈ አርበኝነት
አርበኝነት ፈርጀ ብዙ ነው። አርበኝነት በአውደ ግንባር ይፈጠራል። አርበኝነትን ጠላትን በማንኛውም መገናኛ ብዙኃን በመፋለምም ድል ማግኘት ይቻላል። አገራችን በፋሽስት ኢጣሊያ በተወረረችበት ጊዜ ህዝባችን በዱር በገደሉ መሽጐ ጠላትን ድል እንደነሳ ሁሉ አንዳንድ ዜጐቻችንም በውጭ አገር ሆነው በዲፕሎማሲው መስክ በመሰማራት አርበኝነታቸውን አረጋግጠዋል። በሌላም በኩል አንዳንድ የውጭ አገር ዜጐች ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን በመወገን ዘመን ተሻጋሪ የአርበኝነት ታሪክ አስመዝግበዋል። ለዚህ እውነታ ሁነኛ ማሳያ የሚሆኑት ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ የቁርጥ ቀን ወዳጅና የፀረ- ፋሽዝም ንቅናቄ ፈር ቀዳጅ ሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስት ናቸው፡፡ ይህም ብቻም አይደለም « ዘር ከልጓም» ይስባል እንዲሉ ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ ያላቸውን ፍቅርና ከበሬታ በብቸኛው ልጃቸው አዕምሮ ውስጥ እንዲሰርፅ በማድረጋቸው የዛሬው ፕሮፌሰሩ ልጃቸው ከልጅነት እስከ ዕውቀት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው ያስገኙት ውጤትና የሰጡት አገልግሎት ከዘር የተላለፈ አርበኝነት ሆኖ የሚፈረጅ ነው፡፡
በዚህ ረገድ የዚያን ጊዜው ወጣትና የዛሬው አዛውንት ፕሮፌሰር ከኢትዮጵያና ከህዝቧ ጋር መቼ እና እንዴት እንደተዋወቁ ሲናገሩ « ... በእርግጥ የኢትዮጵያ ተምሳሌቴ እናቴ ናት። በተለይም በዕድሜና በትምህርት እየደረጀሁ ስመጣ እናቴ ስለኢትዮጵያ ታሪክ ትነግረኝ ነበር። ኢትዮጵያ የታሪክ ባለፀጋ መሆኗን ሁሌም ታጫውተኝ ነበር። ኢትዮጵያ በነፃነት የኖረችና ሕዝቧም ለነፃነቱ ተጋዳይ እንደሆነ ትተርክልኝ ነበር። በተለይም ፋሽስት ኢጣሊያ በነፃይቱ አገር ገብቶ እያደረሰ ያለውን ጭፍጨፋም ሀዘን በተሞላበት ሁኔታ ትገልፅልኝ ነበር። ከዚህም ሌላ እናቴ ታዘጋጀው በነበረው 'ኒው ታይም' (አዲስ ዘመን) ጋዜጣ ላይ ኢትዮጵያን የተመለከቱ ጽሑፎችን በማንበብ ኢትዮጵያን ለማወቅ አስተዋፅኦ አድርጐልኛል። ይህ ብቻም አይደለም ዩኒቨርሲቲ ስገባ ኢትዮጵያን የበለጠ የማውቅበት ተጨማሪ መድረክ አገኘሁ። ለንደን ከሚኖሩት ከሐኪም ወርቅነህ ልጆች በተጨማሪ ከነፃነት በኋላ ለንደን ከመጡት ፣ ከመንግሥቱ ለማ፣ ከአፈወርቅ ተክሌ፣ ከሐብተዓብ በአይሩ፣ ከሚካኤል እምሩ ... ወዘተ ጋር ጓደኝነት ፈጠፍኩ። እነዚህ ጓደኞቼ ስለኢትዮጵያ የሰጡኝ ዝርዝር መግለጫ ደግሞ ኢትዮጵያን አቅርበው አሳዩኝ።
« ... እናም የእናቴን ጋዜጣ ከማንበብ ባሻገር የኢጣሊያን ፋሽስታዊ ድርጊት በመቃወም ጋዜጣው ላይ መፃፍ ጀመርኩ። ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በፋሽስት ኢጣሊያን ላይ የሚያወጡትን መግለጫ፣ ስብሰባዎችንና ሰላማዊ ሰልፎችን እየተከታተልኩ ለእናቴ ጋዜጣ መዘገብ ጀመርኩ። ከሁሉም በላይ ደግሞ በአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን ጀርመናዊው የታሪክ ሊቅ ሉደልፍ ስለኢትዮጵያ የፃፈውን በማንበብና ለጋዜጣ በሚሆን መልኩ አዘጋጅ ስለነበር ስለ ኢትዮጵያ ያለኝን ዕውቀት የበለጠ አሰፋልኝ። ይህም በመሆኑ ከእናቴ ጋዜጣ በተጨማሪ በምድር ባቡር ሠራተኞች ጋዜጣ ላይም መፃፍ ጀመርኩ። እናም ገና በልጅነት ዕድሜ የቀሰምኩት እውነታ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን እንድወድ አድርጐኛል። ከሁሉም በላይ ግን እ አ አ 1951 ከእናቴ ጋር አብሬ በመምጣት ኢትዮጵያን ማየት መቻሌ በሁለንተናዊ መልኩ 'ማየት ማመን ነው' የሚለውን አባባል አረጋገጠልኝ...» በማለት የትናንቱን የሕይወት ጉዞአቸውን ያስታውሳሉ።
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ትናንት የጀመሩትን የአርበኝነት ፍልሚያ በቀጣይም የህይወታቸው አካል በማድረግ እናታቸው ሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስት ኢትዮጵያን ለመኖሪያቸውም ሆነ ለመቀበሪያቸው መርጠው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ኢትዮጵያን እንደ እናታቸው በማፍቀር ' አንለያይም' በማለት እ.አ.አ በ1956 አዲስ አበባ ይገባሉ።
ሙሽራው ምሁር
ወጣቱ ዶክተር ሪቻርድ ፓንክረስት እናታቸውን ተከትለው አዲስ አበባ ሲመጡ በቅፅበታዊ ትውውቅ ቢቢሲ ዋና መስሪያ ቤት ፊት ለፊት በሚገኝ አደባባይ ቀጥረው ያናገሯቸው እና በስፔን ሬስቶራንት ራት ጋብዘው ከማፍቀር ባለፈ ለትዳር ከጠየቋት ፍቅረኛቸው ጋር በመለያየታቸው ከአካላቸው ክፍል አንዱን ትተው የመጡ ያህል ሆኖ ይሰማቸዋል። ደግሞም ፍቅር ሩቅ ለሩቅ ሲሆን እንከን እንደማያጣው ያምናሉ። እናም ፍቅረኛቸውን አዲስ አበባ እንዲመጡ ያግባቧቸዋል።
ወጣቷም ጥሪው «ሲሻኝ ጢስ ወጋኝ» ሆነባቸውና ለንደንንተሰናብተው አዲስ አበባ ይገባሉ። ቀንም ሆነ ሌሊት ወደ ለንደን ይጓዝ የነበረው የምሁሩ ዕዝነ ልቦናም መንጐዱን አቆመ። «ሳይደግስ አይጣላም» እንዲሉ ወጣቷ ሪታ አልደን ደግሞ ውለው ሳያድሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የቤተ መጽሐፍት ኃላፊ ይሆናሉ።
ወጣቶቹ የለንደን ልጆች ' የአራዳ ልጆች' ከመሆን ባለፈ ፍቅራቸውን በትዳር ለማጥበቅ ይወሰናሉ። የሠርግ ሥነ ሥርዓታቸውን በእንግሊዝ ኦምባሲ ውስጥ ለመፈፀም ይስማማሉ። ይሁን እንጂ የዚያን ጊዜው ወጣት የምጣኔ ሀብት ታሪክ ምሁር ስለኬንያ ነፃነት፣ ጆሞ ኪንያታ ከእስር እንዲፈቱ፣ አፍሪካውያን የትግል መሳሪያ የሚሆናቸውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት እንዳለባቸው የሚያስገነዝቡ ጽሑፎችን ለንደን ይታተም በነበረው ' ዌስት አፍሪካ በሚባል መጽሔትና በአቶ አሀዱ ሳቡሬ ዋና አዘጋጅነት በሚታተመው ፈረንሳይኛና አማርኛ ጋዜጣ ላይ አውጥተው ስለነበር የጥንዶቹ የሠርግ ግብዥ በኤምባሲው ግቢ ውስጥ እንዳይካሄድ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ይከለከላሉ። እናም የሠርጋቸው ሥነ ሥርዓት በኤምባሲው ቅጥር ግቢ ከተፈፀመ በኋላ የራት ግብዣቸውን በገነት ሆቴል ለማካሄድ ይገደዳሉ።
ሙሽሮቹ ለጊዜውም ቢሆን ገነት ሆቴልን የጫጉላ ቤት ያደርጉታል። ይሁንና በዕድሜ የገፉ እናታቸውን በቅርብ ሆነው ለመደገፍ በማሰብ ኑሮአቸውን በእናታቸው መኖሪያ ቤት ያደርጋሉ። ከእናታቸው ጋር በሰላምና በፍቅር በመኖር ላይ እያሉ ሚስስ ሲልቪያ በፀና ታምመው እ.አ.አ በ1960 ከዚህ ዓለም በሞት ይለያሉ። ዶክተር ሪቻርድ በእናታቸው ሞት ምክንያት መራራ ሀዘን ውስጥ ይገባሉ። በሌላም በኩል የእናታቸው ቀብር ኢትዮጵያውያን ከልብ በመነጨ ሀዘንና በተለይም አፄ ኃይለስላሴ በተገኙበት በታላቅ ሥነ ሥርዓት መፈፀሙን ሲመለከቱ ወገን መሀል መሆናቸውን ያረጋግጣሉ። እናም በጊዜ ሂደት ለእናታቸው ተዘጋጅቶ የነበረውንና ጦር ኃይሎች አካባቢ የሚገኘውን ቤት በመግዛት ወልደው ለመሳም ይበቃሉ።
ተመራማሪው - መሪጌታ
ወጣቱ ሪቻርድ ፓንክረስት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እንዳገኙ እዚያው ለንደን ከተማ በአንድ ታዋቂ ኢንስቲትዩት እና ለንደን ዩኒቨርስቲ በተመራማሪነትና በመምህርነት አገልግለዋል። ይሁን እንጂ እ.አ.አ በ1956 ከእናታቸው ጋር ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላም ለንደን ጀምረውት ከነበረው የሥራ መስክ አልተለያዩም። እናም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ መምህር ሆነው ሥራቸውን ሲጀምሩ ጊዜ አልፈጀ ባቸውም።
በወቅቱ ስለአዲስ አበባም ሆነ ስለኮሌጁ ስለነበራቸው ስሜት ሲናገሩ « ... ለአጭር ጊዜም ቢሆን አዲስ አበባን የአየኋት በመሆኑ ብዙም ግርምት አልፈጠረችብኝም። በእርግጥ ከአውሮፓ ለመጣ ሰው እንግዳ መሆን የማይቀር ነው። ግን ደግሞ እናቴም ስላለችና ቀደም ሲልም ለንደን ያፈራኋቸው ኢትዮጵያውያን ጓደኞች ስለነበሩኝ ባይተዋርነት አስተሰማኝም። በእርግጥ ገና ባልተደራጀ ኮሌጅ ውስጥ መስራት ችግሩ ውስብስብ ነው። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲስቲ ኮሌጅ አደረጃጀቱ ያልተጠናከረ በመሆኑ ክፍተቱን ለመሙላት ተደራራቢ ሥራዎችን መሥራት ግድ ነበር። ይህም በመሆኑ የተለያዩ የትምህርት አይነቶችን ማስተማር ነበረብኝ። በዚህም መሠረት ኢኮኖሚክስ ፣ የዓለም፣ የአፍሪካና የኢትዮጵያ እንዲሁም የግብዕ ታሪክ ሳይቀር አስተምር ነበር። ይህ ሲሆን ግን ያልተማርኩትንና የማላውቀውን የትምህርት አይነት አንብቤ አስተምር ነበር። በወቅቱ የነበረው የሥራ ጫና ደግሞ በሰብዕና ላይ ተጨማሪ ዕውቀት እንዳገኝ አድርጐኛል። ከማስተማሩም ባለፈ ወደ ምርምርና ጥናት እንዳተኩርም አድርጐኛል» በማለት ሃምሳ ስድስት ዓመት ወደ ኋላ ተጐዘው ያስታውሳሉ።
ያም ሆነ ይህ በአፍላ ጉልበታቸው በመምህርነት ከሰጡት የላቀ አስተዋፅኦ ባለፈ ኮሌጁን ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለማሸጋገር በተደረገው እንቅስቃሴ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ማበርከታቸውን ይናገራሉ። በተለይም እ.አ.አ ከ1956 እሰከ 1976 የሰጡት ወሰን የለሽ ሙያ ተልዕኮ ዛሬ ላይ ሆነው የሚኮሩበት መሆኑን ይናገራሉ። ዶክተር ሪቻርድ ፓንክረስት በመምህርነት ብቃታቸው፣ በጥናትና ምርምር ውጤታቸው የረካው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ በማጐናፀፍ ማንነታቸውን አዲስ ምዕራፍ ላይ ያስቀምጠዋል።
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በአብዮቱ ማግስት እ.አ.አ በ1976 ወደ ለንደን በማምራት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጀመሩትን ጥናትና ምርምር በኦርየንታልና በአፍሪካን ጥናት ትምህርት ቤት እና በለንደን ዩንሸርስቲ ይቀጥላሉ። እንዲሁም' ሮያል ኤዥያቲክ ሶሳይቲ' ለተባለው ተቋም የቤተመጽሐፍት ኃላፊም በመሆን አገልግለዋል ። ይሁን እንጂ እ.አ.አ በ1986 አዲስ አበባ በመመለስ የመምህርነትና የተመራማሪነቱን ተግባር አጣምረው በማራመድ ለአገራችንም ሆነ ለዓለም አቀፍ ህብረተሰብ የሚጠቅም የጥናትና ምርምር ውጤቶች በመጽሐፍ እያሳተሙ ይፋ አድርገዋል።
ዘመን ተሻጋሪ ስጦታዎች
« ... ምንም እንኳን የእንግሊዝ ፓስፖርት ቢኖረኝም እኔ ግን የዓለም ልጅ ነኝ። ... እናም ዓለም ደግሞ የእኔ አገር ነች» የሚሉት አዛውንቱ ፕሮፊሰር « ...ኢትዮጵያ ደግሞ ለእኔ ልዩና ታሪካዊ አገሬ ናት...» በማለት በልበ ሙሉነት ይናገራሉ። እናም ከልጅነት እስከ ዕውቀት ባለው የሕይወት ዘመናቸው እርሳቸውና ኢትዮጵያ በአካልም በመንፈስም ባለመለያየታቸው ጥናትና ምርምራቸው ሳይቀር ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረገ መሆኑን በአፅንኦት ይናገራሉ።
ገና በወጣትነት ዕድሜያቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት በማገለገል ላይ እያሉ ኢትዮጵያ እልቆ መሳፍርት የሆነውን ታሪኳን የሚፈትሽ አትዮጵያዊ የሆነ የጥናትና ምርምር ተቋም እንደሚያስፈልግ ይወስናሉ። እናም እ.አ.አ በ1963 የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩትን በማቋቋም ለኢትዮጵያ ህዝብ ታላቅ የማንነት ማረጋገጫ ማዕከል ያበረክታሉ።
«... ኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ ያላት መሆኗን የተገነዘብኩት በ17ኛው ክፍለ ዘመን ሉዳልፍ የተባለው ጀርመናዊ የታሪክ ሊቅ ስለ ኢትዮጵያ የፃፈውን ለእናቴ ጋዜጣ በሚሆን መልኩ ሳዘጋጅ ነው። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን የታሪክ ባለፀጋነት የበለጠ ለማወቅ ደግሞ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ብቻ ያነጣጠረ የምርምር ማዕከል አስፈላጊ ነበርና ተግባራዊ አደረኩት። እነሆ ኢንስቲትዩቱም የታለመለትን ዓላማ ዕውን አድርጓል። ኢትዮጵያው ያን ብቻ ሳይሆኑ ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች ሳይቀሩ የኢንስቲትዩቱ ተጠቃሚ ሆነዋል። በሌላም መልኩ በኢንስቲትዩቱ የተቋቋመው ሙዚየም በአገር ገፅታ ግንባታ የማይናቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው። ቤተ መጽሐፍቱም ኢትዮጵያን ለማጥናትና ለመመራመር ሁነኛ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው። ያም ሆነ ይህ ኢንስቲ ትዮቱ በውስጤ የነበረውን ምኞትና ፍላጐቴን በሕይወት ዘመኔ ተግባራዊ ሲያደርግ በማየቴ ኩራት ይሰማኛል።» በማለት የኢንስቲትዩቱ መስራችና ለአስራ ሁለት ዓመት በዳይሬክተርነት ስለመሩት ዘመን ተሻጋሪ ስጦታ ይናገራሉ።
ፕሮፌሰሩ ሪቻርድ ፓንክረስት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበረከቱት ገጸ በረከት ኢንስቲትዩቱ ብቻ ሳይሆን ለአገራችን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማሪያና እና ለዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች ደግሞ ማጣቀሻ የሚሆኑ ከሃያ ሁለት በላይ መጽሐፍትን ለሕትመት አብቅተው ለትውልድ ሁሉ የሚተላለፉ ህያው ቅርስ አበርክተዋል። ይህ ብቻም አይደለም ከ400 በላይ የተለያዩ የምርምር ጽሑፎችን በመፃፍ ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ለንባብ አብቅተዋል። እ.አ.አ ከ1956 ዓ.ም ጀምረው በመምህርነት፣ በጥናት ምርምር ውጤታቸውና ክህሎታቸው በፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያበቃቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መጠነ ሰፊ ለሆነው ምሁራዊ አስተዋፅኦአቸው የክብር ዶክትሬት (PHD) ዲግሪ አበርክቶላቸዋል።
በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጥናትም ምርምር በማድረጋቸውም ከአፄ ኃይለሥላሴ የሽልማት ድርጅትና ከእንግሊዝ መንግሥት የወርቅ ሜዳሊያና ኒሻን ተሸላሚ የሆኑት እኒህ የአገር መከታ በቅኝ ገዥዎችና በፋሽስት ኢጣሊያ የተዘረፈ ታሪካዊ ቅርሶችን በማስመለሱ ረገድም በፊታውራሪነት ተሰልፈው ውጤት አስመዝግበዋል። ለዚህም የተዘረፉ ቅርሶችን ለማስመለሰ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆንና በፊታውራሪነት በመሰለፍ የአክሱም ሐውልትን ፣ የአፄ ቴዎድሮስ ክታብን ፣ ታቦትና ታሪካዊ የብራና ፅሑፎችን፣ ጋሻና ጦርን ... ወዘተ የመሳሰሉት ታሪካዊ ቅርሶች ለአገራቸው እንዲበቁ በማድረግ ሕዝባችንን ከዘመናት ፀፀትና ቁጭት እንዲላቀቅ አድርገዋል፡፡ ይህን በማድረጋቸው እንደ አርበኛዋ እናታቸው ከኢትዮጵያና ከህብረተሰቡ ከበሬታን ከመጐናፀ ፋቸው ባለፈ እርሳቸውም በልጅነት የጀመሩትን አርበኝነት ዛሬም ገናና ሆኖ እንዲታይ አድርገዋል።
አዛውንቱ ፕሮፌሰር
ፋሽስት ኢጣሊያን ገና በልጅነት ዕድሜያቸው በጽሑፋቸው የተፋለሙት ትንታጉ የለንደኑ ቡቃያ ዛሬ የሰማኒያ አምስት ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ሆነዋል። ከዚሁ የህይወት ዘመናቸው ከሃምሳ አምስት ዓመት በላይ የሆነውን የዕድሜያቸውን ክፍል ደከመኝና ሰለቸኝ ሳይሉ ዕውቀታቸውንም ሥነ ጉልበታቸውን ለኢትዮጵያ እና ለሕዝቦቿ ዕድገት አበርክተዋል።
እነሆ የተፈጥሮ ሕግ ሆነና እኒህ የአገር ባለውለታ ዛሬ እርጅና ተጫጭኖአቸዋል። ይሁን እንጂ የእርሳቸው ውጤት የሆኑት የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ እንዲሁም መማሪያና ማጣቀሻ የሆኑት መጽሐፍ ቶቻቸው የዛሬው አዛውንት ዘላለማዊ ወጣት አድርገው ያሳዩአቸዋል።
ፕሮፌሰር ፓክረስት እንደ እናታቸው ሁሉ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ቁርኝት ወሰን የለሽ ነው። ቤተሰ ቦቻቸውም እርሳቸው ከሚጓዙበት ፈር አላፈገፈጉም።
******************************
http://www.ethpress.gov.et
ሪፖርተር ዋካ ይርሳው
ቀን 2012

አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ