ተክሎ የሚጽፍ፤ ብርቱ ባለቅኔ
“የማይነጋ ህልም ሳልምየማይድን በሽታ ሳክምየማያድግ ችግኝ ሳርምየሰው ህይወት ስከረክምእኔ ለእኔ ኖሬ አላውቅም ::”
(1928-1998 ዓ.ም.)ብላቴን ጌታ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን
የዓለም ሎሪየት ታላቅ ባለቅኔ አንትሮፖሎጂስት እና ኢጂፕቶሎጂስት፣ የኮሜርስ ምሩቅ የህግ እውቀት ባለሙያ ጥዑመ ልሣን (ልዩ የትረካ ችሎታ ያለው) ተመራማሪ፣ ፀሐፌ ተውኔት ደራሲና ተርጓሚ ፀጋዬ ገብረ መድህን ቀዌሣ፤ ዛሬ በአፀደ ሥጋ ከእኛ ጋር ቢኖር ኖሮ በሥነ ጽሑፍከፍተኛውን ዓለም አቀፍ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት (Nobel Prize) ለመሸለም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ባለቅኔ፣ የቋንቋ ጠቢብና የጽሑፍ ጥበብ ሊቅ ለመሆን በቻለ፡፡ በአማርኛና በኦሮምኛ፣ በእንግሊዝኛና በግዕዝ ቋንቋዎች ቅኔን የተቀኘ ብርቱ ባለቅኔ፤ በአማርኛ በኦሮምኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ታላላቅ ሃሳቦችን የፃፈ ታላቅ ጠቢብ ነው - ፀጋዬ ገብረ መድህን፡፡ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ በዓለማችን በተለያየ ሥፍራና ዘመን ከተፈጠሩ ታላላቅ ሊቃውንት አንዱ የሆነው ጋሼ ፀጋዬ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ከአንድ በላይ በሆነ ቋንቋ ከፃፉ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ደራሲያን ጐራ ነው፡፡
ሣህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም በጉራጊኛ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ጽፈዋል፤ በሶስት ቋንቋዎች፡፡ ጋሼ ስብሃት ለአብ ገብረ እግዚአብሔር በተለይ በአማርኛና በእንግሊዝኛ፤ በተወሰነ መጠን ደግሞ በትግርኛና በፈረንሳይኛ ጽፏል፤ በአራት ቋንቋዎች፡፡ አቤ ጉበኛና ዳኛቸው ወርቁ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ጽፈዋል፤ በሁለት ቋንቋዎች፡፡ እንዲሁም ሌሎች ኢትዮጵያውያን የጽሑፍ ጥበብ ባለሙያዎች በሁለትና በሶስት ቋንቋዎች የፃፉ አሉ፡፡ ጋሼ ፀጋዬ በሶስት ቋንቋዎች የፃፈ፤ በአራት ቋንቋዎች ቅኔን የተቀኘ ብርቱ ባለቅኔና ሊቀ ጽሑፍ (የፅሁፍ ጥበብ ሊቅ) ነው፡፡ የዋርካው ሥር ንግርት”፤ ኢትዮጵያን የላይኛው እውነት ከፍተኛው እውነት፤ የላይኛው ዙፋን …ያለበት ኤዞፕ የተሰኘውና ስለመጀመሪያው ጥቁር ፈላስፋ የሚቀኘው ያማረ ቅኔው፤ ቴዎድሮስ የተሰኘውና በእንግሊዝ አገር በሚገኙ ዩኒቨርሢቲዎች ውስጥ የታየ ቲያትሩ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ከፃፋቸው ሥራዎቹ ሶስቱ ናቸው፡፡
እንዲሁም በአማርኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች የፃፋቸው በርካታ በከበረ ሃሳብ፣ በተዋበ ጥበብ የተመሉ ሥራዎች አሉት፡፡ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ የተረጐማቸውም እንደዚሁ በርካታ ናቸው፡፡
የሥመ ጥሩውን እንግሊዛዊ ባለቅኔና ፀሐፌ ተውኔት ዊሊያም ሼክስፒርን ሥራዎች ወደ ኢትዮጵያዊ ቋንቋዎች የተረጐሙ ኢትዮጵያውያን ጠበብት አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ የክብር ዶክተር ደራሲ ከበደ ሚካኤልና መሥፍን ዓለማየሁ ይወሳሉ፡፡ ይሁንና በጋሼ ፀጋዬ መጠን የዊሊያም ሼክስፒርን ሥራዎች ለኢትዮጵያውያን ታዳሚዎች ያስተዋወቀ ማንም የለም፡፡ ጋሼ ፀጋዬ በኢትዮጵያ ቲያትር መድረክ በትርጉም ሥራዎቹም ሆነ በፈጠራ ተውኔቶቹ የራሱ የሆነ አዲስ የብርሃን ፈር የቀደደ (ከዘመን ዘመን ወደፊት ቀድሞ የራሱን ተደራሲ የፈጠረ) ታላቅ የተካነ የኪነጥበብ ባለሙያ ነው፡፡ ፀጋዬ ገብረ መድህን የጽሑፍ ጥበብ ባለሟል ብቻ ሳይሆን በኅብረተሰብ የምርምር ዘርፍ ከፍተኛ እውቀት ያለው፣ ከፍ ያለ ደረጃ የሚሰጠው ተመራማሪ ነው፡፡ ሁልጊዜ ወደ እውነት፤ ሁልጊዜ ከፍ ወዳለ እውቀት፤ ሁልጊዜ ወደተሳለ ጥበብ፤ ሁልጊዜ ወደ ሠፊ ምናብና ጥልቅ እውቀት የሚያድግ፣ ትጉህና የተባ ሊቀ ጽሑፍና ተመራማሪ ነው፡፡
ፀጋዬ ገብረ መድህን ቀዌሣ ከፍ ባለ ጥበብና በተኳለ ውበት፣ በእውነትና በፍቅር የተነካ የተሟሸ አንደበት ነው፡፡ የአፍሪቃና የህዝቦቿ አንደበት፤ የኢትዮጵያና የህዝቦቿ አንደበት፤ የኦሮሞ ህዝብ አንደበት፤ የተፈጥሮና የአምላክ አንደበት፤ የጥበብና የጥልቅ ምርምር አንደበት፤ የብርሃን ቃና ህያው አንደበት ነው፡፡
ዓመተምሕረቱን በትክክል ባላስታውስም፤ ከሠባ አምስት ዓመታት በፊት ግድም በአሥራ ዘጠኝ ሃያዎቹ መጨረሻና በአሥራ ዘጠኝ ሠላሳዎቹ መካተቻ ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ አንድ መቶ ሠላሳ ስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አምቦ አካባቢ ነው ጋሼ ፀጋዬ የተወለደው፡፡ ታላላቅ ሰብዕና ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሠሎሞን ደሬሣ በወለጋ ጩታ፤ ሣህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም በጉራጌ፤ ስብሀት ለአብ ገብረእግዚብሔር በአድዋ ርባገረድ፣ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ…የተወለዱት በዚሁ ዘመን በተለያየ ሥፍራ ነው፡፡ አፈወርቅ ወልደ ነጐድጓድ ከዚህ ዘመን ጥቂት ቀደም ይላል፡፡ የክብር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ደግሞ ከሁሉም ቀደም ማለት ብቻ ሳይሆን፤ ከጐጃም ወደ አዲስ አበባ መጥተው ተፈሪ መኮንን እየተማሩ ፀረ ፋሺስት ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበረው በዚህ ዘመን ነው፡፡ ጋሼ ፀጋዬ የተወለደው ሀዲስ ዓለማየሁ በትግራይ ሠለክለካ የኢትዮጵያን አርበኞች ፀረ ፋሺስት ተጋድሎ ለመምራት እየተሰናዱ ነው፡፡
የታዋቂው አፍሪቃዊ ባለቅኔ፣ የትውልድ አገሩ የሴኔጋል ፕሬዚዳንት፣ በፈረንሣይና በፈረንሣይኛ ተናጋሪ አገሮች (Franco Phone) ተሠሚነት ያለው ትልቅ ምሁር፣ ሴዳር ሴንጐር የልብ ወዳጅ የሆነው ፀጋዬ ገብረመድህን ቀዌሣ፤ ከአምቦ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በወጣትነቱ መጀመሪያ የተማረው የንግድ ሥራ ኮሌጅ (ኮሜርስ) ገብቶ ነው፡፡ ከኮሜርስ በንግድ ሥራ ከተመረቀ በኋላ ነፃ የትምህርት ዕድል በማግኘት በአሜሪካን አገር በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት አጥንቶ ከፍ ባለ ማዕረግ ተመርቋል፡፡
በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በአገሪቱ ከፍተኛውን የሥነ ጽሑፍ ሽልማት ከግርማዊ ጃንሆይ ከተቀበሉ ኢትዮጵያውያን የኪነጥበብ ባለሙያዎችና ሊቃውንት መሀከል አንዱ ጋሼ ፀጋዬ ገብረመድህን ነው፡፡
በጥቁር ግብጽ ጥናት ኢጂፕሎጂስትና በኅብረተሰብ የምርምር ዘርፍ አንትሮፖሎጂስት በመሆን ደማቅና ክቡር እውቅና ያለው ጋሽ ፀጋዬ፤ የታሪክ ምሁርና ከፍ ያለ ተመራማሪ ጭምር ነው፡፡
አንድ ኢትዮጵያዊ ምሁር ስለ ጋሽ ፀጋዬ በፃፈው መጽሐፍ፤ ይሄንን ታላቅና ብርቱ ኢትየጵያዊ ባለቅኔ “ምሥጢረኛው ባለቅኔ” እንዳለው አስታውሳለሁ፡፡
ከሃምሣ ዓመታት በላይ በትጋትና በትባት በጽንአት የተባ ብዕሩን ተክሎ ለመፃፍ የቻለ ሊቀ ጽሑፍ ነው ጋሽ ፀጋዬ፡፡
አብዛኞቹ ሥራዎቹ ግጥምና ቅኔዎች ተውኔቶችና የምርምር ሠነዶች ናቸው፡፡ ከተውኔቶቹ ከፊሎቹ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ የተተረጐሙ ሲሆኑ፤ ከነዚህ ውስጥ አብላጮቹ ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት በአውሮጳ የኖረው ታዋቂው እንግሊዛዊ ፀሐፌ ተውኔት የዊሊያም ሼክስፒር ሥራዎች ናቸው፡፡ እርሱ በእንግሊዝኛ ከፃፋቸው ደግሞ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት መድረኮች የታዩም አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ “ቴዎድሮስ” ነው፡፡
የጋሽ ፀጋዬ ሥራዎች በአገርና በህዝብ ፍቅር፤ በጥናትና በምርምር በአገሪቱና በህዝቦቿ ክቡር ቅርሶችና ዓይነታ (typical) ማንነት ላይ ያተኮሩ ብርሃንማ ቃና ያላቸው የተፈጥሮና የእግዚሃር ምሥክርና ህያው አንደበት ናቸው፡፡
በጥቁር አፍሪቃና በአረብ አፍሪቃ ከሃምሳ ሦስት በሚበልጡ አገራት ውስጥ ከሺህ በላይ ቋንቋዎች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ እንኳን ከሰማንያ የሚበልጡ ቋንቋዎችና ከሦስት መቶ በላይ ዲያሌክት አሉ፡፡ ከነዚህ ሺህ ቋንቋዎች የራሳቸው ፊደል ያላቸው ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ አማርኛና አረብኛ፡፡ ይሁንና በሥነ ፅሁፍ የመጀመሪያውን ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ሽልማት ለማግኘት የቻሉት አፍሪቃውያን ደራሲያን:- ወሌ ሱየንካ ከናይጄሪያ፤ እና ነጂብ ማህፉዝ ከግብፅ ናቸው፡፡ እንዲሁም ከደቡብ አፍሪቃ የሰላም ሰው (A man of peace) በመሰኘት ደግሞ ዴዚሞን ቱቱ እና ኔልሰን ማንዴላ፡፡ ወሌ ሱየንካ ከአፍሪቃ ከፍተኛውን ዓለም አቀፍ የሥነ ፅሁፍ ሽልማት (Nobel prize) በማግኘት ቀደምት አፍሪቃዊ ሊቀ ፅሁፍ ሲሆን፤ ከሶስት እና ከአራት ዓመታት በፊት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክተሬት ዲግሪውን ተቀብሏል፡፡ ከነጂብ ማህፉዝ መፃህፍት ሁለቱ “ሌባውና ውሾቹ” የሚለውና “አሳረኛው” በአማርኛ ተተርጉመዋል፡፡ፊደል ያለው ብቸኛ አፍሪቃዊ ህዝብ ሆነን ለሺህ ዘመናት ፀንተን የኖርን ህዝቦች፤ ከፍተኛውን ዓለም አቀፍ የሥነ ፅሁፍ ሽልማት ለማግኘት ዘገየን፡፡ ከዚህ ሽልማት ጋር አንድ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር፤ ወይም ከአሥራ ሰባት ማሊዮን ብር በላይ አብሮት አለ፡፡
ጋሼ ፀጋዬ ገብረመድህን ቀዌሳ እስካሁን በአካለ ሥጋ ቢኖርና ብዕሩ በህያውነት ቢዘልቅ ያንን ታላቅ የሥነ ፅሁፍ ሽልማት ለማግኘት፤ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የሥነ ፅሁፍ ባለሙያ ሊሆን በቻለ ነበር፡፡ ይሄ ፅሁፍ ለብርቱው ኢትዮጵያዊ ባለቅኔ የዓለም ሎሪየት ፀጋዬ ገብረመድህን ቀዌሳ ታላቅ ነፍስ ክብር ይገባዋል፡፡
************************************************************************************
ምንጭ:--http://www.addisadmassnews.com
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ