መንትያ ጥበባት፤ ግጥምና ሙዚቃ!
መንትያ ጥበባት፤ ግጥምና ሙዚቃ! ሰሎሞን ተሠማ ጂ. ****************** “የአንድን አገር የሥልጣኔ ደረጃ ለማወቅ ብትሻ፤ ሙዚቃውን አድምጥ፣ ሥነ-ጽሑፉን አንብ!” ብሎ ነበር - ዲዜሬል፡፡ ፕ/ር አሸናፊ ከበደም፣ “ የአንዲት አገር ሥልጣኔ አቋም በሳይንስ፣ በፖለቲካ፣ በኤኮኖሚ፣ በቴክኖለጂና በሚሊታሪ ኃይሉ ብቻ ሳይሆን በ ሙዚቃ፣ ሥነ-ጽሑፍና በሌሎችም የኪነ-ጥበባት ዘርፎች የተደላደለ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ በተለይም ሙዚቃና ሥነ-ጽሑፍ ረቂቅ አስተሳሰብና ዲሲፕሊንን ስለሚፈጥሩ ሥልጣኔው ተስፋፍቶ መገኘት አለበት፡፡ የቴክኖሎጂና የኤኮኖሚ እድገት ሊኖር የሚችለው የረቂቁ አስተሳሰብ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ሲኖሩ ነው” ይሉ ነበር (መነን መጽሔት ፣ ሰኔ 1957 ዓ.ም፤ ገጽ 22)፡፡ በማስከተልም፣ “በአዕምሮና በልብ ምንነቱ ሳይታወቅ የሚታሰብ ነገር በሙዚቃ አካል ይኖረዋል በሥነ-ጽሑፍም ግዝፎ ይወጣል፡፡ ታላቅ የተባሉት ሁሉ ዘጠና-ዘጠኝ ከመቶ የሚሆኑት የጥበባዊ (ካላሲክ) ሙዚቃ ተጨዋች የሥነ-ጽሑፍም አፍቃሪዎች ነበሩ፤” ብለዋል (አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ የካቲት 8 ቀን 1960 ዓ.ም፤ ገጽ 5) ፡፡ አይንስታይንም ሆነ ዶክተር ኒኮላ ቴስላ በጥበባዊ ሙዚቃና ሥነ-ጽሑፍ አፍቃሪነታቸው የታወቁ ነበሩ፡፡ በሃገራችንም ቢሆን ጥልቁና ረቂቁ ፍልስፍና የገባውና የኖረው በዜማና በቅኔ አማካኝነት ነው፡፡ በሙዚቃ የተራቀቁት ሊቃውንት - በዜማ ቤት፣ በቅኔ ቤትና መጽሐፍት ቤት ውስጥ ሚስጢራትን አቀላጥፈው የሚያውቁ ምሁራን ስለነበሩ ምናባቸው ሰፊ፣ ሥነ-ሥርዓታቸውም ሥልጡንና የተገራ ነበር (ኃይለ ገብርኤል ዳኜ፤ 1970፣ ገጽ 89-90)፡፡ የዜማ ቤት በአራት ይከፈላል፡፡ የመጀመሪያው ድጓ ቤት ነው፡፡ ዓመቱን ሙሉ በቅዳሴና በሰዐታት ጊዜ የሚዘመ...