ተክሎ የሚጽፍ፤ ብርቱ ባለቅኔ
“የማይነጋ ህልም ሳልም የማይድን በሽታ ሳክም የማያድግ ችግኝ ሳርም የሰው ህይወት ስከረክም እኔ ለእኔ ኖሬ አላውቅም ::” ብላቴን ጌታ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን ( 1928- 1998 ዓ.ም. ) የዓለም ሎሪየት ታላቅ ባለቅኔ አንትሮፖሎጂስት እና ኢጂፕቶሎጂስት፣ የኮሜርስ ምሩቅ የህግ እውቀት ባለሙያ ጥዑመ ልሣን (ልዩ የትረካ ችሎታ ያለው) ተመራማሪ፣ ፀሐፌ ተውኔት ደራሲና ተርጓሚ ፀጋዬ ገብረ መድህን ቀዌሣ፤ ዛሬ በአፀደ ሥጋ ከእኛ ጋር ቢኖር ኖሮ በሥነ ጽሑፍከፍተኛውን ዓለም አቀፍ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት (Nobel Prize) ለመሸለም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ባለቅኔ፣ የቋንቋ ጠቢብና የጽሑፍ ጥበብ ሊቅ ለመሆን በቻለ፡፡ በአማርኛና በኦሮምኛ፣ በእንግሊዝኛና በግዕዝ ቋንቋዎች ቅኔን የተቀኘ ብርቱ ባለቅኔ፤ በአማርኛ በኦሮምኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ታላላቅ ሃሳቦችን የፃፈ ታላቅ ጠቢብ ነው - ፀጋዬ ገብረ መድህን፡፡ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ በዓለማችን በተለያየ ሥፍራና ዘመን ከተፈጠሩ ታላላቅ ሊቃውንት አንዱ የሆነው ጋሼ ፀጋዬ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ከአንድ በላይ በሆነ ቋንቋ ከፃፉ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ደራሲያን ጐራ ነው፡፡ ሣህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም በጉራጊኛ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ጽፈዋል፤ በሶስት ቋንቋዎች፡፡ ጋሼ ስብሃት ለአብ ገብረ እግዚአብሔር በተለይ በአማርኛና በእንግሊዝኛ፤ በተወሰነ መጠን ደግሞ በትግርኛና በፈረንሳይኛ ጽፏል፤ በአራት ቋንቋዎች፡፡ አቤ ጉበኛና ዳኛቸው ወርቁ...