ሲልቪያ ፓንክረስት - የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ
በፍቅር ለይኩን እንግሊዛዊቷ ሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስት በ1953 ዓ.ም. በወርሀ መስከረም በመስቀል በዓል ዕለት አርፈው የቀብራቸው ሥነ ስርዓት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተፈጸመው በማግስቱ መስከረም 18 ቀን ነበር፡፡ ሲልቪያ ፓንክረስት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ፣ የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ ኢትዮጵያ በኢጣሊያን በተወረረችበት ጊዜም ወረራውን በመቃወም የፀረ ፋሽስት ዘመቻን በአውሮፓ ያስፋፉ፣ የፋሽስትን ኢሰብአዊ የሆነ ጭፍጨፋና ግፍ ያጋለጡ፣ የሰው ልጆች መብትና ነፃነት ተቆርቋሪ የሆኑ በታሪክ ትልቅ ስፍራ የተሰጣቸው ታላቅ ሴት ናቸው፡፡ ሲሊቪያ ፓንክረስት ታጋይ ብቻ ሳይሆኑ የታሪክ ተመራማሪና ጸሐፊም ናቸው፡፡ እኚህን የኢትዮጵያን የቁርጥ ቀን ወዳጅ የሞቱበትን 52ኛ ዓመት በማስመልከት ታሪካቸውን በጥቂቱ ልንዘክረው ወደድን፡፡ ሲልቪያ ፓንክረስት የተወለዱት ሚያዝያ 27 ቀን 1874 ዓ.ም. በእንግሊዝ አገር ማንችስተር በተባለው ከተማ ነው፡፡ ለሲልቪያ ፓንክረስት የወደፊት ሕይወት ላይ ደማቅ አሻራን ያኖሩት አባታቸው ዶ/ር ሪቻርድ የእንግሊዝ ሌበር ፓርቲ ንቁ ተሳታፊ፣ ለድሆች ተሟጋችና መብታቸውን ለተነፈጉ ሁሉ ድምፅ ነበሩ፡፡ እናታቸው ኤምሊ ፓንክረስትም ሴቶች በእንግሊዝና በአውሮፓ ፖለቲካና ምርጫ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ትልቅ ሚና የተጫወቱና ብርቱ ትግል ያደረጉ ሴት ነበሩ፡፡ ሲልቪያ የአባታቸውንና እናታቸውን አርአያ በመከተል ዕድሜ ዘመናቸውን ሁሉ ለሰው ልጆች መብትና ነፃነት በመታገል አሳልፈዋል፡፡ በ1928 ዓ.ም. ወራሪው ፋሽስት ኢጣሊያ የኢትዮጵያን ሕዝብ በመርዝ ቦምብ ሲፈጅና የፍትሕ ያለህ እያለ በሚጮኽበት፣ ኢትዮጵያውን አርበኞች በዱር በገደል ለአገራቸው ነፃነት ደማቸውን በማፍሰስ ላይ በነበሩበት ጊዜ ...