አማተር ክበባትና ማህበራት የት ደረሱ?
ዳዊት ንጉሡ ረታ መነሻዬ ሰሞኑን የጥበብ ባለሙያው አብርሃም ወልዴ የአይዶል ሾው የልዑካን ቡድን በደሴና በባህር ዳር ውድድር ሲያካሂድ በቴሌቪዥን መስኮት ተከታትያለሁ። መቼም ወሎና ጎጃም ሲነሱ የቀድሞዎቹን የወሎ ኪነትና የጎጃሙን ጊሽ ዓባይ የሙዚቃ ቡድኖች በማስታወስ “በዚህ የአይዶል ውድድር ምን ዓይነት ጥበብ እናያለን?” የሚል ጉጉት መፈጠሩ አይቀርም፡፡ እነማን ናቸው እነ ይሁኔ በላይንና ሰማኸኝ በለውን የሚተኩት?... እነማንስ ናቸው እነ ዜኒት ሙሃባንና ማሪቱ ለገሰን የሚያስታውሱን? እነኚህ የጥበብ መፍለቂያ ቦታዎች ዛሬም የጥበብ ልጆችን ማፍለቃቸው እንዳልቀረባቸው የሚያረጋግጡልንስ እነማን ይሆኑ?....በሚል ውድድሩን ለመከታተል ትዕግስት አጥቶ እንደኔው የሚቁነጠነጥም አይጠፋም፡፡ ሆኖም ግን ውድድሩ ሲቀርብ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ ተገኝቶአል፡፡ ራሳቸው የአይዶል ዳኞቹን ጨምሮ እኔንና መሰል ተመልካቾችን ባስገረመን መልኩ ይሄ ነው የሚባል/የምትባል ድምፃዊም ሆነ የውዝዋዜ ተሰጥዖ ያለው ተወዳዳሪ ባለመመልከታችን “ምነዋ ወሎ? ምነዋ ጎጃም?” ማለታችን አልቀረም፡፡….ይሄን ጊዜ ጥያቄ ይነሳል፡፡………ባንድ ወቅት በአገሪቱ እንደ አሸን ፈልተው በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች ልዩ-ልዩ የጥበብ በረከቶችን ለጥበብ አፍቃሪው ህብረተሰብ ሲያቀርቡ የነበሩት እነዚያ የአማተር ወጣቶች ክበባትና ማህበራት የት ደረሱብን?...የሚል፡፡ 1980ዎቹ እነዚህ ጊዜያት ዛሬ ዛሬ በኪነ-ጥበቡ ዓለም ጎልተው የወጡና አይናችን በስስት የሚመለከታቸው፤ ጆሮአችን በጉጉት የሚያደምጣቸው ከያኒያን የተፈጠሩበት ጊዜ ነው፡፡ በወቅቱ በአማተር የቴአትር፣ የሙዚቃ፣ የጋዜጠኝነትና የስነፅሁፍ ክበባት ሁሉም እንደየ-ችሎታው ተደራጅቶ፣ ከባህልና ማስታወቂያ ቢሮ ህጋዊ ፈቃድ በማግኘት የሚንቀሳቀስ...