የትምህርት ነገር

በምእራባዊ፡ ትምህርት፡ የኢትዮጵያ፡ አወዳደቅና፤ በጠቃሚ ትምህርት የወደፊት አነሳሷ።
************************************************************************


ጣሊያን፡ የኢትዮጵያን፡ የባህር፡ ጠረፍ፡ ከወረረ፡ በኋላ፡ ወደ፡ መሃል፡ አገር፡ ገሠገሠ፤ በየካቲት፡ ወር፡ ፲፰፻፹፰ ዓ.ም. አድዋ፡ ላይ፡ በተደረገው፡ ጦርነት፡ ቢሸነፍም፡ ሙሉ፡ ለሙሉ፡ ከኢትዮጵያ፡ ሳይወጣ፡ በመረብ፡ መላሺ፡ አካባቢ፡ ቆየ። በዚህ፡ ጊዜም፡ ከኢትዮጵያ፡ ጋር፡ የንግድ፡ ግንኙነት፡ ለማድረግ፡ ይሞክር፡ ነበር። ይህን የጣሊያን፡ እንቅስቃሴ፡ አስመልክቶ፡ በጊዜው፡ ምእራባውያን፡ በየአገሮቻቸው፡ በጋዜጣ፡ ያቀርቡ፡ ነበር። የሚጽፉትም፡ ዘገባ፡ ተመሳሳይነት፡ ነበረው። ከነዚህ፡ ዘገባዎች፡ ውስጥ፡ አንዱን፡ ለምሳሌ፡ ያህል፡ እንመልከት።

ጣሊያኖች፡ የሚሠሩት፡ ሥራ፡ በጣም፡ የሚያስደንቅ፡ ጥበብ፡ ያለበት፡ ነገር፡ ነው። የአቢሲኒያን፡ የባህር፡ በር፡ ተቆጣጠሩ፣ ከዛም፡ የመሃሉን፡ አገር፡ ለመያዝ፡ ሞክረው፡ ከከሸፈባቸው፡ በኋላ፡ አሁን፡ በሚያስገርም፡ ጥበብ፡ አቢሲኒያኖችን፡ አግባብተው፡ ከነሱ፡ ጋር፡ የንግድ፡ ልውውጥ፡ ጀምረዋል። [፩]

ይህን፡ ከዚህ፡ በላይ፡ የሰፈረውን፡ ጥቅስ፡ አዙረው፡ ሲያዩት፡ የምእራባውያንን፡ ባህል፡ ይመለከታሉ። ምእራባውያን፡ የሚያስደንቅ፡ ጥበብ፡ የሚሉት፡ ንጥቂያንንና፡ ማምታታትን፡ እንደሆነ፡ ያያሉ። አንድ፡ ኪስ፡ አውላቂ፡ የአንድን፡ ሰው፡ ቦርሳ፡ ከሰረቀ፡ በኋላ፡ ቦርሳውን፡ መልሶ፡ ለባለቤቱ፡ መሸጡን፡ ነው፡ መልካም፡ ጥበብ፡ ብለው፡ ምእራባውያን፡ የሚያደንቁት። ይህ፡ ጥቅስ፡ ያስፈለገው፡ የዚህ፡ ጽሁፍ፡ መልእክት፡ መሠረታዊ፡ ሃሳብ፡ ለሚያነቡት፡ በቀላሉ፡ እንዲገባቸው፡ ለማድረግ፡ ነው።   

በዚህ፡ ውይይት፡ መልስ፡ የሚያገኘው፡ ጥያቄ፡ ኢትዮጵያ፡ በአሁኑ፡ ዘመን፡ በማንኛውም፡ መስክ፡ ከአገሮች፡ ሁሉ፡ በታች፣ ሰዎቿም፡ ከሰው፡ ዘር፡ ሁሉ፡ በታች፡ የመዋላቸው፡ ጉዳይ፡ ነው።  ከምእራባውያን (ቱርክንም፡ ጨምሮ)፡  ጉብኝት፡ በፊት ኢትዮጵያ፡ ምን፡ አይነት፡ አገር፡ ነበረች? በዛ፡ ዘመን፡ ኢትዮጵያ፡ ምን፡ ትመስል፡ እንደነበር፡ ማወቅ፡ በኋላ፡ ከደረሰችበት፡ ሁኔታዋ፡ ጋር፡ ለማነጻጸር፡ ይጠቅማል። ስለራሳችን፡ ጉዳይ፡ ገድሎችንና፡ ጸሓፊ፡ ትእዛዛት፡ በመዝገብ፡ ያሰፈሩትን፡ ሳንጠቅስ፡ የሌሎችን፣ ያውም፡ የምእራባውያንን፡ የራሳቸውን፡ ምስክርነት፡ ለማግኜት፡ ማርኮ፡ ፖሎ፡ የተባለው፡ ምእራባዊ፡ አሳሽ፡ በአንድ፡ ሺህ፡ ሁለት፡ መቶ፡ ሰማንያ፡ ዓመተ፡ ምህረት፡ (ከሰባት፡ መቶ፡ ሀያ፡ አመታት፡ በፊት) ከቬኑስ፡ ተነስቶ፡ በዓለም፡ ተዘዋውሮ፡ ባገኜው፡ መረጃ፡ ስለ፡ ኢትዮጵያ፡ ያሰፈረውን፡ ምስክርነት፡ እንመልከት።

ስለ፡ አበሻ፡ ሰዎች፡ ይህን፡ ልንገራችሁ። (አበሻ፡ ብሎ፡ የጠራቸው፡ ቃሉን፡ ከአረቦች፡ ሰምቶ፡ ነው፡፡) የአበሻ፡ ሰዎች፡ ዋናው፡ ንጉሣቸው፡ ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ ነው። የንጉሦች፡ ንጉሥ፡ በማሃል፡ አገር፤ ይኖራል። ከዚህ፡ ከአቢዩ፡ ንጉሥ፡ ሌላ፡ በአገሪቷ፡ ስድስት፡ ሌሎች፡ ንጉሦች፡ አሉ፡ ከነዚህ፡ ውስጥ፡ ሶስቱ፡ ክርስቲያኖች፡ ሲሆኑ፡ ሶስቱ፡ ደግሞ፡ በኤደን፡ አቅራቢያ፡ ያሉ፡ እስላሞች፡ ናቸው። ሁሉም፡ ንጉሦች፡ በማሃል፡ አገር፡ ላለው፡ አቢይ፡ ንጉሥ፡ ይገብራሉ። አበሾች፡ የተትረፈረፈ፡ ሰብል፡ ያመርታሉ። ሩዝ፣ ሥጋ፣ ወተት፡ ይመገባሉ። የምግብ፡ ዘይት፡ ከሰሊጥ፡ ይሠራሉ። ዝሆኖችን፡ ከህንድ፡ አስመጥተው፡ ይገለገሉባቸዋል። የበረከቱ፡ ቀጭኔዎች፡ አሏቸው። አንበሶች፣ ግሥላዎች፣ አእዋፍና፡ እንስሳት፡  ሞልተዋል። ብዙ፡ ፍየሎችም፡ አሏቸው። ወፎቻቸው፡ ከኛ፡ ወፎች፡ ይለያሉ። ዶሮዎቻቸው፡ በዓለም፡ ላይ፡ ካሉ፡ ዶሮዎች፡ ሁሉ፡ ያማሩ፡ ናቸው። ግዝፈታቸው፡ አህያ፡ የሚያህል፡ ሰጎኖችም፡ አሏቸው። የሰው፡ መልክ፡ ያላቸው፡ ዝንጆሮዎችና፡ ጦጣወችም፡ ይገኛሉ። በመካከለኛው፡ አገራቸው፡ ብዙ፡ ወርቅ፡ ይገኛል። ከጥጥ፡ የሚያምሩ፡ ልብሶችንና፡ የመጽሐፍ፡ መለበጃወችን፡ ይሠራሉ። ነጋዴዎች፡ በነጻ፡ ይንቀሳቀሳሉ፣ ብዙም፡ ትርፍ፡ ያገኛሉ። ስለ፡ አበሾች፡ ብዙ፡ ልነግራችሁ፡ የምሻው፡ ነበረኝ፡ ነገር፡ ግን፡ አሁን፡ ወደ፡ ኤደን፡ ጠቅላይ፡ ግዛት፡ መሄድ፡ አለብኝ። [፪] 

አባቶቻችን፡ ሲወርድ፡ ሲዋረድ፡ ባቆዩልን፡ ታሪክ፡ እንደምናውቀው፡ እነሆ፡ በባእድ፡ አገር፡ ሰው፡ በማርኮ፡ ፖሎ፡ ምስክርነትም፡ እንደምናየው፡ ኢትዮጵያ፡ በረከቷ፡ የበዛ፣ ሰብሏ፡ የተትረፈረፈ፡ ንጉሧም፡ ክርስቶስ፡ የሆነ፡ ማራኪ፡ አገር፡ ነበረች።

ከምግብ፡ መትረፍረፍ፡ ሌላ፡ በማንኛውም፡ በሌሎች፡ ጉዳዮችም፡ በሰው፡ ፊት፡ የሚያምር፡ ሙያ፡ ያላት፡ አገር፡ ነበረች፤  የሚያሳፍር፡ አንድም፡ ጉድፍ፡ አልነበረባትም። እራሱ፡ ማርኮ፡ ፖሎ፡ እንደመሰከረው፡ ኢትዮጵያውያን፡ ብዙ፡ ሙያዎች፡ ነበሯቸው። የሚያምሩ፡ ሰፈሮችና፡  ሐውልቶችን፡ የሚሰሩ፣  ማህበራዊ፡ አኗኗራቸው፡ የሚማርክ፡ የፈረስ፡ አሰላለፋቸውም፡ ውብ፣ በእግዚአብሔር፡ የሚመካው፡ ጀግንነታቸውም፡ ወደር፡ የሌለው፡ ነበረ።

በህክምናም፡ ቢሆን፡ በመጀመሪያ፡ በሺታን፡ የሚያስከትሉ፡ ምርቶችን፡ አያመርቱም። በሺታም፡ ከመጣ፡ የነቀርሳ፡ በሺታን፡ እንኳን፡ ሳይቀር፡ የሚፈውስ፡ ብልሃት፡ ነበራቸው። የሚበልጠው፡ ቁምነገር፡ የበሺታ፡  መዘዝን፡ የሚያስከትሉ፡ ምግባሮች፡  አልነበሩባቸውም። አሁን፡ የምናያቸው፡ ብዙ፡ ደዌዎች፡ ከምእራባውያን፡ እና፡ ከሸቀጦቻቸው፡ ጋር፡ የገቡ፡ ናቸው። ብዙ፡ አጉል፡ አምልኮዎች፡ ደግሞ፡ ከአረቦች፡ የተገኙ፡ መጤ፡ በሺታወች፡ ናቸው። ለማስታወስ፡ ያህል፡ የሬንደር፡ ፔስት፡ የከብት፡ በሺታ፡ በጣሊያን፡ ወረራ፡ ኢትዮጵያውያንን፡ በምግብ፡ እጦት፡ ለቅኝ፡ ግዛትነት፡ ለማንበርከክ፡ ታቅዶ፡ የተዘራ፣  የአባለዘር፡ በሺታዎች፡ በአጼ፡ ምንሊክ፡ ዘመን፡ ምእራባውያን፣ በኢትዮጵያ፡ መሳፍንቶች፡ መካከል፡ የዘሯቸው፣ የቃልቻ፣ የጥንቆላ፣ የጨሌና፡ የቆሌ፡ አምልኮዎች፡ ደግሞ፡ ከአረቦችና፣ አምልኳቸው፡ ጋር፡ የገቡ፡ እንደሆኑና፡ እነዚህ፡ ደዌዎች፡ በኢትዮጵያ፡ እንዳልነበሩ፡
  ብዙ፡ ኢትዮጵያውያን፡ ያስታውሳሉ።

በእርሻ፡ ሥራም፡ መሬትን፡ የሚመርዝ፡ የኬሚካል፡ ማዳበሪያ፡ ሳያሻቸው፡ ዓለም፡ ገና፡ ብልሃቱ፡ ሳይገባው፡ የሚዘራውን፡ ዘር፡ በመቀያየር፡ አፈሩን፡ ያዳብሩ፡ ነበር። ውኃን፡ የሚያቀዘቅዝ፣ እሳትን፡ ከነሙቀቱ፡ የሚያቆይ፣ ልብስን፡ የሚያጸዳ፣ ምግብን፡ የሚያጣፍጥ፣ በጨለማ፡ አካባቢያቸውን፡ የሚያበራ፣ ሥራቸውንም፡ መዝግበው፡ ለመጭው፡ ትውልድ፡ የሚያስተላልፉበት፣ ሌሎችም፡ አሁን፡ የሌሉ፡ ብዙ፡ ብልሃቶች፡ ነበሯቸው።
 
ይህን፡ ሁሉ፡ ማን፡ ወሰደው? ኢትዮጵያ፡ ሙያዋ፡ እንዴት፡ ነጠፈ፣ ውበቷስ፡ እንዴት፡ ረገፈ? ኢትዮጵያውያን፡ እንኳን፡ የተትረፈረፈ፡ ማምረት፡ እራሳቸውን፡ መመገብ፡ እንኳን፡ የማይችሉ፣ እነሱን፡ ከሚጠሉ፡ የውጭ፡ ሰዎች፡ የእለት፡ ምጽዋት፡ ለመመጽወት፡ እጅ፡ እጅ፡ እያዩ፡ የሚኖሩ፡ ለምን፡ ሆኑ? ልመና፡ የሚያሳፍር፡ መሆኑን፡ እስካለማወቅ፡ ድረስስ፡ ኢትዮጵያውያን፡ ምነው፡ ወደቁ?  ፈረንጅ፡ መጥቶ፡ መብራት፡ ካልሰራ፡ የሚጨልምባቸው፣ የጉድጓድ፡ ውኃ፡ ካልቆፈረ፡ የሚጠሙ፣ ስንዴ፡ ካልመጸወተ፡ የሚራቡ፣ ካላከመ፡ በበሺታ፡ የሚጠቁ፣ ሳይንስ፤ ካላስተማረ፡ የሚደነቁሩ፡ ምነው፡ ሆኑ? አዋቂዎቹ፡ አያቶቻችን፡ ነገር፡ በምሳሌ፡ ብለው፡ እንዳስተማሩን፡ የነሱን፡ ፈለግ፡ በመከተል፡ ጉዟችን፡ እስኪ፡ በምሳሌ፡ እንቃኘው።  



በምጽዋት፡ ግድያ።

በአንድ፡ ቤት፡ ውስጥ፡ ያለች፡ እመቤት፡ ለባልዋና፡ ለልጆችዋ፡ የሚሆነውን፡ ምግብ፡ በማለዳ፡ ተነስታ፡ ታዘጋጃለች፣ ቤቷን፡ ታጸዳለች፣ ባልዋ፡ በንቃት፡ ሰርቶ፡ እንዲመለስ፡ ልቡን፡ በደስታ፡ ትሞላለች። እንዲህ፡ የምታደርግ፡ ብልህ፡ ሴት፡ ቤቷን፡ በደስታ፡ የተሞላ፡ አድርጋ፡ ትይዛለች፣ ልጆቿም፡ መልካም፡ ሥነ፡ ምግባር፡ ይዘው፡ ያድጋሉ፣ ለባልዋም፡ ዘውድ፡ ትሆናለች። ይች፡ ሴት፡ እንዲህ፡ አይነት፡ ብልህ፡ ሴት፡ ባትሆን፡ ኖሮ፡ ቤቱ፡ ምን፡ ይመስል፡ ነበር? ለምሳሌ፡ ይች፡ ሴት፡ ሰነፍ፡ ሴት፡ ናት፡ እንበል። ቤቷ፡ ከሚያፈራው፡ ይልቅ፡ የሩቁ፡ ወይም፡ የጎረቤቷ፡ ያስቀናታል፡ እንበል። ከሩቅ፡ ያለች፡ በብልጭልጭ፡ ያጌጠች፡ ሴት፡ ታይና፡ ብልጭልጯ፡ እንዴት፡ ያምራል፡ ብላ፡ ትጎዳኛታለች። እንግዳዋ፡ ሴትም፡ ወደዚች፡ ሰነፍ፡ ሴት፡ ቤት፡ ትመጣና፡ ቤቷን፡ ታያለች። እንግዳዋም፡ ለሴትዮዋ፡ እንዲህ፡ ትላታለች፥ ለባልሽ፡ እና፡ ለልጆችሽ፡ እኮ፡ ምግብ፡ መሥራት፡ የለብሽም፣ እኔ ምግብ፡ እያዘጋጀሁ፡ በየቀኑ፡ አመጣለሁ፣ አንች፡ ትንሽ፡ ገንዘብ፡ ትሰጭኛለሽ። የምትሰጭኝ፡ ገንዘብ፡ እህል፡ ከምትገዥበት፡ እና፡ ጉልበትሽን፡ ከምታፈሽበት፡ ያነሰ፡ ነው። እኔ፡ እየሠራሁ፡ አመጣለሁ፡ አንቺ፡ ምን፡ አደከመሽ፣ ዝም፡ ብለሽ፡ መተኛትና፡ ቡናሽን፡ መጠጣት፡ ብቻ፡ ነው፡ ትላታለች። ይህችም፡ ሴት፡ በእንግዳዋ፡ ሴት፡ ንግግር፡ ትማረካለች፣ ትስማማለች። እንግዳዋ፡ ምግብ፡ እያዘጋጀች፡ ታመጣለች፣ ባል፣ ሚስት፡ እና፡ ልጆች፡ እንግዳዋ፡ አዘጋጅታ፡ ያመጣችውን፡ እየበሉ፡ መኖር፡ ይጀምራሉ። ምግቡ፡ ይጣፍጣል። ልጆችም፡ ሆኑ፡ ባል፡ የተዘጋጀ፡ መጥቶ፡ ሲመገቡ፡ እንጂ፡ ማንም፡ ሲሠራው፡ አያዩም። የምትሰራው፡ ነገር፡ የላትምና፡ እናት፡ ለልጆቿ፡ ሥራ፡ አላስተማረቻቸውም። ሚስት፡ ሥራዋ፡ አሉባልታ፣ ሐሜትና፡ ወሬ፡ ብቻ፡ ሆነ። ልጆችም፡ ያለ፡ ሙያ፡ አደጉ። እንግዳዋ፡ ባልን፡ ቀርባ፡ ሚስትህ፡ አትሰራ፣ ስለማትሰራም፡ አታምርም፣ ስለምታወራም አታፍርም፣ ለመሆኑ፡ የሷ፡ ሚስትነት፡ ላንተ፡ የሚሰጠው፡ ምን፡ ጥቅም፡ አለ? ምንስ፡ ታደርግልሃለች? አለችው። ባልም፡ ልብ፡ አለ።  የእንግዳዋን፡ ሴት፡ ሙያ፡ እያደነቀ፡ ሚስቱ በስንፍናዋ፡ እያስጠላችው፡ መጣች። የውጭ፡ ሴት፡ አድንቋልና፡ ልቡ፡ ያለ፡ ከውጭ፡ ነው። ትዳሩንም፡ ፈታ። ሴቶች፡ ልጆችም፡ ለአቅመ፡ አዳም፡ ሲደርሱ፡ ሙያና፡ ሥርአት፡  ተምረው፡ አላደጉምና፡ የሚያገባቸው፡ ይጠፋል። ወንዶችም፡ ሥራና፡ ሥነ፡ ምግባርን፡ አላወቁምና፡ ሥራን፡ እራሳቸው፡ አዘጋጅተውም፡ ይሁን፡ ተቀጥረው፡ መስራት፡ አልቻሉም። ሴቶችም፡ ወንዶችም፡ ከጓደኞቻቸው፡ በታች፡ ዋሉ። እራሳቸውን፡ አሳዳጊያቸውንም፡ ጠሉ። ሞትንም፡ ሻቱ። ቤት፡ በብልህ፡ ይገነባል፡ በሰነፍም፡ ይፈርሳል። በኢትዮጵያ፡ የተፈጸመው፡ ታሪክ፡ የዚህን፡ ቤት፡ ታሪክ፡ ይመስላል።

በጥንት፡ ዘመን፡ የጥበብ፡ መፍለቅለቂያ፡ የሆነችውን፡ ኢትዮጵያ፡ በቅርቡ፡ ዘመን፡ የመጡ፣ የሚማርኩና፡ የተብለጨለጩ፡ የውጭ፡ ነገሮች፡ ገብተው፡ ሙያዋን፡ አስጥለዋታል። የውጭ፡ አገር፡ ሰዎች፡ ኢትዮጵያውያንን፡ እንዲህ፡ አሏቸው፥ እኛ፡ ብረት፡ ድስት፡ አዘጋጅተን፡ እናቀርብላችኋለን፣ የገል፡ ድስት፡ በመስራት፡ ለምን፡ ትደክማላችሁ?  እኛ፡ ገበርዲን፡ እና፡ ጀርሲ፡ አዘጋጅተን፡ እናቀርብላችኋለን፣ ጥጥ፡ በመፍተል፡ እና፡ ሸማ፡ በመስራት፡ ለምን፡ ትደክማላችሁ? እኛ፡ መኪና፡ አዘጋጅተን፡ እናቀርብላችኋለን፣ ሠረገላ በመስራት፡ ለምን፡ ትደክማላችሁ? እኛ፡ የብረት፡ ምሰሶ፡ አዘጋጅተን፡ እናቀርብላችኋለን፣ የዝግባ፡ ምሰሶ፡ በመስራት፡ ለምን፡ ትደክማላችሁ? እኛ፡ የምትተዳደሩበትን፡ ህግ፡ አዘጋጅተን፡ እናቀርብላችኋለን፣ ክብረ፡ ነገሥት፣ ፍትሃ፡ ነገሥት፡ እያላችሁ፡ ለምን፡ ትደክማላችሁ? እኛ፡ ለልጆቻችሁ፡ የምታስተምሩትን፡ ሳይንስ፡ አዘጋጅተን፡ እናቀርብላችኋለን፣ ግብረ፡ ገብነት፣ ወንጌል፣ ዳዊት፡ እያላችሁ፡ ለምን፡ ትደክማላችሁ? እንዲህ፡ እያሉ፡ ኢትዮጵያውያንን፡ የሚጣፍጥ፡ ነገር፡ አስቀመሷቸው። ኢትዮጵያውያንም፡ አዳመጡ፣ ቀመሱ፣ ተቀበሉም። የራሳቸውን፡ ናቁ፣ የሰውን፡ አደነቁ። ቤታቸውም፡ ራስን፡ በመጣል፣ በእርስ፡ በርስ፡ መናናቅና፣ በተውሶ፡ ነገር፡ ፉክክርና፡ መናቆር፡ ታመሰ። ኢትዮጵያዊነትም፡ ዋጋው፡ ረከሰ፣ ሰዎቿም፡ ሙያ፡ አጥተው፡ ወደቁ። እነሆ፡ ኢትዮጵያ፡ በዚህ፡ የትውሰት፡ ጎዳና፡ ስትጓዝ፡ በአዋሷትም፡ ተንቃ፣ በልጆቿም፡ ተንቃ፡ አውራ፡ መንገድ፡ ላይ፡ ወድቃለች። ጉልበት፡ ያላቸው፡ መንግሥታት፡ የዳር፡ ድንበር፡ ልብሶቿን፡ እጣ፡ ተጣጥለው፡ ከተቀራመቱ፡ ሰነበቱ። የምትሰራውን፡ ስለነገሯት፡ የናቋት፡ ብዙ፡ መንግሥታትም፡ የስውር፡ ወጥመድን፡ አጠመዱባት። ሰነፍ፡ ናት፡ ብለው፡ አሟት። ተሰብስበውም፡ ትከፋፈል፡ ዘንድ፡ ፈረዱባት። ኢትዮጵያ፡ ተራበች፣ ተጠማች፣ ታረዘች፣ ታሠረችም። የምንመጸውታት፡ እኛ፡ ነን፡ ብለው፡ መንግሥታትና፡ አህዛብ፡ ተሳለቁባት። ዓለም፡ በሙሉ፡ ጽዮን፡ ተራበች፡ ብሎ፡ ተረተባት። የዓለም፡ ጠቢባን፡ ስለረሃብተኝነቷ፡ ጻፉ። ጥንት፡ በንቁ፡ እምነቷና፣ በሙያዋ፡  የተከበረችው፡ ምድር፡ አሁን፡ የሰውን፡ ተውሳ፡ ተዋረደች።


የሃሳብ፡ ድርቀት።

አብዛኞቹ፡ ኢትዮጵያውያን፡ የሚሰሩትን፡ የእለት፡ ከእለት፡ ሥራ፡ በማየት፡ በአሁኑ፡ ዘመን፡ በኢትዮጵያ፡ ታስቦ፡ የሚሰራ፡ ብዙ፡ ነገር፡ እንደሌለ፡ ማወቅ፡ ቀላል፡ ነው።  ጫት፡ የሚሸጥበት፡ ሱቅ፡ መስኮት፡ ላይ፡ ብዙ፡ ጎረምሶችና፡ አዋቂዎች፡ ተሰባስበው፡ ቀኑን፡ በሙሉ፡ ወግ፡ ያወጋሉ። ከመኪና፡ መንገዱ፡ ዳር፡ እስከሱቁ፡ መስኮት፡ ድረስ፡ ያለውን፡ ቦታ፡ አረንቋ፡ የወረሰው፡ ውሃ፡ ከብዙ፡ የሰፈር፡ ቆሻሻና፡ ሽንት፡ ጋር፡ አጥለቅልቆታል። ሸቀጥ፡ ለመገብየት፡ ወደ፡ ሱቁ፡ የሚሄዱ፡ ሰዎች፡ ከአርንቋው፡ ውስጥ፡ ብቅ፡ ብቅ፡ ያሉ፡ ድንጋዮች፡ እየፈለጉ፡ በነሱ፡ ላይ፡ እየተረማመዱ፡ ወደሱቁ፡ ይጠጋሉ። የሚፈልጉትን፡ ነገር፡ ይገዙና፡ ተመልሰው፡ ድንጋይ፡ እየመረጡ፡ በመረገጥ፣ አንዳንድ፡ ጊዜም፡ አንድ፡ እግራቸው፡ አረንቋው፡ ውስጥ፡ እየተዘፈቀ፡ ወደቤታቸው፡ ይመለሳሉ። ከመኪና፡ መንገድ፡ ዳር፡ ሆኖ፡ ለሚያይ፡ ሰው፡ አረንቋው፡ አሰቃቂ፡ ነው። በሽታንም፡ ያመጣል። ባለሱቁ፡ እንኳን፡ ስለ፡ አረንቋው፡ የሚያስብ፡ አይቶት፡ የሚያውቅም፡ አይመስልም። አንድ፡ ወንዝ፡ በአንድ፡ ቀን፡ መገደብ፡ የሚችሉ፡ ጎረምሶች፡ እና፡ አዋቂዎች፡ ተሰብስበው፡ ጫት፡ እየቃሙ፡ አይናቸው፡ የሚያየው፣ ጆሯቸውም፡ የሚሰማው፡ ስለአሜሪካ፡ ብልጽግና፡ እና፡ ስለ፡ እንግሊዝ፡ የኳስ፡ ቡድኖች፡ ጨዋታ፡ ብቻ፡ እንጂ፡ በነሱ፡ ቤት፡ አረንቋው፡ የነሱ፡ ችግር፡ አይደለም። ኢትዮጵያ፡ ውስጥ፡ ማሰብ፡ የመኖሪያ፡ ቦታ፡ የለውም። ከደሃው፡ ሠራተኛ፡ እስከ፡ ከበረው፡ ሃብታም፡ ድረስ፡ የሚያስብ፡ ያለ፡ አይመስልም። የከበሩ፡ ሰዎች፡ ቢኖሩ፡ የከበሩት፡ በማሰብና፡ በማስተዋል፡ ሳይሆን፡ ኢትዮጵያ፡ ውስጥ፡ አሁን፡ ባህል፡ በሆነው፡ በንጥቂያና፡ በብልጠት፡ መንገድ፡ ነው። ማሰብ፡ በኢትዮጵያ፡ ሽታውም፣ ደብዛውም፡ የለም። ለማሰብ፡ አለመኖር፡ አንዱ፡ ምክንያት፡ ማስተዋልን፡ በሚነጥቁ፡ የኢንዱስትሪ፡ ውጤት፡ በሆኑ፡ መርዞች፡ ብዙ፡ ሰዎች፡ መበከላቸው፡ ሲሆን፡ ሌላውና፡ ዋነኛው፡ ግን፡ መሠርቷ፡ እምነት፡ የነበረው፡ ኢትዮጵያ፡ የራሷ፡ የሆነውን፡ መሠረታዊ፡ ባህልና፡ ሙያ፡ ትታ፡ እራስን፡ የሚያስንቁና፡ ጥገኝነትን፡ በሚያበረታቱ፡ የባእዳን፡ ትምህርቶች፡ መወሰዷ፡ ነው። ማስተዋል፡ የሚያስፈልገው፡ ኢትዮጵያ፡ የሌሎችን፡ ትምህርቶች፡ አልወሰደችም፤ በትምህርቶቹ፡ ተወሰደች፡ እንጂ። የውጩ፡ ትምህርት፡ የራሷን፡ ሙያ፡ አስጣላት፡ እራሱ፡ ትምህርቱ፡ ግን፡ ሙያ፡ አልሆናትም። መልካሟ፡ ኢትዮጵያ፡ እንዲህ፡ በባእዳን፡ ትምህርቶች፡ ጠፋች። የውጭ፡ አገር፡ ትምህርቶች፡ ኢትዮጵያዊውን፡ የሚያሰለጥኑት፡ ለውጭ፡ የሚስማማውን፡ ያህል፡ እስኪገራ፡ ድረስ፡ ነው።  የውጭ፡ አገር፡ ትምህርቶች፡ ኢትዮጵያዊው፡ ከነሱ፡ መንገድ፡ ውጭ፡ ወይም፡ በተለየ፡ የትምህርት፡ ጎዳና፡ እንዳይሄድ፡ ዙሪያውን፡ አጨልመውበታል። የውጭ፡ አገር፡ ሰዎች፡ አስበው፡ የአመለካከት፡ መንገድ፡ ይቀይሳሉ። ኢትዮጵያውያን፡ በዚህ፡ በሌሎች፡ በተተለመ፡ መንገድ፡ ይነጉዳሉ። በኢትዮጵያ፡ ውስጥ፡ ከውጭ፡ ተቀምረው፡ የመጡ፡ ትምህርቶች፡ በሙሉ፡ ኢትዮጵያውያንን፡ ከውጭ፡ በተተለመ፡ መንገድ፡ ብቻ፡ እንዲያስቡ፡ ያስገድዷቸዋል። ማንኛውንም፡ የውጭ፡ አገር፡ ትምህርት፡ የተማረ፡ ኢትዮጵያዊ፡ የሚያውቀው፡ ነገር፡ ቢኖር፡ በሌሎች፡ የታሰበውንና፡ የተሠራውን፡ ነገር፡ ሳያስብ፡ መቀበልን፡ ብቻ፡ ነው። የትምህርት፡ ፈተናዎቹም፡ የውጭ፡ ሰዎች፡ አስበው፡ ያመጡትን፡ ጉዳይ፡ አንድ፡ ኢትዮጵያዊ፡ ምን፡ ያህል፡ እንደለመደው፡ ማመሳከሪያዎች፡ እንጂ፡ ኢትዮጵያዊውን፡ የሚያሻሽሉ፡ ወይም፡ እውነተኛ፡ ችሎታውን፡ የሚለኩ፡ አይደሉም። ውሻ፡ ሰው፡ ለሚያደርገው፡ አደን፡ አሰልጣኙን፡ እንዲያገለግል፡ እንደሚሰለጥን፡ በሌሎች፡ ተዘጋጅቶ፡ የመጣን፡ ሃሳብ፡ ለማነብነብ፡ የሚደረግ፡ ሥልጠናም፡ እንዲሁ፡ ውጤቱ፡ የማታ፡ የማታ፡ አሰልጣኙን፡ ማገልገል፡ ብቻ፡ ነው።

የሳይንስና፡ የህብረተሰብ፡ ትምህርት፡ እየተባሉ፡ በትምህርት፡ ቤቶች፡ የሚሰጡ፡ ትምህርቶች፡ ቋንቋን፡ በውጭ፡ አገር፡ ስሞችና፡ አጠራሮች፡ ከማጨቅ፡ ያለፈ፡ ጥቅም፡ ለኢትዮጵያ፡ አልሰጡም። ፒሬዲክ፡ ቴብል፡ ተዘጋጅቶ፡ ኢንዲየም፣ ፌርሚየም፣ ካሊፎርኒየም፣ ኤንስታይኒየም፣ ጋልየም፣ ሞሊብዲነም፣ ይትሪየም፣ ሎውረንሲየም፣ ዳርምስታድትየም፡ እየተባለ፡ ኢትዮጵያዊው፡ ሊጠበብባቸውም፡ ሆነ፡ አስተካክሎ፡ ስማቸውን፡ ሊጠራቸው፡ የማይችል፡ የኤለመንቶች፡ ዝርዝር፡ ከሚታቀፍ፡ በሰፈሩ፡ ያሉትን፡ ነገሮች፡ በራሱ፡ ጥረት፡ ፈልጎ፡ አግኝቶ፣ ኢትዮጵያዊ፡ ስም፡ ሰጥቶ፡ ቢያውቃቸው፡ ለኢትዮጵያዊው፡ ይበጀው፡ ነበር። በእንግሊዝኛ፡ ኤለመንቶች፡ የሚባሉት፡ የራሳቸው፡ አካል፡ የሆኑ፡ የተፈጥሮ፡ ነገሮች፡ መኖራቸውን፡ እንኳን፡ የኢትዮጵያ፡ ቋንቋዎች፡ አያውቁትም፤ ምክንያቱም፡ ነገሮቹ፡ ከውጭ፡ ተዘጋጅተው፡ የውጭ፡ ስም፡ ተሰጥቷቸው፡ ስለሚመጡና፡ ኢትዮጵያዊው፡ ድረሻው፡ የተዘጋጀለትን፡ መቀበል፡ ስለሆነ፡ ስለ፡ ጉዳዩ፡ የጠለቀ፡ እውቀት፡ አይኖረውም። እውቀት፡ ማለት፡ ስለ፡ እቃው፡ የውጭ፡ ሰዎች፡ ያገኙትን፡ ነጠላ፡ ክብደት፣ የሚቀልጥበት፡ ሙቀት፣ ከሌሎች፡ እቃዎች፡ ጋር፡ ቢገናኝ፡ ምን፡ እንደሚሆን፡ እና፡ የመሳሰሉትን፡ መልሶ፡ ማወቅ፡ ሳይሆን፡ ጉዳዩ፡ ኢትዮጵያን፡ ወደሚጠቅም፡ ነገር፡ መቀየር፡ ማለት፡ ነው። ሌሎችም፡ የትምህርት፡ አይነቶች፡ እና፡ ከውጭ፡ የሚመጡ፡ ውጤቶች፡ የሚያስከትሉት፡ ይህንኑ፡ በገደል፡ ማሚቶነት፡ የተሸፈነ፡ ድንቁርና፡ እና፡ የኢትዮጵያዊ፡ የጥበብ፡ ቅርስ፡ መጥፋትን፡ ነው። በተለይ፡ የህብረተሰብ፡ ሳይንስ፡ የሚባሉ፡ ትምህርቶች፡ ደግሞ፡ በቀጥታ፡ ኢትዮጵያዊው፡ ኢትዮጵያን፡ እንዳይጠቅም፡ የሚያደርጉ፣ የሚጨበጥ፡ ፍሬ፡ ሳይኖራቸው፡ የሚጨበጠውን፡ የኢትዮጵያ፡ ፍሬ፡ በትረካ፡ ብዛት፡ ደብዛውን፡ የሚያጠፉ፡ ማደናቆሪያዎች፡ ናቸው። ሳይኮሎጅ፣ ሶሲዮሎጅ፣ ፍልስፍና፣ ህግ፣ የፖለቲካ፡ ሳይንስና፡ የመሳሰሉት፡ በትምህርት፡ ተቋማት፡ የሚሰጡ፡ ትምህርቶች፡ ኢትዮጵያዊ፡ ስም፡ ካላመኖራቸው፡ ጀምሮ፡ ኢትዮጵያዊ፡ ጥበብን፡ እስከማስጣላቸው፡ ድረስ፡ ከጉዳት፡ በቀር፡ ለኢትዮጵያ፡ ያስገኙት፡ ትርፍ፡ አለ፡ ብሎ፡ መናገር፡ ያስቸግራል።

ኢትዮጵያዊው፡ የሚማረክባቸው፡ የውጭ፡ ምርቶችም፡ የሚያደርሱት፡ ጉዳት፡ ቀላል፡ አይደለም። ለምሳሌ፡ አንድ፡ የኦፔል፡ መኪና፡ ወደ፡ ኢትዮጵያ፡ ሲገባ፡ የገባው፡ የውጭ፡ ሥራ፡ ውጤት፡ የሆነ፡ ምርት፡ ነው። ኢትዮጵያዊው፡ ይህን፡ የኦፔል፡ መኪና፡ ሲነዳ፡ ደስ፡ ይለዋል። መኪናውን፡ ሲነዳ፡ ዘመዶቹ፡ እና፡ የሚያውቁት፡ ሰዎች፡ እያዩ፡ ከፍ፡ ያለ፡ ክብር፡ ይሰጡታል። ከርቀት፡ የሚያዩ፡ ሰዎችም፡ ቀረብ፡ ብለው፡ ጓደኛና፡ ወዳጅ፡ ለመሆን፡ በአካባቢው፡ ያንዣብባሉ። መኪናው፡ እንዲሽከረከር፡ ነዳጅና፡ ዘይት፡ እንዲሁም፡ የመለዋወጫ፡ እቃዎች፡ ያስፈልጉታል። እነዚህ፡ እቃዎች፡ የሚገዙት፡ ደግሞ፡ የኢትዮጵያ፡ መንግሥት፡ የኢትዮጵያ፡ ገበሬዎች፡ የሚያመርቱትን፡ የእርሻ፡ ውጤት፡ ሰብስቦ፣ እንዲሁም፡ በኢትዮጵያ፡ የሚገኙ፡ ከብቶችን፡ ሰብስቦ፣ ወርቅና፡ ንጥረ፡ ነገሮችም፡ ቢኖሯት፡ ሰብስቦ፣ እነዚህን፡ ሁሉ፡ ለውጭ፡ ሰዎች፡ በጥቂት፡ ዋጋ፡ ሸጦ፡ በውድ፡ ዋጋ፡ ነዳጅ፣ የሞተር፡ ዘይትና፡ የመኪና፡ መለዋወጫ፡ ይገዛል። ባለ፡ ኦፔሉ፡ ኢትዮጵያዊ፡ ገበሬዎቹ፡ ዘመዶቹ፡ ያፈሩትን፡ ምርት፡ እሱ፡ ነዳጅና፡ ዘይት፡ አድርጎ፡ መኪናዋን፡ ይመግባል። በሌላ፡ አገላለጽ፡ የኢትዮጵያ፡ ገበሬዎች፡ በእርሻ፡ የሚያመርቱት፡ አዲስ፡ አበባ፡ ያለው፡ ጮሌው፡ ወንድማቸው፡ ምርታቸውን፡ በነዳጅ፡ ቀይሮ፡ መጠጥ፡ ቤት፡ ለመጠጥ፡ ቤት፡ እንዲንሸራሸርበት፡ ነው፡ እንደማለት፡ ነው። ጮሌውን፡ የሚያዩ፡ ሁሉ፡ እንደጮሌው፡ ለመሆን፡ ስርቆትና፡ ማምታታት፡ ይጀምራሉ። ይህም፡ ከወረርሺኝ፡ በሺታ፡ በበለጠ፡ ክፋት፡ ኢትዮጵያን፡ አዝቅጧት፡ እናያለን። በእርግጥ፡ የጭነት፡ መኪናዎችም፡ ከከፍለሃገር፡ ክፍለሃገር፡ እቃዎችን፡ ለማመላለስም፡ ነዳጁን፡ ይጠቀማሉ፤ ዋናው፡ ነጥብ፡ ነዳጁን፡ መልካም፡ ነገር፡ ለመሥራትም፡ የሚጠቀሙበት፡ መኖራቸው፡ አይደለም። ቁምነገሩ፡ እያንዳንዱ፡ ሊትር፡ ነዳጅ፡ ቢያንስ፡ የአንድ፡ ገበሬ፡ የወራት፡ ምርት፡ የፈሰሰበት፡ መሆኑና፡ ኢትዮጵያዊው፡ የሚበላው፡ የሌለው፡ እስኪሆን፡ ድረስ፡ የቅንጦት፡ ሱስ፡ አስተናጋጅ፡ መሆኑ፡ ነው።

ትንሽ፡ ቀለል፡ ባለ፡ መንገድ፡ ጉዳዩን፡ እንየው። የውጭ፡ አገር፡ ሰዎች፡ የኢትዮጵያን፡ ፍሬዎች፡ ፈለጉ፤ ነገር፡ ግን፡ ፍሬዎችን፡ ለማግኜት፡ ፍሬ፡ ያለውን፡ ንብረታቸውን፡ እንደመገበያያ፡ አድርገው፡ ለማቅረብ፡ አልፈለጉም። ይልቁንስ፡ ኢትዮጵያዊውን፡ ለሱሰኝነት፡ አሰለጠኑትና፡ ሱሰኛ፡ ሆነ። እነሆ፡ ኢትዮጵያ፡ ውስጥ፡ የሚፈልጉትን፡ ነገር፡ ለመውሰድ፡ በኢትዮጵያ፡ ፍላጎት፡ ፈጥረዋል፣ እሱም፡ የማይጠቅም፡ ነገር፡ ሱሰኝነት፡ ነው። ኢትዮጵያዊው፡ የሰባውን፡ በሬውን፡ ይሰጥና፡ የሱስ፡ እጽ፡ ይመጣለታል። ከመቶ፡ ዓመት፡ ወዲህ፡ የምናየው፡ የኢትዮጵያ፡ ኤኮኖሚ፡ የሚባለው፡ ይሄው፡ ነው። በሙያ፡ ማነስ፡ ምክንያት፡ የመሠረታዊ፡ ምርቶች፡ አቅርቦት፡ ባነሰበት፡ ቦታ፡ እሱኑ፡ በብዙ፡ ቀንሶ፡ በሱስ፡ ፍጆታ፡ ከመቀየር፡ የበለጠ፡ ድንቁርና፡ ምን፡ አለ?

የኦፔል፡ ጉዳቱ፡ የአገርን፡ ምርቶች፡ ከማራቆት፡ ላይ፡ አያቆምም። የውጭ፡ አገር፡ ሰዎች፡ ኦፔሉን፡ ሲሰሩ፡ ሰዎቻቸው፡ ተሰባስበው፡ መኪናው፡ እንዴት፡ እንደሚሽከረከር፡ ይመክራሉ፣ ሃሳብ፡ ይለዋወጣሉ፣ በፍጥነት፡ ሲሽከረከር፡ እንዳይገለበጥ፡ ለማድረግ፡ ብልሃቱን፡ ለመግኜት፡ ሰዎቻቸው፡ ያስባሉ። ሙከራዎችን፡ ያደርጋሉ። መኪናው፡ ምቾት፡ እንዲኖረው፡ ለማድረግ፡ ብልሃት፡ እንዲሰሩ፡ የሚመደቡ፡ አሉ። መኪናው፡ እየበረረ፡ ሲሄድ፡ ከፊት፡ ለፊቱ፡ የሚጋረጥ፡ ነገር፡ ቢመጣ፡ ፍጥነቱን፡ የመቀነሻና፡ የማቆሚያ፡ ብልሃትን፡ የሚያፈልቁ፡ ለዚህ፡ የሚመደቡ፡ አሉ። መኪናው፡ ሲያዩት፡ እንዲያምር፡ የሚያደርገውን፡ ብልሃት፡ የሚፈልጉ፡ አሉ። ሁሉም፡ በሚሠሩት፡ ሥራ፡ አዳዲስ፡ ነገሮች፡ ስለሚያጋጥሟቸው፡ እነዚህን፡ አዳዲስ፡ ነገሮች፡ ለሠሪዎቹ፡ የሚስማማ፡ ስም፡ ይሰጧቸዋል። ለመኪናዎቹ፡ የሚሆን፡ ቀለም፡ የሚያቀርቡ፡ ሰዎች፡ ደግሞ፡ በዚሁ፡ በውጭ፡ አገር፡ ይፈጠራሉ። መስታዎቶችንም፡ ሠርተን፡ እናቀርባለን፡ የሚሉ፡ ይቀርባሉ። ጎማዎቹንም፡ ሠርተን፡ እናቀርባለን፡ የሚሉ፡ ይቀርባሉ። የሚሠራው፡ ሥራ፡ ብዙ፡ መተባበርን፡ የሚጠይቅ፡ በመሆኑ፡ የትብብር፡ ስምምነት፡ ያደርጋሉ። በትብብር፡ ስምምነቱ፡ አንዳንዶቹ፡ በቃላቸው፡ ሳይገኙ፡ ከቀሩ፡ እንዲህ፡ የሚያደርጉ፡ ሰዎችን፡ በህግ፡ የሚጠይቁበት፡ ደንብ፡ ይሰራሉ። መኪናዎቹንም፡ ለገበያ፡ ለማቅረብ፡ እኛ፡ እናስተዋውቃለን፡ የሚሉ፡ ነጋዴዎችም፡ ይመጣሉ። እንደምናየው፡ አንድ፡ መኪና፡ ለመሥራት፡ እጅግ፡ ብዙ፡ የሆኑ፡ የውጭ፡ ህብረተሰብ፡ የሰዎች፡ የሰንሰለት፡ ግንኙነት፡ ተፈጥሮ፡ በብዙ፡ መንገድ፡ ብዙ፡ አዳዲስና፡ በየጊዜው፡ የሚሻሻልን፡ ነገር፡ ይዘው፡ ይቀርባሉ። የኦፔሉ፡ አገር፡ ቋንቋም፡ እነዚህን፡ አዳዲስ፡ የሚፈጠሩ፡ የሥራ፡ አይነቶች፡ እና፡ በሥራ፡ ላይ፡ ያሉ፡ ችግሮችን፡ የሚገልጹ፡ አዳዲስ፡ ቃላቶች፡ እና፡ ምሳሌዎችን፡ ያፈራል። እውቀትም፡ ይዳብራል። መኪናው፡ መኪና፡ ሆኖ፡ ከመውጣቱ፡ ይልቅ፡ መኪናውን፡ ለመሥራት፡ የተደረገው፡ ርብርብ፡ እና፡ ጉዞ፡ የውጭ፡ አገር፡ ሰዎችን፡ ገንብቷል።

ኦፔሉ፡ መኪና፡ ኢትዮጵያ፡ ውስጥ፡ ሲገባ፡ መኪናውን፡ ለመሥራት፡ የፈሰሰው፡ የብልሃት፡ መንገድ፣ ችግሮቹ፣ የችግሮቹ፡ መፍትሄዎች፣ ግንኙነቶቹ፣ ቃላቶቹ፣ ምሳሌዎቹ፣ እውቀቶቹ፡ ሁሉ፡ የሉም። ኢትዮጵያዊው፡ ተመሳሳይ፡ ነገር፡ ሰርቶ፡ ሞቅ፡ ያለ፡ የሥራ፡ ሰንሰለት፡ ግንኙነት፡ እንዳይኖር፣ ህብረተሰቡን፡ እንዳያዳብር፣ በሥራ፡ ላይ፡ የሚያጋጥማቸውን፡ ችግሮችን፡ አውቀው፡ መፍትሄያቸውን፡ እንዳያዘጋጁ፣ ቋንቋውና፡ ባህሉ፡ በሥራ፡ እንዳይዳብር፣ ለትውልድ፡ የሚሆኑ፡ ከሥራ፡ ልምድ፡ የተገኙ፡ ምሳሌዎችን፡ እንዳያፈሩ፡ ተዘጋጅቶ፡ የመጣው፡ ኦፔል፡ ያግዳቸዋል። አሁን፡ ሁሉም፡ እንደሚያየው፡ የኢትዮጵያ፡ ድርሻ፡ ብልጽግናን፡ በማሰብና፡ በሥራ፡ ከማምጣት፡ ይልቅ፡ የውጭ፡ አገር፡ ሰዎች፡ የተጠበቡበትን፡ መግዛት፡ ብቻ፡ ነው። በዚህ፡ የተዘጋጀ፡ በመቃረምና፡ ሳያስቡ፡ በመኖር፡ ጎዳና፡ ስትሄድ፡ የራሷ፡ ሙያ፡ ያጣች፡ ሆና፡ ወድቃለች። ሸቀጣቸውን፡ የሚያራግፉባትም፡ በሙያ፡ ቢስነቷ፡ ከናቋትና፡ ካፌዙባት፡ ቆይተዋል።  ኢትዮጵያ፡ አሁን፡ ያሏት፡ የጥበብ፡ ምሳሌዎች፡ እንኳን፡ ሳይቀር፡  ጥንት፡ የራሷን፡ ሥራ፡ ስትሠራ፡ የተገኙት፡ ብቻ፡ ናቸው። ቤቷ፡ በውጭ፡ የተውሶ፡ ትምህርት፡ ከተወረረ፡ ወዲህ፡ በኢትዮጵያ፡ ሌላው፡ ቀርቶ፡ ለትልውድ፡ የሚሆኑ፡ የጥበብ፡ ምሳሌዎች፡ ተፈጥረውባት፡ አያውቁም።                   

እንግዲህ፡ ማሰብ፡ ሥራን፡ የሚፈጥር፣ በቀላል፡ ወጭ፡ ብዙ፡ ትርፍን፡ የሚያስገኝ፡ ጸጋ፡ በመሆኑ፡ ኢትዮጵያውያን፡ ተዘጋጅቶ፡ የመጣን፡ መቃረም፡ ትተው፡ እያሰቡ፡ እንዲሰሩ፣ አካባቢያቸውንም፡ እንዲያስተውሉ፡ የሚያስችል፡ ኢትዮጵያን፡ በሚጠቅም፡ መንገድ፡ የተነደፈ፡ ኢትዮጵያዊ፡ ትምህርት፡ በትምህርት፡ ቤቶች፡ ሊሰጥ፡ ይገባዋል። በግ፡ እንደ፡ ፍየል፣ ላም፡ እንደ፡ አህያ፣ አንበሳ፡ እንደ፡ ጭልፊት፣ ዶሮ፡ እንደ፡ ወፍ፣ ፈረስ፡ እንደ፡ ግመል፡ ልኑር፡ ቢሉ፡ ኑሯቸው፡ ይበላሻልና፡ ኢትዮጵያውያንም፡ እንደራሳቸው፡ እንጅ፡ እንደ፡ ሩቅ፡ አገር፡ ሰዎች፡ እንኖራለን፡ ሲሉ፡ ኑሯቸው፡ አያምርም። ኑሮን፡ ማሻሻልና፡ እድገትን፡ መሻት፡ መልካም፡ ነገር፡ ሲሆን፡ እድገትን፡ መሻት፡ በኢትዮጵያዊ፡ መንገድ፡ እንጂ፡ በትውስት፡ መንገድ፡ መሆን፡ የለበትም። ለምሳሌ፡ የእግር፡ መንገድ፡ አድክሟቸው፡ ኢትዮጵያውያን፡ የሚሽከረከር፡ ወይም፡ ከቦታ፡ ቦታ፡ ሳይደክሙ፡ የሚያጓጉዛቸው፡ ነገር፡ ቢሹ፡ ተሸካሚውን፡ እራሳቸው፡ መሥራት፡ አለባቸው፡ እንጂ፡ ከውጭ፡ ተሰርቶ፡ ቢመጣ፡  መጓጓዣ፡ ከማጣት፡ የከፋ፡ ውድቀትን፡ ያስከትልባቸዋል። ተሸካሚው፡ ማጓጓዣ፡ መኪና፡ ቢሆን፣ መኪናም፡ በነጻ፡ የሚሰጥ፡ እንኳን፡ ቢሆን፡ ኢትዮጵያውያንን፡ ይጎዳል፡ እንጂ፡ አይጠቅምም።  ጎማውን፡ እንደገና፡ መፍጠር፡ አይጠቅምም፡ የሚለው፡ የውጭ፡ ተረት፡ ተስማሚነቱ፡ ጎማውን፡ ለፈጠሩት፡ እንጂ፡ ለኢትዮጵያውያን፡ አይደለም። የውጭ፡ ሰዎች፡ በጎማው፡ ተሻሽለው፡ ከሆነ፡ እድገትን፡ ያገኙት፡ ጎማ፡ እንድ፡ ውጤት፡ ሆኖ፡ ስለቀረበላቸው፡ ሳይሆን፡ ጎማውን፡ ለመፍጠር፡ ባደረጉት፡ ጉዞ፡ ነው። ኢትዮጵያውያን፡ መልካም፡ ኑሮን፡ እንዲጎናጸፉ፡ ከዚህ፡ ቀደም፡ መልካም፡ ኑሮን፡ ካጎናጸፏቸው፡ የራሳቸው፡ ከሆኑ፡ ጉዳዮች፡ ጉዟቸውን፡ መጀመር፡ አለባቸው።  እነዚህንም፡ በዝርዝር፡ እግዚአብሔር፡ በፈቀደ፡ ወደፊት፡ እናያለን።


እግዚአብሔር፡ የተመሰገነ፡ ይሁን።

*********************************
ምንጭ:--
፩ . ግብይት፡ በአቢሲኒያ፣ ኒው፡ ዮርክ፡ ታይምስ፣ መጋቢት፡ ፴ ቀን፡ ፲፱፻፪ ዓ.ም.

. ሚሊዮኑ፣ ገጽ፡ ፪፻፹፭፡ ሮስቲሸሎ፡ ዳ፡ ፒዛ፡ በ፲፪፻፺፩ እንደጻፈው፣ ማርኮ፡ፖሎ፡ እንዳስጻፈው
http://www.oftsion.org/Education.html
 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

የገጣሚ ነብይ መኮንን እማይነትበዉ ስዉር-ስፌት

ሞክሼ የአማርኛ ፊደላት እና የባለሙያዎች ማብራሪያ

ንባብ ለሕይወት!