ሰኞ, ማርች 21, 2016

ከድርሰት ዓለም


ሊነበብ የሚገባ መጥሃፍ:-
***********************

  ልጅነት

በዘነበ ወላ
***********************

ልጅነት -
እማዬ መዋሸት ነውር እንደሆነ ደጋግማ የምታስጠነቅቀኝን ያክል፤ ለበጐ ሲሆን እንዴት ማበል እንዳለብኝ የምታስጠናኝ ጊዜም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሁሌም ጠንካራ እውነተኝነቷ ስለሚገዝፍ እኔም በአብዛኛው የምከተለው ይህንኑ ባሕርይዋን ነበር፡፡
ቤተሰቦቼ የአንድነት እድር አባል ናቸው፡፡ አንድ ቀን እማዬ ወርሐዊ መዋጮውን ሄዳ መክፈል አልቻለችም፡፡ አባቴም ለሥራ ከወጣበት አልተመለሰም፡፡ እድርተኛው የሚሰበሰብበት ቦታ ቅርብ ስለነበር እኔን ላከችኝ፡፡
“ብሩን ጭብጥ አድርገህ ያዝ፤ ዜራሞ ኢንቻ ሲሉ አቤት በል፡፡ ካርዱን ስጣቸው፡፡ ስለ አባትህ ሲጠይቁህ ሸማ ለደንበኞቹ ሊያደርስ ጠዋት ነው የወጣው በል፡፡ እናትህን ካሉህ ትናንትና አክስቴን አሟት ከሄደችበት አልተመለሰችም በላቸው፡፡”
“እሺ፡፡”
“ስትመለስ እንጎቻ ጋግሬ እጠብቅሃለሁ፡፡ በል ብርርር ብለህ ሂድ!”
የእድሩን መዋጮ ከፍዬ ተመለስኩ፡፡
“ከፈልክ?”
“አዎን”
“ታዲያ ምነው አኮረፍክ?”
“ምንም፡፡”
በዚህ መካከል አደይ ዝማም ወደ ቤታችን እየሳቁ ገቡ፡፡ እንዳዩኝ “አይ ፉንጋይ! እድርተኛውን ሁሉ በሳቅ ሆዳችንን አፈረሰው፡፡”
“በምን ምክንያት?” አለች እማዬ፣ ትንሽ ፈገግ ብላ አደይ ዝማምን እያየች፡፡
“ዜራሞ ኢንቻ ሲባል አቤት አለ፡፡ አባቱን ሲጠይቅ ሸማ ሊያደርስ ከሄደበት አልተመለሰም አለ፡፡ እናትህስ? ሲሉት አትናገር ብላኛለች እንጂ እቤት ውስጥ አረቄ እያወጣች ነው፡፡”
“አንተ! ብላ አፈጠጠችብኝ ዓይኖቿ ግን አይቆጡም፡፡
“አንቺ ነሻ” አልኳት
እኔ ምን አልኩኝ?”
“አትዋሽ እያልሽ ሁልጊዜ ትቆጫለሽ፤ ሰባቂ እያልሽ ትማቻለሽ፡፡ አሁን ደግሞ ብዋሽ…”
ከትከት ብላ ስቃ በብሩህ ዓይኖቿ ቁልቁል አየችኝና “አይ ፉንጋይ! እስኪ ልብ ይስጥህ፡፡ በል ሂድና ትንሿ ጎርጓዳ ሳህን ውስጥ ያስቀመጥኩልህ እንጎቻ አለ፤ ውሰድና ብላ” ብላኝ በቅርቡ የፈፀምኩትን ሌላ የቂልነት ድርጊት ለአደይ ዝማም ልታወራላቸው ስትጀምር፤ አደይ ዝማም አቋርጠዋት የራሳቸውን ልጅ የጐይቶምን ቂልነት ለእማዬ ያጫውቷት ጀመር “እትዬ ባሎቴ የእኔም ጉድ ያው እንደ ፉንጋይ እኮ ነው! በቀደም ዕለት ከትምህርት ቤት ሲመጣ ምሳውን ጓዳ አስገብቼ ደብቄ ያስቀመጥኩለትን እሰጠዋለሁ አልበላም አለ፡፡
“ለምን?”
“አንቺ ከዘመዶትሽ ጋር በጐመን እየበላሽ ለእኔ በአይብ ትሰጪኛለሽ?”
ሁለቱም ከልብ የኮረኮሯቸውን ያህል ሳቁ፡፡

ጋዜጠኛና ደራሲ ዘነበ ወላ
***********************************
(ምንጭ፡ - ዘነበ ወላ “ልጅነት” (2000))
አሁን ‹‹ልጅቴ፣ ልጅነቴ - ማርና ወተቴ …›› በሉ
  -Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን)
ፎቶግራፍ:--   Muluken Asrat
 




ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ማሞ ካቻ (አቶ ማሞ ይንበርብሩ)

  አቶ ማሞ ይንበርብሩ (ማሞ ካቻ) እስቲ እናስታውሳቸው፣ ተቀብሮ እንዳይቀር አኩሪ ታሪካቸው  (ደረጀ መላኩ)   አቶቢሲ ማሞ ካቻ የት ትሄዳለህ? ገብረ ጉራቻ… ታዳጊው ማሞ ይንበርበሩ ገና በጨቅላ እድሜው አባቱ አቶ...