ያዕቆብ ወልደማርያም

ጎምቱ ጋዜጠኛ!__ያዕቆብ ወልደማርያም
*************************
ስለ ኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ሲወሳ ስማቸው አብሮ ከሚጠቀሰው ውስጥ ይመደባሉ። የመንግሥታዊው «ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ» ጋዜጣ የመጀመሪያው ኢትዮጽያዊ ዋና አዘጋጅም ሆነው ሰርተዋል - አቶ ያዕቆብ ወልደማርያም። ዛሬም በ86 ዓመታቸው ከሙያው አልራቁም። ያነባሉ፣ ይጽፋሉ፣ በሌላ ሰው የተጻፉትንም ያርማሉ።
ይህን ተግባራቸውን የነፍሳቸው ምግብ ያህል የሚቆጥሩት አቶ ያዕቆብ፤ በሚዲያ ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ፈቃደኛ አይሆኑም። ስለ ሥራቸውና ማንነታቸውም መናገርን አይሹም። «ታዋቂነትና ዝነኝነት በሥራ እንጂ በቲፎዞ ወይንም በሌሎች ፍላጎትና ግፊት መሆን የለበትም» ብለው ያምናሉ።
ይህን እያሰብኩ ከአንድ ወዳጃቸው ስልካቸውን ወስጄ ደወልኩ፤ ስልካቸውን አነሱ። ማንነቴን ገልጬ ለቃለ ምልልስ ቀጠሮ እንዲይዙልኝ ጠየቅሁ። በቀላሉ ፈቃዳቸው ይሆናል ብዬ ባልገምትም በስልክ ንግግራችን ብዙም የማሳመን ጥረቴን ሳልገፋ «የእኔ ታሪክ ለሌሎች የሚጠቅምና የሚያስተምር ከሆነ መልካም፤ ይሁን!» የሚል ምላሻቸውን አገኘሁ።
በሦስተኛው ቀን በተቀጣጠርንበት ሰዓት ሽሮ ሜዳ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ያቀናሁት እኚህን ጎምቱ (በሳልና አንጋፋ) ጋዜጠኛ፣ በአገሪቱ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፎች ሁሉ ሃሳባቸውን በብዕራቸው ሲያነጥቡ፤ የሌሎችንም ጽሑፎች ሲያረቱ የነበሩትን አረጋዊ እንዴት ባለ አቅም ቃለ መጠይቅ ማድረግ እንደሚገባ እያሰብኩና እያሰላሰልኩም ነበር። የእርሳቸው አቀራረብ ግን ነገሮችን ሁሉ ቀላል የሚያደርግ ሆነ።
ለማንበቢያና ለመጻፊያ ምቹ ሆኖ በተዘጋጀና በመስታወት በተከለለ በረንዳቸው ከሁለት ሰዓት በላይ ባደረግነው ቆይታ የበርካታ ዘመናት ጋዜጠኝነት ሙያዊ አስተዋጿቸውንና የሕይወት ልምዳቸውን እንዲህ አወጉኝ፡፡
ትውልድና እድገት
የአቶ ያዕቆብ የሕይወት ጉዞ እርካብ የሚጀምረው ሰኔ ወር1921 ዓ.ም ከአባታቸው አቶ ወልደማርያም ሹባ እና ከእናታቸው ወለተሚካኤል ሰንበቶ በነቀምቴ ከተማ እንደተወለዱ ነው። ለቤተሰባቸው ሁለተኛ ልጅ ሲሆኑ፤ በሁለት ወንድሞችና ሁለት እህቶች መካከል ነው ያደጉት። በተፈጥሯቸው ነገሮችን የማወቅ ጉጉት ያላቸው የያኔው ልጅ ያዕቆብ፤ በወቅቱ በከተማው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ከአባታቸው እግር ስር ሆነው ፊደል ቆጠሩ፡፡ አማርኛ ማንበብና መጻፍም ቻሉ። አባታቸው ደግሞ ይህንን እውቀት ያገኙት ዝቋላ እና ደብረ ሊባኖስ ገዳሞች ውስጥ እንደ ልጃቸው ከአባቶች እግር ስር ሆነው እየለመኑ የአብነት (የቆሎ) ትምህርት ተምረው ነው። አባታቸው ይህን ዕውቀት ፍለጋ ከነቀምት ደብረ ሊባኖስ አሥራ አንድ ቀን ያህል በእግራቸው ተጉዘው እንደነበር አቶ የዕቆብ ያወሳሉ።
ጣሊያን አገራችን ሲገባ እርሳቸው ሰባተኛ ዓመታቸው ነበር፤ ያኔ ለትምህርት ከነበራቸው ፍቅር የተነሳ ያለ ቤተሰቦቻቸው ፈቃድ የጣሊያንኛ ትምህርት ቤት ገብተው ለሦስት ዓመታት ተማሩ። ጣሊያኖች ሲወጡ ደግሞ ከውጭ የገቡት የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታዮች ያንን ትምህርት ቤት ተረክበው ስለነበር በመደበኛ ትምህርት እንግሊዝኛን መማር ጀመሩ።
ከእዚያም ተፈሪ መኮንን አንደኛ ደረጃ የመንግሥት ትምህርት ቤት ስለተቋቋመ እዚያ ገቡ፡፡ ይህን እንዳጠናቀቁ በአዲስ አበባ ኮተቤ የመጀመሪያው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስለተከፈተ ከየክፍለ አገሩ ጥሩ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች በፈተና ወደእዚህ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ተደረገ። አቶ ያዕቆብ ፈተናውን በከፍተኛ ውጤት አልፈው ከስምንተኛ ክፍል ጀምሮ ዘመናዊ ትምህርታቸውን በእዚህ ጀመሩ። ለአምስት ዓመታትም ተምረው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በከፍተኛ ማዕረግ በማጠናቀቃቸው ሌላ ዕድል አመጣላችው። ላገኙት ከፍተኛ ውጤት ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እጅ ሽልማት ተቀብለው ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ለንደን ይላካሉ፡፡
ትምህርት በለንደን
አቶ ያዕቆብ ወደለንደን ሲሄዱ የሚማሩት ትምህርት ተወስኖላቸው ነበር። ያኔ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል እና የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት መሐንዲሶችን በብዛት ይፈልጉ ነበር። በሳይንስና በሒሳብ ትምህርት የጨረሱትን የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ስፖንሰር በማድረግ እንዲማሩ ሲያደርግ፤ አቶ ያዕቆብና አንድ ሌላ ተማሪም የኤሌክትሪካል ምህንድስና እንዲማሩ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ተሸኙ። የለንደን ዩኒቨርሲቲ አካል በሆነው «ኢምፔሪያል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ውስጥ ትምህርታቸውን በጥሩ ውጤት እየተማሩ የነበረ ቢሆንም፤ በጊዜ ሂደት የመቀጠል ፍላጎታቸው እየተቀዛቀዘ መጣ።
እንዲማሩ በተፈለገው በእዚያ ሙያ በአዕምሮ ብቻ የሚሰራ ነገር የለም። የእጅ ሥራ መብዛቱ፣ ሜካኒካልና ድሮዊንግ ነገር መስራቱ፣ በቤተሙከራ ውስጥ መንደፋደፉ ለእርሳቸው ምቾት አልሰጠም። እናም ከዚሁ እየጠሉት ከመጡት ትምህርት ጎን ለጎን በግላቸው የተለያዩ የፍልስፍና መጻሕፍትን ማንበብ ተያያዙት።
በእዚያው የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎሙ የጀርመን፣ የራሺያና የግሪክ እንዲሁም የሌሎች አገራት የሥነ ጽሑፍ እና የፍልስፍና መጽሐፎች ውስጥ ሰመጡ። ቀስ በቀስ እንዲማሩ የተላኩበትን የኤሌክትሪካል ምህንድስና ትምህርታቸውን እየተዉት መጡ፤ ስለጋዜጠኝነት የሚያወሱ ሙያዊና ታሪካዊ መጽሐፍቶችንም በተመስጥኦ ማንበብን ቀጠሉ። ጋዜጦችና መጻሕፍትንም በፍቅር ማንበቡን ተያያዙት። በዚያው መጠን ሙያውን እየወደዱት መጡ። በተለያዩ የአጻጻፍ ቴክኒኮች እየተደነቁ «እኔ ብሆን» የሚል መንፈሳዊ ቅናትም ያደርባቸው ጀመር። በዚህ ወቅት በኮሌጁ ኢትዮጵያውያን «ላየንስ ክለብ» በሚል መሰባሰቢያቸው ስር ያቋቋሙት መጽሔት ነበርና የያኔው ወጣት አቶ ያዕቆብም የተለያዩ መጣጥፎችን በማዘጋጀት ብዕራቸውን በዚህችው መጽሔት አሟሹ።
ቀጠሉናም የተለያዩ የእንግሊዝ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ሃሳባቸውን የማስፈር ጥረት አደረጉ። «ኦብዘርቨር»፣ «ማንችስተር»፣ «ዴይሊ ቴሌግራፍ» የተሰኙ የህትመት ውጤቶች ላይ ጽሑፋቸው እንዲወጣላቸው መላክ ጀመሩ፡፡ የላኩት አብዛኞቹ ባይወጡላቸውም ወደ ሙያው ለመግባት ፍንጭ ያዩበት ሙከራቸው ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ፕሮፌሰር ሲልቪያ ፓንክረስት በሚያዘጋጁት ኒውስ ታይም የተሰኘ ጋዜጣ ላይም ይጽፉ እንደነበር ያስታውሳሉ። አቶ ያዕቆብ በዚህ ስሜት ውስጥ ሆነው ነው ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ አገራቸው የተመለሱት። ይህም ከትምህርት ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ጋር አጋጭቷቸው ነበር፡፡
ወደ ሥራው ዓለም
በአዲስ አበባ የአምሃ ደስታ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ብር 300 ወርሃዊ ደመወዝ እየተከፈላቸው የሒሳብና የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር መሆን የመጀመሪያ ሥራቸው ሆነ። ውስጣቸው በነበረው የጋዜጠኝነት ስሜት በመነሳሳትም ከማስተማሩ ጎን ለጎን የተማሪዎች ጋዜጣ አቋቋሙ። ከሁለት ዓመት በኋላ፤ 1950ዎቹ መጨረሻ ወደ ትውልድ አገራቸው ነቀምት ተዛውረው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ማስተማራቸውን ቀጠሉ። በእዚያም በተማሪዎች የሚዘጋጅ ተወዳጅ ጋዜጣ በማቋቋም ይበልጥ ወደ ሙያው ተሳቡ። በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚዘጋጀው በዚህ ጋዜጣ የእርሳቸው ሚና የእንግሊዝኛውን ክፍል ማረም እና ርዕሰ አንቀፅ ማዘጋጀት ነበር። በዚህ ወቅት የገጠማቸውን እንዲህ ያወጋሉ።
«...አንዱ ተማሪ አንድ ግጥም ይጽፋል፤ ግጥሙ የሚመኘውን የገለጸበት ነው፡፡ የሚፈልገውን ዓይነት ሙያና የኃላፊነት ደረጃ ከገለጸ በኋላ ከሁሉም ከሁሉም የምፈልገው እንደራሴ መሆን ነው ይላል። ጋዜጣውን ብዙ ኮፒ አዘጋጅተን በሽያጭ ከተማ ውስጥ በተንነው። ታዲያ የጃንሆይ እንደራሴ እዚያው ነበሩና በማግስቱ ጉድ መጣ። ሌሎች ሹማምንትን አስከተለው እንደራሴው ቢሮዬ ከተፍ አሉ። ʿማን ፈቅዶላችሁ ነው ይህን ያደረጋችሁት?ʾ ሲሉ ጠየቁ፤ ምን እንበል...ከዚያ ሁኔታችንን አይተው ለክፋት አለመሆኑን ከተረዱ በኋላ እንደ መቆጣትም እንደ መገሰጽም ብለው ተመለሱ»።
ያቺ ክስተት ግን ለእርሳቸው የመጀመሪያዋ የአርታኢ (Editor) ሙያ ምን ያህል ኃላፊነት እና ጥንቃቄ የሚያሻው መሆኑን ትምህርት ሰጥታቸው አለፈች። የሳንሱር ምልክትንም ያዩት በዚህ አጋጣሚ ነው። የሆነው ሆኖ በትምህርት ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር ሆነው ሁለት ዓመት ካስተማሩ በኋላ የሚለቁበት ሌላ አጋጣሚ ተፈጠረ። አቶ ያዕቆብ አጋጣሚውን እንዲህ ያስታውሱታል።
«ያኔ የልዑል መኮንን መታሰቢያ ሆስፒታል በነቀምት ይሰራ ነበር፡፡ አቶ ኤፍሬም የተባሉ የወቅቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ማዘጋጃ ቤት ሰብስበውን ለሆስፒታሉ ገንዘብ እንድናዋጣ ጠየቁ። እኔ ጥያቄው አልተመቸኝም፤ ʿከደመወዜ አሥር ብር አሰጣለሁʾ አልኩ። የሚፈለገው የአንድ ወር ደመወዝ ነበር። በዚህ ጊዜ ተቃውሞ ገጠመኝ። ʿአድማ መምራት ነውʾ ተባልኩኝ። በዚሁ ምክንያት ሥራዬን ትቼ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ። በአንድ ጓደኛዬ ጥቆማ መብራት ኃይል ባለሥልጣን በ360ብር ደመወዝ በመስመር ዝርጋታና ቴክኒክ ክፍል ተቀጠርኩ። ሥራው ግን አልተ መቸኝም፡፡
«ይህን የተረዳው ኃይለልዑል ጠብቄ የተባለ እንግሊዝ አገር አብረን የተማርን ጓደኛዬ ʿለምን ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ አትገባም። ዋና አዘጋጁ ዶክተር ዴቪድ ኤ ታልቦት ጋዜጠኛ ይፈልጋል፤ ሄድና ተፈትነህ ግባ አለኝ።ʾ ይህን ሊለኝ የቻለው እንግሊዝ አገር እያለን በተለያዩ ጋዜጦች ላይ በምጽፋቸው ጽሑፎች ፍላጎቴንና አቅሜን ስለተረዳ ነው። እንዳለው ሄድኩና ስጠይቅ ʿሄድና ቤትህ ጽፈህ ናʾ ብሎ ፈተናውን ሰጠኝ። ʿየለም? እዚሁ እፅፋለሁʾ አልኩት። ʿበእንግሊዝኛ አርቲክል ጻፍ አለኝʾ ጻፍኩ። ከፈረንሳይኛ ወደ እንግሊዝኛ የሚተረጎም ጽሑፍ ሰጠኝ፤ በጥሩ ሁኔታ ተረጎምኩ። በጣም ተገረመ። ደስ እያለው ʿእንፈልግሃለንʾ አለ፡፡ ገባሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ ጋዜጠኛ ሆንኩ»፡፡
ጋዜጠኝነት
የሥራ አመራር ሥርዓት በአግባቡ ባልተደራጀበት፣ የሲቪል ሰርቪስ ሕግም ሆነ የጡረታ ዋስትና በሌለበት በዚያን ዘመን ብቻቸውን ተፈትነው በማለፍ በ1951ዓ.ም በ400ብር ደመወዝ ጋዜጠኝነት ሙያን ተቀላቀሉ፡፡ ወዲያውም ታላላቅ ጉዳዮችን እያነሱ በፊት ገጽ ዜናዎችን፣ በውስጥ ገጽ ደግሞ መጣጥፎችን በአማረ እንግሊዝኛ ቋንቋ ያዥጎደጉዱት ጀመር፡፡ በዚህ ጊዜ የመብራት ኃይል ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ እጅግ ተገረሙ፤ ትልቅ ሰው እንዳጡ ቁጭት ተሰማቸው። የመብራት ኃይሉ ሥራ አስኪያጅ ሰይፉ ማህተመሥላሴ አግባብተው እንደገና ቢመልሷቸውም ወዲያ ግን የወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት ʿንጉሡ ጋር ሄጄ እከሳለሁʾ በማለት ከፍተኛ ቁጣ ስላስነሱ እንደገና ወደ ሄራልድ ተመለሱ፡፡
በወቅቱ ከዋና አዘጋጁ ዶክተር ታልቦት ቀጥሎ ሁለተኛ ሰው እርሳቸው ነበሩ፡፡ አዘጋጅ ሆነው ጽሑፍ ያርማሉ፣ ሌሎች ጋዜጠኞችን ሥራ ያሰማራሉ፣ በፈረንሳይኛ እና በጣሊያንኛ ከውጭ የሚላኩ ዜናዎችንና ሌሎች ጽሑፎችን ይተረጉማሉ፡፡ ሥራው ፋታ የማይሰጥ ቢሆንም የሚወዱትና የሚመኙት ሙያ ነበርና በትጋት ቀጠሉ፡፡
በሂደት ይከፈላቸው ከነበረው ደመወዝ ላይ ብር 100 ተጨምሮላቸው ወደ ምሽት አርታኢነት ተዛወሩ፡፡ እዚያም ለስድስት ወራት ሰሩ፡፡ አራት ገጽ ያለው ጋዜጣ ለማዘጋጀት እስከ ንጋት 11፡00 ሰዓት ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሆነው ጽሑፎችን የማረምና ለህትመት የማመቻቸት ሥራ ይሰራሉ። ምሽት ላይ የሚመጡ መግለጫዎችን በተለይም ከማስታወቂያ ሚኒስትሩ በቃል እየተቀበሉ በመስራት በማግስቱ እንዲወጣ ያደርጋሉ፡፡
የጋናው መሪ ኑኩርማ ዶክተር ታልቦትን ለጉብኝት ጋብዘዋቸው ለሦስት ወር ወደጋና በሄዱበት ወቅት ግን ሌላ ነገር ተፈጠረ፡፡ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትሩ አቶ አምደሚካኤል ደሳለኝ ጋዜጣዋን በቅርብ ኃላፊነት ይከታተሉት ነበር፡፡ በውስጣቸው ለምን የጋዜጣው (ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ) ዋና አዘጋጅ አይሆንም የሚል ቁጭት ስላደረባቸው በዚህ አጋጣሚ ጥሩ ለሚሰራ ሹመት መስጠትን ፈለጉ፡፡ እናም ለቦታው ይመጥናሉ ብለው ያሰቧቸውን አቶ ያዕቆብ ወልደማርያምን፣ አቶ ነጋሽ ገብረማርያምን እና አቶ አያሌው ወልደ ጊዮርጊስን ቢሯቸው አስጠርተው «በሉ ከሦስታችሁ አንዳችሁ ዋና አዘጋጅ ትሆናላችሁ፤ ፈተና ልስጥ ወይንስ እናንተ ከመሀላችሁ ትመርጣላችሁ? ሲሉ ጠየቁን» ሁለቱም አቶ ያዕቆብ እንዲሆኑ ተስማሙ፡፡ ምርጫው ፀደቀ፡፡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የ«ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ» ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኑ፡፡
የዋና አዘጋጅነቱን ቦታ እንደያዙ በጋዜጣው ቅርጽና ይዘት ላይ ለውጥ አደረጉ፡፡ ለወትሮው የውጭውን ዓለም ታሪክና ዜና ከማቅረብና የንጉሡ እንዲሁም የሹማምንቶቻቸውን አንዳንድ ክዋኔዎች በዜናነት ከማውጣት በዘለለ ሌሎች የማህበረሰቡን ክንዋኔዎች ዳስሳ የማታውቀው ሄራልድ ጋዜጣ አሁን የተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ሌሎች ሁነቶችን በስፋትና በጥልቀት መዘገብ ጀመረች፡፡ አገራዊ ጉዳዮች ላይ እንድታተኩር መደረጓ አቶ ያዕቆብን አስመሰገናቸው፡፡ «አይችሉም!» ተብሎ ተስፋ የታጣለባቸው ኢትዮጵያውያን አቅማቸው ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነም ታየ፡፡
እንደ አቶ ያዕቆብ ትውስታ፤ በዚያን ወቅት ታልቦት ደመወዛቸው 3ሺ 500 ሲሆን፤ የእነ አቶ ያዕቆብ ደመወዝ ከ500 ብር አልበለጠም ነበር። ቀስ ብሎ ግን አደገ፡፡ በወቅቱ ታልቦት የመነሳታቸው ነገር በአንዳንድ ሹማምንቶች ትንሽ ቁጣን ማስከተሉ አልቀረም፡፡ ምክንያቱም ቤተ መንግሥት ድረስ ስር የሰደደ ታዋቂነትና ተቀባይነት ስለነበራቸው፡፡
በዚያን ወቅት አቶ ያዕቆብ የሌሎች አገራት መልካም ተሞክሮዎችን እየጠቀሱ ለአገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት የሚበጁ ሃሳቦችን በርዕሰ አንቀጽ እና በሌሎች ገጾች ይጽፉ ነበር፡፡ በተለይ ስለ መሬት ከበርቴ፣ ስለ ሲቪል ሰርቪስ መቋቋም፣ ስለ ጡረታ ሕግ አወጣጥ ብዙ ወትውተዋል። ስለ ቤት ኪራይ እና ስለ ሹም ሽረት ሥርዓት ጉዳይም አበክረው ጽፈዋል፡፡
የኩዴታው ሰበብ
ለሁለት ዓመታት በዚሁ ኃላፊነታቸው እንደሰሩ ለመልቀቅ ምክንያት የሆናቸውን እንዲህ ይገልጻሉ። «በዚሁ ኩዴታ ወቅት ሕዝቡ ʿእነ ጀኔራል ጃገማ ኬሎ መንግሥት ሊገለብጡ ነውʾ እያለ በመራበሽ ልጆቹን ከትምህርት ቤት ማውጣት ጀመረ፤ ታዲያ እኔ ʿዜና በትክክል ቢሰጥ ኖሮ ይህ ሁሉ ውዥንብር አይፈጠርም ነበርʾ ስል በርዕሰ አንቀፅ ጻፍኩኝ፡፡ በዚህ ጊዜ በመነን መጽሔት እንግሊዝኛው ውስጥ የሚጽፍ ስሚዝ የተባለ አፍሮ አሜሪካዊ ሃሳቤን ይዞ ለውጭ አገር ሚዲያዎች አስተጋባ። ይህ ሲሆን የውጭ ጋዜጦች በአገራችን የጋዜጠኝነት ነፃነት የሌለ መሆኑን በመግለጽ ማስታወቂያ ሚኒስቴርን በመተቸት ወሬውን ተቀባበሉት፡፡ በዚህ ጊዜ በመንግሥት ጥርስ ተነከሰብኝ፡፡ ወዲያውም ደጃዝማች ግርማቸው ወልደሐዋርያት ከጋዜጣው ሥራ እንድነሳ አደረጉ»።
ከዚያም ቀድሞ «አጃንስ» ተብሎ ወደሚጠራው በአሁኑ አጠራሩ «የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ» የእንግሊዝኛው ክፍል ተዛወሩ፡፡ እዚያም ትንሽ እንደሰሩ እንደገና ስለመዛወራቸው የገለጹት «... አንድ ቀን ከቢሮ ሥራ ጨርሼ ቤቴ ለመሄድ ወደ መኪናዬ ሳመራ ግቢው ውስጥ ቀድሜ ያላየኋቸው ማስታወቂያ ሚኒስትሩ ብላታ ግርማቸው ጠሩኝ። ምን ቁጣ ሊያመጡብኝ ይሆን ስል ʿበል ና ይሄ ስሚዝ የሚባለው ሰው አይደለም ዜናውን ያስተላለፈው!?ʾ በል አሁን መነን የእንግሊዝኛው መጽሔት ላይ ሂድና ሥራ ጀምር። ስሚዝን በስድስት ወር ውስጥ ከሥራ አባርረዋለሁ። ከዚያ አንተ በእርሱ ቦታ ዋና ኤዲተር ትሆናለህ አሉኝ» እንዳሉትም ሆንኩኝ፡፡ በማለት ነው፡፡
በዚህ ሁኔታ በአገር ፍቅር ስር ትተዳደር ወደነበረው መነን መጽሔት የተዛወሩት አቶ ያዕቆብ፣ የመጽሔቷ ዋና አዘጋጅ ሲሆኑ ከአማርኛው ጋር ተዳብላ የነበረችውን መጽሔት ራሷን ችላ እንድትወጣ ማድረግ የመጀመሪያ እርምጃቸው ሆነ፡፡ በቅርፅና ይዘት ደረጃ ከሌሎች የውጭ አገር መጽሔቶች ባልተናነሰ ሁኔታ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ዘመናዊነትን ተከትለው ሲያዘጋጁ ብላታ ግርማቸውም ሆኑ ሌሎች ሹማምንቶች መደሰታቸው አልቀረም፡፡ መጽሔቷን ወደ ተሻለ ብቃት ሲያሳድጓት የውጭ መጽሔቶችን አርአያነት እየተከተሉ ነበር፡፡ ብዙ ማንበባቸውና ሙያውን ማፍቀራቸው ሁሌም የተሻለ ሥራ እንዲሰሩ ብርታት እየሆናቸው ቀጠሉ፡፡
በዚህ መጽሔት ለተወሰነ ዓመታት እንደሰሩ የእንግሊዝኛዋ «የቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ» ጋዜጣንም ደርበው እንዲያዘጋጁ ኃላፊነት ተሰጣቸው፡፡ አቶ ያዕቆብ እንደሚሉት፤ ያኔ በአገር ፍቅር ማህበር ያሉ ጋዜጦችንና መጽሔት በዳይሬክተርነት የሚመሩት አቶ ከበደ አበበ የሰጡት የመስራት ነፃነት ለህትመት ውጤቶቹ ጥሩ ደረጃ ላይ መድረስ አስተዋጽኦ ነበረው። በኋላም ሙሉ ለሙሉ ከመጽሔቷ ወደ ቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ተዛውረው ለሰባት ዓመታት ያህል ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
የእንግሊዝኛው ቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ሲዘጋ በእዚያው ይከፈላቸው የነበረውን ደመወዝ ይዘው ወደ ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ ተመልሰው በአማካሪነት ተመደቡ። የደርግ መንግሥት እስኪመጣ ድረስ ከማማከሩ ጎን ለጎን በፍላጎታቸው ርዕሰ አንቀጽና መጣጥፎችን ያዘጋጁ ነበር፡፡ ደርግ ሥልጣን ሲይዝ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የኤሌክትሮኒክሱንና የህትመት ጋዜጠኞችን እያዘዋወረ ሲደለድል አቶ ያዕቆብ የደረሳቸው በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ፐብሊኬሽን ዘርፍ ነበር፡፡ በዚያም የእንግሊዝኛው የየካቲት መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሆነው አገልግሎታቸውን ቀጠሉ፡፡ እዚሁ እየሰሩ ጡረታ ሊወጡ ስድስት ወራት ሲቀራቸው በ1980 ዎቹ አጋማሽ ላይ በእዚሁ የጽሑፍ ሥራቸው ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይዛወራሉ። ያኔ ደመወዛቸው 950 ብር ደርሷል፡፡
በማስታወቂያ ሚኒስቴር በጋዜጠኝነት ሥራ ብቻ ከ34 ዓመታት በላይ የሰሩት አቶ ያዕቆብ በተለያዩ የአገሪቱ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፎች ሳይቀር ሙያው ውስጥ ነበሩ። በደርግም ሆነ በዘውዳዊው ሥርዓት የጋዜጠኛው የሃሳብ ማነቆ እንደነበረበት ይናገራሉ፡፡ «እኔ የመንግሥት ቅጥረኛ እንደመሆኔ የምመራበትን የህትመት ፖሊሲ አስፈጻሚ ነኝ። በደርግ ወቅት የኮሚኒስት ርዕዮተ ዓለም ለመጻፍ ፍላጎት አልነበረኝም። የራሳቸው ሰዎች ይጽፉ ነበር እንጂ እኔ እንድጽፍ ያስገደደኝ አልነበረም» የሚሉት አቶ ያዕቆብ፤ ከአገሪቱና ከሕዝቡ ሁኔታ አንጻር ያንን መስበኩ ዋጋ ቢስ ነው ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ፡፡ ለአገሪቱ የሚበጃትን ሃሳቦች ከማፍለቅ ተቆጥበው እንደማያውቁ ዛሬ በታሪክ የሚጠቀሱት ጋዜጦች ምስክር እንደሆኗቸው ያብራረሉ፡፡
ናሽናል ካንሰር
ዘውዳዊው ሥርዓት በወታደራዊው ኃይል ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ ወጣቶች አገዛዙን በመቃወም ረብሻ በሀገሪቱ ተፈጠረ፡፡ ያኔ በዩኒቨርሲቲም ከፍተኛ ንቅናቄ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ያዕቆብ "National cancer" በሚል ርዕስ ስር የወጣቶችን ተግባር ተቃውመው ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ ላይ የጻፉት ጽሑፍ ተቃውሞ አስነስቶባቸው ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ያንን እያነሱ የሚተቿቸው አልጠፉም፡፡ ያኔ «አድርባይ» የሚል ቅጥያም ተሰጥቷቸው ነበር፡ እርሳቸው ግን ያ አድራጎታቸው ዛሬም ላይ ሆነው ሲያስቡት ትክክል እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡
«በእኔ እምነት በወቅቱ ሀገሪቱን ተረክቦ ማስተዳደር ያለበት ወታደራዊው አገዛዝ ነው። ዱላ ያነገተ ተማሪ ሥልጣን ሊይዝ አይችልም፡፡ እነርሱ የሚሉት ʿሕዝባዊ መንግሥት ይመስረት ነውʾ ያኔ እንዴት ይሆናል? አይቻልም! በሚል ሃሳባቸውን ተችቼ ነው የጻፍኩት፡፡ በወቅቱ ʿአናርኪʾ ከተፈጠረ ማነው ይህቺን አገር አንድ የሚያደርጋት? በበኩሌ ምክር ነው የለገስኩት፡፡ ያንን ማድረጌ ግላዊ ጥቅም በመፈለጌ አልነበረም፡፡ ያኔም ድሃ ነኝ፤ ዛሬም ድሃ ነኝ፡፡ በዚያ ጽሑፌ አልጸጸትም» ነው ያሉት - አቶ ያዕቆብ፡፡
የቀደሙ የጋዜጠኝነት ሥራን ከዛሬው ጋር ሲያነጻጸሩት ብዙ ክፍተቶች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ ሙያው ውስጥ በነበሩበት ባለፉት ሁለት መንግሥታት የሳንሱር ነገር ጋዜጠኛውን አማራሪ እንደነበር ያስታውሳሉ። ዛሬ ይህ ቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) አለመኖሩ አንዱ ልዩነት መሆኑን በመጠቆም፡፡ በደርግ ወቅት ጋዜጣ አለ ለማለት እንደማይደፈር የገለጹት «የኮሚኒስት ቲዮሪ ፕሮፓጋንዳ ብቻ ነበር » በማለት ነው።
አቶ ያዕቆብ፤ በሙያው ሳይንሳዊ እውቀት ሊኖር እንደሚገባ ቢያምኑም በልምድና ፍላጎት ጥሩ ጋዜጠኛ መሆን እንደሚቻል በእርሳቸው ጊዜ የነበሩ ታዋቂ ጋዜጠኞችን በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡ በዚህም ብላታ ወልደጊዮርጊስና አቶ ከበደ ሚካኤል በጣሊያን ጊዜ ʿየሮማ ብርሃንʾ የሚል ጋዜጣን ሲፅፉ የነበራቸውን ልምድ ማስተላለፋቸው ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ይናገራሉ።
የዛሬዎቹን ጋዜጠኞች በእርሳቸው ዘመን ከነበሩት ጋር ሲያነጻጽሩም ብዙ ክፍተት እንዳለ ይጠቅሳሉ። የሃሳብ ብቻ ሳይሆን የቋንቋ ችግር ውስጥም እንዳሉም ይናገራሉ፡፡ የቀደሙት ጋዜጠኞች አንባቢዎች ሲሆኑ፤ የዛሬዎቹ በንባብ ራስን በእውቀት የማበልፀግ ትጋት እንደሌላቸው መታዘባቸውንም እንዲሁ፡፡ ʿየማያነብ ጋዜጠኛ እንዴት ሊጽፍ ይችላል?ʾ ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ «አንድ ጋዜጠኛ የራሱን አቅም የሚለካው ሌሎች የደረሱበትን ሲያውቅ ነው፡፡ የሀገር ውስጥን ብቻ ሳይሆን የሌሎች አገሮች ጋዜጠኞች እንዴት እንደሚጽፉ መረዳት አለበት፡፡ ዓለም አቀፋዊ እውቀት ሲኖር ነው ብስለት ያለው ሥራ መስራት የሚቻለው» ይላሉ አቶ ያዕቆብ፡፡ ያም ሆኖ ተስፋ የሚጣለባቸው ጎበዝ ጋዜጠኞች መኖራቸው፣ ሙያው በዘመናዊ ትምህርት እየተደገፈ መምጣቱ የዘርፉን እድገት እንደሚያመለክት ይናገራሉ፡፡
ስለ አባይ ወንዝ ደጋግመው እንደጻፉ በአንድ ወቅትም ግጥም ሞካክረው ነበር፡፡ ዛሬ ያለበት ሁኔታ የኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋን የሚያሳይ በመሆኑ ይደሰታሉ፡፡ ዛሬም የውጭ ጋዜጦች ስለ ኢትዮጵያ የሚጽፉትን እንደሚመለከቱ የሚናገሩት አቶ ያዕቆብ፤ ስለ ልማቷና እድገቷ በመልካምነት እንደሚያወሱ፤ ስለ ፕሬስ ነፃነት እጦት ደግመው ደጋግመው እንደሚተቹ ይናገራሉ። ሁሉም ነገር በሂደት የሚስተካከል መሆኑ ግን የእርሳቸው እምነት መሆኑንም ነው የተናገሩት።
በአገራችን ስላለው የፕሬስ ነፃነትም በአንጻራዊነት ከ1980ዎቹ ወዲህ የተሻለ መሆኑን ይገልጸሉ፡፡ ይህን ነፃነት በመጠቀም በአንድ ወቅት በርካታ የህትመት ውጤቶች መታየታቸውን፤ ነገር ግን የሀሰት ዘገባ በማብዛታቸው ከገበያ እንደወጡና በክስና ቅጣት ምክንያት እንደከሰሙ ይናገራሉ፡፡ «የህትመት ውጤቶቹ የከሰሙት ነፃነታቸውን መገመት ባለመቻላቸው ነው፤ በወቅቱ ተዉ የራሳችንን መቃብር እራሳችን አንቆፍር እያልኩ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ እጽፍ ነበር፡፡ የሆነው እንዳልኩት ነው።...ያም ሆኖ ዛሬም በአንጻራዊነት ነፃነት አለ ለማለት ይቻላል» ይላሉ፡፡
ሽልማት
በተለያዩ ዘመናት ባከናወኗቸው ተግባራት ሽልማቶችን እና የምስክር ወረቀቶችን አግኝተዋል፡፡ በስፖርቱ ዘርፍ በተለይ በያኔው የኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳሉ ዝላይ እና የመቶ ሜትር ሯጭ ነበሩና በአሸናፊነታቸው ከንጉሡ እጅ ዋንጫ ተቀብለዋል፡፡ በትምህርታቸውም ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውም እንዲሁ አሸልሟቸዋል፡፡ በቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ ጋዜጣ በሙያቸው ባሳዩት ትጋትና የአሥር ዓመት አገልግሎት የፈረሰኛ ኮኮብ ኒሻን ከንጉሡ እጅ ተቀብለዋል፡፡ ባይጠቀሙበትም በስጦታ ያገኟቸው ቤት መስሪያ ቦታና ርስትም ሽልማቶቻቸው ነበሩ፡፡
በደርግ ሥርዓተ መንግሥት ከምስክር ወረቀት በዘለለ የተለየ ሽልማት ያገኙበት አጋጣሚ አልነበረም፡፡ በኢህአዴግም እንዲሁ፡፡ በቅርቡ ግን በረጅም ሙያዊ አገልግሎታቸው የበጎ ሰው ሽልማትን ተቀብለዋል፡፡ «ይህ ሽልማት በሕዝብ ምርጫ ውጤት በመሆኑ ተደሳች ነኝ፡፡ ሥራዬንና ማንነቴን አክበረው ለዚህ ሽልማት ላበቁኝ ሁሉ አመሰግናለሁ» ነው ያሉት - አቶ ያዕቆብ፡፡
ስለ አቶ ያዕቆብ አንዳንድ እውነታዎች
አቶ ያዕቆብ የጋዜጠኝነት ሙያን ቀጥታ ባይማሩትም በተለያዩ አገሮች ሄደው በሥልጠና፣ በሴሚናርና በጉብኝት ያገኙት እውቀት ቀላል አይደለም፡፡ አሜሪካን፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሀንጋሪ፣ ሶቪየት ህብረት፣ ቤልጂየም፣ ላቲቪያ፣ ስቶኒያ፣ ናይጄሪያ፣ ጋና እና ሌሎችም አገራት ለዚሁ ተግባር የተጓዙባቸው አገሮች ናቸው፡፡ ደርሰው ሲመጡ ስለየአገራቱ አንዳንድ ሁነቶች ጽፈዋል፡፡ ኢትዮጵያን ለቀው ኑሮን ውጭ አገር ማድረግ ተመኝተውም፣ ሞክረውትም አያውቁም፡፡ አገራቸውን በእጅጉ ይወዳሉ፡፡ «አየሯ እና ሕዝቧ ያየኋቸውን አገራት ሁሉ የሚያስንቁ ናቸው» ይላሉ፡፡
እርሳቸው ለብዙዎች ምሳሌ እንደሆኑ ሁሉ፤ ዛሬ ላሉበት ማንነታቸው ደግሞ የእንግሊዝ ጋዜጦች አርአያ ሆነዋቸዋል፡፡ የሼክስፒር፣ የዲከንስን፣ የበርናንድ ሾ፣ የቾቬስ እና የሌሎችም ጥንታዊ ጸሐፍት ሥራዎች ይመስጧቸዋል፡፡
ከአሥር ዓመት በፊት ግለ ታሪካቸውን ጽፈው ለንባብ አብቅተዋል፡፡ መጠጥ ካቆሙ 42 ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ የድሮ ለስላሳ የእንግሊዝኛ ዘፈኖችን ማዳመጥን ይመርጣሉ፡፡ ዛሬም የእነ ሞዛርት፣ የእነ ቤትሆቨንን የመሳሰሉ ክላሲካል ሙዚቃዎችን የማድመጥ ልምድ አላቸው፡፡ ለጤንነታቸው በግቢያቸው በመጠኑ የሰውነት እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፡፡ ማህበራዊ ተሳትፎ ውስጥ ግን የሉበትም፡፡
ዛሬ ሰማኒያ ስደስት ዓመት ሆኗቸውም አንድም ቀን ከማንበብና ከመጻፍ ተቆጥበው አያውቁም፡፡ ዛሬም ልጃቸው ባዘጋጀችላቸው ዘመናዊው የማንበቢያ መሣሪያዎች ኢቡክ እና አይ ፓድ መጽሐፍትና መጽሔቶችን እያነበቡ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ «ዘ ኢኮኖሚስት» መጽሔትን ሳያነቡ እንደማያልፉም ይገልጻሉ፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት አንድ ዓይናቸው በግላኮማ ምክንታት ሙሉ ለሙሉ ማየት ባይችልም ቀሪ ዓይናቸውን ለንባብ እየተጠቀሙበት ነው፡፡
በቤተሰባዊ ሕይወታቸው ተደሳች ናቸው፡፡ ትዳር የያዙት በአመሃ ደስታ ትምህርት ቤት መምህር ሳሉ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ በአባቷ የመናዊ የሆነች አንድ ቆንጆ አገቡ፡፡ ወጣትነታቸው በውቤ በረሃ ለዳንስና ለሙዚቃ የተመቸ ነበርና በዚያ አጋጣሚ ነው የተዋወቁት፡፡ ከእርሷ አምስት ልጆችን ወልደው አለመስማማት በመፈጠሩ ምክንያት ተለያይተዋል፡፡ ቀጥሎም አሁን በሕይወት ያሉት ባለቤታቸውን አግብተው ለ50 ዓመታት በትዳር ውስጥ ቆይተዋል፡፡ ከእርሳቸውም አምስት ልጆችን የወለዱ ሲሆን፤ በርካታ የልጅ ልጆችንም አፍርተዋል፡፡ አቶ ያዕቆብ ዛሬ
ዛሬ ከተወሰኑ የቤተሰቡ አባላት ጋር በሰፊው የመንግሥት ኪራይ ቤታቸው አብረው ይኖራሉ፡፡
በኃይለሥላሴ መንግሥት እንደሌሎች ኃላፊነት ቦታ የነበሩ ጋዜጠኞች የተሰጣቸው ቮልስዋገን መኪና ዛሬም ከእርሳቸው ጋር አለች፡፡ 49 ዓመት ሆኗታል። ደርግ ሥልጣን ሲይዝ ግምቱን እንዲከፍሉ ትዕዛዝ በሰጠው መሠረት 2ሺ200ብር ከፍለው ያስቀሯት ይህቺኑ መኪና እየነዱ ለሥራና ለአንዳንድ ጉዳዮች ይንቀሳቀሱባታል፡፡
አቶ ያዕቆብ ዛሬም ሥራ ላይ ናቸው፡፡ በ1980 አጋማሽ ከማስታወቂያ ሚኒስትር ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዛውረው በጽሕፈት ሥራ በማገልገል ላይ ሳሉ ጡረታ ቢወጡም ከዚያ ወዲህ ባሉት ዓመታትም አንድም ጊዜ አላረፉም፡፡ ዛሬም ይሮጣሉ፤ ዛሬም ይሰራሉ! በሪፖርተር የእንግሊዝኛው ጋዜጣ ላይ የአርታኢነት ሥራን በፍሪላንሰነት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በጡረታ የሚያገኙትን «ከወቅቱ የኑሮ ሁኔታ ጋር ያልተገናዘበ ኢ-ፍትሐዊ» ቢሉትም በእርሱ ኑሮን እየገፉ ነው፡፡
በመጨረሻም «ከእንግዲህ ምናልባት በሪፖርተር ጋዜጣ ከሁለት ዓመት በላይ አልሰራም። ከዚያ በኋላ አንድ ገጠር ሄጄ ነፃነት ያለው ቀለል ያለ ኑሮ መኖር ነው ፍላጎቴ። የቀረው አንድ ዓይኔ እያየልኝ ቢቆይ፣ ጤንነቴ እንደተጠበቀ ቢዘልቅልኝ እመኛለሁ…» አሉኝ። ምኞታቸው ምኞቴ ሆኖ ተሰነባበትን።
******************************************************************
ፀሐፊ ደረጀ ትዕዛዙ

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

የገጣሚ ነብይ መኮንን እማይነትበዉ ስዉር-ስፌት

ሞክሼ የአማርኛ ፊደላት እና የባለሙያዎች ማብራሪያ

ንባብ ለሕይወት!