ሞክሼ የአማርኛ ፊደላት እና የባለሙያዎች ማብራሪያ
ክፍል አንድ የፊደል ዘር ይጠበቅ ባህሉም ይከበር በፊታውራሪ አበበ ሥዩም ደስታ በፊደሎቻችን ላይ ሦስት ሀ - ሐ - ኀ፣ ሁለት አ - ዐ -፣ ሁለት ሠ - ሰ ሁለት፣ ጸ - ፀ አሉ፡፡ እነዚህ ፊደሎች የራሳቸው የሆነ የስም አጠራርም አላቸው፤ ሀሌታው ሀ፣ ሐመሩ ሐ፣ ብዙኃን ኀ፣ ንጉሡ ሠ፣ እሳቱ ሰ፣ ጸሎት ጸ፣ ፀሐዩ ፀ ይባላሉ፡፡ በጽሑፍ የሚገቡበትን ተገቢ (ተስማሚ) ቦታም አላቸው፡፡ ለምሳሌ በሁለት ፊደሎች መጠቀም ይቻላል፡፡ ሀገር አገር ይህ ትክክለኛ አጻጻፍ ሲሆን፤ ነገር ግን ከዚህ ውጪ ሐገር፣ ኀገር ብሎ መጻፍ ግን ስሕተት ይሆናል፤ የሚከተሉትን ደግሞ እንመልከት፤ ሕገ መንግሥት፣ ሕገ ወጥ፣ ሕዝብ፣ ሕብረት፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ወዘተ. የመሳሰሉት አጻጻፋቸው ትክክል ነው፡፡ ከዚህ ልማዳዊ አሠራር ውጪ ህገ መንግሥት፤ ህገወጥ፤ ህዝብ፤ ህብረት፤ አቃቤ ህግ ስሕተታዊ አጻጻፍ ይሆናል፤ ሌላ ማስረጃ ቢፈለግ፤ ኃይለሥላሴ የሚለው ስም ሦስት የተለያዩ ፊደሎች ይዟል፡፡ የመጀመርያው ፊደል ብዙኀን - ኃ - ሲሆን፣ ከንጉሡ -ሥ- ሳድስ፣ ከእሳቱ -ስ- ሃምስን በመጻፍ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ ሀይለ ስላሴ ብሎ ቢጻፍ ግን የፊደሎቻችን የአጻጻፍ ሥርዓት ማፋለስ ይሆናል፤ በአቦ ሰጡኝ ፊደሎቻችን አለቦታቸው መግባትም፣ መጻፍም የለባቸውም፡፡ በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በማስታወቂያ ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር የነበሩት የተከበሩ ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ የቅድሚያ ዓይነተኛ ሥራቸው የፊደሎች ዘሮች አለቦታቸው እንዳይጻፉ መጠበቅ ነበር፤ በዚያን ወቅት ተማሪ ሁኜ አልፎ አልፎ በጋዜጣ እንዲወጣልኝ አንድ አንድ ሐሳብ በማመንጨት እጽፍ ስለነበር ብዙ ጊዜ አርመውኛል፡፡ ከእሳቸው በተማርኩት ትምህርትና ባገኘሁት ልምድ አእምሮዬን አሻሽያለሁ፡፡ በቀ...