አማርኛችን ወዴት እየሔደ ነው?
ቋንቋ መግባቢያ ነው፡፡ ከመግባቢያነቱ ባለፈ ቋንቋ የራሱ የሆነ የአነጋገርና የአጻጻፍ ሥርዓት አለው፡፡ አንድ ቋንቋ በራሱ ለተናጋሪው ምሉዕ (የተሟላ) እንዲሆን ዘመኑን የሚዋጁ (ዘመኑ የሚወልዳቸው) ቃላት ሊኖሩት ይገባል፡፡ እኔ ምንም እንኳ የቋንቋ ተመራማሪ ባልሆንም አንድ ቋንቋ ምን ማሟላት እንዳለበት ግን እረዳለሁ፡፡ የሰው ልጅ በበርካታ ነገሮች ሊግባባ ይችላል፡፡ የሚግባባበት ሁሉ ግን ቋንቋ አይደለም፡፡ ወፎችም፣ እንስሳትም ሁሉም ይግባባሉ (የራሳቸው የሆነ መግባቢያ አላቸው) ነገር ግን ቋንቋ የላቸውም፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ሥልጣኔ ውስጥ አብራ የሰለጠነች በዘመናት መካከልም አብራ የዘመነች እንደሆነች በርካታ ማስረጃዎችን ማንሣት እንችላለን፡፡ አክሱም ሐውልትን የመሰለ ልዩ ምህንድስና ያለበት፣ ላሊበላን የመሰለ ልዩ ጥበብ የፈለቀበት፣ ልዩ የሆነውን 13 ወራት የሚይዘው የቀን አቆጣጠር ሃብታችን፣ የራሳችን የሆነው የፊደል ገበታችን ስልጣኔያችን ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር በቂ ማሳያዎቻችን ናቸው፡፡ በርካታ አገራት ፊደላትን ከሌሎች እየተዋሱ ሲጠቀሙ በነበረበት ዘመን ኢትዮጵያ ይህንን የመሰለውን የራሷ የሆነውን ብርቅየ ቋንቋ ከነፊደሉ ማዘጋጀቷ ትልቅ እና የጥበብ መፍለቂያ አገር እንደነበረች ያስረዳናል፡፡ የግዕዝ ፊደላት አማርኛ ቋንቋ ውስጥ የምንጠቀምባቸው ብቸኛ ፊደላት ናቸው፡፡ ቃላት እንደዘመናት መፈራረቅ ሁሉ ይወለዳሉ፣ ያድጋሉ፣ ይሞታሉ፡፡ ይህ ተፈጥሮአዊ የቃላት ዑደት በማንኛውም ቋንቋ ዘንድ እንደሚኖር አልጠራጠርም፤ በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ ግን አለ፡፡ አሁን አሁን ግን እየተወለዱ ያሉት ቃላት አማርኛ አማርኛ የማይሸቱ እየሆኑ በመምጣታቸው ለአማርኛ ቋንቋችን ከፍተኛ ተጽእኖን እያሳደሩ ናቸው፡፡ በቋንቋችን አፍ...